አየር መንገዱ በቀጣዩ ሳምንት ወደ ኤርትራ በረራ ይጀምራል

Daily Ethiopian News, አዳዲስ ዜናዎች።
Forum rules
** When you post a News please include the Source link.
For More Ethiopian News please visit the Home Page
http://ethiopiaforums.com/
selam sew
Leader
Leader
Posts: 558
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

አየር መንገዱ በቀጣዩ ሳምንት ወደ ኤርትራ በረራ ይጀምራል

Unread post by selam sew » 09 Jul 2018 11:52

አየር መንገዱ በቀጣዩ ሳምንት ወደ ኤርትራ በረራ ይጀምራል

Image

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 2 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀጣዩ ሳምንት ወደ ኤርትራ በረራ ሊጀምር ነው።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እንዳሉት፥ አየር መንገዱ በቀጣዩ ሳምንት ወደ ኤርትራ በረራውን ይጀምራል።

በረራው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኤርትራ ባደረጉት ጉብኝት ሁለቱ ሃገራት የደረሱት ስምምነት አካል መሆኑ ተነግሯል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከጉብኝቱ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፥ ሃገራቱ የደረሷቸው ስምምነቶችን የሚከታተል እና ለተግባራዊነቱ የሚሰራ ብሄራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ መቋቋሙን ተናግረዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ ኮሚቴው የድንበር ጉዳይን ጨምሮ የአልጀርስ ስምምነት አተገባበርና መሰል ጉዳዮችን የሚከታተል ይሆናል።

የቴክኒክ ኮሚቴው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ማህበራዊና መሰል ጉዳዮችን በዝርዝር የሚመለከቱ ንዑስ ኮሚቴዎችን ያዋቀረ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በሃገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሚመራው የቴክኒክ ኮሚቴ የተደረሱ ስምምነቶችን ተፈጻሚነት ከመከታተል ባሻገር፥ የወደብ አጠቃቀምን በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮችን የሚመለከት ይሆናልም ነው ያሉት።

በዚህም ወደቡን በጋራ አልያም በኪራይ መጠቀም የሚቻልበትን አግባብ እንዲሁም ሃገራቱ በሚጀምሩት የአየርና የየብስ ትራንስፖርት ታሪፍ ላይም ዝርዝር ጉዳዮችን ይመለከታል ብለዋል።

በቀጣዩ ሳምንት በሚጀመረው የአውሮፕላን ጉዞ መንገደኞች መግቢያ ቪዛ የሚጠየቁ ሲሆን፥ በቀጣይ በሚኖረው ጉዞ ላይ መንገደኞች ያለ ቪዛ መግባት በሚችሉበት ሁኔታ ላይም ኮሚቴው እንደሚወያይ ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው በሁለቱ ሃገራት ጦርነት ወቅት የተያዙ የጦር ምርኮኞች እና እስረኞችን ጉዳይ በተመለከተም፥ ኮሚቴው ጥናት በማድረግ የውሳኔ ሃሳብ እንደሚያቀርብም አንስተዋል።

በሁለቱ መሪዎች ውይይት ወቅትም ሃገራቱ ኤርትራ ወደ ምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ተመልሳ ለቀጠናው ሰላምና ብልፅግና የራሷን ድጋፍ እንድታደርግ ስምምነት መደረሱንም ሚኒስትሩ አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም ኤርትራ እንደ ጅቡቲ ካሉ የቀጠናው ሃገራት ጋር ሰላም እንድትሆን ኢትዮጵያ እንደምትሰራም አስታውሰዋል።

በተጨማሪም በአለም አቀፉ መድረክ ኤርትራ የተጣለባት ማዕቀብ እንዲነሳና መገለሉ እንዲቆምም ኢትዮጵያ ትሰራለች ነው ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ።

አሁን ላይ ሁለቱ መሪዎች በደረሱት ስምምነት መሰረትም በየሃገራቱ ኤምባሲ የመክፈት ሂደቱ የተጀመረ ሲሆን፥ ከቤተሰቦቻቸው የተለያዩ የሁለቱ ሃገራት ዜጎችም ከቤተሰቦቻቸው መቀላቀል እንደሚችሉም አስረድተዋል።

በቀጣይም የሁለቱ ሃገራት ዜጎች የነጻ ቪዛ ጉዳይ በኮሚቴው ታይቶ እልባት የሚያገኝ ይሆናል ተብሏል።

መሪዎቹ በስምምነታቸው የሃገራቱን ብሎም የህዝቦችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ በሰጡት መግለጫ አብራርተዋል።

ሚኒስትሩ ከደቡብ ሱዳን ጋር በተያያዘ በሰጡት መግለጫ ተቀናቃኝ ሃይሎች አሁን ላይ ለደረሱት ስምምነት የኢትዮጵያ ሚና ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።

በመንግስታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ ዶክተር ተቀዳ አለሙ ጋር በተያያዘም፥ የስራ ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል ነው ያሉት።

ከዛ ውጭ ግን ከልዩ መልዕክተኛው ጋር በተያያዘ የሚናፈሱ ወሬዎች ከእውነት የራቁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዚህ ረገድ የሰላም ሽልማት ካለ፥ ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መውሰድ አለባቸው ብላ ታምናለችም ነው ያሉት።

በባሃሩ ይድነቃቸው

Post Reply

Return to “Ethiopian Daily News .. ኢትዮ ዜናዎች”