ኣንደበተ-ርቱእኣዊ ኣነጋገሮች (ክፍል ፪)፦ “ስሜ እከሌ ማንትስ እባል ኣለሁ” ወይስ “ስሜ እከሌ ማንትስ ነው”?

በ ልዑል ካሕሳይ

በክፍል ፩ መጣጥፌ ““ስምዎ ማን ነው?” ወይስ “ስምዎ ምንድን ነው?””፣ ቃሉ ‘ምን’ ግለሰዎችን እንጂ ስሞችን ተደራሽ ማድረጊያ እንደ ኣልሆነ ወይም ሊሆን እንደ የማይገባው ለማስረዳት ሞክሬ ኣለሁ። በዚህ ሁለተኛ ክፍል መጣጥፌ ደግሞ፣ ከስም ጋር በተገናኘ የኣስተዋልሁትን በመጠኑ ለየት ያለ ችግር ኣቀርባለሁ። በዚህ መጣጥፌ ርዕስ ውስጥ የጠቀስኩት ህጸጻዊ ኣነጋገር ብዙ ጊዜ የሚስተዋል ሰዎች ራሳቸውን በመገናኛ ብዙሓን ሲያስተዋውቁ ነው። “ስሜ ኣበበ ከበደ እባል ኣለሁ” ወይም “ስሜ ኣስቴር እባል ኣለሁ” ኣይነት ኣባባሎች እየተለመዱ የመጡ ይመስላል።

በቅርቡ በኣንድ የመገናኛ-ብዙሓን ኣውድ ላይ ኣንድ እንግዳ ራሳቸውን “ስሜ ኣበበ ከበደ እባል ኣለሁ” (እውነተኛ ስማቸውን ቀይሬው ኣለሁ) በማለት እንደ ኣስተዋወቁ ኣስተዋልሁ። ይህ ኣነጋገር ከስዋስው ኣንጻር ስህተት ነው። እንዲያውም ኣረፍተ-ነገሩ ሁለት ስዋስዋዊ ህጸጾችን የኣጣመረ ነው። የመጀመሪያው እና ቀለል ያለው ህጸጽ ከቃሉ ‘ስሜ (ስም)’ ጋር ቃሉ ‘እባል (መባል)’ ኣብሮ መቅረቡ ነው። የቃሉ ‘ስም’ ትርጉም ‘መባል’ ን ያካትታል። ኣንድ ሰው ወይም ኣንድ ነገር የሆነ ነገር ከተባለ ወይም በሆነ ነገር ከተጠራ፣ በዛ በተባለበት ወይም በተጠራበት ነገር ስያሜ ኣግኝቶ ኣል። በመሆኑም፣ የሁለቱ ቃላት ኣብሮ መገኘት ስዋስዋዊ ሰነፍ-ድግግሞሽን ይፈጥራል። በመሰረቱ ‘ኣበበ ከበደ’ የእኔ ስም ነው እንጂ የስሜ ስም ኣይደለም። በሌላ ኣባባል፣ ኣበበ ከበደ ራሱ ስሜ ነው። በመሆኑም፣ ትክክለኛው ኣባባል “ስሜ ኣበበ ከበደ ነው” ኣሊያም “እኔ ኣበበ ከበደ እባል ኣለሁ” ነው።

ሌላው እና ከስዋስው ኣንጻር የከበደው ህጸጽ ኣረፍተ-ነገሩ በ ፫ኛ ወገን ቃሉ ‘ስሜ’ ተጀምሮ በ ፩ኛ ወገን ቃላቱ “እባል ኣለሁ” መገባደዱ ነው። ‘ስሜ’ ማለት ‘የእኔ ስም’ ሲሆን፣ የኣረፍተ-ነገሩ ሳቢ ‘እኔ’ ሳይሆን ‘ስም’ ነው። ‘ስም’ ደግሞ ግዑዝ ስለ ሆነ ፫ኛ ወገን ነው። ‘እባል ኣለሁ’ ውስጥ የተካተተው ስውር ተውላጠስም ‘እኔ’ ሲሆን፣ ስዋስዋዊ ፩ኛ ወገን ነው። እንደ የምናውቀው የ፩ኛ ወገን ውስጥ የሚካተቱት ተውላጠስሞች “እኔ” እና “እኛ” ሲሆኑ፤ በ ፫ኛ ወገን ውስጥ የሚካተቱት ተውላጠስሞች ደግሞ “እርሱ”፣ “እርሷ”፣ “እርሳቸው”፣ እና “እነርሱ” ናቸው።

ቃሉ ‘ስሜ’ ልክ እንደ ቃላቱ ‘ቤቴ’፣ ‘ብዕሬ’፣ ‘ልብሴ’፣ ወዘተ እና እንደ ማንኛቸውም ሌሎች ግዑዛን ነገሮች የሚመደበው በ ፫ኛ ወገንነት ነው። ከስዋስው ኣንጻር ‘እኔ’ ከ ‘ስሜ’ የተለየሁ ስብዕና ያለኝ ፍጡር ነኝ። ስሜን ልቀይረው እችል ኣለሁ፣ እኔን ግን መቀየር ኣልችልም። ስለዚህ ስሜ እና እኔ የተለያየን ነገሮች ነን። ስለ ስሜ ሳወራ፣ ልክ ስለ ስልኬ ወይም ስለ ጫማዬ እንደ የማወራ፣ ከራሴ ለይቼ ነው የማወራ።

ለምሳሌ፣ “ጫማዬ ቆንጆ ነው” እንጂ “ጫማዬ ቆንጆ ነኝ” ማለት ኣልችልም። በተመሳሳይ፣ “ስልኬ ኣይ-ፎን ይባል ኣል” እንጂ “ስልኬ ኣይ-ፎን እባል ኣለሁ” ማለት ኣልችልም። በመሆኑም “እኔ ኣበበ ከበደ እባል ኣለሁ” ማለት እችል ኣለሁ እንጂ “ስሜ ኣበበ ከበደ እባል ኣለሁ” ማለት ኣልችልም–እኔ እና ስሜ የተለያየን ነገሮች ስለ ሆን።

“ስምን መልኣክ ያወጣዋል” እንዲሉ፣ ኣንድ-ኣንድ ሰዎች ለስማቸው ካላቸው ኣክብሮት የተነሳ፣ ወይም ራሳቸውን ከስማቸው ለይተው ለማየት ከመቸገር የተነሳ ይህን ሃሳብ ይቃወሙ ይሆን ኣል። እንዲያውም ይህ ስዋስዊ ችግር የበለጠ የሚጎላ ሰዎች ስለ የራሳቸው የኣካል ክፍሎች ሲያወሩ ነው። ለምሳሌም ኣረፍተ-ነገሩን “እጄን ኣመመኝ” ያስተውሉ ኣል። ትክክለኛው ኣባባል “እጄ ታሞ ኣል” ነው። ከስዋስው ኣንጻር፣ ምንም እንኳን እጄ የእኔ ቢሆንም፣ እጄ እኔ ኣይደለም። የሚቀጥለው ኣረፍተ-ነገር በእጄ እና በእኔነቴ መካከል ያለውን ስዋስዋዊ ልዩነት በትክክል ያሳያል፦ “እጄ ሰፊ ነው።” “እጄ ሰፊ ነኝ” እንደ የማይባል ይመልከቱ ኣል። ይህም ‘እጄ’ ስዋስዋዊ ፫ኛ ወገን መሆኑን እና ከስዋስዋዊው ፩ኛ ወገን ከ ‘እኔ’ የተለየ መሆኑን ያመለክታል።

እየ ኣንድ-ኣንዱ ኣረፍተ-ነገር የራሱ ሳቢ ኣለው። በኣንድ ኣረፍተ-ነገር ውስጥ ሳቢ የሚለይ ድርጊት ፈጻሚ በመሆኑ፣ ድርጊት ፈጻሚ ከኣል ሆነ ደግሞ ስለ እርሱ የተነገረ ነገር በመኖሩ ነው። በየኣማርኛ ስዋስው ሕግ መሰረት፣ የሳቢው እና ግሱ በየሚያመላክቱት ተውላጠስም መጣጣም ኣለባቸው። ለምሳሌ፣ ኣንጋፋውን ኣረፍተ-ነገር ‘ኣበበ ዳቦ በላ’ ያስተውሉ ኣል። በዚህ ኣረፍተ-ነገር ውስጥ ሳቢው ‘ኣበበ’ ሲሆን የሚያመላክተው ስዋስዋዊ ተውላጠስም ‘እርሱ’ ነው። በተመሳሳይ፣ ግሱ ‘በላ’ ሲሆን፣ የሚያመላክተው ተውላጠስም ‘እርሱ’ ነው። “ኣልማዝ ዳቦ በላ” ወይም “ኣበበ ዳቦ በላች” ወይም “ኣልማዝ እና ኣበበ ዳቦ በላ” ካልን ግን ሳቢው እና ግሱ የሚያመላክቱ ኣቸው ተውላጠስሞች ስለ የሚለያዩ ስዋስዋዊ ችግር ይከሰታል ማለት ነው።

“ስሜ ኣበበ ከበደ እባል ኣለሁ” ካልን ሳቢው እና ግሱ የሚያመላክቱ ኣቸው ተውላጠስሞች ላይጣጣሙ ነው ማለት ነው። ምክንያቱም፣ ከላይ እንደ ጠቀስሁት፣ ‘ስሜ’ ማለት ‘የእኔ ስም’ ሲሆን፣ ልክ እንደ ‘የእኔ ተሽከርካሪ’፣ ተውላጠስሙ ‘እርሱ’ ሲሆን፣ ‘እባል ኣለሁ’ ግን የሚያንጸባርቁት ተውላጠስም ‘እኔ’ ነው።

በክፍል ኣንድ መጣጥፌ ማገባደጃ ላይ ለመግለጽ እንደ ሞከርሁ፣ እንደ እነዚህ ኣይነት ህጸጾች ኣሁን ካለንበት ማሕበረ-ምጣኔሃብታዊ ሁኔታ ኣንጻር ግዙፍ መስለው ኣይታዩ ይሆን ኣል፣ ነገር ግን የቋንቋ ኣጠቃቀማችን ያለበትን ኣሳሳቢ ደርጃ ኣመላካች ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ ለኢትዮጵያ ዘላቂ እድገት ወሳኝ የሆነውን ስልጠታዊ መግባቢያ እንድ ኣናዳብር የሚከለክሉ ጋሬጣዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ ውስጥ የቋንቋ ኣጠቃቀም ቀውስ እንደ ኣለ የማምን ስሆን፣ የሚከተሉት የቀውሱ ማመላከቻዎች ሃገራችን ወደ ረቀቀ ማህበራዊ እና ምጣኔሃብታዊ እድገት እንድ ኣትደርስ ማድረግ ኣቸው ኣይቀሬ ነው፦

  • ሃገራዊ ቋንቋዎች ለታላላቅ ሳይንሳዊ እና ቴክኖሎጂያዊ ኣጠቃቀሞች እንዲ በቁ ኣለመዳበራቸው

  • የእንግሊዝኛ ቃላት በድንገት ቋንቋ ኣችንን መውረራቸው እና በዚህም ምክንያት የተከሰቱ በርካታ ችግሮች (ከስዋስው ብልሽትና ከመግባባት እንቅፋት በተጨማሪ በሃገሪቱ ውስጥ በኣለው የመልካም ኣስተዳደር እጥረት ላይ የሚያስከትለው ተጨማሪ ጫና)

  • መንግስት የባእድ ቋንቋን በሃገሪቱ ውስጥ የመማሪያ መሳሪያ መሆኑን መኣቆም ኣለመቻሉ

  • ትልልቅ ሃግራዊ ተቋማት እና ታላላቅ መሪዎች ሳይቀሩ በኣልተማረው ሕዝብ ጫንቃ ላይ ከሞላጎደል እንግሊዝኛን በጉዲፈቻ ማዳበላቸው፣

  • ዜጎች ኣንደበታቸውን በፈቱበት ቋንቋ ሃሳባቸውን በጥራት እና በፍጥነት መግለጽ ኣለመቻላቸው፣ ሰዎች ባዶ ቃላትን (“እንትን”) በንግግሮቻቸው ውስጥ ኣብዝተው መጠቀማቸው፣

  • ዜጎች በገዛ ሃገራቸው የባዕድ ቋንቋ ባለመቻላቸው የሚከሰተው ኣለመግባባት እና የመልካም ኣስተዳደር እጥረት (ለምሳሌ፣ በሃኪሞች እና በተለይም የእንግሊዝኛ ቃላትን በማያውቁ ህመምተኞች መካከል መግባባት ኣለመቻሉ)

በሌላ መጣጥፍ እስክንገናኝ ቸር ሰንብቱ።

Source

Join the Conversation on Facebook and Twitter


AddisNews is not responsible for the contents or reliability of any other websites to which we get contents from and provide a link and do not necessarily endorse the views expressed by them.

Comments

comments

Click Here to Read More on AddisNews

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published.