የጾም ምግብ፤ ለጤንነት ወይስ አዲስ ፈሊጥ

Life, Health, Religion, Social, General Question
Forum rules
No cursing, bad language and offend other users !
No pornographic images or links!
This forum monitored regularly. We will BAN users without warning for not obeying rules.
እባክዎ የፎረሙን ህጎች ያክብሩ::
User avatar
zeru
Leader
Leader
Posts: 952
Joined: 19 Aug 2009 17:01
Contact:

የጾም ምግብ፤ ለጤንነት ወይስ አዲስ ፈሊጥ

Unread post by zeru » 23 Apr 2014 18:39

Image
በዓለም ዙሪያ በአጽዋማት ጊዜ ብቻ ፤ ከሥጋና ከእንስሳት ተዋጽዖዎች የሚታቀቡ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መኖራቸው የታወቀ ነው። ዘወትር የሚጾሙት በተለይ «ቤጋንስ» የሚባሉት የሚከተሉት የአመጋገብ ስልት መንስዔ ምን ይሆን? ከጤንነት አኳያስ አመጋገቸው ምን ያህል የተሟላ ነው?
በዓለም ዙሪያ በየሃገራቱና ማሕበረሰቡ፣ ከምግብ ጋር የተያያዘው ጾም ፤ ዓይነቱ ይለያይ እንጂ እንግዳ ነገር አይደለም። በዓመት ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች ከጊዜ ቀመር ጋር በተያያዘ ሃይማኖታዊ ትእዛዛትን መሠረት አድርገው የሚጾሙ የመኖታቸውን ያህል ፤ ከሃይማኖት ውጭ ጤናን ፣ «ሞራል»ንም ሆነ የኑሮ ፍልስፍናን መነሻ በማድረግ አዘውትረው የሚጾሙ ሰዎች መኖራቸው እሙን ነው። በእንግሊዝኛው አጠራር «ቬጋንስ» ይባላሉ። እነዚህ ፣ ቬጋንስ የሚባሉት ሰዎች ፣ ከጥራጥሬ ፣ አትክልትና ቅጠላ -ቅጠል ተመጋቢዎች (ቬጂቴሪያንስ) ከሚሰኙት ይለያሉ። ቬጋንስ፤ ጥራጥሬ ፣ አትክልትና ቅጠላ ቅጠል ከሚመገቡ (ቬጂቴሪያንስ) የሚለዩት ፣ ከሥጋና ከእንስሳት ተዋጽዖዎች በተጨማሪ እንቁላል የማይበሉ ፣ አንዳንዶቹ እንዲያውም ማርም የማይቀምሱ መሆናቸው ነው። በዚህና በአንዳንድ መሰል ጉዳዮች ላይ በአቋም የሚለያዩ ቬጋኖች መኖራቸው እሙን ነው። ቁጥራቸው የሚያመዝነው ይበልጥ የጠበቀ መመሪያ ያላቸው ቬጋኖች ማር ፤ የሐር ዝሃም ጭምር መጠቀም አይገባም ነው የሚሉት። ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት፤ በተለይ የዘመኑ የንብ ቀፎ አያያዝም ሆነ የንብ ርባታ፣ ጭካኔ የተመላበትና በመበዝበዝ ላይ ያተኮረ ነው ባዮች ናቸው።
ቬጋኒዝም፤ በሰሜን አሜሪካና በአውስትሬሊያ ፣ ከጤንነት፤ አልፎም ከእንስሳት የሕልውና መብት ጋር በተያያዘ ምክንያት በመስፋፋት ላይ መሆኑ ይነገራል። በዩናይትድ ስቴትስ፣ በተለይ እ ጎ አ ከ 1970ኛዎቹ ዓመታት ማለቂያ ገደማ አንስቶ፣ ከሚታረዱ እንስሳት የሚገኝ ፕሮቲንና ቅባት ፤ ለጤና እጅግ ጠንቀኛ መሆኑን ሃኪሞች በጥብቅ ከማሳሰብ እንዳልቦዘኑ ነው የሚነገረው። በተለይ፣ የልብ ድካም፤ የስኳር በሽታና አንዳንድ የካንሰር ዓይነቶች ሰበባቸው እነዚሁ የተጠቀሱት ከአንስሳት የሚገኙ ስብና ፕሮቲን መሆናቸው ነው የሚጠቀሰው።
በዚህ በጀርመን ሀገር «ቬጋን» መሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ ተወዳጅነትን እያገኘ የመጣ የአኗኗር ፈሊጥ ሆኗል። ባለፈው ወር የተካሄደ መጠይቅ እንደሚያስረዳው፤ ከዓዋቂዎች መካከል ከየ 11 ዱ አንዱ፣ (ዘጠኝ ከመቶ መሆኑ ነው) ቬጋኒዝምን የሚደግፍ ነው። በአሁኑ ጊዜ በጀርመን ሀገር ፤ ከ 80 ሚሊዮን ገደማው ኑዋሪ ፤ የቬጋንስ ቁጥር አንድ ሚሊዮን ገደማ መድረሱና ፤ ከዕለት ወደ ዕለትም አኀዙ እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑ ነው የሚነገረው ። ታዲያ በምግብ ምርምር ነክ ጠበብትና ሃኪሞች የሚቀርበው ዋና ጥያቄ «ቬጋኒዝም» የቱን ያህል ለጤንነት አስተማማኝ ነው? የሚለው ነው። የጀርመን የአመጋገብ ጉዳይ ማሕበር ፣ በበኩሉ፣ በተለይ የወተት ተዋጽዖዎችን አሣንም ቢሆን ከምግብ ገበታ ማራቁ ለጤና አይበጅም ነው የሚለው። አያይዞም ፤ ቬጋንስ፣ ግትር አቋም ሳይያዙ ፣ በዚህ ረገድ በጥሞና ቢያስቡበት ይጠቅማል ይላል። ለተሟላ ጤንነት አስፈላጊ ናቸው ያላቸው ፣ በተለይ ፕሮቲን፤ የብረት ማዕድን ፤ ካልሲየም፣ አዮዲን(አዮዳይን ) እና ቢታሚን B 12 አለመጓደላቸውን ማረጋገጥ ይበጃል ሲልም ይመክራል። እንደዚህ የመጋገብ ጉዳይ ማሕበር ማብራሪያ ከሆነ፣ ለደም ግንባታ ተፈላጊ የሆነው ቪታሚን B 12 ከእንስሳት ተዋጽዖ ብቻ ነው የሚገኘው። ስለሆነም ረዘም ላለ ጊዜ ቬጋንስ ሆነው የቆዩ ሰዎች፣ በክኒን መልክ የተዘጋጀ ቪታሚን B 12 አለበለዚያም በፍራፍሬ ጭማቂ ፤ በማርጀሪንና ብስኩት መሰል ምግቦች ውስጥ ለማግኘት ቢሞክሩ የሚጠቅማቸው ይሆናል ሲል ይመክራል። እርግጥ ነው ፣ ካልሲየም ከደረቅ ፍራፍሬዎችና ለውዝ፤ ፕሮቲን፣ ከአተርና ባቄላ፤ አዮዲን ፣ ለምግብ ከተዘጋጀ ጨው፤ የብረት ማዕድን ደግሞ፤ ከጥራጥሬና ከስፒናች ማግኘት ይቻላል።
ቬጋኒዝም ፤ አዲስ የኑሮ ፈሊጥ መስሎ የቀረበ ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን ፣ ብርቅ ሆኖ የሚታያቸው የመኖራቸውን ያህል፤ የሚያጥላሉም አያታጡም፤ ታዲያ የቬጋናዎች የምግብ መደብርና ምግብ ቤት ያላቸው ጀርመናዊ ጎልማሣ ፣ መጀመሪያ ምግቡን በመቅመስ ማጣጣም የተሻለ ነው ይላሉ። የ49 ዓመቱ ጎልማሣ፣ ከዚህ ቀደም ስለቬጋኒዝም ፣ ስለምግቡና ጣዕሙ ራሳቸው ምንም ደንታ አልነበራቸውመe። አሁን ግን የዚህ አመጋገብ ስልት ጠበቃ በመሆን እንዲህ ይላሉ።
«ቬጋኒዝም፤ ምን አለው? ወተትና ምናምን---ነው ምን የሚበላ አለ? ቢኖርም አይጣፍጥም፣ ለሚሉት ወገኖች መልእክት አለኝ። ሳያዩ፤ ሳይቀምሱ የተዛባ አስተያየት የሚሰጡ በመሆናቸው፣ እዚህ አዘጋጅተን ልናሳያቸው አንችላለን።»
የቬጋናዎችን ምግብ ያጣጣሙ አንድ አዛውንት እንዲሁም ሌሎች ሁለት ተመጋቢዎች በበኩላቸው ይህን ነበረ ያሉት።
«በጥሩ ሁኔታ የተቀመመ ነው፣ ጣፍጦኝም ነው የተመገብሁ። »
«እኔም ጣፍጦኛል። ይህ እንደገና ቢቀርብልኝ እንደገና እመገባለሁ።»
« እንደሌላው ፤ እንደማንኛውም ጊዜ በዱቄት ተተምትሞ የተጠበሰ ሥጋ (ሽኒትስል) ያምርሃል፤ እዚህም በእርግጥ ጥሩ ነው።»
አንዲት ሌላ ወይዘሮ ስለቬጋናዎችና ፤ ስለምግባቸው ይባል የነበረውናና አሁን ምን እንደሚመስል ሲገልጹ----
«የቬጋናዎች አመጋገብ ከተደበቀበት የወጣ ይመስለኛል። ባለፉት ጊዜያት፤ ቬጋናዎች ክፍት ጫማ የሚጫመቱ፤ ጺማቸውን የሚያንዠረግጉ ናቸው እየተባለ ነበረ የሚታሰበው። አሁን እንደዚያ አይደለም። እንደማንኛውም ሰው ናቸው። አሁን ፤ አሁን፤ እንዲያውም ወጣቶችን ለማማለል በመታሰቡ ሊሆን ይችላል፤ የሚዘጋጁት የምግብ ዓይነቶች፣ ገበያውም ይህን ፈር ነው የሚከተለው። ይህ ደግሞ ምርጫውን ሰፊ ያደርገዋል። »
ማንናውንም ሥጋና የእንስሳት ተዋጽዖዎችን ያገለለ ፣ በጥራጥሬ፤ አትክልትና ቅጠላቅጠል ላይ ያተኮረ አመጋገብ ፣ ከጥንት ጀምሮ በሕንድ ፣ በግሪክም የሚታወቅ ነበረ። በህንድ ጥንታዊ ብቻ ሳይሆን ዘመናዊም ነው። በኢትዮጵያ ፣ እንዲህ ዓይነቱ የአመጋገብ ስልት ፤ አጽዋማትን በሚከተሉ ክርስቲያኖች ዘንድ የረጅም ዘመናት ሃይማኖታዊ ሥርዓት ነው። በተለይ በገዳማት የሚኖሩ የበቁ ፣ ለነፍስ ያደሩ አባቶችና እናቶች ፤ ሥጋ፣ የሚያጓጓ ምግብ እንዳልሆነ ፣ በገፍ መመገብም እንደማይበጅ የሚመሩት ሕይወት የሚያካፍለው ትምህርት ይኖራል። በተለይ ቅባትና ጮማ የበዛበትን ምግብ ለሚያዘወትሩ!
በምዕራቡ ዓለም፣ ቬጋኒዝም፣ ከ 19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ገደማ አንስቶ ነው የሚታወቀው። በእንግሊዝ ሀገር ፣ በዮርክሸር የተወለዱት የአንድ ት/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ልጅ የነበሩትና ነጻ አስተሳሰብን አዳብረው የመኖረ ዕድልን ያገኙት ዶናልድ ዋትሰን የተባሉት ሰው ናቸው «ቬጋን» የተሰኘውን ቃል የፈጠሩትና የብሪታንያውን « የቬጋን ማሕበረሰብ » የተሰኘውን ማሕበር እ ጎ አ 1944 ዓ ም ያቋቋሙት።
በጥራጥሬ አትክልትና ቅጠላ ቅጠል ላይ ያተኮረው የአመጋገብ ስልት፣ እየተስፋፋ የመጣው ቀደም ሲል እንደተገለጸው፤ ጤናንና በአንዳንዶችም ዘንድ የሞራል ጥያቄዎችን በማንገብ ነው። ማለት ፣ እንስሳትም የመኖር መብት አላቸው ፤ ከሚል አስተሳሰብ በመነሣት !
በመሠረቱ ፣ አትክልት ፤ ጥርጥሬና የመሳሰለውን ብቻ ለመመገብ መምረጥ የግለሰቦች ጉዳይ ነው። በትኩሱ የሚመረተውም ሆነ በገበያ የሚገኘው ጉድለት ላይታይበት ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ እንደሌላው ሁሌ የቬጋንስ የምግብ ዓይነቶች በኢንዱስትሪ በሚዘጋጁበት ጊዜ ፣ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲቆዩ ለማድረግ ተብሎ ጨው በብዛት የሚገኝባቸው ቅባትም የበዛባቸው አለመታጣቸውን፣ለምሳሌ ያህል ጀርመን ውስጥ በሃምበርግ ከተማ የምግብ ተቆጣጣሪዎች ያቀረቡት ዘገባ ጠቋሚ ነው።
ተክሌ የኋላ
ሸዋዬ ለገሠ

Post Reply

Return to “Ethio General .... ኢትዮ ማህበረሰባዊ ርዕሶች”