ከማን አንሼ - በስምአት ተረፈ

Life, Health, Religion, Social, General Question
Forum rules
No cursing, bad language and offend other users !
No pornographic images or links!
This forum monitored regularly. We will BAN users without warning for not obeying rules.
እባክዎ የፎረሙን ህጎች ያክብሩ::
User avatar
zeru
Leader
Leader
Posts: 952
Joined: 19 Aug 2009 17:01
Contact:

ከማን አንሼ - በስምአት ተረፈ

Unread post by zeru » 23 Feb 2016 13:10

ከማን አንሼ በስምአት ተረፈ

እናታችን ኢትዮጵያ በነፃነትዋ ብዙኃን ብሔረሰቦቿን
በሉዓላዊነቷ በሦስቱ ቀለማት ሰንደቅ ዓላማዋ ጥላ ሥር
አቅፋ ይዛለች:: በኅብረ ባህል ከማሸብረቅም ባለፈ ከአፍሪካ
አኅጉር የራስዋ ጽሑፉ ያላትና ከሰማንያ ቋንቋዎች
በላይ ባለቤት ነች:: ከዘመናዊው ጎዳና ከመግባቷ በፊት
በጥንታዊው የአብነት (የቆሎ) ትምህርት ቤት አገር
በቀል ትምህርት በአገር ፊደል የጀመረች፣ በጥቁር
ዓለም የራስዋ ፊደል ከነአኅዙ ያላትና የቀን አቆጣጠርና
ወራትን አጣምራ የያዘች ድንቅ አገር ብትኖር ኢትዮጵያ
ናት:: እንዲህ በዘርፈ ብዙነት ከሦስት ሺሕ ዓመታት
አስቆጥራለች:: ለዚሁም እማኞችዋ በዓለም መዝገብ
የሰፈሩት ናቸው::
ወደ ሐሳቤ እንደ መንደርደረያ ለመግባት ዛሬ
ኢትዮጵያችን በዘመናዊው የትምህርት መስክ በተለያየ
ደረጃ ትምህርቱ እየተሰጠ፣ ባለሙያዎችም በየዘርፉ
እየበቀሉ ነው:: እጅግ ብዙ ወጣቶች በዕውቀት ማፍለቂያ
ያሉን መሆኑ እሰዬው ስንል በምሥጋና ነው:: ከዕውቀት
ማዕዱ ተቀድሰውና አስመስክረው ወጥተው በአገሪቱ
ውስጥ በየተመደቡበት ሥፍራም እያገለገሉ ይገኛሉ::
ከእነዚህ መካከል በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በጋዜጣ፣
በራዲዮ፣ በቴሌቪዥን በመንግሥታዊም ሆነ በግላዊ
ተቋም ውስጥ የተሰማሩት ግንኙነታቸው በዋናነት
ከቋንቋ ጋር የተያያዘ ነው:: ይሁን እንጂ መገናኛ
ብዙኃኑ ከባለሙያዎቹ ጋር መበርከት በሥራዎቻቸውም
አገራዊውን ቋንቋና ሀብት ላይ ከመጠቀም ይልቅ፣
በቋንቋዎቻችን የውጭ ባዕድ ቃል በመደባለቅ አድማጭ
ተመልካችን ሲያደናግሩ ይታያል:: እንደምንታዘበው
በሬዲዮና በቴሌቪዥን ከሚቀርቡት መካከል እያማጠ
ኧኧ እያለ ቋንቋውን ቃል ያጣለት ይመስል የፈረንጅ
ቃል አደባልቆ የዕውቀት መለኪያ ይመስል ሲቋፍ
ይሰማል:: ለቀድሞዎቹ ጋዜጠኞች ምጋና ይግባቸውና
ቃለ መጠይቅ የሚደረግለት ሰው ማን ይሁን ማን አንድ
ቃለ ባዕድ ካስገባ ‹‹አሁን የተናገሩት ምን ማለት ፈልገው
ነው?›› ሞቅ ደመቅ ብለው ሲያፋጥጡት ይቅርታ ብሎ
አማርኛ ሲያገኝለት ታዲያ አማርኛ አለው አይደል?
ይሉና ንግግሩ ይቀጥላል:: ያኔ በንጉሡ ዘመንና ጥቂት
ጊዜ ያህል በወታደሩ አገዛዝ አልከፋም ነበር::
በአሁን ጊዜ የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ እየተበላሸ ነው::
ምሳሌ ‹‹መቼ ትመጣለክ? እንደምን ነክ፣ ደህና ነክ፣
ሰጥቶካል፣ ምሳዬን በላው...›› እነዚህንና ሌሎችም
ግድፈቶች ቤተሰብ ልጆቻቸው የተበላሸ አነጋገር ሲያመጡ
እንደመደሰቻ ዘይቤ ከመቀበል ይልቅ፣ ሳያርሟቸው ችላ
ይሏቸዋል:: ይህ ከትምህርት ቤት ጀምሮ መስተካከል
ሲገባው የቃሉን ግስ ርቢ ማን አውቆት? ከመምህሩ
መካከልም ራሱ ተመሳሳይ ቋንቋ ስለሚናገር ማ ማንን
ያርም ከተራ ንግግር አልፎ በጽሑፎች ላይ እየወጣ
ለንባብ እየበቃ ነው:: ወደ እንግሊዝኛው ስንመጣም
አዲስ አበባ “Addis Abeba” መባል ሲገባው “Ababa”
(አባባ) ተለውጦ ዝንተ ዓለም ተቀምጦአል:: አንዳንድ
መሥሪያ ቤቶች ለውጡን ተገንዝበው እያስተካከሉ
ቢሆንም:: እኛ በአገራችን ውስጥ “Ts” እንደ ፀ (ፀሐይ)
በእንግሊዝኛ ለመጻፍ እንጠቅምበታለን:: ኢትዮጵያ
ለማለት “ETHIOPIA” ተብሎ ይጻፋል:: ነገር ግን ኤች
(H) የተባለችው ዋጋ የላትም:: ይህ አነጋገር ከዓረቦች
አሱቢያ እንደሚሉት ይመስላል:: መሆን የነበረበት
“ETYOPYA” ነው:: በዓለም ላይ ብዙ አገሮች የራሳቸውን
ጥፋት እርምት እያደረጉ ነው:: ለምሳሌ ፔኪንግ ወደ
ቤጂንግ ተለውጧል:: የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አዲሱ
መጠሪያው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ (EBC) ይለናል::
ትርጉም በቋንቋችን መቼ ጠፋ? ብሮድ ማለት ሰፊ
ገላጣ፣ ስቲንግ ማለት ማሠራጨትና በስሚንቶ መሰል
ቁስ አንድን ነገር ማጣበቅ ማለት ነው:: እዚህ ላይ
ቃለ ትርጉም ቢጠፋ እንኳን ከሌሎች የአገራችን ውብ
ቋንቋዎች ለምን አንወስድም? ይታሰብበት:: ‹‹ኢትዮ
ታለንት›› ወይም ‹‹አይዶል ሾው›› ይባልልናል::
ለማን? ማስታወቂያ ሲነገር እንደምንሰማው ፍራሹም
ጫማውም ካንጋሮ እየተባለ ነው ‹‹Kangaroo››
(ካንጋሩ) መሆኑ ቀርቶ ‹‹Kangaro (ካንጋሮ) ሆነ::
‹‹Ceritificate›› (ሰርቲፊኬት) የምስክር ወረቀት ማስረጃ
ነው:: Certeficate (ሰርተፊኬት) ሆኖ አረፈ::
‹‹ተመልከት ዓላማህን ተከተል አለቃህን››
እንደተባለው ዘወትር ‹‹ስትራቴጂና ትራንስፎርሜሽን››
የንግግር መክፈቻ ሆነዋል:: ስትራቴጂ የጦር የውትድርና
ቃል ሲሆን ሥልታዊ ወይም ጊዜያዊ የረቀቀ አመራር
ማለት ሲሆን፣ ትራንስፎርሜሽን ከአንድ ነባራዊ ሁኔታ
ወደ ቀጣይ መሻሻል ለውጥ ወይም ዕድገት ነው:: መልዕክቱ
ለነማን ኢትዮጵያውያን ነው የሚተላለፈው ብሎ ማሰብ
ያሻል:: እኔ እንደ ግለሰብ ዜጋ ክቡር ፕሬዚዳንት ወይም
ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር ሲያደርጉ ስለአገሪቱ ሕዝብ
ጉዳይ ምን አዲስ ነገር አለ ብዬ አዳምጣለሁ እንጂ፣
ሌሎቹ በባዕድ ቋንቋ ሲዘላብዱ ያቅለሸልሸኝና ጆሮዬም
ይጠየፋል:: እኔን የሚገርመኝ ለመሆኑ በቴሌቪዥንም
ይሁን በሬዲዮ ለቃለ መጠይቅ የሚቀርበውና አቅራቢው
የአማርኛ ቋንቋ ጊዜ ስለሆነ እባክዎ ይቅርታ በንግግርዎ
ጣልቃ ባዕድ ቃል እንዳይጠቀሙ ማለት ምኑ ነው
ነውሩ? አንዳንዶች የጽሑፍና የቃል ማስታወቂያዎች
አወቅን አሳመርን እያሉ የፊደሎችን መልክ ቅርፃቸውን
ሲቀይሩ ይታያሉ:: ለምሳሌ ‹‹World Book Series››
የሚለውን ‹‹Serious›› ተብሎ ሲነገር ሰምተናል::
ከፍሎ የሚጽፋቸውም ይሁን ይነገርልኝ ሲባል ሁሉንም
የሚያስወቅስ ነው::
ሌላው ትልቁ ግድፈት የስፖርት ዜና የሚያቀርቡ
ስለኳስ ጨዋታ ትንተና ሲሰጡ ‹‹ድሪብል
በማድረግ፣ ሴንተር አድርጎ፣ ፔናልቲ፣ አግሬሲብሊ፣
ፐርፎርማንስ...›› እያሉ ይጠቀማሉ:: ኧረ ስንቱ ምሁር
ለመሆን የሚሞክሩት ለሬዲዮ ክፍለ ጊዜ ሳይሆን
ዕወቁልኝ ስሙልኝ ችሎታዬን እንደ ማለት ነው:: አንድ
የሬዲዮ ሥርጭት ባለሙያ አንድ አዲስ ቃል ከተናገረ
በቅብብሎሽ በሁሉም ጣቢያዎች ትሰሙታላችሁ::
‹‹ስፖንሰር አደረገልን›› ለሚለው ቃል ይህ ቃል
በግርድፍ ትርጉሙ ደጐመ፣ ቸረ፣ መፀወተ ማለት
ሲቻል አማርኛ ሊሆን የተቃረበ ይመስላል:: በቅርብ
ቀን አንዲት የሕፃናት ዶክተር ስለሕፃናት ሕመምና
ፈውስ በሬዲዮ ሲናገሩ ጠቅላላውን በእንግሊዝኛና
ጥቂት በአማርኛ ነበር የሚጠቀሙት:: መልዕክታቸውም
እንግሊዝኛ ቋንቋ ለሚናገሩ እንጂ የገጠሯን እናት
ወይም ሴቶች ያካተተ አልነበረም:: እኔን የገረመኝ
የጋዜጠኛው ዝምታ ነው:: ለምን እንደማያቋርጣቸው
አይገባኝም:: እዚህ አገር የውጭ አገር ሰዎች ጥርት
ያለ አማርኛ ሲናገሩ እጅግ ያስደንቃል:: እኛ የናቅነውን
ይህ አማርኛ አናባቢ የማይፈልግ የራሱ ቀለም ያለው፣
በሰዋስው የሠለጠነ የቀድሞ ጠቢባን ኢትዮጵያውያን
ሳይንቲስቶች ወይም አርቲስቶች፣ ተመራማሪዎች ያለ
እንከን አዘጋጅተው ያስቀመጡልንን ቅርስ ማጥፋት
አገርንና ወገንን የመበደል ወንጀል ነው::
ከምሁራን አድናቆት ጥቂቱን
ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን ‹‹ይህን አማርኛ
ቋንቋ የሚያህል የለም:: እዚህ ደረጃ በስንት መከራ
አደረስነው፤›› ሲሉ፣ ደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር
በበኩሉ ‹‹አማርኛ ይህ ቀረሽ የማይባል ድንቅና ምቹ
ቋንቋ ነው፤›› ብሏል:: ከአገራችን አንዳንድ ጋዜጠኞች
ጋር የኤርትራው ጋዜጠኛ ጎይቶም ቢሆንን ሳነፃፅር
ክፍተቱ ይታየኛል:: ከላይ ስሙን የጠቀስኩት በሬዲዮ
ጣቢያቸው በአማርኛ ክፍል ሥርጭታቸው ከእሱ ድንቅ
አማርኛ እናዳምጥ ነበር:: የኛዎቹ የቅናት መንፈስ
ለምን አይሰማቸውም? በከበሬታ ቃል ክቡር ሲሉ
ይቆዩና በመደምደሚያው ‹‹እንዲህ ሲሉ ተናግሯል::
አስጠንቅቋል...›› ቃሉን አልባሌ ያደርጉታል::
አንድና ብዙን ይቀላቅሉታል:: እርማቱ ተናግረዋል፣
አስጠንቅቀዋል ነው:: በብዙ ቁጥር መባል የነበረበት
በነጠላ ያደርጉታል::
እርስ በርስ መተራረም የለም ወይ? በአንድ ወቅት
በምክር ቤት ውስጥ ‹‹አካውንተቢሊቲ፣ ክሬዲቢሊቲ››
የሚባሉት ቃላት የንግግር ሽክርክሪት ነበሩ:: አንድ
የሬዲዮ ዘገባ ለሕዝብ ከመቅረቡ በፊት ያለውን
ግድፈት በቅድሚያ የሚፈትሽ ቃፊር የላቸውም ወይ?
ከየትም ሮጦ መጥቶ ያልታረመ መጽሐፍ የሚነበብ
ይመስላል:: ኃላፊነትና ባለቤትነት እምኑ ላይ ነው?
‹‹ን›› የተባለችው ለተጠቃሽ ተሳቢነት የምታገለግለው
ፊደል አለመኖር መልዕክቱን ያዛባዋል:: ለምሳሌ ፖሊሱ
ወንጀለኛው ገደለው ቢባል ማን ሟች ማን ገዳይ
እንደሆነ አይታወቅም:: ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር
ማለቱ ከላይ ከተጻፈው ወቀሳ ጋር ተደምሮ የአገርን
ቋንቋዎች በመበከል ምኑን ትኑር እንላለን:: ከጥቂት
ዓመታት በኋላ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ቃሉ የባቢሎን
ዘመን እናዳናደርገው ያሰጋል::
መንግሥት የመገናኛ ብዙኃንን በሕዝብና በአገር
ላይ ካለው አንፃር ኃላፊነትና ተወቃሽነት መኖሩን
በማነፀር የሚመለከተው ክፍል እነዚህን ተጠቃሽ አካላት
እንዲቆጣጠራቸውና እንዲገስጻቸው፣ በዚህ ጽሑፍ
ላይ አቤቱታና አደራ ሳቀርብ በከፍተኛ ምሬት ነው::
በመደምደሚያዬ የጥላሁን ገሠሠን ውበትሽ ይደነቃል
የሚለውን ዘፈን ጋብዤአችሁ ነው::

Post Reply

Return to “Ethio General .... ኢትዮ ማህበረሰባዊ ርዕሶች”