"ኢህአዴግ ነፃነትና ነፃ ምርጫን እንደ ጦር የሚፈራበት ደረጃ ላይ ደርሷል".. አቶ ስየ አብርሃ

ፖለቲካ ፣ ወቅታዊ ጉዳዮች
Politics , Current affairs
ኦሽንoc
Leader
Leader
Posts: 1129
Joined: 07 Aug 2009 14:20
Contact:

"ኢህአዴግ ነፃነትና ነፃ ምርጫን እንደ ጦር የሚፈራበት ደረጃ ላይ ደርሷል".. አቶ ስየ አብርሃ

Unread post by ኦሽንoc » 27 Oct 2009 12:22

* ስለወ/ት ብርቱካንና ስለሌሎች ወገኖቻችን መታሰር ከኢህአዴግ እና ከመንግሥት ጋራ በሚደረግ ድርድር ጉዳዩ መነሣት ይገባዋል

* በመከላከያ፣ በደኅንነት ፖሊሲዎች እና በተቋማት ግንባታ ዙሪያ የማማከር አገልግሎት ለመስጠት ሥራ ጀምሬያለኹ

* ኢህአዴግ ነፃነትና ነፃ ምርጫን እንደ ጦር የሚፈራበት ደረጃ ላይ ደርሷል

* ለኢሠፓ እና ደርግ የበለጠ የሚቀርበው ኢህአዴግ እንጂ ተቃዋሚዎች አይደሉም

* የኢህአዴግ አመራር ለ30 እና ለ40 ዓመታት በሥልጣን ላይ ለመቆየት ቆርጧል

* የግል ኑሮዬ በፖለቲካ ጥገኛ እንዲኾን አልፈልግም

* መጽሐፍ ጽፌያለኹ፤ አቅሙ ከተገኘ በቅርብ ይወጣል [center]
Siye Abraha.gif
Siye Abraha.gif (27.31 KiB) Viewed 1778 times
አቶ ስየ አብርሃ (የቀድሞ የመከላከያ ሚንስቴር ሚንስትር)[/center]

በሐምሌ ወር 1999 ዓ.ም. ከእስር ከተፈቱ በኋላ አንድ አገራዊ ፕሮጀክት ይዘው እየሠሩ ይገኛሉ። ከቀድሞው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፕሬዝዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ጋራ ስምንት የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማቀናጀት “የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት መድረክ” በተሰኘው ጥምረት ምሥረታ ግንባር ቀደም ተዋናይ ናቸው። እርሳቸው “የጠንካራ ተቃዋሚን ክፍተት የሚሞላ ትልቅ አገራዊ ፕሮጀክት ነው” ይሉታል - ጥምረቱን። ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር በምክክር የቆየውን መድረከ ለጥምረት ካደረሱት እና በጥምረቱ ብሥራት ወቅት በታዛቢነት ከተሳተፉት የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስተር ሚኒስትር አቶ ስየ አብርሃ ጋራ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ ሰፋ ያለ ቃለምልልስ አድርጋለች። ቃለምልልሱን እነሆ! መልካም ንባብ!

መድረኩ ሲቀናጅ በታዛቢነት ተገኝተዋል። የእርስዎ ቀጣይ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ምን ሊኾን ይችላል? በአንዱ ፓርቲ ውስጥ ይጠቃለላሉ፣ ፓርቲ ያቋቁማሉ ወይስ የተቀናጀው መድረክ እስኪዋሐድ ድረስ በታዛቢነት ይቀጥላሉ?

የመድረክ ጅምር ለምክክር ነበር። መስከረም 30 ቀን 2002 ዓ.ም. ግን በፓርቲዎች ማቋቋሚያ ዐዋጅ መሠረት ወደ ቅንጅት ለመሸጋገር እንዲችል ጉባዔ ጠርቷል። ዐዋጁ ግለሰቦች በቅንጅት ውስጥ እንዲታቀፉ ስለማይፈቅድ ከጥምረቱ ምሥረታ ጀምሮ የመድረክ አመራር አባል አይደለሁም። በዕለቱ ጉባዔው ላይ የተገኘሁት በታዛቢነት ነው። ወደ ፊት በመድረክ ያለኝን ተሳትፎ በሚመለከት፦ መድረክ ትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው፤ ተጀመረ እንጂ አላለቀም። የተጀመረው ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ተሸጋግሮ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችን በተገቢው ለማስተባበር የሚችልበት ደረጃ እስኪደርስ፣ አሁን በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ተፈጥሮ ያለው የመራራቅ ስሜት ተገፎ የአንድነት ስሜቱ እስኪጠናከር ድረስ፣ መድረክን እንደ ፕሮጀክት መግፋት እና ከአንድ ደረጃ ወደ ሚቀጥለው ደረጃ የማሸጋገር ሥራ ይኖራል።

እኔ በዚህ ሥራ ውስጥ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ መሳተፌ አይቀርም። አሁን ካለው የመድረኩ ዕድገት አኳያ በአባልነት ደረጃ መሳተፍ ባልችልም በመተዳደሪያ ደንቡ ውስጥ እንደ እኔ ያሉት ሰዎች አስተዋፅዖ ይኖራቸው ዘንድ የሚደነግግ አንቀጽ አለ። የመድረክ ሥራ አስፈጻሚ በዚህ ዙሪያ ተመካክሮ እኔ ለማበርከት የሚያስችለኝን ኹኔታ ያመቻቻል ብዬ እጠብቃለኹ።

በግልዎ አሁን ካሉት ፓርቲዎች በአንዱ ለመታቀፍ አልወሰኑም?

ይህ እንደ አማራጭ ያለ ነገር ነው። በሂደት በፓርቲ መታቀፍ ሊኖር ይችላል። በፓርቲ ከታቀፍኹ እንደ አንድ የፓርቲ አባል ኾኜ በመድረኩ እሠራለኹ። ያ አማራጭ ከሌለ ደግሞ በኾነ መንገድ ለመድረኩ አስተዋፅዖ ማድረጌ አይቀርም።

የአንድነት ፓርቲ አባላት ፓርቲያቸውን እንዲቀላቀሉ ጠይቀዎታል ይባላል?

እኔን እና የመጀመሪያውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፕሬዝዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን፤ የአንድነት ፓርቲ አባላት ሊያነጋግሩን እንደ ፈለጉ ተነገረን። በጥሪው መሠረት ጳጉሜ 4 ቀን 2001 ዓ.ም. ስንሄድ ተሰብስበው ጠበቁን። “አንድነት ውስጥ ገብታችኹ ፓርቲውን እና በኢትዮጵያ ውስጥ ለዴሞክራሲ የሚደረገውን ትግል እንድታጠናክሩ በአክብሮት እንጠይቃለን” አሉን። ስለኾነም ጥያቄው ቀርቦልኛል። ከዛ በፊትም በአመራሩ በኩል ይኸው ጥያቄ ሳይነሣ አልቀረም።

በወቅቱ የቀረበላችኹን ጥያቄ አለመቀበላችኹ፤ ጥያቄውን ያቀረቡ አባላት “ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋራ መሥራት አለመፈለጋቸውን ያሳያል” ማለታቸው ተጠቅሶ በምላሻችኹ ማዘናቸውን የሚገልጽ ዘገባ ተመልክቼ ነበር።

ጥያቄውን በአክብሮት ነው የማየው። በወቅቱ የሰጠኹትም ምላሽ፤ “ለጥሪያችኹ እግዚአብሔር ያክብርልኝ፤ ጥያቄያችኹንም የማየው በአክብሮት ነው፣ እናንተ ጠየቃችሁኝ ፓርቲያችኹስ ምን ያህል ዝግጁ ነው? ለእኔ አይነት ፖለቲከኛ ስፍራ ለመስጠት ምን ያህል ዝግጁዎች ናችሁ?” ነው ያልኹት። በአንድ ጋዜጣ ላይ እንደተጻፈው ጥያቄውን ውድቅ አላደረግኹትም፤ በአክብሮት ነው ያዳመጥኹት። እንደውም የጋዜጣው ዘገባ “አቶ ስዬ አንድነት የፈረሰ ቤት ነው ብለዋል” ይላል፤ አላልኹም። “እኔ ቁጡ ነኝ ብለዋል” ይላል፤ አላልኹም።

በህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ክፍፍል ወቅት አብረዎት ከወጡት እና በዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት ፓርቲ ውስጥ ያልተካተቱት ከፍተኛ አመራሮች መድረኩ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይ ምን አስተዋፅዖ አላቸው? ምን አይነት ሚና ሊኖራቸው ይገባል ብለው ያስባሉ?

በህወሓት አመራር ውስጥ ከነበሩት ሰዎች መካከል ዓረና ውስጥ አቶ ገብሩ አሥራት፣ ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ እና አቶ አውዓሎም ወልዱ ይገኛሉ። እኔ በመድረኩ ውስጥ ስሠራ ቆይቻለኹ። ከዚህ ውጭ ያሉት በመድረኩም ይኹን በዓረና ትግራይ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ በሚመለከት የማውቀው ነገር የለም። በህወሓት ውስጥ አንድ ነበርን ማለት ወደፊትም በፖለቲካ ውስጥ ቀጣይ ተሳትፎ ይኖረናል ማለት አይደለም። እያንዳንዱ ሰው ቀጣይ ዕድሉን በሚመለከት የየራሱን ውሳኔ ነው የሚወስነው። ስለኾነም አንዳንዶቹ ከፍተኛ ትምህርታቸውን ተምረው ወደ ሌላ ሥራ ተሰማርተዋል። አንዳንዶቻችን በአንድ በኩል ኑሯችንን እየመራን ከፖለቲካ ሕይወት አንርቅም ብለን በፖለቲካ ተሳትፏችን ቀጥለን ነው የምንገኘው።

በፖለቲካ ውስጥ ሚና ሊኖራቸው አይገባም ይላሉ?

ይህ ውሳኔ ከእያንዳንዱ ሰው የሚመነጭ ነው። እቀጥላለኹ፤ መተው የለብኝም የሚል ይቀጥላል። በበሌላ በኩል፣ ገና ውሳኔ ላይ ያልደረሰ ሊኖር ይችላል። ስለዚህ የፖለቲካ ጉዳይ ወደው፣ ፈቅደው እና ወስነው የሚገቡበት ነው። እገሌ ስላለ ልግባበት ማለት በተለይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኹኔታ ውስጥ አያዛልቅም። የሚመጣውን ጣጣ ለመሸከም ወደው፣ ፈቅደው የሚገቡበት ነው።

በተቃውሞ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ከገባችኹት የቀድሞ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች “በስተኋላ አቶ ተወልደ ወ/ማርያም አሉ” የሚባለው እውነት ይኾን?

ፊት ለፊት እንጂ በስተኋላ ብሎ የፖለቲካ ጨዋታ የለም። አቶ ተወልደ ቀደም ሲል ከእኔ ጋራ በህወሓት ውስጥ ነበር። የፖለቲካ ብስለቱን አውቃለኹ። አከብረዋለኹ። በክፍፍሉ ከህወሓት ከወጣን በኋላ ግን እኔ እስከማውቀው ድረስ በመድረክም፣ በዓረና ትግራይም ኾነ በሌላ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ስለመኖሩ የማውቀው የለም።

ከእስር ከተፈቱ በኋላ በሞያዎ እና ባካበቱት ልምድ ገቢ ሊያገኙ የሚችሉበት ሥራ እየሠሩ አይመስልም። በንግድ፣ በማኅበራዊ ወይም በሰብዓዊ መብት ችግሮች ዙሪያ ባተኮሩ ተቋማት ለመሥራት ወይም ለመሳተፍ ያሰቡት ነገር አለ?

ከእስር ቤት ከወጣኹ ጊዜ ጀምሮ ኅሊናዬ የተቀበለውን፣ አቅሜ የፈቀደውን ያህል በፖለቲካ እሳተፋለኹ፤ እየተሳተፍኹም ነው፤ ለወደፊቱም እቀጥልበታለኹ። ይህ እንዳለ ኾኖ የእኔ የግል ኑሮዬ በፖለቲካ ላይ ጥገኛ እንዲኾን አልፈልግም። ዕውቀት እና ችሎታ አለኝ። ባለኝ ዕውቀት እና ችሎታ ራሴን ማስተዳደር የምችል ሰው ነኝ። ከዚያ እስር እና እንግልት ወጥቶ፣ “ኑሮዬን እንዲህ አድርጌ ልምራ” ብሎ ግልጽ ኾኖ ወደ አንድ ሥራ ለመግባት ቀላል አይደለም። ይኹንና እያሰብኹበት ቆይቻለኹ። አሁን በግሌ ባለኝ እውቀት እና ልምድ ኑሮዬን ለመምራት እና ቤተሰቤን ለማስተዳደር የሚያስችለኝን ሥራ እየጀመርኹ ነው። እንግዲህ ለወደፊቱ በዚህ ሥራ ኑሮዬን ለመምራት የምችልበት ገቢ አገኛለኹ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

የሚጀምሩት ሥራ ምንይኾን?

ከማማከር አገልግሎት ጋራ የተያያዘ ነው።

በምን ጉዳይ?

ሕይወት ብዙ ትምህርት ሰጥቶኛል። በመከላከያ እና በደኅንነት ሥራ የእኔን ዕውቀት እና አገልግሎት የሚጠይቁ መንግሥታት ካሉ ስለ ሠራዊት ግንባታ፣ ስለ መከላከያ እና ደኅንነት ፖሊሲ እና ስለ ተቋማት ግንባታ በሚገባ ልሠራላቸው እችላለኹ። በቢዝነስ ሜኔጅመንት ሥራም ብዙ ቆይቻለኹ። ኤፈርት ውስጥ ብዙ ኩባንያዎች አሉ። እነዚህን ኩባንያዎች በማደራጀት እና ፋብሪካዎቹን በማቋቋሙ ተግባር ላይ ሠርቻለኹ፤ በፖለቲካም ብዙ ልምድ እና ዕውቀት አለኝ። ስለኾነም በእነዚህ መስኮች ባካበትኹት ዕውቀት እና ልምድ የማማከር አገልግሎት ለመስጠት እችላለኹ።

መድረክ ለዴሞክራሲያዊ ምክክር በኢትዮጵያን ተነሳሽነት ወስዳችኹ ካቋቋማችኹት መካከል የቀድሞ የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ትገኙበታላችኹ። መድረክ በመጪው ምርጫ ለመሳተፍ የሚወስን ከኾነ ኢህአዴግን በልምድ እና በሥነ ልቡና ከማወቅ አኳያ የምርጫው ውጤት የተለየ ገጽታ ይታይበት ይኾን?

በኢህአዴግ ውስጥ ከመኖራችን በተያያዘ፤ ከ30 ዓመት በላይ በፖለቲካ ትግል ውስጥ የቆየን ሰዎች ነን። ባለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ ውስጥ በርካታ የተማርናቸው ነገሮች አሉ። በመኾኑም በመጀመሪያ የወደፊቷን የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሰከነ መንፈሥ በማቃናት ረገድ አስተዋፅዖ ይኖረዋል ብዬ እገምታለኹ። ሁለተኛ፦ በመንግሥት ሥራ ለረዥም ጊዜ አገልግለናል። ይህ ደግሞ መንግሥታዊ ኃላፊነት የሚጠይቀውን ልምድ እና ዕውቀት ሰጥቶናል። ከዚህ ባሻገር በኢህአዴግ ውስጥ በነበረን ቆይታ የኢህአዴግ አመራሮችን አስተሳሰብ እና ስሌት ስጋትም ጭምር እናውቀዋለን፤ እንገነዘበዋለን። ከተቃዋሚ ኃይሎች ጋራም እየሠራን እንገኛለን። የእነርሱን አስተሳሰብ፣ ፖለቲካዊ አቋሞች እና ስጋቶችንም ተገንዝበናል። ይህም በድምር ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሔ የሚኾን ነገር በመጠቆም እና በማስቀመጥ ረገድ ጠቃሚ ነገር ይኾናል የሚል እምነት አለኝ።

በመጪው ምርጫ መድረኩ በምን በምን መልኩ ለኢህአዴግ ተግዳሮት ይኾናል ብለው ያስባሉ?

አገራችን ዴሞክራሲ ያስፈልጋታል። ብዙ ሰው በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲኖር በእጅጉ ይመኛል። ዴሞክራሲ እንዲሰፍን አንዱ በጣም ተፈላጊ ነገር የጠንካራ አማራጭ ፓርቲ የመኖር ወይም ያለመኖር ጉዳይ ነው። በመጀመሪያ ጠንካራ አማራጭ ተቃዋሚ ፓርቲ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሌለ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ይኖራል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ስለዚህ መድረክ ይህን የጠንካራ ተቃዋሚ ያለመኖር ክፍተት ይሞላል። ሁለተኛ፦ ደግሞ መድረክ በአገራችን ፖለቲካ ውስጥ ካሉት ተቃዋሚዎች ትብብር የወጣ ነው። የበርካታ ፓርቲዎች ትብብር እና ቅንጅት ነው። የሕብረ ብሔራዊና የብሔራዊ ፓርቲዎች ትብብርና እና ቅንጅት ነው። ስለዚህ አሉ የሚባሉትን ተቃዋሚዎች ያቀፈ በመኾኑ፣ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተቀባይነት እና ተደማጭነት የማግኘት ዕድሉ ሰፊ ነው። ለመጪውም ምርጫ አዲስ ግብአት ነው። ሦስተኛ፦ እያንዳንዱ ፓርቲ በተናጥል ከሚኖረው አቅም በላይ ስምንቱ አባል ፓርቲዎች ሲተባበሩ የበለጠ አቅም ይፈጥራሉ። የኢትዮጵያ ተቃዋሚች አንዱ ችግራቸው እዚህም እዚያም ያሉ ጠንካራ መሪዎች በተለያዩ ፓርቲዎች መበተናቸው ነው። አሁን ግን በአገር ውስጥ በተለያዩ ፓርቲዎች ተበትነው የነበሩ ነገር ግን ጠንካራ የኾኑ ሰዎች አንድ ላይ ተሰባስበዋል። ልምድ ያላቸው በርከት ያሉ መሪዎች በአንድነት ተቀምጠዋል። ከዚህ አኳያ መድረክ ቀድሞ ከነበሩት የተቃውሞ ስብስብ የተሻለ ይኾናል ብዬ እገምታለኹ። ይህም ሲባል መድረክ ስለመጣ ጠንካራ ውድድር እና ምርጫ ይኖራል ማለት አይደለም። ይህ በመድረክ ብቻ የሚወሰን አይደለም፤ በዋናነት በገዥው ፓርቲ የሚወሰን ይኾናል። ገዥው ፓርቲ የፖለቲካ ምኅዳሩን ከከፈተው ጊዜው እያጠረ እና እያለቀ ቢኾንም የተሻለ ነገር ሊኖር ይችላል።

መድረኩን በጋራ ያቋቋሙት ፓርቲዎች አብዛኞቹ አመራሮች ልምድ ያላቸው ናቸው ብለዋል። ነገር ግን ባለፉት 18 ዓመት በነበሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች መተባበር እና መፍረስ ዋነኛ ተሳታፊ የነበሩ ናቸው። ይህን እንደ ልምድ መውሰድ ይቻላል?

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ሰፈር መውደቅ እና መነሣት ብዙ ጊዜ ታይቷል፤ መተባበር መከፋፈልም ብዙ ታይቷል። ከዚህ ሂደት ትምህርት ሊወሰድ እንደሚችል ግን መገንዘብ አስፈላጊ ነው። በዚህ ሂደት ያለፉት ፖለቲከኞች ከስህተታቸውም ቢኾን የተማሩት ነገር ሊኖር እንደሚችል መገንዘብ ጥሩ ነው። ባለፉት 18 ዓመት በኢትዮጵያ ፖለቲካ የጮኸ፣ መፈክር ያነሣ ብዙ ሰው አለ። እንግዲህ “በዚህ 18 ዓመት ውስጥ የታዩ ፖለቲከኞች የታሉ? መጨረሻቸው ምን ኾነ?” ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። አሁን መድረኩ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች በዚህ 18 ዓመት የፖለቲካ ውጣ ውረድ አልፈውም ቢኾን በቦታቸው ላይ አሉ። አሁንም ቢሆን ተስፋ ሳይቆርጡ ጥርሳቸውን ነክሰው በገዢው ፓርቲ እየተዘለፉም ቢኾን በስፍራቸው አሉ። ይህ ትልቅ ዋጋ ሊሰጠው የሚገባ ይመስለኛል። አንዳንዶቹ ምሁራን ናቸው፤ በሞያቸው፣ በተማሩበት የሥራ መስክ እንደ ሌሎቹ ምሁራን ኑሯቸውን ሊገፉ የሚችሉ ናቸው። ይኹንና እንደ ሌሎች በቃኝ ብለው ዳር ሳይዙ፣ በሞያቸው እየሠሩ በሌላ በኩል ደግሞ በፖለቲካው ላይ አስተዋፅዖ እያደረጉ ያሉ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ስህተት (ድክመት) የለባቸውም ብዬ ስለ እነርሱ ለመከራከር፣ ጥብቅና ለመቆም አልፈልግም። በጉድለታቸው ሰው አይተቻቸው ለማለትም አይደለም። ነገር ግን በጎ ጎንንም መመልከቱ አስፈላጊ ይመስለኛል።

መድረኩ በብዙዎች ዘንድ በጥርጣሬ፣ በሌሎች ዘንድ እንደ አማራጭ በተስፋ የሚታይ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደኾነ ይታመናል። ይኹንና እስከ አሁን በመለስተኛ ፕሮግራሙም ይኹን በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በስሙ የጠራው ህዝባዊ ስብሰባ የለም። በዚህ ረገድ ምን ታስቧል?

የኢትዮጵያ ህዝብ ለውጥ ይፈልጋል፤ ለውጥም፣ አማራጭም እንደሚፈልግ በምርጫ 97 ታይቷል። ይኼም ኾኖ ግን እስከ አሁን ድረስ በነበረው ኹኔታ ብዙ የሚያረካ ውጤት አላየንም። ተቃዋሚዎች በአንድ በኩል ሲተባበሩ በሌላ በኩል ደግሞ ሲፈርሱ እና እርስ በርሳቸው ሲዘላለፉ፣ አንዱ በሌላው ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሲያካሄድ ነበር የሚታየው። በዚሁ ሂደት ምክንያት የለውጥ ተስፋው እየራቀ ሲሄድ ትብብር እና መድረክ ተፈጠረ ሲባል የሚፈጠርበትን ጥርጣሬ በአንድ ጊዜ ለመቅረፍ አይቻልም። ከእነጥርጣሬው፣ ከእነጥያቄዎቹ ተስፋ የሚሰጥ ነገር ሲያይ ደግሞ ተስፋ ማሳደሩ የሚጠበቅ ነገር ነው የሚመስለኝ። መድረክ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ረጅም ጊዜ ነው የወሰደበት፤ በመድረኩ አባል ፓርቲዎች ዘንድም መጣደፍ አልነበረም። ካለፈው ስሕተቶች በመማር የወሰደውን ያህል ጊዜ ይውሰድ ተብሎ ነው የተሞከረው። ምርጫው ወራት ሲቀሩት መድረክ ወደ መቀናጀት ደረጃ ሄዶ ሰነዶቹን ለምርጫ ቦርድ የዕውቅና ማመልከቻ አስገብቷል። እርሱ ቶሎ ቢገኝ መድረኩ በአንድ ድምፅ በአዲስ አበባም ይሁን ከአዲስ አበባ ውጭ እንደ መድረክ ይንቀሳቀሳል ብዬ እጠብቃለኹ። ግን አሁንም ቁልፉ ያለው በኢህአዴግ መንግሥት በምርጫ ቦርድ ነው። የኦፌዴን እና የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ ቅንጅት ለመመሥረት ማመልከቻ ያስገቡት ጥር አካባቢ ነው። እስከ አሁን ድረስ አልተሰጣቸውም። ምርጫ ቦርድ የመድረክን ጥያቄ በዚያ መልክ አያስተናግደውም ብዬ ተስፋ አደርጋለኹ።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጥያቄዎች ታሪክ ዋነኛ የኾኑትን የመሬት ይዞታ፣ የግል እና የቡድን መብት፣ የኢትዮጵያ አንድነት የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በተመለከተ የመድረኩ መለስተኛ ፕሮግራም ግልጽ እና መልክ የለየ እንዳልኾነ ተደርጎ ይተቻል። እነዚህን ተፃራሪ ፍላጎቶች እንዴት ያስተናግደዋል?

ግንዛቤን እና እውነታን ለያይቶ ማየት ጥሩ ነው። አንዳንዶች እነዚህ ጥያቄዎች ተፃራሪዎች ናቸው ይላሉ። ይኹንና እውን ተፃራሪዎች ናቸው ወይ ብሎ የምር ጥያቄ ማንሣት ጥሩ ይመስለኛል። በእኔ እምነት የብሔር ብሔረሰብ መብትን ማስከበር እና የኢትዮጵያ አንድነትን ማስከበር ተፃራሪዎች አይደሉም። አብሮ ኗሪ ናቸው። ነገር ግን የብሔር ብሔረሰብ መብት መከበር አገሪቱን ዴሞክራሲያዊ በማድረግ አስተሳሰብ ከተያዘ ኢትዮጵያን ዴሞክራቲክ የማድረግ መሣሪያ ሊኾን ይችላል። የብሔርን መብት ከኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ነጥሎ የሚያዩ ኃይሎች ቢኖሩም መድረክ ይህን ተሻግሯል። በውስጣችን ያለው ችግር ዴሞክራሲን በማስፋት እንጂ በመገንጠል መፈታት የለበትም የሚል እምነት አለን። ስለዚህ በውስጣችን ልዩነቶች ቢኖሩም ዴሞክራሲን በማስፋት እንፈታዋለን። የመሬትን ጉዳይ ብንመለከተው፤ ኢህአዴግ “መሬት የመንግሥት ነው” ይላል። ከዚህ ውጭ አማራጭ ይምጣ ከተባለ “በመቃብሬ ላይ” ነው የሚለው። ነገር ግን “መሬት የመንግሥት ነው” ማለት በኢህአዴግ አገዛዝ መሬት የኢህአዴግ፣ መሬት የካድሬ ነው ማለት እየኾነ ነው ያለው። “መሬት የህዝብ ነው” ማለት እንዳልኾነ በተግባር እየታየ ነው ያለው። መሬት የአገር አለመኾኑ እየታየ ነው። በርካታ ዜጎች በአንድ ቀላጤ የሚፈናቀሉበት ሥርዓት እየተፈጠረ ነው ያለው። በአንጻሩ መድረክ ሦስት አይነት የመሬት ይዞታዎች እንደሚኖሩ አስቀምጧል። በዘመናዊ እርሻ ሊሰማሩ ለሚችሉ ባለሀብቶች የሚሰጥ መሬት በመንግሥት እጅ ይኾናል። በኅብረተሰቡ የሚቆይ መሬት ይኖራል። ይህ ደግሞ ኅብረተሰቡ እንደ ሀብቱ የሚንከባከበው በተስማማበት መንገድ ጥቅም ላይ የሚያውለው ይኾናል። ሌላው እና ትልቁ ደግሞ መሬት የአርሶ አደሩ የግሉ ይኾናል። እስከዚህ ድረስ በመሬት ላይ ስምምነት አለ። እዚህ ላይ መሬት ይሸጥ ይለወጥ ቢባል የሚያሳድረው ስጋት አለ፤ ሊያመጣ የሚችለው ጥቅምም አለ። ስለዚህ ይህን ስጋት በሚቀርፍ መልኩ ካልተሄደበት አደጋ ስላለው ለወደፊቱ በውይይት እንዴት አድርገን እንፈታዋለን በሚል ለውይይት ክፍት የተደረገበት ኹኔታ ነው ያለው። እስከዚህ ድረስ ግን መቀራረብ መቻሉ ትልቅ ለውጥ መኾኑ ግንዛቤ ሊያገኝ የሚገባው ይመስለኛል።

ኢህአዴግ መድረኩን ለድርድር መጋበዙ ይታወቃል። የድርድር ግብዣው የቀረበው ለምን ይመስሎታል?

ኢህአዴግ መስቀለኛ መንገድ ላይ የቆመ ፓርቲ ነው። በዴሞክራሲ፣ በነፃነት እና በህዝብ ምርጫ ላይ የተመሠረተ መስተዳደር ማቆም ተስኖታል። ነፃነትና ነፃ ምርጫ እንደ ጦር የሚፈራበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ነፃ ምርጫ አቅጣጫ እና አሠራር ቢመቻች፣ ህዝቡ በነፃነት እንዲመርጥ ዕድል ካገኘ ሊመጣ በሚችለው ውጤት ላይ ርግጥኛ አይደለም። ይህ አንዱ የኢህአዴግ ችግር ነው። በሌላ በኩል ኢህአዴግ አገዛዙን ለመቀጠል ቢፈልግም ያለምርጫ፣ ያለተቃዋሚዎች ትርጉም ያለው ተሳትፎ የህዝብ ይኹንታ አግኝቻለኹ ብሎ ሥልጣን ላይ ለመቆየት ቢፈልግ አንደኛ፦ በእኔ እምነት የአገሪቱ ችግር ምርጫ 97 ከፈጠረው ቀውስ በላይ የከፋ ነገር ያስከትላል የሚል እምነት አለኝ። ሁለተኛ እና ለኢህአዴግ ዋና የኾነው ምክንያት ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው መንግሥት ኾኖ ለመቀጠል ይቸገራል። ስለዚህ በዓለም አቀፍ መንግሥታት እና ተቋማት ተቀባይነት ያለው ዕርዳታ እና ድጋፍ የሚቸረው፣ ዕውቅና የተሰጠው መንግሥት ይኾን ዘንድ ተቃዋሚዎች በተሳተፉበት ምርጫ አሸንፎ ሥልጣን የቀጠለ ፓርቲ እንደኾነ ማረጋገጥ ይፈልጋል። በእነዚህ ሁለት ስጋቶች መካከል ነው ያለው። ነፃ ምርጫ ቢያካሂድ ሊመጣ የሚችለው ጣጣ ያሳስበዋል። ምርጫውን አፍኖ በሚያዝያ 2000 ዓ.ም. እንደተደረገው ብቻውን ተወዳድሮ አሸነፍኹ ቢል ደግሞ በዓለም መንግሥታት እና ተቋማት ዘንድ ተቀባይነት አያገኝም። የእነርሱን ድጋፍ ካላገኘ ደግሞ ዕርዳታ እና ገንዘብ አያገኝም። ከውጭ የሚመጣው ዕርዳታ ደግሞ ለኢህአዴግ የሞት እና የሕይወት ጥያቄ ነው። ኢህአዴግ በዚህ መካከል ነው ያለው። ስለሆነም ተቃዋሚዎች እንዲሳተፉ ይፈልጋል። በሌላ በኩል ደግሞ ተቃዋሚዎች ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ነፃ የፖለቲካ ኹኔታ እንዲኖር አይፈቅድም። በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ በመኾኑ ተቃዋሚዎቹን “ኑ፣ እንደራደር” አላቸው። እንደራደር ያለው ግን በአንድ ነጥብ ብቻ ነው - በፖለቲካ ፓርቲዎች ሥነምግባር ደንብ። ኢትዮጵያ ውስጥ ነፃ እና ተዓማኒ ምርጫ እንዲኖር ከተፈለገ ድርድር እና ምክክር የሚጠይቀው ይህ አይነቱ አጀንዳ ብቻ አይደለም። ከእርሱ ሌላ በርካታ አጀንዳዎች አሉ፤ እነርሱም መታየት አለባቸው።

መድረኩ ከድርድሩ ወጥቷል፤ ነገር ግን ተመልሶ እንዲገባ የኢትዮጵያ ወዳጆች የሚባሉ የለጋሽ ሀገራት አምባሳደሮች ከፍተኛ ጫና እንዳሳደሩበት ይነገራል። ይሄ ጫና የተፈጠረው ለምን ይመስሎታል?

የሁሉም ምክንያት አንድ ነው ለማለት አይቻልም። አውሮፓ ሕብረት ቢባልም ሕብረቱ በርካታ አባል አገሮች ያሉት ሕብረት ነው። የሁሉም ስሌት አንድ ነው ማለት አይቻልም። የ2002 ዓ.ም. ምርጫ እንደ ሚያዝያው 2000 ዓ.ም. የአካባቢ ምርጫ ኾኖ ከታለፈ የሚቀጥለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኹኔታ ጥሩ አይኾንም የሚል ስጋት አላቸው። በተወሰነ ደረጃም ቢኾን ያሉትን ውጥረቶች በማርገብ አስተዋፅዖ እንዲኖረው የ2002 ምርጫ ለቀቅ ቢል ስሜቶችን ለማርገብ ይረዳል። ወደ አስቸጋሪ ፖለቲካዊ ቀውስ እንዳይሄድ የሚል ስጋት ያላቸው ይመስለኛል። ይህን መንግሥት እና ሥርዓት በደንብ የሚያውቁት ይመስለኛል። እነርሱስ ቢኾኑ ነፃ ምርጫ በሌለበት ኹኔታ ኢህአዴግ 99 በመቶ አሸንፌያለሁ ቢላቸው እንዴት ሊዋጥላቸው ይችላል? በየአገሩ ያለው መራጭም ይህን ሲሰማ እንዴት እንዲህ ካለው አገዛዝ ጋራ ተሻርካችሁ ትሄዳላችሁ ብሎ ጥያቄ ሊያነሣባቸው ይችላል። ስለሆነም ለእኛም ለራሳቸውም አስበው ሊሆን ይችላል።

ጠ/ሚ መለስ መድረኩ በድርድሩ አካሄድ ላይ ያቀረበውን አቋም በይዘቱ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ እንደኾነ በመግለጽ ከደርግ ጋራ አመሳስለውታል። ይህን ምስስላቸውን እንዴት ያዩታል?

ስለ ደርግ ማንሣቱ ጠቃሚ አልነበረም። ነገር ግን ለማላስተላለፍ የተፈለገው መልዕክት ተቃዋሚዎች ኢሠፓ እና ደርግ ናቸው። እነ ገብሩም እነ ስዬም ከእነርሱ ጋራ እኛን ለማፍረስ እየሠሩ ናቸው ብሎ የኢህአዴግ አባላትን ለመቀስቀስ ተሸንቁሮ የገባ አባባል አድርጌ ነው የማየው። ደርግ ወድቆ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት በሥር ሕጎች እየደፈቀ ህዝብን በማፈን እና በማስፈራራት ሥልጣን ላይ ለ40 እና ለ30 ዓመት እቀጥላለኹ እያለ ያለው ኢህአዴግ ነው። በሥልጣን ላይ ያለውም ኢህአዴግ ነው። በእነዚህ ምክንያቶች ለኢሠፓ እና ደርግ የበለጠ የሚቀርበው ኢህአዴግ እንጂ ተቃዋሚዎች አይደሉም።

መድረኩ መስከረም 30 ቀን 2002 ዓ.ም. ስላደረገው ጥምረት የሚዘግብ ዜና በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ተላልፏል። ይህ ዜና ሲቀርብ “ከዐፄ ኃይለሥላሴ ጀምሮ በነበሩት ጨቋኝ ሥርዓቶች የነበሩት አምባገነን ገዢዎች ...” የሚል ይዘት ያለው የመድረከ መግለጫ ሲነበብ፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የፕሬዝዳንትነት ቃለ መሃላ ሰፈጽሙ፣ አቶ ገብሩ ዐሥራት የትግራይ ምክር ቤትን በፕሬዝዳንትነት ሲመሩ፣ እርስዎም በፓርላማ ውስጥ ተቀምጠው የሚያሳየው ምስል ከማኅደር ወጥቶ ሲታይ ምን ስሜት አሳደረብዎት?

በመሠረቱ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በህዝብ ሃብት የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው። ጋዜጠኞችም ከህዝብ በሚሰበሰብ ግብር ደሞዝ ተከፋይ ናቸው። የመድረኩን ጉባዔ ሲዘግቡ ዘገባቸው ገለልተኛ መኾን ይገባው ነበር። በዚህ የቴለቭዥን ስርጭት የታየው ግን ዘገባው ከኢህአዴግ ቅስቀሳ ጋራ አያይዘው ለማቅረብ መጨነቃቸውን ነው የሚያመለክተው። ይሄ ሊታረም የሚገባው ስህተት ይመስለኛል። መስከረም 30 ቀን የነበረውን የመድረኩን ውሎ ዘገብን እያሉ በመድረኩ ያለነውን የኢህአዴግ አመራር የነበርን ሰዎች ቀድሞ በኢህአዴግ ላይ የነበረንን ተሳትፎ ብቅ ጥልቅ እያደረጉ ማሳየታቸው ለማለት የፈለጉት ነገር ምን እንደሆነ ይገባናል። ሌላ ጊዜ ድርጅት መርተው ለድል ያበቁት እነሱና እነሱ ብቻ እንደሆኑ፣ የጦር መሪዎች፣ የድርጅቱ የፖለቲካ መሪዎች፣ የዲፕሎማሲው መሪዎች እነሱና እነሱ ብቻ እንደሆኑ ሌሎቻችን እንዳልነበርን አድርገው ሲዘግቡ ይታያል። አሁን ደግሞ ሌላ የፖለቲካ ሥራ ላይ ስንሳተፍና ስንተዋቸው እናንተስ አልነበራችሁበትም ወይ የሚል መልዕክት ያለው ምስል በቴለቭዥን ሲያሳዩ ይታያል። እኛ የኢህአዴግ ከፍተኛ መሪዎች እንደነበርን የሚታወቅ ነው። እኔ የህወሓት መስራች ነኝ። የህወሓት ሠራዊትም መሪ የነበርኩ ሰው ነኝ። ህወሓት እና ኢህአዴግ ባደረጉት በጎ አስተዋፅዖ እኮራለሁ። ግን ደግሞ ህወሓት እና ኢህአዴግ ስህተት መስራታቸውን እገነዘባለሁ። በእነዚህ ስህተቶች አዝናለሁ፤ ተምሬአለሁም። አሁን በእኛ እና በእነሱ መካከል ያለው ልዩነት፤ እነርሱ ሥልጣን እና ከሥልጣን የሚገኘውን ቁሳዊ ጥቅም አለቅ ብለው ህዝብን ረግጠው ለ30 እና 40 ዓመታት እንገዛለን እያሉ ነው። እኛ ግን አይደለም ዱሮ እኮ የታገልነው ለዚህ አልነበረምዱሮ እኮ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ፈንጂ እየረገጡ ወደ ምሽግ እንዲገቡ የጠየቅናቸው እና ቃል የገባንላቸው ለዚህ አልነበረም። ለዲሞክራሲ፣ ለህዝባዊ ሥልጣን፣ ለእኩልነት፣ ለነፃነት፣ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እንጂ ለዚህ አልነበረም ብለን ካለፈው ስህተታችን በመማር ካለፈው በጎ ልምዳችንና አስተዋፆአችንም በመማር ይህንንም በመቀመር አዲስ መንገድ፣ አዲስ አካሄድ፣ አዲስ ጎዳና ለማሳየት እና ለመጀመር ጥረት እያደረግን ነው። በዚህ ደግሞ የምንደሰት እንጂ የምናዝን እንዳልሆንን ሊገባቸው ይገባል። አሁን እኔ፣ አቶ ገብሩም ይሁን ዶ/ር ነጋሶ በምንሰራው ሥራ ህሊናችን የተረጋጋና የረካ መሆኑን ሊያውቁ ይገባል። እኛ የራሳችንን ቁሳዊ ሕይወት እና ሥልጣን ችላ ብለን ለአገር ጥቅም ይበጃል ያልነውን አዲስ አቅጣጫ እያመለከት ያለን ሰዎች ነን። ይሄ ስላሰጋቸው ነው በቴሌቭዥን ብልጭ ድርግም እያደረጉና ወደኋላ እየተመለከቱ ያሉት። እኛ ግን ወደፊት ነው እየተመለከትን ያለነው። ብዙ አዳዲስ አቅጣጫዎች ይዘን ወደ ፖለቲካው እንደመጣንም ሊያውቁ ይገባል።

የኢህአዴግ መተካካት ያስፈለገው፤ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ተግባራዊ ከማድረግ መርሕ ነው። “አመራሩ የህዝብ አመኔታን ሳያጣ ከእነ አቅሙ እንዲቆይ ከማድረግ ነው” የሚለውን የኢህአዴግ አስተሳሰብ እንዴት ያዩታል?

አመራሩ የህዝብ አመኔታ አላጣም ማለት ነው? እና እንዳያጣ ነው እየተጨነቁት ያለው? አመኔታ ላለማጣቱስ ምን ማስረጃ አላቸው? ሚያዝያ 2000 ላይ 99 በመቶ ስለ መረጣቸው? ይህ ነው ማስረጃቸው። እኔ ይህ መተካካት በስሌታቸው ያልነበረ ድንገተኛ ነገር አድርጌ ነው የማየው። ሊቀመንበሩ አዲስ ስትራቴጂ፣ አዲስ ፖሊሲ፣ ተኀድሶ ይል በነበረበት ጊዜ ኢህአዴግ ለ30 እና 40 ዓመት በሥልጣን የሚቆይበትን ስሌት የሚያሰላ ነበር የሚመስው። ይህ ተኀድሶ ሲታወጅ “ሥልጣን እለቃለኹ፤ በቃኝ” የሚባለው ነገር በሒሳብ ውስጥ ስለ መኖሩ እጠራጠራለኹ። “ይህ እለቃለሁ በቃኝ” የሚባለው ነገር እንዴት በድንገት መጣ የሚለውን እነርሱ ራሳቸው ናቸው የሚያውቁት። አሁን እለቃለኹ ሲል በትጥቅ ትግል የነበራችሁ ልቀቁ የሚል ነገር እንዴት ሊመጣ እንደቻለ አይገባኝም። ብቃቱ፣ ጉልበቱ፣ ጤንነቱ የሌለው በሂደቱ ላይ ተስፋ የቆረጠ ሊለቅ ይችላል። በትጥቅ ትግሉ ላይ የነበረው ሁሉ ይልቀቅ ብሎ ነገር ምን አይነት አነጋገር እንደኾነ ሊገባኝ አልቻለም። እኔ ከለቀቅኹ አይቀር ሥርዓት እና መልክ እናስይዘው፤ ወግ ያለው እናስመስለው ተብሎ በኋላ የመጣ ነገር ነው የሚመስለው።

ድንገት ከተፍ ያለን ነገር እንደ አንድ ታሪካዊ ዕቅድ እና ታላቅ ኹኔታ ድራማዊ ማድረግ ፋይዳው አይታየኝም። ለኢትዮጵያ ትልቁ ፋይዳ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ኖሮ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ተካሂዶ ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር አለ ወይስ የለም ነው። ይህን ለማየት አይፈልጉም። ሥልጣን ከእጃቸው እንዳይወጣ አድርገው ሁሉንም በሮች ለመዝጋት እንደ ቆረጡ “አዲስ ራዕይ” በተባለው መጽሔት የጻፉት ነገር በግልጽ ያመለክታል። በምንም መንገድ ሥልጣን ሊለቁበት የሚችሉበት ዕድል በማይኖርበት ኹኔታ በቀጣይነት ለ30 እና ለ40 ዓመት በሥልጣን ላይ ለመቆየት የቆረጡ መኾናቸውን ጹሑፋቸው በግልጽ ያሳያል። ይለቃሉ የሚባሉት ሰዎችም በፓርቲው ውስጥ ጫናቸው እንደሚቀጥል በግልጽ ያመለክታል። ለዚያም ተብሎ “አልጋ ወራሽ” የሚሏቸውን ሥልጣን ላይ አስቀምጠው፣ በፓርቲው እና በመንግሥት የሚኖራቸውን ጫና ጠብቀው ግን ደግሞ ከሥልጣን ጋራ የሚኖሩበትን ኹኔታ አመቻችተዋል። ሥልጣን የሚለቁ ባለሥልጣናት ስለሚያገኙት ጥቅማጥቅም በጥድፊያ ዐዋጅ መውጣቱ የሚታወስ ነው።

በአንጻሩ “የባለሥልጣናት ሀብት እና ገቢ ከነምንጩ እንዲመዘገብ ይደረጋል” የሚል ዐዋጅ ከወጣ ዘጠኝ ዓመት አልፎታል። የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሲቋቋም አንዱ ሥራው ይህ ነበር። ይህ ተግባራዊ ሳይኾን እስከ አሁን ቆይቷል። የባለሥልጣናቱ የሀብት ምንጭ እስከ አሁን በማይታወቅበት ኹኔታ ኑሯቸውን በተደላደለ መልኩ እንዲቀጥሉ በማለት ልዩ ጥቅም የሚሰጥ ዐዋጅ በጥድፊያ ፀድቋል። ስለዚህ ኢህአዴግን እንደምንም ብሎ ሥልጣን ላይ በማቆየት ቁርጠኞች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ስለ ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር የማይጨነቁ እንደኾኑ ግልጽ ማሳያው ደግሞ ይኸው ነው። ይህ ባልኾነበት ኹኔታ አንዱን በሌላ “አልጋ ወራሽ” እንተካለን ቢሉ ለእኔ ምንም ፋይዳ የለውም።

መድረኩ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበርን እስር እንደ አንድ ጉዳይ በቀጣይነት እንደሚመለከተው አስታውቋል። ይህ አካሄድ የወ/ሪት ብርቱኳን ጉዳይ የፓርቲው ጉዳይ ኾኖ መታሰቡን አያሣሣውም? በእርስዎ በኩል ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በምን መልኩ ከእስር ሊለቀቁ ይችላሉ ብለው ያስባሉ?

ወ/ሪት ብርቱካን በዚህ አገር በተቃዋሚዎች ላይ ለሚደርሰው ግፍ ማሳያ ተምሳሌት ናት። ስለኾነም እርሷን ለማስፈታት የሚደረገው ትግል ሌሎችንም ለማስፋታት ያለመ መኾን አለበት። ተነጣጥለው የሚታዩ ነገሮች አይደሉም። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተቻለው ሁሉ እርሷን ለማስፈታት ጥረት ማድረግ አለበት። ስለ እርሷና ስለ ሌሎች ወገኖቻችን መታሰር ከኢህአዴግ እና ከመንግሥት ጋራ በሚደረግ ድርድር ጉዳዩ መነሣት ይገባዋል። ተቃዋሚዎች በሚያደርጉት ቅስቀሳ እንደ አንድ ህዝብን የመቀስቀሻ ጥያቄ መነሣት ይኖርበታል። ከዴሞክራሲ ጋራ በተያያዘ እንደ አንድ የምርጫ አጀንዳ መነሣት አለበት። በዚህም “ብርቱካን ትፈታ” የሚለው ድምጽ ጉልበት፣ መሰባሰብ እና ጥንካሬ እያገኘ ይሄዳል፤ ተጨማሪ ጫናም ፈጣሪ ይኾናል፤ ወሳኙ ኃይልም የሚመስለኝ ይህ ነው። ተቃዋሚዎች ኹኔታው ተመቻችቶ ወደ ምርጫ ሲገቡ፣ የሕግ ሉዓላዊነት ጉዳይ፣ የፖለቲካ እስረኞች እና የወ/ሪት ብርቱካን መፈታት ጉዳይ እንደ አንድ ትልቅ ፖለቲካዊ አጀንዳ በሁሉም ቦታ ሲንቀሳቀሱበት እና ስለ ብርቱካን በየቀበሌው ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ዐውቆ ስለ መፈታቷ እንዲጠይቅ ለማድረግ ከተቻለ ትልቁ ጫና ያኔ ይፈጠራል። ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ተካሂዶ ፓርላማው ሲቆም፤ ጠንካራ ድምፅ አግኝቶ “ብርቱካን ትፈታ፤ ፖለቲካዊ እስረኞች ይፈቱ” የሚለው ትግል ሲጨመርበት የበለጠ ድምፅ ያገኛል። ስለዚህ ሁሉም የትግል መልኮች በተቀነባበረ መልኩ በተጓዳኝ ሲሄዱ፣ በእያንዳንዱ በኩል ትልቅ ርምጃ እና ስኬት ሲኖር ወ/ሪት ብርቱካን ትፈታለች። መድረክም ይህን ጉዳይ እስከ መጨረሻው እንደሚገፋበት መናገር እችላለኹ።

የመጨረሻ ጥያቄ ላንሳሎት፤ መጽሐፍ ለመጻፍ አላሰቡም?

እጽፋለኹ። ለመጪው ትውልድ እና ለመጪው ኢትዮጵያውያን ወታደሮች መተላለፍ አለበት የምለው ብዙ ነገር አለ። ይህንን ዕድሜ እና ጤና ከሰጠኝ በወቅት እና በአይነት ከፋፍዬ ልዘግበው እፈልጋለኹ። አንድ ብቻ ሳይኾን በርካታ መጽሐፍት እጽፋለኹ ብዬ ተስፋ አደርጋለኹ። በአኹኑ ወቅት አንድ መጽሐፍ ጽፌያለኹ። አቅሙ ከተገኘ በቅርብ ይወጣል።

Source:Ethiopiazare

Post Reply

Return to “Ethio Politics .... ኢትዮ ፖለቲካ”