ወደ ምስራቅ ተመልከቱ በ ሙሉቀን ተስፋው

ፖለቲካ ፣ ወቅታዊ ጉዳዮች
Politics , Current affairs
User avatar
nebex
Leader
Leader
Posts: 283
Joined: 29 Oct 2009 10:32
Contact:

ወደ ምስራቅ ተመልከቱ በ ሙሉቀን ተስፋው

Unread post by nebex » 19 Apr 2016 19:38

ወደ ምስራቅ ተመልከቱ

‹‹አገር አገር አለች ይህች አገረ ብርቁ፣
እኛም አገር አለን ኢትዮጵያ ሲዘልቁ!››

ብዬ አፌን ሞልቼ መናገር አልችልም፡፡ ይህ ተረት ነው- አሊያ ልብወለድ፡፡ ኢትዮጵያዊ በእውነት ሀገሩ የት ይሆን? በሀገሬ ከሽራሮ እስከ ሞያሌ፣ ከጋምቤላ እስከ ቶጎጫሌ በነጻነት ካልፈነጨኹበት፣ በወገኔ መካከል አብሮነት ካልተሰማኝ ሀገር አለኝ ብዬ እንዴት አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ?

እንዲህ አይነት ኖሮ ያሳፍራል፤ አገር ውስጥ ብቻም ሳይሆን ሀገር ያላቸው ሰዎችም ይንቁናል፡፡ በትዝታ ያስቆዝማል፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ‹‹ትልቅ ነበርን አሁንም ትልቅ እንሆናለን›› ይበሉ እንጅ ቅሉ ትልቅ የመሆን ፍላጎታችን እስካሁን ከምኞት አላለፈም፡፡

ተስፋ ጥሩ ነው - በሕይወት ያቆያል፡፡ ተስፋ የቆረጡ አገራቸውን አሊያም ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ተስፋቸው ቀቢጸ ተስፋ ሲሆን፣ በህልም ያዩት የማይታይ ሲሆን፣ በምናብ ያዩት ሞሶብ የማይበሉት ማዕድ ሲሆን … ሰዎች ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ ተስፋ ቆርጠው ባህር ይሻገራሉ፡፡ ባህር ተሻግረው ከሰዎች ዝቅ ማለትን ይመርጣሉ፡፡ አሊያም ባህር ሲሻገሩ የሚደርሰው አደጋ አገር ላይ ከመዋረድ በታች ስለሚሆን በማያውቁት ቦታ የማያውቁትን ሞት ለመጋፈጥ ይገደዳሉ - በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያውያንና በኤሪትራውያን፡፡ የሁለቱ ሀገር ዜጎች የተሻለ ዓለምን እንፈጥራለን ብለው የከፈሉት መስዋዕትነት ከሁለት አስር ዐመታት በኋላም ጠብ የሚል ነገር አላመጣላቸውም፡፡

አፍሪካዊ ሲንጋፖር የመሆን በርግጥም ህልም ነበር፡፡ አፍሪካዊ ሲንጋፖርነት ወደ አፍካዊ ጓንታናሞነት ሲቀየር፣ ነጻነትና ዲሞክራሲን እስከ አፍንጫችን እንለብሰዋለን ያሉ ህዝቦች በመጫሚያቸው ሲረግጡት ህዝብ ለምን ተስፋ አይቆርጥም?

ኢትዮጵያዊነትና ኤርትራዊነት እኩል ከሶማሊያዊነት ጋር ጥገኝነት ሲያስገኝ፣ በሀገር ክብርና እንጀራ ሲጠፋ በሰው ሀገር ክብርን ትቶ በልቶ ለማደር መሰደድ አማራጭ ሆነ፡፡ እንደ እሪያዎች ሆኖ ጠግቦ ማደርን የሚመኝ ትውልድ በረከተ፡፡

ዳሩ ምን ያደርጋል፡፡ በትውልዱ አይፈረድም፡፡ ሀገራቸው ለዜጎቿ እሾህ ከሆነች ሌላ ምን አማራጭ ሊኖር ይችላል? እልፍ ሲሉ እልፍ አለ ብሎ ከመሰደድ ውጭ፡፡ በያመቱ ከሚወለዱት እኩል የሚሰደድ ዜጋ ባለቤቶች ነን፡፡ በቻድ፣ በሰሜናዊ ግብጽ፣ በሊቢያ፣ በቱንዝያና በደቡባዊ ጣሊያን ፔድሞንት ሰርዲንያ ግዛቶች ወዳድቀው የሚቀሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ቢያሳዝኑንም ምንም ማድረግ የማንችል አቅመ ቢሶች ነን፡፡ በህንድ ውቅያኖስ፣ በኤደን ባህረ ሰላጤ፣ በሜድትራንያንና ቀይ ባህሮች በየቀኑ ለሻርክ ራሽን የሚጣሉ ወገኖቻችን ብናስብም ከንፈር ከመምጠጥ በላይ የማድረግ መብት የለንም!!

የዩንቨርሲቲ ምሩቅ እህቶቻች በሃገራቸው መመከርና ፖሊሲ ከማውጣት ይልቅ በአረብ አገር የማዕድ ቤት ገረድ ሲሆኑ፣ ወንድሞቻችን ለፍዬልና ለግመል ጠባቂነት ሲሸጡ፣ ሀበሻነት ከእንስሳ ጋር እኩል ሲቆጠር ከዚህ በላይ ብሄራዊ ውርደት ከቶ ከወዴት ይገኛል?

ይህም ይሁን ብለን ዝም አልን፡፡ በላያችን ላይ ያለው ቀንበር ግን ከቀድሞው የበለጠ በረታ፡፡ ሸክሙ ከበደ፡፡ ከሸክሙ የሚያሳርፍ በር አንኳኳን ግን አጣንም፡፡

መሰደድ መሰደድ መቸም እንደሚቆም የማይታወቅ የትውልድ ዥረት ነው፡፡ ዜጎቻችን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መሰደድን እንደመፍትሄ ወሰዱት፡፡ የጎረቤት አገራት ዜጎች ተሰደው ወደ እኛ መጡ እንላለን እንጅ የሰደተኛ ጣቢያዎቻችን እንዲሞሉ የራሳችን ወገኖች አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በሰሜን ባሉ ስደተኛ ጣቢያዎች ትግርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውን አርትራዊ ነኝ በማለት፣ በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ባሉ የስደተኛ ካምፖች ሶማሊኛ ተናጋሪ ዜጎቻችን ሶማሊያዊ ነኝ በማለት፣ በምዕራብና በሰሜን ምዕራብ ባሉት ጣቢያዎች ደግሞ አረብኛ እና የኙዌር አኝዋክ ቋንቋ ተናጋሪ ዜጎቻችን ደቡብ ሱዳናዊ ነን በማለት በገንዛ ሀገራቸው በተባበሩት መንግስታት የስደተኛ ጣቢያዎች መታጎራቸውን ማወቅ ያማል፡፡ ከሀገር ለመውጣት እራስን መካድ የተሻለ አለምን በመሻት በማንነት ማፈር ይህም ያማል፡፡ በሀገር ያለ ተስፋ መቀመጥም ያማል፡፡ ለኢትዮጵያዊው ሁሉም ነገር ያማል፡፡

‹በምስራቅ ተስፋ አለ፣ በምስራቅ ጸሀይ ትወጣለች፣ በምዕራብ ጨለማ ነው፣ ከምዕራብ ምስራቅ የተሻለ ነው› ብለው ወደ መካከለኛው ምስራቅ በአቋራጭ የተሰደዱ ሰዎች ጮራ ቀድማቸው ጨለማ አገኟት፡፡

ከዘመናት በፊት ዓለም ገና ሳይሰለጥን፣ የሰብዓዊ መብት ትርጓሜ ባልታወቀበት፣ በዚያ ደግ ጊዜ በ622 ዓ.ም. አካባቢ ወገኖቻቸውን በቤተ መንግስት እንዳላስጠጋን አይናችን ላፈር አሉን፡፡ ያውም እኮ ያኔ ስራ ስሩ ብለው ገዢዎቻችን አላስገደዷቸውም- ሙሉ መብት ከማጎናጸፍ ውጭ፡፡

ሰኮናቸውን ተከተለው ወደ ሀገራቸው የሄዱ ሀበሾችን ግን እራስ እራሳቸውን ቀጠቀጧቸው፡፡ በየቤቱ የፈላ ውሃ የሚደፋባቸው እህቶቻችን ጉዳት ሳያንስ፣ በተናጠል በየምክንያቱ ህይወታቸውን የሚያጡ ወገኖቻችን ጉዳት ሳያንስ በጅምላ መፈናፈኛ አሳጧቸው፡፡ በመኪና ሲገጩ፣ ክቡር የሆነውን የሰው ህይወት በአደባባይ ላይ ሲያርክሱት፣ የተቀደሰ መሬታቸውን በደም ሲያሰክሩት ለሰማያዊው አምላክ ከመጮህ ውጭ ሌላ ምን ማድረግ ይቻላል? ሀፍረት ሲለመድ ጌጥ ይሆናል፡፡ ከንጹህ ሸማ ይልቅ እራፊ አዳፋ ለማጌጫነት ተመርጧል፡፡ ከነጻነት ይልቅ ጭቆናን ባህል አደርገናል፡፡

ቢሆንም ግን ወደ ምስራቅ ከመመልከት አናቁም፡፡ የአይናችን ትክተት አናስረዝም፡፡ በሜዲትራኒያንና ቀይ ባህሮች የሚያልቁ ወገኖቻችን እናስብ፡፡

በሌላም በኩል ወደ ምስራቅ መመልከት ጥሩ ነው፡፡ በምስራቅ የተስፋ ጸሀይ ትወጣለች፡፡ በሀሳብ ወደ ምስራቅ መጓዝ ከጨለማ መላቀቅ ነው፡፡ እኔም መሰደድ አምሮኛል - ግን ወደ ባዕዳን አገር እራስ እራሴን ወደ ምቀጠቀጥበት በረሀ፤ ለሻርክ ወደምጣልበት ባህር አይደለም፡፡ ወደ ተሻለች፣ ለዜጎቿ ወደምታስብ መሀሏ ገነት ዳሯ እሳት ወደሆነች ሀገር ነው፡፡ በምናብ ወደምናስባት ኢትዮጵያዬ!!

‹‹ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ …

ኢትዮጵያ የእኛ መመኪያ!!›› በሙሉ ልባችን ለመዘመር ያብቃን፡፡

ውስተ ጽባኅ ነጽሩ!

Source: Facebook By Muluken Tesfaw
https://www.facebook.com/muluken.tesfaw
https://www.facebook.com/muluken.tesfaw ... 3407343937

Post Reply

Return to “Ethio Politics .... ኢትዮ ፖለቲካ”