አለም ዓቀፍ የአጫጭር ፊልሞች ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ተከፈተ

by ocean

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ሰኔ 7 ቀን 2002 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ላይ እንግዳ ነገር አሳየ፡፡ ከቸርችል ጎዳና ወደ ለገሀር በሚወስደው የቀኙ መንገድ ለትራፊክ ዝግ ሆኖ የቴአትር ቤቱ ሕንፃ መተላለፊያው መንገድም ቀይ ምንጣፍ (50 ሜትር ርዝመት) ያለው ተነጥፎበት የሚመጡትን እንግዶች ለመቀበል እየተጠባበቀ ነበር፡፡

ጉዳዩ ለመጀመርያ ጊዜ በኢሜጅስ ዛት ማተር የተዘጋጀውን አንደኛውን ኢንተርናሽናል የአጭር ፊልም ፌስቲቫል የመክፈቻ ሥርዓትን ለማድመቅ የተዘጋጀ ልዩ መርሐ ግብር ነበር፡፡

እንግዶች በፌስቲቫሉ ቀይ ምንጣፍ ላይ

እንግዶች በፌስቲቫሉ ቀይ ምንጣፍ ላይ

የክብር እንግዶችንና ታዳሚዎችን መቀበል ከተጀመረበት ከ11 ሰዓት ጀምሮ በተዘጋው መንገድ መካከል ላይ የተሰለፈው የማርሽ ባንድ በሚያሰማው ሀገራዊ ጥዑም ዜማ የታጀቡት ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሀገር ዜጎች በክብር አልባሳት ሆነው በባሕር ማዶ እንደተለመደው በቀዩ ምንጣፍ እየተጓዙ ወደ አዳራሹ ሲያመሩ፣ አጋፋሪዎቹም የእንግዶቹን ማንነት በይፋ እያስተዋወቁ የመሩበትም መንገድ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን የፊልም ባለሙያዎች፣ አርቲስቶች፣ የጥበብ ሰዎችና ታላላቅ ሰዎች ባለፉ ቁጥርም የተስተጋባበት ነበር፡፡ በዕለቱ ከተገኙት ታዋቂ ዓለማቀፍ የፊልም ባለሙያዎችና ሞዴሎች መካከል ሱማሌያዊቷ ዋሪስ ዳሪ ትገኝበታለች፡፡ ያልታደመውና እግረ መንገዱን በብሔራዊ ቴአትር በኩል የሚያልፈውም ቆሞ መከታተሉን፣ የሚያከብራቸውና የሚያደንቃቸው የጥበብ ሰዎችን ባየ ቁጥርም ማጨብጨቡን አልተወም ነበር፡፡

እስከ ፊታችን ቅዳሜ ሰኔ 12 ቀን 2002 ዓ.ም. ድረስ በሚዘልቀው የፊልም ፌስቲቫል 100 አጫጭር ፊልሞች፣ በፊልም ዝግጅት ዙርያ ዐውደ ጥናትና የውይይት መድረኮች እንደተዘጋጀለትና እንደሚዘጋጅ በተገለጸበት መሰናዶ ላይ ፌስቲቫሉን በይፋ የከፈቱት አምባሳደር መሐመድ ድሪር የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ናቸው፡፡

እንግሊዝኛና ፈረንሣይኛ፣ ስጳኛና ሱማሊኛ ተናጋሪ የሆኑ ሹማምንትና እንግዶች በተገኙበት መድረክ ላይ አማርኛውን ጨምረው በእነዚሁ ቋንቋዎች አሰባጥረው የተናገሩት አምባሳደር መሐመድ፣ ለኢትዮጵያ ፊልም ዕድገት ሁሉም እንዲተጋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለፊልም የሚመቸው የኢትዮጵያን ገጽታ በመጠቀም ከውጭ የፊልም ባለሙያዎች በፊት ኢትዮጵያውያኑ ቀዳሚ መሆን ይገባቸዋል ያሉት አምባሳደር መሐመድ፣ በሩጫውም፣ በዳንኪራውም የታወቁትን ያህል በትወናውና በፊልሙም ማሳየት ይችላሉ ብለዋል፡፡ በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ የቀረቡት አምስት አጫጭር ፊልሞች “ለዛሬ” (የዘላለም ወልደ ማርያም፣ ከኢትዮጵያ) “ፐርሰን ቱ ፐርሰን (የዊም ወንደርስ፣ ከጀርመን”፣ “ዌልካም ቱ ውመን ሁድ”፣ (የሻርሎቴ ሜትካፍ፣ ከእንግሊዝ”፣ “ኮፊ ኤንድ አላህ” (ሲማ ዑራኤል፣ ከኒውዝላንድ”፣ “ፎን ደ ቲንት” (የሉዊዝ ሜንዲ፣ ከፈረንሣይ) ናቸው፡፡

በፌስቲቫሉ ሥራ አስፈፃሚ ዘላለም ወልደ ማርያም የተዘጋጀው “ለዛሬ” በቅርቡ በተካሄደው የታሪፋ አፍሪካ ፊልም ፌስቲቫል በምርጥ አጭር ፊልምነት ተሸላሚ እንደነበረ አይዘነጋም፡፡

ፌስቲቫሉ በምሥራቅ አፍሪካ አጫጭር ፊልሞች መካከል የሚደረግ ውድድር የሚያስተናግድ ሲሆን፣ የሚዳኙትም ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው ባለሙያዎች ነው፡፡ ከስድስቱ ዳኞች መካከል ኢትዮ-አሜሪካዊቷ የፊልም ፕሮፌሰር ሳሌም መኩርያና ፕሮፌሰር ዐቢይ ፎርድ ይገኙባቸዋል፡፡

ምርጥ የምሥራቅ አፍሪካ አጭር ፊልም ሆኖ በአንደኛነት የሚያሸንፈው በመጪው መስከረም በፈረንሣይ በሚኖረው የ10 ቀን ሥልጠና ተሳታፊ የሚያደርገውን ሙሉ ወጪ የሚገኝ ሲሆን፣ ሁለተኛ ለሚሆነውም በአዲስ አበባ በብሉ ናይል ፊልም ትምህርት ቤት የሦስት ሳምንት ሥልጠና ዕድል ያገኛል፡፡

የፊልም ፌስቲቫሉ በሁለተኛው ቀን ውሎው ትናንትና፣ ዓለማቀፍ ተሸላሚ የሆነውና በሶማሊያቱ ዋሪስ ዴሪ ሕይወት ዙርያ የሚያጠነጥነውና ኢትዮጵያዊቷ ሊያ ከበደ በመሪ ተዋናይነት የምትተውንበት “ደዘርት ፍላወር” ለመጀመርያ ጊዜ ለእይታ በቅቷል፡፡

የአጭር ፊልም ፌስቲቫል መካሄድ ለምሥራቅ አፍሪካ የፊልም ጥበብ ዕድገት ጠቀሜታ እንደሚኖረው ያመለከቱት የፌስቲቫሉ ዳይሬክተር ማጂዳ አብዲ፣ እስከ ቅዳሜ ድረስ በሚቆየው ፕሮግራም ወጣቶች በመገኘት ትምህርት እንዲቀስሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በባሕር ማዶ እንደሚደረገው ሁሉ በቀይ ምንጣፍ በታጀበውና ሃያ በሚደርሱ የተለያዩ የአፍሪካና የአውሮጳ ሰንደቅ ዓላማዎች ያሸበረቀው የፊልም ፌስቲቫሉ ክንውን ከጀማሪነት አኳያ ማለፊያ ነው ብለው አስተያየታቸውን የሰጡ ታዳሚዎች አሉ፡፡

በቀዩ ምንጣፍ ላይ እንግዶቹ መጓዝ ሲጀምሩ በድምፅ ማጉያ ማንነታቸውን እየገለጹ የነበሩት ወንድና ሴት አጋፋሪዎች ይጠቀሙበት የነበረው ድምፅ ማጉያ መበላሸቱ ሱማሊያዊቷ ዓለማቀፍ ሞዴል ዋሪስ ዳሪንም ሆነ ሌሎች ታዋቂ ዓለም አቀፍ የፊልም ባለሙያዎችን ለማስተዋወቅ አላስቻለም፡፡ አስተማማኝ ድምፅ ማጉያ ማዘጋጀት አይቻልም ኖሯል?

አጋፋሪዎቹ ወጣትና አልፎ አልፎ አንጋፋ የጥበብ ሰዎችን ለማስተዋወቅ የተጉበትን ያህል፣ ከአጠገባቸው አማካሪ ኖሯቸው በአገሪቱ ውስጥ ሁነኛ ሥራ ያከናወኑ ታላላቅ ሰዎች ወደ ቀዩ ምንጣፍ ብቅ ሲሉ ተነግሮ ቢሆን ኖሮ፣ ምንኛ ባማረ ነበር፡፡ አስተዋውቀው ቢሆን ኖሮ ፌስቲቫሉን ምንኛ ባሳመሩት ነበር፡፡

ምንጭ: ሪፕርተር

Related Posts

Leave a Comment