መለስ ዜናዊ ተቃዋሚዎችን አስጠነቀቁ

by ocean

መለስ ዜናዊ

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በተጨባጭ ማስረጃ ላይ ያልተመሰረተ ውንጀላ የሚያቀርቡ ናቸው ያሏቸውን ተቃዋሚዎች፣ “እሳት ለኩሶ በመጨረሻ ሰዓት ላይ ሸርተት ማለት አያዋጣም፤” በማለት ከተሳሳተ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማስጠንቀቂያ አስተላለፉ፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው ተአምር ካልተፈጠረ በቀር በአገሪቱ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ይካሄዳል የሚል ግምት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

ትናንት በተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የመንግሥታቸውን የዘጠኝ ወር ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ከፓርላማ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አቶ መለስ፣ በማስረጃ ያልተደገፈ ውንጀላ የሚያቀርቡ ተቃዋሚዎች በምርጫ ብጥብጥ የመፍጠርና አዝማሚያውን አይተው በ11ኛው ሰዓት ሸርተት ለማለት ወይም እስከመጨረሻው ድረስ ለመግፋት በሚል የተሳሳተ ግምት ይዘው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ጠቁመው፣ እነዚህ ወገኖች በያዙት አመለካከት ከቀጠሉ በላያቸው ላይ የባሰ ችግር ሊፈጠርባቸው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡

“አሁን ባለበት ሁኔታ አንድና አንድ አማራጭ ብቻ ነው ያለው፡፡ ሰላማዊና ሕገ ወጥ መንገድ እያጣቀሱ መሥራት ጊዜው አልፎበታል፤” ያሉት አቶ መለስ በቀጣዩ ምርጫ እሳት ለኩሶ በመጨረሻ ሰዓት ላይ ሸርተት ማለትና በሕፃናት ለመጫወት ዕድል እንደማይኖር አስገንዝበዋል፡፡

“በዚህ አስተሳሰብ ረእሳት ለኩሶ ሸርተት ለማለትሪ የምትመሩ ዜጎች ወንድሞቻችን ካላችሁ እንደገና ልምከራችሁ፤ የባሰ ጥፋት ያስከትላል፤ በተለይም በላያችሁ ላይ የባሰ ችግር ይፈጥራል፡፡ የሚሻለው ሕግ፣ ሥርዓትና ሰላማዊ መንገድ ተከትሎ መሄድ ነው፡፡ ብንለያይም ባንለያይም፣ በሰላማዊ መንገድ እናድርገው፤ በሰለጠነ መንገድ እናድርገው፤ በተጨባጭ ማስረጃ ላይ የተመሰረተ እናድርገው፤” ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ ኮንግረስ (ኦሕኮ) ሊቀመንበርና የመድረክ አመራር አባል ዶ/ር መረራ ጉዲና ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅት፣ በምርጫው ሂደት የፓርላማ አባላት ሳይቀሩ መደብደባቸውን፣ ብዛት ያላቸው የመድረክ እጩዎች ከምርጫ ቦርድ በራፍ ተይዘው መታሰራቸውንና ሌሎችም በደሎች እንደተፈጸመባቸው ጠቅሰው፣ በዘንድሮው አገራዊ ምርጫ ተአምር ካልተፈጠረ በስተቀር ነፃና ፍትሐዊ የሆነ ምርጫ በአገሪቱ ይካሄዳል የሚል ግምት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ ከ200 ሺሕ በላይ የሚሆኑት የምርጫው አስፈጻሚዎችም በኢሕአዴግ አባልነት፣ በደጋፊነትና በጥቅም ቁርኝት የሚታወቁ መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

የሥነ ምግባር ደንቡን በሚመለከትም አቶ መለስ በትግራይ ባደረጉት ንግግርና የኢሕአዴግ ልሳን በሆነው አዲስ ራዕይ መጽሔት ላይ በወጣው የምርጫ ስትራቴጂ የተሻረ መሆኑን፣ ኦህዴድ ካድሬዎቹን በሚያሰለጥንበት የምርጫ ሥነ ምግባር ላይ ተቃዋሚዎችን “የጥፋት ግንባር” ብሎ መጥራቱም፣ የሥነ ምግባር ደንቡ መጣሱን እንደሚያሳይ ዶ/ር መረራ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር መረራ ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ዴሞክራሲያዊ የሥነ ምግባር ደንብ ቀርቦለት በተደጋጋሚ ተለምኖ አልፈርምም ያለውና ዴሞክራሲያዊ የትግል አግባብን ለመውሰድ ያልፈቀደው የዶ/ር መረራ ድርጅት ረመድረክሪ ስለዴሞክራሲያዊ የትግል አግባብ ለመከራከር የሞራል ብቃቱ የሚጎድለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አቶ መለስ እንዳሉት፣ ምንም እንኳን መድረክ የሥነ ምግባር ደንቡን ባይቀበልም፣ በዴሞክራሲያዊ ትግል አግባብ ለመሄድ ፈቃደኛነት ቢጎድለውም፣ አባላቱ በዜግነታቸውና ሕገ መንግሥቱ በሚያስከብርላቸው መሠረት መቀጥቀጣቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ለሚመለከተው አካል ቢያቀርቡ መፍትሔ ማግኘት ይችላሉ፡፡

“ተደበደብን፣ ተቀጠቀጥን የሚለው ወሬ ለመጀመርያ ጊዜ የሰማነው አይደለም፤ እርስ በእርሳችሁ ተቀጣቅጣችሁ ስታበቁ ኢሕአዴግ ቀጠቀጠን ብላችሁ ስታወግዙን እጅ ከፍንጅ ተይዛችኋል፤” ያሉት አቶ መለስ፣ ተቃዋሚዎች ያለምንም ማስረጃ ኢሕአዴግን ከመወንጀል ይልቅ በማስረጃ የተደገፈ ጥቆማ ቢያቀርቡ ደረሰ የተባለው ችግር እንደሚቀረፍ አመልክተዋል፡፡ ከሥነ ምግባር ደንቡ ውጪ የኢሕአዴግ አባላት የምርጫ አስፈጻሚዎች አሉ ከተባለም መጠቆም እንደሚቻል አክለው ገልጸዋል፡፡

በኢሕአዴግ ልሳን አዲስ ራዕይ መጽሔት የወጣው የምርጫ ስትራቴጂ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት ወንጀል ሲፈጽሙ ወንጀሉን አጋልጠው ለበላይ አካል እንዲያሳውቁ እንጂ፣ ራሳቸው ርምጃ እንዳይወስዱ የሚከለክል መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎችን የጥፋት ኃይሎች የሚል ስያሜ የሰጣቸው የኢትዮጵያ መንግሥት በአልሸባብ ላይ ርምጃ ለመውሰድ በተዘጋጀበት ወቅት በፓርላማ መቀመጫ ያላቸው ተቃዋሚዎች የጥፋት ኃይል ከሆኑት ሻዕቢያና ከኦነግ ጋር በማበር እርምጃውን በመቃወማቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

“በዚህ መድረክ ላይ በዚህ ምክር ቤት ውስጥ አልሸባብ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ባወጀበት ወቅት፣ ሻዕቢያ ከአልሸባብ ጋር ሆኖ እነ ኦነግን አሰልፎ በዘመተበት ወቅት፣ የአገር ጉዳይ ነው አብረን እንሰለፍ ብለን በምንጠይቅበት ወቅት ሻዕቢያን፣ ኦነግንና መሰሎቹን ከውሳኔው ካላወጣችሁ በስተቀር አንደግፋችሁም ብላችሁ በተግባር ከዚህ ከጥፋት ግንባር ጋር አብራችሁ የተሰለፋችሁ ናችሁ፤ ከሻዕቢያና ከኦነግ ጋር ስላልተሰለፈ ኢዴፓን በጥፋት ግንባርነት አልፈረጅንም፤” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢሕአዴግ ከባዶ መሬት ተነሥቶ ተቃዋሚዎችን የጥፋት ግንባር አድርጎ እንዳልፈረጀ አስረድተዋል፡፡

ኢዴፓ መንግሥትን በጭፍንና ያለምክንያት የመተቸትና የመክሰስ ፍላጎት የሌለው ፓርቲ መሆኑን የጠቆሙት የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው፣ ርሳቸው በሚወዳደሩበት ቡግና ወረዳ በጣም ብዙ ችግሮች መኖራቸውን፣ ፓርቲው የለጠፈው ፖስተር መላጡንና ከደጋ እስከ ቆላ ድረስ በእያንዳንዱ ቤት ሃይማኖት የሚያጠፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መጣባችሁ እየተባለ በነፍስ አባት እየተወገዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መንግሥት የሥነ ምግባር ደንቡ እንዲፈጸም የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበትና በተለይም እንደ ርሳቸው ዓይነት ፓርቲ ጤናማ የምርጫ ሂደት እንዲኖር የሚፈልጉ ፓርቲዎች ችግር ሲደርስባቸው ዝም ብለው መታየት እንደሌለባቸው የገለጹት አቶ ልደቱ፣ ርሳቸው በሚወዳደሩበት አካባቢ የደረሰውን ችግር ለመንግሥት ቢያሳውቁም፣ “የገዢው ፓርቲ ሰዎች ችግሮችን እየፈጠሩ ስለመሆኑ ማስረጃ ካላቀረባችሁ ችግር መኖሩ ቢታይም፣ ምንም ልናደርግ አንችልም፤” የሚል ምላሽ ማግኘታቸው ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአቶ ልደቱን ፓርቲ ሰላማዊ የትግል ስልት ኢሕአዴግ እንደሚያከብረው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፣ በበኩላቸው፣ ኢዴፓ ከዚህ የሰላማዊ ትግል ስልቱ እንዳይንሸራተት መንግሥታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግና በሰላማዊ ትግል ጉዳይም አጋር ሆነው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡ በላስታ አካባቢ አቶ ልደቱ የጠቀሷቸው ችግሮች ተፈጽመው ከሆነም ድርጊቱን የፈጸሙት ሰዎች እጃቸው እንደሚቆረጥ ረበአካል ሳይሆን በአስተሳሰብሪ፣ ሳይፈጽሙ ተወንጅለው ከሆነ ደግሞ የወነጀላቸው ሰው (በአካል ሳይሆን በአስተሳሰብ) ምላሱ መቆረጥ እንዳለበት አክለው ገልጸዋል፡፡

ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ አቶ ልደቱ በላስታ አካባቢ ተፈጽሟል ያሉትን ስሞታ በኢሕአዴግ አመራሮች በኩል መስማታቸውን የጠቆሙት አቶ መለስ፣ ሃይማኖትን መሠረት አድርጎ የምርጫ ቅስቀሳ የሚያደርግ ሰው ካለ፣ ርምጃ እንደሚወስድበት አስታውቀዋል፡፡

“አቶ ልደቱ ሃይማኖት ቀይረዋል፤ እንዲህ ዓይነት ሃይማኖት አምጥተዋል፤ ብሎ የቀሰቀሰ የእኛ ሰው ካለ፣ ያ ሰው የእኛ አይደለም፤ ወራዳ ሌባ ነው፤ ልድገመው ወራዳ ሌባ ነው፡፡ ይህ ከኢሕአዴግ ጋር በምንም መልኩ ሊገናኝ የማይችል የወራዶች አመለካከት ነው፡፡ የኋላ ቀሮች፣ የአድሃሪዎች አመለካከት ነው፤ እንደዚህ ዓይነት ቆሻሻ ይዞ ከኢሕአዴግ ጋር መጠጋት አይገባውም፤ ማንም ሰው ቢሆን የሻገተ አመለካከት ይዞ ከኢሕአዴግ ጋር መጠጋት የለበትም፡፡ ስለዚህ አቶ ልደቱ እንደዚህ ዓይነት ኢሕአዴግ ካገኙ ድርጅታችን ለማጽዳት ይተባበሩን ዘንድ እጠይቅዎታለሁ፤” ብለዋል፡፡

ምንጭ ሪፕርተር

Related Posts

Leave a Comment