የዓርብ ሐምሌ 6/2010 አበይት የሀገር ውስጥ ክስተቶች - Wazema Radio ዋዜማ ሬዲዮ

Daily Ethiopian News, አዳዲስ ዜናዎች።
Forum rules
** When you post a News please include the Source link.
For More Ethiopian News please visit the Home Page
http://ethiopiaforums.com/
selam sew
Leader
Leader
Posts: 560
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

የዓርብ ሐምሌ 6/2010 አበይት የሀገር ውስጥ ክስተቶች - Wazema Radio ዋዜማ ሬዲዮ

Unread post by selam sew » 13 Jul 2018 16:04

የዓርብ ሐምሌ 6/2010 አበይት የሀገር ውስጥ ክስተቶች - Wazema Radio ዋዜማ ሬዲዮ

1.ሽፈራው ሽጉጤ በአምባሳደርነት ተመደቡ፡፡ የግብርና እና አሳ ሀብት ልማት ሚኒስትሩ ሽፈራው ሽጉጤ በሀዋሳ ከተማ ከደረሰው ሁከት ጋር በተያያዘ ከደኢሕዴን ሊቀ መንበርነት መነሳታቸው ይታወሳል፡፡ ከሽፈራው ሽጉጤ በተጨማሪ የአዲስ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩማ እና የኦሮሚያ አፈ ጉባዔ እሸቱ ደሴ እንዲሁም አለማየሁ ተገኑ፣ ያለው አባተ፣ አዛናው ታደሰ፣ ዮናስ ዮሴፍ፣ አብዱልፈታህ አብዱላሂ አምባሳደር ሆነው እንደሚሄዱ ተገልጿል፡፡

2. ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ለሶስት ቀናት የሥራ ጉብኝት ነገ ቅዳሜ ረፋድ አዲስ አበባ ይገባሉ፡፡ ኢሳይያስ ዛሬ በሀገራቸው 31ኛ ዙር የብሔራዊ ውትድርና ሠልጣኞችን በሳዋ ሲያስመርቁ “ነገ የእናንተን እና የመላ ኤርትራ ሕዝብን መልዕክት ይዤ አዲስ አበባ እጓዛለሁ” ብለዋል፡፡ በወጣው ፕሮግራም መሰረት ነገ ለኢሳይያስ በብሔራዊ ቤተ መንግስት ግብዣ ይደረግላቸዋል፡፡ ከቀትር በኋላ ወደ ሀዋሳ ተጉዘው የኢንዱስትሪ ፓርኩን ይጎበኛሉ፡፡ እሁድ ዕለት በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ ንግግር ያደርጋሉ፤ 25 ሺህ ሕዝብ በሚታደምበት በዚሁ አዳራሽ የባሕልና የሙዚቃ ትርዒት ይቀርባል፡፡ ስለ ሠላም የሚዘምሩት አንጋፋዎቹ ማሕሙድ አሕመድና አሊ ቢራ፣ “ሁሉም ቢተባበር”ን የሚያቀርቡት ነዋይ ደበበ፣ ጸጋዬ እሸቱ፣ አረጋኸኝ ወራሽ፤ ሀጫሉ ሁንዴሳ፣ ጸጋዬ ስሜ፣ አብርሀም ገብረመድሕንን ጨምሮ በርካታ ድምጻውያን በብሔራዊ ቴአትር፣ እንዲሁም የባሕል ሙዚቃ ድምጻውያኑ ደግሞ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ልምምድ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ ዛሬ ብሔራዊ ቴአትር ተገኝተው ልምምዱን ተመልክተዋል፡፡

3. “ሕገ መንግስቱ ይከበር” በሚል መሪ መፈክር በነገው ዕለት በመቀሌ ከተማ ሊካሄድ የነበረው ሠልፍ መቅረቱ ተገልጿል፡፡ የመቀሌው ሠልፍ የተሠረዘው… የኤርትራ ልዑካን ኢትዮጵያ ስለሚመጡና በሁለቱ ሀገራት መካከል የተጀመረውን የሠላም ስምምነት ስለሚደግፍ መሆኑን ያብራራው የትግራይ ክልላዊ መንግስት “ለኤርትራ ልዑካን ክብር ሲባል የተሠረዘው ሠልፍ ሌላ ጊዜ ይካሄዳል” ብሏል፡፡ ሌሎች ወገኖች ደግሞ የኢሳይያስ መምጣት በይፋ ከመነገሩ በፊት የመቀሌው ሠልፍ መሰረዙ ይታወቅ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

4. ኤርትራ ለ20 ዓመት ተዘግቶ የቆየ የአዲስ አበባ ኤምባሲዋን እሁድ ዳግም ትከፍታለች፡፡ በደርግ መንግስት የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ወጣቶች ማሕበር (አኢወማ) ጽ/ቤት የነበረውና ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ለኤርትራ ኤምባሲ የተሰጠው ሕንጻ ከ1990 ጦርነት በኋላ በመዘጋቱ ለዓመታት ሙጃ በቅሎበት፣ ዳዋ ወርሶት ቆይቷል፡፡ ላለፉት ሠባት ዓመታት ደግሞ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ቢሮ ሆኖ ያገለግል ነበር፡፡ ከሁለቱ ሀገራት ሠላም ማውረድ በኋላ መስቀል አደባባይ አቅራቢያ የሚገኘው ቅጥረ ግቢና ሕንጻው በአፋጣኝ ታድሶ እሁድ በኤርትራ ኤምባሲነት እንደገና ይከፈታል፡፡

5. የአዲስ አበባ ምክር ቤት ከኃላፊነት የሚነሱ ኃላፊዎችን ጥቅማ ጥቅሞች የሚያስከብር አዋጅ አጽድቋል፡፡ በዚህም መሰረት ኃላፊዎቹ ሥራ ሲለቁ ነጻ የመኖሪያ ቤት፣ የሕክምናና የገንዘብ ክፍያ ያገኛሉ፡፡ በአዋጁ የተጠቀሱ አንዳንድ ጥቅማጥቅሞች የሀገሪቱን አቅም ያገናዘቡ አይደሉም በሚል ከምክር ቤት አባላት ተቃውሞ ቢቀርብም ጸድቀዋል፡፡ ሥራ ሲለቁ ይሕን መብት የሚያገኙት… ዳኞች፣ የከተማ ምክር ቤቱ አፈ ጉባዔዎች፣ ጸሐፊዎች፣ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና የክፍለ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባዔዎች ናቸው፡፡

6. በዛሬው ዕለት በቂሊንጦ የሚገኙ እስረኞች በፖሊስ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ታሳሪዎቹ “መንግስት ያደረገው ምሕረት ለእኛም ይገባል” የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ከኦነግና ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር በተያያዘ የተከሰሱ በርካታዎች አሁንም በእስር ይገኛሉ ተብሏል፤ ቤተሰብ ለእስረኞች ምግብ እንዳይሰጥ ተከልክሏል፡፡ እስረኞችን ሊጠይቁ የሄዱ ቤተሰቦችና ሁናቴውን ለመቃኘት በአካባቢው የተገኙ ጋዜጠኞች በወሕኒ እና አድማ በታኝ ፖሊስ ማዋከብ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ እስረኞች በጠባቂ ፖሊሶች የሰብዓዊ መብት ረገጣ ሲፈጸምባቸው እንደነበር የመንግስት መገናኛ ብዙሀን ከሰሞኑ ሲዘግቡ ሠንብተዋል፡፡

7. በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ በከፍተኛው አመራር ደረጃ የብሔር ብሔረሰብ ተዋፅኦ ተመጣጣኝ አለመሆኑን ምክትል ኤታማዦር ሹሙ ጄነራል ብርሀኑ ጁላ ገልጸዋል። ጄነራል ብርሃኑ ከ"አዲስ ዘመን" ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ "በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ በከፍተኛ አመራር ደረጃ የብሔር ተዋፅኦው ችግር አለበት" ብለዋል፡፡
በሰራዊቱ ውስጥ የብሔር ተዋፅኦው ብዙ ጊዜ ተመጣጥኗል ተብሎ ሲገለፅ እንደነበር ያስታወሱት ጀኔራሉ ከክፍለ ጦር አመራሮች በላይ የተመጣጠነ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ማመጣጠኑን ከግንዛቤ ያስገባ የሪፎርም ስራ እየተሰራ መሆኑንም ጄኔራሉ ተናግረዋል፡፡

SHARE SHARE SHARE
Source: Wazema Radio ዋዜማ ሬዲዮ Facebook Page

Post Reply

Return to “Ethiopian Daily News .. ኢትዮ ዜናዎች”