ረቡዕ ሐምሌ 4/2010 አበይት ዜናዎች- ከዋዜማ

Daily Ethiopian News, አዳዲስ ዜናዎች።
Forum rules
** When you post a News please include the Source link.
For More Ethiopian News please visit the Home Page
http://ethiopiaforums.com/
selam sew
Leader
Leader
Posts: 558
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

ረቡዕ ሐምሌ 4/2010 አበይት ዜናዎች- ከዋዜማ

Unread post by selam sew » 11 Jul 2018 13:36

ረቡዕ ሐምሌ 4/2010 አበይት ዜናዎች- ከዋዜማ ለቸኮለ!

1. የሶማሌ ክልል ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የጎሳ መሪዎች ዛሬ በአዲስ አበባ እያካሄዱት የነበረ ኮንፈረንስ በሁከትና ረብሻ ተቋጨ፡፡ ቦሌ ፍሬንድሺፕ ሆቴል የተዘጋጀውን “…የሶማሌ ሕዝብ እናድን መድረክ ኮንፈረንስ” ያስተባበረው ኮሚቴ አስቀድሞ ባሠራጨው መግለጫ የስብሰባው ዓላማ፣ በክልሉ አምባገነንነት አስፍነዋል ያላቸው “የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የፓርቲው አመራሮች ከሥልጣን እንዲወርዱና ስልጣን ለሕዝቡ ተመልሶ ሕዝባዊ መንግስት እንዲቋቋም መጠየቅ” መሆኑን ነበር የጠቆመው፡፡ ስብሰባው ከተጀመረ በኋላ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ ኢሌ ፎቶ የታተመበት ቲሸርት የለበሱ ወጣቶች ወደ ሆቴሉ በመግባት በኮሚቴው አባላትና በሀገር ሽማግሌዎች ላይ ድብደባ በመፈጸማቸው ተቋርጧል፡፡ በአካባቢው የነበሩ ፖሊሶች ሁከቱን ባለማስቆማቸው ስብሰባው በሁከት ተበትኗል፡፡

በሌላ በኩል የክልሉ ፕሬዚዳንት አብዲ ኢሌ በትናንትናው ዕለት “ጄል ኦጋዴን” የተሰኘውን የማሰቃያ እስር ቤት በመጎብኘት ወደ መስጊድነት እንዲለወጥ ትዕዛዝ መስጠታቸው፣ የቀድሞ የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽነር ጨምሮ በእስር የሚገኙ ባልደረቦቻቸው እንዲፈቱ ትዕዛዝ መስጠታቸው ተገልጿል፡፡ የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ርዕሰ መስተዳድሩ በተገኙበት በጅግጅጋ መደበኛ ስብሰባውን ጀምሯል፡፡

2. ዛሬ በደብረ ማርቆስ ከተማ በተቀሰቀሰ ሁከት በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል። የሁከቱ መንስዔ "የበረከት ስምኦን በደብረማርቆስ መገኘት" እንደሆነ ተገልጿል። በረከት በከተማይቱ ጎዛምን ሆቴል አርፈዋል የሚለው ወሬ ከተዛመተ በኋላ የተሰበሰቡ ወጣቶች የቀድሞው ባለስልጣን እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል። በረከት በሆቴሉ አለመኖራቸው ሲገለጽላቸው የሆቴሉን የህንጻ መስታወት በድንጋይ ሠባብረዋል። በአቅራቢያ የነበረ መኪናም በእሳት ጋይቷል። የምስራቅ ጎጃም ዞን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ሽፈራዉ አየለ ሁከቱ የተነሳው ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ በመዛመቱ መሆኑን ለክልሉ መገናኛ ብዙሀን ተናግረዋል፡፡

3.ከቅዳሜ ሰኔ 30/2010 በኋላ ለዕረፍት የተበተነው ፓርላማ ለአስቸኳይ ስብሰባ ስለሚፈለግ አባላቱ ከአዲስ አበባ ርቀው እንዳይሄዱ ተነግሯቸዋል ተብሏል፡፡ በኢትዮጵያና ኤርትራ መሪዎች የሠላም ስምምነት ከተደረገ በኋላ አንዳንዶቹ ጉዳዮች በአዋጅ መጽደቅ ስለሚገባ፣ ፓርላማው እነዚህን ለማጽደቅ ሲባል በዕረፍት ጊዜው እንደሚሰበሰብ ተገልጿል፡፡ ፓርላማው በይደር ያቆያቸው የምሕረት አዋጅና የስደተኞች ጉዳይ አዋጅን በዚሁ ጊዜ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

4. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ሐምሌ 11/2010 አሜሪካ ከሚገኘው ሲኖዶስ አባቶች ጋር የዕርቀ ሠላም ጉባዔ እንደሚካሄድ አሳውቋል፡፡ ለ26 ዓመታት የራቀው ሠላም እልባት እንዲያገኝ ለማገዝ ሦስት ሊቃነ ጳጳሳትን በልዑክነት መሰየሙን አሳውቋል፡፡ “የዕርቀ ሠላሙ ሂደት በውጪ ሀገር የሚገኙ አባቶች ወደ ሀገር የሚገቡበት፣ የቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚመለስበት እንዲኾን፣ በመላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትና አድባራት፣ ካህናትና ምዕመናን በጸሎት እንዲተጉ” ቅዱስ ሲኖዶስ አሳስቧል፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ወደ ፍጹም ሰላም እንዲመጡ እየተከናወነ ያለውን ጅምር ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደምትደግፈው በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

5. የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ዛሬ ጉባዔውን በአዳማ ሲያጠናቅቅ… የአካባቢ ምርጫ ማድረግ የማይቻል በመሆኑ ለቀጣዩ ዓመት መሻገሩን ገልጿል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ የሚገኙ የወረዳ፣ የከተማዎችና የቀበሌ ምክር ቤቶች ለአንድ ዓመት በኃላፊነታቸው እንደሚቀጥሉም አሳውቋል፡፡

6. ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከውጪ ንግድ 4.7 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት ዐቅዳ ያገኘችው ግን 2.5 ቢሊየን ዶላር መሆኑ ታውቋል፡፡ ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው ከኢንዱስትሪ ምርት የተገኘ ገቢ 418 ሚሊየን ዶላር ነው፡፡ ከፍተኛ ገቢ የተመዘገበው ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ፣ ከባሕር ዛፍ፣ ከቅባት እህሎች፣ ከሻይ ቅጠልና ከጫት ንግድ ነው፡፡

7. ከግንቦት 5/1990 ዓ.ም ጀምሮ የተዘጋው የኢትዮጵያና ኤርትራ አዋሳኝ አየር ክልል ለትራንስፖርት ክፍት እንዲሆን ተጠየቀ፡፡ በጦርነቱ ማግስት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን በጻፈው ደብዳቤ ነበር… ክልሉ የጦር ቀጠና በመሆኑ ዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ለትራንስፖርት ዝግ እንዲያደርግ የጠየቀው፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ ሳይሆን በኤርትራ ሠማይ አቋርጠው ወደ አውሮፓና መካከለኛው ምስራቅ በረራ የሚያደርጉ አየር መንገዶች በሙሉ… የጉዞ መስመር በመቀየራቸው ለተጨማሪ ወጪ ተዳርገው ቆይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ ቀጥታ በረራ ስለሚያደርግ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን የተዘጋው አየር ክልል እንዲከፈት ለዓለም አቀፉ ተቋም በደብዳቤ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ዓለም አቀፉ የአቪዬሽን ድርጅት ጥያቄው በቀረበለት በጥቂት ቀናት ውስጥ የተዘጋውን የአየር ክልል የሚከፍት በመሆኑ፣ ተግባራዊ ሲደረግ ሲቪል አቪዬሽን ለሁሉም ሀገራት ይሕንኑ የሚያበስር ማስታወቂያ ይልካል፡፡

8. በኢትዮጵያ የሚገኙ የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚዎች፣ የሠላም ስምምነቱን ተከትሎ ሕልውናቸው ሥጋት ላይ መውደቁን ገለጹ፡፡ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የሻዕቢያ ተቃዋሚዎች “…የኢትዮጵያ መንግስት ነፍጥ ላነሱበት ኃይሎች ምሕረት በማድረግ ወደ ሠላማዊ ትግል እንዲገቡ ሁኔታዎችን ሲፈቅድ፣ የኤርትራ ተቃዋሚ ኃይሎች ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይገባዋል ብሎ አልመከረም፤ የሠላም ስምምነቱን ጠልተን ሳይሆን ሁሉን አቀፍ የሠላም ስምምነት ተደርጎ ቢሆን ለሁለቱም ሕዝቦች ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን በመረዳት ያቀረብነው ጥያቄ ነው” ማለታቸው ተዘግቧል፡፡

SHARE SHARE SHARE SHARE

Post Reply

Return to “Ethiopian Daily News .. ኢትዮ ዜናዎች”