4 የሰቆቃ ዓመታት በህወሓት እስርቤት

ፖለቲካ ፣ ወቅታዊ ጉዳዮች
Politics , Current affairs
Post Reply
selam sew
Leader
Leader
Posts: 593
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

4 የሰቆቃ ዓመታት በህወሓት እስርቤት

Unread post by selam sew » 30 Mar 2016 12:59

አራት የሰቆቃ ዓመታት በህወሓት እስርቤት - በየነ ገብራይ ከደንማርክ

ክፍል 1

ምንጭ:- በየነ ገብራይ ፌስቡክ ገጽ https://www.facebook.com/btesfu1


ቀኑን ግንቦት 30 1984 ነበር። ወደ ማምሻ ላይ ከባድ ዝናብ ዘንበና ዋልካው የተዋባ መሬት ጭቃ በጭቃ ሆኖ ነበር። ስለሆነም በጊዜ እራታችን በልተን በዕለቱ በዘነበው ዝናብ ምክንያት መሬቱ ቀዝቅዞ ስለነበረ ሌላ ጊዜ በግቢው ውጭ ስንተኛ የነበረ በዛን ዕልት እኔና ባለቤቴ የሁለት ዓመቷ ልጃችን ይዘን ቤት ውስጥ በጊዜ ተኛን። አንድ እኔ ጋር ተጠግቶ የሚኖር የነበረ ዘመድ፣ አንድ ያስጠጋናቸው ሽማግሌና ሌላ እንግዳ ግባዛ ውስጥ ተኙ።
Image
ሁላችን ከተኛን በኋላ በግምት ወደ እኩለ ሌሊት አከባቢ የሱዳን የደህንነት ሰዎች የግቢያችን በር አንኳኩ። ዘመዴ የነበረው ሰው ቀድሞ ሰምቶ በሩ ድረስ በመሄድ ማን ነህ ሲላቸው እኛ ደህንነቶች ነን፣ ቶሎ ብለህ በሩን ክፈት ሲሉት ማንገራገሩ ሌላ ችግር ሊፈጥር ይችላል በሚል ፍርሃት የግቢውን በሩን ከፈተላቸው። ግቢው ውስጥ ገብተው እኔ ቤት ውስጥ መተኛቴን ከሱ ካረጋገጡ በኋላ ቤቱን ከበው የቤቱን በር አንኳኩ። እኔ ሳልሰማ ባለቤቴ ቀድማ ሰምታ ማን ነህ ስትል፣ እኛ ድህንነቶች ነን፣ ቤቱ ተከቦአልና ሌላ ችግር ሳይፈጠር ቶሎ ብለሽ በሩን ክፈቺ ሲሉዋት እሷም ፈርታ ቶሎ ብላ እኔ ሳልሰማ በሩን ከፈተችላቸውና እኔ እንደተኛሁ አንድ የደህንነት ክላሽን ደረቴ ላይ ተክሎ፣ ሌላው ደግሞ ባትሪ ዓይኔ ላይ አብርቶ ተነስ አለኝ። ባለቤቴ ደግሞ ድህነነቶች ናቸው ዝምብለህ ተነስ፣ ያሉህን አድርግ አለችኝ። ክላሽን ደረት ላይ ተተክሎ፣ ባትሪ ዓይንህ ላይ ከበራ በኋላ ምንም ነገር ማድረግ አይቻልም ነበርና እኔም እንደታዘዝኩ ተነስቼ፣ እንደዚህ በድቅድቅ ጨለማ ቤተሰብን ማሸበር ለምን አስፈለገ፣ ቀን ላይ በፈለጋችሁት ቦታ ና ብትሉኝ እመጣላችሁ ነበር ቢያቸው ካናተራና ፕጃማ ብቻ ለብሼ ስለነበረ ልብስ ለመቀየር ልብስ ፍለጋ ስጀምር አይቻልም የለበስከውን እንደለበስክ ቀጥል አሉኝ። አረ ባካችሁ ልብስ ልልበስ ቢየ ብማጸን ፈጽሞ አይሆንም አሉኝና በቅርብ ያገኘሁት አንድ ጃከት በእጄ ይጄ ለመውጣት ስል አንዱ የደህንነት ጃከቱን ከእጄ መንጥቆ ነጠቀኝና እየገፉ ከቤቱ አወጡኝ። ግቢው ላይ አንድ ደህንነት ክላሽን ጀርባዬ ላይ ተክሎ፣ ሌሎች ሁለት በግራና በቀኝ በኩል ሆነው አንዱ እየመራ ከግቢው አወጡኝ።
እኔን ከግቢው ሲያወጡ ለቤተሰብ አንድ ድምጽ እንዳታሰሙ፣ ከግቢው ውጭ ጠባቂዎች አሉ ብለው አስጠንቅቀው ከግቢው ውጭ ቆማ ስትጠብቅ ወደ ነበረች ፒክ አፕ ቶዮታ መኪና ወሰዱኝና ወደ መኪናዋ ውጣ አሉኝ። መኪናዋ ላይ እንደወጣሁ እጆቼን የኋሊት አስረው፣ በ5 የድህንነት ሰዎች ታጅቤ መኪናዋ ከተዋባ ወደ ገዳሪፍ ከተማ አቅጣጫ በፍጥነት በረረች። ሲንያን (የካርቱም ከሰላ መንገድና ወደ ገዳሪፍ የሚወስደው መንገድ መለያያ) አልፈን፣ ገዳሪፍ ከተማን ማኸል ለማኸል የሚያቋርጠው ዋና መንገድ ይዘን በደመኑር በኩል ወደ ራብዓ የገዳሪፍ ደቡባዊ ጫፍ ላይ ደረስንና ቶዮታዋ አንድ ትልቅ ሎሪ አጠገብ ቆመች፣ ከቶዮታዋ እንድወርድና ወደ ሎሪዋም እንድወጣ አዘዙኝ። እጄ ታስሯል እኮ መውጣት አልችልም ስላቸው ሁለት የደህንነት ሰዎች ደግፈው ሎሪዋ ላይ አወጡኝ። ላይ ሎሪዋ ላይ ተዘጋጅቶ ሲጠብቅ የነበረ የድህንነት ሰው በጠመንጃ ሰደፍ ማጅራቴ ላይ መቶኝ በሎሪዋ ወለል ወደቅኩ። እንደወደቁኩም ሌላ የድህንነት ሰው እግሮቼን ወደኋሊት አጥፎ ከእጆቼ ጋር ጠፍሮ አንድ ላይ በጣም አጥብቆ አሰረኝ። በሰደፍ ማጅራቴ ላይ ከተመታሁት ምት ትንሽ ማገገም ስጀምር ከኔ በፊት እንደኔው እጅና እግራቸው አንድ ላይ ታስረው ሎሪዋ ወለል ላይ በሆዳቸው የተኙ፣ እንዲሁም ጥግ ጥጉን ይዘው ቁጭ ያሉም ሰዎች ቢታዩኝም ሁሉም ጸጥ ብሎ ስለነበረ መጀመሪያ ላይ ማንነታቸውን ለመለየት አልቻልኩም ነበር። ትንሽ ጊዜ እንደቆየን ከጎኔ እንደኔ እጅና እግሩ አንድ ላይ ታስሮ በሆዱ ተጋድሞ የነበረ ሰው ማቃሰት ጀመረ። ይህን ጊዜ ያ ሲያቃስት የነበረው ሰው በደምብ የማውቀው ጓድ ስለነበረ በድምጹ ለየሁት። ከዛም ከየቦታው ጓዶችን በሎሪዋ ላይ እያሰባሰቡ መሆናቸው ተረዳሁ፣ አንድ ላይ አሰባስበው ለህወሓት ሊያስረክቡን እየተዘጋጁ መሆናቸውም ወዲያውኑ አወቅኩ።
ትንሽ እንደቆየን መሬት ላይ ከነበሩ የድህንነት ሰዎች አንዱ ጮክ ብሎ በመገናኛ ረዲዮ ሌላ ቦታ ካለ ሰው ጋራ መነጋገር ጀመረ። ወዲያ የነበረው ሰው ምን እንደሚል ባይሰማም አጠገባችን የነበረው የሚናገረው በደምብ ይሰማ ነበርና የሚያወሩት የነበረው ስለ ሌሎች ታፍነው ወደ ሎሪዋ መምጣት የነበረባቸው ጓዶች በተመለከት መኖሩ አውቅኩ። በምጨርሻ ቤቱን ካጣችሁት ክንግዲህ አሰሳዉን ተዉት፣ ከንግዲህ መጠበቅ አንችልም፣ መድረስ ያለብን ቦታ መሬቱ ከመንጋቱ በፊት መድረስ ስላለብን የያዝነውን ይዘን እኛ እንቀጥላለና እናንተ ወደ ሰፈራችሁ ተመለሱ ሲለው ሰማሁ። እንደላውም ከትንሽ ጊዜ ቆይታ በኋላ ሎሪው ለመንቀሳቀስ ሞተሩን ማሞቅ ጀመረ። ከጥቂት ደቂቃዎች ሞተሩን ማሞቅ በኋላ ሎሪው መንቀሳቀስ ጀመረ። ከከተማው እስከምንወጣ ምንገዱ አስፋለት ስለነበረ አንድ ላይ የታሰሩ እጆቼና እግሮቼ አከባቢ ከሚሰማኝ ቃንዛ ውጭ ብዙ ችግር አልነበረም። ከተማውን ጨርሰን ወደ ገጠሩ እንደገባን መንገዱ በጣም የተበለሸ ኮረኮንች መንገድ ስለነበረ ሎሪው ሲበር በሚያደርገው ወደላይና ወደታች መዝለል እኔም በደረቴ ከሎሪው ወለል ጋር መላጋት ጀመርኩ። እጅና እጋራቸው እንደኔው በንድላ ተጠፍሮ የታሰሩ ጓዶችም እንደኔው እንደ ኳስ መንጠርና እርስ በርስ መጋጨት ጀመርን። ስቃዩ ገና ከጀምሩ ከዓቅማችን በላይ ስለሆነብን መጮህ ጀመርን፣ ነገር ግን እሪ ብትልም ሰሚ አልነበረም። በዚህ ዓይንት ሁኔታ ወደ 5 ሰዓት ያሀል ተጉዘን ሊነጋጋ ሲል ወደ አንድ ሰፈር አከባቢ ደረስን። ለሰፈሩ መቃረባችን የተረዳነው በዶሮና በውሻ ጩኸት ነበር። ሌሊቱም ሊነጋ ተቃርቦ ጨለማውን ብርሃን እየወረሰው ስለነበረ በተወሰነ ደረጃ በትክክል ማን ማን መሆኑን ለመለየት ቢከብድም ከተቀመጡት መካከል ሴቶች መኖራቸውን መለየት ቻልኩ።
ትንሽ እንደተጓዝን ሎሪው ቁሞ ለኛ እጅና እግር አንድ ላይ ታስረን ለነበርን ጓዶች እግራችን ተፈቶልን እጃችን ብቻ እንድንታሰር ሃላፊው አዞ እግራችን ተፈታልን። ይህን ጊዜ በቂጤ ቁጭ ማለት ስለቻልኩ፣ እየነጋም ስለነበረ እሎሪዋ ላይ የነበሩ ሰዎቹን ለመለየት አትኩሬ መመልክት ጀመርኩ። በመጀመሪያ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ተቐምጦ የነበረ አንድ ጓድ በቀላሉ ለየሁት፣ ቀጥሎም ሁለት ነጣለ ለብሰው የነበሩ ሴቶች ለየሁ። ብርሃኑ እየጨመረ ሲሄድ ሁሉም ጓዶች በግልጽ ይታዩኝ ጀመርና ሁሉንም ለየሁዋቸው። ለራሴና በሎሪዋ ላይ ለነበሩ ለጓዶቹ ባዝንም በሎሪዋ ላይ ይኖሩ ይሆን እያልኩ በከፍተኛ ጭንቀት ስፈልጋቸው የነበረው ጓድ ጋይምና ጓድ ዑስማን የማእከላዊ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች ሲኒየር ጓዶች እሎሪዋ ላይ አለመኖራቸው ሳረጋግጥ ትልቅ የመንፈስ እፎይታ ተሰማኝ። ሎሪው ትንሽ ከተጓዘ በኋላ አንድ ሰፈር ደርሶ ቆመ።
ሎሪው የቆመበት ሰፈር መተማ ነበር። ሎሪው ቆሞ ትንሽ እንደቆየ መተማ ላይ እኛን ለመረከብ ሲጠባበቅ የነበረው የህወሓት ባለስልጣን ሰራዊቱን አስከትሎ ወደ ሎሪው መጣ። የህወሓቱ ባለስልጣን በአሰተርጓሚው አማካይንት ከደህንነት ሃለፊ ጋር ስለኛ ይጠይቃል። ስንት ናቸው ብሎ የህወሓት መሪ ደህንነቱን ስጠይቀው፣ የድህንነት መሪው በትክክል አልቆጠርናቸውም ወደ 20 ይሆናሉ ብሎ መለሰለት። የህወሓት መሪው እኛ የምንፈለጋቸው በሊስቴ ያሉት 18 ብቻ ናቸው ብሎ ራሱ እኛን ለማየት ወደ ሎሪው ወጣ። ሲያየን እግራቸው የተቆረጠ በክራንች የሚሄዱ፣ በጣም ስስ የውስጥ ልብስ ብቻ የለበሱ ሴቶች፣ ዓይነስዉር፣ ሁለት እግራቸው ፓራላይዝ የሆኑ ሲያይ ድንጋጠውና ሀዘኑ ፊቱ ላይ በጉልህ ይነበብ ነበር። ካየን በኋላ ከመኪናው ዘሎ ወርዶ ምን ዓይንት ሰዎች ናቸው ያመጣችሁልን፣ እኛ የፈለግናቸው ሰዎች እነዚህ አይደሉምና ከ4ቱ ውጭ ያሉትን መልሳችሁ ውሰዱዋቸው ብሎ ከደህንነቱ ሰውየ ጋር በአሰተርጓሚው ብኩል ሲነግረው የድህንነት ሰውየውም ብፍጹም አላደርገውም ከፈግክ ሁሉንም ተቀበላቸው ካልሆን ግን እዚሁ መተማ ላይ አርግፌያቸው ነው የሚሄደ በማለት ክርክር ገጠሙ። የደህንነቱ ሃላፊም የዋዛ አልነበረምና ትረከብ እንደሆነ ተረከብ፣ ካልሆነ ግን እዚሁ አራግፌያቸው ነው የምሄደው ብሚለው አቋሙ እንደጸና ቀረ። ከዛ የህወሓት ባለስልጣን በረዲዮ ከበላዮቹ ጋራ ከተነጋገረ በኋላ እንዳለን ለመረከብ ተስማምቶ ሎሪው ከመተማ ከተማ ወደ ሸሄዲ በሚወስደው መንገድ ከከተማው ወጣ ብሎ አንድ ጎድጓዳ ስፍራ ውስጥ እንዲቆም ተደርጎ እንድንወርድ ታዘዝን። ራሱን ችሎ መውረድ የሚችል ብዙ ሰላልነበረ ለመውረድ ረዳት ያስፈልገናል ብዬ እኔ በትግርኛ ለህወሓት አባላት ተናገርኩ። መሪው ሁኔታውን ተመልክቶ ስለነበረ የተወሰኑ የህወሓት ታጋዮች ሎሪው ላይ ወጥተው እንዲረዱን ተደርጎ ከሎሪው አወረዱን፣ ሎሪዋም እኛን አራግፋ ሲጠብቁን የነበሩ የሱዳን ደህንነቶችን ብቻ ጭና ወደ ሱዳን ተመለስች፣ ከዛች ሰዓት ጀምሮም እኛ በህወሓት ቁጥጥር ስር ገባን።

በክፍል 2 ፣

በመተማ የአንድ ቀን ተኩል ቆይታና ጉዞ ወደ ሸሄዲ ምን ይመስል ነበርን ይጄላችሁ እቀርባልሁ።

▼▼ ክፍል 2ን ለማንበብ ወደታች ይቀጥሉ ▼▼

በየነ ገብራይ ከደንማርክ
btesfu45@gmail.com
0045 20545658

selam sew
Leader
Leader
Posts: 593
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

Re: 4 የሰቆቃ ዓመታት በህወሓት እስርቤት - ክፍል 2

Unread post by selam sew » 30 Mar 2016 13:01

4 የሰቆቃ ዓመታት በህወሓት እስርቤት ክፍል 2

በየነ ገብራይ ከደንማርክ

ቆይታ በመተማና ከመተማ ወደ አዘዞ የእስር ጉዞ፣

ስለ ወደ ወደ አዘዞ የእስር ጉዞ ከማውራቴ በፊት ህወሓት መተማ ላይ ከሱዳን ደህንነቶች የተረከበው የኢህአፓ/ሰ አባላት ምን ዓይነት ሰዎች እንደነበሩ ትንሽ ላብራራልችሁ። አጠቃላይ ቁጥራችን 22 ነበርን። ከ22ቱ ወስጥ፣ 4 የኢህአፓ ነባር አባላት ነበርን፣ ከአራታችን አንዱ ደግሞ በ1971 ወልቃይት ከደርግ ጋራ በተደረገው ጦርነት አንድ እግሩ የተቆረጠ አካለ ጎደሎ ነበር፣ 14 በሜዳ በተለያየ ጊዜ ከደርግ ጋር በተደረገው ጦርነት ቆስለው ለቀጣይ ህክምናና እንክብካቤ ወደ ሱዳን የወጡና አካለጎዶሎ ስለሆኑ ሰራዊቱን በቋሚነት የለቀቁ ነበሩ፣ በተለይ ደግሞ ሶስቱ ከወገብ በታች ፓራላይዝድ የሆኑ፣ አንዱ ደግሞ ሁለቱ ዓይኑ ያጣ ዓይነስዉር ነበር፣ 2 ቁስለኞቹን እንዲመግቡና እንዲከናከኑ በድርጅቱ የተቀጠሩ ሴት ሰራተኞች ነበሩ፣ 2 ደግሞ ከባሎቻቸው ጋራ አብረው የተገኙና የታፈኑ ሴቶች ነበሩ። እነዚህ አባላት ከሱዳን ሲታፈኑ ሱዳን ሙቀቱ ሃይለኛ ስለነበረ ሲተኙ ግማሹ ፓንቲ ብቻ እንደለበሰ፣ ግማሹ ሽርጥ ብቻ ከወገብ በታች እንዳሸረጠ፣ በተለይ ሴቶቹ በጣም ረቂቅ የውስጥ ልብስ ወይም የሌሊት ፕጃማ ብቻ እንደለበሱ ነበር የታፈኑትና ያን ለብሰው የቆዩትን ብቻ እነደለበሱ ነበር። እኔ የአጋጣሚ ነገር ሆኖ ቲ ሸርትና ረጂም ፒጃማ ሱሪ እንደለበስኩ ነበር። ሌላ አስገራሚና በጣም አሳዛኝ ክስት የነበረው ደግሞ የአንዱ ጓድ ሁለት ህጻናት፣ አንዱ ወደ ሁለት ዓመት የሆነው፣ ሌላኛዋ ደግሞ ገና የ9 ውር ህጻን አባትና እናታቸው ታፍነው ከኛ ጋራ ሲመጡ ህጻናቱ ተለይተው ሱዳን ብቻቸው ቤት ውስጥ ተዘግተው የቀረቡት ሁኔታ ነበር።
ሌላ በጣም አስገራሚና አሳዛኝ ክስተት ደግሞ ሱዳኖቹ ከሱዳን አፍነው ለህወሓት ሲያሰረክቡን፣ ህወሓት ከጦርነት ከሜዳ እንደተማረክን ለማስመሰል ሎሪው ከመተማ ወደ ሸሄዲ መንገድ አስገብቶ እንዲያራግፈን የስደረገው ድራማ ነበር። ሎሪዋ ከመተማ ወደ ኢትዮድያ ውስጥ የተጓዘቸው ላጭር ደቂቃዎች ቢሆንም ለኛ ሎሪዋ ካራገፈችን ቦታ ወደ መተማ ከተማ ተመልሰን በእግር ለመጓዝ የወሰደብን ጊዜ ግን ረጅም ሰዓት ነበር። ምክንያቱም በርካታ መደገፍ የሚያስፈልጋቸው አካለስንኩላን ስለነበሩን፣ እንደኔው ዓይነት እግራችንና እጃችን አንድ ላይ ተጠፍሮ የታሰርን እጅና እግራችን ዝሎ መራማድ የማንችልበት ሁኔታ ላይ ስለነበረን የግድ ተደግፈን መጓዝ ያስፈልገን ስለነበረ ነበር። እንደማይደረሰው የለምና እንደምን ተጉዘን መተማ ከተማ ደርሰን ወደምናፍበት እስርቤት ከመግባታችን በፊት ሰዎች ሰብሰብ ብለው ቆመው እናኝን አተኩረው እያዩ የሚያወሩበት ቦታ ላይ ደረስን። በሰዎቹ መካከል እኔ የማውቃቸው እነሱም በደምብ የሚያወቁኝ ፣ ከሁለት ቀን በፊት ተዋባ አብረን የነበርን 2 ሰዎች አየሁና በዓይን ምልክት ሰጥቻቸው እነሱም ሁኔታውን በሚገባ ተረድተው እኛ ወደ እስርቤቱ ተወሰድን፣ ከሰዎቹ አንዱም ወዲያውን ወደ ገዳሪፍ በመሄድ እኛ መተማ ላይ ለህወሓት መረከባችንን ሱዳን ለቀሩ ጓዶችም ቤተሰብም ተናገረ።
መተማ ላይ በጊዜያዊነት የቆየንበት እስርቤት ሶስት ጎጆዎች ያሉት እንጨት አጥር የተከበበ ግቢ ነበር። በግቢው ውስጥ እንደገባን የተወሰኑ ሌሎች እስረኞቸም ነበሩና ከነሱ ጋራ እንድንቀላቀል ተደረገ። በእስረኞቹ መካከልም ሱዳን የማውቃቸው የተወሰኑ ሰዎችም ነበሩበት። እኔና ሌሎች እጅና እግራችን አንድ ላይ ተጠፍሮ የታሰርን ጓዶች ከመኪናው ወለል ጋራ እየተጋጨን በተጓዝነው አስቃቂ ጉዞ ፊታችን አባብጦ በደም ተጨማልቆ ስለነበረ እስርቤቱ ውስጥ የቆዩ እስረኞች በሙሉ በተለይ ደግሞ ሲያውቁን የነበሩ በጣም ደነገጡ። እኔ ደግሞ እባካችሁ ከቻላችሁ ውሃና ጨው አፍልታችሁ ይህ በፊታችን ያለውን ደም እጠቡል ሲላቸው እስረኞቹም ተሯርጠው ውሃ አፍልተው ፊታችን አጠቡልን፣ ከዛም እጅና እግራችንም አሹልንና ትንሽ እፎይታ አገኘሁ፣ ቀኝ እጄ ግን ሙሉ በሙ ዝሎ ፓራላይዝድ ሆኖ ምንም ዓይነት ስሜት ስላልነበረው በጣም አሳስቦኝ ነበር።
እስርቤቱ ውስጥ ትንሽ እንደቆየን፣ እዛው እስርቤት ለሚመጡ እስረኞች ተለክቶ እንዲሰጥ የተቀመጠ የማሽላ ዱቄት፣ ዘይት፣ የተከካ ምስር፣ ጨው ስለነበረ አንድ እስረኛ ቁጥራችን ጠይቆ ከሁሉም ለ22 ሰው የሚሆን በተሰጠው መለኪያ መሰረት ሰፍሮ አስረከበን። ጓዶች ሁላቸውም በጣም ተዳክመው ስለነበረ ከቆዩት እስረኞች መካከል የተወሰኑት የኛን ዱቄት ወስደው አገንፍተው፣ ቆንጆ የምስር ወጥ ሰርተው ገንፎ በምስር ወጥ በጀሪካን ገል ላይ ከፋፍለው በቡድን በቡድን እንድንቀመጥ አድረገው አቀረቡልን። በጣም እርቦን ስለነበረ ገንፎ በምስር መመገብ የመጀመሪያዬ ቢሆንም በጣም ጣፍጦኝ በደምብ በላሁ። ከዛ በኋላ ከባድ ድካም ስለነበኝ ወደ ሽንት ቤት ለመሄድ ተዘጋጁ እስከሚባል ድረስ በደምብ ተኛሁ።
በግምት ከቀኑ ወደ 10 ሰዓት አከባቢ እስረኛውን አጅበው ወደ ሽንትቤት ለመውሰድ የህወሓት ታጋዮች በርከት ብለው መጡና ተሰለፉ ተባልን። የቆዩ እስረኞችና የተወሰኑ ከሱዳን ከታፈን የምችሉት ቢሰለፉም አካለስንኩላን በተለይ በራሳቸው መራመድ የማይችሉ አንድ 4ቱ የግድ ረዳት ያስፈልጋቸው ስለነበረ መርዳት የምችሉ ጓዶች ደግፈዋቸው ሲቆሙ አንድ የህወሓት አባል ለምን ራሳቸው አይቆሙም ብሎ በትግርኛ ይጠይቃል። እኔም በትግርኛ አካለጎዶሎ ናቸው፣ ራሳቸው መቆም አይችሉም የግድ ረዳት ያስፈልጋቸዋል አልኩት። እሱም ከአነጋገሬና ከጓዶቹ ሁኔታ ነገሩን ስለተረዳ ጓዶቹ ተደግፈው እንዲቆሙ ፈቅዶ ሌሎቻችን ደግሞ እንደምን እየተንገዳገድን በሰልፍ ቆምንና ተበጉ ሲናል በሰልፍ ተጉዘን ከሰፈሩ ትንሽ ወጣ ብለን ሜዳ ላይ ደርሰን እዚ ላይ ተጸዳዱ ተባልን። ወንዶች በአንድ በኩል ስንሆን ሴቶች ከኛ ትንሽ ገለል ብለው ሁሉም ለመጸዳዳት ቁጭ አለ። ሁሉም ተጸዳድቶ ካበቃ በኋላ ስንሄድ እንደሄድነው ተሰልፈን ወደ እስርቤቱ ተመለስን። ወደ 11 ሰዓት አከባቢ እንደ ቀኑ የማሽላ ዱቄት ገንፎ በምስር ወጥ በልተን ግቢው ውስጥ ያለ ምንም ምንጣፍና ከላይ የሚለብስ አንሶላ ተኙ ተባልን። ቀን ላይ ሙቀት ስለነበር እራቆት መሆን ምንም አልተሰማንም ነበር። ሲመሽ ግን ትንሽ ቀዝቀዝ ስላለ የሆነ የሚለበስ አንሶላ ብጤ ያስፈልገን ነበር። ነገር ግን ምንም ስላልነበረን እንዲሁ በደረቁ መሬት ላይ ተጋደምን። ከብርዱና ከመሬቱ መቆርቆር ይበልጥ ቀጣዩ እጣ ፋንታችን ምን ሊሆን ይችላል የሜልው ሃሳብ ይበልጥ አስጨነቅኝና በግሌም ሆነ ከሌሎቹ ጓዶች ጋራ ምን ማድረግ እንዳለብን ማሰላሰል ጀመርኩ። ረጂም መንገድ በሃሳብ ባህር ከተጓዝኩ በኋላ ከገዳሪፍ ወደ መተማ በእስር የተጓዝነው ጉዞ በጣም አድክሞን ስለነበረ ብርዱም መቆርቆሩም የሃሳብ ጭንቀቱም ቢኖርም እንቅልፍ ወስዶኝ ለተወሰነ ሰዓት ተኛሁ። ወደ ንጋት ላይ ግን ብርዱም መቆርቆሩም ስለተሰማኝ ነቅቼ ከዛ በኋላ መተኛት አልቻልኩ።
በማግስቱ ገና እንደነጋ ለመጸዳዳት ተሰለፉ ተብለን በጥዋቱ እንደ ማታው ተሰልፈን ወደ ሜዳው ወጥተን ተጸዳዳን። ተጸዳድተን እንደተመለስን ለቁርስ ትንሽ ስኳር፣ ቀጠፍና ማሽላ ዱቄት በየቡድናችን ልክ ተሰፈረልን። የነበሩት ብረት ምጣዶችና ብረት ድስቶች የተወሰኑ ስለነበሩ የግድ ተራ መጠበቅ ነበረብን። እግዚሄር ይስጠው ምጣዶቹንና ብረት ድስቶቹን አጠቃቀም ተራ መዳቢው እስረኛ እኛ መጀመሪያ እንድንጋግርና ሻይ እንድናፈላ ስለወሰነ ቅድሚያ ተሰጥቶን የማሽላ ቂጣ ሁለቱ የቁስለኛ ጓዶች መጋቢ የነበሩ ሴቶች ተጋግሮ ለያዳንዳችን ሩብ ቂጣ ታድሎን ቂጣ በሻይ ቁርሳችን በላን። ከቁርስ በኋላ ማታ ላይ ለብቻዬ ሳብሰለስለው የነበርውን ሃሳብ አብረውኝ ለነበሩ 3ቱ ነባር አባላትም አካፍልኩዋቸውና ይህ ዓይነት አጋጣሚ ለወደፊቱ ላናገኝ ስልምንችል፣ ሊለያዩንም ስለምቻል አሁን ባለን አጋጣሚ ምን ማለት ኣነዳለብን፣ ምን ማመን እንዳለብን፣ ምን ደግሞ የፈለገው ነገር ቢመጣ ማመን እንደሌለብን እንመካከር ተባባልንና በሚገባ ተመካክረን ለቀጣዩ ሊቀርብልን ለምችል ምርመራ ተዘጋጀን።
አራታችን ተነጋግረን ከጨረስን በኋላ ሲጠብቁን ለነበሩት የህወሓት ታጋዮች ከመሪዎቻቸው ጋር ለመነጋገር እንደምንፈልግ ነገርኩዋቸው። ጠባቂዎቻችን አማርኛ በቅጡ መናገር የማይችሉ ትግርኛ ተናጋሪ ወጣት አርሶ አደሮች የነበሩ ሲሆኑ በውቅቱ እኛ ከሱዳን የታፍን የኢህ አፓ አባላት የነበርንበት ፊዚካል ሁኔታ ያሳዘናቸው መሆኑ በቃላት ባይገልጹም በፊታቸው በሚገባ ይነበብ ነበርና ጥያቄየን ተቀብለው ወደ አለቃቸው አስተላለፈ። የጥበቃ ሃላፊውም መጥቶ እናንተ እዚህ የምትቆዩት በጊዜያዊነት ብቻ ስለሆነ መቼ እንድሚወስዱዋችሁ ባላውቅም በቶሎ ወደ ሌላ ቦታ ስለምትወሰዱ እስከዛው በትዕግስት ጠብቁ ብሎ በትህትና ነገረኝ። ከዚህ በኋላ ሌላ ነገር ከሱ ዓቅም በላይ መሆኑ ስለተረዳሁ እኔም ሌላ ጥያቄዎቼን አቁሜ መጠባበቅ ጀመርን።
በግምት ወደ 8 ሰዓት አከባቢ ሲሆን አንድ ባለስልጣን መጣና የኢህአፓ አባላት የሆናችሁ ለመንቀሳቀስ ተዘጋጁ ብሎን ሄደ። ከትንሽ ደቂቃዎች በኋላ የተወሰኑ ወደ አንድ ጋንታ የሚሆኑ የህወሓት ታጋዮች መጡና ከእስርቤቱ ግቢ እንድንወጣ ነገሩን። መደገፍ ያለባቸውን ጓዶች መደገፍ የምችሉ ጓዶች ደግፈው ከእስርቤቱ ግቢ ወጥተን ወደ መኪና መንገዱ ሄድን። አንድ ትልቅ ራሺያ ሰራሽ የወታደር መኪና በከተማዋ ማኸል ላይ ቆሞ ጠበቀንና በመኪናዋ ተሳፈሩ ተባልን። የተወሰኑ የህወሓት ታጋዮች በጋቢናው ላይ ተቀምጠው እየጠበቁን ሌሎች ደግሞ ከኋላችንና ከፊታችን በሌላ መኪና ተጭነው እየመሩንና እየተከተሉን ጉዞው ከመተማ ወደ ውስጥ ወደ ኢትዮዽያ ቀጠለ። እኔ አከባቢውን ባላውቀውም የሚያውቁ የነበሩ የሰራዊቱ አባላት የነበሩ ቁስለኞች ወደ ሸሄዲ አቀጣጫ እየሄድን መሆናችንን ነገሩኝ። ከተወሰነ ጉዞ በኋላም ጓዶቹ እንዳሉት ማምሻው ላይ ሸሄዲ ከተማ ደርሰን አንድ ትለቅ መክዘን ባለው ጊቢ ውስጥ ገብቶ መኪናው ቆሞ እንድንወርድ ተደረገ። ከመክዘኑ ውጭ ግቢው ውስጥ አራግፈውን እግቢው ውስጥ እራታችን እንድናበስል የተወሰነ እንጨት ዱቄት፣ ዘይት፣ ጨውና ያ የተለመደው የተከካ ምስር ሰጡን። ደህና የነበሩ ጓዶች ገንፎውን አገንፍተው ምስሩን ወጥ ሰርተው እራታችን በላን። እራት እንደበላን በትልቁ መካዝን ውስጥ እንድንገባ ተደርጎ በሩን ከውጭ ዘጉብን። መክዘኑ የሆነ ከሚካል የሚቀመጥብት የነበረና ለብዙ ጊዜ ተዘግቶ የቆየ ስለነበረ መጥፎ ሽታው አይጣል ነበር። ከከሚካሉ ጋር በተያያዘም ገና እንደገባን ለሆነ ነገር አለርጂክ ሆነን ብዙዎቻችንን የሳክክን ጀመረ። በሽታውና በማሳከኩም ምክንያት እንቅልፍ የሚባል ነገር ዓይኔ ላይ ዞር ሳይል ሌሊቱ ነጋ። እደነጋም ከመክዘኑ አውጥተው የሆነ ሜዳ ላይ እንደንጸዳዳ ተደርጎ ወደ መኸል ከተማ ተወሰድን ከመተማ ባመጣን ትልቁ የወታደር መኪና ተሳፍረን ጉዞው ከሸሄዲ ወደ ጎንደር የሚወስደው ዋና አውራ ጎዳና ይዞ ቀጠለና ጠመዝማዛ ዳገትን ወጥተን ደጋላ ትንሽ ከተጓዝን በኋላ አምባጊዮርስ ከተማን ደረስን። አምባጊዮርጊስ ላይ ጠባቂዎቻችን ተራ በተራ ምሳ ለመብላት እንዲሄዱ ተነገራቸውና የተወሰኑት እኛን እየጠበቁ ሌሎቹ ምሳ ለመብላት ሄዱ። ምሳ በልተው ያልበሉትን ለመተካት የመጡት ጠባቂዎቻችን በሶስት ሰሃን ላይ እንጀራውን ከሽሮ ወጥ ጋር አደባልቅ ይዘውን መጡና እኛም ምሳችንን በመኪናዋ ላይ እያን በላን። ምሳችን በልተን እንደጨረስን ከአምባጊዮርጊስ ወደ ጎንደር የሚሄዱ የተወሰኑ ሰዎች እኛ ጋር እንዲሳፈሩ ተደርጎ ጎዞው ወደ ጎንደር ቀጠለ። ወደ 4 ሰዓት ገደማ ደግሞ አዘዞ ከተማን ደርስን መከናው ከአዘዞ ወደ ጎንደር ከተማ ከሚወስደው አውራ መንገድ ወደ አዘዞ አይሮፕላን ማረፊያ በኩል ወጣ ብሎ በርከት ያሉ ቤቶች በመደዳ ባሉበት ቦታ ላይ ቆመ ። መኪናው እንደቆመ የኢህአፓ/ሰ አባላት የነበርን ብቻ እንድንወርድ ተነገረንና ስንደወርድ ከአምባጊዮርጊስ አብረውን የተሳፈሩ ሰዎች በመኪና ላይ ቀሩ። ከመኪናው እንደወረድን አከባቢው እንዳለ በጣም በተጎሳቆሉና ያደፈና የተቀዳደደ ልብስ በለበሱ፣ አንዳንዱ ጋምባሌ ባደረጉ ወጣት አርሶ አደሮች ተሞላ። ማንነታቸው ለማወቅ እየጓጓሁ እያለሁ አጠገቤ የነበረው አንድ ቁስለኛ ጓድ የኢህአሰ አባላት ናቸው አለኝ። ከዛም ከኛ ጋር የመጡ ቁስለኞቹና እቦታው የቆዩት የሰራዊቱ አባላት አንዳንዶቹ እየተቃቀፉ መሳሳም ጀመሩ። ቀጥለውም ዳር ቆመን ስንመለከት የነበርነው እኛንም እየመጡ ሰላም አሉን። ከትንሽ ቆይታ በኋላም ከጸለምት ጀምሮ የማውቀው ነባር ጓድና በተለያየ ጊዜ ሱዳን ድረስ እየመጣ የኢህአፓ ጸ/ቤት ሳየው የነበረ አንድ ሌላ ጓድም እዛው አግኝተን ተሳስመን ማውራት ጀመርን።

በክፍል 3 - የአዘዞ የእስርቤት ቆይታ ምን ይመስል ነበር ይጄላችሁ እቀርባለሁና እስከዛው በቸር ቆዩ ።

▼▼ ክፍል 3 ን ለማንበብ ወደታች ይቀጥሉ ▼▼


selam sew
Leader
Leader
Posts: 593
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

Re: 4 የሰቆቃ ዓመታት በህወሓት እስርቤት - ክፍል 3

Unread post by selam sew » 30 Mar 2016 13:04

4 የሰቆቃ ዓመታት በህወሓት እስርቤት፣ በየነ ገብራይ ከደንማርክ


ክፍል ሶስት፣ እስራትና የመጀመሪያ ምርመራ በአዘዞ፣

አዘዞ የደረስነው በግምት በኢትዮዽያ ሰዓት አቆጣጠር ወደ 11 ሰዓት አከባቢ ነበር። እራት ተበልቶ ካለቀ በኋላ ስለነበረ የደረስነው ከቋራ በጦርነት ተማርከው አዘዞ የቆዩት የኢህአሰ አባላት ተቀላጥፈው ዱቄት አሰፍረው፣ ገንፎ አገንፍተው የምስር ወጥንም ሰርተው እራታችን በላን። እራት እንደበላን መጀመሪያ ከሜዳ የማረኩዋቸው የኢህ አሰ አባላትን ግቡ ብለው ሁለት ተለቅ ያሉ ክፍሎች ውስጥ አጎሩዋቸው። ቀጥለው እኛን ደግሞ በሶስተኛው ክፍል ግቡ አሉንና እንደታዘዝነው እክፍሉ ገብተን በሩ ከውጭ ተቆለፈብን። የገባንበት ክፍል ብዙ ጊዜ ሰው ሳይገባበት ተዘግቶ የቆየ ስለነበረ እንደገባን ገና ቁጭ ሳንል ተርበው የቆዩ ቁንጮችና ትዃኖች ይወሩን ጀመር። ብዙ ስለነበርን ስለተከፋፈልናቸው እንጂ ለጥቂት ሰዎች ተባዮቹ የሚቻሉ አልነበሩም። እኛ ከቁንጫውና ከቱዃኑ እየታገልን እያለን ከጎናችን ክፍል የነበሩ የሜዳ ጓዶች ለዘመናት የሚለው የኢህአሰ መዝሙር ጮክ ብለው መዘመር ጀመሩ። የክፎሎቹ ግድግዳ በእንጨትና በጭቃ ብቻ የሚለይ ስለነበረ ድምጻቸው በኛ ክፍልም በደምብ ይሰማ ስለነበረ እኛ ክፍል ውስጥ የነበሩ በተለይ ቁስለኞቹም ከጓዶቹ ጋር ለዘመናት መዘመሩን ተቀላቀሉና ዘምረው ጨረሱ። ከጎናችን ክፍል የነበሩ የሜዳ ጓዶቹ መዝሙራቸውን ጨርሰው ሲተኙ እኛ ክፍል የነበርን ግን ብዙዋቻችን በብርዱም በቁንጫውም ምክንያት መተኛት አልቻልንምና ነበረና ሌሊቱ ምንም ስንተኛ ነጋ።
በማግስቱ ንጋት ላይ ገና ሌሊቱ በደንብ ሳይነጋ በሩ በሃይል ተንኳካና ለሽንት ተዘጋጁ የሚል ድምጽ ተሰማ ሁላችንም ተዘጋጅተን ተጠባበቅን። የኛ ተራ እንደደረሰ ሁለት ጋንታ በቀኝና በግራ በኩል አጅበውን እኛ ማኸል ላይ ተሰልፈን ወደ ምስራቅ አቀጣጫ ሄድን። በስተግራ በኩል የአይሮፕላን ማኮብኮቢያ መንገድ በግልጽ ይታይል። አጠገቡ ደግሞ የፈራረሰ ትልቅ የሆነ መክዘን የነበረ የሚመስል ህነጻ ነበረ። እዛው ስንደርስ እዚሁ ተጸዳዱ ተባልንና እዛ የፈራረሰው መክዘን ገብተን ለመቀመጥ ስንሞክር ቦታው በሙሉ በሰገራ ሞልቶ መቀመጫ አጣንበትና ወጣ ብለን እመክዘኑ ዙሪያ ተጸዳድተን እንደመጣነው ተሰልፈን ግራና ቀኝ ታጅበን ወደ እስርቤቱ ተመለስን። ቀድመው ተጸዳድተው የጨረሱ የሰራዊቱ አባላት ከእስርቤቱ በራፍ አከባቢ ባለው ትንሽ ሜዳ በቡድን ተሰበስበው ሲያወሩ ጠበቁንና እኛም ተቀላቀልናቸው። ማታ ጊዜ በማጠሩ ያልጨረስነው የርስበርስ መጠያየቅ በቡድን በቡድን በመሆን ቀጠልን።እኔ ከድሮ ጀምሮ ከማውቀው የሜዳ ጓድ ጋር ስለ ሜዳ ማወቅ የምፈልገውን በዝርዝር ጠየቅኩትና እሱም የሚያወቀውን ያህል በዝርዝር አወጋኝ። እኛ ከተለያዩ ጓዶች ጋር እያወራን እያለን የተወሰኑ የሜዳ ጓዶች የሆነ ዳቦ አትለው ቂጣ ነገር ጋግረው ሻይ አፍልተው ቁርስ አቀረቡልንና ዳቦ በሻይ ቁርስ በልተን መጨዋወቱ እስከ ምሳ ሰዓት ቀጠለ።
ከጓዶቹ በተለያየ ጊዜ ኢህአሰና ህወሓት/ኢህአዴግ በጎጃምና በጎንደር/ቋራ አከባቢ ብዙ ውግያዎች እንዳደረጉ፣ በርካታ ጓዶች እንደተሰዉ፣ ውግያው እንደበፊቱ ባይሆንም በተለይ በቋራ ቆላማው አከባቢ እንደቀጠለና ህወሓት/ኢህአዴግ ኢህአሰን እንዳለ ለማጥፋት በጣም ብዙ ሰራዊት አሰማርቶ እንደነበረ ከጓዶቹ ለማወቅ ቻልን። በዚህ ሁኔታ ጭውውቱ እስከ ምሳ ሰዓት ቀጠለ። ምሳ በልተን እንደጨረስን አንድ ባለስልጣን መጥቶ ከሱዳን የመጣችሁ ወደዚህ ተለዩ አለን። እንደተለየን የሁላችን ስም ዝርዝርና በሱዳን በድርጅቱ ውስጥ የነበረን ሃላፊነት ከተመዘገበ በኋላ ሌሎቹ ወደ ቀሩት ጓዶች ሲመለሱ፣ አራታችን ሲኒየር አባላት ተለይተን እንድንቀር ተደረገና ተራ በተራ እየተጠራን የመጀመሪያ ምርመራ ተጀመረ።
የመጀመሪያ ምርመራ ያደረጉልን መርማሪዎቹ አንድ የወታደር ልብስ የለበሰና አንድ ሲቪል ልብስ የለበሰ ነበሩ። ከኔ ቀድሞ አንድ ጓድ ተጠርቶ ወደ ምርመራ ክፍሉ ሄደ። ከሱ ቀጥዬ እኔ ተጠራሁና ወደ ምርመራ ክፍሉ ሄድኩ። እክፍሉ እንደገባሁ ከፊታቸው ከተዘጋጀው ወንበር እንድቀመጥ የሲቭል ልብስ የለበሰው መርማሪ በትግርኛ ነገረኝ። ቁጭ እንዳልኩ ከተወለድክበት ዕለት ጀምሮ ህይወት ታሪኬን በዝርዝር እንድነግራቸው ጠየቀኝ። ሲያስፈልገው በመሃል እያስቆመ ይበልጥ እንዳብራራላቸው የሚፈልጉት ነገር ሲኖር እየጠየቀኝ የህይወት ታሪኬ ምዝገባ ካበቃ በኋላ ለዛሬው ጨርሰናልና መሄድ ትችላለህ አለኝ። እነሱ ጥያቄያቸውን ከጨረሹ በኋላ እኔ በተራዬ አንዳንድ ጥያቄዎችና ሃሳቦች አሉኝና መጠየቅ እችላለሁ ወይ ብዬ ስጠይቀው፣ ወታደራዊ ልብስ የለበሰው አትችልም ሂድ ሲለኝ፣ ሲቪል ልብስ የለበሰው ተወው ይጠይቅ ብሎ ለሱ መልሶለት መተየቅ የምትፈልገውን ጠይቅ አለኝ።
ለመሄድ ተነሽቼ የነበረ ተምልሼ እውንበሩ ላይ ቁጭ ብዬ፣ በመጀመሪያ ከሱዳን እስከ መተማ ሲያጓግዙን እጅና እግራችን ወደ ኋላ አንድ ላይ ተጠፍሮ ታስረን የተጓዝን ሁላችን በደረታችን፣ በእጆቻችና በእግሮቻችን ከባድ ስቃይ ስላለን ህክምና እንፈልጋለን፣ ሁለተኛ እንደምታዩት እኔ የለበስኩት ይህ የምታዩት ካናተራና ፒጃማ ብቻ ነው፣ ሌሎች ጓዶችም ልብስ የላቸውም፣ከስቃዩ ጋር ብርዱን ልንቋቋመው አልቻልንም፣ በተለይ ሴቶቹ ደግሞ የውስጥ ልብስ ብቻ እንደለበሱ ነውና የሆነ የሚለበስ እንፈልጋለን፣ በተጨማሪም ምንም የሌሊት ልብስና ምንጣፍ የሚባል ነገር የለንም፣ ትናትና እንዲሁ እራቆታችን ባዶ ወለል ላይ ተጋድመን ሳንተኛ ነው ያደርነው። ሌላ ላሳውቃችሁ የምፈልገው ከሱዳን ከመጣን የኢህአፓ አባላት የሆን 4 ብቻ ነን፣ ሁለት ሴቶች ከኢህአፓ ጋራ ምንም ግኑኝነት የሌላቸው ቁስለኞችን እንዲመግቡና እንዲንከባከቡ በገንዝብ የተቀጠሩ ናቸው፣ አንዲት ሴት የምትጠባ የ9 ወር ህጻንና የሁለት ዓመት ህጻን ልጆችን ሱዳን ትታ የታፈነች ናት፣ እሷ የአንድ ጓድ ባለቤት ናት እንጂ ከኢህ አፓ ጋራ ምንም ዓይነት ግኑኝነት የላትም፣ ቁስለኞቹና አካለ ስንኩላኑም ተዋጉ ሲባሉ ደርግን ተዋግተው የቆሰሉና አካላቸው የጎደሉ አርሶ አደር የሰራዊት አባላት እንጂ የፓርቲው አባላት ስላልሆኑ ለነዚህ ሰዎች አስቸኳይ መፍትሄ ቢሰጣቸውና በኢህ አፓ አባልነት መጠየቅ ያልብን ጥያቄ ሆነ ሌላ ነገር ካለ አራታችን ብቻ መጠየቅ አለብን አልኩ። ሃሳቤን ካዳመጠ በኋላ ሲቪል ልብስ የለበሰው መርማሪ፣ የህክምናው ጉዳይ ቀስ ብለን እናያለን፣ ስለ ልብሱ ያልከው ማድረግ የሚቻል ካለ እናያለን፣ የሌሊት ልብስና ምንጣፍ ስላልከውም ለሚመለከታቸው እንነግራለን። ከ4ታችሁ ውጭ ያሉትን በተመለከተ ምንም ምርመራ አያስፈልግም፣ የተወሰነ ኦሪየንተሽን ከተሰጣቸው በኋላ እንደየምርጫቸው እናሰነብታቸዋል ብሎ ባጭሩ መለሰልኝ።
እኔ በመቀጠል ስለ ቁስለኞቹ ያለከው ተገቢ ነው ግን ከኢህአፓ ጋር ምንም ግኑኝነት የሌላቸው 2ቱ ሰቶችና የህጻናቱ እናት በተመለከተ ግን አሁኑኑ አንድ መፍትሄ ቢሰጣቸው መልካም ይመስለኛል፣ የህጻናቱ እናት አሁን ህጻኗ ስትጠባው የነበረ ጡት በወተት ሞልቶ ወተቱ በደረቷ ላይ እየፈሰሰ ነው በተለይ የሷ ጉዳይ ከሰብኣዊነት አንጻር ታይቶ አስቸኳይ መፍትሄ የሚያስፈልገው ይመስለኛል አልኩት። ይህ ጊዜ ወታደራዊ ልብስ የለበሰው የምንወስነው እኛ ነን፣ አንተ ምን ማድረግ እዳለብን ልትነግረን አትችልም፣ ብሎ በጣም ተቆጥቶ ሲጋራውን አውጥቶ ለኮሰ። እኔ ደግሞ የኔ ውንድም እኔ እንደ አንድ ሃላፊነት የሚሰማው ሰው መፍትሄ ይሆናል ያልኩት ሃሳብ ነው ያቀረብኩት እንጂ ይህን ማድረግ አለባችሁ ብዬ አልወስንኩም፣ በዚህ ሃሳቤ ቅር ካለህ ደግሞ ይቅረታ አልኩት። ያ ሲቭል ልብስ የለበሰው ምንም አይደለም ሃሳብ ማቅረብህም ምንም ችግር የለውም ብሎ እሱም ሮዝማን ሲጋራውን ከኪሱ አውጥቶ ማጨስ ጀመረ። ለ4 ቀን ምንም ሳለጨስ ስለቆዩ የሮዝማን ሲጋራ ሺታና ከአፋቸው ቦሎል እያለ ሲወጣ የነበረ ጭስ የሲጋራ አምሮቴን ክፉኛ ቀሰቀስወና አንድ ሲጋራ ልተሰጠኝ ትችላል ወይ ብዬ የሲቪል ልብስ የለበሰውን መርማሪ ጠየቁኩት። ታጨሳለንዴ አለኝና የረጂም ዘመን አጫሽ መሆኔን ስነግረው አንድ ሲጋራ አውጥቶ ሰጠኝና ሎከሰልኝ። በጣም አምሮኝ ስለነበረ እንደቆምኩ በረጅሙ ሁለቴ ስስበው አዞረኝና ልወድቅ ስንገዳገድ ተቀምጬበት ወደነበረው ወንበር ሂጄ ቁጭ አልኩኝ። ሲቨል የለበሰው መርማሪ ቁጭ ብለህ አጭሰህ ጨርሰው አለኝና ቁጭ ብዬ ሲጋራየን ጨርሼ ልወጣ ስል እንካ ይዘህ ሂድ ብሎ ፓከቱን ሰጠኝ። በፓከቱ እሱና እኔ አንድ አንድ አንስተንለት 18 ሲጋራ ነበረውና አምስግኜ ስጋራዬን ይጄው ከምርመራ ክፍሉ ወጣሁ።
4ታችን አንድ በአንድ እየተጠራን ምርመራውን እንደጨረስን ምን ዓይንት ጥያቄዎች ለያንዳንዳችን እንደቀረቡ ስንጠያየቅ ለሁላችን የቀረቡ ጥያቄዎች አንድ ዓይነት እንደነበሩ ለማወቅ ቻልን። ኑሮአችን አንድ ክፍል ውስጥ ስለነበረ ቀጣዩ ምርመራ ምን ሊመስል እንደምችል፣ ምን ዓይንት ጥያቄዎች ሊቀርቡልን እንደምችሉና እኛ ምን ማድረግ እንዳለብን ለመመካከር ይህ የመጀመሪያ ምርመራ ጥሩ ዕድል ሰጠን። ከምርመራው በኋላ ምሳ በልተን ትንሽ እንደቆየን ከሱዳን የመጣችሁ ወደዚህ ቅረቡ ተባልንና ለምንጣፍ አንዳንድ ኬሻ፣ ለሌሊት ልብስ ደግሞ አቡጀዲድ በጣቃ መጥቶ እየተለካ እየተቆረጠ ለያንዳንዳችን ወደ 4 ሜትር ተሰጠንና ሜዳ የነበሩ የሰራዊቱ አባላት አንሶላውን ሰፉልን፣ ቀሪው ጊዜ የተለመዱ ምግብ መመገብ፣ ወደ ሽንት ቤት መሄድና በቡድን በቡድን በመሆን በማውራት ተገባደደና ማምሻው ላይ ወደየ ክፍላችን ገብተን እንደተለመደው በሩ ከውጭ ተዘጋብን። ክፍላችን ጓዶች ቀን ላይ ውሃ አርከፍክፈው በሚገባ ስለጠረጉት ቁንጨውና ትዃኑ እንደ ትናንትና አላሰቃዩንም። በተጨማሪም ለምንጣፍ ኬሻና የሚለበስ አንሶላም ስለተሰጠን ኬሻውን አንጥፈን የተወሰኑ አንሶላዎችም ላዩ ላይ ደርበን ስለተኛን የተሻለ እንቅልፍ ለመተኛት ቻልን። በሁለተኛ ቀን እርስ በርሳችን እያወራንና ያ የተለመደው በተወሰነ ሰዓት መመገብ፣ ወደ መጸዳጃ ቦታ መሄድ ውጭ ቀኑን ሙሉ እንደፈለግነው ከምንፈልገው ሰው ጋር እያወራን ውለን ማታ ወደ ማጎሪያ ክፍላችን ገባን።።
በሶስተኛው ቀን ተጸዳድተን ቁርስ እንደበላን ከሜዳ የተማረኩና ከ4ታችን ሲኒየር አባላት ውጭ የነበሩ ከሱዳን የታፈኑ ቁስለኞች፣ የሁለቱ ጓዶች ባለቤቶችና ሁለቱ የቁስለኛ ጓዶች ሰራተኞች አንድ ላይ ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ ተዘጋጁ ተባሉ። ወዴት ልትወስዱዋቸው ነው ብዬ ለአንዱ በቦታው የነበረ ባለስልጣን ስጠይቀው ኦሬንተሽን ለመስጠት ወደ ትግራይ ልንወስዳቸው ነው አለኝ። ካጭር ኦረንተሽን በኋላ ደግሞ ወደየፈለጉበት እንሰዳቸዋለን አለኝ። ይህን እያወራን እያለን 4 ትልልቅ የወታደር መኪናዎች መጡና ከሜዳ የተማረኩት በርከት ያሉና ከ4ታችን ሲንየር አባላት ጋራ ከሱዳን የታፈኑት 18ቱ በመኪናዎቹ ላይ እንወጡ ታዘዙ። ጓዶቹ እኛን ተሰናብትው በታዘዙት መሰረት ወደ መኪናዎቹ ወጥተው እንደጨረሱ መኪናዎቹ ከቦታው ተንቀሳቀሱና እኛ ከሱዳን የመጣን 4ና አንድ ከሜዳ የተማረከ ጓድ አዘዞ ላይ ተለይተን እንድንቀር ተደረገ።
5ታችን ተለይተን ከቀረን በኋላ ለ5ታችን የምትበቃ አንዲት ጠባብ ተዘግታ የነበረች ክፍል ውስጥ እንድንገባ ተነገረንና የምትጠብቀን የነበርችው ሀይል መሪ የነበረ ሰው መመሪያ እክፍሏ ውስጥ ለመስጠት አብሮን ገባ። ልክ እንደገባን ቁንጫዎቹ እንደ አንድ ነገር ወረሩንና አብሮን የገባው መሪ የቁንጫዎቹ ወረራ ሊቋቋመው ስላልቻለ ዘሎ ወደ ውጭ ወጣ። እኛንም ኑ ውጡ አለንና በሉ አሁን ክፍሏን ውሀ አርከፍክፋችሁ በደምብ አጽዷትና እንደጨረሳችሁ ለዋርዲያው ንገሩትና ከዛ እኔ መጥቼ እዚህ እስካላችሁ ድረስ ማድረግ ስላለባችሁ ነገር አንዳንድ መመሪያዎች እሰጣችኋለሁ ብሎን ሄደ። ከሱዳ ከመጣን አንዱ አካለስንኩል ስለነበረ የቀረነው ደግሞ ያ እጅና እግራችን አንድ ላይ ተጠፍሮ ከገዳሪፍ እስከ መተማ በተጋዝነው ጉዞ ጊዜ ከደረሰብን ጉዳት ገና በደንብ ስላላገገምን ብዙ ልንረዳ አንችልም ነበር። ከሜዳ የተማረከው ጓድ ክፍሏን ውሃ ረጭቶ ወለሉንም ግድግደውንም በደንብ አድርጎ ከሁለት ጊዜ በላይ ከጠረገው በኋላ የሆነ ቅጠልና እንጨት በአንድ ሶስት ቦታ ላይ አንድቦ ክፍሉ በጭስ እንዲታፍን በሩን ለተወሰኑ ደቂቃዎች ዘጋውና ከአንድ ግማሽ ሰዓት በኋላ ክፍሉ ተመልሶ ሲከፈት የክፍሉ ሽታም ተቀየረ፣ ቁንጫዎቹም ጠፉ። እንደታዘዝነውም የክፍሉ ጽዳት መጨረሳችን ለዋርዲያው ነግረን የጥበቃው ሃይል መሪ ንዲመጣ ተደረገ።
የምትጠብቀን የነበረችው ሀይል መሪ መጣና ስሜ ገብረሚካኤል እባላለሁ፣ ከንግዲህ እዚህ እሰካላችሁ ድረስ ማንኛውም ነገር ሲያስፈልጋችሁ የምትጠይቁት እኔን ብቻ ነው፣ ጠባቂዎቻችሁ አድርጉ የሚሉዋችሁን ማደርግ አለባችሁ፣ ትክክል ያለመሰላችሁ እንኳን አድርጉ ቢሉዋችሁ ዝምብላችሁ ማድረግ ብቻ ነው ያለባችሁ፣ ከዛ እኔ ስመጣ ከኔ ጋር መነጋገር ትችላላችሁ፣ምግብን በተመለከ እንጀራና የቁርስ ዳቦ ከምትጠብቃችሁ ጋንታ ጋር አብሮ ይጋገራል፣ ለቁርስ ሻይም አብሮ ይፈላል። ወጥ ግን በየቀኑ ራሳችሁ ማተሪያሉን ከጋንታዋ እየተረከባችሁ ራስችሁ ነው የምታዘጋጁት ብሎ መመሪያውን ከሰጠን በኋላ ሌላ ጥያቄ ካለችሁ አለን። እኔ አዎ አንዳንድ አስቸኳይ መፍትሄ የሚያስፈልጋቸው ችግሮች አሉብን፣ እንደምታየው የለበስነው ልብስ የምታየው ነው፣ ብርዱን ፈጽሞ አልቻልነውም፣ ሶስታችን ከሱዳን እሰከ መተማ ታስረን የመጣንበት ሁኔታ በጣም መጥፎ ስለነበረ እጃችንና እግራችን ክፉኛ ተጎድቷልና ህክምና እንፈልጋለን፣ እኔ ቀኝ እጄ አሁን ምንም ስሜት የለውም፣ ፓራላይዝ የሆነ ይመስለኛል አልኩት። በሁኔታው በጣም አዘነና ጥያቄዎቻችሁን ለሚመከታቸው አቀርባለሁ፣ ከዚህ ውጭ ለጊዜው ሌላ ነገር ለማድረግ አልችልም ብሎ ሲመልስ፣ ያ ከሜዳ የተማረከው ጓድ በሰራዊቱ ውስጥ በህክምና ሞያ ለረጅም ዓመታት ያገለገል ስለነበረው ለጊዜው የሆነ ማሻ ቅባት ስሙን ነግሮ ከፋርማሲ ብታመጣልኝ እኔ ላሻቸው እችላለሁ፣ ይህ ደግሞ በጣም ሊረዳቸው ይችላል ሲለው ሃይል መሪው ስሙን ጻፍልኛና አሁን ሂጄ አመጣልህ አለሁ ብሎ መኪናውን አስነስቶ ሄደ። በግምት ከአንድ ሰዓት በኋላም ቅባቱንና የተወሰኑ ልብሶች ከራሱም ከሌሎች የኃይሏ አባላትም አሰብስቦ ይዞልን መጣ፣ ባመጣልን ሸሚዞችና ጃከቶችም በተወሰነ ደርጃም ከብርዱ ተገላገልን።
የጥበቃ ሃይሏ መሪ የተማረ፣ ለተወስኑ ዓመታትም በደርግ እስርቤት ያሳለፈና ሁኔታዎችን በሚገባ የሚረዳ ርህሩህ ሰው ነበር።ከሱ ውጭ የነበሩ ጠባቂዎቻችን ግን አማርኛ የማይችሉ ትግርኛ ብቻ የሚናገሩ የትግራይ አርሶ አደሮች ነበሩ፣ በተጨማሪም ስለ ኢህአፓ የተነገራቸው ኢህአፓ የትግራይ ህዝብ ጠላት፣ ትግራዊያንን እንደ ፍየል አርዶ ቆርበታቸውን የገፈፈ፣ እንደ ምሳሌ ብዘት ላይ የተገደለ የህወሓት አባል ቆዳውን ገፈውታል በሚል፣ የኢህአፓ አባላት በሙሉ አማራ ብቻ መሆናቸው እንዲያምኑ የተደረጉና በዚህ ምክንያትም ኢህአፓ ላይ ከፍተኛ ጥላቻ የነበራቸው ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በወቅቱ በቋራ ጦርነት እየተካሄደ ስለነበረና በጥርነቱም የተወስኑ የህወሓት አባላት ይገደሉና ይቆስሉም ስለነበረ ይህም ለጥላቻቸው ተጨማሪ ምክንያት ነበር። ስለሆነም ለተወሰኑ ቀናት ሃይል መሪው ተመልሶ እስከሚያስተካክለው ድረስ ለሽንት ከምንወጣበት ጊዜ ውጭ በሩ እንዲዘጋ፣ እክፍሉ ውስጥ እንዳናወራ የሚል መመሪያ ነበር የሰጡን። በሀይል መሪው በተነገረን መመሪያ መሰረትና ሁኔታውን በደምብ ስለተገነዘብን ከሀይል መሪው እስከምነገናኝ ያሉትን ማድረጉ ይሻላል በሚል እኛም ያሉትን ፈጸምን።
ሁለት ቀን በሩ ለሽንት ለመውጣት ብቻ እየተከፈተ፣ ከዚህ ውጭ እንደተዘጋብን አሳለፍን። ለሽንት ቤት መውጫ ሰዓት ውጭ ወደ ውጭ መውጣት የምችለው ወጥ የሚሰራ ተረኛ ብቻ ነበር። በሶስተኛ ቀን ሀይል መሪው የጥበቃው ሁኔታውን ለማየት መጥቶ ክፍላችን ሲመለከት በሩ ተዘግቶ ነበርና ለምን ተዘጋ ብሎ ሲጠይቅ በ06 መመሪያ መሰረት መዘጋት ስላለበት ዘጋነው አሉት። ከንግዲህ የነሱ በር መዘጋት ያለበት ከሰዓት በኋላ ተጸዳድተው ከተመለሱ በኋላ ብቻ መሆነ አለበት፣ ፀሀይ መሞቂያ ሰዓት 2 ሰዓት በቀን ከክፍሉ ወጥተው ውጭ እንዲቆዩ፣ የተቀረው ጊዜ በሩ ተክፍቶ እክፍላቸው እንደፈለጉ እንዲጫወቱ፣ ማታ እስከ 3 ሰዓት የሚያበሩት ኩራዝና ላምባ እንዲሰጣቸው በሚል ለምትጠብቀን ጋንታ ትእዛዝ አስተላለፈ፣ የተዘጋው በራችንም ወዲያውኑ ተከፈተ።
በአሳሪዎቻችን በኩል ምን ዓይንት አዲስ ምርመራ ሆነ ሌላ እርምጃ ሳይወሰድ አንድ ሳምንት ያ የተለመደው ጥዋት ሲነጋ ወደ ሽንትቤት መሄድ፣ በቁርስ ሰዓት ዳቦ በሻይ መብላት፣ ምሳ ሰዓት ላይ እንጀራ በምስር ወጥ መብላት፣ እርታ ከቀሙ ወደ 10 ሰዓት ላይ መብላት፣ ወደ ሽንትቤት መሄድና ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በሩ ከውጭ ተቆልፎ እስከ ንጋት በመተኛት አለፈ። በኛ በኩል ደግሞ ለወደፊቱ ሊኖር የምችለው ምርመራ ምን ሊሆን ይችላል፣ ምንስ ማድረግ አለብን በሚለው በስፋት እየተወያየንና ከእስርቤቱ ኑሮ ራሳችንን ይበልጥ እያስተዋውቀን ሳምንቱ አለፈ።

በክፍል 4 ፣ ህወሓት የኢህ አፓ ሲኒየር አባላት ከሱዳን ሲያሳፍን ዓላማው ምን ነበር፣ ይህ ዓላማውስ ለምን ከሸፈ፣ የሚለውን ይጄላችሁ እቀርባለሁ፣ እስከዛው በቸር ቆዩ።

ክፍል 4 በቅርብ ይለጠፋል


selam sew
Leader
Leader
Posts: 593
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

Re: 4 የሰቆቃ ዓመታት በህወሓት እስርቤት

Unread post by selam sew » 01 Apr 2016 13:58

4 የሰቆቃ ዓመታት በህወሓት እስርቤት፣

ክፍል 4 ፣ ህወሓት የኢህ አፓ ሲኒየር አባላት ከሱዳን ሲያሳፍን እቅዱ ምን ነበር፣ ይህ እቅዱስ ለምን ከሸፈ፣

በቀጥታ ወደ ጥያቄው መመለስ ከመግባቴ በፊት ከደርግ ግብአተ መሬት ቀደም ብሎ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሁለቱ ድርጀቶች ከደርግ መወገድ በኋላ መኖር ስለሚገባው ሽግግር ምን መሆን አለበት በሚለው የነበራቸው የአቋም ልዩነቶች ባጭሩ ማስቀመጥ ተገቢ ይሆናል። ህወሓት ከደርግ ውድቀት በኋላ መኖር ስለሚገባው ወደ ህዝብ የተመረጠ መንግስት ሽግግርና የኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ጥያቄ ላይ ከኢህ አፓና በወቅቱ ኢህ አፓ አባል ከነበረበት ኢዴሃቅ በጣም የተለየ አቋም ነበረው። ኢህ አፓና አባል የነበረበት ኢዴሃቅ ኢትዮጵያ ሲሉና ከደርግ ውድቀት በኋላ የምትኖረው ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ኤርትራንም የጨመርች እንድትሆን ያለመ ዓላማ ነበራቸው፣ ዝርዝሩን በዚህ ልንክ ገብታችሁ ማየት ትችላላችሁ። http://yatewlid.com/index_htm_files/Dem ... m_1982.pdf

ባንጻሩ ህውሓት ከደርግ ውድቀት በኋላ የምትኖረው ኢትዮጵያ ኤርትራ የተለያት እንድትሆን ያለመ ዓላማ ነበረው። የሽግግር መንግስቱ አመሰራረት በተመለከተም ኢዴሃቅ ሁሉም ተቃዋሚ ሃይሎች ህወሓት፣ ኦነግና ሻዕቢያንም ጭምር ያሳተፈ መሆን አለበት የሚል አቋም የነበረው ሲሆን፣ በህወሓት በኩል ኢዴሃቅን ያገለለ፣ ሻዕቢያ የራሱ መንግስት በኤርትራ እንዲመሰርት የሚፈቅድና በሽግግር መንግስቱ እሱ የሚፈልጋቸው ሃይሎች ብቻ የሳተፈ እንዲሆን ያለመ እቅድ ነበረው። ኢትዮጵያዊ የሆኑ በኢትዮጵያ ህዝብ ንብረትና ጉለበት በረጂም ዓመታት የተገነቡ ተቋማት ለምሳሌ የኢትዮጵያ መለዮ ለባሽ (ጦር ሰራዊቱና ፖሊሱ) ሃይል ዓነቶቹ በተመለከተ ኢዴሃቅ እነዚህ ተቋማት እንደ ተቋም መቀጠል አለባቸው፣ ካስፈለገ የተለያየ ወንጀል የፈጸሙ የበላይ መኮነኖች እንደ ወንጀላቸው ክበደት ታይቶ ሊወገዱ ይችላሉ የሚል አቋም የነበረው ሲሆን፣ ህወሓት ደግሞ በተለይ ሰራዊቱ እንዳለ መፈራረስ አለበት የሚል አቋም ነበረው። ኢዴሃቅ ከሁሉም ተቃዋሚዎች የሚመሰረተው የሽግግር መንግስት ዕድሜ ከሶስት እስከ አራት ዓመት ሆኖ በዚህ ወቅት ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች በነጻ ዓላማቸውን ሊኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያስተዋውቁ፣ በተለይ ኤርትራን በተመለከት ሻዕቢያ የኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠል አስፈላጊነት ላይ የራሱ አቋም ለመግለጽ ሙሉ መብት ኖሮት በሌላ በኩል ደግሞ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋራ መቀጠል ለኤርትራ ህዝብም ለተቀሩት የኢትዮጵያ ህዝቦችም እንደሚጠቅም፣ ለኤርትራ ህዝብ በዳዮቹ አገዛዞቹ እንጂ የተቀሩት የኢትዮጵያ ህዝቦች እንዳልሆኑ ማሰረዳና መስተማር የሚፈልጉ የአንድነት ሃይሎችም ሙሉ መብት ኖሮአቸው በሽግግሩ ወቅት እንዲያስተምሩና የሽግግር መንግስቱ ዕድሜ ሲያበቃ የኤርትራ ህዝብ ያለ አንዳች ተጽዕኖ ፍላጎቱ እንዲወስን እንዲደርግ የሚል አቋም ነበረው። ባንጻሩ ህወሓት የኤርትራ ህዝብ በኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት የተገዛ ህዝብ ስለሆነ ከደርግ ወድቀት በኋላ በቀጥታ ነጻነቱ ማግኘት አለበት የሚል አቋም ነበረው። ኢዴሃቅ በሽግግሩ መንግስት ወቅት ለወደፊቱ በኢትዮጵያ የመንግስት ስልጣን መያዝ የሚፈልጉ ፓርቲዎች ስለ ዓላማቸው ህዝቡን በነጻ አስተምረው ከዛ በኋላ ህዝቡ የሚፈልገውን ፓርቲ ወይም ፓርቲዎች የሚመርጥበት ነጻ ምርጫ ተዘጋጅቶ በዚህ ህዝባዊ ምርጫ ለሚመረጥ ፓርቲ ወይም ፓርቲዎች የሽግግር መንግስቱ ስልጣኑን ማስረከበ አለበት የሚል አቋም ነበረው።
ይህ ዓይነት የአቋም ልዩነት የነበራቸው ህወሓትና ኢህ አፓ በውቅቱ በወታደራዊ ሃይል በኩል እጅግ ትልቅ ልዩነት ነበራቸው፣ ህወሓት የመንግስት ስልጣን በጠምንጃ ሃይል ለመያዝ የሚያስችለው ብቃት ያለው ወታደራዊ አመራርና ዘመናዊና አስፈላጊ ትጥቅ ሁሉ ያሟላ መካናይዝድ ደረጃ ላይ የደረሰ ጦር ነበረው። ኢህ አፓ ግን ገና በጉሪላ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ብቻ የነበረ ደካማ አመራርና አነስተኛ ሰራዊት ነበረው። በውቅቱ ኢህ አፓና አባል የነበረበት ኢዴሃቅ ከህወሓት ጋራ ሲነጻጸሩ፣ በወታደራዊ ሃይል በኩል እጂግ ደካሞች ሲሆኑ በፖለቲካው ተደማጭነትና ተቀባይነት በኩል ከህወሓት የበለጡ ነበሩ። በወቅቱ ህወሓት ከትግራይ ህዝብ ውጭ ብዙ ተቀባይነትና ተደማጭነት አልነበረውም ቢባል ስህተት አይሆንም። ባንጻሩ በኢዴሃቅ ስር የተሰባሰቡ ሃይሎች በሞላዋ ሀገሪቱ ተደማጭነትም ተቀባይነትም ነበራቸው። በተለይ ኢህ አፓ ትንሽ ቢሆንም የተደራጀና የታጠቀ ስራዊት ነበረው፣ በተወሰኑ ከተሞች አዲስ አበባን ጨምሮ እንደ ቀድሞው የተጠናከረ ባይሆንም መዋቅሩን እየዘርጋ ነበር፣ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋራ የሚገናኝበትና በስፋት እየተደመጠ የነበር ራዲዮ ነበረው፣ በጎረቤት ሃገር ሱዳን ጠንካራ ድርጀታዊ እንውስቃሴና መዋቅርም ነበረው፣ . . . . ። ስለሆንም ህወሓት በኢዴሃቅ በውቅቱ ከፈተኛ ሚና የነበረውና ህወሓትን ከስር መሰረቱ ጠንቅቆ የሚያውቀውን ኢህ አፓን ለህልውናውና ለዓላማው ማሳካት ከኢተዮጵያ ፖለቲካ በነበረው የጠምንጃ የበላይነት ተጠቅሞ ለማጥፋት መስራት የግድ ይለው ነበር፣ ይህን ለማድረግ ደግሞ በኢትዮጵያ ሜዳና በአጎራባች ሱዳን የነበረውን የሀገርቤቱንና የውጩን ትግል በማገናኘት ከፈተኛ ሚና የነበረው የኢህ አፓን እንቅስቃሴ ይመሩና የካሄዱ የነበሩ የፓርቲው ሲንየር አባላት በመጀመሪያ ደረጃ ማጥፋት የግድ ነበርና ልክ ደርግ በወደቀ ማግስት በቋራና በሱዳን በኢህ አፓ ላይ ባንድ ጊዜ ዘመተ። ይህን ዘመቻውን ተግባራዊ ለመደርግ ደግሞ ከሱዳን መንግስት ጋራ በቅርበት በመስራት በሱዳን የድርጀቱን ሲኒየር አባላት ማንም ሳያውቅ አሳፍኖ ወደ ኢትዮጵያ በመውሰድ ለመግደ ያለመ ነበር አፈናው።
ይሀ እቅዱ ለምን ከሸፈ፣
ገና በ1983 ደርግ እንደወደቀና አጠላይ የኢህ አፓ እንቅስቃሴ በሱዳን እንደታገደ፣ በውቅቱ ሱዳን የነበርን የኢህ አፓ ሲንየር አባላት በሱዳን ደህንነቶችና በህወሓት ሲደረግብን የነበረው ክትትልና ተጽዕኖ በተመለከተ በየጊዜው የሚደረጉብን የነበሩ ክትትሎችና ተጽዕኖዎች ሱዳን ለነበሩት የUNHCR ባላስልጣኖች ሁኔታው እንደተፈጸመ ከነመርጃው በየጊዜው እናመልክት ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ከፈተኛ የሆነ አደጋ ውስጥ ናቸው ያልናቸው ጓዶች ስም ዝርዝር ሰጥተን በሱዳን ውስጥ ደህንነታቸው አደጋ ውስጥ ስለሆነ ለንዚህ ጓዶች አስቸኳይ ሌላ ሶስተኛ በስደተኝነት የሚቀበል ሃገር ይፈለግልን ብለን አምልክተን ስለነበረና እነሱም ጉዳዩን እሰክ ጀነቫና ኒዮርክ ያሉት መስራቤቶቻቸው ድረስ አስተዋውቀ ጉዳዩን በቅርበት ይከታትሉት ነበር። ሁኔታው በእንዲህ እያለ ነበር ህወሓት በሽሽግ ማንም ሳይሰማና ሳያይ፣ ዱካቸው ሳይገኝ 18ቱ የኢህ አፓ ሲኒየር አባላት በሌሊት ታፍነው እንዲሰጡትና ልክ ከሜዳ ማርኮ የወሰዳቸው የድርጅቱ አመራር አባላት እንደገደለው ለመግደል ተዘጋጅቶ የነበረው። ሆኖም ግን በሱዳን ድህንነቶች ዝርክርክነት ይህ የህወሓት እቅድ ሳይሳካ ቀረ፣ ከ18ቱ ተፈላጊዎች 4ታችን ብቻ በሱዳን ደህንነቶች ታፍነን ለወሓት ተሰጠን። 4ታችን ሲኒየር የፓርቲው አባላትና 18ቱ ቁስለኞችና አካለስንኩላን የሰራዊቱ አባልት ስንታፈን ለ4ታችን ሲኒየር አባላት በህይወት መተረፍና እኔ ዛሬ እየሰጠሁ ያለሁትን ምስክርነት እንዲሰጥ ያበቁ ሌሎችም የተለያዩ ምክንያቶች ነበሩ። እነሱም፣

ሀ. አባትና እናታቸው ታፈነው ተወስደው ሁለት ህጻናት (የ9 ወርና የሁለት ዓመት) ብቻቸው እቤት ተዘግተው መቅረትና ሁለቱ ህጻናት በማግስቱ ለUNHCR መረከብ፣ ገዳሪፍ የነበሩ የUNHCR ሰዎችም ስለ አፈናው ሱዳን ለነበሩ ዲፕሎማቶችና ለሚዲያ ወዲያውኑ ማሳራጨት፣ ሚዲያም ወዲያውኑ በተለይ BBC ለዓለሙ ማሰራጨት፣
ለ. በሌሊቱ ታፍነን ሲንጓዝ አድረን በማግሱቱ ከነደማችን የየን በሱዳን የተወሰነውን በሚገባ የሚያውቀን፣ ከሁለት ቀን በፊት አበረን ያወራን የድርጅት ሰው በህወሓት ወታደሮች ታጅበን ወደ እስርቤት ስንወሰድ መተማ ላይ አይቶን በቀጠታ ወደ ገዳሪፍ በሚሄድ ለህወሓት መረከባችን ለUNHCR፣ ለቤሰብና ለቀሩት ጓዶች ነግሮ የUNHCR ሰዎችም ለሚዲያ ወዲያውኑ ዜናውን ተናገረው የታፈነው ሰዎች በመተማ ላይ ለህወሓት መረከባችን መዘገብ።
ሐ. ሱዳን ገዳሪፍና አከባቢዋ ከነበሩት የህወሓት የብዙሃን ማህበር አባላት ብዙዎች ስለ አፈናው ከፈተኛ ተቃውሞ ማሰማትና ለምን ታፈሉ ብለው በስፋት አመራሮቻቸውን መጠየቅ፣ ለጠየቁት ጥያቄ የተሰጠው ኢህ አፓ ጸረ የትግራይ ህዝብ ስለሆን መጥፋት አለበት የሚለው የአመራሮቹ መልስ መቃወምና በተለይ የኔ ዓይነቶቹን በሚገባ የሚያውቁን የነበሩ ጠንካራ የህወሓት አባላት እንደ ምሳሌ እኔን በመጥቀስ፣ በየነን ብዙዎቻቻችን በሚገባ እናውቀዋለን እሱ ፈጽሞ ጸረ የትግራይ ህዝብ አይደልም፣ በርግጥ ህወሓትን አጥበቀው ከሚቃወሙና ከሚጠሉ አንዱ ነው፣ የትግራይ ህዝብን በተመለከት ግን ከናንተም በላይ ለትግራይ ልጆች በሱዳኖች ሲበደሉ ሽንጡን ገትሮ ሲሟገት የነበረ፣ በነበረው ስራም ያለ አንዳች ፖለቲካዊ አድልዎ ለሁሉም እኩል ሲያገለግል የነበረ ሰው መሆኑ በሚገባ እናውቀዋለንና መታፈኑንም በጥብቅ እናወግዛለን በማለት አጥብቀው ለመፈታታችን መሟገትና መከራከር።
መ. እነ ቢቢሲ፣ ጀርመን ራዲዮ፣ የአመሪካ ድምጽ የመሳሰሉ ሚዲያዎች ጉዳዩን በቅርበት በመከታተልና በየደርስነበት ሁኔታውን እየተከታተሉ መዘገብ የግድያ ውሳኔያቸውን ካስቅየሩት ምክንያቶች ዋነኞቹ ነበሩ።
ከዚህ በኋላ ህወሓት ሊገድልን ቢችልም ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ኪሳራ እንጂ ምንም የሚያገኝበት ትርፍ አልነበረም። እንደፈለገውና እንዳቀደው ዱካችን ሳይገኝ ወደ እጁ ሊያስገባንና ሊገድልን የሚችልበት ሁኔታ አከተም። ከዚህ በኋላ እናኝ ከመግደል ከተቻለ እኛን አሳምኖ የኢህ አፓ ስተትኝነት እንድንቀበልና እንድንመስክር በማድረግ ላይ አተኩሮ መስራቱን መርጦ እስራቱ ቀጠለ።

በክፍል 5 ፣ ትልቁ ምርመራ በአዘዞ ይጄላችሁ እቀርባለሁ፣ እስከዛው በቸር ቆዩ።


selam sew
Leader
Leader
Posts: 593
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

Re: 4 የሰቆቃ ዓመታት በህወሓት እስርቤት

Unread post by selam sew » 03 Apr 2016 12:32

4 የሰቆቃ ዓመታት በህወሓት እስርቤት፣

ክፍል 5 ፣ ሁለተኛ ምርመራ በአዘዞ እስርቤት፣

ወደ አንድ ወር ያህል ያ የተለመደው የእስርቤት ዕለታዊ ኑሮ ከኖርን ውጭ ሌላ ምንም አዲስ ነገር ሳይከሰተ አለፈ። በዚህ የአንድ ወር ጊዜ በኛ በኩል ምን ማድረግ አለብን፣ ለምን ዓይነት ጥያቄዎች ምን ዓይነት መልስ መስጠት አለብን፣ ምን ዓይነት ጥያቄዎች ማመን አለብን፣ የተኞቹስ መካድ አለብን በሚለው በሚገባ ለመዘጋጀት ጥሩ ዕድል አገኘን። በተጨማሪም ጠባቂዎችን ጋራ ይበልጥ ለመተዋወቅና በኛ ላይ የነበራቸው ከፈተኛ ጥላቻ ከነሱ ጋራ በረጋ መንፈስ በመወያየት በከፈተኛ ደረጃ ለማለዘብ ጥሩ ዕድል አገኘን። ከአንድ ወር በኋላ ወደ ከጥዋቱ አራት ሰዓት አከባቢ ያ መጀመሪያ የህይወት ታሪካችን የመዘገበው መርማሪና አንድ ሌላ ሰው ወደ ታስርንበት ቦታ በአንድ ቶዮታ ፒክ አፕ መኪና መጡ። በእጃቸው የሆኑ ዳጎስገ ያለ ዶሴ እያንዳቸው ይዘዋል፣ ወደ ታሰርንበት ክፍል ገቡና የእጅ ሰላምታ ለሁላችን ከሰጡን በኋላ አንዳንድ ጥያቄዎች በየግላችሁ ልንጠይቃችሁ ስለምንፈልግ አንድ በአንድ ወደ ምርመራው ክፍል ትመጣላችሁ ብለው አንድ ጓድን ይዘው ሄዱ። የጓዱ ምርመራ እንዳበቃ ጓዱ ወደ ክፍሉ ሳይመለስ ለብቻው አንድ ዛፍ ስር እንዲቀመጥ ተደርጎ እኔ ተጠራሁ። እክፍሉ ውስጥ እንደገባሁ ያ መጀመሪያ ጊዜ የህይወት ታሪኬን የመዘገበው መርማሪ እንዴት ሰነበትክ በየነ ብሎ የቃል ሰላምታ ከሰጠኝ በኋላ ሲጋራ ጋበዘኝና ወደ ስራችን እንግባ ብሎ በጥያቄና መልስ ምርመራው ቀጠለ።
መርማሪ፣ አዘዞን እንዴት አገኘኸው?
እኔ፣ ከፍተኛ የመኝታ፣የልብስ ችግር አለብን፣ የእጆቼ በተለይ የቀኝ እጄ ከፍተኛ ስቃይ አለብኝ፣ 24 ሰዓት ምንም የምትሰራው ስራ ሳይኖር፣ የሚነበብ ነገር ሳይኖር፣ በዓለም ላይ ምን እየሆነ እንዳለ የምትሰማበት ረዲዮ ሳይኖር ወደ አንድ ወር መቀመጥ ከባድ ነው፣ ከዚህ በተጨማሪም የወደፊት እጣ ፋንታችን ምን ሊሆን ይሆን ብሎ መጨነቁም አለ። ከዚህ በተረፈ ግን የኸው እንደምታየው አለን።
መርማሪ፣ ጥበቃው እንዴት ነው?
እኔ፣ ደህና ነው፣ እኛም ብዙ አንጠይቅም፣ አድርጉ ያሉንን እናደርጋለን፣ ከነሱ ጋራ ብዙ የሚያገናኘን ነገርም የለም፣ አሁን ከወር በፊት ከነበረው ይበልጥ ተለማምደናል ።
መርማሪ፣ ለምን ከሱዳን ተይዘህ እንደመጣህ ታውቃለህ?
እኔ፣ በፍጹም አላውቅም።
መርማሪ፣ ሱዳን ውስጥ ምን ስትሰራ ነበር?
እኔ፣ ILO ጋር ለኑሬ መደጎሚያ ገንዘብ ለማግነት እንደ ካውንስለር እሰራ ነበር፣ ከኢህአፓ ጋር ደግሞ በምስራቃዊ ሱዳን የሚደረገውን የማደራጀት ስራ በመምራት እሰራ ነበር።
መርማሪ፣ በኢህአፓ ውስጥ ሃላፊነትህ ምን ነበር?
እኔ፣ የምስራቃዊ ሱዳን ዞን አመራር ኮሚቴ አባል ነበርኩ።
መርማሪ፣ የኢህአፓ ማእካላዊ ኮሚቴ አባል አይደለህም?
እኔ፣ አይደለሁም።
መርማሪ፣ የዞን ኮሚቴ አባላት ስንት ነበራችሁ፣ እነማን ናቸው?
እኔ፣ 3 ነበርን፣ እኔና አንዱ እዚህ አዘዞ አለን አንዱ ደግሞ እዛው ሱዳን ቀርቷል።
መርማሪ፣ የኮሚቴያችሁ ግኑኝነት ከማን ጋር ነበር?
እኔ፣ ግኑኝነታችን በቀጥታ በጓድ መሓመድ ጀሚል በኩል ከውጩ የማእከላዊ ኮሚቴ ኦቶኖሞስ አካል ጋር ነበር።
መርማሪ፣ ከሜዳ ከሰራዊቱ ጋር ግኑኝነት አልነበረህም?
እኔ፣ አልነበረኝም፣ የኛ ኮሚቴ ስራ በሱዳን የፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ማደረጃትና ወደ ትጥቅ ትግሉ የሚሄዱ አባላት መልምሎ ወደ ሜዳ ለሚልከው አካል ማስረከብ ብቻ ነው የነበረው።
መርማሪ፣ ከሱዳን ወደ ሜዳ ለስልጠና የሚሄዱትን የሚልከው ታዲያ ማን ነበር?
እኔ፣ የጽፈት ቤቱን ስራ ሲሰራ የነበረ ባለ ሶስት አባላት ኮሚቴ ነበር። ይህ የኛ ኮሚቴ ሆነ የጽፈትቤቱ አስተዳዳሪዎች ድርጅታዊ ስራ ደግሞ ደርግ ተወግዶ እናንተ ስልጣን እንደያዛችሁና የኢህ አፓ ድርጅታዊ ስራ በሱዳኖች እንደታገደና ጽፈት ቤቶቻችን እንዲዘጋ ከተደረገ በኋላ አከተመ።
መርማሪ፣ ኢህ አፓ በሱዳን በህግ ከተዘጋ በኋላ የህቡእ ስራ ስትሰሩ እንደነበረ፣ በዚህ የህቡእ ስራም አንተ ከፈተኛ ሚና እንደነበረህ ማስረጃዎች አሉንና ስለዚህ የምተለው አለህ፣
እኔ፣ በሱዳን ደህንነቶችና በናንተ ካድሬዎች ለ24 ሰዓት በዓይነቁራኛ እየተጠብቅኩ በቁም እስረኝነት ነበር የምኖረውና ብፈልግም ለመስራት የምችልበት ዕድልና ሁኔታ አልነበረኝም።
መርማሪ፣ ማስረጃ አለን እኮ ነው እያልኩህ ያለሁት፣
እኔ፣ እኔ ደግሞ አልሰራሁም እያልኩህ ነው፣ በርግጥ ቁስለኞቹንና አካለ ስንኩላንን ለመንከባከብ በሱዳን መንግስት በተሰጠን ፍቃድ መሰረት፣ የተወስን ጉዶች ቁስለኞቹን እንዴት እናስተዳድር፣ ወደ ህክምና መወሰድ ያለባቸውን ማን ይወሰድ፣ ምን የጎደላቸው ነገር አለ ለመመካከር እገናኝ ነበር፣ ከዚህ ውጭ ግን ምንም ሌላ ድርጀታዊ ስራ ለመስራት የምንችልበት ሁኔታ አልነበረምና ምንም ድርጅታዊ ስራ ከደርግ ውድቀት በኋላ አልሰራንም ነው እያልኩህ ያለሁት።
መርማሪ፣ አንተ የኢህ አፓ ማእከላዊ ኮሚቴ አባል ነህ ወይስ አይደለህም፣
እኔ፣ አይደልሁልም
መርማሪ፣ የማእከላዊ ኮሚቴ አባል ሳትሆን የድርጅቱ አቋሞች ምን እንደሆኑ እንዴት ልታውቅ ቻልክ፣ ለምሳሌ ኢህ አፓ ከህወሓት ጋራ በትጥቅ ትግል መዋጋት የለበትም የሚል አቋም እንደነበረው እንዴት አወቅክ፣
እኔ፣ ማናቸውም መሰረታዊያን አቋሞች የሚወሰኑት በድርጂቱ ጉባኤ ነው። ለምሳሌ በድርጀቱ ሁለተኛ ጉባኤ የጠላት አፈርጃጀት በተመልከተ በዋና ጠላትነት ደርግ ተፈርጆ፣ ህወሓትና መሰል ድርጅቶችም በጠባብ ብሄረተኛ ድርጅትነት ተፈርጀው በሁለተኛ ደረጃ ጠላትነት ተፈርጀዋል። በጠምንጃ የምንታገለው ደርግ ብቻ ሆኖ ጠባብ ብሄረተኛ ድርጅቶችን የሚንታገለው በፖለቲካ ትግል ብቻ ነው የሚለው አቋም የተወሰደውም ያኔ ነበር። በጉባኤ የተወሰነውን አቋም ሊሽረው የምችለው ደግሞ ሌላ ጉባኤ ብቻ ነው። አመራር ደግሞ ጉባኤ የወሰነውን ወሳኔዎችና አቋሞች ማስፈጸም ብቻ ነው ስራው።
መርማሪ፣ አንተ የኢህአፓ ማእከላዊ ኮሚቴ አባል አይደለሁም እያልክ ብዙ ነገሮችን ታውቃለህ፣ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ፣
እኔ፣ እኔ አህአፓን ስቀላቀል በርግጥ በጣም ወጣት የነበርኩ ብሆንም የፍልስፍና የሁለተኛ ዓመት ትምህርቴን ጨርሼ ሶስተኛ ዓመት እንደጀመርኩ ነበር ወደ ትግሉ ሜዳ የወጣሁት። ራሱ በትግሉ ወስጥ በቆየሁባቸው ዓመቶች ተመክሮው ራሱ ብዙ አስተምሮኛል፣ በተለይ ሱዳን በቆየሁባቸው 10 ዓመታት በተቻለ መጥን ለማንበብም ዕድል አግኝቼያለሁ፣ ከነበርኝ የስራ ዓይነት ምክንያትም ከብዙ ሰዎች ጋራ የመገናኘትና የምንጋገር እድሉ ነበርኝ፣ ይህም ብዙ ነገሮች እንዳውቅ ረድቶኛል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ አህአፓ ውስጥ አንድ ሰው ለማወቅ ከፈለገ ገደብ የለውም። ሌላም እኔ በኢህአፓ ውስጥ ስታገል ራሴ ወድጄ እንጂ ተገድጄ አይደለም፣ በተራ አባል ደርጃ ወይም በዝቅተኛ ኮሚቴ የሚያገልግሉ የነበሩ ከማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ያልተናነሰ እውቀት የነበራቸው ብዙ ጓዶች አውቃለሁና በመሰራዊ ጉዳዮች ላይ የተወሰነ ዕውቀት ስላለኝ ብቻ የኢህአፓ ማእካለዊ ኮሚቴ አባል ልሆን አልችልም፣ ስላልሆንኩም ነው የማእከላዊ ኮሚቴ አባል አይደለሁም እያልኩህ ያለሁት።
መርማሪ፣ የኢህአፓ ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ስንት ናቸው፣ ስማቸውስ ማን ይባላል፣ የት ይኖራሉ?
እኔ፣ በጉባኤው የተመረጡት 11 ነበሩ ከዚህ በኋላ በጉባኤው የተመረጡት የቁጥራቸው አንድ ሶስተኛ አባላት ኮኦፕት ማደርግ ይችላሉ የሚል ህግ ስላለ ስንት ኮኦፕት እንደተደረጉ አላውቅም። በሜዳ ራሱን የቻለ አንድ ኦቶኖኖሞስ የሆነ አካል መኖሩን አውቃለሁ፣ እንዲሁም ሱዳንን ጨምሮ በኤውሮዻና አመሪካ የነበረውን ድርጅታዊ ስራ ኦቶኖሞስ ሆኖ ሲመራ የነበረ አንድ ሌላ አካል መኖሩንም አውቃለሁ። እኔን በቀጥታ የሚመለከተኝ የወጭ ድርጅታዊ ስራ ሲመራ የነበረው አካል ነበር። የውጩን ድርጅታዊ ስራ በማእከላዊ ኮሚቴ ደረጃ ሲመሩ የነበሩ ደግሞ አቶ መርሻ፣ አቶ ፋሲካና አቶ መሓመድ ነበሩ። የት ይኖራሉ ላልከው አቶ መሓመድ በኤውሮዻ ፣ አቶ መርሻና አቶ ፋሲካ ደግሞ በአመሪካ መኖራቸውን አውቃለሁ።
መርማሪ፣ አንተ ትውልድህ ከትግራይ ነው፣ ትግራዋይ ሆነህ እያለህ እንዴት እስከዛሬ ከኢህአፓ ጋር ሊትቆይ ቻልክ?
እኔ፣ ኢህአፓ ለሁሉም ብሄር ብሄረሰብ ከደርግ ጭቆና ለማላቀቀቅ የሚታገል ህብረብሄር ድርጅት ስለሆነ።
መርማሪ፣ ኢህአፓ ጸረ የትግራይ ህዝብ የሆነ ድርጅት ነው እኮ፣
እኔ፣ ኢህአፓ ጸረ ትግራይ ህዝብ የሆነ ድርጅት ፈጽሞ አይደለም፣ ጸረ የትግራይ ህዝብ የሆነ ድርጅት ቢሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ዓመት ይቅርና አንድም ቀን ከኢህአፓ ጋራ አልቆይም ነበር።
መርማሪ፣ ጸረ ትግራይ ህዝብ ባይሆን ኖሮ አሁን ትክክለኛ የትግራይ ህዝብ ወኪል ከሆነው ከህወሓት ጋር አይዋጋም ነበር ፣
እኔ፣ እኔ እስከመውቀው ኢህአፓ ከደርግ ውጭ በትጥቅ ትግል ከማንኘውም ሌላ ድርጅት ጋር መታገል የለብን የሚል አቋም እንዳለው ነው። ድሮም ሆነ አሁን በህወሓትና በኢህአሰ መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት በናንተ ፍላጎትና በናንተ አነሳሽነት ነው እየትካሄደ ያለው። ኢህ አፓ ህወሓት ጠባብ ብሄርተኛ ድርጅት ነው፣ ህወሓትን በፖለቲካ ትግል በቀላሉ ጠባብ ዓላማውን ለህዝብ በማጋለጥ ልናሸንፈው ስልምንችል በትጥቅ ትግሉ ደርግን ለማሸነፍ በምናደርገው ትግል ላይ ነው ማተኮር ያለብን የሚል አቋም ኣንደነበረው ነው እኔ የማውቀው።
ህወሓት የትግራይ ህዝብ ወኪል ነው ላልከው፣ አጭር መልሴ አይደለም የሚል ነው። ምክንያቱም ህወሓት የትግራይ ህዝብ ወኪል መሆኑ ሊረጋገጥ የምችለው ህወሓትና ሌሎች ለምሳሌ ኢህ አፓ ተወዳድረው ህዝቡ ያለ ተጽዕኖና የናንተ ጣልቃ ግብነተ ድምጹን ሲያሰማ ብቻ ነው። እስካሁን የትግራይ ህዝብ ይህን ዕድል አላገኘምና ህወሓት ፈጽሞ የትግራ ህዝብ ወኪል አይደልም።
መርማሪ፣ ሌላ ተጨማሪ ምርመራ ሊኖረን ይችላል ለዛሬው ግን እዚሁ አብቅተናል መሄድ ትችላለህ ብሎ አሰናበተኝና ክፍሉን ጥዬ ወጥቼ ከምርመራው በኋላ ለብቻው ተለይቶ ከተቀመጠው ጓድ ጋራ ተቀላቀልኩ። የቀሩት ሁለቱ በየተራቸው ተምርምረው ካበቁ በኋላ ሁላችን እንደገና በክፍላችን ተሰባሰብንና ምን ዓይንት ጥያቄዎች ለያንዳንዳችን እንደቀረቡ መነጋገር ጀመርን። በዚህ ሁለተኛ ዙር ምርመራ ለያንዳንዳችን የቀረቡ ጥያቄዎች ተመሳሳይነት የነበራቸው እንዳሉ ሁሉ ልዩነትም እንደነበራቸው ለመረዳት ቻልን።

በክፍል 6 የአዘዞ ወደ ሁለት ወር ቆይታ አብቅቶ ጉዞ ወደ ትግራይ ምን ይመስል እንደነበረ ይጄላችሁ እቀርባለሁ፣ እስከዛው በቸር ስንብቱ

Post Reply

Return to “Ethio Politics .... ኢትዮ ፖለቲካ”