የማክሰኞ ሰኔ 26/2010 አበይት የሀገር ውስጥ ዜናዎች -ዋዜማ ሬዲዮ

Daily Ethiopian News, አዳዲስ ዜናዎች።
Forum rules
** When you post a News please include the Source link.
For More Ethiopian News please visit the Home Page
http://ethiopiaforums.com/
selam sew
Leader
Leader
Posts: 593
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

የማክሰኞ ሰኔ 26/2010 አበይት የሀገር ውስጥ ዜናዎች -ዋዜማ ሬዲዮ

Unread post by selam sew » 03 Jul 2018 12:49

የማክሰኞ ሰኔ 26/2010 አበይት የሀገር ውስጥ ዜናዎች

1. በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር በዛሬው ዕለት ግጭት ተከስቶ፣ በሁለቱም ወገን ሰዎች መገደላቸው ተዘገበ፡፡ ዛሬ ጧት ግጭቱ የተከሰተው በመተማ ወረዳ፣ “ደላሎ ቁጥር 4 እርሻ እና ኢንቨስትመንት” እና በሱዳን ባሶንዳ ዞን መካከል መሆኑም ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የሚጠቀሙበትን የእርሻ መሬት እንዳያርሱ የሱዳን የጸጥታ ኃይሎች መከልከላቸው ለግጭቱ ዋና ምክንያት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ወደ አካባቢው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ማምራታቸው ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ለበርካታ ዓመታት መሬቱን ሲጠቀሙበት መቆየታቸውን ለ“አማራ ቲቪ” የተናገሩት የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ “የእርሻ መሬቱን መጠቀም ያለብን እኛ ነን” ብለዋል፡፡ ሁኔታውን ለአካባቢው የሱዳን አመራሮች ማስረዳታቸውን፣ ሆኖም ግን የሱዳን አመራሮች የተነገራቸውን ባለመቀበላቸው መግባባት አለመቻሉን አስተዳዳሪው አስረድተዋል፡፡

2. የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በዛሬው ዕለት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ጋር መወያያታቸው ተጠቁሟል፡፡ ኮሚቴው ቀደም ሲል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያሳዩት ላለው ለውጥ ድጋፉን በመግለጽ ከመንግስት ጋር ውይይት እንዲደረግ ጠይቆ ነበር፡፡ ላለፉት ስድስት ዓመታት ሕዝበ ሙስሊሙ ሕገ መንግስታዊ መብቱ እንዲከበር ያነሳው ጥያቄ እንዲሁም የእምነት ነጻነት እንዲከበር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይቱ እንደሚያጠነጥን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ መንግስት ከሃይማኖት ተቋማት እጁን እንዲያነሳ የኮሚቴው አባላት በተደጋጋሚ መጠየቃቸውና ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡


3. የቤንሻንጉል ጉምዝ ፖሊስ ኮሚሽነርና የክልሉ ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ታገዱ፤ የክልሉ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ አዛዥና ምክትላቸው ደግሞ ከሥራ ተባርረዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት በአሶሳ ከተማ ለ14 ሰዎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት በነበረው ግጭት ተጠያቂ ናቸው የተባሉ 54 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርምራ እየተከናወነባቸው ነው፤ ከታሰሩት አስራ አንዱ የፖሊስ አባላት ናቸው፡፡ የክልሉ ፖሊሶች በወሰዱት ሕገ ወጥ እርምጃ የሰው ሕይወት መቅጠፋቸውን የክልሉ መንግስት አምኗል፡፡ በውሳኔው መሰረት እርምጃ የተላለፈባቸው አራቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የፖሊስ ኮሚሽነር አብደላ ሸህዲ፣ የፍትሕና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ዲንሳ በየነ፣ የልዩ ኃይል አዛዥ ፈረደ ቦዲ እና ምክትላቸው ረጂብ ኢስማኤል ናቸው፡፡

4. ሰኔ 30 ለዕረፍት የሚበተነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ የድሬዳዋ አስተዳደር ቻርተር አዋጅን በሚያሻሽለው ረቂቅ ላይ ተወያይቶ ጉዳዩን ለቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡ ሐምሌ 1/2005 ዓም ሥራውን የጀመረው የድሬዳዋ አስተዳዳር ምክር ቤት ሥልጣኑ አብቅቷል፡፡ በ2010 ዓ.ም መካሄድ የነበረበት ምርጫ ባለመካሄዱ፣ ሥልጣኑ ያበቃው የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤትን እንደገና ማደራጀት ባለመቻሉ… አዲሱ ማሻሻያ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ያለው ምክር ቤት ሥራውን እንዲቀጥል ያስችለዋል ተብሏል፡፡ ምክትል ከንቲባው ከምክር ቤት ውጪ እንዲመረጥም በማሻሻያው ተካትቷል፡፡

5. በደቡብ ክልል ኮንሶ ወረዳ በተካሄደ ሁከት ታስረው የነበሩ የ188 ሰዎች ክስ እንዲቋረጥ ተወሰነ፡፡ ከ2007 እስከ 2009 በነበረው ሁከት ተሳታፊ ነበሩ ከተባሉት ውስጥ በሰው መግደል ከባድ ወንጀል ከተከሰሱ ሁለት ግለሰቦች በቀር ሁሉም እንዲፈቱ የተወሰነ ሲሆን፣ ከተፈቺዎቹ መሐል የኮንሶ ባሕላዊ መሪ ካላ ገዛኸኝ ወልዱ ይገኙበታል፡፡

6. የተዋሀዱ ሁለት የአፋር ተቃዋሚ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ እና የኤርትራ የሠላም ድርድር፣ በተለይ የአሰብ ጉዳይን እነሱን ማካተት እንደሚኖርበት አሳሰቡ፡፡ የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚ የሆኑ ሁለት የአፋር ድርጅቶች ባለፈው ሳምንት በስዊድን ኡፕሳላ ከተማ ባደረጉት ጉባዔ መዋሃዳቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ ሁለቱ ድርጅቶች ከውሕደት በኋላ “የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ጉባዔ” ተብለው እንደሚጠሩ አሳውቀዋል፡፡ በዋናነት በኤርትራ አፋሮች ላይ የሚደርሰውን የመብት ጥሰት በተቀናጀ ሁኔታ ለመመከት እንንቀሳቀሳለን ብለዋል፡፡ በጉባዔው ለኢትዮጵያና ለኤርትራ መንግስታትም ጥሪ ቀርቧል፡፡ አሰብ ከማንም በላይ አፋርን የሚመለከት በመሆኑ… የአሰብ ወደብን ለመጠቀም በሚደረግ ድርድር የአፋርን ሕዝብ ማማከር እንደሚገባ አሳውቀዋል፡፡

7. ጠ/ሚ ዐብይ አህመድ ከሰሞኑ ወደ አሜሪካ በማምራት በዋሽንግተን ዲሲ ከዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ጋር እንደሚወያዩ ተረጋግጧል። በዲሲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም ፕሮግራሙን አስቀድሞ አመቻችቷል። ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ስለ ጉዳዩ ምንም መረጃ እንደሌለው የገለጸው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር "በነገው ዕለት ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞ ማብራሪያ እሰጣለሁ" በማለት ለመንግስት ሚዲያዎች ጥሪ ማድረጉ ታውቋል።

8. የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጉብኝት እያደረጉ ነው። ከሀገሪቱ አልጋ ወራሽ ጋር ውይይት አድርገዋል። የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ኢትዮጵያና ኤርትራን በማደራደር ቁልፍ ሚና መጫወቷ ሲነገር ቆይቷል።

አንብበው ሲጨርሱ ያጋሩ-SHARE!
Image

Post Reply

Return to “Ethiopian Daily News .. ኢትዮ ዜናዎች”