ዳር ድንበራችን በአገር ከሃዲዎች አይሸጥም! (ከኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ)

ፖለቲካ ፣ ወቅታዊ ጉዳዮች
Politics , Current affairs
selam sew
Leader
Leader
Posts: 618
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

ዳር ድንበራችን በአገር ከሃዲዎች አይሸጥም! (ከኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ)

Unread post by selam sew » 18 Dec 2015 16:21

ዳር ድንበራችን በአገር ከሃዲዎች አይሸጥም! (ከኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ)
Ethiopian Border Affairs Committee

ከኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ
ታህሳስ 7 ቀን 2008 ዓ/ም (December 17, 2015)

በቅርቡ የወያኔ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ የሱዳንን ምክትል ፕሬዚዳንት ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት በሰጡት መግለጫ በያዝነው ወር ውስጥ የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር በመሬት ላይ የመካለሉ ሥራ እንደሚጀመር በድፍረት የሰጡት ቃል የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴን ጨምሮ መላው የኢትዮጵያን ሕዝብ በእጅጉ ያሳዘነና ያሳፈረ ከፍተኛ የአገር ክህደት ወንጀል ነው። በሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ ሥር የተተኩት አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ የተረከቡት የመንግሥት ስልጣን ብቻ ሳይሆን፤ እሳቸውም እንደ አቶ መለስ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ማፍረስና የአገሪቷን ሕልውና ማናጋት ነው።

የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ፤ ለበርካታ ዓመታት ባደረገው ያላሰለሰ ክትትል የወያኔ ገዢ ቡድን ከሱዳን መንግሥት ጋር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በሚዳፈርና ዘለቀታዊ ጥቅማችንን ለባዕዳን አሳልፎ በሚሰጥ መልኩ በድብቅ እየተሸረበ ያለውን ደባና አሣፋሪ ተግባር በተገቢ ጥናትና በመረጃ ላይ ተመስርቶ በተከታታይ ሲያጋልጥ ቆይቷል። ይሁን እንጂ፤ የወያኔ መሪዎች በዚህ የአገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በሚያክል ትልቅ ጉዳይ ላይ ከዋናው የጉዳዩ ባለቤት ከሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጀርባ የጀመሩት ድብቅ ድርድር አጠናቀው ዛሬ አፋቸውን ሞልተው በቅርቡ ወደ ተግባር ለመተርጎም ቀነ ቀጠሮ መያዛቸውን ከራሳቸው አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ አንደበት እየሰማን ነው።

Image

ወያኔ የሕዝብ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲበዛበት ከሱዳን ጋር የድንበር ስምምነት ለማድረግ እየተወያየን ነው፤ ሆኖም እስካሁን የተደረሰበት ስምምነት የለም ከሚል የተለመደ ቅጥፈት በቀር ምንም ዓይነት ዝርዝር መረጃ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይገልጽ እንደ ግል ንብረቱ ብቻውን ተወያይቶ ብቻውን ወስኖ በመሰዋዕትነት የተከበረውን የድንበር መሬት እንደለመደው ለባዕድ ሊያስረክብ ነው።ይህ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አጥብቆ የሚጠላና ለማጥፋት የተነሳ ቡድን በተደጋጋሚ የአገር ሃብትን አሳልፎ ሲሰጥ ለዓመታት ቁጭ ብለን አየን። ወያኔ አገሪቷንና ሕዝቧን መጉዳት ሥራዬ ብሎ ሲቀጥልበት እኛ ደግሞ ዝምታውን አበዛነውና፤ እነሆ ዛሬ በለምነቱ፤ በውሃ ሐብቱ፣ በኣዕዋፋትና በእንሰሳት፣ በደንና በእፀዋት የተከበበ ሰፊና ለም መሬት ለሱዳን ገፀ በረከት ቀረበ።ይሄ ከክህደቶች ሁሉ ትልቁ ክህደት የሆነው አገር የማጥፋት ስራ ነገ ሳይሆን ዛሬ አንድ ሆነን ካላስቆምነው “ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ቆመው ማውረድ ያዳግታል’’ እንደተባለው የሚያስከትለውን መዘዝ ከፍተኛ ነው።

አገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት አንድነቷንና ነፃነቷን በቀጣይነት ማስከበርና ማቆየት የቻለችው ተቀናቃኝ ጠላት ሳይኖራት ወይም በጎረቤቶቿ ፈቃድና እንዲሁ በታሪክ አጋጣሚ ሳይሆን፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብና በተለይም በድንበሩ አካባቢ የሚኖረው ወገናችን ለአገሩ አንድነትና ክብር ካለው ፍቅርና ቀናኢነት የተነሳ በከፈለው መሪርና ክቡር መስዋዕትነት ነው። የፖሊቲካ ርዕዮታቸውንም ይሁን እምነቶቻቸውን ተገን አድርገው የአገራችንን የውሃና የሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶቻችን ሲቻል በቀጥታ ለመቆጣጠር አሊያም እንደልባቸው ለመዝረፍ የፈለጉ የቅርብም ሆኑ የሩቅ ኃይሎች በተደጋጋሚ ያደረጉት ጥረት ምኞት ብቻ ሳይሆኑ ቅዠት ሆነው እንዲቀር የተደረገው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጎሣ፣የሃይማኖት፣የቋንቋም ይሁን የአካባቢ ልዩነት አጥር ሳያግደው ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች በአንድነት ቆመው በከፈሉት ከፍተኛ የሕይወት ዋጋ ነው። የኢትዮጵያ ታላላቅ መሪዎች፥ አፄ ቴዎድሮስ፣ ንጉስ ተክለሃይማኖት፣ አፄ ዮሐንስን፣ አፄ ምኒልክ እና አፄ ኃይለሥላሴ ክቡር መስዋዕትነት እየከፈሉ አስከብረውት ያቆዩቱንና በአካባቢው ጀግና ሕዝብ የመረረ ተጋድሎ ተጠብቆ የኖረውን የኢትዮጵያ ወሰን ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት የሚደረገው ሕገ ወጥ ውል ውሎ አድሮ የሚያስከተለውን መዘዝ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ችግሩ ሁለቱን እህትአማች አገራት ወደ አይቀሬ ጦርነት የሚወስድ እና ይህም ኢትዮጵያና ሱዳን በመልካም ጉርብትና ተከባብረው እንዳይኖሩ አልፎም ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ ጠንቅ እንደሚሆን፤ ይህን ለማስፈጸም በመሯሯጥ ላይ ያሉ ሁሉ ሊያውቁት ይገባል።

የሚሰማ ጠፍቶ ይህንን የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት አሳልፎ የሚሰጠው ድንበሩን የመከለል ሥራ ቢቀጥል፤ ዛሬም ሆነ ወደፊት በሚፈጠረው ድንበርን የማስከበር እርምጃ ለሚደርሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ተጠያቂው ዛሬ የመሬቱን የፖለቲካ ሽያጭ ያስፈጸሙና የተባበሩ ሁሉ መሆናቸውን ማስጠንቀቅ እንወዳለን። የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎችን የአፍሪካን ምድር እንዳሻቸው ሲቀራመቱ በነበረበት ወቅት ግብጽን ጨምሮ ትገዛ የነበረችው ቅኝ ገዥዋ እንግሊዝ የኢትዮጵያን ድንበር በተመለከተ በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት ብልሁ መሪ ከአጼ ምኒልክ ጋር እ.አ.አ. በ1902 ዓ.ም. ድርድርና ውል ማድረጋቸው ይታወቃል። ይሁን እንጅ፤ የእንግሊዙ መኮንን ሻለቃ ቻርልስ ጉዌን እ.አ.አ. በ1903 ከስምምነቱ ውጭ በብቸኝነት በመሬት ላይ ያደረገውን የድንበር ክለላ አፄ ምኒልክም ሆኑ አፄ ኃይለሥላሴ እንዲሁም የደርግ መንግሥት እንዳልተቀበሉት በተደጋጋሚ ተገልጿል። አፄ ምኒልክ እና ሌሎች የኢትዮጵያ መሪዎች ከአውሮፓ መሪዎች ጋር ውል ሲዋዋሉና ሲደራደሩ በእነዚህ ባዕዳን የተበተቡት ብዙ ሥራዎችን እያከሸፉና የአገራቸውን ጥቅም ለአፍታም አሳልፈው ሳይሰጡ አገራዊ ኃላፊነታቸውንና የመሪነት ግዴታቸውን በሚገባ የተወጡ እንደነበሩ በኩራት የሚዘከር ነው።

በአንድ ወቅት አጼ ዮሐንስ አራተኛ “ምጽዋን ለጣሊያኖች አልሰጠኋቸውም እንግሊዞች ናቸው የሰጡአቸው። ምጽዋ የኢትዮጵያ ነው ። እኔ የኢትዮጵያ የሆነውን ማንኛውንም ግዛት የመተው ፍላጎትም ሆነ ስልጣንም የለኝም’’ ሲሉ እንዳረጋገጡት ሁሉ፤ በአገር ወዳድነት የሚታወቁት የኢትዮጵያ መሪዎች ከፈጣሪ በታች ጠያቄ የሌለባቸው እና ምንም ነገር ለማድረግ ሙሉ ሥልጣን የነበራቸው ቢሆንም እንኳ፤ የአገራቸውንና የሕዝባቸውን ጥቅም አሳልፈው እንዳልሰጡ ሕያው ታሪካቸው ይመሰክራል። ጥንት የኢትዮጵያ ይዞታ የነበሩና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከኢትዮጵያ ይዞታ ውጪ የሆኑትን ለማስመለስ ያለ መታከት የሚጥሩ፤ በዚህም ጥረትም ሕይወታቸውን መስዋዕት ያደረጉ የምንኮራባቸው መሪዎች እንደነበሩ እናስታውሳለን። ይህን ሐቅ እኛ ብቻ ሳንሆን ባዕዳን ታሪክ ጸሐፊዎች ጭምር የመሰከሩት እውነት ነው።

ያለ መታደል ሆነና ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ያሉት ገዥዎች አገርን አስከብረው መስዋዕት ሆነው እንዳለፉት መሪዎች ሳይሆኑ፤ ለባዕዳን ጥብቅና የቆሙና አገራቸውን ሳይወዱ በመንግስት ስም እነሆ ያሻቸውን እያደረጉ እስካሁን ተቀምጠዋል። ለአገር መስዋዕት ሆነው ያለፉት ቀደምት ጀግኖቻችን ቀና ብለው ይህን ሁኔታ ቢመለከቱ እንዴት ያዝኑ ይሆን? የወዱቀበት መሬት በተወጉት ጠላት ተወስዶ ዳሩ ተገፍቶ መሃሉ ዳር ሲሆን ሲረዱ እንዴት ይረግሙን ይሆን? ትላንት የባሕር በራችንን አሰብን እና ኤርትራን አሳልፎ የሰጠ አገዛዝ ዛሬ ከሰሜን ምሥራቅ ጫፍ እስከ ደቡብ ምሥራቅ ግርጌ ያለውን ለም የድንበር መሬት ለሱዳን መንግስት አሳልፎ አይሰጥም ብሉ መገመት የዋህነት ብቻ ሳይሆን በአገር ጉዳይ ግድ የለሽነት መሆንን ከማመልከት በላይ ምን ሊባል ይቻላል። ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳየው የተባለውን የመሬት ክልል ለሱዳን መንግስት በገጸ በረከትነት የማስረከቡ ጉዳይ አንድ ሐሙስ ብቻ ነው የቀረው። የኢትዮጵያን ቅርፅና ህልውናዋን የማጥፋት ቀዳሚ አጀንዳ አድርጎ የተነሳው የወያኔ አገዛዝ ይህን የመሰለ ሤራና የአገር ክህደት ወንጀል ከመጸም የሚገታው መቼ ነው? መጨረሻው የት ነው? የሚለው ጥያቄ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ቀዳሚ ጥያቄ መሆን ይኖርበታል። የአገሪቷ ዳር ድንበር ተሸርሽሮ መሃሉ ድንበር ከመሆኑ በፊት፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ሁሉ የወያኔን ሥራ በህብረት ድምፅ በኃይል ሊዋጋውና ሊቃወመው ግድ ይላል።

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንዳስገንዘብነው ሁሉ ይህ ጉዳይ በድንበሩ አካባቢ ላሉ ወገኖቻችን ብቻ የሚተው አይደለም፤የሁሉም የጋራ ጉዳይ ነውና። የዚህ አሳፋሪ ድርጊት ዕዳ ከፋይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በመሆኑ በመሐከላችን ምንም ዓይነት የፖለቲካ አመለካከት ይሁን የጎሳ፣ የሃይማኖት ወይም የአካባቢ ልዩነትን ሳናሳይ ወዳጅ ቀርቶ ጠላት በመሰከረልን በተለመደ በአገር መውደድና በአንድነት መንፈስ ድምፃችንን እንድናሰማና ጠንካራ ክንዳችንን አንስተን በጋራ እንድንቆምና ይህን የወያኔ የአገር ክህደት ተግባር በአጭሩ እንድናስቀር አገር አድን ጥሪ እናቀርባለን።

ዛሬ “ሁሉም በእጄ ሁሉም በደጄ’’ በሚል ፈሊጥ ይህንን የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጠውን ከሱዳን ጋር የሚደረገውን የድንበር ክለላን ለማድረግ ቀነ ቀጠሮ የያዛችሁ ከክልል እስከ ፌደራል ሥርዓት ያላችሁ ባለሥልጣናት ሁሉ፤ ስምምነቱ የሱዳን እንጂ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅም እንደማያስጠብቅ በመረዳት ውሉን ዳር ከማድረስ እንድትቆጠቡና የቆየውን የኢትዮጵያ የግዛት አንድነት እንድታስከብሩ አጥብቀን እናሳስባለን። የአገር ሉዓላዊነት በመካድ ዛሬ የምትፈጽሙት ተግባር መዘዙ አሁን ላለው ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለተከታታይ ትውልዶች በሙሉ የሚተርፍ መሆኑ ተገንዘቡ። ይሁን እንጂ፣ የሕዝብን ጭሆት ንቃችሁ፤በእቅዳችሁ መሰረት ብትቀጥሉ በእርግጠኝነት ልንነግራችሁ የምንፈልገው፤ እንደማንም አምባገነን መንግሥት የእናንተም ሥርዓት ይፈርሳል፤ በአገር ክህደት ትልቁ ወንጀል በሕግና በሕዝብ ትጠየቃላችሁ፣ በታሪክ ጥቁር መዝገብም ትመዘገባላችሁ። ለእናንተ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማዳችሁ ሁሉ ሃፍረትና ፀፀት ትሆናላችሁ። አሁንም ጊዜ አላችሁና የተስማማችሁበትን ሰነድ ውድቅ አርጋችሁ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት አስጠብቁ።

የኢትዮጵያ ዳር ድንበር በቆራጥ ልጆቿ ደም ይከበራል!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

Post Reply

Return to “Ethio Politics .... ኢትዮ ፖለቲካ”