በእንግሊዝ መንግሥት አነሳሽነት ኢሕአዴግ እና ተቃዋሚዎች ከነገ ጀምሮ ይወያያሉ

ፖለቲካ ፣ ወቅታዊ ጉዳዮች
Politics , Current affairs
ኦሽንoc
Leader
Leader
Posts: 1129
Joined: 07 Aug 2009 14:20
Contact:

በእንግሊዝ መንግሥት አነሳሽነት ኢሕአዴግ እና ተቃዋሚዎች ከነገ ጀምሮ ይወያያሉ

Unread post by ኦሽንoc » 31 Aug 2009 12:24

በእንግሊዝ መንግሥት አነሳሽነት ኢሕአዴግ እና ተቃዋሚዎች ከነገ ጀምሮ ይወያያሉ
Sunday, 30 August 2009
በፍሬው አበበ

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በ2002 አገር አቀፍ ምርጫ የሥነ ምግባር ደንብ ላይ እንዲወያዩ የእንግሊዝ ኤምባሲ ሁለቱንም ወገኖች ማስማማቱን፣ በዚሁ ስምምነት መሠረት ስብሰባው ከነገ ጀምሮ እንደሚካሄድ ተጠቆመ፡፡

ተቀማጭነታቸው በኢትዮጵያ የሆኑ የለጋሽ አገራት አምባሳደሮች ቡድን ለእንግሊዝ ኤምባሲ በሰጡት ውክልና መሠረት ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት የመጪውን ምርጫ የሥነ ምግባር ረቂቅ ደንብ ላይ እንዲወያዩ ሁለቱንም ወገኖች ሲያግባባ ቆይቷል፡፡

ምንጮቻችን እንደጠቆሙት የኤምባሲው ተወካዮች ባለፉት ሣምንታት ተቃዋሚዎችን በጉዳዩ ላይ አግኝተው ያነጋገሩ ሲሆን በተመሳሳይ ሁኔታ ከኢሕአዴግም ጋር ተነጋግረዋል፡፡ ውይይቱን ለማካሄድ በሁለቱም ወገኖች በኩል ፍላጎት በመኖሩ ምክንያት በተለይ በፓርላማ መቀመጫ ያላቸው ፓርቲዎች ከነገ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት መከላከያ አዳራሽ ውስጥ ውይይታቸውን እንደሚጀምሩ ምንጫችን አስታውቋል፡፡

ነገ በሚካሄደው የመጀመሪያ ቀን ውይይት ላይ በውይይቱ ሞዳሊቲ ማለትም ድርድሩ መቼ ይጀመር፣ አጀንዳዎቹ ምን ምን ይሁኑ፣ ውይይቱን ማን ይምራው፣ በፓርላማ መቀመጫ የሌላቸው ፓርቲዎች ይገኙ ወይስ አይገኙ፣ ውጤቱ እንዴት ለሕዝብ ይገለፅ በሚሉና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም ከተያዘ በኋላ ዋናው ውይይት እንደሚጀመር ምንጫችን ጠቁሟል፡፡

የምርጫ የሥነ ምግባር ደንብ (Election Code of Conduct) ውይይት የሚካሄደው ሠላማዊ ምርጫ በማካሄድ መልካም ስም ያላቸው የአፍሪካ አገራት ማለትም የጋና፣ የደቡብ አፍሪካ እና የናይጄሪያ የምርጫ የሥነ ምግባር ደንቦች መነሻ በማድረግ ነው፡፡

ምንጮቻችን እንደገለፁት በምርጫ የሥነ ምግባር ደንቡ ላይ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ የሚጠበቁት በፓርላማ መቀመጫ ያላቸው ፓርቲዎች ቢሆኑም በተዘዋዋሪ ውክልና ያላቸው እንደ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ፣ መኢአድ፣ ስምንት ፓርቲዎችንና ሁለት ግለሰቦችን የያዘው መድረክ የተሰኘው ስብስብ ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁሟል፡፡

አንድ ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ የመድረኩ ከፍተኛ አመራር ስለ ጉዳዩ ከሪፖርተር ጋዜጣ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በኢሕአዴግ በኩል በቀጥታ ለስብሰባው ጥሪ የተላለፈው በፓርላማ መቀመጫ ላላቸው ፓርቲዎች ብቻ መሆኑን ጠቁመው ሆኖም መድረኩም የሚሳተፍበት ዕድል ዝግ እንደማይሆን ገልፀዋል፡፡ ሆኖም በመድረኩ ስም ስብሰባውን እንዲሳተፉ የቀረበ የግብዣ ጥሪ እንደሌለም ጠቁመዋል፡፡

የምርጫ የሥነ ምግባር ደንቡ ሁሉም ፓርቲዎች ለሕግና ለሥርዓት ተገዢ በመሆን፣ ለግጭት የሚገፋፉ ችግሮችን ከወዲሁ እንዲፈቱ፣ አለመግባባቶችን በሠላማዊና በሠለጠነ መንገድ እንዲፈቱ የሚያስችል ነው፡፡

የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ጽ/ቤት ኅላፊ አቶ ሙክታር ከድር ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ ሰሞኑን ለመንግሥት መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ መጪው ምርጫ ፍትሐዊ፣ ሠላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ግልፅነት የተሞላበት ለማድረግ ግንባሩ ሰፊ ጥረት እያደረገ ነው፡፡

በአሁኑ ሰዓት በፓርላማ ከገዢው ፓርቲ ቀጥሎ ከፍተኛ ወንበር ያለው ኢዴኃኅን ጨምሮ ኦፌዴን፣ አንድነት፣ መኢአድ እና የመሣሠሉት ፓርቲዎች በተለይ በደቡብ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ ክልሎች አባሎቻችን እንዳይንቀሳቀሱ ተደርገዋል፣ ታስረዋል፣ ማስፈራሪያና ዛቻ እየደረሰባቸው ነው የሚሉ ተደጋጋሚ አቤቱታዎችን በማቅረብ ላይ መሆናቸው አይዘነጋም፡፡
source:ሪፖርተር

Post Reply

Return to “Ethio Politics .... ኢትዮ ፖለቲካ”