ክቡር ሚኒስትሩ በጠዋት ወደ ቢሮ ሊሄዱ ሲሉ ሚስታቸው ነጭ ልብሳቸውን ለብሰው ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ አገኟቸው

ፖለቲካ ፣ ወቅታዊ ጉዳዮች
Politics , Current affairs
selam sew
Leader
Leader
Posts: 593
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

ክቡር ሚኒስትሩ በጠዋት ወደ ቢሮ ሊሄዱ ሲሉ ሚስታቸው ነጭ ልብሳቸውን ለብሰው ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ አገኟቸው

Unread post by selam sew » 30 Dec 2015 11:18

ክቡር ሚኒስትሩ በጠዋት ወደ ቢሮ ሊሄዱ ሲሉ ሚስታቸው ነጭ ልብሳቸውን ለብሰው ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ አገኟቸው

– ዛሬ በጠዋቱ አምሮብሽ ወዴት ነው?
– ቀኑንም ረሳኸው?
– ግንቦት 20 ነው እንዴ?
– ጤነኛ ነህ?
– የብሔር ብሔረሰቦችም ቀን አልፏል እኮ፡፡
– አሁን አሁን ጤነኝነትህ እያጠራጠረኝ ነው፡፡
– የምሬን እኮ ነው በጠዋቱ እንዲህ አምረሽ ወዴት ነው?
– ወዴት የምሄድ ይመስልሃል?
– የሴቶች ሊግ ስብሰባ አለብሽ?
– እውነትም ለይቶልሃል፡፡
– እኔ የማላውቀው ቀን በፓርላማ ተሰየመ እንዴ ታዲያ?
– የምን ቀን?
– እንዲህ ነጭ ከለበሽ የሰላም ቀን ነዋ የሚሆነው፡፡
– እፀልይልሃለሁ ለማንኛውም፡፡
– ምን ብለሽ?
– ልብ ስጠው፡፡
– የምፈልገውን ዓይነት ግን እንዳትረሺ፡፡
– ምን ዓይነት ነው የምትፈልገው?
– ልማታዊ ልብ፡፡
– ምነው ኪራይ ሰብሳቢው ልብ ሰለቸህ?
– ወሬማ ማን ብሎሽ?
– እውነቴን ነው፡፡
– ለማንኛውም ወዴት ነው የምትሄጂው?
– ወደ አራት ኪሎ፡፡
– ምን ልታደርጊ?
– ልሳለም፡፡
– ፓርላማውን ነው?
– ምን ይላል ይኼ?
– ጽሕፈት ቤታችንን ነው?
– ኧረ የዓመቱ ነው፡፡
– የዓመቱ ምን?
– ገብርኤል፡፡
– ለዚህ ነው እንደዚህ የዘነጥሽው?
– ምን አለበት?
– ምነው ለብሔር ብሔረሰቦች ቀን እንደዚህ አልዘነጥሽ?
– እየቀለድክ ነው?
– አሁን እኔ በብሔር ብሔረሰቦች ስቀልድ ዓይተሽኝ ታውቂያለሽ?
– መጽሐፉ የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር እንደሚል አታውቅም?
– የትኛው መጽሔት አዲስ ራዕይ?
– የለም ዮሐንስ ራዕይ፡፡
– ምን ልታደርጊ ነው የምትሄጂው?
– ልሳል፡፡
– እኮ ምንድን ነው የምትሳይው?
– ጧፍ ነዋ፡፡
– የምን ጧፍ አመጣሽ?
– እና ምን ልሳል?
– አምፖል ነዋ፡፡
– ለምን ሲባል?
– እኛ ግድብ የምንገነባው ሁሉም ቦታ መብራት እንዲበራ አይደል እንዴ?
– ስለቴም እኮ እሱ ነው፡፡
– ምንድን ነው የተሳልሽው?
– እንዳይጠፋ ብዬ፡፡
– ምኑ?
– መብራቱ!
[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸው ገባ]
– ክቡር ሚኒስትር እንግዶች ይፈልጉዎታል፡፡
– የምን እንግዳ?
– ዳያስፖራዋች ናቸው፡፡
– ተላላኪዎች ናቸው አትለኝም፡፡
– የምን ተላላኪ?
– የኒዮሊብራሎች ነዋ፡፡
– ኧረ ክቡር ሚኒስትር እነዚህ አገር ወዳድ ዳያስፖራዎች ናቸው፡፡
– ምን ፈልገው ነው?
– እኛን ሊረዱን ፈልገው ነው፡፡
– በምንድን ነው የሚረዱን?
– ባለፈው ያወጣነውን ጨረታ ዓይተው ነው፡፡
– የቱን ጨረታ?
– ለሶፍትዌር ያወጣነውን ጨረታ፡፡
– ታዲያ ጨረታውን ስጡን ሊሉን ነው የመጡት አትለኝም?
– እሱማ ስጡን ሊሉን ነው የመጡት፡፡
– እኔ መቼ አጣሁት?
– ግን በነፃ ሊሠሩልን ይፈልጋሉ፡፡
– ምን በነፃ?
– አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
– እባክህ በጐን ሌላ ነገር ፈልገው ሊቀበሉን ነው፡፡
– ክቡር ሚኒስትር፣ እስካሁን በጐን የጠየቁን ነገር ስለሌለ ብንሰማቸው ጥሩ ነው፡፡
– ለመሆኑ አሁን አሉ?
– አዎን ቢሮ እየጠበቁኝ ነው፡፡
– እስቲ አስገባቸው፡፡
– እሺ፡፡
[ዳያስፖራዎቹ ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ገቡ]
– እናመሰግናለን ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ስለምኑ?
– ሊያናግሩን ፈቃደኛ ስለሆኑ፡፡
– ዳያስፖራውን መስማት ሥራችን ነው፡፡
– ዛሬ የመጣነው ለምን እንደሆነ ያውቃሉ?
– አላውቅም ለምንድን ነው?
– መሥሪያ ቤታችሁ እንዲሠራለት የሚፈልገውን ሶፍትዌር ለመሥራት ነው፡፡
– እሺ፡፡
– ሶፍትዌሩን እኛ ብንሠራው ብዙ ጠቀሜታ አለው፡፡
– ምን ዓይነት ጠቀሜታ?
– ገንዘብ ይዘን እንመጣለን፡፡
– እሺ፡፡
– የቴክኖሎጂ ሽግግር እናደርጋለን፡፡
– ሌላስ?
– ሶፍትዌሩ የሚሠራው በኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በመሆኑ የዕውቀትም ሽግግር እናደርጋለን፡፡
– ጥሩ፡፡
– አገሪቷ ለሶፍትዌሩ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ እናስቀራለን፡፡
– ለመሆኑ ሶፍትዌሩን ሠርታችሁታል?
– ይኸው ክቡር ሚኒስትር ይዘነው መጥተናል፡፡
– በቃ ምላሻችንን እናስታውቃችኋለን፡፡
– እናመሰግናለን ክቡር ሚኒስትር፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
– ክቡር ሚኒስትር ሶፍትዌሩን ተመለከቱ አይደል?
– ዓይቼዋለሁ፡፡
– ስለዚህ በዚሁ መሠረት ይሥሩልን አይደለ?
– ለምን ሲባል?
– ምን ችግር አለው?
– ኪራይ ሰብሳቢ ሶፍትዌር ነዋ የሠሩት፡፡
– ክቡር ሚኒስትር እኛ የምንፈልገውን ዓይነት ሶፍትዌር እኮ ነው የሠሩልን፡፡
– እኛ ያቋቋምነው ድርጅት ለምን አይሠራውም?
– መጀመሪያ ዕድል የሰጠነውማ ለእሱ ነበር፡፡
– እና ምን ሆነ?
– የሠራቸው ሶፍትዌሮች የሚሠሩ አይደሉም፡፡
– ለምን?
– ድርጅቱ እኮ መዋጥ ከሚችለው በላይ ነው እንዲያላምጥ እያደረግነው ያለነው፡፡
– ቢሆንም ዕድል ይሰጠው፡፡
– እስከ መቼ? እስከ ምፅአት ቀን?
– መካከለኛ ገቢ ያለን አገር እስክንሆን ድረስ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ወዳጃቸው ሚኒስትር ጋ ደውለው ሻይ ለመጠጣት ተቀጣጠሩ]
– የሰሞኑን የባንኮቹን ውህደት እንዴት ዓየኸው?
– በዓይኔ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
– እኛም ብናስብበት ጥሩ ይመስለኛል፡፡
– ምኑን?
– መቀላቀሉን፡፡
– አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
– የሁለታችንን መሥሪያ ቤት መቀላቀል ነዋ፡፡
– ለምን?
– ለሥራው ቅልጥፍና ነዋ፡፡
– ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡
– የምን ጥንቃቄ?
– አንዳንድ ጋዜጦች እኮ ቀልደውብናል፡፡
– ምን ብለው?
– የባንኮቹ ቅልቅል የፈረስና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽንን እንደመቀላቀል ነው ብለው፡፡
– ሁለቱም ፌዴሬሽኖች ሩጫ ላይ ያተኮሩ ስለሆኑ ቢቀላቀሉ ምን ችግር አለው?
– ያው ልክ እንደ ውኃና ዘይት የማይቀላቀሉ ነገሮች ስላሉ ብዬ ነው፡፡
– በፊት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አንድ አልነበረም እንዴ?
– እሱማ ነበረ፡፡
– ስለዚህ ውኃና ዘይት ይቀላቀላሉ ማለት ነው፡፡
– ለማንኛውም የእኛን ቅልቅል እናስብበት፡፡
– በል እሺ እኔም ልሂድ፡፡
– የት ነው የሚሄዱት?
– ቅልቅል!
[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቅልቅሉ ከሹፌራቸው ጋ እየሄዱ ነው]
– ይኼን ማስታወቂያ ዓየኸው?
– የቱን የቢራውን ነው?
– ካለሱ የሚታይህ ነገር የለም ማለት ነው?
– አይ በየቦታው ተለጥፏል ብዬ ነው፡፡
– ይኼም እኮ በየቦታው ተለጥፏል፡፡
– የቱ ማስታወቂያ ነው ክቡር ሚኒስትር?
– ያ ፊት ለፊት ስልክ እንጨቱ ላይ የተሰቀለው፡፡
– ሄሎ ደላላ የሚለው፡፡
– አዎን፡፡
– ለነገሩ እኔም በየቦታው ዓይቼዋለሁ፡፡
– ለመሆኑ ምንድን ነው የሚሠራው?
– ድለላ ነዋ፡፡
– ምን?
– ድለላ፡፡
– እኛ ደላሎችን ለማጥፋት ተነስተናል ጭራሽ በስልክ መጡ?
– ክቡር ሚኒስትር ግን ይህ ተግባራችሁ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አይሆንባችሁም?
– ለምን ይሆንብናል?
– በርካታ ሰው ሥር አጥ ይሆናላ፡፡
– ለምን?
– ደላላ ያልሆነ ሰው የለማ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸው ጋ ደወሉ]
– ስማ ባለፈው አንድ ዳይሬክቶሬት እንዲቋቋም ነግሬህ ነበር አይደል?
– የትኛው ነበር ክቡር ሚኒስትር?
– የጋኔን አስወጪ ዳይሬክቶሬት ነዋ፡፡
– የምን ጋኔን?
– የሙስና ጋኔን፣ የኪራይ ሰብሳቢ ጋኔን፣ የኒዮሊብራል ጋኔንና እንዲሁም ሌሎችም፡፡
– አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ለዚህ ዳይሬክቶሬት አንድ የስልክ መስመር ከቴሌ መውሰድ አለብን፡፡
– የምን የስልክ መስመር?
– አጭር የስልክ መስመር ከቴሌ ይውጣለት፡፡
– ምን ያደርግለታል?
– ሰዎች ጋኔኖችን ሲያዩ ሪፖርት የሚያደረጉበት፡፡
– እ…
– እኔን ያስጨነቀኝ ቁጥሩ ስንት ይሁን የሚለው ነው?
– ሁሉም የሚጀምሩት በ8 ቁጥር ነው፡፡
– ግን አራት ዲጂት መሆን አለበታ?
– ሦስቱ ዲጂትማ ይታወቃል፡፡
– እንዴት ይታወቃል?
– የጋኔን ቁጥር እኮ 666 ነው፡፡
– ስለዚህ 8 – 666 እንበለው እያልከኝ ነው?
– እህሳ ባይሆን ስሙን ምን እንበለው?
– የምን ስም?
– አይ ሄሎ ደላላ፣ ሄሎ ካሽ እንደሚባለው የዚህን ቁጥር ስም ምን እንበለው?
– ሄሎ ጋኔን!

Post Reply

Return to “Ethio Politics .... ኢትዮ ፖለቲካ”