እናቴ፣ መንግስቷ እና መሬቷ [የአቤ ቶኪቻው ጨዋታ]

ግጥሞች፣ታሪኮች፣ፎቶዎች፣ሙዚቃዎች
Poems,Short stories, graphics,pictures,musics,Technology
User avatar
zeru
Leader
Leader
Posts: 952
Joined: 19 Aug 2009 17:01
Contact:

እናቴ፣ መንግስቷ እና መሬቷ [የአቤ ቶኪቻው ጨዋታ]

Unread postby zeru » 16 Feb 2012 11:09

እናቴ፣ መንግስቷ እና መሬቷ [የአቤ ቶኪቻው ጨዋታ]
ወዳጄ እንዴት ሰነበቱልኝ…
እውነቱን ለመናገር በየሳምንቱ ለሀገሬ አንድ ለእናቱ የሆነችው ፍትህ ጋዜጣ ላይ በየሳምንቱ ብከሰት ደስታዬ ወደር አልነበረውም። ነገር ግን ጋዜጣዋ የምትውለው “አርብ አርብ ይሸበራል እየሩሳሌም” በተባለበት አርብ ቀን በመሆኑ የኔ ነገር ደግሞ በተለይ ከዚህ ከስደት በኋላ አንዳንዴ የምፅፋቸው ፅሁፎች “ፆም የነካካቸው” እየሆኑብኝ የጦም ሀገር ለሆነችው ኢትዮጵያዬ አልሆን እያለኝ ስተወው፤ ስተወው ቆይቼ በዛሬው አርብ ግን በተቻለኝ አቅም ጦም ያልነካካው ጨዋታ ይዤ አዲሳባ ብቅ ብዬ ነበር።
እስቲ ዛሬ ሁላችንም ፆም ያልነካካው ጨዋታ እንቃመስ…!
እኔ የምለው ሙስሊም ወዳጆቼ “ያ ነገር እንዴት ሆነ…? እንትን ተደረገ ወይስ እንትኑ አሁንም ቀጥሏል?” ምን ላድርግ ብለው ነው ወዳጄ… በግልፁ መጅልሱ አሁንም እየነጀሳችሁ ነው? ወይስ ሊወርድ ተቃርቧል? አሕባሽስ… “ላሽ” አለ ወይስ “ባስ” አለ? ብዬ ልጠይቅ ነበር። ነገር ግን እንዲህ ብሎ በግልፅ መጠየቁ መንግስቴን እንዳያስከፋብኝ ሰግቼ ትቼዋለሁ። (በቅንፍ የቃላት መፍቻ፤ “ላሽ” ማለት በአራዳ ቋንቋ እልም ብሎ መጥፋት ማለት ሲሆን “ባስ” አለ ማለት ደግሞ ያው ባሰበት ወይ? ለማለት ነው…)
ይሄ “አሕባሽ” የሚባለው የሙስሊም እምነት አስተምሮ ከኦርቶዶክሶች “ተሀድሶ” እምነት ጋር እኩያ መሆኑን አዋቂ ወዳጆቼ አውግተውኛል። እነዚህ ወዳጆቼ እንደሚጠረጥሩት ከሆነ (መቼም መጥርጠር ነውር የለውም…?) መንግስት ነብሴ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በሙሉ “አሕባሽ” ቢሆኑለት ደስታው ወደር የለውም አሉ።
እኔማ ለመንግስቴ ጥብቅና ቆሜ አይሆንም ብዬ ተከራከርኩ… እውነቴን ነዋ መንግስታችን የራሱ የሆነ የኮራ የደራ ሀይማኖት አለው “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” የሚባል… እና ታድያ እንዴት በሰው እምነት ውስጥ ጣልቃ ይገባል ብዬ ልጠረጥር እችላለሁ? ህገ መንግስቱም ሀይማኖትና መንግስት ለየቅል መሆናቸውን አበክሮ ተናግሯል።
በርግጥ “እኛ ሀገር ብዙ ግዜ የሚከበረውም ሆነ የሚፈራው ህገ መንግስቱ ሳይሆን መንግስቱ፣ መንግስቱም ሳይሆን፤ የመንግስት ባለስልጣናቱ ናቸው።” እየተባለ ይነገራልና “ጨላጣው መንግስት ህገመንግስት ለማክበር ሲል፤ በሀይማኖት ውስጥ ጣልቃ አልገባም ብሎ አፍን ሞልቶ ለመናገር ከባድ ነው” የሚሉ ብዙዎች ናቸው። (ልብ አድርጉ ይህ የሰዎች አስተያየት ነው እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ዝም ነው የምለው… ለራሴ ነገር ይገንብኛል!)
ባለፈው ሳምንት ውስጥ የመጅልሱ ተቃዋሚዎች የመንግስት አንጀት ቢራራ ብለው፤“አባይ ይገደባል መጅልስ ይወገዳል!” ሲሉ ተቃውሞ ሲያሰሙ ነበር። ከዚህ እንደምንረዳው መንግስቴ በእመነቶች ጉዳይ የመነካካት ነገር እንዳለው ነው። እንዲህ ከሆነ የመጣው ይምጣ ብዬ እናገራለሁ… በሀይማኖት ጉደይ ከአባይ ይልቅ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ቢገደብ የተሻለ ነው…! እላለሁ። (ባይሆን ካጠፋሁ ካአሁኑ ይቅርታ ልጠይቅ። በኋላ ሰዎቹን ስራ አስፈትቼ ለኔ ይቅርታ ሲፅፉ እንዳይውሉ! (ይሄ ንግግር ራሱም ጥፋት ከሆነ “በቅድስት” አብዮታዊ ዴሞክራሲ ስም ይቅር ይበሉኝ ብዬ አቡኑን እለምናለሁ…))
በነገራችን ላይ ሙስሊም ወንድሞቻችን “አይዟችሁ አላህ ይርዳችሁ! እናንተ ቤት ያለው ችግር እኛም ቤት አለ እና አንድ ቀን የጋራችን የሆነው ፈጣሪ ነገሮችን ያደላድላል…!” ሲሉ ክርስቲያን ወንድሞቻችሁ መልዕክት አስተላለፈውላችኋል።
አሁን ወደ ዋናው መስመር እንመለሳለን…
እናቴ መሬቷ እና መንግስቷ
መቼም ስለ እናቴ ማንነት አላስታውሳችሁም። እርሷ ማለት አሽሟጣጭ ጎረቤት እና ወንድሜ ሳይቀር “መንግስት መስተፋቅር አሰርቶባት ቀበሌ ለቀበሌ ያንከራትታታል!” እያሉ የሚያሸሙሯት አፍቃሬ ኢህአዴግ ናት። እራሷም ብትሆን ምቀኛን ደስ አይበለው በሚል መልኩ ከመንግስቷ ጋር በጥብቁ የተቆራኘች ናት። ሌላው ቀርቶ የተናገረችውን ለማሳመን እንኳ “ከኢህአዴግ ይነጥለኝ” ብላ የምትምል ታማኝ የኢህአዴግ ወዳጅ።
በእውኑ ከእናቴ በቀር እንዲህ ብሎ በድርጅቱ ስም የማለ አባል ከዚህ በፊት አልገጠመኝም። የእርሷ ፍቅር ለብቻው ነው። እኛ ልጆቿ ድሮ ስናውቃት ከመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዮሃንስ ረዕይ” ን ታነብ የነበረችውን እንኳን ትታው “አዲስ ረዕይ” የተባለውን ኢህአዴግ መፅሔት ማንበብ ከጀመረች ስንት ግዜዋ…?
እናቴ መንግስት በተለያየ ግዜያት የሚያወጣቸው አዋጆች በሙሉ ድግሷ ናቸው። ዘወትር አዋጁ በወጣ ቁጥር መላው የቤተሰቡን አባል ሰብስባ ታወያየናለች። (“መላው” ያልኩት እኔ ወንድሜ እና እርሷን ነው።) ወንድሜ የቤተሰቡ ሀላፊ ሆናበት ነው እንጂ ከየ አዋጆቹ በኋላ የሚደረግ ውይይት ላይ ባይሳተፍ ደስታው ነው። ዘወትር በውይይቱ መጀመሪያ የሚጠይቀው ጥያቄ፤ “በፀደቀ ጉዳይ ላይ መወያየት ፋይዳው ምንድነው?” የሚል ነው። እናቴም “… መልካም በጣም ገንቢ ጥያቄ ነው…” ብላ ትጀምርና “የውይይቱ ጠቀሜታ አሌ የሚባል አይደለም… ቢያንስ ቢያንስ በአዋጁ ላይ ግንዛቤ እንድንጨብጥ ያደርገናል!” ትላለች። ወንድሜም ቱግ ብሎ “የእኛ ችግር ገንዘብ እንጂ ግንዛቤ አይደለም…!” ብሎ ይጮሀል። እናቴም “አካሄድ… አካሄድ… ልብ አድርጉልኝ… ግራ ቀኝ…” ብላ ከግራ እኔን ከቀኝ ራሱ ተቃዋሚ ወንድሜን ታያለች።
አንዳንዴ ሳስበው እናቴ ከእኛ ጋር የምታደርገው ውይይት በቀጣይ ለሚኖራት የቀበሌ ስብሰባ እንደ ልምምድ የምትቆጥረው ይመስለኛል። ያው እኛም የቤተሰቡ አስተዳዳሪ እንደመሆኗ መጠን “እምቢኝ አንሰበሰብም!” ብንላት የሚፈጠርብንን ጦስ ስለምናውቀው ሁሌም “ለልምምዱ” ተባባሪ ነን። እንኳን ሌላው ቀርቶ “እናቴ ዛሬ ስላመመኝ በውይይቱ ላይ አልገኝም” ብንላት “ከታወቀ ሃኪም ማስረጃ ይዘህ ና…!” ታላለች እንጂ አትለቀንም። እኛም ይህንን ስለምናውቅ እንሰበሰባለን፤ እርሷም ቀበሌ ሄዳ በአዋጁ ላይ ውይይት ስታደርግ፤ “ከልጆቼ ጋር በጉዳዩ ላይ ተወያይተንበት ነበር… በእውነቱ በዚህ አጋጣሚ ልጆቼ ያለ ምንም ተቃውሞ በሙሉ ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ውይይት ስላደረጉ ላመሰግናቸው እወዳለሁ።” ብላ አመስግናን፤ ሌሎች ተሳታፊዎችም የእርሷን ልምድ እንዲቀስሙ እንደምትመክር ሰምቻለሁ።
ከዚህ በፊት በተለያዩ አዋጆች ላይ ተወያይተናል። ያው እንደሚታወቀው ሁሌም አዋጆቹ ከፀደቁ በኋላ ነው ውይይቱ። ቢሆንም ግን አንዴ ውይይቱ ከተጀመረ በኋላ የጦፈ ክርክር ይደረግበታል። አሁን በቅርቡ “ፀረ ሽብር” አዋጁ ላይ ያደረግነው ውይይት ለዚህ እንደ ማሳያ ነው። በእናቴ እና በወንድሜ መካከል ታላቅ ፍጭት ሆኖ ነበር። ዋናው ጥያቄ የነበረው በውጪ ሀገር ከሚገኘው ወንድሜ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መገናኘት እንችላለን ወይስ አንችልም? የሚለው ጉዳይ ነበር። አዋጁ “በሽብርተኝነት ከተፈረጀ ግለሰብ ወይም ድርጅት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ማድረግን” ይከለክላል። ታድያ ወንድሜ ሽብርተኛ ነው ወይስ አይደለም? ይሄ ነበር ከባዱ ጥያቄ። በአንድ ወቅት ወንድሜ በአንድ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተነሳውን ፎቶግራፍ ልኮልን ያውቃል። ታድያስ…? መንግስትን የተቃወመ አንድ ግለሰብ ሽብርተኛ ከመባል ያመልጣል ወይስ አያመልጥም?
በእውነቱ በወቅቱ እናቴ ይሄንን ጥያቄ ለመመለስ አቅም አልነበራትም። በመጨረሻ ግን “ብልሃት አትጪ” ሲላት አንድ ዘዴ አሰበች። እናም “በሰልፉ ላይ የተነሳውን ፎቶግራፍ አምጣልኝ” ብላ አዘዘችኝ። እኔም ታዛዥነት ያደግሁበት ነውና አመጣሁ። ፎቶውን እንመርምረው… አለች ተመረመረ…
ባንዲራ ለብሷል። ባንዲራው ኮከብ አልባ ነው። ጣቱን በ ”ቪ” ቅርፅ ቀስሯል። እናቴ ፎቶውን “ልብ አድርጉልኝ” እያለች አሳየችን… “ወንድማችሁ ኮከብ አልባ ባንዲራ የያዘው፤ የባንዲራ አዋጁን ደንብ በመተላለፍ ነው…” አለችን። አዋጁ ኮከብ የሌለው ባንዲራ ይዞ አደባባይ መውጣት እንደሚከለክልም ነገረችን። እኔ “ገባኝ” ለማለት አናቴን ስወዘውዝ፤ ወንድሜ ደግሞ “ያሳዝናል” ለማለት አንገቱን ይነቀንቃል። እናቴ ቀጠለች “ጣቱንም ቢሆን የቀሰረው… ጠቅላይ ሚንስትራችን ከዚህ በኋላ ጣቱን የቀሰረ ጣቱ ይቆረጣል ብለው ካወጁ በኋላ ነው…” እናም መጀመሪያ፤ ጠየቀችን “ከዚህ የበለጠ ሽብር ከየት ይመጣል?” አለችን። ቀጥሎም ወሰነች። ወንድሜ ከሽብር ጋር አብሮ የሚኖር ተብሎ ተፈረደበት። እናም “ከእርሱ ጋር የተደዋወለ፣ ፖስታ የተለዋወጠ፣ ስለ እርሱ በህልሙ ያየ፣ ህልሙንም በበጎ ያስተረጎመ፣ ወይም የተረጎመ፣ ወይም ሊተረጉም ያሰበ፣ እርሱን የናፈቀ፣ ሰዎች ሲናፍቁት በቸልታ የተመለከተ፤ በሽብር ሴራ ሊጠየቅ” በአንድ የድጋፍ ድምፅ በአንድ ተዓቅቦ እና በአንድ የተቃውሞ ድምፅ ፀደቀ።
እንግዲህ እናቴ ለመንግስት አዋጆች ያላት ታማኝነት የገዛ ልጇን አሳልፋ እስክትሰጥ ድረስ የዘለቀ ነው። “አንድያ ልጁን አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ ወደደን” እንዲል መፃፍ እርሷም ኢህአዴግን ይህንን ያህል ወደደችው…
አሁን ግን በእናቴ እና በመንግስቴ መካከለ አንድ ሳንካ የገባ ይመስላል። እናታችን እንዳማንኛውም ኢትዮጵያዊ በርስቷ ሲመጡባት አትወድም። አባቴም ድሮ “በሚስቴ እና በርስቴ አልደራደርም!” ይል ነበር። እናቴም አባታችን ከሞተ በኋላ “በመሬቴ እና በመንግስቴ አልደራደርም!” ትለን ነበር። አሁንስ?
አሁን አንድ አዋጅ ወጥቷል… ኢትዮጵያችን በኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን በአዋጆችም ብዛት ታላቅ እድገት ያሳየች ሀገር ሆናለች። እኔም እሰይ እላለሁ። ወንድሜ ግን በየ አዋጁ ስብሰባ ስለሚጠራ አዋጅ ወጣ በተባለ ቁጥር ፊቱን ያጨፈግጋል።
ዛሬ እናታችንም ፊቷ ላይ ግራ መጋባት ይነበባል። በአንደኛ ልጇ ላይ እስክትፈርድ ድረስ የወደደችው መንግስቷ ዛሬ አስጨናቂ አዋጅ አውጥቶባታል። “መሬትሽን መሸጥ መለወጥ አትችይም…” የሚል አዋጅ። ስብሰባ ተጠራን… ወንድሜ እያጉተመተመ እኔ ግን ምንም ሳልል በስብሰባው ላይ ተገኘን።
ዛሬስ እናታችን እንደ ፖለቲከኛ ሳይሆን እንደ እናት ታወራን ጀመር… አዋጁ የእውነት እንዳሳሰባት ታስታውቃለች። “ልጆቼ ክፉ ቀን በመጣ ግዜ ሸጠን፤ ለእኔም መጦሪያ ለእናንተም መሯሯጫ ይሆናችሁ ይሆናል ያልኩት መሬት አዲስ አዋጅ ወጥቶበታል… ምን ትመክራላችሁ?” ስትል ጠየቀችን። እኔም እናቴን በሚያስተዛዝን ድምፅ “ከትላንት በስተያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር መሬታችን እንደማይነካ ነግረውን የለም እንዴ?” ስል ጠየቅሁ… ወንድሜ ግን ቆጣ ብሎ “የመጀመሪያው ነገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚታመኑ ሰው አይደሉም…!” ሲል ጀመረ። እናቴ ሌላ ግዜ ቢሆን “አካሄድ…አካሄድ… ግራ ቀኝ ልብ አድርጉልኝ” ብላ ታስቆመው ነበር ዛሬ ግን ምንም አላለችም። ወንድሜ ሲቀጥልም “የሆነው ሆኖ” ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉትን ደገመልን። “በርግጥ ነባር ይዞታ አይነካም… ብለዋል። በርግጥ ነባር ይዞታ ወደ ሊዝ አይዞርም… ብለዋል። ነገር ግን ነባር ይዞታ ሲሸጥ ወደ ሊዝ ይዛወራል… ብለዋል። ታድያ በደህናው ግዜ ይቅርብኝ ብለን የገዛነውን መሬት ሸጠን ካልተጠቀምን የመሬቱ ባለቤቶች እኛ ነን ማለት እንዴት ይቻላል?” ሲል ሁለታችንንም በጥያቄ አየን። ለመጀመሪያ ግዜ እናታችን ወንድማችን ሲናገር ከልቧ ሰማችው። ቀጠለ ወንድሜ “…በእውነቱ ከሆነ ይህንን መሬት ሲቸግረን ሸጠን መጠቀም ካልቻልን… እኛ የመሬቱ ዋርዲያ ነን እንጂ ባለቤት አይደለንም።” አለን። እናቴ ዝም አለች። ዝም…! የዝምታ ትርጉሙ ምን ነበር? ተቃውሞ? ወይስ ድጋፍ?
እናቴ በመንግስቷ ላይ አኩርፋ ይሆን? እንጃ…!
በመጨረሻም
ልጆችዎን መግቡ
ሰሞኑን በኢቲቪ አንድ ሲንግል ተለቋል። (ለነገሩ ቆይቷል መሰል እኔ ግን ሰሞኑን ነው ልብ ያልኩት) በርካታ ታዋቂ አርቲስቶች የተሳተፉበት ይህ ሲንግል “ልጅን መግቡ በእድሉ ያድጋል አትበሉ!” ይላል። በክሊፑም ቋንጣ ስጋ፣ እንቁላል፣ ዶሮ እና የመሳሰሉት የደህናው ግዜ ምግቦች የአሁኑ ግዜ ተረቶች እንደዋዛ ያልፋሉ። የዘፈኑ ሀሳብ ለልጅዎ እነዚህን በሙሉ አብሉ መሆኑ ነው… ጥሩ ነው። እንደዚህ ለህዝብ ማሰብ እንደዚህ ለአመጋገባችን መጨነቅ መልካም ነው… ነገር ግን ዘፋኞቻችንን አንድ ትያቄ መጠየቅ እፈልጋለሁ…?
ውድ ሙዚቀኞቻችን እስከ መቼ ዝም ብሎ ግጥም ሲሰጣችሁ ቆማችሁ እየተውረገረጋችሁ ታዜማላችሁ? ስለምን የአመክንዬ ጥያቄ አታነሱም? ይህ ዘፈን በእውኑ የተሟላ እንዲሆን የማድረግ ሃላፊነት የናንተ የሙዚቀኞቹ አልነበረምን? ይህው እነ ንዋይ “እንባ ከቅንድቤ ከአይኖቼ ሲታፈስ” ብለው ዘፍነው አይደል እንዴ… እስከ ዛሬ ድረስ “እንባ ከቅንድብ እንዴት ይታፈሳል?” የሚለው ትችት ሰለባ የሆኑት? እናንተም ግጥሙን ማንም ይስጣችሁ ማን ትውልድ ይጠይቃችኋል… (አይዟችሁ አትደንግጡ… ያን ያህል የከረረ ነገር እንኳ የለም) ነገር ግን “መግቡ በእድሉ ያድጋል አትበሉ…” ብላችሁ ዝፈኑ ስትባሉ… “ሰዉ ምንጩን የጠየቀን እንደሆነ ከየት አምትጣችሁ መግቡ ብለን እንመልሳለን?” ማለት ነበረባችሁ። የሆነ ሆኖ አስዘፋኞቹን እጠይቃለሁ… “መግቡ… በእድሉ ያድጋል አትበሉ…” እሺ ግን “ከየት አምጥተን?”
ወዳጄ አሁን እንሰነባበት
እስቲ አማን ያሰንብተን!
abeto2007@yahoo.com


Return to “Ethio Art and Culture..ኢትዮ ጥበብ ፤ስነ ጽሁፍ ፤”