ይድረስ ለአነስተኛ እና ጥቃቅን ስድብ አምራቾች! አቤ ቶኪቻው

ፖለቲካ ፣ ወቅታዊ ጉዳዮች
Politics , Current affairs
User avatar
zeru
Leader
Leader
Posts: 952
Joined: 19 Aug 2009 17:01
Contact:

ይድረስ ለአነስተኛ እና ጥቃቅን ስድብ አምራቾች! አቤ ቶኪቻው

Unread postby zeru » 28 Jan 2012 23:04

አቤ ቶኪቻው
abeto2007@yahoo.com
በመጀመሪያም
ይህ ፅሁፍ ባለፈው አርብ ለወጣችው ለምናፍቃት ፍትህ ጋዜጣ ልኬው ታትሞም የነበረ ነው። ታድያ ለፍትህ ስፅፈው በተቻለኝ አቅም በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ያሉት ፈላጭ
Image
አቤ ቶኪቻው
ቆራጮቻችን ደም ብዛታቸው ከፍ እንዳይል በመጨነቅ አንዳንድ ሃሳቦች ላይ ቁጥብ ስድር ለማለት ሙከራ አድርጊያለሁ። ምክንያቱም ሰዎቹ ደማቸው ሲፈላ የሚያደርጉትን አያውቁትምና፤ የአዲሳባ ወዳጆቼ እንዲሁ ያለባቸው ጦስ ሳያንሳቸው እኔ ደግሞ ተጨማሪ አልሆንባቸውም ብዬ ነው። እናም ይህ ፅሑፍ ዛሬ ለዌብ ሳይቶች ስልከው ትንሽ ከለስ ከለስ አድርጌዋለሁ…
እስቲ አንብቡልኝ…!
ከውዲቱ ሀገሬ ከተሰደድኩ እንደዋዛ ሶስት ወራት አለፉ። እስከምመለስ ድረስ ስንት ወራት እንደሚያልፉ እንጃ! ነግቶ በመሸ ቁጥር ሁሌም ፒያሳ በአይኔ ላይ ትሄዳለች። አራት ኪሎ መቀጣጠር ያምረኛል። ሽሮሜዳ ደረስ ብሎ መመለስ ይናፍቀኛል። የአዲሳባ ስታድየም ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን ለመታደም እጓጓለሁ። በተቃዋሚዎች ስብሰባ ላይ መገኘት ያሰኘኛል። እንኳን ሌላው ቀርቶ ካገር እንድሰደድ ምክንያት የሆነኝ ኢህአዴግ፤ የሚጠራቸው ባለ አበል ሰልፎች ላይ ራሱ አባልም ባልሆን አበልም ባይሰጠኝ ለመታደም የማደርገው ጥረት ራሱ ዛሬም ይናፍቀኛል።
ትዝታ
“የባንዲራ ቀን” ክበረ በዓል በአመቱ መጀመሪያ መከበር ከጀመረ አራት አመት አልፎታል። በርግጥ ባንዲራ ከተፈጠረ የትየለሌ ዘመናትን አስቆጥሯል። ነገር ግን ኢህአዴግ በባንዲራ ጉዳይ ላይ ልብ ከገዛ አራት አመት ሞልቶታል። እንዲሁ በሰባዊ መብት ጉዳይ ላይ፣ በተንሸዋረረ ፖለቲካ ጉዳይ ላይ፣ በሴራ አስተዳደር ጉዳይ ላይ፣ በሙስና ጉዳይ ላይ፣ በስንፍና ጉዳይ ላይ፣ በወዘተ ጉዳይ ላይ ልብ ይገዛል ብለን ብንጠብቀው፤ ብንጠብቀው ልብ ተወደደበት መሰለኝ ይህው ሃያ አመት ሙሉ ልብ አልገዛም። የሆነ ሆኖ በዚሁ አመት መጀመሪያ ላይ የባንዲራ ቀንን “ላከብር” አዲሳባ ስታድየም ዙሪያ ታድሜ ነበረ።
በርካታ ጎስቋላ እናቶች ጉስቁልናቸውን በሚሸፍን ቅባት ወዝተው የቤታቸውን ችግር በሚሸፍን ደማቅ ሻርፕ አምረው ከበርካታ ህፃናት ተማሪዎች ጋር እየተጋፉ ወደ ስታደየሙ ቅጥር ግቢ ለመግባት ይጥሩ ነበር። በዚህ ግዜ ግፊያው አቅማቸውን ክፉኛ የፈተናቸው አንድ እናት እኔ አገጨን ይዤ ወደቆምኩበት ጥግ መጡ እና “ም…ነው!” ብለው አጠገቤ ቆሙ… በ “ም” እና በ “ነው” መሃል ያለው ርቀት ከሰፈራቸው እስከ ስታድየም የሚደርስ ነው… (እዝች ጋ ያው እንደምትጠረጥሩት አጋንኛለሁ… ነገር ግን ከ “ም….. ነው?” አባባላቸው ትክት እንዳላቸው መረዳቴ ግን እውነት ነው።) “አይዞን እናቴ… ግፊያው በረድ ሲል እንገባለን። ለሁላችንም የሚበቃ ቦታ አለኮ!” በሚል ጨዋታ ጀመርኩ። በርግጥ መግቢያ ካርድ የሌለው ሰው ስታድየም ገብቶ የባንዲራ ቀንን ማክበር እንደማይችል ሰምቻለሁ…
ይገርማል ኢህአዴግ ማግለል እና አድሎ ላይ የተካነ መሆኑን የተረዳሁት ይህንን ስሰማ ነበር። ልብ አድርጉልኝ ባንዲራው የአገሪቱ ነው የፓርቲው አይደለም። ግን አበል እና የመግቢያ ካርድ የተሰጣቸው “ውድ” የኢህአዴግ ልጆች ብቻ ናቸው የሚገቡት። እኛ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ግን ዳር ዳሩንም በመከራ ነው ያገኘነው። ወይ አድሎ…!
አሮጊቷ ጠበቅ አድርገው የያዟትን ካርድ እያሳዩኝ፤ “እውነትህን ነው ልጄ በቂ ቦታ አለ ሰዉ አመል ሆኖበት ነው የሚጋፋው!” ብለው ፈገግ አሉልኝ። ጥርሳቸው ወላቃ ነው። ቢሆንም የእናትነት ፈገግታቸው ያምራል። እኔም ፊት እንደሰጡኝ ሳውቅ ግዜ የተለያዩ ጨዋታዎችን አጫወትኳቸው እና በደንብ ከተግባባን በኋላ፤ አንድ ፈታኝ ጥያቄ ሰነዘርኩላቸው… “አሁን እንደው አንድ ጋዜጠኛ መጥቶ የበዓሉ ጥቅም ምንድነው? ቢልዎት ምን ይሉታል?” አልኳቸው እርሳቸውም “እኔ የአንተ እናት…!” ብለው ከፎከሩ በኋላ፤ “እውነትም ልጄ… ምንድነው ጥቅሙ እላለሁ…? አረ እንጃ… ብቻ አበሏ ትጠቅማለች ለኛም ቡና ለእናንተም ያቺን…” ብለው በእጃቸው የመጠጥ ምልክት አሳዩኝ እና ከትከት ብለው ሳቁ። “ኑሮ በዘዴ ነው ልጄ…!” ሲሉም ጨመሩልኝ።
አዲሳባ እያለሁ በርካታ የኢህአዴግ አባላት ወዳጆች ነበሩኝ። ሁሉም ቢሆኑ “ኑሮ በዘዴ!” ብለው ነው አባልነቱን የፈረሙት። አብዛኛዎቹ ከእኛው ጋር ስላቅ የበዛበትን የሀገራችንን ፖለቲካ አብረውን ያሽሟጥጡ ነበር። አብዛኛዎቹ “ቀን እስኪያልፍ…” የሚለውን ተረት እየተረቱ በቁርጡ ቀን ግን የህዝባቸው አጋር እንደሆኑ አውቃለሁ። ግን ኑሮ፤ እንጀራ ይሉት ጣጣ የግድ የኢህአዴግ አባል እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። አዎ አዲሳባ አባልነት እንጀራ ነው። አባል ካልሆኑ አበልም ደሞዝም የለም። ይሁን ጥሩ ነው። ሰው አይኑር አይባልም። አይብላ አይጠጣ አይባልም። ስለዚህ የኢህአዴግ አባል መሆንን አልቃወምም!
እንግዲህ ከሀገሬ የተሰደድኩበት ምክንያት “ከመግባት መውጣት ይሻላል!” የሚል አጥጋቢ ምክንያት እንደነበረ ጠቅሻለሁ። በዚህ አጋጣሚ በዛን ግዜ እኔ የመጣው ይምጣ “ልታሰር…!” ብዬ “አካኪ ዘራፍ” ስል “ይህ አጉል ጀብደኝነት ነው ከመግባት መውጣት ይሻልሃል!” ብላችሁ አበክራችሁ የሞገታችሁኝ ወዳጆቼ አሁን አሁን እያመሰገንኳችሁ ነው። ምክንያቶቼ አዲስ መስመር ላይ አሉላችሁ።
ምክንያት 1
ከሀገሬ ከወጣሁ ግዜ ጀምሮ ከምወደው የፅሁፍ ስራ የተገታሁት ለሁለት ሳምንት ብቻ ነበር። ሌላውን ጊዜ በሙሉ እየፃፍኩ ፌስቡክን ጨምሮ በተለያዩ ዌብሳይቶች ላይ እየለጠፍኩ እገኛለሁ። ታድያ እኔ አዲሳባም ብሆን ከመፃፍ ውጪ ምን እሰራ ነበር…? ታስሬ ቢሆን ኖሮስ…? እውነቱን ለመናገር የአንድነቱ ናትናኤል እስር ቤት የተደረገውን በሰማሁ ግዜ፣ ጋሽ ደቤ ያለውን በሰማሁ ግዜ የስለሺ ሀጎስን ሁኔታ በሰማሁ ግዜ… እኔ ሳስበው የነበረው መታሰር እና የኢህአዴግ እስር የተለያዩ እንደሆኑ በጣም ተረድቻለሁ። ወዳጆቼ ደጋግማችሁ እንደነገራችሁኝ ታስሬ ብቆይም አልፅፍም ነበር፤ ታስሬ ብፈታም ከተፈታሁ በኋላ እፅፍ ነበር ወይ? የሚለውን እጠራጠራለሁ… ሰዎቹ ሲያስሩ… ምን እንደሚያደርጉ ወደፊት የሚጣራ ነው። አሁን ግን ምስጋና ለእናንተ ምክር እና ተግሳፅ ይህው አልታሰርኩም፤ እናም እፅፋለሁ… አንድ ወረቀት እና ባዶ አንድ እስክርቢቶ እስኪቀረኝ ድረስ… (ብዬ ላጋን እንዴ!?)
ምክንያት 2
ያ… ደህንነት ወዳጄ ደጋግሞ እኔ ከኤልያስ ክፍሌ ጋር ግንኙነት እንዳለኝ ነግሮኛል። ለዚህም በቂ ማስረጃ አለን ሲለኝ ነበር የቆየው። እውነቱ ግን ከኤልያስ ክፍሌ ጋር እንኳንስ ያኔ ይቅርና አሁን እንኳ አለመገናኘቴ ነው። በዛን ወቅት ጓደኞቼን “ካሰሩም ይሰሩኝ” ብዬ ስሞግት በልቤ የማስበው አጣርተው ነፃ መሆኔን ሲያውቁ ይለቁኝ የለ…? የሚል የየዋህ አስተሳሰብ ነበር። ነገር ግን በነ ርዮት አለሙ እና ውብሸት ታዬ የፍርድ ሂደት የተመለከትኩት ነገር ቢኖር የፍርድ ቤቱ ክርክር የቱንም ያህል አሳማኝ ባይሆን፣ የቱንም ያህል የቀረቡት መረጃዎች ውሃ የማያነሱ ቢሆኑም በቃ መንግስት ከከሰሰ ከሰሰ ነው። አኪልዳማ ድራማ ካሰራብህማ አለቀልህ ማለት ነው…!
የእነ ርዮት እና ውብሸትን የፍርድና እና ክርክር እንዲሁም የምስክርነት ሂደት በተወሰነ መልኩ ተከታትያለሁ። በተከታተልኩ ግዜ በጣም የሚሰቀጥጡ አይነት ምስክርነቶችን ታዝቤያለሁ። ዳኛው እና ፖሊሶች አዩን አላዩን ብለን ከትከት… ብለን የሳቅንባቸው ርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ምስክርነቶችን ተከታትለናል። በርግጥ በወቅቱ ይህንን መግለፅ በፍርድ ሂደቱ ጣልቃ መግባት ነው በሚል ትህትና ትንፍሽ ሳልል ቆይቼ ነበር። ያው እንደሚታወቀው እኛ ፍርድ ቤት በያዘው ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት አይፈቀድልንም። እኛ ያልኩት ፍትህ እና አውረምባን የመሳሰሉት ነፃ ጋዜጦች ማለቴ ነው። እነ ኢቲቪ ግን እንዳሻቸው “መንቦራጨቅ” እንደሚችሉ በተደጋጋሚ አይተናል። (ውይ ይቅርታ እነ ኢቲቪ ትንሽ ስሜታዊ ሆኜ “መንቦራጨቅ” ያልኩት መዘገብ ለማለት ነው። ምን ነካኝ?)
አሁን የፍር ሂደቱ አክትሟል ጋዜጠኞቹ እና ፖለቲከኞቹም ጥፋተኛ ተብለዋል… “የተዋረደው ፍርድ ቤት!” የሚል መፅሐፍ ከዚህ በፊት ታትሞ ነበር። በበኩሌ ይህ መፅሐፍ ቁጥር ሁለት ቁጥር ሶስት እያለ እንዲቀጥል ፍላጎት የለኝም። ነገር ግን ፍላጎቴ የሚሳካ አይመስለኝም። “ተዋርደናል ተንቀናል… ብታምኑም ባታምኑም በቁም ሞተናል!!!” አሉ መንግስቱ። (የፍርድ ሂደቱን የተከታተለ በሙሉ እንዲህ ማለቱ አይቀርም) እናላችሁ አለመታሰር ነው እንጂ መንግስት ያሰረው ሁሉ ጥፋተኛ ነው። እናም መካሪዎቼ እንዳልታሰር መክራችሁኛልና ምስጋናዬ ይድረሳችሁ።
ወደ ዋናው መስመር ስንመለስ…
ውድ “አነስተኛና ጥቃቅን ስድብ አምራቾች” ሞት ይርሳኝ ርስት አደረኳችሁ እኮ… በዋናነት ይህን መልዕክት ያዘጋጀሁት ለእናንተ ነበር። ነገር ግን ከወዳጆቼ ጋር ጨዋታ ይዤ ዘነጋዋችሁ። ይህውልችሁ እንግዴ እኔና ወዳጆቼ ከተገናኘን እንዲህ ነው… አንዱን ስናነሳ አንዱን ስንጥል… ሳይታወቀን አራት ገፅ እንሞላላችኋለን? አይደንቃችሁም…?
ወዳጄ… “አነስተኛ እና ጥቃቅን ስድብ አምራቾች” ያልኳቸው እነማን መሰሏችሁ… ሀገሬን ትቼ ከወጣው ግዜ ጀምሮ እንዳልኩዎት በየዌብሳይቱ ላይ የተለያዩ ፅሁፎችን እየፃፍኩ መሆኑን ነግሬዎትም አልነበር…? ታድያልዎ አንዳንድ ግለሰቦች ሆዬ የተለያዩ አነስተኛና ጥቃቅን ስድቦችን በኢሜል እየላኩልኝ ይገኛሉ። እንግዲህ እነርሱ ዋና የኢህአዴግ ተቆርቋሪ መሆናቸው ነው። (ድንቄም እቴ የሚል ጨምሩልኝ።) ምነው እንኳ አዲሳባ ሆኜ ስፅፍ በነበረበት ግዜ በርካታ የኢህአዴግ አባላት ሁላ በሽሙጣችን አብረውን ሲስቁ፤ ሲሳሳቁ አልነበረም እንዴ? እንደውም እኮ አንዳንዴ ኢህአዴጉ እኔ ልሁን እነርሱ አይለይም ነበር። ታድያ እነዚህ እነማን ናቸው…?
አንዳንዶቹ እንደነገሩኝ ከሆነ በተለያየ የውጪ ሀገር ዩንቨርስቲዎች ኢህአዴግ ለትምህር የላካቸው ናቸው። ሌሎቹም ወይ ሲራራ ነጋዴ ናቸው ወይ ደግሞ ደላሎች ናቸው… ብቻ ግን ብዙዎቹ በውጪ ሀገር የሚኖሩ የኢህአዴግ ተደጋፊዎች ናቸው። (እነርሱን ደጋፊ ብዬ ብጠራ ኢህአዴግን ማኮሰስ ይሆንብኛል ብዬ ስለሰጋሁ ነው።) “ድሮስ ቢሆን ኢህአዴግ ኮሳሳ አይደለም እንዴ?” ብለው ሊጠይቁኝ እንደሚችሉ ጠረጠርኩ… እውነቱን ለመናገር ጠንከር ብሎ ለታገለው ኢህአዴግ ኮሳሳ ስለመሆኑ ብዙ ምልክቶች አሉ። አንበሳ የመሰላችሁ ካላችሁ እርሾ በዝቶበት ተነፋፍቶ መሆኑን ውስጥ አዋቂዎች እናቃጥራለን!
ሰዎቹ የሚልኩልኝ ስድባ ስድቦች የሚቀራረቡ ከመሆናቸው አንፃር እንደገመትኩት ከሆነ ለኢህአዴግነት ሲመለመሉ የተወሰነ “ክሬዲት ሃወር” “ስድቦ ሎጂ…” ስልጠና የወሰዱት ይመስለኛል። በጥቅሉ “አነስተኛና ጥቃቅን ስድቦች” ናቸው። ለዚህም ነው ዛሬ “ይደረስ ብዬ ለአነስተኛና ጥቃቅን ስድብ አምራቾች” ስል መፃፍ ያሰኘኝ።
በርግጥ በኢህአዴግ ቤት ስድብ ብርቅ አይደለም። የተከበሩት ጠቅላይ ሚኒስትራችንም… በተለያዩ ግዚያት ካደረጓቸው ንግግሮች ውስጥ በርካታ ስድባ ስድቦች ተገኝተውባቸዋል። እናም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርመራ ውጤት ራሱ “ስድብ ፖዘቲቭ” ነው ማለት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል፤ “ይሄንን የበከተ አስተሳሰብ ይዞ የሚቀርብ ወራዳ… የበከተ…አስተሳሰብ የያዘ የተዋረደ…” የሚሉት ከታወቁባቸው የስድብ አልበሞች መካከል ተጠቃሽ ናቸው። እናም በኢህአዴግ ቤት ስድብ ብርቅ አይደለም… ነገር ግን የእኔዎቹ ጉዶች የሚልኩልኝ ስድቦች ግን ከዚህም የወረዱ… ፀያፍ ናቸው። እንደው አጋነንክ ባይሉኝ፤ (ቢሉኝም ግድ የለም) አንዳንዶቹን የኢሜል ስድቦችማ ገና ኮምፒውተሬ ላይ ከፈት ሳደርጋቸው የኮምፒውተሩ አንቲቫይረስ ቀይ አብርቶ “Detected” የሚለኝ ግዜ አለ።
አንዳንዶቹን ተሳዳቢዎቼን በትህትና ብዛት አንጀታቸውን ልበላ ያላደረግሁት ጥረት የለም። “አረ በረድ ይበሉ አረ ሰከን ይበሉ ካጠፋሁ ልጥፋ… ካስቀየምኩዎ… ልቀሰፍልዎ…” ብዬ ሁሉ ላባብል ብሞክር ምንም የሚገባቸው አለሆን አለኝ። ወይ ጉድ አንድ እንኳ ሙድ ያለው የአራዳ ልጅ ኢህአዴግ ይጥፋ! ብዬ ልል ነበር እነዛ የአዲሳባዎቹ ኢህአዴግ ወዳጆቼ ትዝ አሉኝ። ለነገሩ እነርሱ አብዛኛዎቹ ውስጣቸው ቅንጅት ነው። (እዝች ጋ ሳቅ አለ።)
ለማንኛውም ለ”አነስተኛና ጥቃቅን ስድብ አምራች” ወዳጆቼ የሚተላለፈው መልዕክት እንደሚከተለው ይቀርባል።
ውዶቼ… ወቅቱ ኢሃዴግ የተለያዩ እድገቶችን ያስመዘገበበት ወቅት እንደሆነ እናውቃለን። በተጨባጭም እንዳየነው ከሆነ በስድብም ታላቅ የእድገት ደረጃ ላይ መድረሳችንን ከእናንተ በላይ ማሳያ ከየት ይመጣል? ነገር ግን ምክር እንኩ፤
ስትሳደቡ መረጥ መረጥ ለማድረግ ሞክሩ። አለበለዛ በእውኑ ለእናንተ እናት ለሌሎች እንጀራ እናት የሆነ ድርጅታችሁን እያወረዳችሁት እነደሆነ እወቁ። ከዛም አልፎ፤ አንድ ቀን የላካችሁልኝን ስድቦች በሙሉ ሰብስቤ ለዋናዎቹ ሃላፊዎቻችሁ የሰጠው ግዜ በኪራይ ሰብሳቢነት እንደሚገመግሟችሁ ጥርጥር የለኝም። አዎና እነርሱ ዘንድ እንኳ የሌለ ስድብ አከማችታችሁ ስትገኙ ከዚህ የበለጠ ኪራይ ሰብሳቢነት ከየት ይመጣል? እናንተስ ስንቱን ክስ ትችሉታላችሁ? ያላግባብ ያከማቻችሁት ሀብት አንሶ ያለአግባብ ስድብ ማከማቸት መልካም ነውን?
ያዋጣናል ካላችሁ፤ እንግዲህ እንዲህ እላችኋለሁ። እኔ ስራዬን መስራቴን ቀጥያለሁ። በተቻለኝ አቅም ሁሌም ከምናፍቃቸው ወዳጆቼ ጋር የተለያዩ ጉዳዮችን እያነሳን እናወጋለን… (እንዋጋለን አላልኩም!) እንኳንስ ተዋግተን አውግተንም በአሸባሪነት ከመጠርጠር አላመለጥንም! እናንተም በአነስተኛና ጥቃቅን በስድብ ምርታችሁ ግፉበት ስንት ፐርሰንት እድገት እንዳሳያችሁም ሪፖርት አድርጉልን!
በመጨረሻም 1
አቶ በረከት ስምዖን በፖለቲካው ከታወቁት ይልቅ ባሳተሙት የሁለት ሀውልቶች ወግ ይበልጥ ታዋቂ እየሆኑ ነው። እንደውም ሰውየውን አቶ በረከት ሰሞን ብዬ ስጠራ አንዳንድ ግለሰቦች “ደራሲው” ብለህ ጨምር እያሉኝ ይገኛሉ። እናም ሳስበው ፖለቲካው ላይ ያጠፉት ካለ ተሰጥዖቸው ድርሰት ስለሆነ ሊሆን ይችላልና ይቅር ሊባሉ ይገባል እላለሁ።
አቶው በመፅሀፋቸው ካገኙት ታዋቂነት በተጨማሪ ግን አንዳንድ “ፋዎሎችንም” ነክተዋል። እየቆጠብን እናወጋለን፤ ለዛሬ… በመፅሐፋቸው የሆነው ገፅ ላይ ዳኛ ብርቱካን ሚዴቅሳን የሚመለከት አንድ ነገር እናንሳ፤ እንዲህም አሉ “የብረቱካን ነገር በየዋህ እጅ የዘንዶ አፍ ይለካል እንደሚሉት አይነት ነው” ካሉ በኋላ “…ሁሉም እጁን ወደ ዘንዶው ጉድጓድ የሚልክ የዋህ እስኪያገኝ በመጠባበቅ ላይ በነበረበት ወቅት መሞከሪያ አያሳጣ፤ እንዲሉ የውሃውን ጥልቀት ለመለካት ወይዘሪት ብርቱካን ብቅ አለች…” ዘንዶውም ቀብ አደረጋት… ሰረዝ የተደረገበትን የጨመርኩት እኔ ነኝ።
ወይ ጉድ… ሰው የራሱን ድርጅት እንዴት ዘንዶ ይላል? አቶ በረከት ችግር አለ እንዴ? ብዬ ልጠይቅ ነበር ግምገማ ላይ ብንገናኝ ይሻላል! (ሳቅ)
በመጨረሻም 2
የፍትህ አምደኛ የነበረችው ርዮት አለሙ ባለፈው ሳምንት ልደቷን በቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዳከበረች ሰማሁኝ። እናም እንኳን ተወለድሽ ልላት ወደድኩ። በነገራችን ላይ ርዮት አለሙ ምንም እንኳ የተከሰሰችበት ክስ እንኳንስ በሌላው ሰው አይን እና በራሱ በኢህአዴግ አይንም ቢሆን እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም ጥፋተኛ ከመባል ግን አላመለጠችም። ምክንያቱ ምን እንደሆነ ልንገርዎ… ርዮት ለቅርብ ሰዎቿ በግል እንዲሁም ለፍርድ ቤቱ በይፋ እንደተናገረችው “በኤሊያስ ክፍሌ ላይ ምስክርነት ስጪ እና ትፈቻለሽ ብለው መከራዋን ሲያበሏት የማውቀውን እንጂ የማላውቀውን አላውቅም” በማለቷ ነው። እኔ የምለው ግን ኢህአዴግ ከዝች አንዲት ፍሬ ልጅ ጋር እንዲህ እልህ የሚጋባው በደህና ነው? ጥያቄዬን ባላገር ያሉ ወዳጆቼ ቢሰሙ እርሱም እኮ ገና “ውርጋጥ” ነው ይሉኝ ነበር። “ውርጋጥ” ማለት በጎጃም እና ጎንደር አካበቢ ትንሽ ልጅ ማለት ነው። ትንሽ ልጅ ደግሞ ትንሽ ሆነህ ቆይ ከተባለ ከሃያ አመትም ይዘላል…!
ትልቅ ያድርግዎ ወዳጄ!
በመጨረሻም 3
ወዳጄ አሁን ልሰናበትዎ ነው… ሰላም ይሁኑልኝ እቴ!
አማን ያሰንብተን!

Return to “Ethio Politics .... ኢትዮ ፖለቲካ”