የዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 11/2010 አበይት ዜናዎች - Wazema Radio ዋዜማ ሬዲዮ

Daily Ethiopian News, አዳዲስ ዜናዎች።
Forum rules
** When you post a News please include the Source link.
For More Ethiopian News please visit the Home Page
http://ethiopiaforums.com/
selam sew
Leader
Leader
Posts: 558
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

የዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 11/2010 አበይት ዜናዎች - Wazema Radio ዋዜማ ሬዲዮ

Unread post by selam sew » 19 Jul 2018 10:44

የዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 11/2010 አበይት ዜናዎች
https://www.facebook.com/Wazemaradio/

1. ከኃላፊታቸው በተነሱት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንዷለም አድማሴ (ዶ/ር) ምትክ ምክትላቸው የነበሩት ፍሬሕይወት ታምሩ ቦታውን ተረክበዋል፡፡ የድርጅቱ ቺፍ ኦፕሬሽን ኦፊሰር በነበሩት አቶ ኢሳይያስ ዳኘው ቦታ ደግሞ አማረ አሰፋ ተተክተዋል፡፡ በርካታ የመምሪያ ኃላፊዎችን ያሰናበተው ኢትዮ ቴሌኮም በሁለት የተለያዩ ተቋማት እንዲከፈል የተወሰነ ሲሆን፣ በይዞታነት አጥሮ የያዛቸውን ቦታዎች ለመንግስት እንዲያስረክብ መመሪያ ተላልፎለታል፡፡ ድርጅቱ ያሉት ሀብቶች ተጠቃልለው እንዲተመኑ በተወሰነው መሰረት አራት የውጪ አማካሪ ኩባንያዎች ለውድድር መቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡ በሌላ የሹም ሽር ዜና የመንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አርአያ ግርማይ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዲኤታ ሲሆኑ፣ በእሳቸው ምትክ ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር) ተመድበዋል፡፡

2. ከአዲስ አበባ ከንቲባነት የተነሱት ድሪባ ኩማ በአስቴር ማሞ ምትክ የካናዳ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡ በካናዳ አምባሳደርነት ሲሰሩ የቆዩት አስቴር ማሞ ከባለቤታቸው ጋር በአንድ ኤምባሲ መስራት እንደማይገባ ተገልጾ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዝውውር ወደ ሀገር ቢጠሩ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የስንብት ደብዳቤ ተጽፎላቸዋል፡፡ አለማየሁ ተገኑ ደግሞ በሩሲያ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ተመድበዋል፡፡ በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ግሩም አባይ አስቀድሞ በብራሰልስ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደርነት ተሹመዋል፡፡

3. አቶ ሬድዋን ሁሴን በኤርትራ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ተሾሙ። አቶ ሬድዋን በአየርላንድ አምባሳደር ሆነው ሲሰሩ ቆይተዋል። መረጃውን ይፋ ያደረገው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው።

4. የበረራ ቁጥር ET 0312 ቦይንግ 787 ዛሬ ከአዲስ አበባ ተነስቶ አስመራ አውሮፕላን ጣቢያ ሲያርፍ የአበባ እቅፍ በያዙ ኤርትራውያን እንዲሁም በውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልሕ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡ ለ20 ዓመት ተዘግቶ የነበረው የአየር ክልል ከዚህ በኋላ ለመደበኛ በረራ ክፍት ሆኗል፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድም በዛሬው ዕለት ብቻ ሁለት በረራ አድርጓል፡፡ አየር መንገዱ በኤርትራ አየር ክልል አልፎ ወደ መካከለኛው ምስራቅና አውሮፓ መዳረሻዎቹ እንዲበር በመፈቀዱ በሚሊየን ዶላሮች እንዲቆጥብ የሚያስችለው መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወልደ ገብረማርያም ተናግረዋል፡፡ የቀድሞ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ በመሩት የአስመራው ተጓዥ ልዑክ ውስጥ ባለቤታቸው፣ ሚኒስትር ዲኤታ አፈወርቅ ካሱ (ፕሮፌሰር)፣ አርከበ ዑቅባይ፣ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ መካተታቸው ታውቋል፡፡

5. የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ዛሬ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ቁጥርን ይፋ አድርጓል፡፡ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ… ቢያንስ በቀን 1 ዶላር እንዲቆጥቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደረገ ጥሪ መሰረት ነው ፈንዱ የተመሰረተው፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ Ethiopian diasporas trust fund የተከፈተው ሂሳብ ቁጥር 1000255726725 ነው፡፡ ወደፊት ይፋ ይደረጋል በተባለው ድረ ገጽ በመጠቀም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስዊፍት አድራሻን CBETETAA እንዲሁም ሌሎች ከንግድ ባንክ ጋር የሚሰሩ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችን መጠቀም እንደሚቻል ተገልጿል፡፡

6. ዛሬ ማምሻውን ወደ አሜሪካ የሚጓዙትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አባቶች አስታራቂ ልዑካንን ጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ በቢሮዋቸው አነጋግረዋቸዋል፡፡ “የቤተ ክርስቲያኒቱ ሠላም የሀገር ሠላም ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ለሠላም የሚከፈልን ማንኛውም ዋጋ ከፍላችሁ የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት እንዲመለስ ጥረት እንድታደርጉ አደራ እላለሁ” የሚል ማሳሰቢያ ሠጥተዋል፡፡ የዕርቅ ሂደቱ ከመጨረሻው ምዕራፍ መድረሱን የጠቆሙት የሠላምና ዕርቅ ኮሚቴው አባላትም “በሁለቱም በኩል ያሉ አባቶችን በማስማማት በቅርቡ የሠላምና የፍቅር ብስራት ለኢትዮጵያ ይሆናል፤ በኢትዮጵያም ሆነ በአሜሪካ የሚገኙ ብፁዓን አባቶች ላደረጉልን ትብብርና ለሰጡን ቀና ምላሽ ከልብ እናመሰግናለን” ብለዋል፡፡

7. ዛሬ ጧት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ አድርገው ነበር፡፡ ሠራተኞቹ ከአበል፣ የትርፍ ሠዓት ክፍያ፣ ደመወዝ ጭማሪና ከመኖሪያ ቤት ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ያነሱት ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ ዛሬ ሥራ አቁመው የነበረ ሲሆን፣ በጧቱ ክፍለ ጊዜ ቻይናውያን የድርጅቱ ባልደረቦች በተወሰኑ ባቡሮች የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበር ተነግሯል፡፡ ረፋድ ላይ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ኃላፊዎች ከሠራተኞች ጋር ውይይት ካካሄዱ በኋላ የመብት ጥያቄዎቹ እንደሚከበሩ ከስምምነት በመድረሳቸው ሠራተኞቹ ከቀትር በኋላ ሥራ ጀምረዋል፡፡

Source: Wazema Radio ዋዜማ ሬዲዮ Facebook Page
ለሌሎችም ያጋሩ SHARE SHARE

Post Reply

Return to “Ethiopian Daily News .. ኢትዮ ዜናዎች”