‹‹የነ እንትና ታቦት›› :በ ዳንኤል ክብረት

Life, Health, Religion, Social, General Question
Forum rules
No cursing, bad language and offend other users !
No pornographic images or links!
This forum monitored regularly. We will BAN users without warning for not obeying rules.
እባክዎ የፎረሙን ህጎች ያክብሩ::
selam sew
Leader
Leader
Posts: 554
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

‹‹የነ እንትና ታቦት›› :በ ዳንኤል ክብረት

Unread post by selam sew » 26 Feb 2015 13:50

[left]ዳንኤል ክብረት Image

ዓርብ ዕለት የተከበረውን የአቡነ አረጋዊ በዓል ለማክበር አውስትራልያ አደላይድ ነበርኩ፡፡ እዚያ ከተማ የሚገኝ አንድ የድሮ ወዳጄ በፌስ ቡክ አገኘኝና አደላይድ መሆኔን ነገርኩት፡፡ ‹‹የት እንገናኝ›› ሲለኝ ‹‹ነገ (ቅዳሜ) የአቡነ አረጋዊን በዓል ለማክበር ስለምሄድ እዚያ እንገናኝ›› አልኩት፡፡ ‹‹አንተም እርሱን በዓል ታከብራለህ?›› አለኝ፡፡ በዓይነ ኅሊናየ ራሱን እየነቀነቀ ታየኝ፡፡ ‹‹እንዴት?›› አልኩት፡፡ ‹‹የእነ እንትና ታቦት አይደል እንዴ›› አለኝ የሆነ የኢትዮጵያ አካባቢ ጠርቶ፡፡ ‹‹ማን እንደዚያ አለ?›› ስል ጠየቅኩት፡፡ ‹‹ምን፣ የታወቀኮ ነው›› አለኝ፡፡ እየገረመኝ ተለያየን፡፡

በማግሥቱ በዓሉ ላይ ተገኘሁ፡፡ በዓሉን እኩለ ቀን ላይ ጨርሼ ስወጣ ሌላ የጥንት ዘመዴን አገኘሁት፡፡ ያ ትናንት ማታው ጓደኛዬ እዚህ ከተማ እንዳለ የማላውቅ መስሎት ይኼኛው ነገረኝ፡፡ እኔም ሰው ላለማጋጨት ብዬ ያለኝን ሳልዘረዝር እንዴው በደፈናው ደውዬለት መምጣት አልችልም እንዳለኝ ነገርኩት፡፡ ይኼኛውም እኔ እንዳልነግረው የደበቅኩትን እርሱ ገልብጦ ነገረኝ ‹‹የኛ ታቦት ሲሆንኮ እነ እንትና አይመጡም›› አለኝ ፈገግ እያለ፡፡ ‹‹ማን ነው የእናንተ ታቦት ያደረገው›› አልኩ በአግራሞት›› ‹‹ያው አቡነ አረጋዊ የኛ ሀገር ሰው አይደሉ›› አለኝ የሠፈሩ ሰው ያህል ርግጠኛ ሆኖ፡፡ ወይ ግሩም፣ ይኼ በሽታ ለካ ማናችንንም ሳይለይ በደንብ ይዞናል አልኩ በልቤ፡፡
ጋሽ ግርማ ከበደ ‹‹ሰው የሚጠላውን ኃጢአት ደጋግሞ ይሠራዋል›› ይል ነበር፡፡ ብዙዎቻችን የሌላውን ሰው ዘረኛነት ለመግለጥ የምንጠቀምበት መንገድ ራሱ ዘረኛ ነው፡፡ አሁን እየተጓዝንበት ያለው አቅጣጫ በመካከላችን ምንም ዓይነት የጋራ ነገር እንዳይኖረን የሚያደርግ ነው፡፡ የጋራ ሆነው የቆዩትን ነገሮች እንኳን አሁን አሁን ወደ ራስ መውሰድ፣ አለበለዚያም ደግሞ የሌላው ብቻ አድርጎ ከራስ ክልል ማስወጣት ጀምረናል፡፡ ምንም እንኳን የኔታ እሸቱ ‹‹የጎጥ ጀግና የለም፤ ጀግና ከሆነ የሁላችንም ነው፤ ያለበለዚያ ደግሞ ጀግና አይደለም›› ቢሉም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ምንኖርባትንና የቆምንባትን ኢትዮጵያ ያወቅናት አልመሰለኝም፡፡ ከሰሜን የጀመረ መስቀል ደቡብ፣ ከደቡብ የጀመረ ቆጮ ሰሜን በዘለቀባት ሀገር፤ የኮንሶ የእርከን ሥራ የትግሬ ገበሬ ገንዘብ፣ የትግራይ አምባሻ የደቡብ የቅንጦት ምግብ በሆነባት ሀገር፣ የኦሮሞ ጉዲፊቻ የሁሉም ባህል በሆነባት ምድር፣ ይኼ የእነ እገሌ ብቻ ነው፣ እኛን አይመለከትም ብሎ ለመናገር እንደመድፈር ያለ የአላዋቂ ድፍረት የለም፡፡ ማንኛውም ነገር መነሻ ይኖረዋል፡፡ ዓባይ ከግሼ ዓባይ እንደሚመነጨው፡፡ ነገር ግን መነሻው መድረሻው አይደለም፡፡ ዓባይ ከግሼ ዓባይ ስለመነጨ የጎጃም ቀርቶ የኢትዮጵያ ብቻ ሊሆን አልቻለም፡፡ አዋሳኙ ሁሉ የእኔም ነው ብሎ ሲመክርበት ይኖራል፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ የተጀመሩትን ኦሪትን፣ ክርስትናንና እስልምናን የኛ አድርገን እየኖርንባቸው አይደል እንዴ ? ከአውሮፓ የወረስነውን ኮትና ሱሪ ቂቅ ብለንበት እየተዳርንበት አይደለም እንዴ? በፖርቹጋሎች በኩል ከሜክሲኮ የደረሰን በርበሬ ይኼው የአበሻ መለያ ሆኖ የለም እንዴ፤ የአውስትራልያ ባሕር ዛፍ ኢትዮጵያዊ ሆኖ የለም እንዴ፤ እንዴት ነው ጎበዝ፡፡ ጤፍ ለምግብነት ዋለ የሚባለው ከክርስቶስ ልደት በፊት 5000 ዓመት ቀደም ብሎ በሰሜን ደጋማ ቦታዎች ነው፡፡ ዛሬ ግን ይኼው ድፍን ሐበሻ ባሕሉ አድርጎት፤ ዘልቆም ድፍን ዓለም ሊበላው እየተሻማ ይገኛል፡፡ የሰሜን ነው ብሎ ማን ተወው፡፡ መልካም ነገር ከአንድ ቦታ ይነሣል፡፡ ከዚያም ሌላውም ከባሕሉና እምነቱ ጋር እያዛመደ ይዋረሰዋል፤ ወይም ገንዘብ ያደርገዋል፡፡ ከዚያም የእርሱም ጭምር ይሆናል፡፡ በተለይ በታሪካችን ውስጥ ከአንዱ የተነሣ ነገር ሰፍቶና መልቶ የሌላውም ገንዘብ የሆነበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ እንዲያውም በሚያስደንቅ መልኩ ከመነሻው ጠፍቶ ከመድረሻው የተገኘ ብዙ ነገር አለ፡፡ ከላይ መነሻዬ ከሆነው የአቡነ አረጋዊ ነገር ልጀምር፡፡ አቡነ አረጋዊ ሀገራቸው ኢትዮጵያ አይደለም፡፡ ሮማዊ ናቸው፡፡ በ5ኛው መክዘ ከተሰዓቱ ቅዱሳን አንዱ ሆነው ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡ አቡነ አረጋዊ መጨረሻቸውን በደብረ ዳሞ፣ ትግራይ ቢያደርጉትም በወሎ፣ በጎንደር፣ በጎጃም፣ በሸዋና በደቡብ ታሪክ ውስጥ ግን አሉ፡፡ ደቡብ ጎንደር ውስጥ ጥንታዊው ገዳማቸውና የዝማሬ መዋሥዕት ማስመስከሪያው ዙር አባ አረጋዊ አለ፡፡ ጣና ቂርቆስ፣ አዲስ አበባ አጠገብ የሚገኘው የረር፣ እንዲያውም ከዚያ ተሻግሮ ጋሞጎፋ የምትገኘው ብርብር ማርያም ታሪካቸውን ከእርሳቸው ጋር ያገናኛሉ፡፡ የመጨረሻውና ታላቁ ገዳማቸው ደብረ ዳሞ ስለሆነ የኛ አይደሉም ብለው አያውቁም፡፡ የጎንደር ሊቃውንት በ17ኛውና በ18ኛው መክዘ ለዓመት የሚቆመውን ዚቅ ሲያዘጋጁ ቦታ ከሰጧቸው ቅዱሳን አንዱ አቡነ አረጋዊ ናቸው፡፡ የአቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቱ ድንበር ጠባቂ ሆኖ ሞያሌ ላይ ይገኛል፡፡ ለሁለቱ ኢትዮጵያውያን የምንኩስና መሠረቶች ለአቡነ ተክለ ሃይማኖትና አቡነ ኢየሱስ ሞአ ምንኩስናን የሰጠው ደብረ ዳሞ ነው፡፡ ዋርካው ሲሰፋ እዩት፡፡ እንግዲህ እኒህን ከሁሉም በላይ ሆነው፣ የሁሉም የሆኑትን አባት ነው አንዳች ጎጥ ውስጥ ልንከታቸው መከራ የምናየው፡፡ ልክ አንዳንዶቹ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ከሸዋ ብሎም ከአማራ ጋር ለማያያዝ እንደሚሞክሩት፡፡ እንዲያውም በሚገርም ሁኔታ ገድላቸው የአያቶቻቸውን ጥንተ መሠረት ከትግራይ፣ በኋላም ከዋድላ ጋር ነው የሚያያይዘው፡፡ በኋላም ሥርዓተ ምንኩስናን የፈጸሙት በአምሐራና በሐይቅ እስጢፋኖስ(ወሎ)፣ በስተ መጨረሻም በደብረ ዳሞ(ትግራይ) ነው፡፡ በውስጣቸውም የትግራይ ገዳማትን የመጎብኘት ልዩ ፍላጎት ስለነበራቸው ለብዙ ዓመታት በዚያው በትግራይ እየተዘዋወሩ አገልግለዋል፣ ተሳልመዋልም፡፡ ታላቁንና የሰሜን ኢትዮጵያ የምንኩስና መሠረት ከሆኑት አንዱ የሆኑትን አቡነ መድኃኒነ እግዚእንም አመንኩሰዋል፡፡ እንዲያውም እዚያው ትግራይ ውስጥ ቀንጦራር በተባለ ቦታ(በደቡብ ምሥራቅ ትግራይ?) ለመቅረትና ገዳም ለመመሥረት ፈልገው ነበር፡፡ አያሌ የኤርትራና የትግራይ ገዳማት የምንኩስና ሐረጋቸውን ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት የሚጀምሩትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ እንደ አጭር ማሳያ የዋልድባውን አቡነ ሳሙኤልና የቆየጻውን አቡነ ሳሙኤል መጥራቱ ብቻ ይበቃል፡፡ በጣና ገዳማት የሚገኙት የግድግዳ ላይ ሥዕሎች ሁለቱን አባቶች – አቡነ ተክለ ሃይማኖትንና አቡነ ኤዎስጣቴዎስን ጎን ለጎን ነው የሚሥሏቸው፡፡ ከሰሜን ተነሥቶ ደቡብ መምጣት፣ ከደቡብ ተነሥቶም ሰሜን መሄድ እንዲህ እንዳሁኑ ከባድ አልነበረም፡፡ እነ አቡነ ፊልጶስና አቡነ አኖሬዎስ ነገሥታቱ ሲያሳድዷቸው የተጠለሉት በትግራይ ገዳማት ነበር፡፡ የተጋዙትም ወደ ዝዋይና አርሲ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሠራዔው አቡነ ኤዎስጣቴዎስ እስከ ሸዋ ምድር ድረስ ደርሰው አስተምረዋል፡፡ የአኩስም ጽዮን ካህናት ከዮዲት መዓት ለማምለጥ ወደ ዝዋይ ነበር የመጡት፡፡ ያለ ሀገራችሁ፣ ያለ ክልላችሁ ያላቸው አልነበረም፡፡ በ14ኛው መክዘ በነበረው የሰንበት ክርክር ጊዜ የሞረቱ ዜና ማርቆስ ገዳም መነኮሳት በቦታ ከሚቀርባቸው ደብረ ሊባኖስ ገዳም ይልቅ የኤርትራ ገዳማት የያዙትን አቋም ደግፈው ነበር፡፡ የሙገርን ቅዱሳን ያስተማረው ሐራንኪስ የአኩስም ተወላጅ ሲሆን የቡልጋን ቅዱሳን ያስተማረው ሕይወት ብን በጽዮን ደግሞ የተማረውና የማስተማሪያ መጽሐፉን ያገኘው ከትግራይ ገዳማት ነው፡፡ እንዲያውም ለብዙ ዓመታት በትግራይ ገዳማት ቆይቶ ተምሮ ሲመለስ የተወለደባትን ዞረሬን ባያት ጊዜ ‹‹እንደ ሀገሬ እንደ አኩስም መሰለችኝ›› ነበር ያላት፡፡ በኤርትራ ታላቅ ቦታ ያላቸው አቡነ አብራንዮስ የጎጃም ሁለት እጁ እነሴ ተወላጅ ሲሆኑ፣ በምሥራቅ ጎጃምና በደቡብ ጎንደር ታላቅ ቦታ ያላቸው አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ደግሞ የኤርትራ ተወላጅ ናቸው፡፡ የምሥራቅ ጎጃም ገበሬ በኤዎስጣቴዎስ ከማለ መላሽ የለውም፡፡ የሙገሩ አቡነ አኖሬዎስ በሸዋ የነበረው ገዳማቸው ሲጠፋ በላስታና በደቡብ ወሎ ግን ገዳማቸው አሁንም በክብር አለ፡፡ እንዲያውም ልብሳቸው፣ መስቀላቸው፣ የጸሎት መጽሐፋቸው የሚገኘው ላስታ፣ ዋናው ገድላቸው የሚገኘው ተንቤን ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ አኩስም ቢወለድም ድጓው የሚገኘው ደቡብ ጎንደር ቤተልሔም፣ ዝማሬ መዋሥዕቱ የሚገኘው ደቡብ ጎንደር ዙር አምባ ነው፡፡ አሁን በያሬድ ዜማ ሲዘም ማን አኩስምነቱ ትዝ ይለዋል፡፡ የላስታው ላሊበላ በላስታ ካለው ደብር በላይ በምዕራብ ጎጃም ያለው ይልጣል፡፡ በዚያ ከአምስት በላይ በስሙ የሚጠሩ አድባራት አለው፡፡ በጉራጌ ትልቁን ሐዋርያነት የሠሩት የሰሜን ሸዋው አቡነ ዜና ማርቆስ ናቸው፡፡ በጎንደር ደግሞ ትልቁን ሥራ የሠሩት የጉራጌ ሊቃውንት ናቸው፡፡ በግራኝ አሕመድ ዘመን ከሆነው ጥፋት በኋላ ጎንደርን ሊያቀና የተነሣው ዐፄ ሠርፀ ድንግል ትልቅ ችግር የሆነበት ለጎንደር አድባራት የሚሆኑ ሊቃውንትን ማግኘት ነበር፡፡ በኋላ ግን እነዚህ ሊቃውንት ከጉራጌ ምሑር ኢየሱስ ገዳም ተገኙ፡፡ እነዚህ ‹‹አርባዕቱ ሊቃውንተ ምሑር›› በመባል የሚታወቁት አባ መሰንቆ ድንግል ዘቤተ ልሔም፣ አባ ለባዌ ክርስቶስ ዘዙር አምባ፣ አባ ብእሴ እግዚአብሔር እና መምህር ተክለ ወልድ ዘለገደባ ማርያም ናቸው፡፡ በላይ ጋይንት ደብረ ማርያም የሚገኘው ሃይማኖተ አበው ‹‹ዐርባዕቲሆሙ ኅቡረ፣ ቃላቲሆሙ ሥሙረ – አራቱም አንድ ነበሩ፣ ቃላቸውም የሠመረ ነበረ›› ይላቸዋል፡፡ እነዚህ ሊቃውንት ነበሩ እየተማከሩ ጎንደርን እንደገና አቅንተው የሊቃውንት መፍለቂያ ያደረጓት፡፡ በጎንደር ከተማ የዘር ነገር የማይነሳው ለዚያ ይሆን? ከጎንደር ሳንወጣ ዛሬ አደባባይ ኢየሱስ የሚባለው ቤተ ክርስቲያን ታቦት ጥንት የነበረው ከምባታ ነበር፡፡ (በገድለ ተክለ ሃይማኖት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ አካባቢው ባደረጉት ጉዞ መጀመሪያ የተከሉት ታቦተ ኢየሱስን መሆኑ ይናገራል፤ ምናልባት እርሱ ሊሆን ይችላል) በግራኝ ጊዜ በተፈጠረው ስደት ካህናቱ ተሰደዱ፡፡ ታቦቱንም በአንድ ቦታ ሠረወሩት፡፡ የመከራው ጊዜ ሲያልፍ ደብሩን እንደገና ቢደብሩትም ታቦቱን ግን ማግኘት አልቻሉም፡፡ በዐፄ ሠርፀ ድንግል ዘመን አባ ንዋይ የተባሉ አባት ወደ ከምባታ ወርደው ታቦቱ ያለበትን ቦታ ለ47 ዓመት ሲፈልጉ ቆይተው በ1570 ዓም አካባቢ አገኙት፡፡ ወደ ንጉሡም ይዘውት መጡ፡፡ ዐፄ ሠርፀ ድንግልም ያመፀውን ባሕረ ነጋሽ ይስሐቅንና ቱርኮችን ለመውጋት በዝግጅት ላይ ስለነበሩ በ1572 ዓም ደንቢያ ላይ እያሉ ከአባ ንዋይ ጋር ተገናኙ፡፡ በዚህ ጊዜ የባሕረ ነጋሽ የትዕቢት መልእክት ከሁለት ጥይት ጋር መጥቶላቸው ነበርና አንዱን በታቦተ ኢየሱስ፣ ሌላውን በግምጃ ቤት ማርያም ላይ አድርገው እንዲጸልዩበት አዘዙ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ታቦተ ኢየሱስ ከንጉሡ አልተለየም፡፡ በ1572 ረዳዒ የተባለውን የቤተ እሥራኤል መሪ፣ በ1579 ጎሼን ለመውጋት ሲዘምቱ አብሮ ነበረ፡፡ በኋላ በዐፄ ፋሲል ዘመን አደባባይ ኢየሱስን ሠርተው ታቦቱን በዚያ አኖሩት፡፡ ይኼው ከከምባታ መጥቶ ጎንደር ላይ ተተክሎ ይኖራል፡፡ ልክ ወሎ መካነ ሥላሴ የነበረውና በግራኝ ተቃጥሎ ፍራሹ የሚታየው የመካነ ሥላሴ ታቦት አሁን አራት ኪሎ ሥላሴ ካቴድራል እንደሚገኝው ማለት ነው፡፡ የቁልቢ ገብርኤል ታሪክ ከአኩስምና ከቡልጋ ጋር እንደተያያዘው፡፡ መርጡለ ማርያምን ቤተ ክርስቲያንን ከግራኝ ዘመን ትንሽ ቀደም ብሎ ባመረ ሁኔታ እንደገና አሠርተዋት የነበሩት እቴጌ ዕሌኒ የሐድያ ተወላጅ ነበሩ፡፡ ሕዝቡ በደግነታቸው ስለሚወዳቸው በሞቱ ጊዜ ከሩቅ ሀገር ሳይቀር እየሄደ መርጡለ ማርያም ከመቃብራቸው ላይ ያለቅስ ነበር ይላል አልቫሬዝ፡፡ እንዴው ባጠቃላይ እንደ ዘሐ ዘጊ ወዲህና ወዲያ እንዲህና እንዲያ በተዋረሰውና በተወራረሰው ሕዝብ መካከል ‹‹የዚያ ብቻ›› ወይም ‹‹የእኔ ብቻ›› የሚል ነገር ማምጣት ካለ ማምጣቱ ይልቅ የሚከብድ ይመስለኛል፡፡ እንኳን ደጉ ነገር ክፉው ነገራችን እንኳን ተዋርሶ ተዋርሶ የሁላችን ሆኗል፡፡ ምንም እንኳን የራሳችን ቋንቋ፣ ባሕልና ማንነት ቢኖረንም፣ የበለጠ የሚያዋጣን የኛንም ሸጠን፣ የሌላውንም ገዝተን የተዋርሶና የተገናዝቦ ማንነት ብንፈጥር ነው፡፡ ከአጥሩ ይልቅ ድልድዩ ያተርፈናል፡፡ ሀገር እንደ ገና ዳቦ ስትያያዝ እንጂ እንደ ቡሄ ዳቦ ስትነጣጠል ዘላቂ አትሆንም፡፡[/left]

Post Reply

Return to “Ethio General .... ኢትዮ ማህበረሰባዊ ርዕሶች”