Page 24 of 29

Re: የጀምጀም ልጆች መገናኛ

Posted: 13 Apr 2013 00:21
by ሞፊቲ
ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን::


ውድ ጂግሳ ሰንበትበት ብለህ ብትመጣም ዋናው አለመጥፋትህ ነውና ቸር እመኝልሃለሁ::
እዚህ ብ ኤት ለመምጣት ከራሴ ጋ ስሟገት ነበር ያልከውን ግን አልተቀበልኩልህም::
ሁላችንም እኮ አንድ አይነት አመለካከት ሊኖረን አይገባም::በሃሳቦች ዙርያ ተፋጭተርን ወደነበርንበት መመለሱ ነው ዋናው ቁምነገር::
እኛም የጠፉትን ስንለምን የራቁትን ስንማጸን መከራችንን በላን እኮ?ፕሊስ ሁላችንም እንደዛ ባናስብ መልካም ነው::


አደቆርሳዬ ደግሞ እኔ ምን አድርጌ ይሆን ብለህ ነው የምመሰገነው? ሃይይይይይ?ባታውቀው ነው እንጂ ቀልበቢስ ሆኜልሃለሁ::ብዙ ሚመመሰገኑ የሚነገርላቸውና በስራቸው የሚኮሩ አሉልህ::
ለማንኛውም ግን እኔ ባላደርግም የእማማ ምርቃት እንዳያልፈኝ አደራህን::ቢያንስ ቢያንስ ልቡን አራራው...እንዲያስብ አድርገው ብ ለው ይጸልዩልኝ::


አደቆርሳዬ..አንድ መጣጥፍ ከኢትዮሜድያ ያገኘሁት ነውና ምናልባት ካላነበብከው ከዚህ በፊት የተወያየንበት ነገር ነውና እንድትመለከትው እዚህ ለጥፌዋለሁ::
ስለአካባቢያችን ጥሩም መጥፎም ሲወራ ይመለከተናልና ነው::


<<የለገደንቢ ወርቅ ሽያጭ ድራማ!!(በኢትዮ-ጀርመኒድረገጽ)


እ.አ.አ በ1997 በጨረታ ወደ ግል ንብረትነት ተዛወረ የተባለው የኢትዮጵያውያን ሀብት የተሸጠው172ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ሽያጩ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ሽያጩን ተከትሎ በርካቶች አርረዋል፤ ተቃጥለዋል።“ዋይዋይ ወርቃችን” ብለው አንብተዋል። ህዝብ የፈለገውን ቢል ደንታ የሚሰጠው አካል ስለሌለ የለገደንቢ ወርቅ ማዕድን ከኢትዮጵያ ህዝብ እጅ በአዋጅ ተነጠቀ።

ሽያጩን እውን ያደረገው የኢትዮጵያ የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት የወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሀሰን አሊ ሲሆኑ፣ የአቶ ስዬ አብርሃ ወንድም አቶ አሰፋ አብርሃ የኤጀንሲው ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ነበሩ። ሁለቱም ባለስልጣናት ዛሬ ሃላፊነት ላይ የሉም። ስለ እውነትና ስለ አገር ሲሉ የሚያውቁትን ለመተንፈስ እስከዛሬ ቢጠበቁም ያሉት ነገር የለም። ሃሰን አሊ ሲኮበልሉ፣ አቶ አሰፋ አብርሃ ከወንድማቸው ጋር በሙስና ተወንጅለው የወህኒ ቤት ጊዜያቸውን አጠናቀው እየኖሩ ነው።

ምዕራብ ሃረርጌ አሰበ ተፈሪ መምህር የነበሩትና ኢህአዴግን መንገድ ላይ የተቀላቀሉት ሀሰን አሊ ካገር መኮብለላቸውን ተከትሎ የተለያዩ መረጃዎች ይወጡ ነበር፡፡ በርካቶች ጉዳዩን ከኦነግ ጋር ቢያያይዙትም“ካገርውጡ ተብለው፣ ሀብትና ንብረት ተዘጋጅቶላቸው ኮብልለዋል” የሚል መረጃ ለባለስልጣናትና ለባለሃብቱ ቅርብ ነን ከሚሉ ወገኖች እንሰማ ነበር። በወቅቱ ኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ውስጥ በነበረኝ ሃላፊነት ሳቢያ ከሰማኋቸው መረጃዎች ውስጥ ሃሰን አሊ“ውጡ”ተብለው እንደ ኮበለሉ የሰማሁት መረጃ ካለኝ ሃላፊነት ጋር ተዳምሮ እንዳጣራው ወሰንኩና ጊዜ ሰጥቼ አነፈንፍ ገባሁ።

የሌሎችን ባላውቅም እንደ ኦሮሞነቴ የለገደንቢ ወርቅ ማዕድን ውድ ንብረት ለሼኽ መሃመድ ሁሴን አላሙዲ መሸጡ ሁሌም ያንገበግበኛል። ሽያጩን አስመልክቶ የተለያዩ ጽሁፎች ቢወጡም እኔ ካሰባሰብኩት መረጃና እውነት ጋር የሚመጣጠን መስሎ ስላልታየኝ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ለመተንፈስ ወሰንኩ።

ሼኽ መሐመድ አላሙዲና ሃሰን አሊ እንዴት ተዋወቁ?

ሼኽ መሀመድ አላሙዲና ሀሰን አሊን እንዳስተዋወቃቸው የነገረኝን ሰው ባንድ አጋጣሚ የማወቅ እድል አጋጥሞኝ ነበር። ተግባሩ ብዙም ደስ ስለማያሰኝ ፊት እነሳው ነበር፡፡ ባለስልጣናትን በገንዘብ እየደለለ ሲሰርቅ ብዙ ጊዜ ስለማውቅ አልወደውም ነበር። የራሱን ትልቅነት ለመግለጽ ድንገት ቢሮዬ በመጣበት ወቅት የነገረኝ ፍንጭ ትዝ ሲለኝ ላገኘው ወሰንኩ። ይህ ሰው ባለኝ ሃላፊነት እንደፈለገኝ ላገኘው ስለምችል፣ እሱም ለሚሰራው ድለላና አየር ባየር ንግድ እኔ ከፈለኩት ቅር ስለማይለው ፊት ነስቼው ያቋረጥኩትን ግንኙነት እንደገና መቀጠል ብቸኛ አማራጬ ሆነ፡፡ይህን ሰው ከተጠቀሙበት በኋላ ወርውረውት በነበረበት ወቅት ላይ ስላገኘሁት የፈለኩትን ለማግኘት አጋጣሚው ተመቻቸልኝ፡፡

ቀደም ሲል ሃሰን አሊን ያውቃቸው እንደነበር፣ አብረው ሃድራ እንደሚያሞቁ፣ የፈለገውን ነገር ማድረግ ከፈለገ ሃድራው በሚሞቅበት ወቅት እዛው በሙቀት እንደሚያከናውኑ አውግቶኛል። ለዚህ ጽሁፍ ስለማይጠቅም እንጂ በርካታ ታላላቅ ጉዳዮች ቢሮ ውስጥ ሳይሆን በተፈረሸ መደብ ላይ እንደሚከናወን በስፋት ስም እየጠቀሰ ነግሮኛል። እንግዲህ ይህ ሰው የ“ባለሃብቱ” ወዳጅ ነበር። ለዚያውም የመጀመሪያ!

በዚሁ ሽርክናቸው ሰውየው ሃሰን አሊን መተዋወቅ እንደሚፈልጉ ባሳወቁት መሰረት ሃሰን አሊን በመያዝ ሳር ቤት አካባቢ አገናኛቸው። ባለሃብቱ በወቅቱ ብዙም የሚያውቃቸው ባልነበረበት ወቅት ሃሰን አሊን አስቀድመው ተወዳጁ። በመኖሪያ ቤት ሃድራ ላይ የተመሰረተው ወዳጅነት ጠበቀ። በኦሮሚያ በኩል አድርገው ዋናውን ሳሎን ወረሱ።

ሀሰን አሊ ከኦሮሚያ ፕሬዚዳንትነታቸው ለቀው ስደትን ለምን መረጡ?

አሰበ ተፈሪ የሁለተኛ ደረጃ መምህር እያሉ ወያኔ ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ በረዣዥም በአለም የምግብ ድርጅት ሽንጣም የጭነት ተሽከርካሪዎች በሸራ ተሸፍነው ቀለሃ ሳያባክኑ ወደ ሃረርና ድሬዳዋ ሲተሙ ቆቦ የምትባል የመስመር ከተማ ላይ ሆኜ የመከታተሉ እድል ነበረኝ፡፡ ወያኔ የሀረርንና የድሬዳዋን ከተማ ለመያዝ ስትሮጥ አሰበ ተፈሪ ከተማ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከአቶ ሀሰን አሊ ጋር ተገናኙ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ሀሰን አሊ የክልሉ ፕሬዚዳንት ሆኑ፡፡ አስተማሪው ፕሬዚዳንት በስልጣን በቆዩባቸው ጊዜያት ከሚታሙባቸው ከፍተኛ ሙስናዎች መካከል፣ ባሌ ውስጥ ተከስቶ በነበረው የዋና ከተማነት ጥያቄ ተከትሎ የተቀበሉት ብር ነው። የባሌ ሮቤ ነጋዴዎች ሮቤ በዋና ከተማነት እንድትቀጥል ያሰባሰቡትን አንድ ሻንጣ ብር በስጦታ አቅርበውላቸው ነበር። ያረፉበት ቤት ድረስ የቀረበላቸው ስጦታ ሮቤን በዋና ከተማነት ጸንታ እንድትቆይ ወሰነ። ገንዘብ ተናገረ። ከአገር የመኮብለላቸው ጉዳይ ከዚሁ ጋር ተያያዥ ነው ቢባልም በፖለቲካው መስመር ደግሞ ኦነግ ናቸው የሚል ሰፊ ሃሜት ነበረባቸው። እኔ ባካሄድኩት ማጣራትና በሰበሰብኩት መረጃ መሰረት ቀደም


ሲል የጠቀስኩዋቸው ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው፣ አቶ ሀሰን አሊ በለገደንቢ ወርቅ ሽያጭ በሙስና መጨመላለቃቸው ለመኮብለላቸው ዋናው ምክንያት ስለመሆኑ ሚዛን የደፋ ምርመራ አካሂጃለሁ፡፡

የለገደንቢን ወርቅ ማዕድን ለመሸጥ ወጥቶ በነበረው ጨረታ የተለያዩ ኩባንያዎች ቢሳተፉም ሼክ መሀመድ አላሙዲ ያሸነፉበት ድራማና የሀሰን አሊ ወደ አሜሪካ መኮብለል በተመለከተ ያሰባሰብኩትን መረጃ ከዚህ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡ ለራሴና ለወዳጆቼ ደህንነት ስል ስም ከመጥቀስ ግን እቆጠባለሁ፡፡

ሃሰን አሊ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የሚመሩት የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ የለገደንቢን ወርቅ ሽያጭ ጨረታ ከማስፈጸሙ በፊት ለገደንቢን አስመልክቶ ከፍተኛ የማባበል ስራ ተሰርቷል። በየጊዜው ሲደረጉ የነበሩ ማባበሎችን ይከታተል የነበረው የመረጃ መነሻ እንዳስረዳኝ ለገደንቢ እንደ መስቀል ሰንጋ ጠልፎ የተበለተው አስቀድሞ ነው። ኢህአዴግ በተለይም ህወሃቶች ከኢትዮጵያ ኪስ የሚወስዱትን ንብረት ህጋዊ ለማስመሰል ያቋቋሙት ይህ ኤጀንሲ በቁንጮ አመራሩ መመሪያ ሰጪነት ባካሄደው ጨረታ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያዎችም ተሳትፈው ነበር።

አንድ ቀን እዛው ቤት ውስጥ እንደተለመደው ሃድራው እየሞቀ በጨረታው የተሳተፈ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያ የተሻለ ገንዘብ ማስገባቱ ባለሃብቱ ጆሮ ይደርሳል፡፡ ኩባንያው ያስገባው ገንዘብ መጠን ይገለጽላቸዋል፡፡ መጀመሪያ ያስገቡት ሰነድ ተቀይሮ ሌላ ሰነድ እንዲያስገቡ በተነገራቸው መሰረት አዲስ ሰነድ እንዲዘጋጅ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ድራማ ለገደንቢ ወርቅ ማዕድን ከኢትዮጵያ ህዝብ ሀብትነት ወደ ሼክ መሀመድ አላሙዲ ንብረትነት በ1997 ለስምንት ዓመት ተዛወረ፡፡

በጉጂ ዞን ሻኪሶ ወረዳ ሳካሮ በተባለው ቦታ የተሰራው ይህ አዲስ4ኪሜየዋሻ መንገድ ቀጭን ረጅም ጥቅልል ብረት ከምድር በታች እስከ70ሜትርይዘልቃል፡፡(ፎቶ፡ስቬን ዱሜሌ)

በዓመት3.5ቶን ወርቅ በአማካይ ሲያመርት ቆይቶ ምርቱን በማሳደግ በአሁኑ ሰዓት ከ4.0 ቶን በላይ ማሳደጉን ይፋ ያደረገው ሚድሮክ ጎልድ በዚህ ዓይነት አሳፋሪ ድራማ ወደ ግል ይዞታነት ከተዛወረ በኋላ ሀሰን አሊ አገር ጥለው እንዲወጡ ተወሰነባቸው፡፡ የሽያጩ ድራማ ደብዛ መጥፋት ስላለበት ሀሰን አሊ በኦነግ ስም ካገር እንዲኮበልሉ ሁሉም ነገር ተዘጋጅቶ ከተጠናቀቀ በኋላ አሜሪካ ለስራ በሚል ሰበብ እንዲሄዱ ተደርጎ በዛው ቀሩ፡፡ አሜሪካን አገር ሱፐር ማርኬትና ነዳጅ ማደያ ተገዝቶላቸው ስለነበር ከነቤተሰቦቻቸው ወደ ንግድ ዓለም መግባታቸው ተሰማ። አሜሪካ ተገኝቼ ማጣራት ባልችልም አደራውን እዚያው ለምትኖሩ ታጣሩትና ትጎለጉሉት ዘንድ አሳስባለሁ። ምንም በሉ ምን የኢትዮጵያው“ለገደንቢ”የግለሰብ“ሚድሮክ”የሆነው በተፈረሸ ፍራሽ ላይ ነውበምርቃና!!

ከ2005 በኋላ ለገደንቢ ወርቅ የማን ይሆናል?

ሚድሮክ ጎልድ ይፋ እንዳደረገው ሃያ ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ዘመናዊ መሳሪያ ተገዝቶ ወርቅ የማምረቱ ስራ እየተከናወነ ነው፡፡ በማስፋፊያ በተከለሉ ቦታዎች ላይ ከ4.7 እስከ6.52ቶን የሚደርስ ወርቅ በዓመት ለማምረት የተጀመረው ስራ ውጤት ማሳየት ጀምሯል፡ ፡ ስለማስፋፊያ ስራው አዲስ ስምምነት መንግስትም ሆነ ማዕድን ሚኒስቴር ያሉት ነገር የለም፡፡ ሚድሮክ ከኮንትራት ዘመኑ(2005)በማለፍ እስከ2020በያዘው ዕቅድ ከ70 ቶን በላይ ወርቅ ለገበያ በማቅረብ ለመሸጥ ማቀዱን በመንግስት ሚዲያ ይፋ አድርጓል፡፡1.6ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ትርፍ እንደሚያገኝም አፉን ሞልቶ ተናግሯል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን አገር ምን ታገኛለች በሚለው ጉዳይ ላይ ጥያቄ ማንሳት ሃጢያት ነው፡፡ያስገድላል፣ ያሳስራል፣ ያስደበድባል...

ለመሆኑ ከ1997 ለስምንት ዓመት ኮንትራት የተሰጠው ለገደንቢ ወርቅ እስካሁን በአላሙዲ እጅ እንዲቆይ የተደረገበት ውልና የውሉ ዝርዝር ለምን ምስጢር ሆነ? በምን ዓይነት አዲስ ውልና ክፍያ ተጨማሪ ቦታ ተከለለ? በምን ያህል ዶላር የሽያጭ ውልና መግባቢያ

ባለሃብቱ ወርቁን እንዲዝቁ ተወሰነ? ማዕድን ሚኒስቴር አለሁ ቢል ወይም ራሱ ሚድሮክ በግልጽ በድረ ገጹ ቢያሰፍረው ቢያንስ ቂማችን ይቀንስ ነበር።

ለወትሮውም በብድር እንደተሸጠ የሚነገርለት ለገደንቢ ወርቅ ማምረቻ ብድሩ ሙሉ በሙሉ መከፈሉ በይፋ ባይገለጽም ሀብቷን በድራማ ጨረታ በብድር የሸጠችው ኢትዮጵያና ህዝቧ ከሃብታቸው ድርሻቸው2%ብቻ ነው፡፡ ከሮያሊቲ ክፍያ ማግኘት የሚገባትን ሚጢጢ ገንዘብ እንኳን ባግባቡና በወቅቱ አታገኝም፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር አቶ ሱፍያን የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሃላፊዎችን ሰብስበው ሲያነጋግሩ‘’ለመሆኑሚድሮክ ጎልድ ላይ ያለን ድርሻ ስንት ነው? ማስገባት ያለባቸውን ገንዘብስ ይከፍላሉ?” በማለት መጠየቃቸው በወርቅ ማዕድኑ ዙሪያ ያለውን እንቆቅልሽ ወለል አድርጎ እንደሚያሳይ ስብሰባው ላይ የተሳተፉ በወቅቱ የተናገሩት ነው። በቀኝ በኩል የሚታየው አርቲፊሻልና በኬሚካል የተፈጠረ ሐይቅ ሲሆን በግራ ደግሞ ያለው የተፈጥሮ ሐይቅ ነው፡፡ አርቴፊሻሉ ሐይቅ ቀለም የተከሰተው በቁፋሮ የሚወጣውን ወርቅ ለማጣራት ጥቅም ላይ በሚውለው ኬሚካል አማካኝነት ነው፡፡(ፎቶስቬን ዱሜሌ)

ይህ ብቻ አይደለም ከለገደንቢ ከርስ የሚጣራው የኢትዮጵያ ደም/ወርቅ/ወደገበያ ሲሄድ ቁጥጥር አለመደረጉ ሌላው አስገራሚ ድራማ ነው፡፡ አገርና ህዝብ እመራለሁ የሚለው ኢህአዴግ ሚድሮክ በቀጠራቸው ባንዳዎች አማካይነት ወርቁን በሉፍትሐንሳ አውሮፕላን ብቻ


የሚያመላልሱት ለምንድነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ የለውም፡፡ በሌላ አነጋገር አገር የሚገባትን የሽያጥ ታክስም ወደ ውጪ በሚላከው መጠን መሰረት እየተሰላ አይከፈልም። በእንዲህ ዓይነት መልኩ በአገራችን ኢኮኖሚና ህልውና ላይ ይጋለብበታል፡፡ ሚድሮክ ወርቅ አንዱ ማሳያ እንጂ ማጠቃለያ ግን አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወርቁን ወደሚላክበት ስፍራ በማመላለስ የትራንስፖርት ንግድ ለመነገድ ጠይቆ“አይሆንም”ነው የተባለው ለምን? ኢህአዴግና ባለስልጣናቱ ለዚህም መልስ የላቸውም፡፡ አገር ወዳዶች ግን መልሱን ያውቁታል፡፡ ልባቸው እየደማ፣ ኅሊናቸው እየቆሰለ፣አገራቸው ስትታረድ የሚመለከቱ ወገኖች ለምንና እንዴት ብለው ሲጠይቁ አሁንም ይገደላሉ፣ይታሰራሉ፣ ይገረፋሉ፣ ህዝብን በማነሳሳትና በሽብርተኛነት ወንጀል ይከሳሳሉ፡፡ እስከ ህልፈታቸው ወህኒ እንዲጣሉ የተሸጡ ወንድሞቻቸው ይፈርዱባቸዋል፡፡ በሃገረ ማሪያምና በቡሌ ሆራ ወረዳ የሆነው ይኸው ነው!

ሚድሮክ ወርቅ እያግበሰበሰ ያለው ሃብት ስለጣፈጠው በግልጽ ባልተቀመጠ ውል ግዛቱን እያስፋፋ የአካባቢውን አርሶ አደሮች ሲያፈናቅል የቡሌ ሆራና የሀገረ ማሪያም ነዋሪዎች ከልማቱ ተጠቃሚ አለመሆናቸውንና ባካባቢው ላይ እየደረሰ ያለው ብክለት ጉዳት እያደረሰባቸው መሆኑን ገልጸው በመቃወማቸው በሽብርተኛነት ወንጀል ተከሰዋል፡፡

ጥር5ቀን2002በሻሸመኔ ምድብ ችሎት በሽብርተኛነት ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው የአካባቢው ተወላጆች ላይ የደረሰውን መከራ የሰብአዊ መብት ጉባኤ34ኛመደበኛ ጉባኤ ህዳር8ቀን2003ዓም ስም በመዘርዘር ይፋ አድረጓል፡፡ ከሳምንት በላይ ትምህርት ተቋርጦ በርካታ ተማሪዎችና ነዋሪዎችም ታስረው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

የፌዴራሉን እንተወውና ኦሮሚያና ሼኽ መሃመድ አላሙዲ በምን ምክንያት ተጣሉ? በወቅቱ የተቀሰቀሰው ተቃውሞና ኦህዴድ፣ ወደፊት የባለሃብቱና የኦሮሚያ እጣ ፈንታ ምን ይመስላል? በሚሉት ርዕሶች ዙሪያ ተጨማሪ ዘገባ ይዤ እመለሳለሁ። በመግቢያዬ እንዳልኩት ዋይ ዋይ ወርቃችን!!

ኢትዮሚድያ- Ethiomedia.com April 11, 2013>>

ቸር እንሰንብት!!

Re: የጀምጀም ልጆች መገናኛ

Posted: 13 Apr 2013 16:44
by ሞፊቲ
ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን::


ክብረመንግስት ካፌ ሩም ውስጥ ያገኘሁት ፖስት ማርኮኝ እዚህ አምጥቼዋለሁ::ባለቤቱን ሳላስፈቅድ ስላመጣሁት በሃገር ልጅ ስም ይቅርታ እጠይቃለሁ::


<<Wegen Solomon
በኤሮግራም ደብዳቤ የተፃፃፋችሁ
- ራሺያ እጅ ስራ ተሰርቶ የመጣ ፎቶ ቤታችሁ የነበረ
- የካሴት ክር ለማጠንጠንና የምትፈልጉትን ዘፈን ለመስማት በእርሳስ ወይ በእስኪብርቶ ስታሽከረክሩ የዋላችሁ (ኤ እና ቢ የተምታታባችሁ፡ ወደፊት እና ወደ ኃላ የተደበላለቀባችሁ)
- የተቆለፈ ስልክ በሹካ፣ በፀጉር ማስያዣ ስትደውሉ እጅ ከፍንች የተያዛችሁ
- የማይክል ጃክሰንን "አይ አም ባድ" "አምቤ አምቤ" እያላችሁ ያቀነቀናችሁ፡ "ፋንኪ ታውን"ን "ኮቱም ጃኬቱም
ቆሽሿል "ብላች...ሁ ያስነካችሁ
- ፀጉራችሁን በእሳት በጋለ ሹካ የተተኮሳችሁ
- የሰኞ ጠዋት የግል ንፅህና ፍተሻ ያማረራችሁ
- ጠዋት ጠዋት ከኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ጋር "ኢንተርናሲዮናል"ን ልባችሁ እስኪፈርጥ ያቀነቀናችሁ፡
- "ጉልቴ ዘ ላንድ ሎርድ"፣ ሽልንጌን"፣ "የቡልቻ ልብ ነኝ"፣"አብዲሳ አጋ"፣ "ፋኖስና ኩራዝ "ከልባችሁ የቀረባችሁ
- "አፕሮች"፣ "ጋይድ "እና "ኮመን ሚስቴክ ኢን ኢንግሊሽ" የተባሉት መፅሃፍት መቼም የማይረሷችሁ
- ኮኮስ እየለቀለቃችሁ ያደጋችሁ
- የቢራ ጠርሙስ የሚመስለውን የፓራፊን ቅባት ክዳን በሚስማር የበሳችሁ
- እንሾሽላ ውስጥ እጅና እግራችሁ እስኪቃጠል የሞቃችሁ
- የአጥሚት ድስት ቂጥ እየተሻማችሁ የላሳችሁ
- ጆሯችሁን ተበስታችሁ ሰበዝ የሰካችሁ
- ቅልልቦሽ በየደረጃው ጣታችሁ እስኪፋፋቅ የተጫወታችሁ
- ቅጠል ቆርጣችሁ፣ በክር አስራችሁ፤ እግራችሁ እስኪጣመም ጢቢጢቢ የተጫወታችሁ
- ለኳስ መስሪያ የአባቶቻችሁን ካልሲ ከቁጥር ያጎደላችሁ
- ለሱዚ መጫወቻ የእናቶቻችሁን /የታላቅ እህታችሁን ስቶኪንግ አበላሽታችሁ የተገረፋችሁ
- በሾላ ላስቲክ ምን የመሰለ ኳስ የገነባችሁ
- ስልክ እንጨት ላይ ኳስ አስራችሁ ቴዘር የተጫወታችሁ
- ክረምትን በቆርኪ፣ በብይና በጠጠር ጨዋታ ያሳለፋችሁ
- በዱቤ ዱቄት ላስቲክ ደብተር የያዛችሁ
- በ" ሰይ ባንከረባብት"የብይ ሃብታችሁን ያደረጃችሁ
- አረንጓዴ- አረንጓዴ- ቢጫ- ቢጫ- ቀይ! አንዴም እየዘለላችሁ፣ አንዴም ቁጢጥ እያላችሁ፡ ከዚያም እንደስልክ እንጨት እየተገተራችሁ የፈነደቃችሁ
- አሌ ቡም የተጫወታችሁ
- የልጅነት ኩላሊታችሁ ከሹሌ እርግጫ የተረፈላችሁ
- በ”አኩኩሉ አልነጋም” ጨዋታ አልጋ ስር ተደብቃችሁ በዚያው እንቅልፍ ያሸለባችሁ
- "ፒቲ ጎል" ሰርታችሁ ኳስ የተራገጣችሁ
- የዛሬን አያድርገውና መጠጥ እንዲህ ሳይስፋፋ ሻሜታ በመጎንጨታችሁ የተገረፋችሁ
- ከባድ ጥፋት ፈፅማችሁ በሳማ የተለበለባችሁ፡ በርበሬ የታጠናችሁ
- እስኪብርቶና እርሳስ ጣቶቻችሁ መሃል ተደርጎ ክፉኛ የተቀጣችሁ፡ በባለእንጨቱ ማስመሪያ የተገረፋችሁ
- እጅ በጆሮ ይዛችሁ መቀመጫችሁ በቺንጋና በቁራጭ የውሃ ጎማ ያረረ

…እስቲ እንያችሁ!

ሕይወት እምሻው....>>ቸር እንሰንብት::

Re: የጀምጀም ልጆች መገናኛ

Posted: 13 Apr 2013 23:59
by ሞፊቲ
አዶላና ውሃ ዛሬም አልተዋደዱም!
ኢጆሌ! ማን ጄታኒ?

Re: የጀምጀም ልጆች መገናኛ

Posted: 14 Apr 2013 02:32
by ጎሳ
ሰላም ለሁላችንም ይሁን!
ወይ ሞፊቲ!
እኔም እንደሰዎቹ ጊዜ አጠረኝ ብል ይሳቅብኝ ይሆን::
ግን ግን ምነው እንዲህ ካረጀን በኌላ የህጻንነት ጊዜያችንን ታስታውሰናለህ:: አቤት....ከሁሉም ከሁሉም "ጉልቴ ዘ ላንድ ሎርድ"፣ ሽልንጌን"፣ "የቡልቻ ልብ ነኝ"፣"አብዲሳ አጋ"፣ "ፋኖስና ኩራዝ "ከልባችሁ የቀረባችሁ " ስንት ነገር ቀሰቀሰብኝ:: መ/ር ጸጋዬ ፍሰሀ "ላንድ ሎርድ ጉልቴ ኮውት አላይቭ:: ስኞር ብሩኖን ደረስክበት ይሆን? “Once a year signor Bruno prepares a party for all his workers. At the end of the party he makes a speech. He usually says “Comrades, as you all know I am generous and Christian, I believe in hard work. That is how I became rich. You are obedient and friendly but you don’t work hard as you supposed to be. That's why you will never be as rich as I am....” ይላቸው ነበር:: ግራመሩ በወቅቱ እንደምናስታውሰው ሳይበረዝ ስላስቀመጥነው ማስተካከል አይቻልም ቅቅቅ:: በደቂቃ 72 የሚመታው የቡልቻ ልብ....አጠጥተውት ያበሉትን ሰዎች አብዲሳ አጋ ፈረስ መቀማቱ ትክክል መሆን አለመሆኑን በዚያ ጨቅላ እድሜያችን ኤትክስ ሲያስተምሩን እና ሲያከራክሩን....”ፋኖስ እና ብርጭቆ” ነው ወይስ “ፋኖስ እና ኩራዝ” ነው ነገሩ? እኔ ፋኖስ እና ብርጭቆ ይመስለኛል:: "ገለል በይ ከፊቴ ብርሀኔ ይስፋ " ብላ ፋኖስ ብርጭቆዋን ብርሀኗ በደንብ እንዳይታይ ያድረገች ይመስል በምቀኝነት ስትከሳት እና ብርጭቆዋ ትታት ብትሄድ ንፋስ በሰከንድ እንደሚያጠፋት...ያ እራሱ የሆነ ትምህርት ያስተማራል:: ሽልንጌን ስሰማ መ/ር አስቻለው የሚባል መጀመሪያ መ/ርት ይርጋ ሀይለ ስላሴን አግብቶ የነበረ እና በኌላም የይርባዋን አለምገና ባህሬን ያገባት ( ከቀላቀልኩ አርመኝ ቅቅቅ ከይርባዎች ውጪ ሞቼ እገኛለሁ የማለቱ ጉዳይ ሚስጢሩ አልገባኝም ብለለች ፍቅረአዲስ:: አሁን ሳስበው ደግሞ አለምገናን ገብረመስቀል ነው ማን የሚሉት አንድ የኢህአዴግ ባለስልጣንም ያገባት ይመስለኛል....ዝብርቅርቅ አለብኝ ደግሞ የኔ ነገር) ሰውዬ ትዝ ይለኛል:: "ፋጤ ወጂን ዴማ "ስ ትዝ ይልህ ይሆን? ብቻ ዛሬ ቦሬን ለጉድ አስታወስከኝና ሰሞኑን ካደፈጥኩበት አስወጣኽኝ:: ሁለተኛ እንዲህ መዐት ትዝታ የሚቀሰቅስ ነገር ከየትም እየለቃቀምክ ትካዜ ውስጥ አትክተተን አባው:: የስራህን ይስጥህ ቅቅቅ::
እኔ የምልህ ሞፊቲሻ...ልትሰድበኝ ከፈለክ ለምን በቀጥታ አትሰድበኝም ነብሱ? እንደው ላንተ እልህ ብዬ ያንን የጽጌን ጉዳይ ከቆጥ አውርጄ አስር መጽሀፍም ቢሆን አሳትመዋለሁ:: ባለሱቅ ደግሞ ጽሁፉ የምግብ ሜኑ ይመስላል እየተባለ እንዴት አድርጎ ነው ድርሰት የምጽፈው? ግጥም ነው ወይ ስድ ንባብ ሊባል? ለነገሩ ባለሱቃችን የአጻጻፍ ስልቱን ቢቀይር እራሱ አይመቸንም ብዬ አምናለሁ:: ለምደነዋላ! ቅር ይለናል:: እያንዳንዱን መስመር ስንጨርስ ማረፋችን እራሱ ጽሁፉን ብቻ ሳይሆን ድምጹንም የምንሰማው አይነት ሆኖ ነው የሚሰማኝ:: ስለ አባባ ዓለሙ ፈይሳ ጉዳይ ሌላ ቀን እንመለስበታለን::
ሌላው ሞፊቲ ኪያ በጣም የሚያናድደኝ የወርቁ ጉዳይ ነው:: የጉጂ ህዝብ ከምድሩ ከሚዛቀው ከወርቅ ማዕድን ከጥንት ጀምሮ ምንም ጥቅም አላገኘም:: አሁንም እያገኘ አይደለም ወደ ፊትም የሚያገኝ አይመስለኝም ማንም ስልጣን ብዪዝ:: እኔ እንደው ያ የተረገም ማዕድን ድሮውንም እዚያ ባይገኝ ምናለበት! በአከባቢው በቸልተኝነት የሚለቀቀው የኬምካል እጣቢ ወንዝ እና ሀይቅ ሰርቷል ይባላል:: የሚያሳዝነኝ ምስኪኑ ህዝብ ያ መረዝ በጤናቸው ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት እንኳ ሳያውቁ ዝም ብለው የዕለት እለት ኑሯቸውን መኖራቸው:: ምናለ ሁሉም ነገር ቀርቶባቸው የለመዱትንና የኖሩበትን አንድ ማሳ በቆሏቸውን እያረሱ ጤንነታቸው እንደተጠበቀ ቢኖሩ:: አዲስ የወርቅ ስፍራ በተገኘ ቁጥር መፈናቀላቸውስ? ብንናደድም ሀቁን ስላስነበብከን ተባረክ ሞፊቲ ኪያ::
ወይ ጂግሳ ኪያ
እንኳን መጣህልን እንጂ:: በዚያ ብትጠፋ ኖሮ ይህ ሞፊቲ የሚሉት ልጅ በመጥፋትህ ተጠያቂ አድርጎኝ አንድ ቀን ቀንቶኝ ወደ ቦሬ ብሔድ የቀሌን ሰዎች ሰላማዊ ሰልፍ ያስወጣብኝ ይሆናል ብዬ ትንሽ ማሰቤ አልቀረም ነበር:: እንኳን ብቅ አልክ ወንድማችን:: ጂግሳ ኪያ አንተ 95% በኔ ሀሳብ ከምትስማማው በላይ እኔ ደግሞ 100% ባንተ ሀሳብ ለመስማማት እራሴን እያስማማሁ ነው:: ድሮም ተኗቆሩ ሲለን እንጂ አንዱ ባንዱ ሀሳብ ቢስማማ ሁላችንም አንድ ብንሆን እና ባንድ አዕምሮ ብናስብ ምን የሚጎዳን ነገር አለ ብለህ ነው:: “ዛሬ ደግሞ ሁላችሁም ምናልባትም ድሮ ከነበረበት ወደ ተሻለ ፍቅር ገብታችሁ ሳይ…” ለዚህ ደግሞ ክሬዲቱን መውሰድ የሚገባው ወንድማችን አደቆርሳ ነው:: እኔ እንኳን ሞፊቲን እየኮረኮምኩት እንዳላሳደኩ ሁሉ በዚህ ዕድሜዬም አንዳንዴ እንደ አስራ ስድስት አመት ወጠጤ የልብ ልብ ተሰምቶኝ የትም ላልደርስ እደነፋለሁ:: ሚስጢሩ የገባው አደቆርሳም ዘራፍ ብሎ ሳይከተለኝ ምሩቁን በዋጠ ሰው ስታይል አቀራረቡን አስተካክሎ አሸነፈኝ:: ክብር እና ምስጋና ሁሉ ለ.....እግዚአብሔር ይሁን ልበል እንጂ አደቆርሳም ይገባው ነበር:: እኔም ከእንግዲህ ነገሮችን እየዘለዘልኩ ላራዝም አልፈልግም:: አሁንማ ሁሉንም ነገር ትተን በሁሉም ተስማምተናል እንጂ በዚያ መንፈስ ቢሆን ኖሮ ለባለፈው

"በነገራችን ላይ በ1984 ዓ.ም ቁቤ አፋን ኦሮሞ ሲጀመር በፈቃደኝነት ለማስተማር ከዘመቱት መካከል አንዱ ነበርኩኝ በአዶላ! "
ያልከውን ሁሉ በጥያቄ አይን እመለከተው ነበር ቅቅቅቅ:: በማያገባኝ ነገር “ወንድሜ..... በዚያን ወቅት ቁቤን ለማስተማር መዝመትህ የሚያስመሰግንህ ጉዳይ ነው:: ግን ግን እንደዚያ ስትለፋ የነበረው አፋን ኦሮሞን ሰዎች ኩሺና ውስጥ ብቻ እንዲገለገሉበት ብቻ ነበር ወይ የትምህርትና የስራ ቋንቋ እንዲሆን ከነበረህ ጽኑ እምነት የተነሳ ነበር?” እያልኩ ጥያቄ እጠይቅህ ነበር:: አይገርምም ግን የኔ ነገር? "ጌታ ይገስጸው ያንን መንፈስ " እንል ነበር ድሮ ትንሽ የጴንጤን ሀይማኖት እናከርር በነበርንበት ወቅት:: አሁንማ ስራውም ፌስቡኩም ዋርካውም ኢትዮፎረሙም የነበረንን የጸሎት መንፈስ እንክት አድርጎ በልቶብን ይኽው እንደምታየው ያነጫንጨናል...ብዙም መናደድ በማይገባን ነገር ጥርሳችንን ያስነክሰናል...ፖለቲከኛ ያደርገናል...ኧረ ስንት ነገር:: እንደው አንዴ ካነሳን ዘንዳ የያኔው ጎሳ ቢሆን በቀሩት አሁን ባነሳሀቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምን ይልህ እንደነበር በትዝብት አይን አብረን እንየው እስቲ ጂግሳ ኪያ::
"አንድ የጉጂ ልጅ ተምሮ ሙያ ኖሮት መቀሌ ወይም ባህርዳር ማዘጋጃ ተቀጥሮ ለመስራት መብት ሊኖረው ይገባል ብዬ አምናለሁ በተቃራኒውም እንደዚሁ፡፤ ይሄ ብዙዎቻችሁየዚህ ቤተሰብ አባላት ከፋም ለማም ሰው ሃገር ሄዳችሁ እየሰራችሁ አይደል!”
ካልጠፉ መስሪያቤቶች እንደ ምሳሌ የወሰድከው የማዘጋጃ ቤት ስራ የቦሬን ማዘጋጃ ቤት አስታወሰኝ:: ከበጀታቸው ማነስ የተነሳ የመንገድ ላይ መብራትን ሂሳብ ለመብራት ሀይል መክፈል አቅቶት ከጥቂት የዋና መንገዶች መብራት በስተቀር ወደ ውስጥ የሚገቡ መንገዶች መብራት እንዳልነበራቸው ከንቲባው ሲናገሩ ሰምቻለሁ:: እንደዚህ አይነት መስሪያ ቤት ስንት ሰው ከባህርዳር ወይንም ከመቀሌ አስመጥቶ ሊቀጥር እንደሚችል አላውቅም እንግዲህ:: እስቲ የማዘጋጃቤቱን እንተወውና ብዙ ሰው ሊቀጥሩ የሚችሉትን መስሪያቤቶች እናንሳ:: "The majority (80 %) of the population works in the agricultural sector, and contributes to 40 percent of the economy” ከተባበሩት መንግስታት ሪፖርት ያገኘሁትን ልጥቀስልህና የግብርናን ቢሮ እንደምሳሌ ልውሰድ:: ዲፕሎማ ያለው አንድ የግብርና ሰራተኛ እንደ ድሮው ጊዜ ከተማ ወይንም በከተማ አቅራቢያ ወዳሉት የቅርብ ቀበሌ ገበሬ ማህበራት ብቻ በሞተር ወይንም በመስሪያቤት መኪና በመሄድ የአጭር ሰአት ጉብኝት አድርጎ መመሪያ ነገር ሰጥቶ አይመለስም:: ያሁኑ የግብርና ሰራተኛ ግን ቦልቱ ጊሪሳ ድረስ በመሄድ እዚያው ከገበሬዎች ጋር እየኖረ በሰርቶ ማሳያ ጣቢያ ሳይወሰን በየገበሬው ማሳ እየዞረ እያማከራቸው እውቀቱን ያካፍላቸዋል :: ታዲያ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ብቻ የትም መቀጠር አለበት ብለህ ከባህርዳር ወይንም ከመቐለ የምታመጣው ንጹህ ኢትዮጵያዊ በምን ቋንቋ ይሁን ይህንን የጉጂ ህዝብ ሊረዳ የሚችለው? አስተርጓሚ ሊቀጠርለት? የግብርናን መስሪያቤት እንደምሳሌ ወሰድኩኝ እንጂ የጤና ቢሮንም ብትወስድ ያው ነው:: በየገጠሩ የሚሰሩት ነርሶችም ሆኑ የጤና ኬላ ሰራተኞች የአከባቢው ህዝብ የሚናገረውን ቋንቋ መናገር መቻል አለባቸው:: የሚያመኝን በትክክል ካልሰማኝ ምኑን ያክመኛል:: በምን ቋንቋ ነው ስለ በሽታ መከላከል preventative measures ህዝብን የሚያስተምረው? መምህራንም እንደዚያው:: አሁን አሁንማ የገጠሩ ህዝብ አንድን ጉዳይ ለማስፈጸም እንደ ድሮ 100 ኪሜ እንዳይሄድ አዳዲስ ወረዳዎች በየገጠሩ ተቋቁመው ህዝብን እያገለገሉ ነው:: በህግ LLB ያለው ጓደኛዬ መኪና እንደልብ የማይገባበት ግርጃ ተመድቦ በአቃበ ህግነት እያገለገለ ነው:: ከመቐለ የሚመጣው LLB በምን ቋንቋ ይሆን ታዲያ ለተበደሉት ሰዎች ቆሞ የሚከራከረው? መልሱን ላንተው ወንድሜ ጂግሳ ኪያ:: ከሰፊው ህዝብ ጋር ሊያገናኝ የሚችል ስራ የሚሰሩት ሰራተኞች ሁሉ አላማቸው ህዝብን በትክክል ለማገልገል እስከሆነ ድረስ ህዝቡ የሚናገረውን ቋንቋ መናገር መቻል አለባቸው "አራት ነጥብ " ብዬ ሌላ መጥፎ ትዝታ አልቀሰቅስብህም ወንድሜ ጂግሳ:: ሌላው እራስህ ያመጣኽው ቆንጆ ምሳሌ...ስለ ውጪ ሀገር ስራ:: እኛ ውጪ አገር የምንሰራው እኮ በአፋን ኦሮሞ አይደለም:: ስራ ለመቀጠር ኢንተርቪው ስትቀመጥ ቋንቋቸውን በደንብ መናገር እና መጻፍ መቻልህን እያናገሩህ እና እያጻፉህ ይገመግሙሀል:: ካልቻልክማ ምኑን ልታገለግል ትቀጠራለህ? ማንም ሰው እኩል መብት አለው ቢባልም እዚህ ላይ ግን መብትህ አይሰራም:: በኛም ሀገር መሆን ያለበት ይኸው ነው:: አንድ ያንተን በኢትዮጵያዊነትህ ብቻ በየትኛውም ክልል ስራ የማግኘት መብትህን ለመጠበቅ ብቻ ሲባል የብዙ ህዝብ በሚገባው ቋንቋ የመገልገል መብቱ ሊነካ አይገባም:: እዚህ ላይ ከሰው ጋር ብዙ የማያገናኝህ የውጭ ሀገር ስራዎች ቋንቋን እንደ ወሳኝ መስፈርት ላይጠይቁ ይችላሉ:: በነገራችን ላይ በሌላ ቋንቋ የዶክትሬት ድግሪ ያለው ሰው እዚህ አገር በተማረበት ፊልድ መቀጠር አቅቶት የታክሲ ሾፌር ሆነው የሚያገለግሉ እንዳሉ ልጠቁምህ እወዳለሁ::
“ግን የገረመኝ አንድም ተቃዋሚ እስር ቤት የለም ነው ያልከኝ;;;;; በጣም ነው ያሳቀኝ፡፡ ኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞችን በማሰርና በማፈን ከ ኤርትራ ቀጥሎ ሁለተኛዋ ሃገር ናት…”

ከዚህ በፊት የተነጋገርንበት ሀሳብ'ኮ ወንድሜ ጂግሳ " የኦሮሞ መብት ዛሬም ከድሮው ባላነሰ መልኩ አፈር ድሜ እየበላ ነው!! " ባልከኝ መሰረት አንተ ከምታውቃቸው የአዶላ እና አካባቢው ልጆች በኦሮሞነታቸው ብቻ ታስረው ከሚማቅቁት አንድ ሁለቱን ጥራልኝ ነበር ያልኩት እንጂ የታሰረ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባል አንድም የለም አላልኩም:: በእርግጥ ወደ ቦሬ በተመላለስኩበት ወቅት አንድም የፖለቲካ እስረኛ አለመኖሩን ለማረጋገጥ አንተ እንዳልከኝም ኢቲቪን መስማት አልነበረብኝም:: እንኳን ኢቲቪ ደስ ሲለን ኢሳትንም እየሰማነው'ኮ ነው...ጆሮ ምን የማይሰማው ጉድ አለ ብለህ ነው ጂግሳ ኪያ ቅቅቅ:: እንደምከታተለው መረጃ ይሆነኝ ዘንድ ይሄንን ሊንክ እይልኝ እስቲ::
http://www.youtube.com/watch?v=InBfZiDv ... r_embedded


ዛሬ ደግሞ መለስ ብለህ ስለታሰሩት ጋዜጠኞች አነሳህብኝ:: ጋዜጠኞች የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆነው የአንድን ፓርቲ አላማ የሚያራምዱ ከሆኑ እንደ ጋዜጠኞች ሳይሆን እንደ ፖለቲከኞች መታየት ያለባቸው ይመስለኛል:: ስለዚህ ተቃዋሚ ፖለቲከኛን እና ጋዜጠኛን አናምታታ:: በመቀጠልም ሰዎች ሁሉ በህግ ፊት እኩል መሆናቸውን ባንጻሩም ሁሉም ሰው ህግን የማክበር እኩል ግዴታ እንዳለበትም አምናለሁ:: ይህ ገበሬ ነው...ያከባቢውን ህዝብ ለረብሻ ቢቀሰቅስም አይጠየቅም ወይንም ይህ ጋዜጠኛ ስለሆነ ህዝብን ለርብሻ እና ለጦርነት የሚቀሰቅስ ጽሁፍ ቢጽፍ እና ቢያሰራጭ በህግ አይጠየቅም አይባልም:: የጋዜጠኝነት መታወቂያው ከመጠየቅ ነጻ መብት (immunity) አይሰጠውም:: አንድ ጋዜጠኛ በመታሰሩ ብቻ የታሰረበትን ጉዳይ እንኳ አጣርተን ሳናውቅ መታሰር የለበትም ብለን መከራከር ከጀመርን ተሳስተናል:: ደግሞም የእያንዳንዱ ጋዜጠኛ ጉዳዩ በተናጠል ታይቶ የተከሰሰበት ወንጀል ያስከስሰዋል ወይ አያስከስሰውም ብለን የየራሳችንን አስተያየት መስጠት ያለብን ይመስለኛል:: ለምሳሌ CPJ በድህረ ገጹ የኢትዮጵያን መንግስት ከወቀሰበት የጋዜጠኞች ጉዳይ አንዱ ባንድ ወቅት ኦጋዴን ውስጥ ተይዘው ታስረው የነበሩትን ሁለት የስዊድን ዜጎች ጉዳይ ነው:: "They were simply doing their business " ብሏቸዋል:: አንዲት ሉአላዊት አገር የራሷ የሆነ ህጋዊ ወዳገርውስጥ የመግቢያ መንገዶች አሏት:: ያንን የመግቢያ መንገዶች ሳይከተል እና የመግቢያ ቪዛ ሳያስመታ መንግስት ሳያውቀው በአገሪቷ ክልል ውስጥ የተገኘ ግለሰብ ሁለት አማራጭ ብቻ ነው ያለው:: ስደተኛ ከሆነ የተሰደደበትን ጉዳይ አቅርቦ ለስደተኞች ወደተዘጋጀው ካምፕ የመግባት አለበለዚያ ደግሞ ወንጀለኛ ስለሆነ ወደ ህግ የመቅረብ:: የሚቀርጹት ዶክሜንትሪ ፊልም እንኳ እንደመብታቸው ቢታይላችው በህገወጥ በኩል ወዳገር በመግባታቸው ብቻ ሊፈረድባቸው ይገባል:: ታዲያ ይህንን እንኳ የማይቀበል CPJ ከአድልዎ ነጻ ነው ብዬ የሚያወጣቸውን ዘገባዎች እንደመጽሀፍ ቅዱስ ቃል መቀበል የለብኝም:: ስለታሰሩት የተለያዩ ኢትዮጵያውያን "ጋዜጠኞች " ፍርድ ቤት ቀርበው የተፈረደባቸው እንዳሉ ሁሉ ፍርድቤት በነጻ የለቀቃቸውም አሉ:: ማንም ሰው ባንድ ወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ይውላል:: አቃበ ህግ በቂ ማስረጃ በማቅረብ ችሎቱን ካሳመነ ይፈረድበታል:: በቂ መረጃ ካላቀረበ ደግሞ በነጻ ይለቀቃል:: ከህግ ፊት ሊሰወር ይችላል፤አሊያም እውነትን ሊደብቅ ይችላል፤ ካልሆነም አደጋ ሊያደርስ ይችላል ተብሎ የተጠረጠረ አንድ ሰው ፍርድቤት በነጻ እስኪያሰናብተው ድረስ በቁጥጥር ስር ውሎ የፍርድን ሂደት የመከታተሉ አሰራር የትም አገር ያለ ነው:: የተወሳሰቡ ጉዳዮች ደግሞ የፍርዱን ሂደት ሊያራዝሙት ይችላሉ:: የጋዜጠኞች መታሰርም ሆነ በእስር ቤት መቆየት ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው የሚመስለኝ:: እዚህ ላይ የታሰሩት ጋዜጠኞች ሁሉ ወንጀለኞች ናቸው ማለቴ እንዳልሆን ይታወቅልኝ:: ያ እያንዳንዱን ጉዳይ በጥልቅ መርምረው ፍርዱን የሚሰጡት የፍርድቤትዳኞች ሀላፊነት ነው:: የ CPJ ሪፖርት የኢትዮጵያን የፍትህን ሂደት ሊቀይር ይችላል ብዬ አላምንም::
እንደው ያንን ጎሳ ለመታዘብ ያነሳሁት ጉዳይ ነው እንጂ ያሁኑ ጎሳማ ተቀይሮ ባንተም ሀሳብ ሙሉ ተስማምቷል:: በል እንግዲህ ጂግሳ ኪያ አትጥፋ:: ኦዶአችንስ ወዴት ጠፋ ይሆን: ለነገሩ እሱ ድሮም ሲለው አመት ጠፍቶ በድንገት እንደ መንፈስ ብቅ ይላል:: ለዚያ ነው እንጂ መቼም ተቀይሞኝ እንዳልሆነ አምናለሁ:: በሉ ይመቻችሁ:: አሁን ሌላ ሌላ ጨወታ እያመጣን እንጫወት:: ዛሬ መቼም በጽግዬ ትዝታ ባህር ውስጥ ሆኜ እጽፍ በነበረበት ስታይል ነው ቁጭ ብዬ ይህንን ታይፕ ስተመትም የዋልኩት:: ለዛሬ በበቃኝ ተዘረርኩ::

Re: የጀምጀም ልጆች መገናኛ

Posted: 14 Apr 2013 06:42
by አደቆርሳ
እንዲህ ያለ በጣም አስደናቂና ወቅታዊውን ሁኔታ የሚያስረዳንን ታሪክ እንድናነብ ስለረዳኸን ሞፊቲኮ ትልቅ ምስጋና አቀርብልሃለሁ::
በእርግጥ ከዚህ ቀደም በለገደምቢ ሁኔታ ከሽያጩም በፊት ጀምሮ ስለነበሩት ችግሮችና አሁን ስላሉት እንዲሁም ስለ ወደፊቱ የአካባቢው ህብረተሰብና ኅልውናቸው ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ማድረጋችን አይረሳም::
እንደዚሁም አንድ አስራደ የሚባል ከወደፈረንሳይ ምድር ብቅ ያለ የአዶላ ሰው አንድ ጽሁፍ አቅርቦ የእሱንም ጉዳይ እዚያው ቤታችን ውስጥ እንደተነጋገርንበት አስታውሳለሁ::
የአላሙዲን እና የፋብሪካው ጉዳይ ግን አሁን ያየነው እጅግ አስገራሚ ከመሆኑም በላይ በሼሁ ላይ ያለኝ አመለካከት እስኪቀይርብኝ ድረስ ደርሻለሁ::
በሌሎች አንዳንድ ጉዳዮች ዙሪያ ሰውዬውን በቀና መልኩ የምመለከትበት ዓይኔ ከሌሎች ጓደኞቼ ጋር አልፎ አልፎ ሲያጋጨኝ የመቆየቱን ያህል ከሚያደርጋቸው መልካም ነገሮች በስተጀርባ ለምሳሌ የፋብሪካው የኬሚካል ውዳቂ ወይንም ዝቃጭ የአካባቢውን ህብረተሰብ ከመኖር ወዳለመኖር እየለወጠ መኖሩ እስካሁን ከአስራ አምስት አመታት በላይ ሊያሳስበው አለመቻሉ አሳዝኖኛል::
እስቲ እኔም እዚህ ያለውን አንዳንድ ነገር ተመልክቼ የምለውን በቀጣዩ ጽሁፍ ለመዳሰስ እሞክራለሁ::
ሌላው ያቀረብከውን የኛን ዘመን የሚመለከት ጽሁፍ አንዴ ከሸገር ራዲዮ ላይ አዳምጬ በጣም ነበር የሳቅኩት ምክንያቱም በትክክል እኛ ያደረገነውና ያለፍንበት ሁኔታ ስለሆነ ያስገርማል ደስም ይላል::
ጅግሳ ኪያ እና ጎስሽክም ባቀረባችሁት ሃሳብ ላይ ቅዱስ የሆነ አስተያየት ብሰጥ በጣም ነበር ደስ የሚለኝ የሆነው ሆኖ አስቀድሜ ለመናገር የምወደው ግን ጎስሽክም በሃሳብ ልዩነቶች ላይ በዚህኛው ጽሁፍህ የተናከርከው አንጀቴን አርሶኛል::
በመጀመሪያ ጅግሳ ኪያ በተናገርከው እውነታ ላይ ያለቺኝን ትንሽ አስተያየት ልስጥ
ይቅርታ እንደቻልኩ ነገ ወይንም ከነገ ወዲያ እመለሳለሁ
በድጋሚ ይቅርታ ወዳጃችሁ አደቆርሳ

Re: የጀምጀም ልጆች መገናኛ

Posted: 19 Apr 2013 18:15
by አደቆርሳ
የሰሞኑ የአለም ፈተና ያንን ክፉ ጊዜ እንደገና እንዳያመጣው ፈራ ተባ እየተባለ ነበር ሳምንቱ ያለፈው
የአለም ኪሳራ ተብሎ ሺህ ምንተሺ ባለስራዎች እቤታቸው ቁጭ ያሉበት
መንግስታት ግራ የተጋቡበት እኛ ደሞ አንድ እንጀራ በወጥ 15 ብር ከመክፈል ወደ 80 ብር የተሸጋገርንበት ዘመነ ኪሳራ እንዳይደገም ፈራና ! ማን ይከለክለናል መፍራት !
ለማንኛውም እንደምን ሰነበታችሁ ባለፈው እኔ ትቼው የወጣሁበትን ቤት እንዳለ ስመለከተው አፈርኩ
እመለሳለሁ ብዬ ብወጣ እንኳን አይ ይመለሳል ብላችሁ እንደው አንድም ቃል አትተነፍሱም እንዴ ጎበዝ ? እንደው እንደደራሲው መጽሃፍ ዝም ጭጭ ብላችሁ አሳፈራችሁኝ
እየጠበቃችሁኝ እንደሆነ ተሰማኝና መቆየቴ ነው መሰለኝ አሳፈረኝ::
ለነገሩ እኔ ማፈር አውቃለሁ ብላችሁ ነው ? በልጅነቴ ዓይናውጣ ነበርኩ የማፍረው ሴትን ማናገር ብቻ ነበር ይመስለኛል እንጂ በሌላ ነገር አፍሬ አላውቅም::
እስቲ ወሬ አትዘብዝብ አሁን የመጣህበትን ........ አላችሁኝ አይደል ? እሺ ::
ጎስሽክም እና ጅግሳ ያረፈውን ነገር አላሳርፍ ብለው ሊያስለፈልፉኝ እንዳሰቡት ነበር ያቆምኩት
አስቤ አስቤ አስቤ ደከመኝ .... በማለት ስለተናገረው እረኛ የቀድሞው ሰው መለስ ዜናዊ ሲናገሩ የሰማሁ ቀን በጣም ነበር የሳቅኩት ዛሬም በራሴ ላይ ብስቅ እንደምትስቁብኝ ገምታለሁ::
ምክንያቱም እኔም አስቤ አስቤ አስቤ ደክሞኛልና :
የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ ያላደጉ አገሮችን ችግር ለመፍታት ውይይት መቀመጥ እንደተለመደ ያህል አንዲትም መፍትሄ አለመገኘቱም የተለመደ ነው::
የሆነው ሆኖ እኔም ብሆን በሃገሬ ጉዳይ ውይይት ብቀመጥና የሃገሬ ጉዳት ሆኖ ለሚሰማኝ አነጋገር ትክክል ይሁን አይሁን በኅአይለቃል መናገሬ አልያም መናደዴ የማይቀር ጉዳይ ነው::
ለምሳሌ የርሃብተኛ ሃገር ሰው ብሎ አንድ የሌላ ሃገር ሰው ቢናገረኝ በየትኛውም መልኩ የራሴን አስተያየት በመልካም አገላለጽ መልሼ ከመንገር ይልቅ መናደዴ አይቀርም::
1ኛ/ መስራት እየቻልን ሳንሰራ በመቅረታችን በመንግስቶቻችን አልያም በእድላችን ተናድጄ
2ኛ/ ቃሉ በቀጥታ የስድብ አልያም የበታችነትን የሚያመለክት በመሆኑ
በነዚህ በተለያዩ ንጽረ ሃሳቦች ውስጥ ሁልጊዜ ጉዳቴን እና የበታችነቴን በሚያሳዩኝ ነገር ግን የበታች ባልሆንኩበት ኩፈሳ ወይንም ስሜት ውስጥ ራሴን አገኘውና እንደገና እናደዳለሁ::
ከዚህ አንጻር ስለ ኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ወቅታዊውን ፖለቲካ ፈታ አድርጌ በምወደውና ቀጥተኛ በሆነው ስሜቴ የኔን ትክክለኛ አቋም ብገልጽ እንኳን
ሌላውም የራሱን ቀጥተኛ ሃሳብ ብቻ መልሶ የመግለጽ ልምዱ እንዲኖረን እመኛለሁ ምክንያቱም እኔም በደንብ እንደምታውቁኝ የድሃ ሳህን ነኝ:
በውይይት የመግባባት ልምዱ በኛ ብቻ ሳይሆን በመንግስታቱም ደረጃ በጣም ጎደሎ ነው::
የሃገራችንም የአህጉራችንም ችግር ይሄው ነው !
ይህንን የምለው በኛ መካከል ይፈጠራል ብዬ አይደለም ባጠቃላይ በማህበረሰባችን ዘንድ ሊሆን የሚችለውን ሁናቴ አገናዝቤ ነው::
ዬኛማ ሁኔታ በውነት ያስቀናኛል ሰው በራሱ ሲቀና አይገርማችሁም ?
የዚህ ቤት መከባበርና መተማመን ያስቀናኛል ምክንያቱም ይሄ ጉዳይ ከራሴ ቤተሰብ ጋር እያጋጨኝ ያለ ጉዳይ ነው::
ሌላው የምንኖርበት ሁኔታም በአስተሳሰብ ጥቂት ይለየናል ብዬ አምናለሁ
ለምሳሌ እኔ አዲስ አበባ ካለሁት ይልቅ ሻኪሶ ያለው ስለ አዶላ ወቅታዊ ሁኔታ የተሻለ መናገር ይችላል::
ባጭሩ ግን በሃገራችን ውስጥ የቋንቋ ነጻነት የሚባለው ፖለቲካ ውስጥ የተሸነቆሩ አሜኬላዎችን አጥርቶ በማያይ አይን መመልከትና አጥርቶ በሚያይ ዓይን መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ ነው::
አንድ ምሳሌ ልድገምና ክብረመንግሥት የከተማዋን አጠቃላይ መዋቅራዊ አስተዳደር ፍርድ ቤት ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ውሃ ልማት ግብርና ወዘተ የሚጠቀሙበት የስራ ቋንቋ ኦሮምኛ ነው
ይህ ደሞ ያለ ጥርጥር ለኦሮሞው ታላቅ ድል ሆኖ የሚቆጠር ነው: :
አካባቢውን የሚያስተዳድሩት ደሞ የአካባቢው ልጆችና ተወላጆች ናቸው አንዳንዴን ይደባለቃሉ
ይህንን አካባቢ ለአመታት ብንመለከተው ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ምናልባትም ከጥቂት ግለሰቦች የፎቅ ግንባታ በስተቀር ከመሰረታዊ ልማቱ ውስጥ አንዲትም ለውጥ አልታየም::
በቅርብ ከሚወጣው ውሃ አቅም እንኳን እስካሁን ያለው ከሃምሳ ዓመታት በፊት የነበረችው ጉድጓድ ነች::

ከዚህ የሚብሰው በተፈለገው ቦታና ሁኔታ ውስጥ ብንሄድ አካባቢው በመልካም አስተዳደር ጉድለት ታንቋል .... ይህንን እንደምሳሌ አልኩ እንጂ በብዙ ቦታዎችም ይሄው ነው
ደግሜ ያነሳሁበትም ጉዳይ :-
ሀ/ በዚህ ችግር መንግስትን መኮነን ቂላቂልነት ስለሆነ
ለ/ ለዚያ ህዝብ ከነዚህ ልጆች የቀረበ ከየትም ሊመጣ ስለማይችል ::
ከዚህ የተነሳ መቼ ነው ? ሃገራችን ..... ብዬ አስብ አስብ አስብና ድክም ይለኛል::
ዴርቶጋዳ የኢትዮጵያን ከርሰምድር ጸጋ እንዴት አድርጎ እንደገለጸው አስታውሱ... ኢትዮጵያዊ ብሩ ላይ ቆሞ ይለምናል !!!!!
ዴሞክራሲም እድገትም እንዲሁ ነው ሃገራቸውን ማሳደግ ማልማት የሚችሉት ሰዎች ቦታቸው ላይ ደርሰዋል ነገር ግን ቆመዋል ምንም አይሰሩም ::
አንዳንዴ እንዲህ የሚል ጥያቄ ይፈጠርብኛል ... ለሃገሩና ለወገኑ እድገትን ለማምጣት ፍጹም ዴሞክራሲን ለማስፈን ወዘተ መስዋዕትነት የሚከፈለው ጫካ ውስጥ ብቻ ነው ማለት ነው ?
በመቶ ሺህ የሚቆጠር ዜጋ የወደቀላቸው ዓላማዎች አንዳቸውም እውን ሲሆኑ አልታዩም ይሄ ለምንድር ነው ?
ስለዚህ የምወዳችሁ ወንድሞቼ ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል እንዲሉ ነውና ባዶዬን እንዳልቀር ዝም ልበል::

ቸር ያቆየን ወዳጃችሁ አደቆርሳ ዘሃገረ አዶላ

Re: የጀምጀም ልጆች መገናኛ

Posted: 22 Apr 2013 07:04
by ራስብሩ
ጤና ይስጥልኝ
አውሮፓና አሜሪካ የበረዶ ወራት ሲወጣ ቤታችን ደሞ መግባቱ ነው መሰለኝ መቀዝቀዝ ጀምሯል
ከላይ እስከታች እንደምን አላችሁ
በፌስቡክ ወደ አዶላ ካፌ ሩም ውስጥ በፊት የጻፍናቸውን አንዳንድ ወጎች አየሁኝ
ደስ የሚል ትዝታ ነበር:
ዛሬ አንድ የመወያያ ርዕስ ይዤ ነው የመጣሁት
በአሁን ጊዜ በጣም በብዛት የአለም ሜዲያዎች የመነጋገሪያ ጉዳይ ከሆኑት ውስጥ የኢትዮጵያ ስደተኞችች ሁኔታ ዋነኛው ነው :
በድንበር በኩል የሚወጡ ኢትዮጵያውያን በጣም አሰቃቂ ህይወት ውስጥ ናቸው በተለይ በአንዳንድ አማተር ቨዲዮዎች
(በሞባይል) በሚቀረጹ ምስሎች እንዲሁም በዩ ቱዩብ
በሚለቀቁ ሁሉ የኢትዮጵያውያንን ስቃይ ለማየት በሚከብዱ ሁኔታዎች እናያለን ::
ወንዝ ውስጥ ይጣላሉ: የውስጥ አካላቸው ይወሰዳል: ይደፈራሉ : ሁሉንም በመገናኛ ብዙሃን የምንሰማው ነው
የአሜሪካና የጀርመን ድምጽ ራዲዮ ከኢትዮጵያ መንግስት ከሚባሉት ጋርም ሲያነጋግሯቸው እንሰማለን ከስደተኞችጋርም እንዲሁ እንሰማለን ::
እኛ ምንም ትልቅ ነገር ማረግ ባንችልም የሚሰማንን አስተያየት መስጠት አለብን ብዬ አምናለሁ::
በውነት በጣም ነው የሚያስጨንቀው ምናልባት ለአለም የስደተኞች ድርጅት ይሁን ለአሜሪካ መንግስት እንዴት ነው አቤት የሚባለውስ?
ማለቴ በቀጥታ ለማን ነው መጮህ የሚቻለውስ ?
እስቲ መፍትሄ ባናመጣም በመፍትሄ ዙሪያ ያላችሁን አስተያየት ሰንዝሩ !

ራስብሩ

Re: የጀምጀም ልጆች መገናኛ

Posted: 22 Apr 2013 08:11
by አንፈራራ
ሰላም ወገኖች

ራስብሩ ያነሳኸው ርዕስ በጣም የሚያሳስብ ነው። ይኸው ርዕስ በፌስቡክ እየተነሳም ውይይት ተካሂዶበታል፣ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራዉያንና ሱማሊዎች ናቸው የዚህ ዓይነት ስደት ሰለባ የሆኑት። አንዳንዴ ዓረቦች በነዚህ ስደተኞች ላይ የሚፈጽሙትን በደል በቪዲዮ አይቶ መጨረስ እንኳን አይቻልም። በዚሁ ርዕስ ዙሪያ ስንወያይ እና እነዚያም ስደተኞች ከአገር ለመውጣት ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ሀብታቸውንና ንብረታቸውንም በመሸጥ እንዲህ ዓይነቱን መስዋዕት ሲያደርጉ፣ ድርጊታቸው ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም። የውይይቱ ተሳታፊ የነበረች አንዲት ልጅ እንዳለችው "ግን ለምን?"

እነዚህ ሰዎች አረብ አገር ለመሄድ ይህን ሁሉ ገንዘብ አፍሰው መጨረሻቸው መሰቃየት ከሆነ "ግን ለምን?" የሚለው ጥያቄ ትክክለኛ ይመስለኛል።