ይወስዳል መንገድ፣ ያመጣል መንገድ

ግጥሞች፣ታሪኮች፣ፎቶዎች፣ሙዚቃዎች
Poems,Short stories, graphics,pictures,musics,Technology
Post Reply
User avatar
girreda
Runner
Runner
Posts: 55
Joined: 01 Oct 2009 12:45
Location: Adama University
Contact:

ይወስዳል መንገድ፣ ያመጣል መንገድ

Unread post by girreda » 20 Dec 2009 10:36

አዲስ አበባ ሜክሲኮ፡፡ ኅዳር 2 ቀን 2002 ዓ.ም.፡፡ ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት አይናፋሩ ማርቸዲስ አውቶቡስ ፊቱን ወደ ሰሜን አዞረ፡፡ የሁለት ሰዓት ቀጠሮ ከተጠበቀው በላይ ረዘመ፡፡ 2፡30፣ 3፡00 እያለ 4፡00 ሰዓት ሲሞላ ቦታ ቦታችን እንድንይዝ ተደረገ፡፡ አዲስ አበባ እንቅስቃሴዋን እያቀላጠፈች ነበር፡፡
አይናፋር መንገድ ጀመረ፡፡ ሰው እንደየ ፍላጎቱ የሚያነበው ያነባል፣ የሚያወራውም ያወራል፡፡ አምበርብር የመንገዱን ትዕይንት ለመመዝገብ ማስታወሻውን ይዟል፡፡ የአዲስ አበባ መንገዶችን እያቆራረጥን በደሴ በር ወጣን፡፡ መንገዱ ፈርሶ እየተሠራ ነው፡፡ አንዴ በተቀያሪው ጥርጊያ፣ አንዴ በአስፋልቱ እያለ አውቶቡሳችን መንገዱን ይፈጨው ገባ፡፡ ጭሱን እያጨሰ፣ አቧራውን እያቦነነ፡፡

ከሜዳማው፣ ተራራማው ይበልጣል፡፡ ከቀጥታው፣ ጠመዝማዛው ይበልጣል፡፡ አውቶቡሳችን ከሌሎቹ ጋር ሲወዳደር ዘገምተኛ ነበር፡፡ መኪናው ልሂድ እያለ፣ ሾፌራችን ልጓም እየያዘ የሚቀድመን በዛ፡፡ ይህንን የተመለከቱ ተጓዦች አጉረመረሙ፡፡ ቅያሪ ሾፌር ጠየቁ፡፡ ይህንን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ቴክኒሻኖችና የጉዞ አስተባባሪዎች እየተከታተሉት ነበሩ፡፡ ጠመዝማዛውን መንገድ የሚያሸንፉ ሌላ አሽከርካሪ ተተኩ፡፡ ከመንገድና ከሕይወት እንዳንቀር ለሚመለከተው ማሳሰቢያ ሰጠን፡፡ ምክንያቱም ቀን የጎደለበት መንገድ ላይ ተገልብጦ አይተናልና፡፡

በ2001 በፈረቃ ያማረረን ማብራት ዘንድሮ መፍትሄ እንደሚገኝለት ተነግሮናል፡፡ ብርሃን ይሰጡናል ተብለው ከሚጠበቁት መካከል ተከዜ አንዱ ነው፡፡ የመብራት ጉድለታችንን ተከዜ ሊያሟላልን እንደሆነ ስንሰማ ጓጓን፡፡ ማየት ማመን ነው የሚለውን ብሂል በመቀበል አምበርብር ለማየት ተጣደፈ፡፡ ተጣድፎ ግን በአንድ ቀን የሚሳካለት አልሆነም፡፡ ለመድረስ ብቻ ሦስት ቀናት አስፈለጉ፡፡

ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ሸኖ ደረስን፡፡ ሸኖ ላይ ቁርሳችንንም ምሳችንንም አንድ ላይ አጠናቀቅን፡፡ ሸኖ የምትታወቅበት ቅቤ ግን ልንቀምስ አልታደልንም፡፡ ዕለቱ ረቡዕ ነውና ቤት ያፈራውን ቀማምሰን ጉዟችንን ቀጠልን፡፡ የጎደለውን መኪና ውስጥ ገብተን በውኃ አስተካከልነው፡፡

ለማንጠግቦሽ ስልክ መታሁላት፡፡ ከሰፈራችን ኢንዱስትሪ መንደር የሚወጣውን ኃይለኛ ጭስ ምጋ፣ ምጋ ተኛች፡፡ ሐኪም (የጤና ቢሮ) ጭሱ ለመተንፈሻ አካላት ህመም እንደሚያጋልጥ ከነገራት ቆይቷል፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር ሲፈልግ መኖሪያ ቤትና ኢንዱስትሪ መንደርን ያቀላቅላል፣ ሲፈልግ ይለያያል፡፡

የተበተነው ሃሳቤን መለስ አደረግኩት፡፡ መንገዱ ተተርትሮ እየተሰፋ ነው፡፡ ፈርሶ እየተገነባ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ችሎ አይናፋር አውቶቡስ መንገዱን ፈጨው፡፡ ደብረብርሃን ስንደርስ ቀዝቃዛውን አየር ለማስወገድ፣ ፀሐይ ያለ የሌለ ጉልበቷን ተጠቅማ አገኘናት፡፡ ቅዝቃዜው መኪና ውስጥ ላለነውም ደርሶናል፡፡ የደብረ ሲና ዋሻ ጣራው እያፈሰሰ ነበር፡፡ የነፍስ የዓለም ውኃ?

የሰሜን መንገድ፣ የሰሜን ተራራዎች ብዙ ተአምር አይተዋል፡፡ የአንድ እናት ልጆች በዓላማ ተለያይተው ብረት ተማዘውባቸዋል፡፡ ሰው እንደ ጉድ የተጨፋጨፈባቸው፣ የተገዳደለባቸው፣ ደም እንደ ውኃ የፈሰሰባቸው". ተራሮች፡፡ ሰማይ ለሰማይ የሚንጠራሩ ተራሮች፡፡ እጅ ለእጅ የተያያዙ፣ ሰንሰለታማ ተራሮች፡፡ የተራራ ስብሰባ፣ የተራራ ጉባዔ፡፡ ዶሮ ግብር፣ ቆቦ፣ ዋዳ፣ አላማጣ፣ ኮረም".፡፡ ለተራራ አገልግሎት ብቻ ተብሎ የተከለለ ይመስል ዙሪያው በሙሉ ተራራ በተራራ ነው፡፡

የአላማጣው ጠመዝማዛ፣ ቁልቁለታማና ዳገታማ መንገድ ቁና ቁና አስተነፈሰን፡፡ ነፍስ ውጪ፣ ነፍስ ግቢ፡፡ አይናፋር አውቶቡስ፣ በተራራ ወገብ ተጠምጥሞ በተሠራው መንገድ ዚግዛግ እየሠራ የሞት ሽረት ትግሉን ቀጥሏል፡፡ እዚህ ቦታ ላይ ለብልሽት የተዳረገ መኪና ዕጣ ፈንታው ምን እንደሚሆን ሲገምቱት ይቀፋል፡፡ እዚህ መንገድ ላይ ለአፍታ የተዘናጋ ሾፌር አለቀለት፡፡

አውቶቡሳችን በመታመሙ መቆም ግድ ሆነብን፡፡ ሰዓቱ እየሄደ ነው፡፡ ተጓዦች እየተዳከሙ ነው፡፡ ለአውቶቡሳችን ሕክምና ለመስጠት ርብርሩ ቀጠለ፡፡ እንደፈራነው አልሆነም፡፡ ታክሞ መንገድ ጀመረ፡፡ ሌላ ንባብ፣ ሌላ ሃሳብ፡፡

የሰሜን ሸለቆዎች፣ ጉብታዎች፣ ፈፋዎች".ተራራዎች ደረታቸውን ገልብጠዋል፡፡ የምድርን ሰቆታ ላለመስማት ጆሯቸውን የያዙ ተራራዎች፡፡ እንደ እባብ የሚጥመለመል መንገድ፡፡ ተፈጥሮ የተፈተነበት፣ በተራው ደግሞ የተፈተነበት ቦታ፡፡ ኩሩ አበሾች፣ ኩሩ ተራሮች፡፡ በተራራ የተከበቡ ከተሞች፡፡

የታረሰ፣ የተቀደደ፣ የተቆረጠ፣ የተቦተረፈ፣ የተነጨ መንገድ፡፡ ውኃን በብልሃት ያቃጥሉታል እንዲሉ፣ ከተራራ እምብርትም በብልሃት መንገድ ይወጣል፡፡ በባለሙያ አስፋልት ይገነባል፡፡

ደሴ ፈርሳ እየተሰራች ነበር፡፡ "አረ ደሴ ደሴ፣ ገለል በል ገራዶ፤ አለቀልሽ ልቤ ተንዶ ተንዶ" የተባለላት ደሴ፡፡ ብዙ ድምፃውያን ጉሮሯቸውን ያሟሹባት፡፡ አሃዱ ያሉባት ደሴ፡፡ መንገዱ ተሠርቶ ሲያልቅ የሚመጣው ውበት እያሰቡ መጽናናት ይቻላል፡፡ የደሴ የውኃ እጥረት ግን መቼ ምላሽ ያገኝ ይሆን?

ለአምበርብር ዓይነቱ ደላላ፣ መንገድ ቢከብደው አይገርምም፡፡ በአዲስ አበባ መንደሮች ተወስኖ የቆየ ደላላ ስለሆነ፡፡ ይሁን እንጂ ማየት መልካም ነው፡፡ ዘመኑ አንድ ቦታ ተወስኖ መቆየት አይፈቀድምና አምበርብር ወጣ ወጣ ማለት አለበት፡፡ ደንበኞቹን ለማብዛት፡፡

ደሴ ወደ ጎን ለመስፋት ገራዶንና ጦሳን ማስፈቀድ አለባት፡፡ በግራና በቀኝ ገድበዋታልና፡፡ በቀጭኑ ግን በተራራዎች መሃል እየተለጠጠች ነው፡፡ በወዲህም በወዲያም ተራራ ቀስፎ ይዟታል፡፡ በፈለገችበት አቅጣጫ የመስፋፋት ዕድል የላትም፡፡ በዚህ መስመር ያሉት ከተሞች ብዙዎቹ ከተራራ ጋር እንቁልልጭ የሚጫወቱ ይመስላሉ፡፡

አላማጣን፣ ኮረምን፣ አሸንጌ ሐይቅን አልፈን ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት መቀሌ ተቀበለችን፡፡ በመቀሌ ቤት ያፈራው ተቋደስን፡፡ ጎናችንን ለማሳረፍ መዟዟር ጀመርን፡፡ አምበርብር ወገቤን ማለት ከጀመረ ደቂቃዎች አልፈው ነበርና ለማረፍ ቸኮለ፡፡ በእራት ላይ የጠፋው ሰዓት ቀላል አልነበረም፡፡

መቀሌም እንደ ደሴ የውኃ እጥረት አለባት፡፡ በዚህ መስመር ያሉ ከተሞች አንዱ ፈተናቸው ውኃ ነው፡፡ በአቧራና በሙቀት ለዋለ ሰውነት የሚሆን ውኃ ማግኘት የሚቻለው በስለት ነው፡፡ ችለን፣ ተቻችለን ወገባችንን አሳረፍን፡፡ በማግስቱ በጧት መነሳት ስለነበረብን በጧት ለጉዞ ዝግጁ ሆንን፡፡ ወደ ተከዜ፡፡

መንገድ ውሎ፣ መንገድ ላይ ማደር፡፡ መንገድ ላይ መክረም፡፡ አምበርብር በየሰዓቱ አዲስ አበባ፣ ደንበኞቹ፣ ማንጠግቦሽ ወዘተ. ውልብ ይሉበታል፡፡ ከቤቱ የወጣ እቤቱ እስኪመለስ፣ ቢጭኑት አህያ ቢለጉሙት ፈረስ ነውና ይሄደዋል መንገዱን፡፡

ሰላም ባስ ወደ ተከዜ ይዞን ሊበር ከተፍ አለ፡፡ አንድ መቶ አርባ ስምንት ኪሎ ሜትሩን መንገድ በአንድ ሰዓት ከ30 ይጨርሰዋል የሚል እምነት ነበረኝ-እኔ በበኩሌ፡፡ እኔ እንዳሰብኩት ግን ቀላል አልሆነም፡፡ ሐገረ ሰላምን አልፈን ይህም አውቶቡስ ታመመ፡፡ ሕመሙ የበረታ ሆነ፡፡ የውስጥ አካሉ ተናወጠ ተባለና ሰዉ ወረደ፡፡ ወደየፈለገበት ተበተነ፡፡

ከመቀሌ መኪና እስከሚላክ ብዙ ሰዓቶች በከንቱ ባከኑ፡፡ በጧት ተከዜ ግድብ እንደርሳለን ተብሎ ታቅዶ ሳይሆን ቀረ፡፡ ከሰዓት በኋላ ሌላ መኪና ተልኮ ጉዞ ቀጠልን፡፡ ተከዜ ባንዲራዋን ሰቅላ፣ ጽሑፎችን አዘጋጅታ ጠበቀችን፡፡ ሰው እየጎረፈ ነው፡፡ የመሃል አገር ሰው ግልብጥ ብሎ መጥቷል ወይ እስኪባል ድረስ፡፡

ተከዜ እንግዶቿን ለማስተናገድ ወገቧን ያዘች፡፡ ልጆቿ ላባቸውን አንጠፈጠፉ፡፡ የበረሃው ሙቀት ይጋረፍ ጀመር፡፡ ውሃ ይጠጣል፣ ውኃ ይወጣል፡፡ እኛ ለአንድና ለሁለት ቀን እንዴት መቋቋም ያቅተናል? ሰው እዚያ እየኖረ ፈታኝ ግድብ ገድቧል፡፡ ፈታኝ ግድብ ገድቦ መብራት አብርቷል፡፡

መንገድ ላይ ሲከታተሉን የነበሩ ተራሮች እስከ ተከዜም አልተለዩንም፡፡ የሰሜን ተራሮች፡፡ ሰንሰለታማ ተራሮች፡፡ "መንገድ ዓይንህ አፈር አይባልም ደርሶ፣ የወሰደውን ሰው ያመጣል መልሶ ተብሏል፡፡" ደህና ሁኑ፡፡ ሰላም"[center][/center]

User avatar
girreda
Runner
Runner
Posts: 55
Joined: 01 Oct 2009 12:45
Location: Adama University
Contact:

ፍቅር

Unread post by girreda » 20 Dec 2009 10:56

"ይናገራል እንባ "

በክህደት በደል
በሽፍጥና ተንኮል
በሞት ሀዘን ጊዜ
እምነት በማጉደል
ሲታጣ ደጋፊ
የሰው ችግር አይቶ
ፍቅር ቃሉ ሲቀር
ተግባሩ ተረስቶ
ይናገራል እንባ
የውስጥን አውጥቶ::

ፍቅር
እንደማለዳ ፀሀይ ብርሀንስትፈነጥቅ
እንደ ባህር አልማዝ ስትፍለቀለቀለቅ
እንደ እሳት ላንቃ አብረቅርቃ
ከቀተር ፀሀይ በርታ ደምቃ
ስተጀምር ማለት ድንግዝግዝ
መባባት አይቀት መተከዝ


ግን ፍቅር ........
ፀፀት ትዝታን ድርድራ
ምኞትን ከህልም አዋቅራ
በብቸኝነት ስትማቅቅ
ቀን ከሌሊት አትል ስትጨነቅ
ፍቅር ......
ብርቅርቅታ ናት ታበራለች ቀን ጠብቃ
እንደጨለመች አትቀርም እንዳኮረፈች ተደብቃ
ውሎ ቢያደርም ታበራለች በህብረቀለማት አሸብርቃ ::

Post Reply

Return to “Ethio Art and Culture..ኢትዮ ጥበብ ፤ስነ ጽሁፍ ፤”