የ “ሶስት ማዕዘን” ፊልም ፕሮዲውሰር አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ ላይ የ10 ሚሊዮን ብር ዕገዳ ተላለፈበት

by Zelalem

የ “ሶስት ማዕዘን” ፊልም ፕሮዲውሰር እና የሴባስቶፖል ሲኒማ ቤት ባለቤት አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ ላይ የ10 ሚሊዮን ብር ዕገዳ ተላለፈበት፣
(AddisNews) – በተለያየ ወቅት በሰራቸው ሰማያዊ ፈረስ፣ ዓባይ ወይስ ቬጋስ እና በቅርቡ በሰራው ተሰርቶ እይታ ላይ ባለው ሶስት ማዕዘን በተሰኘው ፊልሙ የምናውቀው እንዲሁም የሴባስቶፖል ሲኒማ ቤት ባለቤት በሆነው በአርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ ስም በዘመን ባንክ ከሚገኘው ሂሳብ 10 ሚሊዮን ብር እንዳይንቀሳቅስ ፍርድ ቤት የዕግድ ትዕዛዝ አስተላለፈበት፡፡
ለዕግዱ ምክንያት የሆነው ደራሲ አቶ አትንኩት ሙሉጌታ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ክስ በማቅረባቸው ሲሆን ደራሲ አትንኩት ሙሉጌታ ነሐሴ 13 ቀን 2006ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ባቀረቡት ክስ አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ በቀርቡ ሰርቶት ለዕይታ ያቀረበው “ሶስት ማዕዘን” የተሰኘው ፊልም ታሪኩ በ 2000 ዓ.ም ካሳተመኩት “ፍቅር ሲበቀል” ከተሰኘው የረዥም ልብወለድ መጽሀፌ የተወሰደ ነው የሚል አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡
በክሱ ሶስት ማዕዘን የተሰኘው ፊልም መጽሀፉ ታትሞ ከወጣ ከ 5 ዓመታት በኋላ ለዕይታ እንደበቃም ተጠቀሷል፡፡ አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ ያለደራሲው ፍቃድ የቦታና የገፀ ባህርያት ስሞችን በመመቀያየር ብቻ የመጽሐፉን መሰረታዊ የጭብጥና የታሪክ ፍሰት በፊልሙ ውስጥ መጠቀሙን በክሱ አቤቱታ ውስጥ ተጨምሮ ተጠቅሷል፡፡

Sost Maezen Ethiopian Movie Trailer – Sost Maezen (Triangle)

አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ ፊልሙን እስከአሁን ድረስ በተደጋጋሚ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ ለተመልካቾች በማሳየት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን በክስ ማመልከቻቸው ላይ የጠቆሙት ደራሲ አትንኩት ሙሉጌታ፤ ተከሳሽ በፈጸሙት ተግባር ከፍተኛ የሞራል ጉዳት እንደደረሰባቸውና ወደፊትም ለማሳተም በማዘጋጀት ላይ ባለው የመጻሐፉ ቀጣይ ክፍል ላይ ፊልሙ ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖ እንደሚፈጠረባቸው እና እስከአሁንም ለደረሰባቸው ጉዳት የ10 ሚሊዮን ብር ካሳ ጠይቀዋል፡፡ ከሳሽ በክሳቸው የመጽሃፉን ጭብጥ፣ መቼትና የተለያዩ ታሪኮች እንዴት በፊልሙ ውስጥ እንደተጠቀሙበት ከሶስት ማዕዘን ፊልም ታሪክ ጋር በማመሰከር ለፍርድ ቤቱ በማስረጃነት አቅርበዋል፡፡
የክሱ አቤቱታ የቀረበለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ባለፈው መስከረም 6 በዋለው ችሎት የክሱ አቤቱታ ለተከሳሽ እንዲደርሰው እና መልስ እንዲሰጥበት ለጥቅምት 28 ቀን 2007ዓ.ም. ቀጠሮ አስተላልፏል፡፡ በተጨማሪም ከሳሽ ጳጉሜ 3 ቀን 2006 ዓ.ም በጻፉት ማመልከቻ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ተመልክቶ ቢፈርድላቸው ፍርዱን የሚያስፈጽሙበትን ንብረት በመጥቀስ ተከሳሹ በተለያዩ ባንኮች ካላቸው ገንዘብ ላይ 10 ሚሊዮን ብር እንዲታደገላቸው ፍርድ ቤቱን በጠየቁት መሠረት በአርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ ስም በዘመን ባንክ ከሚገኘው የሂሳብ ደብተራቸው 10 ሚሊዮን ብር ጉዳዩ ውሳኔ እስኪያገኘ ድረስ ታግዶ እንዲቆይ ትዕዛዝ አሰተላልፏል፡፡
አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ በአሁኑ ወቅት ከፊልሙ ስራው በተጨማሪ ሴባስቶፖል በተሰኘውና በኤግዝብሽን ማዕከል እና በብስራት ገብርኤል በሚገኘው ሲኒማ ቤቱ የተለያዩ ፊልሞችን በማሳየት ላይ ይገኛል፡፡
አዲስኒውስ የፍርድ ቤቱን ሂደት እና ውሳኔ ተከታትሎ እንደሚያቀርብላችሁ ከወዲሁ እንገልጻለን::Click Like to Get updated News Everyday.

Related News

Comments

comments

Related Posts

Leave a Comment