እማሆይ የጨርቆሷ ዶክተር

User avatar
Ethiopian News
Leader
Leader
Posts: 967
Joined: 19 Aug 2009 17:01
Contact:

እማሆይ የጨርቆሷ ዶክተር

Unread post by Ethiopian News »

ከበልጅግ አሊ

ትንሽ ጠጠር የሃሞት ከረጢቴን መተላለፊያ ዘግታ በሆድ ቁርጠት ብሰቃይ ለግልግል ሆስፒታል ተኝቼ ነበር
።ሐኪም ቤት አልወድም ። አልጋው አይመቸኝም ፣ ምግቡንም እጠላለሁ . . . ።ከምርመራው በኋላ አነስተኛ የሆነ ቀዶ
ጥገና እንደማደርግ ነግረውኝ አልጋ አስያዙኝ ። መድሃኒት ሰጥተውኝ ቁርጠቱ ጋብ ሲልልኝና እፎይታ ሳገኝ አጠገቤ
የነበረውን ወረቀት አንስቼ የሰሞኑን ስቃይ ትዝታ ሳይጠፋ በፅሁፍ ላስፍረው ብዬ ጀመርኩ። በስድ ንባብ ሞከርኩት ።
ታመምኩ ብሎ መፃፍ ብዙም አዲስ ነገር ላይኖረው ይችላል። ብዙ ሰው ይታመማል ። ያለሕክምና ይሰቃያል ። በተለይ
እኛ ሃገርማ ምኑ ቅጡ ። ያውም ለበሽታ ! ስንቱ ዓይነት ሞልቶ ተትረፍርፎአል። ሐኪምና መድሃኒት በበዛበት
የአውሮፓ ከተማ ውስጥ ግና በሀሞት ከረጢት ሕመም ተሰቃየሁ ብዬ ብጽፍ ማንም አይደነቅ ። በጥቂት ደቂቃዎች ቀዶ
ጥገና መገላገል ይቻላል ። ህመሙስ ቢሆን ካንድ ኪኒን የሚያልፍ መች ሆነና ?/ በጣሙን እያመመው ያለህክምና
የሚንገላታ አንድ ሰው አግኝቶ ቢያነበው “የደላው ሙቅ ያኝካል” ብሎ መሳቂያ ነው የሚያደርገኝ ብዬ ተውኩት ።ግን
ለሁለት ቀን ያህል ቁርጠቱ፣ በበላሁት ምግብ ምክንያት ሊሆን ስለሚችል፣ ከአሁን አሁን ይሻለኛል በማለት ያሳለፍኩትን
ችግር ደግሞ ልረሳው አልፈለግሁም።ትንሽ ግጥም ቢጤ ልሞክርበት ብዬ ጀመርኩ :፡ ጻፍኩ፣ አልተስማማኝም፣
ቀደድኩ፣ ተውኩት ፣እንደገና ቀጠልኩ ፣ በመጨረሻ ለራሴ የሚያረካኝን ያህል በግጥም ፃፍኩና „ተንኮለኛይቱድንጋይ“
የሚል ርዕስ ሰጠሁት።
ተንኮለኚት ድንጋይ ፣ከሆዴ ውስጥ ገብታ፣
ምንም ሳልጠረጥር ፣ ድንገት አዘናግታ፣
የሃሞት ከረጢቴን ፣ቱቦውንም ዘግታ፣
ልትገለኝ ነበረ ፣ በጣም አንገላታ።
ከስንቱ መርዛ መርዝ፣ አሸዋ ከባሰ ፣
መከራ ካበዛ ፣ ሰው ካላላወሰ፣
እሆድ ውስጥ ገብቶ፣ ካላንቀሳቀሰ፣
ድንጋይ አሸንፎ ፣ ሰው ላይ ከነገሰ፣
የሰው ሰውነቱ ፣ አበቃ ጨረሰ።
ለምትወዱት ሁሉ ፣አፈር ልብላ አትበሉ፣
ወደ ሆድ ከገባ ፣ ወርዶ በቀላሉ፣
አፈር አንፈራፍሮ፣ ተቀይሮ አመሉ፤
ድራሹን ያጠፋል ፣ውስጥ አንጀትን ሁሉ፣
ሁለተኛ ባፈር ፣ በስሙ እንዳትምሉ፣
ከሞት መች ያንስና፣ ካምሳያ መሰሉ።
ወረቀቱን ወደቦታው መልሼ ዘና ብዬ አልጋው ላይ ጋደም አልኩ ። አጠገቤ አንድ ሥጋው ከሰውነቱ አልቆ አጥንቱ የሚቆጠር ሽማግሌ ፈረንጅ ተኝቶ ነበር ። በበሽታው ምከንያት ይሆን እንዲህ የከሳው? ብዬ ራሴን ጠየቅኩ ።ለነገሩ የዚህ ሃገር ሰው ለምን እንደከሳ በግምት መናገር አይቻልም ። የተስተካከለ ቅርፅ እንዲኖራቸው ሲሉ ምግብ ስለማይበሉ ሥጋቸው ከላያቸው ላይ ያለቀ ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም ።በተለይ ሴቶቹ ከወፈሩ ባል ወይም የወንድ ጓደኛ አናገኝም ብለው ሰለሚሰጉ ከምግብ ጋር ላለመገናኘት ጥረቱ ብዙ ነው ። የሥጋ ዘር አንበላም ብለው፣ ጣዕረ ሞት መስለው የሚሄዱ፣ ግን ጤነኛ የሆኑ ብዙ ናቸው።ክሳትን ብቻ በመመልከት በሽተኛውንና ጤነኛውን መለየት አስቸጋሪ ነው።
ከክሳቱ ተጨማሪ ሽማግሌው ዝምተኛ ነው ።ተኝቶ ነው የሚውለው።እዚህ ክፍል ከገባሁ አላነጋገረኝም ። በሽታው
አድክሞት ይሁን ወይም እኔን ላለማነጋገር ፈልጎ እንደሆን አልገባኝም ። ለነገሩ የዚህ ሃገር ሰው ለምን ዝም እንደሚል አይታወቅም ።ምንአልባት ጥቁር አይወድ ይሆናል ብዬ አሰብኩ ። ለጥቁር ጥላቻ ያላቸው የዚህ ሃገር ዜጎች ትንሽ አይደሉም ። ዘረኝነታቸዉን በሚመለከት ብዙ ገጠመኝ ስላለኝ ቀድመው ራሳቸው ካላነጋገሩኝ እኔ ቀድሜ ንግግር መጀመር አልፈልግም ። እንደ ቅጥነታቸው ሁሉ ዝምታቸውም ድርብ ስለሆነ መለየት አይቻልም ።
ይህ ሰው ታሞ ይሁን ዝም ያለኝ፣ ወይስ... ዘረኛኝነት??... ወይስ ዝምተኛነት??...ሁኔታው እስከሚለይ ዝምታን መረጥኩ ። u4656 .ላም ብሎ ንግግር እስኪጀምር ጠበቅሁት ።ከጥቂት ቆይታ በኋላ ገልበጥ ብሎ ፊቱን ወደ እኔ አዞረ ። ፈገግ ብሎም ሰላምታ ተለዋወጥን ፡ -
- “ምን ሆነህ ነው?” አለኝ ።
- “ሆድ ቁርጠት ነው” አልኩት ።
- “አንተስ?”
- መልስ አልሰጠኝም ።የእጁን ጥፍር አሳየኝ ።ጥፍሮቹን ስመለከታቸው ቢጫ ናቸው ።ቶሎ ብዬ ዐይኖቹን
ተመለከትኩ። እነርሱም ቢጫ ሆኑዋል ።... “ያቺ መናጢ ነች ! “ አልኩኝ በሆዴ ።
- “መድሃኒት እየሰጡህ ነው ?” ብዬ ጠየቅሁት ።
- “አስራ አምስት ቀኔ ነው ። ደሜን ይቀዱታል ። ይመረምሩኛል።እስካሁን ግን ምንም ውጤት የለም” አለኝ ።
- “ አንዴ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስማር እኔንም ይህ በሽታ ይዞኝ ነበር” ብዬ ነገርኩት ።
- “እንዴት ለቀቀህ ታዲያ “ አለኝ መልሱን ለመስማት በመቸኮል ።
- “እኛ ሃገር የወፍ በሽታ ትባላለች ። አንድ አሮጊት ናቸው ያዳኑኝ “አልኩት።
- “እንዴት...??? ምን የሚባል መድሃኒት ሰጥተው አዳኑህ ?”
ሰለመድሃኒቱ ምንነት እንደማላውቅና በሃገር ውስጥ ብቻ የምንጠቀመበት የሃገር መድሃኒት መሆኑን ነገርኩት።ትንሽም
ታሪኩን ተረክሁለት ፡፡ በዚህ በሰለጠነ ሃገር እንዲህ የተጨነቁበት በሽታ እንዴት በአፍሪካ መድሃኒት ተገኘለት ብሎ ነው መሰለኝ የመጠራጠር ፈገግታ አሳየኝ። ከዚያም ከተኛበት ቀና በማለት ተስተካክሎ ተቀመጠና መልስ ያላገኘሁላቸዉን ጥያቄዎቹን አዥጎደጎዳቸው።
ይህንን ያህል ፍቱን የሆነ መድሃኒት ካላቸዉ ታዲያ ሴትዬዋ ለምን ለትልልቅ ኩባንያዎች አልሸጡትም ???
እማሆይ የጨርቆሷ ዶክተር
መድሃኒቱስ እንዴት በዓለም አልታወቀም?.?.... መድሃኒቱ የት ነው የሚገኘው ?...ሴትየዋ አሁን በሕይወት አሉ ወይ?... መድሀኒቱን ልታስመጣልኝ ትችላለህ ወይ? ... አሁን እኔ ወደእዚያ ሃገር ብሄድ ሴትዬዋን አገኛቸዋለሁ ወይ?... በድህነት ተቆራምደዉ መቃብር ቤት ውስጥ ነው የሚኖሩት ነው የምትለኝ?..... በተለያየ የሥልጣኔና የባሕል ደረጃ ዉስጥ የኖርን በመሆናችንና ሁሉም ዓለም እንደ አውሮፓ ስለሚመስለው ልንግባባ ባንችልም የአቅሜን ያህል መመለሴን ቀጠልኩ። በመልሶቼ
እንዳልተደሰተ ከፊቱ ላነብ ቻልኩ ። ታላቅ የሆነ ፈዋሽ መድሃኒት እያወቁ በድህነት ተቆራምዶ መሞት ይቻላል ብሎ ማመን አቃተው ።ከንግግሬ መድሃኒቱን የማግኘቱ ተስፋ የመነመነ መሆኑን ከተረዳ በሁዋላ ፣ እንደውሽት ቆጥሮት ይሆን ወይም በሽታው አድክሞት በማያስታዉቅ ሁኔታ ምንም ሳይናገር ተመልሶ ተጋደመና ወደ ዝምታው አመራ ።እኔም በዝምታ ትዝታ ውስጥ ገብቼ ለጥቂት ጊዜ ሳወጣና ሳወርድ ቆየሁ : ፡ ከዚያም የጀመርኩለትን ታሪክ ሳልጨርሰዉ በሚል የግል እልህ ሳቢያ ወደጎን የገፋሁትን ማስታወሻዬን አንስቼ ከብዕሬ ጋር አገናኘሁት።
ዘመኑ ቀይ ሽብር ማለቂያው ላይ ነው ። በወቅቱ ወጣት ከነበርነዉ ብዙዎቻችን ታስረን ተፈተናል ። ዐዕምሮአችን
ባለፈው የመከራ ዘመንና በወደፊቱ ተስፋ ቢስ ኑሮ ምስሎችና ሃሳቦች ታጭቋል ። የደርግ መንግሥት ሃገሪቱን
በኢኮኖሚ አድቋቷል። ከእስር ቤት መፈታታችን ባልከፋ ነበር ። ነገር ግን በችግር በተቆራመዱት ቤተሰቦቻችን ላይ፣ በችግር ላይ ችግር ሆነን፣ በላያቸው ላይ መውደቃችን የበለጠ ጭንቀት ውስጥ ከቶናል ። “ከሞቱት በላይ ከቆሙት በታች” የሚሉትን ዓይነት ኑሮ መግፋት ጀምረናል ። የሕዝቡን ችግር እየተረዱ መፍትሔ ማምጣት አለመቻልን የመሰለ አሰቃቂ ነገር ከቶ የለም ።መፍትሔዉም ሆነ ለመፍትሔዉ የነበረን ተስፋ በጉልበተኛ ገዥዎች ጫማ ሥር ተረጋግጦአል።
አዲስ አበባ በረሃብ ተወጥራለች። ምግብ ገንዘብ ለሌለው ቀርቶ ላለውም ጠፍቷል ። በየሆቴል ቤቱ ሳይቀር ይበላ
የነበረው የበቆሎ እንጀራ ነው ። ድሮ በወፍጮ ቤቶች ውስጥ ተከምሮ ይታይ የነበረው የእህል ዓይነት የሕልም እንጀራ ሆኑዋል ።ጤፍ ፣ ስንዴ ፣ ሩዝና ሌሎች የእህል ዓይነቶች በቀበሌ የሕብረት ሱቆች እንደ ስኳር በኩፖን ይታደሉ ጀምረዋል ። የአዲስ አበባ ነዋሪ ካለበት ድህነት በተጨማሪ ባለው ገንዘብ እንኳ ገዝቶ እንዳይበላ ከፍተኛ በሆነ የመንግሥት ቁጥጥር የተነሳ እህል የሚሸጥበት ሌላ ቦታ የለም ።ከገበሬው ላይ ነጋዴው ሳይሆን መንግሥት ራሱ ነበር ገዝቶ የሚያከፋፍለው ። እናትና አባት ልጆቻቸውን መመገብ አቅቷቸው ዓይናቸው እንባ አቅሮ፣ ቅስማቸው ተሰብሮ የመከራን ሕይወት ይገፉ ነበር ።ከወታደርነት ሌላ ሥራ ስለሌለ አብዛኛው ወጣት ሱቅ በረንዳ ቆሞ ሲያዛጋ ይውል ነበር። ሥራም ተፈልጎ ቢገኝ የድጋፍ ወረቀት ሰለማይሰጥ መቀጠር አይቻልም ።”ያጠቆራችሁትን የአብዮት ሸማ እስካላፀዳችሁት የድጋፍ ወረቀት የለም” ተብለን ፣ እንዳንሰራ ተከልክለን ፣ ምግብ እንዳናቆም ሰው ሆነን የምንኖርበት ወቅት ላይ ነበርን ።
በወቅቱ እንደ አብዛኛዉ የሕብረተሰብ ክፍል የእኔም ቤተሰብ በኢኮኖሚው እጅጉኑ የተጎዳ ነበር ። የአባቴ የጡረታ
ደሞዝ ለዘጠኝ ልጆች አትበቃም። ያ ወቅት ኑሮ ከብዶኝ በጣም የተጨነቅኩበት ፣ ቤተሰብ ላይ ሸክም መሆን በየቀኑ ጭንቅላቴን በሃሳብ የበጠበጠበት ፣ ወጣቶች ኢትዮጵያ ለወደፊቱ የተሻለች ሀገር ትሆናለች በሚል የነበረንን የረዥም ጊዜ እምነት ከጥያቄ ዉስጥ ያስገባንበት ፣በየትላልቆቹ ከተማዎች ውስጥ ለዐዉደ ዓመት እንደተገዛ በግ ጥዋት ማታ የምንታሰርበት ፣ አዲስ አበባ ጣፋጭ ትዝታዋ ቀርቶ አሰቃቂ ገጽታዋ ብቻ የሚታወስበት ፣ ከቀበሌ የሕብረት ሱቅ ደጃፍ መገተር ልምድ ሆኖ የተያዘበት ጊዜ ነበር ።
ከዚህ ሁሉ አበሳ ለመገላገል ፡ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና (ማትሪክ) በማለፍ ዩኒቨርስቲ ለመግባት እንቅልፍ አጥቼ አጠና ጀመር ። የምግብ እጥረት ፣ጭንቀትና ድካም የቀይ ሽብር ግርፋት በጎዳው አካሌ ላይ ተነባብረዉ፣ ፈተናውን ለመውሰድ አራት ወራት ያህል ብቻ እንደቀሩኝ፣ በተለምዶ „የወፍ በሽታ „ተብሎ ለሚታወቀዉና የቆዳን ቀለም ሁሉ ለሚያወይበዉ በሽታ ዳረጉኝ ። ሰውነቴ በጣም ደከመ ። ምግብ መብላት የማይታሰብ ሆነ ። በተለይ የሽንኩርት ቁሌት ሽታ በጣም ይጓጉጠኝ ጀመር ። ደከምኩ ። የሠፈራችን ሐኪም የነበሩት አሥር አለቃ ባመመኝ ቁጥር የሚወጉኝና የሚያሽለኝ ምንነቱ የማይታወቅ መርፌ እንኩዋ እንደ ወትሮዉ ሊያድነኝ አልቻለም ።ከሕመሜ
በተጨማሪ ማትሪክ ከወደቅሁ የሚጠብቀኝን መሪር ሕይወት በማሰብ ሰውነቴ ይበልጡኑ ተጎዳ ። ለማንበብ ፣
ለማጥናት አልቻልኩም ። ሥራዬ እንደ ደላው ሰው መተኛት ብቻ ሆነ ።
ለተሻለ ሕክምና ገንዘብ ስላልነበረ የሠፈር ሐኪሞችን በሞላ አዳረስኩ። ግን አልተሻለኝም ።በዚያን ጊዜ ልደታ አካባቢ የነበሩት ሐኪሞች በሙሉ በጦር ሠራዊቱ ውስጥ “ድሬሰር” የነበሩ ናቸው ። ምናልባት ከዚያ የላቀ ደረጃ የነበራቸዉ ሐኪሞች ነበሩ ከተባለ ቢበዛ “ነርስ” የነበሩቱ መሆን አለባቸዉ ። ቢሪሞ ወፍጮ ጋ የነበሩትን ውንዴሳን የሚረሳ የልደታ ልጅ ይኖራል ብዬ አላምንም ። ቃጫ ፋብሪካ አካባቢ የነበሩትስ ከበደ የሚባሉት??? ...አቤት ጥርስ ሲነቅሉ!
መንጋጭላን ጨምረዉ ነበር አብረው የሚነቅሉት ። ግን ዋናው ዓላማ ከሕመሙ መገላገል ስለነበር እሳቸው ጋር ሄደን እንነቀላለን ። ሌላ የተሻለ ሐኪም ጋ ለመሄድ ገንዘብ ከየት መጥቶ??/...ጠጃቸውን ካልጠገቡ መርፌ የማይወጉት መጋቢስ ???... መርፌዎቻቸው የታጨቁባትን የመነጽር መያዣ የምትመስል እቃ በላስቲክ ጠቅልለው ይዘው ቀኑን ሙሉ እየዞሩ መርፌ ሲወጉና ሲጠጡ ነበር የሚውሉት ። ስድባቸው ከሁሉም ትዝ ይለኛል ። የሚወጉን መርፌ ካመመንና ትንሽ እንኩዋ ከተንቀሳቀስን “ ዝም ብለህ ቁም። አንተ ዜብራ ፣ ኩሽ ማንኩሽ ሌባ “ ይሉናል። ይህቺን ስድብ ያልሰማ የልደታ ልጅ ይኖር ይሆን? ሁሉም ሐኪሞቻችን ያኔም ያረጁ ስለነበሩ ዛሬ በሕይወት ይኖራሉ ብዬ አልገምትም ።
ልደትዬ ጤንነታችንን ተከታትለው ያሳደጉንን ባለሙያ አዛዉንቶችዋን ከጎኗ ታስቀምጥልን ።
የወፍ በሽታው እየጠነከረ ሲመጣ ቤት ተኝቼ መዋል ጀመርኩ ።ጎረቤታችን የነበሩት እማማ ፈለቄ ሰውነቴ በጣም መክሳቱን ባዩ ጊዜ ድንግጥ ብለው „ ምነው ልጅዎትን ልትገሉት? እንዲህ እስከምታደርገው ድረስ??“ ብለው ከአዘኑ በኋላ ከእናቴ ጋር በጠዋት ተነስተን ወደ ጨርቆስ ቤተክርስትያን መቃብር ቤት ውስጥ ወደሚኖሩ አንዲት መነኩሴ ዘንድ እንድንሄድ መከሩን ። ሰለ መነኩሴዋ አዋቂነት ብዙም አጫወቱን ። በወቅቱ የአበሻ መድሃኒት መጠኑ ስለማይታወቅ ይጎዳል የሚለዉን አስተያየት አምንበት ነበርና ምክራቸዉን ብጠራጠረዉም ፣ በእንደዚህ ዓይነት ከመኖር መሞት ይሻላል ብዬ ተስማማሁና ሲነጋ ወደተባልንበት ሥፍራ አመራን ።
ወደ መቃብር ቤቱ ውስጥ ስንገባ መነኩሴዋ ከሚያስደስት ቁመናቸውና ደግነት ከሞላው ፈገግታቸው ጋር መሀል ላይ ቆመዉ አየናቸዉ ።ገብተን እንድንቀመጥ ቦታ ካሳዩን በኋላ ጠጋ ብለው ተመለከቱኝ ። ምንም ስለበሽታው
ሳንነግራቸው እጄን አንስተው ጥፍሮቼን አስተዋሏቸዉ። በጣምም አዝነው “ይህቺ መናጢ ልጄን ከየት አገኘችው??..
አይዞህ ድራሿን ነው የምናጠፋት” ብለው አበረታቱኝ ። “በሉ በቶሎ ሄዳችሁ አዲስ መሃረብና ሰባት ሎሚ ገዝታችሁ ኑ” ብለው አዘዙን ። እናቴ ለመግዛት ጨርቆስ ገበያ ስትሄድ እኔ እዚያው ቀረሁ ።
አጠገቤ አንድ ትንሽ ቀይ ልጅ ከእናቱ ጋር ተቀምጧል ። ፊቱ በጣም ከመገርጣቱ የተነሳ ያስፈራል ። መነኩሴዋ
ቀጥለው እናቱን “ልጄ ምን ሆኖ ነው ??”ብለው ጠየቁ። እናቱም የልጁን እጅ ገልጣ አሳየቻቸው ።ወዲያዉ መነኩሴዋ “ልጄን! ፣ ልጄን!” ብለው መጮህ ጀመሩ። ።”ይሄ እርኩስ ልጄን ሊገድለው እኮ ነው ! . . . ቆይ ብቻ . . . !” ብለው መዛትና በጠባቧ ክፍል ውስጥ መንጎራደዳቸውን ተያያዙት ። መጀመሪያ ላይ አጠገቤ በተቀመጠው ልጅ እጅ ላይ አንዳችም ነገር ለመመልከት አልቻልኩም። በርጋታ አተኩሬ ስመለከት ግን አንዳች አረንጓዴ የመሰለ የተዝለገለገ ነገር በቆዳው ውስጥ ሲላወስ አስተዋልኩ ። ልክ እንደሚሳብ ትል ስውነቱ ውስጥ ይንቀሳቀስና አንድ ቦታ ላይ ይሰበሰባል ። ከዛም ይበተናል ። እንደገና ተመልሶ ይሰበሰባል ።ሲሰበሰብ በልጁ ገጽ ላይ የሕመም ምልክት ይታያል ። ሲበተን ይሻለዋል ። መነኩሴይቱ ልጁን ከእናቱ ወስደው አጠገባቸው አስቀመጡት ።
ወደ እኔ ትኩር ብለው ተመለከቱ ። ዐዕምሮዬ ዉስጥ ሳዉጠነጥነዉ የነበረዉን ጥርጣሬ የተረዱት ይመስል ጮክ
ብለው “ለመሆኑ ትንባሆ ታቦናለህ?” አሉኝ ።ከጥያቄአቸዉ ለማምለጥ ዝምታን መረጥኩ ። “ትንባሆ ላንተ
አይሆንህም ሰውነትህ ይነግረኛል” አሉኝ ። በቁጣዉ ብዙም አልገፉበትም ፡፡ ትንሽ ደክሞኝ ስለነበር ስቅለሰለስ
ተመልክተው ኖሮ ወዲያዉኑ በርህራሔ ያጽናኑኝ ጀመር ። “ደግሞ ለዚች ነው የምትደክመው???. . . በሁለት ቀን ነዉ ነቅለን የምናወጣት . . . “ ብለው ፈገግ አሉልኝ ። ደግነታቸውና እምነታቸው በልቤ ውስጥ ጠዉልጎ የሰነበተዉን ተስፋ አለመለመው ።...“ ለአንዲት ወፍ እንዴት ልሸነፍ ??? „ ብዬ ነቃ አልኩ ።
እኔን ትተው ለልጁ እናት “ሰባት ቀን ይወስዳል የልጅሽ ጉዳይ ። ተዘጋጅተሻል ?” እናትየዋ እንዳልተዘጋጀች ተናግራ በሌላ ቀን ተዘጋጅታ ለመመለስ ቃልዋን ሰጠቻቸዉ ።አልተቀበልዋትም ። “በፍጹም ልጁ ከዚህ አይወጣም ። አንቺ ከፈለግሽ ሌሊት የምትለብሽውን ልብስ ሄደሽ አምጪ። ለማደር እዚሁ ተጠጋግተን እናድራለን” አሉ። ሴትየዋም “አባቱን አላስፈቀድኩ እንዴት ይሁን ?.. ሄጄ ብመለስ ይሻለል” አለች ። “ልጄ ልጅሽ እኮ በከባድ ተይዟል ። በጥቂት ቀናት ልታጪው ትችያለሽ ። ምንም ቀን የለሽም ። አባቱም ቢሆን እዚሁ ይምጣና ይቀመጥ እንጂ ብዙ ተስፋ አታድርጉ። ምን አልባት በልቦናሽ ፈረንጅ ሐኪም አስበሽ ከሆነ ተሳስተሻል ። እስከ አሁን ያላዳኑልሽን ወደፊትም አያድኑልሽም። እሞክራለሁ ካልሽ ልጅሽ ነው መውሰድ ትቻያለሽ ። ከዓይነ ውሃሽ ግን ሞክረሽ ደክመሽ የመጣሽ ይመስላል ።
አስቢበት። “ ብለው ወደ ሌሎቻችን ተመለሱ ።
“ለመሆኑ ስምህ ማነው ?” ብለው የድንገተኛ ጠየቁኝ ። ነገርኳቸው ። “የታላቁ ጀግና ሥም ???... አንተም እንደ እሱ መሆን አለብህ ።ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ታነባለህ ?” ጥያቄአቸዉን በአሉታ መለስኩ ። “ታዲያ ሰለ ስምህም
አታውቅም ማለት ነዋ ?/... መጽሐፈ መሳፍንት ላይ ይገኝልሃል አንብብ” አሉና አዘዙኝ ።
በአካባቢው ተመላላሽ የሆኑ በሽተኞች ስለነበሩ ሁሉም እየጠየቁ ምክር ሲሰጡ ነበር እናቴ የደረሰችው ። እንደገባች
ሰባቱን ሎሚዎች ከተቀበልዋት በሁዋላ ቆራርጠው በብርጭቆ ውስጥ እንድትጨምቀው ለእናቴ ሰጧት ። ያ ሎሚ
ሲጨመቅ ግማሽ ያህል ብርጭቆ ወጣው ። “በል ባንድ ትንፋሽ ጠጣው” ብለው አዘዙኝ ። ሎሚ አልወድም ። በተለይ ያን ዕለት ሆዴ ባዶ የሰነበተበት ሆነና እምቢ አለኝ ። እንደገና መጥተው “የምን መቅበጥ ! ልትድን አይደለም የመጣኸው?” በርትተህ ጠጣ ። አይዞህ”።
እንደምንም ብዬ ጠጣሁት ። ክዚያም መሀረሙን እንድትሰጣቸዉ እናቴን አዘዙዋት። ተሰጣቸው ። ወደ ጓዳ ገብተው አንዳች ነገር ይዘውበት መጡና ለኔ ሰጡኝ ።በአንክሮ ተመለከትኩት ፡--- በትንንሹ የተቆራረጠ ቂጣ ነው ። ..“ብላውና መሃረቡን በራስህ ላይ አዙረህ ወደ ጀርባህ ጣለው „አሉኝ ። በላሁት። ሌላ ምንም ነገር የሌለዉ የስንዴ ቂጣ ነው ።
ከምግቡ በኋላ የቀረውን ሎሚ እንድበላ አዘዙኝ ። እንደምንም ሞከርኩት ። በዚህ ጊዜ የልጁን እናት ሊሸኙ ወጡ ። ሲመለሱ እኔን እየተመለከቱ ፡-
“ዛሬና ነገን የስንዴ ዘር አልፈቅድልህም ። ፓስታ ሹታ ፣ መኮሮኒ ክልክል ነው ። . . . ቡና ፣ስኳር ፣ ሻይ አያስፈልግም። . . . የምፈቅደው የጤፍ እንጀራ በነጭ ሽንኩርትና በጨው ተፈትፍቶ ነው ። . . . እሱም ከሰዓት በኋላ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ነው መብላት ያለበት ። . . . በጣም ሊርበው ይችላል ። መድሃኒቱ እስከሚሠራ ምንም እንዳትሰጭው ። . . . ከምግቡ በኋላ አንድ ጠርሙስ የገብስ ጠላ ጥሩ ነው ።. . . መቼም የዘንድሮ ልጆች ጠላ አንወድም ነው የሚሉት ።
ቢሬታ ክልክል ነው ።. . . ጠላውን እምቢ ካለ ውሃውን ይጠጣ ። ብዙ ይጠጣ ። ከሁለት ቀን በኋላ ይድናል . . .”። ብለው አሰናበቱን ። እናቴ ገንዘብ ልትሠጥ ብትፈልግ በራፉ አጠገብ ከተቀመጠችዉ የእንጨት ሳጥን ውስጥ የቻለችውን ያህል እንድትከት ነገሯት ።
ወደ ቤት እንደተመለስን ደክሞኝ ስለነበር ተኛሁ ።ምግብ አስጠልቶኝ እንዳልከረመ ሁሉ አምሮቱ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ከእንቅልፌ ቀሰቀሰኝ ። እንደ ነፍሰ ጡር ሴት ሁሉም የምግብ ዓይነቶቸች ያምሩኝ ጀመር ። በተለይ የተከለከልኳቸውና ዘወትር ግን በድህነት የተነሳ የማላገኛቸውና የማልበላቸው እነ “ፓስታ ሹታ” በዐይኔ ይንከራተቱ ጀመር። ...“በል አርፈህ ተቀመጥ ተባልኩና ሆዴን እያሻሸሁ ዘጠኝ ሰዓት እስኪደርስ እጠብቅ ጀመር ። ዘጠኝ ሰዓት ላይ እንጀራ በጨውና በነጭ ሽንኩርት ተሰጠኝና በላሁ ። አንድ ብርጭቆ ጠላም ጠጣሁ ። አላጠገበኝም ። አንድ በጣም የምወደው ጣሳ ቤት ውስጥ ነበር ። በዚህ ጣሳ ውሃ ስጠጣ ያረካኛል ። ይህ ጣሳ ጉደኛ ነው ። እንደ ፍሪጅ ውሃ ያቀዘቅዛል ። እንደ እርጎ ውሃውን ያወፍረዋል ።ጣሳውን እወደዋለሁ ። በሱ ሙሉ ውሃ ጠጣሁና ጋደም አልኩ ። ከትንሽ ጊዜ በኋላ ሽንት ወጠረኝና ልሽና ተነሳሁ ።....እናም ሸናሁሁሁሁ.... በዚያ ቅጽበት ግን ከበሽታው እንደተገላገልኩ አወቅሁት ። ለወትሮው ደም የሚመስለው ሽንት ቀለሙ ተቀይሮ አመዳማ መልክ ያለው ሽንት ሆኖ ነበር ። ከሰውነቴ ውስጥ በሽታውን በሰባት ትንንሽ ቂጣ አውጥተው በሽንት መልክ እንደመነገሉት ተረዳሁ ።
በሁለተኛው ቀን በዐይኔ ኩዋስ ላይ የነበረው ቢጫ መግፈፍ ጀመረ ። መጽሐፍ ቅዱስ አውጥቼም መጽሐፈ
መሳፍንትን ማንበብ ጀመርኩ ። በአራተኛው ቀን በጣም ስለተሻለኝ እማሆይን ላመሰግን ወደ ጨርቆስ አዘገምኩ ። ደጅ ተቀምጠው ከዚያ ሕመምተኛ ትንሽ ልጅ ጋር ይጫወታሉ ። ልጁም የተሻለው ይመስላል ። ገና እንዳዩኝ „ለቀቀችህ አይደለም?” አሉና ጠየቁኝ ። በፈገግታ አረጋገጥኩላቸው ። አመሰገንኳቸውና መጽሐፈ መሳፍንትን ማንበቤን ነገርኳቸው። ስሜን ፈልጌ ማግኘቴንም ታሪኩንም እንደማውቅ ተናገርኩ ። “ልጄ ችግር ሲገጥምህ መጽሐፍ ቅዱስ እያወጣህ አንብብ ። ይጠቅምሃል አሉኝ “። ተሰናብቼ ልወጣ ስል “ ያን የትምባሆ ነገር አደራ ልጄ ። ለአንተ አይሆንም አሉኝ” ።
የእማሆይን ማስጠንቀቅያ ከሰማሁ ከብዙ ዓመታት በኋላ በአስም ሕመም ምክንያት ወደ አንድ የሳንባ ሐኪም
ልመረመር ሄጄ ያንኑ ቃላቸዉን አንድ ፕሮፌሰር ደገመልኝ ። የዚያን ቀን እርሳቸው ትዝ አሉኝ ። ከብዙ ልፋትና
ምርመራ በኋላ ፕሮፌሰሩ የደረሰበትን ውጤት እርሳቸው ከዓይኔ አንብበውት ነበር ።....“በትንባሆ ጢስ ሳቢያ የአየር መተላለፊያህ ስለቆሰለ እያበጠ አየር እንደልብ እንዳታገኝ ይከለክልሃል „ብሎ አስረዳኝ ። የፕሮፌሰሩን ፍርድ ከሰማሁ ወዲያ እማሆይ እንዳዘዙኝ መጽሐፍ ቅዱሴን አንብቤ ለራሴ በእማሆይ ስም ቃል ገባሁ ።ከዛ ቀን በኋላ እማሆይን ቀደም ብዬ ባለመታዘዜ እያዘንኩ ከትንባሆ ተለያየሁ።
እማሆይ አልፈዋል ;; ዘመናትን ባሳለፈዉ ግና ባልዘመነዉ ጥበባቸዉ አብነት የወፊቱ በሽታዬ ተረት ሆና አለፈች ።
ማትሪክም ...ችግርም ... ታለፉ። አሁንም ቢሆን ከታመምኩ የማስታውሰው እማሆይን ነው ። ዛሬ ያንን ችሎታቸውን ይዞ የቀጠለ ወራሽ ይኑራቸው ፣ አይኑራቸው አላውቅም ። የምታውቁ ምን አልባት ትነግሩን ይሆናል ብዬ አምናለሁ ።
በሃገራችን እንደማሆይ ዓይነት አዋቂዎች ፣ ሐኪሞች ብዙ ናቸው ። ጥበባቸውና ችሎታቸው በየቦታው ከትውልድ ወደ ትውልድ ሳይተላለፍ ፣ በተሻለ ዘዴ ለሕዝብ የሚዳረስበት ዘዴ ሳይበጅብት በየቦታው ተበትኖ የቀረውን ቤቱ
ይቁጠረው። ለእማሆይ ማስታወሻ ጨርቆስ ቤተክርስትያን ውስጥ ሃውልታቸውን የምናቆመው መቼ ይሆን ?ጨርቆስ እማሆይን ከጎኑ ያሰቀምጥልን ዘንድ እንፀልይ ። ለካስ ስለበሽታ ብዙ በስድ ንባብም ሊጻፍ ይችላል ።
ስለኛ የሚያስብ በሰላም ይክረም !

በልጅግ አሊ
beljig.ali@gmail.com
Source- mestawet news paper
Post Reply

Return to “Minnesota”