የዓርብ ሐምሌ 13/2010 አበይት ዜናዎች

Daily Ethiopian News, አዳዲስ ዜናዎች።
Forum rules
** When you post a News please include the Source link.
For More Ethiopian News please visit the Home Page
http://ethiopiaforums.com/
selam sew
Leader
Leader
Posts: 692
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

የዓርብ ሐምሌ 13/2010 አበይት ዜናዎች

Unread post by selam sew »

ለቸኮለ የዓርብ ሐምሌ 13/2010 አበይት ዜናዎች

1. በሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ የሰው አጽሞች መገኘት ብዙዎችን አስደንግጧል፡፡ በግለሰቦች ጥቆማ ፖሊስ ኮሚሽኑ ግቢ ውስጥ ሐምሌ 9/2010 አጽም ተገኝቷል፡፡ ግምጃ ቤቱ ውስጥ ሌላ የሰው አስከሬን እንደሚገኝ ተጨማሪ ጥቆማ በመድረሱ ግምጃ ቤቱ ተከፍቶ ሲፈተሽም አስከሬን ተገኝቷል፡፡ የክልሉ ጸጥታና ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ለክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች… አስከሬኖች መገኘታቸውን አረጋግጠው ጉዳዩን የሚያጣራ የምርመራ ቡድን ተዋቅሮ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ለዲኤንኤ እና ተጨማሪ ምርመራ ወደ ፌደራል ፖሊስ እንደሚላክም ጠቁመዋል፡፡ የሀረሪ ክልል ፖሊስ ከሰሞኑ በአመራሮቹ ላይ ተቃውሞ አቅርቦ… ምክትል ኮሚሽነሩ የዋና ኮሚሽነሩን ሥራ ተረክበው እንዲሰሩ ውሳኔ መተላለፉ ይታወቃል፡፡

2. የኢትዮጵያና ኤርትራ ንግድ ምክር ቤቶች ትናንት ረቡዕ በአስመራ በተካሄደ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ሲመክሩ ውለዋል፡፡ ምክር ቤቶቹ በሀገራቱ መካከል የተሻለ የንግድ ግንኙነት መፍጠር ስለሚቻልበት ሁኔታ ተነጋግረዋል፡፡ ይሕ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሁለቱ ሀገራት መካከል የጀመረውን በረራ በማስመልከት በአስመራ ፓላስ ሆቴል ዝግጅት ተካሂዷል፡፡ በፕሮግራሙ የቀድሞው ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የአየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወልደ ገብረማርያምን ጨምሮ ባለሀብቶች፣ የንግድ ሰዎች፣ አርቲስቶችና ጋዜጠኞች ታድመዋል፡፡

3. ግርማ ብሩ ግርማ ብሩ ከትናንት ሐምሌ 12/2010 ጀምሮ መኮንን ማንያዘዋልን ተክተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የቦርድ ሊቀ መንበር እንዲሆኑ በጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ ተሹመዋል፡፡ ከሰሞኑ የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽነር የሆኑት ኢዮብ ተካልኝ፣ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ በቃሉ ዘለቀ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትሩ አብርሀም ተከስተ፣ የቀድሞው የባንክ ገዢ ተክለወልድ አጥናፉ በቦርድ አባልነት ተሰይመዋል፡፡ ግርማ ብሩ ለአምስት ዓመት በዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ከመሆናቸው በፊት የንግድና ኢንዱስትሪ እንዲሁም የኢኮኖሚ ልማትና ትብብር ሚኒስትር ሆነው ሠርተዋል፡፡

4. ሰኔ 16/2010 በመስቀል አደባባይ ከደረሰው የቦምብ ፍንዳታ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ለሶስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል፡፡ የአ/አ ፖሊስ ኮሚሽነር ግርማ ካሳን ጨምሮ ኃላፊነትን ባለመወጣትና በጥቃት አድራሽነት የተጠረጠሩት ተከሳሾች ዛሬ ልደታ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት 10ኛ ችሎት ቀርበዋል፡፡ ፖሊስ ምርመራውን ባለማጠናቀቁ የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ሲጠይቅ፣ ተከሳሾች በበኩላቸው የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡ ግራ ቀኙን ያዳመጠው ችሎትም የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ ያደረገ ሲሆን፣ ፖሊስ የጠየቀውን ጊዜ በመቀነስ በሠባት ቀን ቀሪ ምርመራውን እንዲያጠናቀቅ በማዘዝ ለሐምሌ 20/2010 ቀጠሮ ሠጥቷል፡፡

5. ለሁለት ወራት በውጪ ሀገር ሕክምና ላይ የነበሩት የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ቱት የጤናቸዉ ሁናቴ በመሻሻሉ ወደ ሥራቸው ተመልሰዋል፡፡ በግንቦት አጋማሽ በጠና ታመው በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ሕክምና ሲያደርጉ የነበሩት ርዕሰ መስተዳድሩ በጤናቸው ለውጥ ባለመታየቱ ወደ ውጪ ሀገር ሄደው እንዲታከሙ ሪፈር ተጽፎላቸው ነበር፡፡ ሆኖም ፕሬዚዳንቱ ውጪ ሀገር ሄደው የሚታከሙበት ገንዘብ እንደሌላቸዉ በመግለጻቸው፣ ግንቦት 20/2010 የክልሉ ካቢኔ አስቸኳይ ስብሰባ በማካሄድ ከክልሉ መጠባበቂያ በጀት ለሕክምናቸው አንድ ሚሊየን ብር ወጪ ማድረጉ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡

6. በሱዳን ድንበር የኢትዮጵያ ይዞታ የሆነ መሬት በሱዳኖች ይገባኛል ጥያቄ በመቅረቡ የግብርና ሥራ መስተጓጎሉን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ፡፡ “በቋራ ነፍስ ገበያ፣ በመተማ እንዲብሎ እና ደለሎ በሚባሉ ሶስት አካባቢዎች ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የሚያርሱትን፣ የእኛ የሆነውን መሬት ሱዳኖች 'የእኛ ነው' በማለታቸው እና ግጭት በመፍጠራቸው የእርሻ ሥራ ተስተጓጉሏል” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ “የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችን የሱዳን ወታደሮች ሊያስተጓጉሉ አይገባም የሚል መልዕክት የፌደራሉ መንግስት ቢያስተላልፍም ሱዳኖች 'እሺ' ከማለት ያለፈ ሥራ አልሰሩም” ብለዋል፡፡ ሆኖም ሱዳን ወዳጅ ሀገር ከመሆኗ አንጻር ችግሩን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት እየተሞከረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

7. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የይቅርታና ምሕረት አዋጅ አጽድቋል፡፡ አዋጁ በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት የተላለፈባቸውን ተጠያቂነት የሚሰርዝ ነው፡፡ የፖለቲካ መብታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ በመንቀሳቀሳቸው ምክንያት በመንግስት ተወንጅለውና ክስ ቀርቦባቸው በስጋት ወደ ስደት የወጡ ዜጎች ምሕረት እንዲደረግላቸው ያግዛል፡፡ ከግንቦት 30/2010 በፊት የተዘረዘሩ የወንጀል ድርጊቶችን ፈጽመዋል በሚል በሕግ የሚፈለጉ፣ ጉዳያቸው በምርመራ ላይ የሚገኝ፣ የወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው፣ የጥፋተኝነት ፍርድ የተላለፈባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች እንዲሁም በኩብለላ ወንጀል የተከሰሱ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በአዋጁ ምሕረት ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ፓርላማው አዋጁን ባጸደቀው በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለዐቃቤ ሕግ ሪፖርት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስምንት የቦርድ አመራሮችን ሹመት አጽድቋል፡፡ የኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዲኤታ ካሳሁን ጎፌ የቦርዱ ሰብሳቢ ሲሆኑ፣ አባላቱ፡- ዳንኤል ክብረት፣ ተካ አባዲ፣ ጀሚላ ሽምቢሩ፣ አበበች ሸከቻ፣ በቀለ ሙለታ፣ ዮናስ አስናቀ እና ወንደሰን አንዷለም ሆነዋል፡፡

8. ትናንት ምሽት በበሔራዊ ቤተ መንግስት የእራት ግብዣ ተደርጓል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ለሶስት ቀናት በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት በስኬት በመጠናቀቁ፣ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና ማቅረብ የሚል ነበር፡፡ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ በክብር እንግድነት በተገኙበት ግብዣ ለጉብኝቱ አስተዋጽኦ አድርገዋል ለተባሉ ባለሥልጣናት፣ የጸጥታና ደሕንነት አካላት፣ አርቲስቶችና የሚዲያ ባለሙያዎች ሠርተፊኬት ተበርክቷል፡፡

ለወዳጆችዎ ያጋሩ SHARE SHARE
Post Reply

Return to “Ethiopian Daily News .. ኢትዮ ዜናዎች”