ሞዴሏ ሊያ ከበደ የምትተውንበት ፊልም...

Daily Ethiopian News, አዳዲስ ዜናዎች።
Forum rules
** When you post a News please include the Source link.
For More Ethiopian News please visit the Home Page
http://ethiopiaforums.com/
Post Reply
User avatar
selam
Leader
Leader
Posts: 175
Joined: 25 Aug 2009 01:59
Contact:

ሞዴሏ ሊያ ከበደ የምትተውንበት ፊልም...

Unread post by selam » 12 Oct 2009 17:47

ሞዴሏ ሊያ ከበደ የምትተውንበት ፊልም... Image
Sunday, 11 October 2009
ሞዴሏ ሊያ ከበደ የምትተውንበት ፊልም በአውሮፓ ለእይታ ይበቃል

በጋዜጣው ሪፖርተር

ኢትዮጵያዊቷ ሞዴል ሊያ ከበደ የምትተውንበትና "ዘ ደዘርት ፍላወር" (የበረሃዋ አበባ) የተሰኘ ፊልም ለእይታ እንደሚቀርብ ዶቸ ቬሌ በድረ ገጹ ዘገበ፡፡

ሰሞኑን በጀርመን የሚቀርበው ፊልም፣ በዋሪስ ዳሪ ሲዘጋጅ በአፍሪካ ሴቶች ላይ የሚፈጸመው ግርዛት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት መሆኑ የሚያሳይ መሆኑ ታውቋል፡፡ የጀርመንና የአሜሪካ ዜግነት ባላት የፊልም ዳይሬክተር በተቀናበረው ፊልም ኢትዮጵያዊቷ ሞዴል ሊያ ከበደ ተዋናይ ሆናበታለች፡፡
የፊልሙ መነሻ ድርሰት፣ ሶማልያዊቷ ዋሪስ ዳሪ ከጻፈችው ግለታሪኳ የተወሰደ ሲሆን፣ መጽሐፉ በተለያዩ አገሮች ውስጥ በከፍተኛ ቁጥር የተሸጠ እንደሆነም ይነገርለታል፡፡ በ1957 ዓ.ም. ግድም የተወለደችው ደራሲዋ ዋሪስ ዳሪ፣ 13 ዓመት ሲሞላት ቤተሰቦችዋ ሊድሯት ማሰባቸውን በማወቋ ከገጠር ወደ ሞቃዲሾ ከተማ በመሸሽ፣ በተፈጠረላት አጋጣሚም እንግሊዝ በመግባት ለፎቶ ሞዴልነት ለመብቃትና ዝናን ለማትረፍ ችላለች፡፡

ዝናዋ በመናኘቱ ምክንያት ላነጋገራት ቢቢሲ ጋዜጠኛ በሰጠችው ምላሽ፣ የሶማሊያን በረሃ በባዶ እግሯ አቋርጣ፣ ሞቃዲሾ መድረሷ ከዚያም ወደ ለንደን በቤት ሠራተኛነት መምጣቷን በተለይ ደግሞ ለማታውቀው ወንድ፣ ቤተሰቦቿ ሊድሯት በዝግጅት ላይ እንደነበሩና ለዝግጅቱም መገረዝዋን በመግለጽዋ የምዕራቡን ዓለም ትኩረት እንደሳበች ዶቸ ቬሌ ዘግቧል፡፡

አጋጣሚውም ለዋሪስ ዳሪ ከሞዴልነት ተግባርዋ ጎን ለጎን የሴት ልጅ ግርዛትን በመቃወምና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት መሆኑ በመግለጽ የተባበሩት መንግሥታት ልዩ አምባሳደር ለመሆን አስችሏታል፡፡

ውጣ ውረዷ "ዘ ደዘርት ፍላወር" (የበረሃዋ አበባ) የተሰኘውን ግለታሪክ መጻፍ እንዳስቻላትና ለፊልም እንደበቃም ዜናው አመልክቷል፡፡ የደራሲትና የውቢት ሶማሊያዊት ታዋቂ ሞዴል ታሪክን የያዘውና ሰሞኑን በጀርመንና በሌሎች የአውሮፓ አገሮች ለመጀመሪያ ጊዜ የሚታየው ፊልም፣ መሪ ተዋናይዋ ኢትዮጵያዊቷ ታዋቂ ሞዴል ሊያ ከበደ ነች፡፡ በጀርመናዊት ፊልም ዳይሬክተር የተቀናበረው ፊልም የሁለት ሰዓት ርዝመት ሲኖረው በጅቡቲ፣ በኒውዮርክ፣ በኮለኝና በሙኒክ ከተማዎች ቀረፃው ተካሂዷል፡፡

በዶቸ ቬሌ ድረ ገጽ አዘጋገብ፣ ፊልሙ እንደ ሰንደሪላ ታሪክ እልም ካለ ገጠር ወጥታ፣ በረሃን አቋርጣ ለሕይወት ታግላ በዓለም ታዋቂነትን ስላገኘች ሴት ታሪክ ይተርካል፡፡

ፊልሙ በአዳጊ አገራት በተለይም በአፍሪካ በሚታየው የሴት ልጅ ግርዛት ሰበብ በርካታ ሕፃናት በደም መፍሰስና በንጽህና ጉድለት ሳቢያ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ይተርካል፡፡ በፊልሙ ማብቂያ ጥናታዊ ዘገባዎች እንደሚገልጹት በቀን 6000 ልጃገረዶች እንደሚገረዙ ሲያሳይ፣ ይህም አጉል ልማዳዊ ድርጊት በመሆኑ መቅረት እንዳለበት በግልጽ ያስቀምጠዋል፡፡

ሶማሊያዊቷ ደራሲት ዋሪስ ዳሪ፣ "ከበረሃዋ አበባ" በማስከተልም "የአርብቶ አደሩ ልጅ"፣ "ሕመምተኞቹ ሕፃናት' እና "ለእናቴ ደብዳቤ" የተሰኙ መጻሕፍትን ለአንባብያን ማቅረቧ ታውቋል፡፡ ዋሪስ "የሴት ልጅ እንዳትገረዝ በሚለው መርኋ ጸንታ በዓለም ዙሪያ ቅስቀሳ በማካሄድ ላይ ስትሆን፣ በአውሮፓ ኅብረት ለበርካታ ጊዜ በመጋበዝ ንግግር ማድረጓንና ከፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኒኮላ ሳኮዚ፣ ከቀድሞ የሶቭየት ኅብረት መሪ ሚኻኤል ጎርባቾቭና ከቀድሞዋ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮንዶሊዛ ራይስ ሽልማት መቀበሏ ይታወቃል፡፡Image
Last edited by selam on 12 Oct 2009 19:53, edited 3 times in total.

User avatar
selam
Leader
Leader
Posts: 175
Joined: 25 Aug 2009 01:59
Contact:

Re: ሞዴሏ ሊያ ከበደ የምትተውንበት ፊልም...

Unread post by selam » 12 Oct 2009 18:06

ልመና የተሳካልን ¡ E-mail
Sunday, 11 October 2009

ደላላና መንገድ አይተጣጡም ብቻ ሳይሆን አይለያዩም፡፡ ሰሞኑን ቦሌ መስመር አንድ የድለላ ቀጠሮ ስለነበር ይዤ ከታክሲ የወረድኩት ሳይ ኬክ ቤት አካባቢ ስደርስ ነበር፡፡ የወረድኩበት ቦታ ጥንድ የውጪ ዜጎች በለማኝ ሕፃናት ተወረው ሳይ ክው ይበል ጠላትህ ክው አልኩኝ፡፡ ፈረንጆቹ በምልክት ዞር በሉልን ቢሉም ሕፃናቱ አልሰሟቸውም፡፡ ሰዎቹ ከወረራው ለማምለጥ ተወራጩ፣ ተርገፈገፉ፡፡ ሰሚ አላገኙም፡፡ የሚያደርጉት ቢያጡ ዝም ብሎ የቆመ ታክሲ ውስጥ ጥልቅ አሉ፡፡ እኔ በሁኔታው ስቅቅ አልኩኝ፡፡ ልጆቹ በፈረንጆቹ ድርጊት ተፍነከነኩ ወይም የተፍነከነኩ መሰለኝ፡፡ አይ" . . . ልጅነት፤ አሁን ይኼ ምን ያፍነከንካል?


መቼም ነገሩ ስቅቅ አለኝ ያልኩት ያለምክንያት አይደለም፡፡ ይህ መከረኛ ድህነታችን አሳቅቆ ባዶ አጥንታችንን ያስቀረን ዛሬ አይደለም መች ዛሬ ሆነና" ግን በስንት ውትወታ፣ ልመና አገራችንን ጎብኙ ብለን ያመጣናቸው ቱሪስቶች እንዲህ መሄጃ፣ መላወሻ ሲያጡ ከማየት የበለጠ ምን የሚያሳቅቅ ነገር አለ?

እስቲ አሁን በሞቴ፤ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና እያሉ መኩራራት፣ አረ ከዚህም አልፎ ማበጥ ብቻውን ምን ይፈይዳል? በአንድ በኩል ለማኙ፣ በሌላ በኩል የማያላውሰው ሽታ እንኳንስ የአፍሪካ . . . ብቻ ይቅር፡፡ ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል አይደለም ተረቱስ፡፡

ሳይ ኬክ ቤት አካባቢ ዓይኔን ከወዲያ ወዲህ ሳንከራትት አንድ ፖስተር ላይ ዓይኔ አረፈ፡፡ ፖስተሩ ቴዲ አፍሮ የሚካፈልበት የሙዚቃ ኮንሰርት ዛሬ እንደሚካሄድ ይናገራል፡፡ መፈክር ቢጤም ይዟል፡፡ መፈክሩ "ልመና ይብቃ" ይላል፡፡ ልመና ማብቃቱንስ ያብቃ፤ መለመን የሚወድ የለምና ፡፡ "ግን እንዴት?" ብሎ መጠየቅ ግድ ነው፡፡ ይሄ ድህነት አኝኮ እየተፋው ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልስ አለ፡፡ ጉልበቱና አቅሙ እያለው መሥራት ጠልቶ የሰው እጅ ሲቃርም የሚውልም አለ፡፡ በሽታ እና ዕድሜ አቅም የነሳውም አለ፡፡ የልመና ብዛቱ፣ ዓይነቱ የትየለሌ ቢሆንብኝ "አስቤ . . . አስቤ ሲደክመኝ ተውኩት" እንዳለው ወገኛ ትውት አደረኩት፡፡

እስቲ አሁን ማን ይሙት ማን የማይለምን፣ የማይመፀውት አለ? ማንም፡፡ መንግሥታችን የቁጥሩ ብዛት ላይ እየተሟገተም ቢሆን በየዓመቱ እየለመነ ስንዴ የሚሰፍርላቸው ወገኖች አሉን፡፡ መንግሥታችን ገቢና ወጪው የሰማይና የምድር ያህል እየሆነ አልጣጣም ቢለው ያው የዓመት በጀቱን ተበድሮ ተለቅቶ የእኛኑ ከርስ ይሞላል፡፡ ይኸው በልመና በሚመጣ ገንዘብና ስንዴ ፋፍተን፣ ሁሌም ለምለሚቷ አገሬን እየዘመርን ይኸው እንዳለን አለን፡፡

ብድርና ልመና የጊዜ፣ የቦታ ወሰን ሳይገድበው እንደጥላ ይከተለናል፡፡ አንዳንዱ የወር ደመወዙ ከልደታ-ባዕታ አላደርስ ሲለው "ለደመወዝ የሚመለስ ትንሽ ፍራንክ ይኖርሃል?" ይልሃል፡፡

ማንጠግቦሽም በአቅሟ የጎረቤት ሰዎች ሽሮና በርበሬ ልመና እንዳስመረራት ደጋግማ ስትናገር የሰማሁባቸው ቀናቶች ብዙ ናቸው፡፡ ምን ይደረግ በድህነት ተወልደን፣ በድህነት የምንሞት ምስኪን ሕዝቦች ነን፡፡ ምንይደረግ" ያለችንን ትንሿን በአግባቡ ቆጥበን፣ አብቃቅተን መኖር ያቃተን ነን፡፡ ምንይደረግ" ጥረን፣ ግረን፣ ለፍተን፣ ዛሬን ማቀንም ቢሆን ለነገ ብርሃን እንዲወጣልን የማንተጋ ራዕይ አልባ ነንና መቸገር ይነሰን?

አሁን ለታ ከባሻዬ ጋር ስንጫወት ያነሳሳናቸው ቁም ነገሮች በዓይነ ሕሊናዬ ውልብ አሉብኝ፡፡ ልብ በሉ" . . . ወጣቶች ለአቅመ አዳም/ሔዋን ከደረሱ በኋላ ያው ጊዜውን ጠብቀው ሦስት ጉልቻ ይመሠርታሉ፡፡ ይወልዳሉ፣ ይከብዳሉ፡፡ ጥንዶቹ ልጆቻቸውን ያሳድጋሉ ብቻ ሳይሆን በማሳደጋቸው ውለታ ያቆያሉ፡፡ ያ-ልጅ አድጎ ይጦረኛል ይላሉ፡፡ ልጆች በተራቸው ለአቅመ ሥራ ሲደርሱ ውለታ የመመለስ ግዴታ ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ በለጋ ዕድሜያቸው ስለራሳቸው፣ ስለኑሮአቸው ሳይሆን ስለወላጆቻቸው እያሰቡ፣ እየማቀቁ ይኖራሉ፡፡ የባሻዬ ጎረቤት ልጆች አንዱ የሆነው (ታላቅየው) አሜሪካ በዲቪ ከገባ ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በየጊዜው ዶላር ይልካል፡፡ እህቶቹ፣ ወንድሞቹ በዶላሩ ይኖራሉ ሳይሆን ይምነሸነሻሉ፡፡ . . .ዶላር ሳይልክ የዘገየ ወቅት ይዶለታል፡፡ "ዛሬ ሲያልፍለት . . ". ይባላል፡፡ ወንድም እንደተሳቀቀ . . . ላቡን እንደዘራ . . . እህቶቹም እንዳንጋጠጡ ይኸው አሉ፡፡ "ይኼ ልጅ መቼ ለራሱ ይኖር ይሆን?" ብዬ ሳስብ ሐዘን ከፊቴ ይቀድማል፡፡

በልመና፣ በጥገኝነት ታመናል፡፡ ታመናል ብቻም ሳይሆን ፈውስም አጥተናል፡፡ ከዚህ ደዌ እንኳንስ የአንድ ቀን የሙዚቃ ድግስ ቀርቶ የወርም፣ የዓመትም ቢሆን የሚፈውሰን ቢሆን ምንኛ በታደልን ነበር፡፡

በቅርቡ ያቺ መከረኛ ራዲዮኔ በአዲስ አበባ በልመና ሥራ የተሰማሩ ወገኖች ወደቀዬአቸው ተሸኙ ባለቺኝ ሰሞን አባ ከሠፈር ጠፉ፡፡ ያው እሳቸው ከቀዬአቸው ወጥተው በሠፈራችን አካባቢ ልመና ከጀመሩ ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ ከብዙዎች ጋር ይግባባሉ፡፡ የወለደ፣ የታመመ ይጠይቃሉ፡፡ ሐዘን ቤት ፈልገው ያስተዛዝናሉ፡፡ ያው እሳቸውም በፍቃደኝነት ወደቀዬአቸው ተሸኙ ከተባሉት አንዱ ነበሩ፡፡ በሄዱ በወሩ ግን አባን ሠፈራችን አገኘናቸው፡፡ ያው የሠፈሩ ሰው በየመንገዱ እያስቆመ አዋያቸው፡፡ ያለውንም እያስተዛዘነ ሰጣቸው፡፡ አባ የሚታረስ መሬት እንዳላቸው ሠፈሩ ሁሉ ያውቃል፡፡ "ካልለመንኩ ሰውነቴ ይቆራረጣል፣ ክፉ ደዌ አለብኝ" ይላሉ እንጂ የምልሰው፣ የምቀምሰው የለኝም አይሉም፡፡ ይሄን እኔም፣ ማጠግቦሽም፣ ጎረቤቶቻችንም፣ ሠፈርተኛውም እያወቀ ሁሌም የደንቡን ይሠጣቸዋል፡፡ እሳቸውም ሞልቶ ከተረፈ ምርቃት ያዥጎደጉዱታል፡፡ እናም አባን ከዚህ ሕይወት በአፈሳ ማላቀቅ ይቻላል? አይቻልም፣ አልተቻለምም፡፡ ድህነታችን በየዕለቱ እየሸረፈን . . . እየሸረፈን ተገፍተን ጎዳና እየወጣን ነው፡፡ ድህነታችን ሲቀረፍ . . . አዎ" ድህነታችን ሲቀረፍ ወደ እውነተኛ ቤታችን እንመለሳለን፡፡ በየመንገዱም በወገኖቻችን የልመና ወረራ ከማፈር እንድናለን፡፡ አቦ" ደህና ሁኑልኝ፡፡ ሠላም፡፡

Post Reply

Return to “Ethiopian Daily News .. ኢትዮ ዜናዎች”