የስኞ ሐምሌ 2/2010 አበይት ዜናዎች : Wazema Radio News

Daily Ethiopian News, አዳዲስ ዜናዎች።
Forum rules
** When you post a News please include the Source link.
For More Ethiopian News please visit the Home Page
http://ethiopiaforums.com/
selam sew
Leader
Leader
Posts: 692
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

የስኞ ሐምሌ 2/2010 አበይት ዜናዎች : Wazema Radio News

Unread post by selam sew »

የስኞ ሐምሌ 2/2010 አበይት ዜናዎች


1. ጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ እና ፕ/ት ኢሳይያስ አፈወርቂ ዛሬ ጧት በሁለቱ ሀገራት መሐል የነበረው ጦርነት በይፋ መቆሙን የሚያበስር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ዐብይ የአስመራ ጉብኝታቸውን አጠናቀው አዲስ አበባ ተመልሰዋል፡፡ ዛሬ ጧት የተፈረመው ስምምነት አምስት አበይት ክፍሎች እንዳሉት የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል አብራርተዋል፡፡ እነዚህም 1) የጦርነት ዘመን አክትሞ አዲስ የሠላምና ወዳጅነት መስፈን፣ 2) ሁለቱም ሀገራት በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማሕበራዊ፣ ባሕላዊና ጸጥታ ጉዳዮች ጥብቅ ትስስር መፍጠረ፣ 3) የትራንስፖርት፣ ንግድ እና ቴሌኮሙኒኬሽን ግንኙነትን መቀጠልና የዲፕሎማቲክ ግንኙነትን ማደስ፣ 4) በአልጀርስ ስምምነት መሰረት የድንበር ውሳኔውን መተግበር እንዲሁም 5) የአካባቢውን ሠላም፣ ልማትና ጸጥታ ለማስከበር ሀገራቱ በጋራ መስራት ይኖርባቸዋል የሚሉ ናቸው፡፡

2. የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት በኤርትራ ላይ የጣለውን ማዕቀብ እንዲያነሳ ኢትዮጵያ በይፋ ጥያቄ አቀረበች። ይህም የኤርትራና ኢትዮጵያ መሪዎች ዛሬ ጧት ከፈረሙት ስምምነት ውስጥ የሚካተት ነው። ጠ/ሚ ዐብይ አህመድ ዛሬ አመሻሹ ላይ ከተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጋ በተወያዩበት ወቅት በኢትዮ-ኤርትራ ዕርቀ ሠላም ዙሪያ ተወያይተዋል።

3. ኢትዮጵያና ኤርትራ ያደረጉትን ስምምነት የሚከታተል እና ለተግባራዊነቱ የሚሰራ ብሔራዊ ኮሚቴ በዛሬው ዕለት ተመስርቷል፡፡ አዲሱ ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ በሥሩ ንዑሳን ኮሚቴዎችን ያዋቅራል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ዜጎች የቪዛ ጉዳይ፣ የጦር ምርኮኞችና የእስረኞች ልውውጥ፣ የአየረ መንገድና ታሪፍ ማውጣት… ወዘተ የመሳሰሉትን ጉዳዮች እየተነጋገረ ወደፊት መፍትሔ የሚሰጠው ይሕ የቴክኒክ ኮሚቴ ይሆናል ማለት ነው፡፡ የአልጀርስ የድንበር ስምምነትና አተገባበርንም ይከታተላል፡፡ በሁለቱ ሀገራት ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሚመራው የቴክኒክ ኮሚቴ የወደብ አጠቃቀምን ጉዳይ ይመለከታል፤ ወደብን በጋራ ማልማት ወይስ በኪራይ መጠቀም የሚለውን በመፈተሽ ውሳኔ ያሳልፋል፡፡ ሁለቱ ሀገራት ከሌሎች ጎረቤቶች ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት፣ ኤርትራ የተጣለባትን ማዕቀብና መገለል እንዲነሳ እትዮጵያ ስለምታደርገው እንቅስቃሴ፣ በሁለቱም ሀገራት ኤምባሲና ቆንስላዎች መከፈት የመሳሰሉ ጉዳዮችም በኮሚቴው ይታያሉ፡፡

4. ጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ በአስመራ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) መሪ ኦቦ ዳውድ ኢብሳ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተው መነጋገራቸው ተረጋግጧል፡፡ የውይይታቸው ዝርዝር ይፋ ባይደረግም ቀጣይ ድርድር በውጪ ሀገር ይካሄዳል፡፡ ባሳለፉት ሳምንታት በምዕራብ ወለጋና በምስራቅ ኢትዮጵያ የኦነግን ባንዲራ የያዙ ወጣቶች በጠመንጃ የተደገፈ የኃይል እንቅሰቃሴ ያካሄዱ ሲሆን፣ የኦነግ አመራሮች ግን ይሕ እንቅስቃሴ ከግንባሩ ዕውቅና ውጪ መሆኑን ሲገልጹ ሠንብተዋል፡፡ በአስመራ የከተሙት ዳውድ ኢብሳ በቅርቡ በሰጡት ማብራሪያ “…የኢሕአዴግ መንግስት ብቻውን የመፍትሔ አካል መሆን ስለማይችል ሁሉም ቡድኖችን የሚያስተናግድ የሽግግር መንግስት መመስረት ይኖርበታል” ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ ፓርላማ ኦነግን ከሽብርተኛ ዝርዝር እንዲወጣ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

5. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ወደ አስመራ ቀጥታ መደበኛ በረራ ይጀምራል፡፡ ከአዲስ አስመራ ቀጥታ በረራ በመቋረጡ አየር መንገዱ ማግኘት የነበረበትን ብዙ ገንዘብ አጥቷል፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት በሚጀመረው የአውሮፕላን ጉዞ መንገደኞች የመግቢያ ቪዛ የሚጠየቁ ሲሆን፣ ወደፊት ያለ ቪዛ መግባት ስለሚቻልበት ሁናቴ ቀጣይ ውይይት ይካሄዳል፡፡

6. ሰኔ 16/2010 በመስቀል አደባባይ ከደረሰው ፍንዳታ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ እስረኞች ዛሬ በድጋሚ ፍርድ ቤት ቀርበው የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል፡፡ ምክትል ኮሚሽነር የነበሩት ግርማ ካሳ ለፍርድ ቤቱ ባሰሙት አስተያየት “ጠ/ሚ ዐብይ አህመድ ጥፋተኛ እንዳልሆንኩ ሲያውቁ ይቅርታ ይጠይቁኛል” ብለዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ አስራ አንድ የምርመራ ቀን በመፍቀዱ ተጠርጣሪዎቹ ለሐምሌ 13/2010 ተቀጥረው ወደ እስር ቤት ተመልሰዋል፡፡ በሌላ በኩል በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ባለፈው ሐሙስ ፍርድ ቤት የቀረቡት የቀድሞው የኢንሳ ምክትል ዳይሬክተር ብንያም ተወልደ በጊዜ ቀጠሮ ቆይተው ከምርመራ በኋላ ሐምሌ 9/2010 እንዲቀርቡ ታዟል፡፡

7. የኦሮሚያ ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) ዛሬ በአዳማ ጉባዔውን ጀምሯል፡፡ “ለውጡን ለመቀልበስ የሚደረጉ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች ለማምከንና እንቅፋቶችን ለማስወገድ እንሰራለን” ያሉት የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ እሸቱ ደሴ “በክልሉ ሠላምና የሕግ የበላይነት እንዳይረጋገጥ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በመታገል የጨፌው አባላት ከሕዝብ ጋር እንዲሆኑ” ጠይቀዋል፡፡ የክልሉ ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ የ2010 ዓ.ም በጀት ዓመት ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

8. በአሜሪካ የተለያዩ ከተማዎች ኮንሰርት በማቅረብ ላይ የሚገኘው ቴዲ አፍሮ በቅርቡ በአዲስ አበባ የሙዚቃ ዝግጅት እንደሚኖረው ይፋ አድርጓል፡፡ ድምጻዊው ከወራት በፊት በርዕሰ መዲናይቱ ሊያካሂደው የነበረው ኮንሰርት በከንቲባው ጽ/ቤት እምቢተኝነትና በጸጥታ ኃይሎች ተባባሪነት መሠረዙ አይዘነጋም፡፡ ያኔ የቴዲን ኮንሰርት ሊያዘጋጅ የነበረው ጆርካ ኢቨንትስ ዛሬ እንዳሳወቀው ከሆነ በአስመራ ከተማ ቀኑ ያልተቆረጠለት የሙዚቃ ትርዒት እንደሚያዘጋጅ ጠቁሟል፡፡ በዝግጅቱ ማሕሙድ አሕመድን ጨምሮ ኢትዮጵያውያን ድምጻውያን ይሳተፋሉ ብሏል፡፡

ለወዳጅዎ ያጋሩ-SHARE

Source: Wazema Radio Facebook
Post Reply

Return to “Ethiopian Daily News .. ኢትዮ ዜናዎች”