ሐሙስ ሐምሌ 5/2010 አበይት ዜናዎች - Wazema Radio ዋዜማ ሬዲዮ

Daily Ethiopian News, አዳዲስ ዜናዎች።
Forum rules
** When you post a News please include the Source link.
For More Ethiopian News please visit the Home Page
http://ethiopiaforums.com/
selam sew
Leader
Leader
Posts: 692
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

ሐሙስ ሐምሌ 5/2010 አበይት ዜናዎች - Wazema Radio ዋዜማ ሬዲዮ

Unread post by selam sew »

ለቸኮለ ሐሙስ ሐምሌ 5/2010 አበይት ዜናዎች - Wazema Radio ዋዜማ ሬዲዮ

1. ዛሬ ጧት በደቡብ ክልል፣ የም ወረዳ፣ ሳጃ ከተማ ከመስጊድ ይዞታ ጋር ተያይዞ በተቀሰቀሰ ግጭት ቢያንስ የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉ፣ በርካታዎች መቁሰላቸው፣ መንገድ መዘጋቱ ተነግሯል፡፡ ከሶስት ቀናት በፊት ለመድረሳ (ለእስልምና ሀይማኖት ትምሕርት ቤት) የሚሆን ቦታ እንዲሰጣቸው የጠየቁ ሰዎች ጥያቄያቸውን በሰላማዊ ሠልፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ ዛሬም በተመሳሳይ ጥያቄ በሚያቀርቡበት ወቅት ችግሩ በመከሰቱ፣ የፌደራል ፖሊስና ልዩ ኃይል በሥፍራው እንደነበሩ ተገልጿል፡፡ የከተማዋ ባለሥልጣናት ጉዳዩ በወረዳው የማይፈታ በመሆኑ ወደ ክልል መላኩን ገልጸው በዛሬው ግጭት የደረሰው አደጋ እየተጣራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡


2. የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ዛሬ ባወጣው መግለጫ የተኩስ አቁም ማወጁን አሳውቋል፡፡ ከመንግስት ጋር የተጀመረውን የሠላም ንግግር ለማሳካት ይረዳል በሚል እምነት በጊዜያዊነት ተኩስ ማቆሙን ያስታወቀው ኦነግ ከተጀመረው የሰላም ውይይት መልካም ነገር ሊኖር ይችላል የሚል ተስፋ እንዳለው ጠቁሟል፡፡ የኦነግ ሊቀ መንበር ዳውድ ኢብሳ በሳምንቱ መጀመሪያ በአስመራ ከተማ ከጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተው የተነጋገሩ ሲሆን፣ ግንባሩ ከመንግስት ጋር የሚያደርገው ቀጣይ ንግግር ከሀገር ውጪ እንዲሆን ከስምምነት ደርሰዋል፡፡

3.የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ አዲስ አበባ እንደሚመጡ ተዘገበ፡፡ ዜናውን ዛሬ ከምሳ በፊት ቀድሞ ያሰራጨው “የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት” ከ30 ደቂቃ በኋላ መረጃውን ከገጹ አጥፍቶታል፡፡ ቅዳሜ ረፋድ ኢሳይያስ አዲስ አበባ እንደሚገቡ የገለጸው ፕሬስ ድርጀት “የፕሬዚዳንቱን ጉብኝት የተሳካ ለማድረግ ከወዲሁ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ምንጮቻችን ገልጸውልናል፤ የኤርትራው ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝት የተጀመሩ ለውጦችን አጠናክሮ ያስቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል” የሚል ማብራሪያ አቅርቦ ነበር፡፡ በመንግስት ይዞታ ሥር የሚገኘው የዜና ተቋም ዜናውን ከገጹ እንዲያጠፋ የተደረገው ከጸጥታ ሥጋት ጋር በተያያዘ ሊሆን እንደሚችል የሚገልጹ አሉ፡፡ ሌሎች ገለልተኛ መገናኛ ብዙሀን ኢሳይያስ ወደ አዲስ አበባ እንደሚያመሩ ዘግበዋል፡፡

4. በሌንጮ ለታ የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) እና በከማል ገልቹ (ሜጀር ጄኔራል) የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት አንድነት ግንባር (ኦነአግ) በምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ፓርቲ ሆኖ ለመመዝገብ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ገለጹ፡፡ ሁለቱም ፓርቲዎች በሠላማዊ እንቅስቃሴ ለመሳተፍ የሀገር ውስጡን የፖለቲካ ሂደት በማጥናት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡ የኦዴግ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሌንጮ ባቲ ከመንግስት ጋር የሚደረገውን ድርድር ጨርሰው ፓርቲያቸውን በማስመዝገብ ሂደት ምዕራፍ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ ከማል ገልቹ (ሜ/ጄ) በበኩላቸው “በሕጋዊ ፓርቲነት ለመመዝገብ ሂደቱን ለመጀመር ጥያቄ አቅርበን መልስ እየተጠባበቅን ነው” ብለዋል፡፡

5. የቀድሞው ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ በዚምባብዌ የምርጫ ታዛቢ ልዑክ መሪ ሆነው ሐራሬ ሊሄዱ ነው፡፡ ኃይለማርያም ጁላይ 30/2018 በዚምባብዌ የሚካሄደውን ምርጫ ለመታዘብ ከሚያመራው ሁለት የአፍሪካ ሕብረት ቡድን አንደኛውን እንዲመሩ በሕብረቱ ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ተመርጠዋል፡፡ ሕብረቱ ኃይለማርያምን “በሀገራቸው አልፎም በአሕጉሪቱ ሠላምና መረጋጋት ለማምጣትና የዲሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት ባደረጉት አስተዋጽኦ” እንደመረጣቸው ገልጿል፡፡ በሌላ በኩል በአፍሪካ ሕብረት የተመድ ዋና ጸሐፊ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት ሳሕለወርቅ ዘውዴ ዛሬ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለሕብረቱ ኮሚሽነር አቅርበዋል፡፡

6. “በአማራ ክልል ሠላም እንዲናጋ ሕወሐት ምክንያት ሊሆን አይችልም” ያሉት ርዕሰ መስተዳድር ገዱ አንዳርጋቸው የብአዴን የቀድሞ አመራሮችም ምክንያት ሊሆኑ እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር “…በክልሉ ሠላምን የሚያናጋ የውጪ ኃይል የለም፤ ለክልሉ ጥፋትም ሆነ ልማት ተጠያቂዎች እኛ ነን፤ ጣትን ወደ ውጪ መቀሰር አዋጪ አይደለም፤ ደብረ ማርቆስ ላይ የተከሰተው ብጥብጥ ራስን በራስ የማጥፋት እንቅስቃሴ ነው፤ እጅ መቀሰር የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ አይደለንም” ነው ያሉት፡፡ በነገራችን ላይ በደብረማርቆስ ትናንት የተጀመረው ግርግር ዛሬም ቀጥሎ የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ ውሏል፤ ከቀትር በኋላ በሀገር ሽማግሌዎች ጥረት አንጻራዊ ሠላም መስፈኑ ተጠቁሟል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ከነገ በስቲያ ቅዳሜ ለገዱ አንዳርጋቸው የክብር ዶክትሬት ያበረክታል፡፡

7. የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ሀገር ውስጥ ገብቶ በሰላማዊ ፖለቲካ መድረክ እንዲንቀሳቀስ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ጥሪ አቀረቡ፡፡ እስካሁን ለተፈጸመው ስሕተት ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ የክልሉ ምክር ቤት ጉባዔ ትናንት በጅግጅጋ ሲጀመር ርዕሰ መስተዳድሩ አብዲ መሐመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ) ጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ በአጭር ጊዜ ላከናወኗቸው ተግባራት ክልሉን የሚመራው ኢሶዴፓ ክብር እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡ በአስገድዶ መድፈርና በነፍስ ማጥፋት ከታሰሩት በቀር በክልሉ ያሉ 150 እስረኞች በሙሉ መለቀቃቸው፣ አስራ ሠባቱ የኦብነግ አባላት መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ አብዲ ኢሌ ትናንት በተሰራጨ የቪዲዮ ቃለ ምልልሳቸው… የሀገሪቱ ደሕንነት ኃላፊ የነበሩት አቶ ጌታቸው አሰፋን በስም ጠቅሰው በሥራቸው ጣልቃ በመግባት፣ ፕሬዚዳንት እስከ መሾምና መሻር የሚደርስ ትዕዛዝ ይሰጡ ነበር ሲሉ ስሞታ አቅርበዋል፡፡

8. በዩናይትድ ስቴትስ የውጪ መስሪያ ቤት አንጋፋ የሚባሉትና የሀያ ሰባት ሽልማቶች ባለቤት የሆኑት ዶናልድ ያማማቶ በሶማሊያ አምባሳደር ተደርገው ተሰየሙ። ያማማቶ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ሰርተዋል። በምስራቅ አፍሪቃ ፖለቲካዊ ቀውሶችን ለመፍታት ስማቸው ቀድሞ የሚጠራው ያማማቶ ፈረንሳይኛ ፣ቻይና (መንደሪን)ና እና ጃፓንኛ ይናገራሉ። በቅርቡ ኢትዮጵያና ኤርትራን ለማቀራረብ በተደረገው ጥረትም ተሳታፊ ነበሩ።
Post Reply

Return to “Ethiopian Daily News .. ኢትዮ ዜናዎች”