“ጠላፊው” ሀሳብ ወለድ ጨዋታ – አቤ ቶኪቻው

ፖለቲካ ፣ ወቅታዊ ጉዳዮች
Politics , Current affairs
User avatar
zeru
Leader
Leader
Posts: 952
Joined: 19 Aug 2009 17:01
Contact:

“ጠላፊው” ሀሳብ ወለድ ጨዋታ – አቤ ቶኪቻው

Unread postby zeru » 11 Jan 2012 10:52

አቤ ቶኪቻው
abeto2007@yahoo.com
ወዳጄ … እንዴት ሰነበቱልኝ!?
ዛሬ አንድ እንግዳ ይዤ መጥቻለሁ። እንግዳዬ ለበርካታ ግዜያት በጠላፊነት ሙያ ሀገሩን እና መንግስቱን ይበልጡንም ደግሞ እናት ድርጅቱን አገልግሏል። በስራው የሚኮራ ታታሪ

አቤ ቶኪቻው
ጠላፊ ነው። ቀጥሎ በራሱ አንደበት ያወጋችሁ ዘንድ እኔ እንደሚከተለው ገለል እላለሁ።
እንተዋወቅ… ስሜን ለግዜው ዝለሉት። የስራ መደቤ ጠላፊ ነው። በሀገሬ የደህንነት መስሪያ ቤት የጠለፋ ስራ ዋና የስራ ሂደት ባለቤት ነኝ። ለነገሩ በርካታ አለቆች ከበላዬ ስላሉ፤ ዋና የስራ ሂደት ባለቤትነቱን ለነርሱ ትቼ እኔ የስራ ሂደት ውሽማ ነኝ። ብል ይሻላል።
በነገራችን ላይ ጠላፊነት የተከበረ ሞያ ነው። እኔ ደግሞ በሙያው ከመሰልጠኔም በፊት ታላቅ ልምድን ያከበትኩኝ በመሆኔ፤ የምሰራውም በታላቅ የስራ ፍቅር እና ተነሳሽነት ነው።
አስታውሳለሁ፤ መስሪያ ቤቱ ለስራ መደቡ ማስታወቂያ ሲያወጣ እንድመዘገብ የነገሩኝ ጓደኞቼ እውነት ስራውን አልፎ ለእንዲህ ያለ ወግ ይበቃል ብለው ሳይሆን ሊያፌዙብኝ ፈልገው ነበር። “የደህንነት መስሪያ ቤት ጠላፊ ይፈልጋል አንተ ደግሞ በቂ የስራ ልምድ እና ክህሎት ስላለህ ብትመዘገብ መልካም ነው…” ብለውኝ ሲያበቁ፣ የሳቁብኝ አሳሳቅ አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ለአመት በዓል ብቻ የሚስቀው አይነት ሳቅ ነበር። ይሳቁ። እኔ ግን ሄጄ ለመቀጠር አመለከትኩ። የስራ ልምድ ተብዬ ስጠየቅም ከአሁን በፊት ሁለት ሚስቶች በጠለፋ አግብቼ እንደማውቅ ነገርኳቸው። በርግጥ አሁን ሁለቱም አብረውኝ አይኖሩም። ነገር ግን የተሳካ ጠለፋ ነበር ያካሄድኩት። ስል በኩራት ተናገርኩ። ቀጣሪዎቼም የደስታ ይሁን የአግርሞት ያለየለት ፈገግታ ለገሱኝ። ደስም አለኝ። በእውኑ ለአንድ ተቀጣሪ ከደሞዙ ቀጥሎ የሚስደስተው ነገር የቀጣሪዎቹ ፈገግታ አይደለምን? ስልም አሰብኩ።
ስራ ጀመርኩ። እሰይ በሉልኝ። እልልታም ያንሳል። ያ መውደቂያው የት ይሆን? የተባለ ሰው፤ ያ በጓደኞቹ ዘንድ ባላገር የተባለ ወጣት፤ “እኔ” ስራ ጀመርኩ። እናም ደስ ይበላችሁ። ከእንግዲህ ሚስት ጠለፋ አግባብ አለመሆኑን አምኜ ሂሴን ውጫለሁ። ከዚህ በኋላ የምጠልፈው ለመንግስቴ የሚጠቅመውን እንጂ ለአንድ እኔ ስጋዊ ፍላጎት አይደለም።
እጠልፋለሁ። ለመንግስቴ የማይመች “ኮረኮንች” ፖለቲካን የሚያራምዱ ግለሰቦችን እጠልፋለሁ። ጠልፌም ወደ አንድ ሰዋራ ስፍራ ካደረስኩ በኋላ እኔ፤ ተጠላፊው እና አምላካችን ብቻ ባለንበት ቦታ “ዋ …!” ስል አስጠነቅቃለሁ። “ዋ… ብላለች አሞራ!” ብዬ መልክት አስተላልፋለሁ። (አሞራ የተባለው መንግስቴ መሆኑን ተጠላፊዎቼ እንዲረዱም መንግስት የሰጠኝን “ደህንነት” የሚል “ሃርድ መስጫ” መታወቂያ አሳያለሁ። ከወደ ጎኔም አንዳች አበጥ ያለ ነገር መኖሩን እንዲያዩ ጃኬቴን ገለጥ አደርጋለሁ።) እሰይ የኔ አንበሳ አትሉኝም እንዴ!?
እጠልፋለሁ። በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብሰባ ላይ እየተገኘሁ የስብሰባውን ሃሳብ እጠልፋለሁ። ጠልፌም ስብሰባው በተጠለፈለት ቦይ መፍሰሱን ርግጠኛ ካልሆንኩ “ወይ ፍንክች የአባ ክላሽ ልጅ!” ከስብሰባው አልወጣም። አስፈላጊ ሲሆንም አንድ ጋንታ ሙሉ ተባባሪ ጠላፊዎችን ያግዙኝ ዘንድ እጠራለሁ። ከዛም በስብሰባው አጀንዳ ያልነበረ ጥያቄ እጠይቃለሁ። ተተቃውሞን በስልት አወግዛለሁ። “የዚህ የዚህማ ያለው መንግስት ምን አለኝ…?” ስል በየተቃውሞው ስብሰባ እጠይቃለሁ። ከዛም ያላለቀውን ቀለበት መንገድ፣ ያልታሰበውን አምባር መንገድ፣ የተሸለመውን አርሶ አደር፣ ያልተሸለመውን ጠግቦ አደር፣ ጥቃቅን እና አነስተኛ ነጋዴዎችን፣ የብሄር ብሄረሰቦችን ሙዚቃ እያነሳሁ ይሄን ሁሉ ያመጣልን መንግስት የተባረከ ይሁን እላለሁ። ይሄኔ በአጋርነት የማመጣዋቸው ጋንታ ጠላፊዎችም ያጨበጭባሉ። በዚህ ግዜም በርካታ ተጠላፊ ተቃዋሚዎችም አብረውን ያጨበጭባሉ። የተሳካ ጠለፋ አይሉኝም!?
ምርጥ የጠለፋ ባለሞያ ነኝ። ለምሳሌ ሰሞኑን ኦነግ የመገንጠል ሃሳቡን ትቶ “ኢትዮጵያ ውስጥ ኦሮሚያ አለች ኦሮሚያ ውስጥ ደግሞ እኔ አለሁ። አንዳችን ያለ ሌላችን ብንሆን ብርታት ከኛ ይርቃል፤ እናም ከሁሉ ጋር በማበር ለሁሉም እታገላለሁ።” ብሎ ተናግሮ፤ በአለቆቼ ዘንድ ታላቅ መደናገጥ ሆኖ ነበር። እንደ እድል ሆኖ ታድያ አንዱ የኦነግ ክንፍ በሃሳቡ አልተስማማሁም አለ። እኔም “ኡፈይ…!” አልኩ ይህ ጉዳይም ለውይይት ይቀርብ ጀመር። ይሄኔ የጠለፋ ስራ ዛር የሚቆምበት ግዜ ነው። የአዝመራ ወቅት ብለው ይሻላል እንጂ… እንደ “ፓልቶክ” በመሰሉ የተለያዩ የውይይት ቦታዎች እኔ ታታሪው ጠላፊ እገኛለሁ። ተገኝቼም “ኦነግ ካልተገነጠለ ሞቼ እገኛለሁ። ዋናው ችግራችን አምባገነኑ መንግስት ሳይሆን እናንተ ናችሁ…!” ብዬ አብረን እንታገል እንተጋገዝ የሚሉትን “በጥቀመኝነት” እና በጠላትነት እወቅሳለሁ። ለዚህም የሚጠቀስ ታሪክ ካገኘሁ ታሪክ ለመጥቀስ እሞክራለሁ። የሚጠቀስ ታሪክ ከጠፋ ከጓደኞቼ ጋር እየተጠቃቀስኩ የጠለፋ ሃሳቤን በውይይቱ ውስጥ አጣፍጪ አቀርባለሁ። ብዙ ግዜ ጠለፋዬ የተሳካ ነው። ብዙዎች ተከትለውኝ አዎ “ወተታችንን ልትጠጡ? ወርቃችንን ልትወስዱ? ገብሳችን ለታፍሱ…? ወዘታችንን ልትወዝቱ…?” እያሉ እንተባበር የሚሉትን እንዲሰድቡ አድርጊያለሁ። በዚህም ድንጋጤ የተማቸው አለቆቼ ፈገግታቸው ተመልሷል። እኔም ከደሞዜ እኩል የአለቆቼ ፈገግታ የሚያስደስተኝ ታታሪ ነኝና! ደስ ብሎኛል።
በጠለፋ ስራ ከተሰማራሁ ግዜ ጀምሮ እንደ ስልክ ጠለፋ የሚያስደስተኝ የለም። እንደውም አንዳንድ ግዜ ከደስታዬ ብዛት “ከሚስት ጠለፋ አንስተህ ስልክ ጠላፊ ያደረግሀኝ እኔ ማነኝ!?” እያልኩ ለመንግሰቴ ዘምር ዘምር ይለኛል። በአንድ ወቅትም እንዲህ ሆነ…
መንግስታችን ሽብርተኝነትን ለመከላከል ብሎ የእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ስልክ እንዲጠለፍ ገበናውም እናዳምጥ ዘንድ በአዋጅ ፈቀደልን። አንዳንዶችም “አስደናቂ የሆነ መንግስት ለእኛ “ገመና” ድራማ በቴሌቪዥን ያሳየናል፤ ለራሱ ደግሞ የእኛን ገመና ይኮመኩማል።” ሲሉ መተቸት ጀመሩ። እኛም “ከንግዲህ በኢትዮጵያ ምድር ከእግዜር እና ከደህንነት የሚደበቅ ነገር የለም!” ስንል ፈከርን። አዎ… ግዜው የጠለፋ ነው። እናቶቻችን በአነስተኛ እና ጥቃቅን ድርጅቶች ታቅፈው ጥልፍ ሲጠልፉ የሚውሉትን ያህል መንግስታችን ደግሞ በአነስተኛና ጥቃቅን ጥርጣሬ ታቅፎ የእያንዳዱን ወጣት፣ ሽማግሌ ስልክ እንዲጠለፍ አዟል። እኛም በጠለፋው እየተጋን እንገኛለን።
ባለፈው ግዜ በርካቶች በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ነበር። አሁንም ብዙዎች አየተጠረጠሩ ይገኟሉ። ታድያ ከተጠርጣሪዎች መካከል የሆነ አንድ ወጣት የስልክ ውሎውን በሙሉ እንድጠልፍ እኔ ጎበዙ፣ እኔ ታታሪው፣ እኔ በተለያዩ ጠለፋዎች ልምድ ያለኝ… እኔ! እንድጠልፈው ሃላፊነት ተሰጠኝ።
የወጣቱን የስልክ ውሎ ጠልፌ ሳበቃ ለአለቃዬ በየግዜው ሪፖርት ማቅረብ የስራዬ አካል ነው።
ተጀመረ!
ጎረመምሳዬ ስልክ በደወለ ቁጥር ብቻውን የሚያወራ ቢመስለውም ቅሉ እኔ ግን አጠገቡ አለሁ። እናንተዬ ወጣቱ ተበላሽቶ የለም እንዴ? በቀን ውስጥ ስንቷን ሴት “የኔ ቆንጆ!” እንደሚል… ቢሰሙት ሀገር ሁሉ የእርሱ ቆንጆ ነውን? ሲሉ ይጠይቃሉ። በቀን ውስጥ ስንቷን ሴት “ራት ካልጋበዝኩሽ” እንደሚል ቢሰሙት በአንድ ቀን ውስጥ ስንት ምሽት አለ? ብለው ይደነቃሉ። አንዷ ጋ ሲደውል… “ውይ ዛሬ ባለቤቴ ከፊልድ ይመጣል አልችልም?” ስትለው ከመቅስበት ሌላዋ ጋር ደግሞ ይደውልና “የኔ ቆንጆ ዛሬ ራት ለምን አብረን አንበላም?” ይላታል። ወይ ጉድ የሚደንቅ እኮ ነው! ይሄ የእኛ ድርጅት አባል ቢሆን ኖሮ ስንት ግዜ “በግለኝነት” እና “በኪራይ ሰብሳቢነት” ይገመገም ነበር? ስል አስበኩለት። ቢቸግረኝ ይህ ወጣት ለደወለላት በሙሉ “የኔ ቆንጆ!” ከማለት እና “ዛሬ እራት ልጋብዝሽ!” ከማለት ውጪ ምንም አይነት የሽብር ተግባር ውስጥ የሚሳተፍ አይመስልም ብዬ ለአለቃዬ ሪፖርት አደረግሁ። አለቃዬ ግን “ይህ ወጣት ከቁጠባ ተቋማት ሳይበደር፣ ይሄንን ሁሉ ኮረዳ ለመጋበዝ አቅሙ እንዴት ሊኖረው ቻለ?” ሲሉ ስል የሆነ ጥያቄ ጠየቁኝ። እንጃ…! አልኩ በሆዴ… (አለቃን በአንደበት “እንጃ!” ማለት እንደ “አንጃ” ስለሚያስቆጥር ነው በውስጤ ማለቴ!”) ብልሁ አለቃዬ “የወጣቱ የገንዘብ ምንጭ በውጪ ሃገር ያሉ “አሸባሪዎች!” ሊሆኑ ይችላሉ እና ክትትሉ ይቀጥል” አሉኝ። እሺ አልኩ “ሺ” ን ጠበቅ አድርጌ። (በነገራችን ላይ አለቃዬ ከጠረጠሩ ጠረጠሩ ነው። በቃ አስረው ካልቀጡ መላቀቅ የለም።)
እኔም ጠለፋዬን፤ ጎረምሳዬም የሰውንም የራሱንም ሚስቶች ማባበሉን ቀጥሏል። የደወለላትን ሁሉ ራት ካልጋበዝኩሽ ማለት ልማዱ ነው። አንዳንድ ግዜ አንዷን መክሰስ ጋብዞ፤ ሌላዋን ራት ልጋብዝሽ ይላል። ይሄኔ እኔም ። ይህ ወጣት በራት ግብዣ እና ጥቅማጥቅም እያባበለ ሴት እህቶቻችንን ለሽብር ስራ እየመለመለ ሊሆን ይችላል! ስል አሰብኩ። ይህንንም ለአለቃዬ ነገርኩ። በአለቃዬ ፊትም ሞገስን አገኘሁ።
ጠለፋዬ ቀጥሏል።
ወጣቱ ምላሱ ቅቤ ይቆላል። የደወለላትን ሁሉ “እናትዬ… ርሃቤ ዛሬ ሳላይሽ ውዬ ታምኩልሽ!” ይላታል። ሌላዋ ጋ ደግሞ ይደውልና “ማበዴ ነው… አይንሽን ካየሁሽ ሁለት ሰአት አለፈኝ!” ይላትና፤ የናፈቁትን የሰውነቷን ክፍሎች ዝግ ባለ ድምፅ ተራ በተራ ይጠራል። ልጅትም በዛኛው የስልክ መስመር ወንድነትን የሚፈትን ድምፅ እያሰማች… ሁሉም የእርሱ መሆናቸውን ትገልፅለታለች… በተለየዩ ቀናት የተለያዩ ሴቶች ዘንድ እየደወለ፤ “ፀጉርሽ ውስጥ ገብቼ ደስታዬን ላብዛ… ከንፈርሽን በከንፈሬ ገጥሜ ዕድሜዬን ላርዘመው… አንገትሽ ውስጥ ውሽቅ ብዬ የአለምን ጣጣ ልርሳ…” ይላቸዋል። የተደወለላትም ሴት በአልጋ ይሁን በስልክ በሚያጠራጥር ድምፀት “እሺ የኔ ጌታ… እሺ የኔ አንበሳ… እሺ የኔ ነብር…” እያለች አሉ የሚባሉ የዱር እንስሳትን እየጠራች በተቅለሰለሰ ድምፅ ታደንቀዋለች። ይሄኔ እኔ የወንድነት ደሜ እተሯሯጠ ወይኔ ወንዱ… እኛስ…? ለእኛ ምን ታስቧል? ብዬ አምርሬ እጠይቃለሁ። ጎረምሳው ሁሉንም ሴቶች በምላሱ የግሉ አደረጋቸው ብዬ ብስጭቴ ጣራ ይነካል።
በእውነቱ በጠለፋ ህይወቴ እንዲህ የተፈተንኩበት ግዜ የለም። አለቃዬን በሽብርተኞች አዋጅ ውስጥ “ሴሰኛ ወጣቶች እንደ ሽብርተኛ ይቆጠራሉ!” ስለማይል የዚህን ሰው ስልክ መጥለፉ ይብቃ ልላቸው ነበር። ነገር ግን እርሳቸው የጠረጠሩትን እንደማይጠረጠር አድርጎ መቁጠር ትልቅ ድፍረት ሆኖ ተሰማኝ። ታድያ እስከ መቼ ራሴን እየፈተንኩ እዘልቀዋለሁ። አስቤ አስቤ ክስ አገኘሁ።
አሁን ወስኛለሁ። ይሄ ጎረምሳ መከሰስ አለበት እኔም የእሱን ስልክ በመጥለፍ ወንድኔቴን የማስጨንቅበት ምክንያት የለም። አዎ ጠለፋዬ አብቅቷል ብዬ ሪፖርት ማደረግ። ከዛም ክስ እንዲመሰረት መጠየቅ አለብኝ።
አለቃዬ ዘንድ ቀርቤ የጠለፋ ስራዬን በአግባቡ እንደጨረስኩና አጠቃላይ ሪፖርት ማቅረብ እንደምችል ተናገርኩ።
በሪፖርቴም ይህ ወጣት የተሰማራበት የሽብር ስራ ከዚህ በፊት ያልተለመደ እና እጅግ ውስብስብ አካሄድም እንዳለው ገለፅኩ።
ወጣቱ በፍቅር ስም የሚያሰባስባቸውን ኮረዶች የዜጎችን የመደራጀት እና የመስራት አቅም የሚያዳክም ከመሆኑም በላይ ሴቶቹ በማህበር ተደራጅተው አምራች ዜጋ እንዳይወጣቸው አስተጓጉሏቸዋል። ይህንንም እጅግ በተቀነባበረ መልኩ እንደሚሰራ አስረዳሁ። አንድ ክፍለጦር የሚሆኑ ሴቶችን የሚጋብዝበትም የገንዘብ ምንጭ ሊጣራ የሚገባው ነው። ከዛም በተጨማሪ በተደጋጋሚ በሚደውላቸው ስልኮች ረጅም ሰዓት ስለሚይዛቸው የአካባቢውን ኔትዎርክ ስራ እንዲበዛበት አድርጓል። ይህም የቴሌ ተቋምን ከማፈራረስ ተለይቶ አይታይም። ስልም ጨመርኩለት።
በአሁኑ ግዜ ወጣቱ በውስብስብ የሽብር ስራ ተጠርጥሮ ምርመራ ላይ ይገኛል። እኔም ወጣቱ ዘወትር ምሽት በስልክ በሚሰራው ፍቅር ወንድነቴን ከመፈተን ድኛለሁ።
አንድ ምስጢር ግን ልንገራችሁ… በወጣቱ ስልክ ጠለፋ ባዳበርኩት ልምድ መሰረት በርካታ ቆነጃጅትን ለማባበል እየተጋሁ ነው። እስከ አሁን በቅጡ አልተሳካልኝም። ነገር ግን ቀድቼ ያስቀመጥኩትን የዛን “አሸባሪ” ወጣት ጥበብ ደጋግሜ እየሰማሁ ደጋግሜ እሞክራለሁ። (አትሳቁብኝ ጥቅማ ጥቅማችን እኮ ይቺው ናት!)
ወዳጄ የዛሬው ሀሳብ ወለድ ጨዋታችን በዚህ ያበቃል… በሚቀጥለው ሳምንት እስክንገናኝ…
አማን ያሰንብተን!

Return to “Ethio Politics .... ኢትዮ ፖለቲካ”