ኢትዮጵያ የቋንቋና ፊደል ድንጋጌ ባለማውጣቷ በዘፈቀደ እየተጻፈ መሆኑ ተጠቆመ

ግጥሞች፣ታሪኮች፣ፎቶዎች፣ሙዚቃዎች
Poems,Short stories, graphics,pictures,musics,Technology
ኦሽንoc
Leader
Leader
Posts: 1129
Joined: 07 Aug 2009 14:20
Contact:

ኢትዮጵያ የቋንቋና ፊደል ድንጋጌ ባለማውጣቷ በዘፈቀደ እየተጻፈ መሆኑ ተጠቆመ

Unread post by ኦሽንoc » 27 May 2011 14:32

ኢትዮጵያ የጽሕፈት ጥበብ ባለቤት ከኾነች ሦስት ሺሕ ዓመታት ብታስቆጥርም እንደሌሎች አገሮች እስካሁን ለቋንቋዎቿና ፊደሏ ድንጋጌ ባለማውጣቷ በዘፈቀደ እየተጻፈ መሆኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁሩ አስታወቁ፡፡

የሥነ ቋንቋ ምሁሩ ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ ባለፈው ሳምንት በሻማ ቡክስ አማካይነት ካስመረቋቸው ሁለት መጻሕፍት አንዱ በኾነው "የአማርኛን ሞክሼን ሆሄያት ጠንቅቆ ያለመጻፍ ችግርና መፍትሔ" በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንዳስታወቁት፣ ኢትዮጵያ የጽሕፈት ጥበብ ባለቤት የሆነችው ከክርስቶስ ልደት ከ1000 ዓመት ገደማ በፊት ቢሆንም፣ ከሷ በኋላ የዚህ ጥበብ ባለቤት የሆኑ ብዙ አገሮች ለቋንቋቸውና ለፊደላቸው የማያወላውል ድንጋጌ ስላወጡለት ያወጡትን ድንጋጌ አክብረው ይሠሩበታል፤ እኛ ግን እስካሁን ድረስ እንዲህ ያለን ሥርዓት ለመደንገግ ሳናስብበት ስለቀረን በዘፈቀደ እንጽፋለን፡፡ ሌሎችም እንደኛው በዘፈቀደ የጻፉትን ቅር ሳይለን እናነባለን፡፡

ከዚህ በፊት ለዚህ ጉዳይ አትኩሮት የሰጠ አካል ባለመኖሩና እንዲሁም መመርያም ስለሌለ ማንም እንዳሻው አድርጎ ቢጽፍ የሚወቅሰውና የሚከሰው የለም ያሉት ዶ/ር አምሳሉ፣ ይህ ሁኔታ በአማርኛ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን በግእዝም ቋንቋ እየተለመደ መሔዱን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቋንቋዎች መርሐ ልሳን [ካዴሚ] በ1973 ዓ.ም. ካወጣው የአጻጻፍ ሥርዓት ውሳኔ በስተቀር ሌላ ወሳኝ ጥናት ባለመደረጉ፣ ለዚህ ጉዳይ ተጠያቂ ሊሆን የሚችሉ መምህራንንም ስለዚህ ጉዳይ ሆን ብሎ ያስተማራቸው ሰው ባለመኖሩ እነሱ ራሳቸው በዘፈቀደ ስለሚጽፉ ተማሪዎቻቸውም የነሱን ፈለግ በመከተል በዘፈቀደ ይጽፋሉ፤ የሚሉት ዶ/ር አምሳሉ፣ አንዳንድ ወገኖች ሞክሼ ሆሄያት ከፊደል ገበታው እንዳይወገዱ አጥብቀው ይከራከራሉ፡፡ ዋናው አቋማቸውም፣ “ከአባቶቻቸን ተያይዞ የመጣልንን ፊደል አክብረን እንደ ታሪካዊ ቅርሳችን በማቆየት ፋንታ ይህን እንጣል፤ ያኛውን እናቆይ፣ ማለት በረጅሙ የሥልጣኔ ታሪካችን ላይ ይቅርታ የማይደረግለት ትልቅ በደል እንደ መሥራት የሚቆጠር ነው” የሚል ነው ብለዋል፡፡

ምሁሩ በመፍትሔነት ባቀረቡት ሐሳብም፣ የሁለቱንም ወገን ፍላጎት ለማመቻቸት የሚከተለውን መንገድ መያዝና አማራጭ የሌለውን መንገድ መከተል እንደሚያስፈልግ፣ ከሞክሼ ሆሄያት ውስጥ በአንዱ ብቻ መጻፍ ያለበት አንድ ቃል በአንድ ዓይነት የአጻጻፍ መንገድ ብቻ መጻፍ አለበት የሚለውንም ጠቅሰዋል፡፡ አያይዘውም፣ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ዕውቀቱ ያላቸው ሰዎች አንድ ቃል በእነዚህ ፊደላት ብቻ መጻፍ አለበት ብለው፤ የቃላት መድበል ሲያዘጋጁልን ያንን ተከትለን መጻፍ እንችላለን፡፡ ከዚያ ውጭ ከጻፍን ግን ስሕተት እንደሠራን ስለሚቆጠርብን ጠንቅቀን እንጽፋለን ማለት ነው በማለት አጽንዖት ሰጥተውበታል፡፡

ሻማ ቡክስ ያሳተመው ሁለተኛው የዶ/ር አምሳሉ መጽሐፍ “ግዕዝ መማሪያ መጽሐፍ Ge’ez Text book” ነው፡፡ የግእዝ መማርያ መጽሐፉ 22 ምዕራፎች ከነመድበለ ቃላቱ ተካትቶበት ይገኛል፡፡ በሦስተኛው ክፍል በመጽሐፉ ውስጥ ላገለገሉት የግእዝ ቃላት በፊደል ተራው መሠረት ከእንግሊዝኛ አቻቸው ጋር ቀርበዋል፡፡

መልመጃ ምንባባትንም ለተግባራዊ ትምህርት ይረዳ ዘንድ ከተለያዩ ጥንታውያን መጻሕፍት የተውጣጡ ተካተውበትል፡፡ በምሳሌነት ከሚጠቀሱት የአፄ ዓምደ ጽዮን ዜና መዋዕል፣ መጽሐፈ ፈላስፋ ጠቢባን ይገኙበታል፡፡

መጽሐፉ በመግቢያው ስለግእዝ ቋንቋ መዝገበ ቃላት ታሪክም ያወጋል፡፡ በተለይ በአውሮጳ በ17ኛው ምእት ዓመት በሮም የታተመው የጄ.ዌመርስ፣ የግእዝ-ላቲን (1638) መዝገበ ቃላት የመዠመርያው ነው፡፡ የላቲን-ግእዝ መርኆ (ኢንዴክስ) አለው፡፡ በ1661 በሎንዶን የታተመው የሒዮብ ሉዶልፍ ተመሳሳይ መዝገበ ቃላትም ለኢትዮጵያ ጥናት አዲስ ምዕራፍ መክፈቱ ተጠቅሶበታል፡፡ በኢትዮጵያውያን ሊቃውንትም የግእዝ ሰዋስውና ግእዝ-አማርኛ መዝገበ ቃላት በየዘመኑ መዘጋጀታቸውን፣ ከነዚህም በመነሻነት አለቃ ታየ በምንኵሉ በ1889 ያሳተሙት “መጽሐፈ ሰዋስው”፣ በ1948 በአለቃ ደስታ ተክለወልድ የታተመው የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ “መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ግእዝ-አማርኛ መዝገበ ቃላት ይገኙበታል፡፡


በሔኖክ ያሬድ
http://www.ethiopianreporter.com/life-art-culture

Post Reply

Return to “Ethio Art and Culture..ኢትዮ ጥበብ ፤ስነ ጽሁፍ ፤”