የጀምጀም ልጆች መገናኛ

Forum rules
No cursing, bad language and offend other users !
No pornographic images or links!
This forum monitored regularly. We will BAN users without warning for not obeying rules.
እባክዎ የፎረሙን ህጎች ያክብሩ::
አደቆርሳ
Jogger
Jogger
Posts: 45
Joined: 13 Jan 2012 04:13
Contact:

Re: የጀምጀም ልጆች መገናኛ

Unread post by አደቆርሳ » 03 Apr 2013 20:56

አይ አንተ ባለሱቅ እንደው ምናባቴ ባደርግህ ይሻለኛል ?
ለነገሩ ምንም አላደርግህም ምክንያቱም ጥያቄዬን በትክክል ለመመለስ የምትጥር ስለሆንክ አንድ ነገር ከማድረጌ በፊት ላመሰግንህ ይገባኛል::
እንዳልከው ጉግልን አስቸግሬ ከማግኘቴ በፊት በወጪ ቅነሳ መርሆ ራሴን አስቸገርኩና በቂ የሆነ መልስ አገኘሁ አንተንም አመሰግናለሁ ::
ከመልክቶችህ መሃል በሃዋሳ የሚሊኒየም መሪ ቃል የነበረው (( ልዩነታችን ውበታችን ነው ))
የሚል እንደነበረ አስታወስከኝ::

ሞፊቲኮ ትናንት ሰርቀህ በጻፍክበት ኮምፒውተር ምክንያት ስስቅ ነው ያመሸሁት ዕግረመገድህንም የዛሬን አያርገውና ቀደም ሲል በዲሽ ምክንያት በየቀኑ የነበረንን ንትርክ እንዳስታውስ አድርገኸኛል
ያንተዋ ግን በጣም ነው ያሳቀቺኝ ምክንያቱም ፖለቲካ እንዳታጋባባት ኮምፒውተሯን ካንተ ማራቋ....
ቅቅቅቅ በል ሁለተኛ እንዳትነካባት ::
ጎስሽክም በዚያው እንደማትቀር ሆዴ ይነግረኝ ስለነበር መልሼ እንደማይህ አልተጠራጠርኩም :
አንድ ሁለት ቀን ወረድክብኝኮ ዳሩ በጠበቅኩህ ቦታ ስላገኘሁህ ያለኝ ፍቅርም ክብርም እንደተጠበቀ
ነው::
የዛን የፍቅር ታሪክ ጉዳይ በጥሞና ካነበብኩ በኋላ ጥቂት ኮፒ አድርጌ በተለይም የፍቅርን ባህርይ እንዳውቅ ረድቶኛል : ያኔ ከዋርካ ቆየት ብዬ ስለነበር የሰጠሁህን አስተያየት መቼም አትረሳብኝም::
ግን ምን መሰለህ በስነጽሁፍ ዝግጅት ጊዜ ኔጋቲቭ አስተያየቶችን እንደ ስህተት እንዳታያቸው ልነግርህ ፈልጋለሁ ስነጽሁፍ ባህርይ ነው ስለዚህ ሁሉንም ሰው ደስ ሊያሰኝ አይችልም::
ይህም ነው እውነተኛነቱ ምናልባት ያኔ ብዙ ያልተነጋገርንበት ጉዳይ ስለመሰለኝ ነውና ደጋግመህ አስብበት ለማለት ነው::
በሺህ ዘጠኝ መቶ አርባዎቹ መጀመሪያ ገደማ ከገጠር ወደከተማ በእግራቸው ብዙ ኪሎሜትሮችን እየተጓዙ የሚማሩ ከነበሩ የገጠር ልጆች ውስጥ ኩኖ ገለልቻ የሚባል ልጅ ነበረ ::
ይህ ወጣት በተፈጥሮው ልዩ ችሎታ የነበረውና ገና የአራተኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ እንግሊዝኛ ማንበብና መጻፍ ይችል ነበር ::
በሺህ ዘጠኝ መቶ አምሳ የዘመናዊውን የአየር ኃይል ለማደራጀት በተደረገው ምልመላ ኩኖ በአየር ኃይል መኮንንነት ተመልምሎ ማሰልጠኛ ይላካል ያኔ የስምንተኝ ክፍል ተማሪ ነበር ::
ኩኖ ልመናን እና ልምምጥን የማያውቅ ቀጥተኛና መብቱን የማያስነካ ተሟጋችም እንደነበር በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ነው::
የአየር ወለድ ትምህርቱን በሚገባ አጠናቆ ሲያበቃ በስራ ዓለም ላይ ሳለ አንድ ቀን ወደቤተሰቦቹ ወደ አዶላ (ደራርቱ) አካባቢ ይመለሳል::
እናቱም አባቱም ወንድምና እህቶቹም ሁሉንም ያገኛቸውና ይደሰታሉ ዘመዶቹ ሁሉ የኩኖን መመለስ አይተው ደስታቸውን ሊያቆሙ አልቻሉም: እርሱ ግን ከአንድ ቀን በላይ ሊደሰት አልቻለም::
ሁለትና ሶስት ቀን ሲሆነው በፍጹም ደስታን እየረሳ መጣ አንድ ቀን ጠዋት አባቱን እንዲህ ይላቸዋል
ወደስራዬ ተመልሼ አልሄድም እዚሁ ከእናንተ ጋር እቆያለሁ !
እንዴ ? እንዴት ይሆናል ይሄንን የመንግስት ማዕረግ ይዘህ
የመንግስት ስራ ይዘህ ኃላፊ ሆነህ ይሄማ አይቻልም ሄደህ መስራት አለብህ ይሉታል አባቱ ::
ነገር ግን ኩኖ ወደደብረዘይት መመለስ በፍጹም አልወደደም ይህንንም ደጋግሞ ለአባቱ ይነግራቸዋል::
ታዲያ ነገሩ የቸገራቸው አባት መልሰው ለመሆኑ ምክንያትህ ምንድርነው ? ለምድርነው የማትመለሰው ? ብለው ይጠይቁታል የኩኖም ፍላጎት ይሄው ነበረና ደስ ይለዋል::
አባኮ እኔ ስለቋንቋ ምንነት አወቅኩኝ አማርኛን ተምሬ በአማርኛ ተማርኩኝ
ከኔ በኋላ ያሉት ግን በቋንቋቸው ሳይቸገሩ መማር አለባቸው ስለዚህ እዚሁ ትምህርት ቤት መከፈት አለበት አለበለዚያም ከተማ ሄደው በኦሮምኛ መማር አለባቸው ::
ጥሩ ብለሃል ይሄ የመማር ውጤት ነው ታዲያ ይህ እንዴት ይሆናል ?
እንዴትም ይሆናል ! ይልና እርሱ ተምሮ ብዙ ነገር አውቆ ሊሆን የሚችሉ ነገሮችንም መቀየር እንደሚችል እና እዚህ ገጠር ያሉ የሱ ወገኖች ግን ሳይማሩና ሳያውቁ ኑሯቸውን በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ሊገፉ መገደዳቸው አግባብ እንዳልሆነና ከተማ ያለው የሰዎች መብት እዚያ አለመኖሩ ከተማ የምንሄድበት ምክንያት ለመማር ብቻ ነው ልዩነቱ ትምህርት ቤቱ እስከሆነ ድረስ ለምንስ እዚህ እንዲከፈት ጥረት አናደርግም ? እስከመቼ ነው እንደዚሁ ዝም ብለን የምንኖረው ብሎ አባቱን መልሶ በጥያቄ ያጣድፋቸዋል::
አባቱም አሰቡ አሰቡና :-
በል ስሜቱም ፍላጎቱም ከኔ በላይ ሊገባቸው የሚችለው እነሱ ስለሆኑ ታናናሽ ወንድሞችህን ሰብስብና ንገራቸው ! ብለው መለሱለት ................................................:: ( ነገሩ በትክክል የሚገባንና የአነጋገራቸው ሚስጥር የሚገለጸው በኦሮምኛ ቢሆን ነበር )
እንግዲህ የኔም እናት አማርኛን አሁን ድረስ እጅግም አታውቅም የሚቀናት ኦሮምኛ ነው
ታዲያ ይህንን ታሪክ ያጫወተቺኝ ኩኖ ይህቺን ዓለም ሲሰናበት ዜና ዕረፍቱ ለቤተሰቡ በተላከ ጊዜ ነበር ለውጥ ከመጣ በኋላም ደጋግማ ይህንን ጉዳይ ስታነሳ እሰማት ነበር::
የኩኖ ገለልቻ ታሪክ በዚህ አላበቃም ረዥም ታሪክ ነው በነጌሌ የሰራዊቱ ዋና አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ጃገማ ኬሎ ድረስ ደርሶ ሙግት ገጥሞ እስከመጨረሻው ድረስ ታግሏል::
ምናልባት አንፈራራችን ኩኖን ሊያውቀው እንደሚችል በደንብ እገምታለሁ ::
ምክንያቱም የዛን አካባቢ ልጆች ከነበሩትና የገጠር ልጆች ከዚህ በፊት ስታነሳቸው የሰማኋቸው ስላሉ ነው::
በትምህርት ቤት ከሌሎች ልጆች የበለጠ ችሎታ የነበራቸው በተለይም በእንግሊዝኛና በሌሎችም ሳብጀክቶች ቶፕ ቶፕ ውጤት የነበራቸው ጠንካራ ጠንካራ
የአዶላ ልጆች እንደነበሩ አሁን ያሉበት ደረጃቸው ምስክር ነው::
ከዝነኛ የጦር ጄት አብራሪነት እስከ ሳይንቲስትነት ከመሃንዲስነት እስከ ህዋ ተመራማሪነት ድረስ አሁንም በአለም ዓቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑና በህይወት ያሉ የጉጂ ተወላጆች አንድና ሁለት አይደሉም::
ከአላብዱ ማቲ ሆኩ ጉጂና ዑራጋ ሳይቀር ሃረግ መዘን ብዙዎቹን ከነሙሉ ታሪካቸው ስናስታውሳቸው ነው የቆየነው አሁንም ወደፊትም እናስታውሳቸዋለን ::
እግረመንገዴን ከዚህ በፊት ካልጠቀስኳቸው ውስጥ በዚህ በያዝነው ርዕስ ጉዳይ አካባቢ አንድ የማውቀውን ታሪክ አጫውታችኋለሁ ::
ባጭሩ ከዛሬ አምሳ ዓመታት በፊትም ጀምሮ በወንድሞቻችን የነበረውም አመለካከት ምን ይመስል እንደነበረ የኩኖ ታሪክ ይነግረናል ብዬ አስባለሁ::
ባለሱቅና ጎስሽክም በቋንቋ ላይ ያለኝን አቋም በቁጣ ስትቃወሙኝ መልሼ ያልተቆጣሁበት ምክንያት
አዋቂ ሳላልሆንኩ ብቻ ሳይሆን የናንተን ሃሳብ የሚቃወም አስተሳሰብ ስለሌለኝ ነው : በቋንቋ እኩልነት ላይ የምጠራጠር አይደለሁም ምናልባት ገባ ብለን ወደፊት በረጋ መንፈስ እንወያይበት ይሆናል ::
የሆነው ሆኖ ዛሬ ዓለም መልኳ ተቀይሮ የነበረው ወዳልነበረበት ዘመን የተሸጋገርን ቢሆንም በሃገራችን ፍትህ እኩልነትና ነጻነት ሰፍኖ ሁላችንም በኣንድነት ለፍቅር የምንዘምርበትን ጊዜ ማየት የምንጊዜም ፍላጎቴ ነው::
ቸር ያቆየን ወዳጃችሁ አደቆርሳ ዘሃገረ አዶላ

ሞፊቲ
Jogger
Jogger
Posts: 33
Joined: 03 Jan 2012 14:19
Contact:

Re: የጀምጀም ልጆች መገናኛ

Unread post by ሞፊቲ » 04 Apr 2013 15:57

ሰላም ብለናል;;


ውድ ጎሳ እንደምን አለህልኝ
የሁለት ብር ካርድ ፍቔ ለምን አንዳልደወልኩልህ ወቅሰሀኛል;;አባ እንዴት አድርጌ ልደውልልህ;;
ፈራሁህ እኮ/ የማላውቅህ ያህል ሆነህብኝ እንዳልተኮላሸ ድመት ስትሆን ምናባተ ላድርግ ብለህ ነው, እንደውም ፔጃችን ላይ ያንተን ጨዋነትና የቀድሞ ባህሪ በመግለጥ አሁን ምን እንደነካብኝ አላውቅምና እባካችሁ ጠበል ውሰዱልኝ ለማለት እሩብ ሰአት ሲቀረኝ እኮ ነው እራስህን ያገኘሀው;;


ባለፈው ጋሽ ቦጋለ አለሙን ስታነሳ አንድ ነገር ትውስ ብሎኝ ነበር;;ታስታውስ እንደሆን ሁሌም አስተርዮ ማርያምና የይርባሙዳው ገብሬል ሲነግስ የኔታ የ እለቱን በአል ለመእመናን በአማርኛ
ሲያስተመሩ ከስር ከስር በኦሮምኛ እየተረጎመ የሚያስተላልፈው ጋሽ ቦጋለ ነበር;;
ይህን ነገር ሁሌም ከደረጀ ከበደ ጋ እያነሳን እናወራዋለን;;ከሁሉም የሚገርመኝ ከገጠር የሚመጡት
ታቦት አንጋሾች የጴንጠ እምነት ተከታዮች ቢሆኑም 'ማርያሚን ማን ኑጎቴ' ብለው በአሉን ማክበራቸው ነበር;;
ጋሽ ቦጋለ ሱታ አካባቢ የምታምር ቆንጆ የጉጂ ሚስትስ እንደነበረው ታውቃለህ/ በነገራችን ላይ መአት ሚስቶች በማግባት ጋሽ ቦጋለንስ የሚስተካከል ይኖር ይሆን/


ይህ እንዲህ እንዳለ ባለፈው ወር የሰማሁት ወሬ በጣም አስደንጋጭ ነበር;;የጋሽ ቦጋለ ልጅ ማለትም የታምራት ቦጋለ ሚስት በህመም ምክንያት ትሞታለች;;ወይንሼትን እኔም
ስለማውቃት በጣም ነበር ያሰንኩት;;ወይንሼት የቦረና ልጅ ናት;;እንደሰማሁ ለታምራት ደውየለት አጽናንቼው ነበር;;በኋላ ላይ በሷ መሞት ቅስሙ የተሰበረው ታምራት እራሱን በመስቀል ህይወቱን ለማጥፋት ሲሞክር ሰው ደርሶ ያተርፈዋል;;
የሃገር ሽማግሌዎች በመስብሰብም ለሶስት ልጆቹ ያለው እሱ በመሆኑ ይህን ማድረጉ ተገቢ እንዳልሆነ በመምከር ወደራሱ ይመልሱታል;;እኔም በልጆቹ ምክንያት ተጸጽቶ ይህን አስቀያሚ ነገር እንደማይደግመው አምኜ ነበር;;ይሁንና ጥቂት ቀናቶች እንደገፉ በውሳኔው
የጸናው ታምራት ሶስት ልጆችን በትኖ በሁለተኛው ሙከራው እራሱን አጥፍቶአል;;
ይህ ባለፈው ወር ቦሬ ውስጥ የተፈጸመ አስከፊ ነገር ነበር;;


ውድ አደቆርሳ የጀመርከው ታሪክ የድምጽ ትረካ ያህል አፍ ያስከፍታል;;በነገራችን ላይ የሚጥም ታሪክ ሳነብ ድምጼን ከፍ በማድረግ በትረካ መልክ በመሆኑ አፍ ያስከፍታል
ያልኩት ያለምክንያት አይደለም;;[የቋንቋ አስተማሪ ወንድም ያለው ጎሳ እንዳይተርበኝ መከላከያዬን አቅርቤአለሁ;;]እባክህ ቶሎ ቀጥለው........
ቸር እንሰንብት

ጎሳ
ጀማሪ Starter
ጀማሪ Starter
Posts: 8
Joined: 13 Mar 2013 02:51
Contact:

Re: የጀምጀም ልጆች መገናኛ

Unread post by ጎሳ » 04 Apr 2013 22:51

ሰላም ለሁላችንም!
ትናንት የራሴን ሪከርድ እራሴው ሰበርኩ:: የምን አትሉኝም...ፊልም የማየት ሪከርድ:: እስከዛሬ ጀምሬ የጨረስኳቸው ድራማዎች (የኢትዮ) ብዙ አይደሉም:: ሰፍ ብዬ እጀምርና አካሄዱ ትንሽ ካልተዋጠልኝ መቀጠል አልችልም:: ታዲያ ትናንት ለሰባት ሰአታት ያህል ቁጭ ብዬ ባለ አስራ አምስት ተከታታይ ክፍሎች "ቅብብል " ን በማየት የእረፍት ጊዜየን አባከንኩት:: እደውልላችኌለሁ ባልኳቸው ሰአት ሳልደውልላቸው በመቅረቴ ካገር ቤት የሚስድ ኮል መአት ሲያጨናንቀኝ ድራማውን አቁሜ ደውዬላቸው "ቅብብል "ን እያየሁ መሆኔን ስነግራቸው በነ ጋሽ ቦጋለ ዘመን በኢቲቪ የታየ ተከታታይ የቲቪ ድራማ መሆኑን ነገሩኝ:: "ለምን በነ ቡቁዩ ዘመን የታየ አይሆንም: አይቼ ስጨርስ እደውልላችኌለሁ " ብዬ ዘግቼባቸው ወደ ፊልሜ ተመለስኩ:: ሰዎች እዚህ ላይ አንድ ነገር ልጠይቃችሁ...ፊልም እና ድራማ ልዩነት አላቸው እንዴ? የትኛውን ፊልም ብለን የትኛውን ድራማ እንበል? እናላችሁ አጨራረሱ ቢያናድደኝም ጨረስኩት:: እዚህ ቤት ገብቼ የሆነ ነገር እንዳልሞነጫጭርም ምቀኛ የሆነብኝ ቅብብሉ ነው ማለት ነው::

“ጎስሽክም በዚያው እንደማትቀር ሆዴ ይነግረኝ ስለነበር መልሼ እንደማይህ አልተጠራጠርኩም :
አንድ ሁለት ቀን ወረድክብኝኮ ዳሩ በጠበቅኩህ ቦታ ስላገኘሁህ ያለኝ ፍቅርም ክብርም እንደተጠበቀ
ነው::”
አደቆርሳ ወንድሜ እውነትም ቀላል አልወረድኩብህም:: አሁን መለስ ብዬ ሳነበው እኔው እራሴ የጻፍኩት አልመስልህ አለኝ:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለምን እንዲህ ትዕግስት እንዳጣሁ አላውቅም:: ብቻ ልለፈው::
የኩኖ ገለልቻ ታሪክ በጣም ነው ያሳዘነኝ:: ልክ እንደ ጉዱ ካሳ መንቃት ባልነበረበት ሰአት ነበር የነቃው:: በዚያን ዘመን የአፋን ኦሮሞን ት/ቤት ለመክፈት ማሰብ ቀላል አይደለም:: እስቲ ታሪኩን ቀጥልበት እባክህን::
“የዛን የፍቅር ታሪክ ጉዳይ በጥሞና ካነበብኩ በኋላ ጥቂት ኮፒ አድርጌ በተለይም የፍቅርን ባህርይ እንዳውቅ ረድቶኛል : ያኔ ከዋርካ ቆየት ብዬ ስለነበር የሰጠሁህን አስተያየት መቼም አትረሳብኝም::
ግን ምን መሰለህ በስነጽሁፍ ዝግጅት ጊዜ ኔጋቲቭ አስተያየቶችን እንደ ስህተት እንዳታያቸው ልነግርህ ፈልጋለሁ ስነጽሁፍ ባህርይ ነው ስለዚህ ሁሉንም ሰው ደስ ሊያሰኝ አይችልም::
ይህም ነው እውነተኛነቱ ምናልባት ያኔ ብዙ ያልተነጋገርንበት ጉዳይ ስለመሰለኝ ነውና ደጋግመህ አስብበት ለማለት ነው:”
አደቆርሳችን በዚያ ታሪክ ላይ የሰጠኽንኝን አስተያየት መቼም አልረሳም:: ልክ ነህ.....ምንም አይነት ነገር ብትጽፍ ሁሉንም ሰው ማስደሰት አትቻልም:: ነገር ግን እኔ በየዋህነት የጻፍኩት ነገር እያወቅኩ ሆን ብዬ እውነትን እንደደበቅኩ ተደርጎ እንዲታይብኝ አልፈለኩም:: ምንም ነገር ሳልሰማ በዚያው ለህትመት አቅርቤ ብሆንና ከዚያ በኌላ ተቃውሞ ቢቀሰቅስብኝ ምንም አይመስለኝም ነበር:: አሁን ግን እየተነገረኝ እየሰማሁ ዝም ብዬ ማሳተሙ ይከብደኛል:: ለዚሁም ነው የማሳተሙን ጉዳይ ትቼ የራሴ የዋርካ ማስታወሻ እንዲሆነኝ በመጽሀፍ መልክ ጠርዤ ያስቀመጥኩት::
“ባለሱቅና ጎስሽክም በቋንቋ ላይ ያለኝን አቋም በቁጣ ስትቃወሙኝ መልሼ ያልተቆጣሁበት ምክንያት
አዋቂ ሳላልሆንኩ ብቻ ሳይሆን የናንተን ሃሳብ የሚቃወም አስተሳሰብ ስለሌለኝ ነው : በቋንቋ እኩልነት ላይ የምጠራጠር አይደለሁም ምናልባት ገባ ብለን ወደፊት በረጋ መንፈስ እንወያይበት ይሆናል ::”
ሙሉ በሙሉ ተስማምተናል ወንድማችን:: እንደውም እንደዚህ አይነት ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ጉዳዮች ባይነሳ ደስ ይለኛል:: ድሮም ሞፊቲ ነው እንዲህ አይነት ነገሮችን እያመጣ ሰላም የሚነሳን:: የስራውን ይስጠው::
ሞፊቲ ኪያ “እንዳልተኮላሸ ድመት ስትሆን ምናባተ ላድርግ ብለህ ነው”
ቦሬ በነበርክበት ወቅት ድመት ታኮላሽ ነበር እንዴ? እኔን ስንት ታሪክ አምልጦኛል ማለት ነው ጎበዝ....ጉግሳም ጉንጩን በአረንጓዴ በለስ ወጥሮ ከብት ሲያኮላሽ እንጂ ድመት ላይ ሲዘምት አላየሁትም:: ፈረንጆቹ ደግሞ ድመቶቹ እንዳይመቱ እየተከራከሩላቸውና በቁምነገር ምግብ እየሰጧቸው እንደ ሰው ሁሉ እንዳይዝናኑ አሁን አንተ ያልከውን ያደርጓቸዋል:: ግፈኞች:: "አርጋላ "ሆነው ጫካ ገብተው የግል ኑሯቸውን እንዲኖሩ ቢተውአቸውስ? ሲለን ደግሞ የድመት መብት ተከራካሪም ያደርገናል... "ወይ ዘንድሮ " አለ ኤፍረም'ኮ ነው አውስትራሊያ መጥቶ በቂ ህዝብ አልገባ ሲለው ቅቅቅቅ:: ኧረ ስቀልድ ነው...ደግሞ ሹክ በለውና አጣላኛ በጣም ከምወደው ድምጻዊ ጋር::
ስለ ጋሽ ቦጋለ ባለፈው ያነሳሁት ጉቦን በተመለከተ እንጂ ዘረኛ ነው ብዬ አላልኩም:: ለማንኛውም ደግመህ ስላነሳኽው እንዴት ደስ እንዳለኝ! ለምን አትለኝም?...አንተ ያልከው ቀይ ቆንጅየዋ ሱታ የምትኖረው የባለቤቱን ማንነት በዚሁ አጋጣሚ ልነግርህ....አዱሌ በሪሶ ትባላለች...ከቦሬ አዲስ አበባ ሁለቴ የተነዳው የባሪሶ(ዲማ) ቶኖሪ ልጅ ነች:: ይህች ሴትዮ እህቴ እንደሆነች እወቅ.... የዋቀዮ እናት:: እንዴት ተዛመዳችሁ ትለኝ ይሆናል...ገልቹ ባንታ ላሎ አኖሌ ሼቦ..ልቀጥል ይሆን?...ይብቃኝ...እና አቶ ገልቹ አራት ወንዶች ልጆች ብቻ ነው የነበሩት:: በቅደም ተከተል ቶኖሪ፣ አሬሪ፣ አጋ እና ታናሹ እና የመጨረሻ ልጃቸው ቡቁዩ:: ባሪሶ ደግሞ የቶኖሪ የመጀመሪያ ልጁ ነው:: አቤት ቁንጅናው...ፈረንጅ ይመስላል ብልህ ያንተ ነገር ዞር ብለህ በጥቁር ቆዳ ቁንጅና አታምንም ስለምትለኝ ልተወው:: ጡንቻውም "ጊንጋሚ ኮያ " የሚባል ነው:: ይህንን አባባል ወቤ ጃሎ ካወቀ እንጂ አንተ እንኳ የምታውቅ አይመስለኝም:: ለዚሁም ነው መሰለኝ ጡንቻውን አይተው ሁለቴ ያመላለሱት:: የምገርመው መጨረሻ ላይ ወጣት ሚስት አግብቶ ነበር የሞተው:: ያቺ ወጣት ሚስቱ( ዱሬ ትባላለች:: ሳባ አዲሱ የቦሬ ሀይስኩል አጠገብ ነው ቤቷ) ከእናቴም ጋር የቀረበ የስጋ ዝምድና አላት:: ከሁለት ቀን በፊት ለናቴ ስልክ ስደውል በጣም እያለቀሰች ነበር ዱሬ መሞቷን የነገረችኝ:: ለቀብሯ ሀሮ ከገጠር እስኪመጣ እየተጠበቀ ነበር:: እና ያወራሁትን ማጣራት ትችላለህ ሞፊቲ ኪያ::
የጋሽ ቦጋለ አለሙ አሁን ይቀመጥ እና የአባቱን የአቶ አለሙ ፈይሳን አንድ ታሪክ ልንገርህ....መቼም ዛሬ አውራ አውራ ብሎኛል:: ልጅ ሆኜ ሳውቀው ኑሮ ያልተመቸው ሰው ነበር:: ያኔ ጋሽ ቦጋለ እንደዚያ ቆንጆ ደረጃ ላይ እያሉ ሽማግሌው ለምን እንደዚያ ኑሮ እንዳልተመቻቸው አላውቅም:: ታዲያ ልክ እንደ ጋሽ ቦጋለ ሁሉ አቶ አለሙም ካባቴ ጋር ሽርክ ነበሩ:: እኛ ቤት ይመጡና ሁለት ሶስት ቀን አድረው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ:: ታዲያ ያሳለፉትን ታሪክ ሲያወሩ ብትሰማ ያኔ በጣም ያስቅህ ነበር...በልጅ አዕምሮ:: አሁን ላይ ቆሜ ሳስብ ግን አያስቅም::
ከወደ ቡሌ አካባቢ ከተወሰኑ ባለስልጣናት ጋር ወደ ቦሬ እየተመለሱ ነበር:: ጋሽ አለሙ “ ሽንት ይዞኛል እና ቋጥኝ ነገር እፈልጋለሁ: ቀስ ብላችሁ ኑ” ብሏቸው ሌሎቹን ቀድሟቸው ይሄድና ከሰዎቹ አይን ይሰወራል:: የሆነ ወንዝ ሲሻገር ሶስት ሆነው ከብቶቻቸውን ውሀ ያጠጡ የነበሩትን አዛውንቶችን ሰላም ካላቸው በኌላ ከፈረስ ወርዶ አንድ ትልቅ ድንጋይ መርጦ ከካፖርቱ ስር ለብሶ በነበረው ጋቢው እንዲያሸክሙት ሰዎቹን ይለምናቸዋል:: ሰዎቹ በልመናው ግራ ተጋብተው እምቢ ቢሉም ለስለት የሚሸከም መሆኑን አሳምኗቸው ያሸክሙታል:: ልክ ከሀላው የነበሩት ሰዎች ሲመጡ ኡኡታውን ያቀልጠዋል አቶ አለሙ:: ሰዎቹ ፍጥነት ጨምረው እየጋለቡ ሲደርሱ አለሙ ሆዬ ድንጋውን እንደተሸከመ ወድቋል:: "እስከ ዛሬ ስታሰቃየን ኖረህ ዛሬ አገኘንህ ብለው ድንጋይ አሸክመውኝ ወንዝ ሊከቱኝ ሲሉ ደረሳችሁልኝ ወንድሞቼ:: ድንጋዩን ብቻ አውርዱልኝ: እኔ አለሙ በቁሙ ተቀብሬያለሁ... "ዘራፍ አለ:: ነገሩን ለማሳጠር እዚያው ሽምግልና ተይዞ አንዳንድ ከብት ባጠቃላይ ሶስት ከብት ወስዶ ታረቃቸው:: ሌላውን ሌላ ጊዜ እቀጥላለሁ::
ያኔ በመንደር ምስረታው ወቅት ለዚሁ ጉዳይ ወደ ጎሳ በዋናነት ተመድቦ የነበረው ጋሽ ቦጋለ ነበር:: ሁሌም የሚያርፈው እኛ ቤት ነው:: ስጋ የሰለቸኝ ያኔ ነው:: በየቀኑ የሚታረድ በግ...ቦሬ እቤቱ የሚላክ በግ ቁጥር የለውም:: በጉማሬ ሁሉ ሰው ይማታ ነበር:: ገበሬዎችን ቀላል አላስለቀሰም:: አይደለም ገበሬዎችን ጴንጤዎችን አንድ ባንድ እየገረፋቸው ካቲካላ ያግታቸው እንደነበር ባይኔ በብረቱ አይቻለሁ:: አቤት የግፍ ዘመን:: አቤት የሰው ልጅ ግፍ:: ምን ያደርጋል...ያ ስርአት አልፎ ኑሮ ተበላሽቶበት እንደዚያ ሲፈራ እና ሲከበር የኖረ ሰው አሟሟቱ አላማረም:: አሁን እዚህ ላይ አልጽፍም::
ሌላው የታምራት ጉዳይ በጣም ያሳዝናል:: ባይኔ አይቸው አላውቅም:: ንጉሴ ነበር ድሮ ባንድ ወቅት "መስመር ላይ ተገናኝታችኌል " ብሎኝ በማላውቀው ሰው ቂም እንድይዝ ያደረገኝ:: እስከዛሬም ያ ታሪክ እውነት ይሁን ውሸት አላጣራሁም:: የንጉሴ ፈጠራም ይሆን ይሆናል ማን እሱን ያምናል:: ነብሱን እግዜር ይማረው:: የፍቅር ጉዳይ መጥፎ ነው:: አንድን ሰው ለምደህ ተመልሰህ ስታጣው ማንም አፍቃሪ የሚሰማው ጉዳይ ቢሆንም ቢያንስ ለልጆቹ ስል በህይወት ቢኖር ጥሩ ነበር:: ምን ይደረጋል:: ይልቅ ትናንትም ከቦሬ የአንድ ጎረቤት ሰዎች አንዱ ታሞ ሌላው ደግሞ ታንቆ መሞታቸውን ሰምቻለሁ:: ቦሬ የቀሩህ የቅርብ ዘመዶችህን እና ወዳጆችህን በዝርዝር ስለማላውቅ ስማቸውን ልጠቅስ አልፈልግም:: ሌላ እዚህ ገብቶ የሚያነብ የቦሬ ሰው ቢኖርስ ደግሞ:: እራስህ ደውለህ አጣራ:: ደረጀ ከበደም ዋርካ ገብቶ ይጽፋል ሲባል ሰምቼ ነበር:: ለሁሉም ነገር አንዲት አይፋን ብቻ በምስክርነት ከማስቸግራት እሱንስ ለምን አላስመሰክርም? ለአመታት የክፍል ጓደኛየ ነበር:: ስታገኘው ሰላም በልልኝ::
በል አቦ ለዛሬ ይብቃኝ::
ይመቻችሁ::

ሞፊቲ
Jogger
Jogger
Posts: 33
Joined: 03 Jan 2012 14:19
Contact:

Re: የጀምጀም ልጆች መገናኛ

Unread post by ሞፊቲ » 06 Apr 2013 03:31

ሰላም ለናንተ ይሁን;;


ወይ ጎሳሳሳሳሳ....የማታመጣው ታሪክ የለም;;የአባባ አለሙ ፈይሳን ወሬ ማምጣትህ እስካሁን ድረስ ግርምምምምምም እያለኝ ነው;;እኔ በ እውነት ነው የምልህ ረስቻቸው ሁሉ ነበር;;
ጉደኛ በጣም ጉደኛነህ;;


አንተ እንደው ተንከራተት ሲልህ ነው እንጂ የነ ጽጌን ታሪክ ጽፈህ ወድያ ወዲህ ማለትህ...መስራት የነበረብህ አባትህ ስር ቁጭ ብለህ የቃረምከውን ወሬ ነበር;;
አቤት ጆሮ....ምን ያላጠራቀምከው ነገር አለ...


ሌላው የጋሽ ቦጋለ ሚስት ያልኩህ የነዋቀዮ እናት መሆኑአን እኔም አስታወስኩ;;እንደምንም ቆጥረህ ሰኚ ሆንክ አይደል....ትንሽ መንገድ ካገኘህ እኛም ቤት አለሁ ብለህ መምጣትህ አይቀርም;;


ባለፈው ቦሬ አንድ የቤተሰብ የፍርድ ጉዳይ ነበረንና ጉዳዩ ትንሽ አስቸጋሪ ነበር;;ሰዎች በተንኮል እጃቸውን ያወናጨፉበትን የቤተሰብ የውርስ ቤት ባንክ ሊወስደው ከጫፍ ደርሶ ኖሮ ሃገሬው
ይሰማና ይናደዳል;; ይህም ብቻ ሳይሆን የሚያስገርመው ታሪክ የተፈጠረው አንድ ይገበያ ቀን ከ80ንያ በላይ የሆኑ የቀሌ ነዋሪዎች አስተዳደር በመሄድ ሰላማዊ ሰልፍ ያደርጋሉ;;ምንም
ይሁን ምን ቤቱ ቅርስ ስለሆነ እንዳይነካ የሚል ነበር ማስጠንቀቅያቸው;;
ወሬውን ከቤተሰብ እንደሰማን ወደሚመለከተው አካል በመደወል የተንኮሉን ድር ፈታ በማድረግ ህጋዊ በሆነ መልኩ ወደ እጃችን አስገብተነዋል;;
ከሁሉም የደነቀኝና በአጭሩ ለማውራት የፈለኩት የሰልፉ ጉዳይ ገርሞኝ ነበር;;መወለድ ብቻ ሳይሆን አብሮ መኖር እንዲህ ያዋድዳል;;
ይህን ታሪክ ወደፊት በሰፊው እመለስበታለሁ;; ቀደም ብዬ እንደነገርኳችሁ መጻፍያዬ አስቸግሮኝ ፊደል በማውስ እየለቀምኩ ነው የምጽፈው;;አንዳንዱ ፊደልማ የት እንደገባብኝ
አላውቅም;;


ለማንኛውም ጓድ ጎሳ ትላንት በጻፍከው ጉዳይ በሳቅ ሞቻለሁና እንመላለስበታለን;;


በነገራችን ላይ የራስ ብሩ የመክፈቻ ቁልፍ[ፓስ ዎርዱ] ስለጠፋበት ነውና ሰሞኑን ያልታየው እባካችሁ ካገኛችሁ ላኩለት;;


ቸር እንሰንብት

ራስብሩ
Starter
Starter
Posts: 23
Joined: 03 Jan 2012 09:45
Contact:

Re: የጀምጀም ልጆች መገናኛ

Unread post by ራስብሩ » 07 Apr 2013 15:31

ጤና ይስጥልኝ
ሞፊቲኮ ዛሬ ሰንበት ስለሆነ ፓስወርዱን ለመፈለግ ጊዜ አግኝቼ ነው ብቅ ያልኩት
የሰንበት ነገር ሲነሳ የኢትዮጵያ ቤተክርሥቲያናት ጉዳይ ከጊዜ ወደጊዜ አሳዛኝ ሁኔታ እየታየበት መምጣቱ አስፈርቶኛል በውነት በጣምም ነው የሚያሳዝነው
እግዚአብሄር ይጠብቀን ከማለ ሌላ ምን እላለሁ ::
ኦዶ ኪያ ባለፈው ግዜ ለመመዝገብ ተቸግረህ ነበር አሁን ተሳክቶልህ በመምጣት´ህ እንኳን ደህና መጣህ ብያለሁ ከባለሱቅ ጋርም ልክ እንዳንተ መንገድ ላይ ተገናኝተን ተጨቃጭቀን ነበር ባለሱቅም እንኳን ደህና መጣህ ብያለሁ::
ኦዶ ከስንት ጊዜ በኋላ ትላንት ከገኒ ጋር በቴሌፎን ተገናኘን በዓይን ከተያየን በጣም ረዥም ጊዜ ነው ቢሆንም አንድ ቀን እዚህ መገናኘታችን
አይቀርም ከቻልኩ ወደዚህ ቤት ይዣት እመጣለሁም ብያለሁ ::
በተረፈ የውይይቱ አርእስት ጥሩ ነበር በሳል እና አስተዋይ ሰዎችን እንዲሁም ብዙ ቁምነገሮችን ያየንበትና የተማርንበት ሊሆን መቻሉ ደስ ስ ስ ስ አሰኝቶናል::
ጂግሳ እንደምናለህ ምነው ሰሞኑን ጠፋህ አንተም እንደኔ የፓስወርድ ችግር እንዳልገጠመህ አምናለሁ
ከታላቅ ወንድምህ ጋር ጁኒየር አብረን ነው የተማርነው የሚገርምህ በጣም ከረዥም ዓመታት በኋላ ካልተሳሳትኩ ከጁኒየር በኋላ የዛሬ 5 አመት ክብረመንግስት ሄጄ ሳገኘው አንድም ለውጥ
አላየሁበትም ያው እንደድሮው ነበር በጣም ነው የገረመኝ::
በልጅነታችንም ረጋ ያለ ግን በጣም እልኸኛ ነበር የሚገርመኝ አስተማሪዎችን በአለባበሳቸው
አስተያየት ይሰጥ ነበር ማለት ስለ አለባበስ ይናገር ነበር ታዲያ ባለፈው ሳገኘው ሽክ ብሎ ጫማውን እንኳን አዋራ እንዳያበላሽበት ዓይነት ሲሄድ ነው ከኋላው የያዝኩት::
ስላገኘሁት ግን በጣም በጣም ነው የተደሰትኩት እሱም ደንግጦ ነበር ያየኝ ከኛ ጓደኞች ውስጥ እሱንና ተሰማ አዱኛን አግኝቻቸዋለሁ::
ሌላ ባለፈው ሳምንት ውስጥ በባሌ የመምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ የሆነችው ሥንታየሁ ወልዴን ስልክ ደውዬ በደንብ አነጋግሬያታለሁ ለሁሉም
የዚህ ቤት ልጆችና የወላጅ አልባዎቹን ማሳደጊያ አካውንት ለምታዳብሩ ሁሉ እንባ የተሞላበት ምስጋና አቅርባለች::
ዝርዝር ሁኔታውን ሁላችንም ስንገናኝ አስረዳችኋለሁ በተጨማሪም በሚቀጥለው ዓመት ተመራቂ ስለሆነችና ለኛም የመጀመሪያ ልጃችን እንደመሆኗ መጠን ተነጋግረን አንድ የምርቃት ስጦታ እንድናደርግላት ጥሪ አቀርባለሁ::
እነዚያን ህጻናት ስናነሳ አስቀድመን ከንጠራቸው ውስጥ አንዱ የሆነው ሽልንግዬም ክብረመንግስት ሄዶ ከተመለሰ ጥቂት ጊዜው ነው በሱ በኩል የተደረጉትን እና ሌሎችንም በተመለከተ ለመነጋገር መገናኘታችን አስፈላጊ መስሎ ይታየኛል ::
ስለዚህ ባለፈው የነበረንን ሩም አክቲቭ ለማድረግ ብሞክር አስቸግሮኝ
አሁን ሪሴንድ ተደርጎልኝ ሩማችንን በጃችን አስገብቻለሁ ማለት ነው::
የልጆቻችንን ጉዳይ በተመለከተ ጥሩ ልንነጋገርባቸው የምንችላቸው ጉዳዮች ስላሉን እንደዚሁም በስንታየሁ ወልዴ ጉዳይ እንድንነጋገር አንድ ቀን እንገናኛለን ፕሊስ ሁላችሁም ብዙም ባልሆን ያለነው በትክክል የምንገኝበትን ቀን አክብረን እንድንገኝ አደራ ዋቃ ! እላለሁ::
ጊዜው የጾም እንደመሆኑ ለምትጾሙ መልካም ጾም ይሁንላችሁ
የዌብ ሳይቱን አድሚን ስለፈጣን እርዳታቸው ከልብ ላመሰግናቸው እወዳለሁ
ራስብሩ

ሞፊቲ
Jogger
Jogger
Posts: 33
Joined: 03 Jan 2012 14:19
Contact:

Re: የጀምጀም ልጆች መገናኛ

Unread post by ሞፊቲ » 08 Apr 2013 00:39

ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን::


ራስ ብርሻ...በጓሮ በኩል ያደረስከኝ መልክት <እኛ እንዲህ ነን> እንድል አድርጎኛል::ለማንኛውም ጠንቀቅ በል ....የመረጃ ምንጮቼ በዘመኑ መሳርያ የተደገፉ ናቸው::


ስለ ስንታየሁ ወልዴ ያነሳኸው ነጥብ በጣም የሚያስደንቅ ነበር::ልጆቹ እዚህ ደረጃ መድረሳቸውን አላውቅም::ግዜው እንዴት ነው የሚሮጠው ባክህ?
ከዚህ በላይ የሚያኮራ ስራ አለ ለማለት አልደፍርም::ድሮ አስተማሪዎቻችን እንኳ በዛች የትም በማታደርስ ደሞዝ ሲኖሩ ይኮሩ የነበሩት በተርማሪዎቻቸው ውጤትና ደረጃ ነበር::
አንድ አስተማሪ አንድም ትሁን ሁለት አመት ያስተማረው ተማሪው ትልቅ ደረጃ ደርሶ እራሱን ቤተስቡንና ሃገሩን መጥቀም ሲጀምር <የኔ ተማሪ እኮ ነበር> በማለት ኩራት ይሰማዋል::
ዛሬም የልጆቹ ደጋፊና ረጂ የሆናችሁ ሁሉ እዚህ ደረጃ በመድረሳቸውና ከነሱም የሚገጥማችሁ የፍቅርና የምስጋና መልክት ከምንም በላይ መንፈሳዊ እርካታ እንደሚሰጣችሁ ጥርጥር የለውም::
ራስብሩ ላደረስከን መልካም መልክት ከልብ እናመሰግናለን::


ሱቅሻ=ጠፍተህ የመጣህበትን ታሪክ ሳትነግረን እንደገና ልትጠፋ ያስብክ ይመስላል::ምነው እንዲህ ባተሌ ሆንክሳ?
ድርስት መጻፍ ጀመርክ እንዴ?ተ....ው አያዋጣም ብያለሁ? ካላመንከኝ የነጽጌን ወዳጅ ጠይቅ::እኛ ስንት ቀን ሙሉ ስራችንን ትተን ስናርምና ስንመረምር የነበረውን ታሪክ
አይደል እንዴ! ቦሬ ሄዶ ቆጥ ላይ ሰቅሎት የመጣው....
ስለዚህ ቢቀርቦት ይሻላልና እዚሁ ያሎትን ወሬ ዘርገፍ አርጉልን::


ኦዶ ኪያ ባለፈው እኔም አይቼህ ሰላም ሳልልህ ነውና የወጣሁት እንኳን ደህና መጣህልን ብያለሁ::


ቸር እንሰንብት::

Jigsa
Starter
Starter
Posts: 21
Joined: 13 Feb 2013 01:27
Contact:

Re: የጀምጀም ልጆች መገናኛ

Unread post by Jigsa » 10 Apr 2013 14:56

ውድ ወንድሞቼ
ሃርካ ፉኔ አከም ጂረታኒ…
ስሞኑን ልጻፍ ልተው እያልኩኝ ከራሴ ጋር ስሟገት ቆይቼ ዛሬ ራሴን አሳመንኩት( ወይሴ ራሴ አሳመነኝ)፡፡ ከራሴ ጋር ሙግት የገባሁት እኔ በጀመርኩት ጽሑፍ ምክንያት የቆዩ ምንድማማቾችን ከኋላ መጥቼ አጣልቼ የት አባቴ ልግባ ብዬ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ሁላችሁም ምናልባትም ድሮ ከነበረበት ወደ ተሻለ ፍቅር ገብታችሁ ሳይ… በበቃኝ ተዘረርኩኝ እጅ ሰጠሁኝ… ለፍቅራችሁ ቺርስ!!
ትንሽ ደግሞ ቢዚ ነገር ሆንኩኝ፡፡ ዎርክሾፕ፤ ትሬኒንግ፤ ፕላኒንግ፤ ምናምን …..የሆድ ነገር ነዋ!!
ያንን ርእስ ማርያምን አልደግመውም! ግን ትንሽ ነገር ብዬ ነው ርእሱን የምዘጋው ከሁሉ በፊት በእርግጠኝነት ከጎሳ ጋር 95 በመቶ እስማማለው፡፡ ግን የገረመኝ አንድም ተቃዋሚ እስር ቤት የለም ነው ያልከኝ;;;;; በጣም ነው ያሳቀኝ፡፡ ኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞችን በማሰርና በማፈን ከ ኤርትራ ቀጥሎ ሁለተኛዋ ሃገር ናት… የ CPJ ን ሪፖርት ተመልከት … and almost every genuine opposition politician is either in jail or fled the country.
አንድነገር ግን እርግጥ ነው፡፡ አንድ ህዝብ አንድ ቋንቋ የሚለው ጉዳይ ከዚህ በኋላ የትም አያደርስም በነገራችን ላይ በ1984 ዓ.ም ቁቤ አፋን ኦሮሞ ሲጀመር በፈቃደኝነት ለማስተማር ከዘመቱት መካከል አንዱ ነበርኩኝ በአዶላ! ሆኖም ግን አንድ የጉጂ ልጅ ተምሮ ሙያ ኖሮት መቀሌ ወይም ባህርዳር ማዘጋጃ ተቀጥሮ ለመስራት መብት ሊኖረው ይገባል ብዬ አምናለሁ በተቃራኒውም እንደዚሁ፡፤ ይሄ ብዙዎቻችሁየዚህ ቤተሰብ አባላት ከፋም ለማም ሰው ሃገር ሄዳችሁ እየሰራችሁ አይደል! በቃኝ ጥይት ጨርሻለሁኝ፡፡


ጎሳ ኪያ አቲቀየመኝና ስለ ኢትዮጵያ መረጃ የምታገኘው ከኢቲቪ ብቻ ሳይሆን አይቀርም ፡፡ቅቅቅቅ Adola dhugaa kiyya !

አደቆርሳ
Jogger
Jogger
Posts: 45
Joined: 13 Jan 2012 04:13
Contact:

Re: የጀምጀም ልጆች መገናኛ

Unread post by አደቆርሳ » 12 Apr 2013 20:34

የዋህ ልቤ እንግዲህ ቅመሰው
ለምን አመንክ የማይታመን ሰው
ስትከተላት በልጣህ በቅኔ
ይህ ይመጣል መች አልክ ያኔ .... ጸሃዬ ዮሃንስ በአንድ ዜማው ላይ የተጫወታት ስንኝ ናት
ጸሃዬ መቼም ለዜማ የተፈጠረ ይመስለኛል ዘፈንን ማሳመር ማንቆላጰስ መኳል ለስላሳ ዜማዎችን በተለይ መሞሸር ይችልበታል ::
ከበፊትም ጀምሮ መቼም ባላፈቅረውም እንደምወደው አልክድም ለዜማዎቹ ብዙ እንደሚጨነቅና ግዴለሽ እንዳልሆነ ከብዙ ነገሮቹ መረዳት ይቻላል::
ከዚህ በፊት እናንተም እንደምታስታውሱት ሃረር ጂጂጋን አልፌ ቀላፎና ጎዴ በረሃ ሳለሁ አንዳንድ ነገር አጫውታችሁም ነበር ታዲያ አንዱን ቀን ከድሬደዋ ወደ አዲስ አበባ ስመለስ አንድ የሚወስደኝ ወዳጅ አገኘሁና በአዲስ አይሱዙ ጋቢና ውስጥ ከነጂውና ከባለቤቱ መሃል ተፈደልኩ :
ደንገጎን በዝግታ ስናሻቅብ በመሃላችን የነበረው ሳቅና ጨዋታ በጣም ምቹ ነበር ቁልቢ ገብርዔል እንደደረስን ትራፊኩና የአይሱዙው ባለቤት ፍቅራቸው አላለያይ ስላላቸው እዚያችው ትንሿ ከተማ ቁርስሳችንን አስተካከልንና ሸንተረሯን ተሻግረን የለጋ ልምጭ የሚመስለውን ጠይም ሰባሌ (ሰባሃሌ) አንዳንድ ጥቅል ለየራሳችን ፈታን:: (ያኔ ሰባሌና አሰቦት ያላቸው ኃይል ከአወዳይ ይልቅ ታዋቂዎችም ነበሩ)
አሁንም ጨዋታችን አልቆመም ቀስ እያልን ግን ካራሚሌ ቦረዳ ሂርና አሰበተፈሪን ወዘተ ወደኋላችን እየተውን ስንመጣ ሁላችንም በየዝምታችን ውስጥ እየገባን ወደየራሳችን መስመጥ ጀመርን
ይህኔ ነበር ጸሃዬ ዮሃንስ አሸንፎን ልባችንን ከፋፍቶ ገብቶ እንዳሻው ሲያደርገን ናዝሬት ያደረሰን ናዝሬት ደርሰን መንቀሳቀስ ባንጀምር ምን እንደምንሆን አላውቅም ነበር::
ታዲያ ሶስታችንም ዓይኖቻችን ከልክ በላይ ፈጠው በቃ ልዩ ፍጥረቶች መስለን ነበር መቼም ሀረሬዎች ብልሆችም ናቸው ሾፌሩ ይሄ ምርቃና ቶሎ መሰበር አለበት ብሎ እዚያው ናዝሬት መዓት ሜታ ድራፍትና በደሌ ቀምቅመን ነው እንደገና መነጋገር የጀመርነው ::
እንደዚያም ሆኖ አዲስ አበባ ናፍቆቴ ስር ውሽቅ ብዬ ተኝቼም ዛሬ ምን ዓይነት ነገር ነው የቃምከው ተብዬ ተጠይቄያለሁ ይህንን ሁሉ የማወራው የጸሃዬን ታሪክ ለመናገር ሳይሆን የዘፈኑን ጉልበተኛነት ለማስታወስ ነው::
ምርቃና ሲጀምር የምትወዱትን ሙዚቃ ወይንም ልብን የሚነካ ለስላሳ ሙዚቃ መስማት ከባድ ነው ዳሩ አሁን መቃም ከተውን ወዲህ ሙዚቃውም ፖለቲካ ሆኖ ነው የሚሰማን ነው መሰለኝ ሁሉንም ተውነውኮ አቦ !
እኮ ለምን ጸሃዬን አነሳኽው አትሉኝም ?
ጸሃዬን ያነሳሁትማ
የዋህ ልቤ እንግዲህ ቅመሰው
ለምን አመንክ የማይታመን ሰው
ብሎ ስለዘፈነልኝ ስህተቱን ለልቤ ስለነገረልኝ ነው
ውድ ራስብሩ መቼም እኔና አንተ ቀኝና ግራ እጅ ነበርን....... ይቅርታ ነን ::
ሥንታየሁ ወልዴ ኮሌጅ ገብታ ለምረቃዋ እንዘጋጅ አልክ ?
ኸረ እንደው በፈጠረህ ያ ትንሽዬ ልጅ ከፊት ለፊት ቁጢጥ ብሎ በሁለት እጆቹ አገጩን ይዞ የሚታየው ምን ደረሰ ?
ግን አንዳንዴ አይገርማችሁም ?
ደሃ ነው ጥሩ ልብ ያለው ? ወይንስ አንድ ሰው ሃብታም የሚሆነው ጥሩ ልብ ስለሚኖረው ነው ?
የዚህ ቅኔ ባይፈታልኝም እኔና ልቤ አንድም ቀን እኩል ሆነን አናውቅም እንስማማለን ግን አንመሳሰልም::
ስለዚህም ልቤ ስህተትን ይሰራል የማይችለውን አደርጋለሁ ይላል
በተለይ የማይታመነውን ራሱን ያምናል !
በውነት እነዚህን ልጆች ከሜዳ አንስቶ አስተምሮ ለኮሌጅ ማብቃት ማለትኮ ከራስ በላይ ነው
እማማ ይህንን ነገር ባነሳሁላት ቁጥር እጄን ይዛ ስትመርቃችሁ አንዳንዴ እንባ ይተናነቀኛል
ድህነትን አሳምራ ስለምታውቀው የልጅን ነገር ጠንቅቃ ስለምታውቀው በነገርኳት ጊዜ ሁሉ ትደሰታለች::
ራስብሩ ሰኞ መልክትህን እንዳየሁ ወዲያው ተነስቼ እማማ ወዳለችበት ሄድኩ
ሁኔታውንም አንድ በአንድ አስረዳኋት .
አንዳንዴ በጣም የምትወዱትን ሰው ስታዩ ወይንም ድምጽ ስትሰሙ በተለይ የእናት ወይንም የአባት አልቅስ አልቅስ የሚላችሁ
ጊዜ የለም ? ሁላችሁም ውጪ ሃገር ስላላችሁ ይቺን ነገር እንደምታውቋት አልጠራጠርም::
ታምኑኛላችሁ እከሌ እከሌ ብላ ነው ያስታወሰቻችሁ ደጉ ሰው መቼም ደግ ነህ
ማህሙዶ ዓደም ስለሺ ተስፋዬ ዝናዬ አሰጋኸኝ ........... እዚህ ያላችሁትን መጥራት አያስፈልገኝም
በረከት በዘር ማንዘራችሁ ይሁን !
እልፍ ሁኑ እማማ በኦሮምኛ ስትመርቅ ከአንደበቷ የሚወጣው ዜማዊ ስልት ያስለቅሳል ::
ቀኝ እጄን ይዛ በልጅ ልጆቻችሁ በትውልዳችሁ ሁሉ ተባረኩ
እጆቻችሁ ይለምልሙ የወለዳችኋቸው ጸጋ ይልበሱ
የአሮጊት ምርቃት ይደርሳል አሜን በሉ ብላለች ሳትረሱ አሜን በሉ !
ራስብሩ ተባረክ !የግልዬ ተባረኪ ! ሽልንግዬ ተባረክ ! ባለሱቅ ተባረክ ! ሞፊቲኮ ተባረክ ! አንፈራራችንተባረክ ! ኦዶኪያ ተባረክ !
የደጋግ ልጆች ናችሁ በዘመናችሁ ሁሉ ሙሉ ሁኑ !
የኔን ደስታ መናገር አልችልም
ተወልዳችሁ ያደጋችሁበትን ቀርቶ ወልዶ ያሳደገውን ዞር ብሎ የሚያይ በጠፋበት ዘመን
በህጻንነታቸው መንገድ የወደቁ ልጆችን አንስቶ ወደተማሪ ቤት ሰዶ አስተምሮ ለኮሌጅ ማብቃት
ምን ማለት ነው ? ከዚህ የበለጠ ምን ትልቅ ነርስ ይኖራል ?
ማን እንዲህ ያደርጋል መንግስት ? የሃይማኖት መሪ ? የፖለቲካ መሪ ? ማንም !
እኔ በበኩሌ ከህመሜ እንደተፈወስኩ ደስታ በደምስሬ ሲወራጭ ነው የተሰማኝ
ምክንያቱም ትንሽ ዝምታ በዝቶብኝ ስለነበር እንዳላነሳውም አቅም ስለሌለኝ እንዳልተወውም ሃላፊነት ስለተሰማኝ እንደው ብቻ ፈራ ተባ
እያልኩ በነበረበት ሰዓት ይህንን ነገር ስሠማ ድንጋጤና ደስታ ተቀላቀለብኝ::
ሞፊቲኮ አንተም የተሰማህን ደስታ ከመልክትህ አይቻለሁ እንግዲህ ፈጣሪ የድሃ አምላክ ጅማሮውን ይፈጽምልን ! እናንተ ደጎች የክብረመንግስት ልጆች
ብሩክ ናችሁ ብሩክ ሁኑ ራስብሩ የግልዬ ባለሱቅ ሞፊቲኮ አንፈራራችን ኦዶ ኪያ ሽልንጋዬ ወቤ(ጃሎ) ጎስሽክም ጅግሳ ጀምጀምዬ ቅሩንፉድዬ
ኮሎኔል ልጅ ተድላ ከንቲባ ንጉስ ጦና ፈለገ ብርሃን ባጠቃላይ ስማችሁን ያልጠቀስኩ ካላችሁ የጀምጀም ልጆች
በውነት ኮራሁባችሁ እወዳችኋለሁ ሌላ ምን እላለሁ
እኔ ግን በቃሌ ስላልተገኘሁ የራሴን ልብ ወቀስኩት እናንተን ግን አመሰገንኳችሁ !

ቸር ያቆየን ወዳጃችሁ አደቆርሳ ዘሃገረ አዶላ

Post Reply

Return to “የጀምጀም ልጆች መገናኛ”