ሰንደቅ – አዲስ አበባ፣ ኦሮምያና ሕገ-መንግስቱ! (ዘሪሁን ሙሉጌታ)

ፖለቲካ ፣ ወቅታዊ ጉዳዮች
Politics , Current affairs
User avatar
zeru
Leader
Leader
Posts: 952
Joined: 19 Aug 2009 17:01
Contact:

ሰንደቅ – አዲስ አበባ፣ ኦሮምያና ሕገ-መንግስቱ! (ዘሪሁን ሙሉጌታ)

Unread post by zeru » 24 Apr 2014 20:28

የአዲስ አበባና የኦሮምያ ግንኙነት የፌደራል ስርዓቱ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ጊዜ አንስቶ እያወዛገበ ያለ ጉዳይ ነው። በቅርቡ ደግሞ የአዲስ አበባ አስተዳደር የ10 እና የ25 ዓመት የተቀናጀ የጋራ ልማት ፕላን በማዘጋጀት በተለምዶ “ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ ከተሞችን ከአዲስ አበባ ጋር ለማቀናጀት ጥረት መጀመሩ ተድበስብሶ ያለፈውን የፌደራሊዝም ጥያቄ እንደገና እንዲያገረሽ አድርጎታል።
የተቀናጀ የጋራ ልማት ፕላኑ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮምያ ከተሞችን ወደ አዲስ አበባ ሊቀላቅል ነው በሚል ሥጋት በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፉ የኦሮሞ ብሔር ፓርቲዎችና በክልሉ ገዢ ፓርቲ ኦህዴድ አመራርና አባላት ጭምር ጥያቄ እየተነሳ ነው። ጥያቄው የመርህ፣ የአፈፃፀም ችግሮችና ሕገ-መንግስታዊ ጥሰትን ያነገበ ቢመስልም በውስጡ ከማንነት ነጠቃ ጋር የተያያዘም መልዕክት አለው። ጥያቄው በመርህ፣ በአፈፃፀም መጓደል፣ የማንነት ነጠቃና ሕገ-መንግስታዊ ጥሰት መፈፀም የታጨቀ በመሆኑም ለመፍትሄ አሰጣጥ አስቸጋሪ አስመስሎታል።
የጥያቄውም አቀራረብ በገዢና በተቃዋሚ ጎራ ባሉ የኦሮሞ ልሂቃን ዘንድ እየተነሳ በመሆኑም ሁኔታውን ውስብስብ ያደረገው ይመስላል። የጥያቄውም ይዘት ቀደም ሲል “ፊንፊኔ የኦሮምያ ናት” የሚለውን ትቶ “ፊንፊኔ ወደ ኦሮምያ መስፋት የለባትም” ወደሚል ተቃውሞ መሸጋገሩም ሌላኛው አወዛጋቢ ሁኔታ ነው። ይህ ሁኔታ በእስራኤልና ፍልስጤም የሚታየውን የዘመናት አለመግባባት በአዲስ አበባ እና በኦሮምያም ይደገም ይሆን ያሰኛል።
በመርህ ደረጃ “ፊንፊኔ የኦሮምያ ናት” የሚል አመለካከት ካለ ከተማዋ ወደየትኛውም የኦሮምያ አካባቢዎች መስፋፋቷን መቃወም የግራን እጅ በቀኝ እጅ ከመቁረጥ አይለይም። በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ አበባ እንደ ፌዴራሉ ስርዓት መቀመጫ ማደግና መስፋፋት ይኖርባታል። አዲስ አበባ የሀገሪቱ ሁሉም ሕዝቦች መኖሪያ የአህጉሪቱም መዲና እንደመሆኗ መጠን እድገቷ ወደላይ (Vertical) እንጂ ወደ ጎን (Horizontal) መሆን የለበትም የሚለው የኦሮሞ ሊሂቃን መከራከሪያ በቀጥታ የፌደራል ስርዓቱን በሙሉ ልብ ያለመቀበል ችግር መሆኑን ሊጠቁም ይችላል።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹና ዋና ፀሐፊው አቶ በቀለ ነጋ “ፕላንና ልማት” በሚል ሰበብ ሕገ-መንግስቱ መጣስ የለበትም ብለው ከሚከራከሩ የክልሉ ተወላጆች መካከል ግንባር ቀደሞቹ ናቸው።
በተለይ አቶ በቀለ ብሔር ብሔረሰቦች መተዳደር ያለባቸው በፌዴራል ስርዓቱ ነው ሲሉ ለሰንደቅ ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት ይገልፃሉ። የፌዴራል ስርዓቱን ተማምነንበት የምንኖረው ካልሆነ መሸዋወድ የለብንም ይላሉ። የፌዴራል ስርዓቱ ለኦሮምያ ክልል የሰጠው ድንበር በልማትና በከተማ ልማት ስም ሊጣስ አይገባም። ክልሎችም እራስን በራስ የማስተዳደር መብት በሕገ-መንግስቱ የተረጋገጠላቸው በመሆኑ ሊከበር እንደሚገባም ያስረዳሉ።
አቶ ሙላት ገመቹም በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) ላይ ኦሮምያ ከአዲስ አበባ ማግኘት የሚገባት “ልዩ ጥቅም” አልተከበረም ሲሉ ሌላ መከራከሪያ ያቀርባሉ። በእርግጥም በተጠቀሰው አንቀፅ ላይ የኦሮምያ ክልል፣ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮምያ ክልል መሐል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቃል ሲል ገልጾ ዝርዝር ሕግ እንደሚወሰን ያስረዳል።
የሕገ-መንግስቱን ድንጋጌ መሬት ለማውረድ ዝርዝር ሕግ ማስፈለጉ ይዋል ይደር የሚባል ጉዳይ አይደለም። ያም ሆኖ በኦሮሞ ልሂቃን ዘንድ በተደጋጋሚ የሚነሳው ኦሮምያ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ልዩ ጥቅም ማግኘት አለበት የሚል የአንድ ወገን መከራከሪያ ያቀርባሉ። ይሁን እንጂ በዚሁ ሕገ-መንግስታዊ ድንጋጌ ውስጥ አዲስ አበባም በኦሮምያ ክልል ውስጥ ማግኘት የሚገባት ልዩ ጥቅም ማግኘት እንዳለባትም አሻሚ አተረጓጎም ያለው በሚመስልም አዲስ አበባም እንደ ፌዴራል ከተማ ከኦሮምያ ክልል ማግኘት የሚገባት ልዩ ጥቅም እንዳለም መረዳት ያስፈልጋል።
በሌላ በኩል አዲስ አበባ በድርብ የፌዴራል መንግስቱና የኦሮምያ ዋና ከተማ እንደመሆኗ መጠን የአዲስ አበባን ወደ ጎን መስፋፋት መቃወም ሌላ ጥያቄ ያጭራል። እነ አቶ ሙላት ግን አዲስ አበባ በድርብ የፌዴራል ስርዓቱና የኦሮምያ ክልል ዋና ከተማ ብትሆንም አዲስ አበባ በኦሮሞዎች እየተመራች አይደለችም የሚል መከራከሪያም ያነሳሉ። ይሁን እንጂ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረና ከተማዋንም በከንቲባነት መተዳደር ከጀመረች ጊዜ አንስቶ በከንቲባነት የሚሾሙ ግለሰቦች ከኦሮሞ ብሔር ብቻ መሆኑን ማስታወስ ይቻላል።
አቶ ሙላትና ሌሎች በገዢውም ሆነ በተቃዋሚው ውስጥ የሚገኙ የኦሮሞ ሊህቃን የአዲስ አበባ መስፋፋት የኦሮምያ የቆዳ ስፋት (Size) ሊያንስ ይችላል የሚሉት በዋናነት የፌዴራል ስርዓቱንና ሕገ-መንግስቱን በመጥቀስ ነው። ነገር ግን ሕገ-መንግስቱም ሆነ የፌዴራል ስርዓቱ መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እየተጣጣመ የሚሻሻል እንጂ አንድ ቦታ የሚቆም እንዳልሆነ ይታወቃል። በፌዴራል ስርዓቱ ማዕቀፍ ውስጥ የተዋቀሩ ክልሎችን ድንበር የሀገር ሉአላዊነት አስመስሎ ተለጥጦ ሲቀርብም ይታያል።
የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 48(1) ስለ ክልሎች አከላለል ለውጦች ያወሳል። በዚሁ ድንጋጌ ላይ የክልሎችን ግንኙነት እንደ “ድንበር” ሳይሆን እንደ “ወሰን” ያቀርባል። በክልሎችም መካከል የወሰን ጥያቄ ሲነሳ ከተቻለ በሚመለከታቸው ክልሎች ስምምነት እንደሚፈታ ያ ካልተቻለ ግን በፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደሚወሰን ያስረዳል። የፌዴሬሽን ምክር ቤቱም የሕዝብን አሰፋፈርና ፍላጎት መሠረት በማድረግ እንደሚወስን ተደንግጓል።
በዚሁ ድንጋጌ መሠረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአዲስ አበባ አስተዳደርና በኦሮምያ ክልል መካከል የወሰን አለመግባባት ሲከሰት የሕዝብ አሰፋፈርና ፍላጎትን መሠረት በማድረግ እልባት እንደሚሰጥ መረዳት ይቻላል። ይህም ማለት ክልሎች በሕገ-መንግስቱ የራሳቸው ወሰን ቢኖራቸውም በጊዜ ሂደት በሚነሱ የልማትም ሆነ የከተማ ልማት እቅድ ጥያቄ ወሰኑን በማሸጋሸግም ሆነ በሌላ አሰራር የሕዝብን አሰፋፈርና ፍላጎት በማየት መፍትሄ እንደሚሰጥ ይጠቁማል። በሌላ አነጋገር አዲስ አበባ ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ያላት ድንበር ላይ ቆማ ትቀራለች ማለት እንዳልሆነ ይልቁኑ በሕዝብ ፍላጎትና አሰፋፈር መሠረት ወሰኗ ወደ ኦሮምያ ክልል እየሰፋ ሊሄድ እንደሚችል መረዳት ይቻላል።
የእነ አቶ በቀለም ሆነ የሌሎች የኦሮሞ ልሂቃን ሌላው መከራከሪያ የኦሮምያ መሬት እየተቆረሰ ለአዲስ አበባ መሰጠት እንደሌለበትና አሰራሩም አንድ ቦታ መቆም እንዳለበት በአፅንኦት ይናገራሉ። ነገር ግን የክልሎችን ስልጣንና ተግባር በሚዘረዝረው የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 52(2)መ ላይ ክልሎች መሬትና የተፈጥሮ ሐብትን የሚያስተዳድሩት የፌዴራል መንግስቱ በሚያወጣው ሕግ እንደሆነ ይደነግጋል። ይህም ማለት የኦሮምያ ክልል ሕዝብ በሕገ-መንግስቱ ተወስኖ በተሰጠው “ወሰን” ሕዝቡ እራሱን በራሱ የማስተዳደርና የመምራት መብት ቢኖረውም, የኦሮምያን መሬትና የተፈጥሮ ሐብት የሚያስተዳድረው ግን የፌደራል መንግስቱ በሚያወጣው ሕግ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባውም።
በእነ አቶ በቀለም ሆነ በሌሎች የኦሮሞ ልሂቃን ዘንድ የአዲስ አበባ መስፋፋት የኦሮሞ ተወላጆችን ያፈናቅላል፣ ከከተማዋ የሚወጣው ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ የኦሮምያን ወንዞች እየበከለ ነው። ከዚያም አለፍ ሲል “የማንነት ነጠቃ” ነው። ቀደም ሲል በነበረው ሀገር የማቅናት ስም የኦሮሞን ሕዝብ እንደገና ገባር ለማድረግ ነው ሲሉም ስጋታቸውን ይገልፃሉ።
በመርህ ደረጃ ሕዝብን ማፈናቀል ሕገ-ወጥነት ነው። በሕገመንግስቱ አንቀጽ 40(4) ላይ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬት በነፃ የማግኘትና ከመሬታቸውም ያለመነቀል መብታቸው የተከበረ እንደሆነና አፈፃፀሙም በሕግ እንደሚወሰን፤ እንዲሁም በዚሁ ድንጋጌ አንቀፅ ንዑስ አንቀጽ 7 ላይ መንግስት ለሕዝብ ጥቅም ሲል ለሚወስደው መሬትም ሆነ ንብረት ተመጣጣኝ ካሣ እንደሚከፍል ያስገነዝባል። ስለሆነም በአዲስ አበባ መስፋፋት ሳቢያ የሚፈናቀሉ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ወይም አርሶ አደሮች ተመጣጣኝ ካሣ አግኝተው ሊነሱ ይችላሉ እንጂ አዲስ አበባ አትስፋፋም ብሎ መቃወም የሕገ-መንግስቱን ድንጋጌ መቃወም ሊሆን ይችላል።
ከከተማዋ የሚወጣው አካባቢን የሚበክለው ቆሻሻም በተመለከተ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 44 ላይ ተደንግጓል። መንግስት ዜጎች ንፁህና ጤናማ በሆነ አካባቢ እንዲኖሩ ኃላፊነቱን ይወጣል እንጂ አዲስ አበባ የኦሮምያን ክልል በቆሻሻ ስለበከለች ብቻ ከተማዋ ማደግና መስፋፋት እንደሌለባት አይደነግግም። በመሆኑም የአፈፃፀምና የመርህ ጥያቄዎችን አደባልቆ በማንሳት የከተማዋን እድገት ባለበት እንዲቆም ማድረግ ተገቢም ተመካሪም አይሆንም።
የማንነት ነጠቃ እና ከሀገር ማቅናት ጋር ተያይዞ የተነሳው የገባርነት ስጋትም በተመለከተ በሕገ-መንግስቱ መግቢያ ላይ እንደቀረበው በሀገሪቱ ታሪክ አንዱ ሌላኛውን የሚያስገብርበት ስርዓት ግብአተ-መሬቱ መረጋገጡ፣ ይልቁኑ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ መሆኑን ይህም ተግባራዊ መሆኑን ያስረዳል። “የማንነት ነጠቃ” የሚለው አገላለፅም ከጠባብነት አመለካከት ጋር ሊዛመድ እንደሚችልም ያስጠረጥራል። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከተሜነትን (Urbanization) የአንድ የተወሰነ ብሔር ማንነት ነጠቃ አድርጎ መወሰዱ ጉንጭ የሚያለፋ ክርክር ሊሆን ይችላል።

Post Reply

Return to “Ethio Politics .... ኢትዮ ፖለቲካ”