በጎንደር ከተማ በህዝቡ እና የጸጥታ ሃይሎች የተነሳው የተቃውሞ ግጭት ቀጥሏል – በፎቶ እና ቪዲዮ

AddisNews: በጎንደር ከተማ የወልቃይትን ሕዝብ የማንነት ጥያቄ በኮሚቴ አባልነት የሚመሩትን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚል የተንቀሳቀሱ የደህንነት አባላት እና የከተማው ህዝብ መካከል በተፈጠረው ግጭት በሁለቱም ወገን የተገደሉ እና የቆሰሉ መኖራቸው እየተዘገበ ነው::

ይህ ዘገባ እስከተጻፈበት ጊዜ ድረስ ከሃያ የማያንሱ ሰዎች በግጭቱ መገደላቸው እየተነገረ ነው::

ከሰው ህይወት በተጨማሪም የከተማው ህዝብ በስልጣን ላይ ላለው የገዢው ፓርቲ ቅርብ እና ደጋፊ ናቸው ያላቸውን ሰላም ባስን ጨምሮ የንግድ መደብሮችን: ሆቴሎችን እና ተሽከርካሪዎችን በእሳት በማቃጠል እና በመሰባበር ተቃውሞውን እየገለጸ ነው::

ይህ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ የተባሉ የማንነት ኮሚቴ አባል ለማሰር በሚሞክሩበት ወቅት የአካባቢው ህዝብ ተቃውሞ በማስነሳቱ  ተፈጠረ በተባለው በዚህ እንቅስቃሴ ከትላንት ጀምሮ ተባብሶ አብዛኛው የጎንደር ከተማ ወጣት የተቃውሞ ድምጹን እያሰማ ይገኛል::

ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ግለሰቦች የማንነት ኮሚቴ አባላቱን ለማፈን የተንቀሳቀሱት የጸጥታ ሃይሎች ከትግራይ ክልል የመጡ እንደሆነ እየገለጹ ነው::

በኢሳት ቴሌቭዥን እና በማህበራዊ ድረ-ገጾች በተለጠፉ ምስሎች እንደሚታየው የጸጥታ ሃይሎች ጥይት እየተኮሱም የከተማው ነዋሪ በብዛት ወጥቶ ገዢውን መንግስት በሰላማዊ ሰልፍ በመቃወም ላይ እንደነበር ያሳያል::

ፋናን ጨምሮ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ግጭቱን በኤርትራ የሚታገዙ ሃይሎች እንደፈጠሩት እና በቁጥጥር ስር ለማዋል የሞከሩትም በትግራይ ሰዎችን የገደሉ ግለሰቦችን እንደሆነ ዘግበዋል