የዛሬ 15 ዓመት ገደማ የካቲት 19 ቀን 2001 ዓ·ም በጋዜጠኛ ማስረሻ ማሞ የተዘጋጀ ስለ ኤልያስ መልካ የሙዚቃ ሕይወት የሚያትት ጽሑፍ አዲስ ነገር ጋዜጣ ይዛ መውጣቷ የሚታወስ ሲሆን … የህልፈቱን 4ተኛ ዓመት ለማሰብ ያህል በሁለት ክፍል እንካችሁ! አንብቡት።
ጋዜጠኛ ማስረሻ ማሞ ከገነት ቤተ―ክርስቲያን እስከ በገና ስቱዲዮ ያደረገውን የኤልያስ መልካን የሙዚቃ ዱካ እንደሚከተለው ከትቦልናል፡፡

፤፨፠፨፤ ― ክፍል አንድ ― ፤፨፠፨፤
የዛሬ ሦስት ዓመት ግድም (1998 ዓ·ም አካባቢ መሆኑ ነው።) ወደ ሃና ማርያም አካባቢ ለነበረው ቀጠሮ አክብሮ ለመገኘት የቅርብ ወዳጁ የኾነውን ዘካርያስ ጌታሁንን ከኋላ እና ከፊት ለፊት እዩኤል ሆሳዕና የሚባለውን ጓደኛውን አስቀምጦ ከቀኑአምስት ስዓት ሲኾን በቀለበት መንገድ ላይ በከፍተኛ ፍጥነት ይጋልብበታል፡፡ ኤልያስ ራሱን ጥንቃቄ እንደሚጎድለው ሾፌር ዐይቶትም አስቦትም አያውቅም። በዚያ ፍጥነት በሚበርበት አጋጣሚ ከፊት ለፊቱ የነበረው የዕቃ መጫኛ የሚጎትት አሽከርካሪ እርሱ የሚጓዝበትን አቅጣጫ ዘጋበት፣ ኤልያስ ከአደጋ ማምለጥ የሚችልበት ስዓት ወደ መጨረሻው ሰከንዶች ተቃርቧል፡፡
ሌላኛውን አቅጣጫ መምረጥ የመገልበጥን አደጋ ያመጣል፡፡ እኔም ኾንኹ ኤልያስ እንደምንጋጭ አውቀነዋል። እኔ ከኋላ ወንበር ላይ ኾኜ በጭንቀት የምይዘውም ኾነ የምጨብጠው አልነበረኝም:: ፊት ለፊት መኪናው ከዕቃ መጫኛው ጋራ ሊጋጭ ኮፈኑ መስተዋቱ ጋራ ደረሰ፡፡ ወንበሩ መትቶኝ የግራ እጄ መሰበሩን ያወቅኹት ከቆይታ በኋላ ነበር እንደ አጋጣሚ ኾኖ ኤልያስም ኾነ እዩኤል ምንም ዐይነት አደጋ አላገኛቸውም።» ይላል ዘካርያስ፣ ኤልያስ ከሞት ጋራ ፊት ለፊት መነጋገር ማለት ምን ማለት እንደኾነ የገባው በዚያች ቅጽበት በፈጠረቻት የሰከንድ ስሕተት አማካኝነት ነበር። ሹፌርነት ለኤልያስ ውኃ ከመጠጣትም የሚቀል ይመስለው ነበር። በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ መኪና መንዳት ግን ውኃ እነደመጠጣት የሚቀል አልነበረም። በሰከንድ ውስጥ ሕይወትን ለመቀማት የሚያስችል ጉልበት ያለው እንጂ ለኤልያስ ይህ አጋጣሚ ሕይወትን ቆም ብሎ እንዲያስባት የሚያስገድድ ነበር፡፡ ያኔ ኤልያስ «አትቸኩል ረጋ ብለህ» የሚለውን ዘፈን ሊያደምጠውም ኾነ ሊያቀናብረው በሚችል መንገድ ገና አልታሰበም፡፡
ችኩልነትን ይተው ዘንድ ራሱንም ሌሎችንም የሚመክርበትን የመንገድ ትራንስፖርት ዘፈን ዝማሬ ከማቀናበሩ በፊት ኤልያስ ረጅም ጉዞ እና ጎዳና ተጉዞ ቦሌ መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ካለው ስቱዲዮው ውስጥ ከተመ፣ ከካልዲስ ካፌ ፊት ለፊት በሬድዋን ሕንጻ ውስጥ ዘወትር ምሽት መብራቷ የማይጠፋው የኤልያስ ስቱዲዮ ናት፡፡
የክፍል ቁጥሯ 102 የኾነችው ይቺው ስቱዲዮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁት የሙዚቃ ሪከርዲንግ ስቱዲዮዎች አንፃር ስትታይ የስቴዲዮን ስፋት ያሟላች አይደለችም:: ጠባቧ ባለ ሁለት ክፍል ስቱዲዮ ከአምስት ሰው በላይ ሲገባባት በጭንቅ ትወጠራለች። ይኹን እንጂ እረፍት የለሽነቷ እንደ የጥበቷን ያህልም አይደለም። ምናልባትም ሌት እና ቀን መምሽት እና መንጋታቸው ሳይታወቅ አንዱ በሌላኛው ላይ እርስ በርሳቸው ይተካኩባታል፡፡ በዚች ጠባብ ስቱዲዮ ውስጥ የኢትዮጵያን ሙዚቃዎች የሚቀምረው ኤልያስ መልካ ከመሸገ ከርሟል፡፡ ስቱዲዮዋ ምንም እንኳ የምሽግነት ሚና ቢኖራትም ያለ ስያሜ የተፈጠረች አይደለችም፡፡ ጥንታዊውን እና የኢትዮጵያ የሙዚቃ መሣሪያ የኾነውን የበገናን ስም ወርሳለች፡፡
፤፨፠፨፤ ― በሙዚቃ ፍቅር ውስጥ የተገኘ ማንነት ― ፤፨፠፨፤
ኤልያስ መልካ የመሸገባት በገና ስቱዲዮ እንዲህ መፈናፈኛ ያጣች እስክትመስል ድረስ የጠበበቸው ለብቸኛው አቀናባሪ የምትበቃ በመኾኗ ብቻ አይመስልም፡፡ ሌላም የሚፈታ ምስጢር የምትገልጥ ትመስላለች፡፡ ከኤልያስ የሙዚቃ ሥራ እና የሕይወት ፍልስፍና ጋራ የሚጣጣም ዐይነት ትሥሥርን ሳታመላክትም አትቀርም። ኤልያስ በሙዚቃ ሥራ እና በጊታር ፍቅር ውስጥ ራሱን ካገኘበት ሰዓት አንስቶ ስለ ሙዚቃ አንድ ወጥ የኾነ መረዳት እና ግንዛቤ አልነበረውም፡፡ ራሱን በተለያዩ ውጣ ውረዶች ውስጥ አግኝቶታል፡፡ ያመነበትን ሲያደርግ፤ ያንን አመንኹበት ያለውንም ደግሞ በሌላ ዐይነት አዲስ ሓሳብ እና የሙዚቃ ግኝት ሊተካ እና ሲያፈራረቅ ከርሟል፡፡ በሕይወቱ ውስጥ ይህ ዐይነቱ መዘበራረቅ ሲገለባበጥ ተመልክቷል፡፡ ኤልያስ ውጣ ውረዱን እና በሕይወቱ ውስጥ ያለፈውን ዝብርቅርቅ ዓለም እንደ ሰፊ የሕይወት ተራራ ምዕራፍ ማየት አልመረጠም፡፡ ከዚያ ውስጥ ጥበብ ልታሰኝ ከምትችለው ትሩፋት ይልቅ ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ የዘንበለ እና ወይ አንድ ክፍል ብቻ እየጠበበ የሚሄድን ትርጓሜ መምረጥ የሚያዋጣ እና «ሰላም የሚሰጥ ነው።» ሲል አውጇል።
ነገሮችን ከመጽሐፍ ቅዱስ አውድ እና ትርጓሜ አንጻር መመልከት እና «እግዚብሔርን መፍራት የጥበብ ኹሉ መጀመሪያ ነው» በሚለው ላይ መንተራስ ለኤልያስ የሕይወት እና የሙዚቃ ሥራ ቁልፍ ጉዳይ ተደርገው ተወስደዋል፡፡
ኤልያስ አሁን ካለበት ድምዳሜ ላይ ከመድረሱ በፊት ባለፉት ዐሥር ዓመታት ውስጥ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ዘፈኖችን እና የፕሮቴስታንት መዝሙሮችን አቀናብሯል፡፡ መዝሙሮቹንም ኾነ ዘፈኖቹን ያቀናበረበት መንገድ የራሱ የኾነ አንድ ዐይነት ፍስት አልነበረውም፡፡ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ዐይነት የቅንብር ስታይሎችን ተጠቅሟል፡፡ ይህን የመቀያየር ስልት አንዳንድ የሙዚቃ ባለሞያዎች በየጊዜው ዕድገት እያሳየ ከመኾኑ ጋራ ያያይዙታል፡፡ የ23 ዓመት ልጅ ያቀናበረውን የቴዲ አፍሮን ሙዚቃ ስለማ እና በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ስሜ ኣልተጠቀሰም ተጠቅሷል» በሚል ክርክር ኤልያስን ለመጀመሪያ ጊዜ ላወቀው የተፈጠረብኝ ስሜት የተለየ ነበር» ይላል የሙዚቃ ባለሞያው ሠርፀ ፍሬ ስብሐት፣ ሠርፀ ምን ምድር አፈራቸው ሲልም ኤልያስን እስቦታል፡፡

Subscribe Our YouTube Channel
፤፨፠፨፤ ― የኤልያስ ጎሕ ሲቀድ ― ፤፨፠፨፤
ይህን የሙዚቃ ሰው ያፈራችው መንደር አዲስ አበባ ውስጥ ካሉት መንደሮች ኹሉ እጅግ ዝቅተኛ በሚባለው ረባዳ ስፍራ ውስጥ ትግኛለች፡፡ አዲስ አበባ ዳሎል የሚባል ስፍራ ሊሰየምላት ካስፈለገም ይቺን መንደር ሊቀድም - የሚችል አይኖርም። ከአብነት ወደ ሰባተኛ በሚወስደው መንገደ ላይ ከብሌን ሆቴል ፊት ለፊት ያለችው ይቺው መንደር እንደ ልብ ተንሰራፍተው የሚገቡባት አይደለችም፡፡ ወደ መንደሯ የሚያስገባው ቀጭን የአስፋልት መንገድ ሰዎች እና መኪናዎች እርስ በርሳቸው ያለመተፋፈር የሚገፋፉበት ነው፡፡
እርስ በርሳቸው የተዛዘሉ ትናንሽ ቤቶች ዳር እና ዳሩን አካባቢው እንዳይፈናፈን አድርገው ወጥረው ይዘውታል፡፡ ኤልያስ በዚያ ረባዳ ስፍራ ከዋናው መንገድ 300 ሜትር ያህል ወደ ውስጥ ዘልቆ በሚገኝ በግንብ በታጠረ ግቢ ውስጥ ነው ያደገው፡፡ ቤተሰቦቹ ፊደል እንዲቆጥር ወደ ትምህርት ቤት የላኩት የአራት ዓመት ልጅ ሳለ ነበር፡፡ ፊደል ከሚቆጥርበት ቦታ ሲመለስ ግን እንደ ልጆች በጋራ የሚያሳትፍን ጨዋታ ከማዘውተር ይልቅ በራሱ የጨዋታ ምርጫ መመሰጥን ይወድ ነበር:: ከቆርቆሮ የተሠሩ ቅራቅንቦዎችን ሰብስቦ እርስ በርላቸው እያጋጨ የሚያወጡት ድምጽ ይደሰት ነበር ይላሉ ወላጅ አባቱ አቶ መልካ ገረሱ፡፡ ኤልያስ ግን ይህን እንደሚያደርግ ትዝታው የለውም፡፡
ለኤልያስ ሙዚቃ በሕሊናው ታትሞ የቀረው በቤታቸው ውስጥ ይደረግ በነበረው የኅብረ ዝማሬ አጋጣሚ ነበር፡፡ የኤልያስ ቤተሰቦች የገነት ቤተክርስቲያን አባላት እና የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ናቸው፡፡ ደርግ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ላይ ያደርግ በነበረው ተጽዕኖ ምክንያት የኤልያስ ቤተሰቦች እና መሰሎቻቸው በነፃነት የማምለክ ዕድል አልነበራቸውም፡፡ የራሳቸውንም ቤተክርስቲያን በአደባባይ ገንብቶ እንደፈለጉ የመኾን አጋጣሚ ጠባብ ነበር ያላቸው አማራጭ ሰፋ ያሉ ቤቶችን በድብቅ ለጸሎት' ለአምልኮ እና ለዝማሬ መጠቀም ነበር፡፡
ይህን ዐይነት አገልግሎት በመስጠት የእነ ኤልያስ ቤት በአካባቢው ቀዳሚ ስፍራ ያለው ነበር፡፡ ትንሹ ኤልያስ ከጸሎትም ከዝማሬም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምኅርትም በላይ ቀልቡ የሚወሰደው በጊታር ድምጽ ነው፡፡ ዘውትር ያለማቋረጥ የሚጫወተውን የገነት ቤተ ክርስቲያን ጊታር ተጫዋች የኾነውን ክፍሉ ወልዴን እንደ ጅል ፈዞ ያየዋል፡፡ ወዲያውም እርሱን በኾንሁ የሚለው ፍላጎት በልጅ ልቡ ውስጥ ይገላበጥበታል፡፡ ኤልያስ ግን በምኞት እና በፍላጎት ብቻ መታጠርን አልወደደውም፣ የፕሮግራም እረፍት እና የምሳ ሰዓት አጋጣሚን ተጠቅሞ የጊታሩን ክሮች በጣቱ እየነካካ ጣቶቹ በፈጠሩለት ድምጽ ይቦርቃል። ይህን ስሜቱን እና ፍላጎቱን የተረዱት አቶ መልካ ገረሱም ለኤልያስ ትናንሽ ጊታር መሰል ነገሮች እና ማሲንቆዎች ገዝተው ያመጡለታል፡፡ እህቶቹም የሙዚቃ መሣሪያ ስጦታ ያበረከቱለት ነበር ይላሉ አቶ መልካ
ጊታሪስቱ ክፍሎም የኤልያስን ፍላጎት ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ ጊታር እንዲነካካ - በመፍቀድ ጊታር ፍቅር እንዲያድርበት አደረገው:: ለምጠይቀው ጥያቄ ኹሉ ላይሰለቹ አጠር ያለ መልስ ይሰጠኝ ነበር ይላል ኤልያስ፡፡ በ19 83 ዓ·ም ኢሕአዴግ አገሪቱን ሊቆጣጠር ኤልያስ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነበር፡፡ ቤተሰቦቹ ለዕድገቱ እና ለችሎታው የሚመጥን የራሺያ ጊታር የገዙላትም ያኔ ነበር። ጊታሯን ግን ለራሱ ደስታ ብቻ ሊያደርጋት የሚችል አልነበረችም፡፡
በአካባቢው ያሉ የገነት ቤተ ክርስቲያን ኣባላት ፕሮግራሞች ላይ ዝማሬዎችን ማጀብ ዋነኛ ሥራው ኾነ፡፡ ኤልያስ ዝማሬዎቹን ከጀርባ ኾኖ ያጅብ እንጂ ዜማዎቹን መከተል እና ቀጥሎ የሚመጣው ዜማ ምን አንደኾነ የሚያውቅበት አንዳችም ችሎታ አልነበረውም፡፡ የመጀመሪያውን ዜማ ሳይጨርሱ ቀጥሎ ምን ሊመጣ ይችላል የሚለውን መገመትን የተማርኹት ያኔ ነው፤ አሁን በሥራዬ ላይም ጠቅሞኛል ይላል ኤልያስ።

፤፨፠፨፤ ― በነዳጅ ማደያ የተለኮሰ ተሰጥኦ ― ፤፨፠፨፤
ኤልያስ በአንድ አጋጣሚ ከአማኑኤል አጂፕ ጋዝ ገዝቶ እንዲመጣ ቤተሰቦቹ ይልኩታል፥ የጋዝ ጀሪካኑን አንጠልጥሉ ከጋዝ ማደያው ጋራ ሲደርስ ወረፋው ብዙ ነበር:: ተራው ደርሶ ከኢሉ ብር ሲያወጣ እንድ ነገር ትወድቅበታለች:: የጋዝ ቀላው የወደቀችውን ነገር ዐይቶ ምን እንደኾነች ጠበቅ ባለ መንገድ ይጠይቀዋል፡፡ ትንሹ ኤልያስ ለሰውየው ጥያቄ አጭር እና ፈጣን ምላሽ ሰጠ፣ ፒክ ዋ ሲል፣ በኤልያስ ፈጣን ምላሽ የተገረመው ይኼ ሰው ልጁን ከእነ ጋዝ ወደ ቤቱ መላክን አልመረጠም።
ጊታር መጫወት ይችል እንደኾነ ከጠየቀው በኋላ ሊፈትነው ወደ ቢሮው ውስጥ አስገባው። ኤልያስ ወደ ቢሮው ከመግባቱ በፊት አንድ ወሳኝ ድርድር ተደራድሯል። ካልቻለ ኩርኩም ሊቀምስ፣ ኤልያስን ወደ ቢሮ ይዞት የገባው ሰው አቶ መለስ ይባላል። ኤልያስ ከአቶ መለስ ቢሮ ያገኛት ጊታር አንፈ እርሱ የራሺያ ጊታር ከባድ አይደለም። ለአጨዋወትም ኾነ ለአያያዝ የቀለለች ነበረች ቅለቷ ኤልያስ የበለጠ እንዲዝናና አደረገችው:: አቶ መለስ እና ኤልያስ የልብ ወዳጆች ኾኑ።
አቶ መለስ ኤልያስ ጋዝ ከመግዛትም ባሻገር ጊታርዋን እንዲጫወትባት ፈቀደለት ስለ ጊታር አጨዋወትም እነማን የተሻለ እንደኾኑ ያስረዳው ጀመር። በጊዜው የሮሃ ባንድ ጊታሪስት የነበረውን የሰላም ስዩምን በሙዚቃ መሣሪያ የተቀነባበሩ ሥራዎች እንዲያደምጥ ካሴት አዋሰው፡፡ ኤልያስ ሰላም ስዩምን በኅብረ ትርኢት በሚተላለፍ ክሊፕ ላይ ከማየት ባለፈ ማን እንደኾነ እንኳ አያውቅም ነበር:: ኹሌም ኅብረ ትርኢት ላይ ሲጫወት ሳየው ግን በጣም እገረም ነበር። ይላል፡፡ የአቶ መለስ የሰላም ስዩም ወሬ ኤልያስን ስለ ስዩም ከማሳወቅም አልፎ የሥራው ተከታይ እንዲኾንም አደረገው፡፡ «እንደ ሰላም ለመጫወት የኅብረ ትርኢቱን ለማስመሰል (Imitate) ጥረት አደርግ ነበር። ይላል ኢልያስ።
ኤልያስ በአካባቢው የነበረውን የገነት ቤተ ክርስቲያን ኅብረት የሴቶች፣ የወጣቶች እና የቤተሰብ ፕሮግራም ሳያቋርጡ መጫወት አንዳንድ ጊዜ መሰልቸትን እና ድካምን ይፈጥርበት እንደነበር ያወሳል። በዚያው ወቅት ኤልያስ ለቤተ ክርስቲያን ዝማሬ ከኳየር ጋራ ተቀላቀለ፡፡ ኳየሩ የእናቱ እኩዮች የሚዘምሩበት ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን ከጊታርም ባለፈ ከሌሎች የሙዚቃ መሣሪያዎች ጋራ እንዲተዋወቅ ዕድል ፈጠረችለት:: ፒያኖ እና በዐይነታቸው ልዩ የኾኑ ጊታሮችን የማግኘት ዕድሉም ሰፊ ኾነለት፡፡ የኤልያስ ነፍስ የሙዚቃ ጥማቷን ለማርካት ከተማዋ ውስጥ አሉ የሚላቸውን የሙዚቃ ትምህርት ቤቶች እንዲያስስ አድርጎት ነበር፡፡