ወልቃይትን መሬቱን እንጂ…

ፖለቲካ ፣ ወቅታዊ ጉዳዮች
Politics , Current affairs
selam sew
Leader
Leader
Posts: 593
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

ወልቃይትን መሬቱን እንጂ…

Unread post by selam sew » 13 Jan 2016 17:02

ወልቃይትን መሬቱን እንጂ…

----------------------------------
(የቀለም ቀንድ ቅጽ 3 ቁጥር 24 ታህሳስ 26 ቀን 2008)
ሙሉቀን ተስፋው Muluken Tesfaw


ከአንድ ሳምንት በፊት የወልቃይት አማሮች የማንነት ጥያቄ አስተባባሪዎቹ ሊያገኙኝ እንደሚፈልጉ ገልጸውልኝ በቀጠሯችን መሠረት ተገናኘን። ለኢፌዴሪ የፌደሬሽን ምክር ቤት ያስገቡትን የማንነት ጥያቄ ማመልከቻ እንዲሁም 116 የት እንደደረሱ የማይታወቁ ወገኖቻቸውን ስም ዝርዝር የያዘ ሰነድ ፎቶ ኮፒ ሰጡኝ። ሰነዱ በራሱ ገላጭ ቢሆንም የአካባቢውን ተወላጆች መሠረታዊ ጥያቄ በሚገባ ለመረዳት በዕድሜና በተመክሮ በሳል የሆኑ ሰዎችን ማነጋገሩ የተሻለ
መስሎ ስለተሰማኝ ሐሳቤን ገለጽኩላቸው። እነሱም ጥያቄየን ተቀብለው ከአንድ የ70 ዓመት አዛውንት ጋር አገናኙኝ።
ያገኘዋኋቸው አባት ታሪክን ጠንቅቀው የሚያውቁ የቤተ ክህነት ሊቅ ናቸው። እኚህ አዛውንት ስለወልቃት ጠገዴ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵና ሱዳን ጉዳይ ላይ ያላቸው ዕውቀት ከፍተኛ ነው። ይህ ከዚህ ቀጥሎ የቀረበው የዕድሜ ባለጸጋው የወልቃይት ተወላጅ የነገሩን ነው።

የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ወንዱም ሴቱም ጅግና ነው። በጣሊያን ወረራ ዘመን እናቶቻችን ልጆቻቸውንና ባሎቻቸውን አልጋ ሥር ጠመንጃ አቀባብለው እንዲደበቁ ያደርጋሉ። እነርሱ ደግሞ በርበሬ (ሚጥሚጣ) ድቁሱን በውኃ በጥብጠው ያስቀምጣሉ። ከዚያም የጠላት ወታደር በውበታቸው ማርከው ወደ ቤት ያስገቡታል። የወልቃይቷን ሴት ውበት ዓይቶ በስስት የሚገባው ፈረንጅ ፊትና ዓይን ላይ ያን የተበጠበጠ በርበሬ ይደፉበታል። ያ ወታደር ሲደናበር አልጋ ሥር የተደበቀው ባለነፍጥ አናቱን ብሎ እየሸለለ የጠላትን ትጥቅ ቀምቶ ጫካ ይገባል።
ኢሕአፓና ሕወሓት ታኅሣሥ 21 ቀን 1972 ዓ.ም. በወልቃይት ደጀና ከተባለ ቦታ ላይ ጦርነት ገጠሙ። ‹‹ግንብ›› የተባለ ጎድጓዳ ቦታ አለ። ግንብ ውስጥ ሰው ቢጮህ ማንም አይደርስለትም። ጥይት ቢተኮስም ርቀት ቦታ አይሰማም። ደጀና ላይ ሲዋጉ የነበሩ የኢሕአፓ ወታደሮች ሁሉ ግንብ ውስጥ ዶግ አመድ ሆኑ። አስከሬን ቀባሪ አጥቶ ለአሞራ ቀለብ ሆነ። የሰው ልጅ ለካ ያን ያክል ስብ ይሸከማል? ስቡ ቀልጦ የሚፈሰው መሬቱን ሁሉ አጥቁሮት ነበር። የጥይት ድምጽ አፍኖ የሚይዘው ግንብ አስከሬኖቹ የሚተፉትን መጥፎ ጠረን ግን አፍኖ መያዝ ተሳነው። ድፍን ወልቃይትን በመጥፎ ጠረን አሰከረው።
ከሞት ያመለጡት የኢሕአፓ ሠራዊት አባላት ወደ ሱዳን ተሰደዱ። የወልቃይት ጠገዴ ጣዕር ከዚህ ጊዜ ይጀምራል። ሕወሓቶች ወልቃይት ጠገዴን ዙረው ሲመለከቱ በመሬቱ ለምነት ጎመዡ። በዚህ ምክንያት መሬቱን ለመውሰድ ሕዝቡን በልዩ ልዩ መንገድ ማሰቃየትና ከአካባቢው ማፈናቀልን ሥራዬ ብለው ተያያዙት። በዚህ መንገድ ሕወሓት ‹‹ኢሕአፓን አስጠልላችኋል›› በማለት በወልቃይት ሕዝብ ላይ መከራውን አንድ ብሎ ጀመረ። ያኔ የተጀመረው መከራ አሁንም ይበልጥ ተጠናክሮ ቀጠለ እንጂ አልቆመም። ኢሕአፓን አስጠግተዋል ያላቸውን አማሮችን ቤትና ንብረት ማቃጠል የጀመረው ሕወሓት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የወልቃይት ወጣቶችን ሰበብ እየፈለገ መግደል ሥራው ሆነ፤ የግፍ አገዛዝ በሕዝቡ ላይ ተጫነ። ለዚህ ደግሞ የሱዳን መንግሥት ታላቅ ሚና ተጫውቷል።
አሁንም ቢሆን የሱዳን መንግሥት የጥፋት እጆች አልተሰበሰቡም። የወልቃይት ጠገዴ አማሮች የተከፈተባቸው ጥቃት ሁለንተናዊና ከብዙ አቅጣጫ ነው። የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የሥነ ልቦናዊ ጦርነት ሰላባ ናቸው። በመንግሥት መሥሪያ ቤት ቅድሚያ የሚሰጥ ከመሐል አገር ለሚመጣ የትግራይ ተወላጅ ነው። የወልቃይት ልጆች ትምህርት በአማርኛ መማር አይችሉም፤ ትምህርት ቤት ውስጥ በአማርኛ ቋንቋ ማውራትም አይችሉም። ክልክል ነው። ሕወሓት በዚያ አካባቢ መንቀሳቀስ ከጀመረበት ጊዜ አንሰቶ ከሰላሳ በላይ ለሚሆኑ ዓመታት የኢትዮጵያም ሆነ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያላወቅ ብዙ በደል ደርሷል። አያሌ የወልቃይት ተወላጆች ተገድለዋል፤ ተሰደዋል። ቁጥራቸውን የማናውቀው ልጆቻችን የት እንደወደቁ ሳይታወቅ ደብዛቸው ጠፍቷል። የሕወሓቶች ግፍ ወልቃይት ጠገዴ አማሮች የተፈጥሮ ስሜታቸውን እንኳ በወዱ እንዳይገልጹ ነው የሚያስገድዷቸው። የዳንሻ ከተማ ከንቲቫ ሕዝቡን ሰብስቦ ‹‹ልጆቻችሁ ስለምን አማርኛ ያወራሉ!›› በማለት በአደባባይ ሕዝቡን ማስፈራራቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው። አማርኛ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ‹‹የኢሕአፓ ቅሪቶች›› በመባል ይታወቃሉ።
አማርኛ የሚናገሩ ሰዎች ምንም ዓይነት መብት የላቸውም። የሕግ አካላት የአማራ ተወላጆችን አያስተናግዱም። የወልቃይት ተወላጆች ከትግራይ ብሔረሰብ አባላት ጋር ተጋጭተው ወይም ሌላ በደል ደርሶባቸው ለሚመለከተው የፍትሕ አካል ቢያመለክቱ የፍትሕ አካሉ ለትግራዩ እንደሚያዳላ ማንም ያውቃል። የተለመደ ነው። ትግርኛ በአግባቡ ባለመናገራቸው በደል የሚደርስባቸው የወልቃይት አማሮች ብዙ ናቸው። ለናሙና አንድ እናንሳ። የአካባቢው ሕዝብ ባህሉም ሥነ ልቦናውም ምርጫው አማራነት ነው። ሕዝቡ ለትግራይና ኤርትራ ቅርብ በመሆኑ እንደሌሎች በአዋሳኝ አካባቢዎች እንደሚኖሩ ሕዝቦች የተለያየ ቋንቋ ይናገራል። የዚህ ዓይነት ሁኔታ በየትም አካባቢ ያለና ተፈጥሯዊ ነገር ነው። የድሬዳዋ ሕዝብ ከአማርኛ ሌላ ሶማሊኛም ኦሮምኛም እንደሚናገር ይታወቃል። ኢትዮጵያውያን በሌሎች የአገራችን ጥአካባቢዎችም እንዲሁ ነው። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብም ከአማርኛ ሌላ ትግርኛ ይናገራል።
ዐረብኛ ቋንቋ የሚናገሩም ብዙዎች ናቸው። ሕዝቡ ትግርኛ ይናገር እንጂ የአካባቢው ትግርኛ የተለየ ነው። ወደ አማርኛ በእጅጉ ይቀርባል። የትግራይ ብሔረሰብ አባላት ይህን በሚገባ ያውቃሉ። በዚህ ምክንያትም ብዙ በደል አለ። ትምህርት ቤት ሞክሼ የአማርኛ ፊደላትን የሚጽፉ ተማሪዎች ካሉ በጣም
ይወገዛሉ። ለምሳሌ ኀ፣ ሠና ፀ የአማርኛ ፊደላት ናቸው ተብለው ስለሚታሰቡ መምህራን ለፊደላቱ ያላቸው ጥላቻ የበዛ ነው። እንደሚታወቀው ጉራጌ ዞን ውስጥ ለምሳሌ ለኦሮሚያ ክልል ቅርብ በሆነው ሶዶ ወረዳ ውስጥ ብዙዎች ኦሮምኛ ቋንቋ ይችላሉ። ኦሮምኛ ስለሚናገሩ ኦሮሞ ናቸው በሚል ወደኦሮሚያ ክልል ለመጠቅለል ጥረት ቢደረግም ሕዝቡ ማንነቱን አሳልፎ አልሰጠም። መታወቅ ያለበት የብሔረሰቦች መብት ተከብሯል እየተባለ ድቢ በሚመታበት ዘመን የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ያለታሪኩና ፍላጎቱ ወደትግራይ ክልል እንዲጠቃለል የተደረገው በሕወሓት ውሳኔ በመሣሪያ አፈሙዝ ነው። ሕዝቡ ፈጽሞ አልተጠየቀም፤ ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድልም አልተሰጠውም። አካባቢው በትግራይ ክልል ሥር እንዲሆን ከተወሰነ ጀምሮ የመብት ጥያቄ የሚያነሱ ልጆቻችንን ስንቀብር ኖረናል። ጥያቄው ወደፊት እንዳይቀርብና ለአንዴና ፋይሉን ለመጨረሻ ጊዜ ለመዝጋት ሲባል በሺህዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን በአያት ቅድመ አያቶቻችን ርስት ላይ በማስፈር የትግራይን የበላይነት ለመፍጠር ያልተሞከረ ነገር የለም። የሕዝባችን በደል ድርብ ድርብርብ ነው የምንልበት ምክንያት በደሉ በባለመሣሪያው ሕወሓት የሚፈጸም በመሆኑ እንደሌሎች ሕዝቦች ጥያቄ በኢትዮጵያ ሕዝብና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ እስካሁን ጎልቶ ባለመውጣቱ ነው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተሻለ ሁኔታ ቢኖርም ከደረሰብን በደል ጋር ስናወዳድረው በጣም የሚያሳዝን ነው።
የሱዳን መንግሥት ለኢትዮጵያ የአጥንት ቲቢ ነው!
የሱዳን መንግሥት እኮ ለአገራችን የአጥንት ቲቪ ነው። የሱዳን መንግሥት የወልቃይትን አማሮች ከሕወሓት ጋር እንዴት አድርገው እንደፈጇው በሚገባ እናውቃለን። ከ1972 ጀምሮ ሕወሓቶች አስቀድመው የሚያጠና ሰው ይልካሉ። ሰላይ መሆኑ ነው። አስቀድመው የሚመጡት ሰላዮች በራሱ መተማመን ያለውንና ቆይቶም ለሕወሓቶች ተቃውሞ ያነሳል የሚሉትን ወጣት በስም ዝርዝር ይልካል። ሕወሓቶች ለሱዳኖች ይናገራሉ። ሱዳኖች መኪና ይዘው ይገባሉ። ወጣቶቹን ይይዙና ወደ ግዛታቸው ይወስዷዋል። ‹‹ዛሬ እከሌ ጠፋ! ዛሬ ከሌ በሱዳኖች ተወሰደ!›› ሁልጊዜም የሚሰማ እሮሮ ነው። ይህ እሮሮ በሕወሓቶች የሽፍትነት ዘመን ብቻም ያቆመ አይደለም። እስካሁን ድረስ የቀጠለ ደረቅ ሐቅ እንጂ። ሱዳን ድንበር ከገቡ በኋላ በጥይት ተደብድበው ይገደላሉ። ትልልቅ ከተማዎች አደባባይ ላይ ይሰቀላሉ። ከተማ አደባባይ ላይ የሚሰቀሉትን በተመለከተ ሱዳኖቹ የሚሉት ‹‹ሐበሻ ራሱን አጠፋ›› ነው። ሕወሓቶች ራሳቸው የወልቃይት አማራ ወጣቶችን ጉድጓድ እንዲቆፍር ካደረጉ በኋላ በቆፈሩት ጉድጓድ ይቀብሯቸዋል። ‹‹የትግሬ እናት ሐዘን ተቀምጣ አንተ ጠግበህ ትበላለህ?›› በማለት ውኃ በቀጠነ ይገድሏቸዋል።
ሕወሓቶች እንዲህ ይላሉ። መሬቱ እንጂ ሕዝቡ አያስፈልገንም። የሱዳን ዜጎች ድንበር አካባቢ የሚያገኟቸውን ኢትዮጵያውያን ሳይጠይቁ የማያልፉት ነገር አለ። ይኸውም ‹‹አማራ ነህ ትግሬ!›› የሚል ነው። ለሱዳኖች ሰው ማለት ትግሬ ነው። አማራ የሱዳን ጠላት አድርገው ይቆጥሩታል። የሱዳን ደህንነቶች የፈለጉትን የወልቃይት ተወላጅ በፈለጉት ጊዜ መጥተው መውሰድ ይችላሉ። የህወሓትም ደህንነቶች እንዲሁ። የወልቃይት ተወላጆች ወደ ሱዳንም ቢገቡ እዚህ ቢቀመጡ ያው ነው። የወልቃይት ተወላጆችን ግፍ ሊያስረዳ የሚችል አንድ ምሳሌ እንጥቀስ። ቄስ ተገን እንየው የሚባል ካርቱም እስጢፋኖስ የሚያገለግል የወልቃይት አማራ አለ። ቄስ ተገን በቤተ ክህነት ትምህርት ከዚህ ቀረህ የማይባል ምሁር ነው። በግዕዝ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በዐረብኛ ደግሞ ከግብጥ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያኖች ይቀድሳል። ቄስ ተገን ያለውን ለአገሩ ልጆች አካፍሎ ይበላል። ሕወሓቶች ቄስ መስፍን አገር ውስጥ ላሉ ለሚማሩ ልጆች ገንዘብ እንደሚረዳ ደረሰቡት። ለተቸገረ ገንዘብ መለገስ የሚያስመሰግን እንጅ የሚያስወቅስ ሆኖ አልነበረም። ባለፈው መጋቢት ወር 2007 ዓ.ም. ካርቱም የተላከ የወያኔ ደህንነት ይዞት መጣ። ማዕከላዊ እስከ ጥቅምት 2008 ዓ.ም. ከማንም ከምንም ጋር ሳይገናኝ ጨለማ ቤት አቆይተው ‹‹ለማንም እንዳትናገር›› ብለው ለቀቁት። ቄስ ተገን ምንም አማራጭ ስላልነበረው አሁን ወደ ካርቱም ተመልሷል። የወልቃይት ልጃገረዶች በትምህርት ቤት የሚደርስባቸው አበሳም ከፍተኛ ነው። ሐሙስ ሐሙስ ሴት ተማሪዎች የመምህራንን መኖሪያ ያጸዳሉ የሚባል ያልተጻፈ ሕግ ነበር። ገና ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ ሕፃናት የመምህራኖቻቸውን ቤት ማጽዳት በተራ ሁልጊዜ ሐሙስ ‹እነ ጋሽዬ› ቤት ይሄዳሉ። ሕፃናቱ በመምህራኖቻቸው ይደፈራሉ። ያረግዛሉ ይወልዳሉ። በሕግ ሊያገቡ የታጩ ልጃገረዶች ሁሉ እየተደፈሩ ያገባሉ። ምክንያቱ ደግሞ አማሮችን ትግራዊ ለማድረግ ብቻ ነው። የወልቃይት አባቶች ተጨነቁ። ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ላለመላክ ወሰኑ። በዚህ ጊዜ ደግሞ ለትምህርት የደረሰ ልጁን እቤት ያስቀመጠ ሰው ይቀጣል የሚል ሕግ መጣባቸው። ወላጆች አሁን ሌላ አማራጭ ፈለጉ። ‹በመምህራን› ልጆቻቸው ከመደፈራቸው በፊት በልጅነታቸው መዳር። መጨነቅ ነው። ይህም ሌላ ጣጣ አስከተለ። በሴቶችና ሕፀናት ጉዳይ ‹‹ያለ ዕድሜ ጋብቻ›› በሚል ክስ ይመሰረትባቸዋል። ያለ ዕድሜያቸው በሚደፍሯቸው መምህራን ላይ ግን ማንም ምንም አይልም። ይህ ሁሉ ችግር የሚደራረብባቸው ወልቃይቴዎች ያላቸው አማራጭ ሁለት ብቻ ነው። አንደኛው ልጆቻቸውን ወደ ጎንደርና ሌሎች አካባቢዎች ወስዶ ማስተማር ሲሆን ሁለተኛው ግን የመምህሮቹን ‹‹ዲቃላ›› ማሳደግ። መታወቅ ያለበት አንድ መሠረታዊ ነገር አለ። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ጥያቄ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ አይደለም። ይህ ማለት ሕዝቡ የመልካም አስተዳደር ችግር የለበትም ማለት አይደለም። በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች እንደሚታየው በእኛ አካባቢም የመልካም አስተዳደር ችግረ አለ። የእኛ ዐቢይ እና የሕወሓት ሰዎች የቱንም ያህል ቢገድሉንና ቢያሳድዱን የማንተኛለት፤ እኛ መፈጸም ባንችል ጉዳዩን ለልጅ ልጆቻችን የምናወርሰው ጥያቄ የማንነታችን ጉዳይ ነው። አማሮች ነን። ትግራይ አይደለንም።
የደረሰብንና እየደረሰብን ያለውን ያልተነገረለት በደል ኢትዮጵያውያንና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲገነዘብልን እንፈልጋለን።

(ማሳሰቢያ፡ ይህ ጽሑፍ ለሕትመት ከመብቃቱ በፊት የሱዳንን ኢምባሲ የሚሉት ነገር ይኖር ይሆን ብለን ለመጠየቅ ብንሞክርም ኢምባሲው ሊያናግረን ፈቃደኛ አልሆነም)

ምንጭ: Muluken Tesfaw ፌስቡክ

Post Reply

Return to “Ethio Politics .... ኢትዮ ፖለቲካ”