ለታላቁ ሽልማት የበቃው የሚሌኒየሙ ሥነ ጥበብ

ግጥሞች፣ታሪኮች፣ፎቶዎች፣ሙዚቃዎች
Poems,Short stories, graphics,pictures,musics,Technology
User avatar
morefun
Leader
Leader
Posts: 152
Joined: 06 Sep 2009 01:52
Contact:

ለታላቁ ሽልማት የበቃው የሚሌኒየሙ ሥነ ጥበብ

Unread post by morefun » 06 Oct 2009 01:33

Image

ኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ መፍለቂያ አውድማ ለመሆኗ ድርሳናቷ ይመሰክራሉ፡፡ በአክሱም ዘመነ መንግሥት የተተከሉት የሥልጣኔ ጮራዎች፣ ሐውልቶቹና የያሬድ ወደር የለሽ የዜማ ድርሰት፣ የረቀቀ የላሊበላ ውቅር ሕንፃ ጥበብና በየዘመኑ የተነሱ ፀሐፍትና ሰዓሊያን ሁሉም የማይነጥፍ አሻራቸውን ጥለው አልፈዋል፡፡ አንዴ እያበበ ሌላ ጊዜ ደግሞ እየከሰመ፤ አንዴ እያደገ ሌላ ጊዜ ደግሞ እየወረደ ኪነ ጥበብ እዚህ ደርሷል፡፡ ብዙ ተስሏል፤ ብዙ ተፅፏል፤ ብዙ ተብሏል፤ ብዙ ተገጥሟል፤ ብዙ ተለፍቷል፤ ብዙ አስደምሟል፤ አስገርሟል የኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ፡፡

ኪነ ጥበብ ጥረት ይጠይቃል፣ ልፋት ይፈልጋል፣ ያደክማል፣ ተመስጦ ይሻል፣ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ በአንድ ጀምበር ተወጥኖ በአንድ ጀምበር አያልቅም፡፡ ነገን ይሻል፡፡ ወዲያ አሻግሮ ያያል፡፡ ውጤታማነትን ይናፍቃል፡፡ የእድሜ ልክ ሂደት ይሻል፡፡ በዚህ ማለፍ ያስፈልጋል፡፡ ሳይታክቱ መሥራት፣ መሣል፣ መፃፍ፣ መዝፈን፣ ዜማ ማፍለቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ብቻ ሁሉም ትዕግሥት ይላል፡፡ ጥንካሬን ጉዞን ይጠይቃል፡፡

የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ረጅሙን ርቀት ገና በወጣትነት ዕድሜአቸው አሐዱ ብለው ጀመሩ፡፡ ዛሬ የእድሜ ልክ ክብር/ታላቅ ሰው ተባሉ፡፡ የአርቲስቱ ጥበብ በቃላት ብቻ አይገለጽም፡፡ ሥራቸውን በማየት ብቻ ማጠቃለልም መገምገምም አይቻልም፡፡ በአርምሞ መደመም፣ ማድነቅ፣ በኩራት በኢትዮጵያዊው ጠቢብ የተሰሩ ሥራዎች ማለት ብቻ፡፡ ለዚህ ጥበባዊ ሥራ የተፈጠሩ ሰው፣ በቀለም ብሩሻቸው ብዙ የተናገሩ፣ ዓለምን የዳሰሱ፣ ታሪክን የተረኩ፣ ማንንነትን የገለፁ፣ ኢትዮጵያን ያሸበረቁ፣ የፈጠራ ሰው በርግጥ ታላቅ ሠዓሊ ማለት፡፡

የኢትዮጵያን ሚሌኒየም በዓል ምክንያት በማድረግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ሦስት ኢትዮጵያንና አፍሪካን የሚወክለ አዳዲስ የሥነ ጥበብ ሥራዎች ለወርልድ ፎረም ፌዴሬሽን በዋሽንግተን ዲሲ ከሰኔ 22 እስከ ሰኔ 27 ቀን 2001 ዓ.ም. ባዘጋጀው ኢንተርናሽናል ዐውደ ርዕይ ላይ በማቅረብ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እጅግ ታላቅ አርቲስት በመባል ከተመረጡት አንድ ሺ የተለያዩ ሰዎች መካከል የምርጦች ምርጥ “ዘ ግሬተስት ማን” በመባል ለሽልማት በቅተዋል፡፡

ሽልማቱ በባራክ ኦባማ የምርጫ ዘመን የተከናወነ በመሆኑ ታሪካዊነቱ ከፍ ያለ ነው ተብሏል፡፡ ለዚህ ታላቅ ክብር መብቃታቸውን ምክንያት በማድረግ በቤቲ አድቨርታይዝ አማካይነት በራሳቸው መኖሪያ “ቪላ አልፋ” ባለፈው ረቡዕ ነሐሴ 20 ቀን 2001 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ስለ ሥዕሎቻቸው ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡ የሽልማቱን ሥነ ሥርዓት በሲዲም ጭምር በማቅረብ ገልጸዋል፡፡

በሜትር አርቲስት አፈወርቅ አገላለጽ የመጀመሪያው ሥዕል ሦስተኛውን የኢትዮጵያ ሚሌኒየም በማስመልከት በአዲስ አበባ ከተማ ትልቅ አደባባይ ላይ የሚያርፍ የሐውልትና የመስታወት ሥራ ነው፡፡ አንድ ትልቅ በር ያለው ይህ ሐውልት፣ ምሳሌነቱም ከበሩ ወደ ውስጥ ያለፈው ዘመን፣ ከበሩ ወደ ውጭ ደግሞ ገደቡ እስከ ሰማይ የሆነ መጪውን ጊዜ 3ኛውን ሚሌኒየም የሚያሳይ ነው፡፡ የበሩ ቅርፅ የሚሰራው በኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎቹ ያሉ ታሪካዊ እሴቶች በሚወክሉ ቅርሶች ይሆናል፡፡ በዙሪያው ስድስት ሐውልቶች ይኖሩታል፡፡ ሁሉም የየራሳቸው የሆነ ተምሳሌታዊ ፍቺ አላቸው፡፡ መፃኢ ዘመንን ይወክላሉ፡፡ ተስፋ ሰንቀው ከ2ኛ ወደ 3ኛ ሚሌኒየም ይሻገራሉ፡፡ አንድነትን ይሰብካሉ፡፡ የአስተሳሰብ አድማስን ያሳያሉ፡፡ ከሁሉም ጐልቶ የሚታየው የአክሱም ሐውልትም ለወጣቱ፣ ታሪክ እንዲህ ነው ወይም እንዲህ ነበር ይላል፡፡

ሁለተኛው ሥዕል የአክሱም ሐውልት ከጣሊያን ወደ ኢትዮጵያ መመለስን የሚያመላክት በአድዋ ተራሮችና በአክሱም መካከል አደባባይ ላይ የሚሰራ ሐውልት የሚያሳይ ዲዛይን ነው፡፡ ዱሮ በልጅነታቸው በሮም አደባባይ የተተከለው የአክሱም ሐውልት እዚያ ተተክሎ መኖሩ የቆጫቸው አርቲስቱ፣ መመለሱን ሁል ጊዜ ይናፍቁ ነበርና የዚህን መልካም ዜና ሲሰሙ አዕምሮአቸውንና ብሩሻቸውን አገናኙ፡፡ ስለ አክሱም ሐውልቱ በቡሩሻቸው ተናገሩ፡፡ ሐውልቱ ሁለት እጆች አሉት፤ በአንድ እጁ የኢትዮጵያን የፈጠራ ኃይል በሌላኛው እጁ ጊዜ እየደነሰ የሚያሳየው ይህ ሥራቸው መሀሉ ላይ የራሱን አክሱም ሐውልቱን አስፍሮ በበሩ ፀሐይስ ትወጣና ስትጠልቅ ያሳያል፡፡ ከኋላም በዐድዋ ተራራ ደምቋል፡፡ ሁሉም ነገር ተምሳሌታዊ፣ ታሪካዊ እና እውነታዊ ትርጉም ያዘሉ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ የዘመነ የሀ ጥንታዊውን የ፣መ፣ን ፊደል ይዛ የአክሱም ሐውልት ተመልሻለሁ ትላለች፡፡ ወገቡን የያዘ አንድ የዘመኑ ትውልድ በኩራት ይኸ ሐውልት በእኔ ዘመን ተመልሷል፡፡ ይኸን ተመልክቻለሁ ይላል፡፡

ዐድዋ ብዙ ታሪክ የተፈፀመበት ዐውድ ነው፡፡ የአንድ ወገን የበላይነት ሂደት የታየበት ነው፡፡ የጥቁሮች ፈርጥ ነው፡፡ የአፍሪካውያን ኩራት ነው፡፡ ዐድዋ የዓለም ታሪክ ነው፡፡ ለረዥም ጊዜ የነበረን የዓለም አካሄድ አቅጣጫን የለወጠ፣ የነጮች የበላይነት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰበረበት የለውጥ ታሪክ ነው፡፡ ዐድዋ ብዙ ነው፡፡ ተገጥሞለታል፣ ተዘፍኖለታል፣ ተዘምሮለታል፣ ተጨብጭቦለታል፡፡

አንድ ሐውልት የድርጊት ገላጭና ስሜት ያለው (ዘ ኢሞሽን ኦፍ ዘ አክሽን) መሆን አለበት ይላሉ የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ፡፡ ጥረቱ ቢመሰገንም ዐድዋ ብሎ በእንግሊዝኛ ጽፎ ማስቀመጥ በጥበባዊ እይታ ተቀባይነት እንደሌለው ይገልጻሉ፡፡ ዐድዋ ትልቅ የኢትዮጵያ ጀብዱ የተፈጸመበት ቦታ የታሪክ ቋት ነውና፡፡

Image

ሦስተኛው ሥዕል አፍሪካውያን የኢትዮጵያን ሚሌኒየም የራሳቸው ሚሌኒየም እንደሆነ አድርገው መቀበላቸውን ለማጠየቅ የተሠራ ሲሆን ይህም በአኅጉሪቱ ካሉት አገሮች በአንዱ አደባባይ ላይ ሊሠራ የሚችል፣ የአፍሪካን ባህላዊ ትስስርንና አንድነትን የሚያመላክት ዲዛይን ነው፡፡ ከጥንት ሉሲ ጀምሮ፣ የአክሱም ሐውልትን ይዞ ልዩ ልዩ የአፍሪካን ሥዕሎች አካትቶ ከእስክንድሪያ እስከ ኬፕ ኦፍ ጉድ ኦፕ ደቡብ አፍሪካ፣ ከሶማሊያ እስከ ሴኔጋልና ጊኒ ያሉትን የአፍሪካ ባህልን ያንፀባርቃል፡፡ የሳባ፣ ግእዝና፣ ዓረብኛ ጽሑፍ ያካተተ፣ የአፍሪካ አንድነት መመሥረትን የሚያመለክት የአፍሪካን የመጀመሪያውን ቻርተር ያቀፈ ሐውልት ነው፡፡

እኚህ ታላቅ ሠው ሦስቱ ከላይ በተዘረዘሩት በሥዕል መልክ የቀረቡት ሥራዎቻቸው ከአሜሪካን ባዮግራፊካል ኢኒስቲትዩትና ከዩናይትድ ኪንግ ደም ኢንተርናሽናል ባዮግራፊካል ሴንተር እጅግ ታላቅ አርቲስት በመባል ሽልማት አስገኝቶላቸዋል፡፡

ይህን ሽልማታቸውን ተከትሎ አንቱ የተባሉና ለሥነ ጥበብ ቅርበት ያላቸው የአሜሪካ ማህበረሰብ አባላት ለሜትር አርቲስት አፈወርቅ የእንኳን ደስ አልዎት ሥነ ስርዓት አዘጋጅተው ጋብዘዋቸዋል፡፡ ሎሬት ለኢትዮጵያ ልዩ ስሜት እንዳላቸው ለገለፁት ለፕሮግራሙ አዘጋጆች፣ የኢትዮጵያ ባህል በተለይ አለባበስንና ለሰዎች ክብር መስጠትን እንዴት እንደሆነ በሚገባ አሳይተዋል፡፡ በዋሽንግተን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በመጋበዝ የተገኘውን ክብር አድምቆታል፡፡ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደሩ ዶ/ር ሳሙኤል አሰፋ እንደተናገሩት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ፣ የሥነ ጥበብን ስልት ያስተማሩ በኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ታሪክ ትልቁን ድርሻ የሚይዙ “ታላቁ ሰው” ብለዋቸዋል፡፡ አዲሶቹን የጥበብ ሥራዎቻቸውን እውን ለማድረግ ለእያንዳንዱ ሐውልት እስከ 60 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚፈጅ የገለጹት ሎሬት አፈወርቅ ለኢትዮጵያና ለራሳቸው ስም የሚበቃ/የሚተካከል ሥራ እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡ የገንዘብ አቅም ተገኝቶ በዚህ ዘመን ወይም በተተኪ ትውልድ ሊሠራ ይችላል ብለዋል፡፡

የሽልማት ታሪካቸው ገና ወጣት ሳሉ ይጀምራል፡፡ በተማሪነት ጊዜያቸው አሥር ያህል ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥትም ከአቶ ከበደ ሚካኤል ጋር የመጀመሪያው የሥነ ጥበብ ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ እጅግ ብዙ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ በተለይ ዘጠኙ የታወቁት ሥዕሎቻቸው ዓለም አቀፋዊ ታላላቅ ሽልማቶችን አስገኝቶላቸዋል፡፡ እምቅ ችሎታቸውን ከሳይንሳዊው ትምህርት ጋር በማዋሃድ ኢትዮጵያዊ፣ አፍሪካዊና ዓለም አቀፋዊ ነፀብራቅ ያለው ሥዕላቸው ለተለያየ ክብር አብቅቷቸዋል፡፡ የአሜሪካ ዩናይትድ ካልቸራል ኮንቬንሽን ዋና ፀሐፊነትን ከነተገቢ ክብሩ ጋር በማድረግ ክብርን አጎናጽፏቸዋል፡፡ “የዕድሜ ልክ ክቡር፣ ታላቅ ሰውም” ተብለው ተከብረዋል፡፡

ታላቅነት የተጎናጸፉባቸው ሥዕሎቻቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊነታቸው ከፍ ያለ ቢሆንም የእሳቸው ምኞት ግን በኢትዮጵያውያን እጅ እንዲኖር ነው፡፡ ለዚህም ነው ደግመው ደጋግመው “ኢትዮጵያ ትጠይቀኛለች” የሚሉት፡፡ ሥዕሎቻቸው ዘመናት ተሻግረውና በኢትዮጵያ ኖረው በቱሪዝምና በምርምር ረገድ እንዲያገለግሉ የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ፡፡

የተከበሩት አርቲስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሠሯቸውና ቀደም ብለው የፈጠሯቸው ሥራዎቻቸውን ለሕዝብ ክፍት ለማድረግ ከቤቲ አድቨርታይዝ ጋር እያሰቡበት ሲሆን ሥራዎቻቸውን በክራቫት፣ በካርታ፣ በሻል፣ በሲዲ በተለያዩ መልኩ ለሕዝብ እንዲቀርቡም እየተደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
------------------------------------------------------------
Morefun Free Ethiopian Forum
http://www.yared.tk" onclick="window.open(this.href);return false

or

http://morefun.niceboard.net" onclick="window.open(this.href);return false

Image


Post Reply

Return to “Ethio Art and Culture..ኢትዮ ጥበብ ፤ስነ ጽሁፍ ፤”