ጋዜጠኛ ተመሰገን ደሳለኝ ጥፋተኛ ተባለ የዋስ መብቱም ተነስቶ ማረሚያ ቤት እንዲወረድ ትዕዛዝ ተሰጠ

by Zelalem

አዲስ አበባ (አዲስኒውስ) – ገዢውን መንግስት አስመልክቶ በሚጽፋቸው ጽሁፎቹ የሚታወቀው እና ፍትሕ የተሰኘው ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ተመሰገን ደሳለኝ ዐቃቤ ህግ በመሠረተበት ሶስት ክሶች የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 9ኛ ወንጀል ችሎት የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላለፈበት፡፡ በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ የዋስትና መብቱ ተነስቶ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርድ ትዕዛዝ መስጠቱን የአዲስኒውስ ሪፖርተር የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ጠቅሶ ዘግቧል::

የፍትሕ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በነበረው ጋዜጠኛ ተመሰገን ደሳለኝ ላይ ሶስት ክሶችን ያቀረው የፌዴራል ዐቃቤ ህግ የጋዜጣዋ አሳታሚ በሆነው ማስተዋል ህትመትና ማስታውቂያ ድርጅት ላይ ደግሞ አንድ ክስ አቅርቧል፡፡
የአቃቤ ህግ ክስ እንደሚያመለክተው ፍትሕ በመባል ለህትመት ትበቃ በነበረው ጋዜጣ ተከሳሾቹ “ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሀይልና በአመጽ ለማፍረስ እና አመጽ ለማስነሳት ተንቀሳቅሰዋል፡፡” ይላል፡፡

Temesgen-Desalegn
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

የዐቃቤ ህግ የመጀመሪያ ክስ በጋዜጣው በቅጽ 4 ቁጥር 149 ነሐሴ 23 ቀን 2003ዓ.ም ታትሞ በተሰራጨው ጋዜጣ ላይ ሲሆን በጋዜጣው “ሞት የማይፈሩ ወጣቶች” በሚል ርዕስ በተከሳሹ ተመሰገን ደሳለኝ በተጻፈው ጽሁፍ ላይ ክስ አቅርቧል፡፡ የዐቃቤ ህግ ክሱ እንደሚያሳየው በጽሁፉ “ወጣትነት አብዮት ነው፣ ወጣትነት ለውጥ ነው፣ ወጣትነት ድፍረት ነው” በሚል የአጼ ሀይለሰላሴን ስርዓት ወጣቶች እንዴት እንደፈራረሱት በመጥቀስ አሁን ያለውን አፋኝና ጨቋኝ ስርዓት ለመገረሰስ የተዘጋጁ ብዙ ሞት የማይፈሩ ወጣቶች አሉን በማለት በአረብ ሀገራትና በሰሜን አፍሪካ የተከሰተው የህዝብ አመጽ በኢትዮጲያ እንዲተገበር እና ወጣቶች ለአመጽ ወደ አደባባይ እንዲወጡ ቀስቅሷል፡፡ እንዲሁም በጋዜጣዋ ዕትም ቅጽ 05 ቁትር 177 የካቲት 22 ቀን 2004ዓ.ም ታትሞ በተሰራጨው ህትመት “የፈራ ይመለስ” በሚል ርዕስ ስር “ሰለአድዋ ጀግንነት ካተተ በኃላ ወጣቶች ሆ ካሉ ምንም እንደማያስፈራቸው አስታውሶ በአሁኑ ውቅት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከመፍራት ይልቅ እንድንቆጣ የሚገፋፋ ነው በማለት ወጣቱን ለአመጽ ቀስቅሷል::” ይላል የዐቃቤ ህግ ክስ፡፡
የዐቃቤ ህግ ክስ በተጨማሪም ተከሳሹ “በሀገሪቱ ያለው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች ህዝቡን ወደ አደባባይ ሆ ብሎ እንዲወጣ ያሰገድዱታል፡፡ የኢትዮጲያ ህዝብም ሆ ብሎ እንዲወጣና መንግስትም የህዝቡን ድምጽ ለመግታት ነጭ ለባሾችን ቢያሰልፍ ህዝቡ ያሸነፋል፣ አንድ እንጂ ዘጠኝ ሞት የለም ፡፡ ለዚህም የሁስኒ ሙባረክ አመራርን ህዝቡ እንዴት እንዳስወገደው የኢትዮጲያ ህዝብ እንደምሳሌነት ሊወስደው ይገባል በማለት አመጽ እንዲነሳ ቀስቅሷል፡፡” ይላል

 

ጉዳዩን ሲመረመር የነበረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍድ ቤት ልደታ ምድብ 16ኛ ወንጀል ችሎት በወቅቱ ተከሳሽ ይከላከል ሲል ብይን መስጠቱ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሠረት ተከሳሽ የተለያዩ የጽሁፍ ማስረጃዎችን፣ አንድ የባለሙያና ሁለት የሰው ምስክሮችን አቅርበዋል፡፡ የሙያ ምስክርነታቸውን የሰጡት የህግ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ያሬድ በምስክርነት ቃላቸው ተከሳሹ ሙያው በሚፈቅደው መንገድ ጻፈ እንጂ ለአመጽ አልቀሰቀሰም በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ሌሎች ሁለት የሰው ምስክሮች በበኩላቸው ተከሳሹ በተከሰሰባቸው በሶስቱም ክሶች ሙያዊ ግዴታውን ተወጥቷል ሲሉ የምስክርነት ቃላቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ግን ተከሳሽ ከተሰጠው መብት አልፎ በመጠቀም የሌሎችን መብትና ጥቅም በሚነካ መልኩ ከጋዜጠኝነት ሙያ ስነ ምግባር ወጥቶ ህዝብን ለአመጽ የሚያነሳሱ ጽሁፎችን ለንባብ አብቅቷል፡ ያቀረባቸውም ምስክሮች ክሱን በሚገባ አላስተባበሉም በማለት ተከሳሹ በተመሠረተበት ሶስት ክሶች ጥፋተኛ ነው ሲል የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 9ኛ ወንጀል ችሎት የጥፋተኝነት ውሳኔ አሰተላልፎበታል፡፡ ተከሳሹ ጋዜጠኛ ተመሰገን ደሳለኝ እስካሁን ውጪ ሆኖ ክሱን ሲከታተል የነበረ ቢሆንም የጥፋተኝነት ውሳኔ መሰጠቱን ተከትሎ የዋስትና መብቱ ተነስቶ የቅጣት ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በማረሚያ ቤት እስዲቆይ ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡ ፍርድ ቤቱም የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለጥቅምት 17 ቀን 2007ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ጋዜጠኛ ተመሰጌን ደሳለኝ የተከሰሰው በኢፌዲሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 257 ሲሆን በዚህም አንቀጽ ጥፋጠኛ ነው የተባለ ሰው ከ1 ዓመት እስከ 15ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣም ይህ የህግ አንቀጽ ይደነግጋል፡፡
የጋዜጠኛ ተመሰጌን ደሳለኝ የክስ ክርክር ከሁለት ዓመታት በላይ የፈጀ ሲሆን በዚህም ውቅት ጉዳዩን ሲመለከቱ የነበሩ ከአራት ያላነሱ ዳኞች በተለያይ ምክንያት መቀያየራቸው ይታወቃል፡፡
አዲስኒውስ የፍርድቤቱን ውሳኔ ተከታትሎ ለአንባቢያን እንደሚያቀርብ ከወዲሁ ያስታውቃል፡፡Click Like to Get updated News Everyday.

Related News

Comments

comments

Related Posts

Leave a Comment