የአውሮፕላኑ አደጋ ሪፖርት ቀረበ

Ethiopian airlines related News, Info, Experience , Comment , Anything
Guest

የአውሮፕላኑ አደጋ ሪፖርት ቀረበ

Unread postby Guest » 08 Mar 2010 19:53

የአውሮፕላኑ አደጋ ሪፖርት ቀረበ

"የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት በመሆኑ ይህ ነው ማለት አይቻልም"
አቶ ግርማ ዋቄ

በሊባኖስ ዋና ከተማ ከቤይሩት አቅራቢያ ድንገተኛ አደጋ የደረሰበትን የኢትዮጵያን አየር መንገድ ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን የአደጋ መንስኤ ለማወቅ፣ ጥናት የሚያካሂደው መርማሪ ቡድን ያዘጋጀው የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት ሪፖርት፣ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት በዚህ ሳምንት ቀረበ፡፡ አየር መንገዱ እስከአሁን በቀረበው የምርመራ ውጤት፣ የአደጋው መንስኤ ይህ ነው ብሎ ለመደምደም አያበቃም ብሏል፡፡

በመርማሪ ቡድኑ የተዘጋጀው የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት፣ በሊባኖስ የትራንስፖርት ሚኒስቴር አማካይነት ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን እና ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ከትናንት በስቲያ እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡

ቀረበ ስለተባለው ሪፖርት ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ግርማ ዋቄ፣ መርማሪ ቡድኑ ያቀረበው ሪፖርት በቡድኑ የተሰበሰቡ መረጃዎችን የያዘ ነው፡፡ "ይህ ሪፖርት የመጀመሪያ ደረጃ ነው፡፡ በውስጡ ቡድኑ የሰበሰባቸውን የመረጃ ዓይነቶች ይዟል፡፡ ዝርዝር ጥናት ገና አልተዘጋጀም፡፡ በዚህ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ተሞርኩዞ ማንም ቢሆን፣ የሊባኖስ ባለሥልጣናትን ጨምሮ የአደጋው መንስኤ ይህ ነው ብሎ መናገር አይችልም" ብለዋል፡፡

አደጋው ከተከሰተ ጊዜ አንሥቶ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊዎች የምርመራው ሂደት ሳይጠናቀቅ ስለአደጋው መንስኤ መላምት ከመስጠት የተቆጠቡ ቢሆንም፣ የሊባኖስ ባለሥልጣናት እና የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት በመርማሪው ቡድን ያልተረጋገጡ መላምቶችን ሲያስተጋቡ ቆይተዋል፡፡ አቶ ግርማ በተለይ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለጹት፣ አየር መንገዱ በምርመራው ሂደት እና ምርመራውን በሚያካሂዱት ባለሙያዎች ላይ ቅሬታ የለውም፡፡ ሆኖም አንዳንድ የሊባኖስ ባለሥልጣናት በሚሰጡት አላስፈላጊ ግምታዊ አስተያየቶች አሳዝኗቸዋል፡፡

አሁን የቀረበው ሪፖርት የአደጋው መንስኤ ምን እንደሆነ አይጠቁምም ወይ ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ፣ "ምርመራው ተጀመረ እንጂ፣ አላለቀም" ሲሉ ምላሽ የሰጡት አቶ ግርማ "መርማሪዎቹ ከመረጃ ሳጥኑ እና የድምፅ መቅጃ መሣሪያ መረጃ ወስደዋል፡፡ የአደጋው ሰለባዎችን አስክሬኖች ተመልክተዋል፡፡ እንዲሁም በአውሮፕላኑ ስብርባሪዎች ላይ ምርመራ አካሂደዋል፡፡ አሁን ያቀረቡት ሪፖርት ያሰባሰቡትን መረጃ ዓይነቶች የሚገልጽ እንጂ፣ በተገኙት መረጃዎች ላይ ዝርዝር ጥናት ተዘጋጅቶ ወደ መደምደሚያ ገና አልተደረሰም" ብለዋል፡፡

ከአውሮፕላኑ ጠቅላላ አካል ከባሕር የወጣው ገና ስምንት ከመቶ ብቻ ነው ያሉት አቶ ግርማ፣ 92 ፐርሰንቱ አሁንም በባሕሩ ውስጥ ይገኛል ብለዋል፡፡ በዋና ሥራ አስፈፃሚው አነጋገር፣ "ከመረጃ ሳጥኑ፣ አስክሬኖቹ ከአውሮፕላኑ ስብርባሪ የተገኙት መረጃዎች በባለሙያዎች መተንተን ይኖርባቸዋል፡፡ የዓይን ምስክሮችም አሉ፤ የእነርሱም ቃል በመርማሪው ቡድን መደመጥ አለበት፡፡ አውሮፕላኑ ምን ችግር እንደገጠመው ለማወቅ ሰፊ ጥናት ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ አውሮፕላኑ ችግር ነበረበት ወይ? የጥገና ችግር ነበረበት ወይ? አደጋው የደረሰው በነበረው መጥፎ አየር ጠባይ ምክንያት ነው? ወይስ የሌላ ኃይል እጅ አለበት የሚለውን ለማወቅ ዝርዝር ጥናት መደረግ አለበት፤ ያን ለማድረግ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ትክክለኛውን የአደጋ መንስኤ በእርግጠኝነት ለመናገር ጊዜው ገና ነው፡፡ የተሟላ መረጃ ሳይኖር መናገር ለማንም ተገቢ አይሆንም፡፡"

በኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን የአደጋ መከላከልና ምርመራ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ በአቶ ግርማ ገብሬ የሚመራ የኢትዮጵያ የአቭዬሽን ባለሙያዎች ቡድን የምርመራውን ሂደት ከጅምሩ ሲከታተል ቆይቷል፡፡ ቡድኑ እስከአሁን ወደ አዲስ አበባ አልተመለሰም፡፡ የቡድኑ አባላትን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካልንም፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ያነጋገርናቸው ኃላፊ፣ የመጣውን የምርመራ ሪፖርት የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ባለሙያዎች እየተመለከቱት መሆኑን ለሪፖርተር ጋዜጣ ገልጸዋል፡፡ "ሪፖርቱን በዝርዝር ከተመለከትን በኋላ በተገቢው ወቅት መግለጫ እንሰጣለንም" ብለዋል፡፡

የሊባኖስ ባለሥልጣናት በዚህ ሳምንት የአውሮፕላን አደጋውን ሪፖርትና በሪፖርቱም ዙሪያ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በሲቪል አቪዬሽን አሠራር ደምብ አደጋ በደረሰ ጊዜ በሚዘጋጁት ሪፖርቶች ዙሪያ መጀመሪያ ሪፖርቱን ይፋ የሚያደርገው እና ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጠው፣ አደጋው የደረሰበት አየር መንገድ ወይም የአውሮፕላኑ አምራች ሳይሆን አደጋው የደረሰበት አገር ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ይህን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ፣ የሊባኖስ ባለሥልጣናት የሚሰጡትን መግለጫ ከተመለከቱ በኋላ፣ እነርሱም በፊናቸው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር ጋዜጣ ገልጸዋል፡፡

የሊባኖስ ባለሥልጣናት "የአብራሪዎቹ ጥፋት ነው" የሚሉ ከሆነ የአየር መንገዱ እና የሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣናት በቂ ምላሽ ለመስጠት እና ጉዳዩንም ወደ ሕግ ለመውሰድ እንደሚዘጋጁ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ምንጮቻችን "የሊባኖስ ባለሥልጣናት መግለጫ ከመስጠታቸው በፊት ብዙኅን መገናኛዎቻቸው አስቀድመው "የአብራሪዎቹ ጥፋት ነው" ብለው ሕዝቡን ለማሳመን ቢንቀሳቀሱም እንደዚህ የሚል ነገር ግን በሪፖርቱ ውስጥ አልተካተተም ብለዋል"፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በቦይንግ 737-800 አውሮፕላን በበረራ ቁጥር ኢቲ 409 በደረሰው አደጋ ሰለባ የሆኑ 90 መንገደኞችና የአውሮፕላኑ ሠራተኞች በሙሉ በስክሬኖቹ ላይ በተካሄደ የዲኤን ኤ ምርመራ መለየቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በትላንትናው ዕለት አስታውቋል፡፡ አየር መንገዱ ለሪፖርተር ጋዜጣ በላከው መግለጫ የኢትዮጵያውያኑ እና የሌሎቹንም ዜጐች አስክሬን ወደ የአገራቸው ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጿል፡፡ አየር መንገዱ የአደጋ መርማሪ ቡድኑ ሥራውን አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጾ፣ ምርመራውን ለማጠናቀቅ ግን የሚጐሉ መረጃዎች እንዳሉ በመግለጫው አስታውቋል፡፡ ቡድኑ ሥራውን በመቀጠል ወደ ዝርዝር ጥናት ለመግባት፣ የተጓደሉ ጠቃሚ እና ወሳኝ መረጃዎችን ማግኘትም አለበት ብሏል፡፡ ይሁን እንጂ የጐደሉት መረጃዎች ምን ምን እንደሆኑ ለመግለጽ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡

የምርመራው ሂደት ባልተጠናቀቀበት ሁኔታ ስለአደጋው መንስኤ መናገር ከግምት ያለፈ እንደማይሆን የጠቆመው አየር መንገዱ "ግምታዊ ንግግሮች የተዛቡ እና አሳሳች ናቸው" ብሏል፡፡

የሪፖርተር ጋዜጣ የዜና ምንጮች እንደሚሉት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱን ከተመለከተ በኋላ፣ አሥር ጥያቄዎችን ለመርማሪ ቡድኑ አቅርቧል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሙያዎች፣ የቦይንግ ኩባንያ ተወካዮች እና የሊባኖስ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ባለሥልጣኖች በዛሬው ዕለት ከመርማሪው ቡድን ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩም ምንጮች ገልጸዋል፡፡


Last bumped by Anonymous on 08 Mar 2010 19:53.

Return to “Ethiopian Airlines”