የወጣቱ ችግር የሚነገረው በማን?

ግጥሞች፣ታሪኮች፣ፎቶዎች፣ሙዚቃዎች
Poems,Short stories, graphics,pictures,musics,Technology
Post Reply
User avatar
girreda
Runner
Runner
Posts: 55
Joined: 01 Oct 2009 12:45
Location: Adama University
Contact:

የወጣቱ ችግር የሚነገረው በማን?

Unread post by girreda » 20 Dec 2009 10:25

(በምሕረት አስቻለው)

ዘርፈ ብዙ እንደሆነ የሚነገርለትን የወጣቱን ችግር ለመፍታት በማሰብ ከቅርብ ቀናት በፊት የተደረገውን ጨምሮ ሶስት አገራዊ የወጣቶች ኮንፈረንሶች በአዲስ አበባ ተካሂደዋል፡፡ ከተለያዩ ክልሎች ተወክለው በኮንፈረንሶቹ ላይ የተገኙ በርካታ ወጣቶችም ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር ወጣቱን በሚመለከቱ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡ ሶስቱ አገራዊ የወጣቶች ኮንፈረንስ ላይ የተነሱ የወጣቱን ችግሮች፣ የወጣቶቹን ተሳትፎና የወጣቱን ችግሮች በመፍታት ረገድ የተስተዋሉ ለውጦችን በማስመልከት ወጣቶችን አነጋግረናል፡፡

ዲግሪውን ከያዘ አምስት ዓመት ሆኖታል፡፡ በተለያዩ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ የሰራ ሲሆን፣ አሁንም በአንድ መንግስታዊ ባልሆነ እርዳታ ድርጅት ውስጥ ፕሮጀክት አስተባባሪ ሆኖ በማገልገል ላይ ነው፡፡ የሚሰራበት ድርጅት በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ውስጥ ከሚገኙ ቀበሌዎች ጋር እንደሚሰራ በዚህም በቀበሌዎች ያሉ የወጣቶችን ጨምሮ የተለያዩ አደረጃጀቶችን የመመልከት እድል እንዳገኝ አጫውቶናል፡፡

ወጣቱ እንደሚለው አገራዊ የወጣቶች ስብሰባ የወጣቱን ችግር ከመፍታት ባለፈ ወጣቱን ባለራዕይና የወደፊት መሪ ከማድረግ አንፃር ትልቅ ግምት የሚሰጠው ቢሆንም በወይይት መድረኩ ላይ ከተለያዩ ክልሎችና ከተሞች ተወክለው የተገኙት ወጣቶች በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ወጣት ይወክላሉ ወይም የወጣቱን ችግር ያንፀባርቃሉ ብሎ እንደማያምን ገለፀልን፡፡ እኛም ለምን? ብለን ጠየቅነው፡፡ "ከተለያዩ ክልሎች ወይም ከተሞች ስለተሰባሰቡ የተማረውን፣ ሥራ አጥ የሆነውና በገዢው ፓርቲ የፖለቲካ አደረጃጀት ያልታቀፈውን ወጣት ፈጽሞ ይወክላሉ ማለት አይቻልም፡፡ ከእድሜ አንፃርም በውይይት መድረኩ ላይ ተሳታፊ የነበሩትን ብንመለከት ወጣቶች ናቸው ማለት ይከብዳል፡፡ ከዚህ አንፃር ከውይይቱ ምን ዓይነት ውጤት ይጠበቃል?" ብሎናል፡፡

በወጣቱ እይታ ከጥቂት ቀናት በፊት በተደረገው አገራዊ የወጣቶች ኮንፈረንስ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ወጣቶች ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት በገዢው ፓርቲ የተለያዩ የቀበሌ አደረጃጀቶች የታቀፉ ስለሆኑ እንጂ በእድሜ ወጣት የሚባሉ አይደሉም፡፡ ከዚህ አንፃር ሊነሱ የሚገባቸው የወጣቱ ችግሮች ለውይይት መቅረባቸውን፣ የስብሰባውን አስፈላጊነትና ውጤት ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል፡፡ "በሶስተኛው አገራዊ የወጣቶች ኮንፈረንስ ላይ ወጣቶቹ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ምስል ያለበትን ነጭ ቲሸርት ለብሰው ይታያሉ፡፡ ምን ለማለት ነው የተፈለገው? አብዛኞቹ የተሰባሰቡት የኢህአዴግ ካድሬዎች ናቸው፡፡ ኮንፈረንሶቹንም እንደማንኛውም ፕሮፖጋንዳ ነው የምመለከታቸው"

እሱ እንደሚለው በተለያየ መልኩ የወጣቶችን ሥራ አጥነት ከመፍታት አንፃር ተደጋግሞ የሚጠቀሰው የተደራጁ ወጣቶች ከአነስተኛና ጥቃቅን የብድር ተቋም ብድር የሚያገኙበት አሰራር እንኳ ብድር ማግኘት የሚችሉት ምን ዓይነት ወጣቶች ናቸው? በጥቃቅንና አነስተኛ ብድር ተደራጅተው ከሚንቀሳቀሱ ምን ያህሉ ውጤታማ ሆነዋል? የሚሉና ሌሎችንም ተመሳሳይ ጥያቄዎች ይነሱበታል፡፡ "ማንኛውም የተደራጀ ወጣት ከጥቃቅንና አነስተኛ የብድር ተቋም ብድር ማግኘት ይችላል ቢባል እንኳ የወጣት ሊግ ወይም የወጣት ፎረም አባል በመሆናቸው በተደረገላቸው ተደጋጋሚ ድጋፍ ተሳካላቸው ተብለው በተደጋጋሚ የምንመለከታቸው ጥቂት የተደራጁ ወጣቶች የቀሪዎቹን ሁኔታ ያሳያሉ ብዬ አላምንም"

የድህረ ምረቃ ትምህርቷን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመስራት ላይ የምትገኝ ወጣትም በተለያዩ ጊዜ የተደረጉ አገራዊ የወጣቶች ኮንፈረንሶችን ፋይዳ ወጣቶችን የጥቃቅንና አነስተኛ የብድር ተቋም ተጠቃሚ ከማድረግ፣ የማምረቻ ቦታ ከማግኘት እንዲሁም አዳዲስ ምሩቃንን ሥራ ከማስያዝ አንፃር በአዎንታዊነቱ ትመለከተዋለች፡፡ ነገር ግን በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የገዢውን ፓርቲ የፖለቲካ አቋም መደገፍ ወይም የፓርቲ አባልነት እንደ መመዘኛ መታየታቸው አዎንታዊ የሚባሉትን መሻሻሎች ኢምንት እንደሚያሰኛቸው ትናገራለች፡፡

ያነጋገርነው ሌላ ወጣት ደግሞ አብዱገስፋር ሁሴን ይባላል፡፡ የኢኮኖሚክስ ዲግሪ ምሩቅ ሲሆን በአገራዊ ወጣቶች ኮንፈረንሶች ላይ ተሳታፊ የሆኑ ወጣቶች በቀበሌ በፖለቲካም ሆነ ከፖለቲካ ውጭ ከሆነ አደረጃጀት የተውጣጡ መሆናቸውን ከዚህ አንፃርም የተለያዩ የወጣቶችን ችግሮች በውይይት መድረኩ ላይ ሊያነሱና ሊወያዩ የሚችሉ እንደሆኑ ይናገራል፡፡ "ከወጣት ሊግ የተወከሉት የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ቢሆኑም ከወጣት ማህበራት የተወከሉት ፖለቲካዊ ተሳትፎ ያላቸው ወይም አባል ናቸው ማለት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ከዚህ አንፃር የወጣቱ ውክልናና ተሳትፎ ችግር የለበትም" ብሎናል፡፡

የወጣቱን ችግር በመፍታት ረገድ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተስተዋሉ ለውጦች መኖራቸውን፤ የተደራጁ ወጣቶች ስራ እንዲሰሩ የሚያስችል የብድር አገልግሎት የሚያገኙበት መንገድ መመቻቸቱ ጉልህ እርምጃ መሆኑን ገልጿል፡፡ ከጥቃቅንና አነስተኛ ማንኛውንም አይነት የብድር አገልግሎት ለማግኘት ወጣቶች ላይ የሚቀመጥ ምንም አይነት የፖለቲካ መመዘኛ አለመኖሩንም በእርግጠኝነት ይናገራል ወጣት አብዱገስፋር፡፡[center][/center]

User avatar
girreda
Runner
Runner
Posts: 55
Joined: 01 Oct 2009 12:45
Location: Adama University
Contact:

ያወቀ . . .

Unread post by girreda » 20 Dec 2009 10:27

(በትዕግስት ዘሪሁን)[center][/center]
"አንዳንዴ የሚያስደነግጥ ነገር እናያለን፡፡ ወጣትነት አፍላነት እንደመሆኑ ወጣቶች ያዩትንና የሰሙትን ነገር ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚጣደፉበት እድሜ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የድንገተኛ እርግዝና መከላከያ ፈልገው ወደ ማዕከላችን ከሚመጡ ወጣቶች ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊ ሕፃናት ቁጥራቸው ይበዛል፡፡

ይሄ አስደንጋጭ ነው፡፡ የዕርግዝና መከላከያውን መጠቀም ሳይችሉ ቀርተውም ውርጃ መፈፀም የሚችሉበትን ቦታ እንድንጠቁማቸው የሚጠይቁን በርካቶች ናቸው" ይሄንን ያለን በቤተሰብ መምሪያ የሸገር ወጣት ማዕከል የወጣቶች ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሰብሳቢ የሆነው ወጣት ያሬድ ብርሃኑ ነው፡፡ በወጣት ማዕከሉ ውስጥ እያገለገለ ያለው በበጎ ፈቃደኝነት ነው፡፡

ወደ በጎ ፈቃደኝነት ስራው ሲገባ የመጀመሪያው ፍላጎቱ ስለ ስነተዋልዶ ጤና መረጃዎችን በማግኘትና በማወቅ ለራሱ መጠቀም ነበር፡፡ በስራው በቆየበት ጊዜ ግን ከራሱ አልፎ በሃገራችን በተለይ በወጣቶች ላይ የሚታየውን የስነ ተዋልዶ ጤና ችግር ለመቅረፍ በሚደረገው ስራ ላይ የራሱን አስተዋፅኦ ለማበርከት እንደቻለ ይናገራል፡፡ ከመሰል ጓደኞቹ ጋር ወጣቶችን በፈቃደኝነት ለማገልገል የተለያዩ ስራዎችን ይሰራል፡፡ ወርሃዊ የኪነ ጥበብ መድረክ በማዘጋጀት ሙዚቃ፣ ድራማ፣ የመኪና ላይ ቅስቀሳ በየሦስት ወር በሚታተም ጋዜጣ ላይ በመፃፍና የመሳሰሉ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ወጣቶች ስለ ስነተዋልዶ ጤና መረጃው እንዲኖራቸውና ራሳቸውን እንዲጠብቁ ለማስቻል እንደሚሰሩ ጠቁሟል፡፡

"አንዳንድ ወጣቶች ባህሉን እየለቀቁ ነው በኢንተርኔት ጠቃሚ መረጃዎችን ከመፈለግ ይልቅ የወሲብ ፊልሞችን ማየት ይመርጣሉ፣ በሕገወጥ ቪዲዮ ቤቶችም ይሄንኑ ያያሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በሱስ ተጠምደዋል፡፡ ጫት በመቃምና መጠጥ ቤት በማምሸት ጊዜ የሚያጠፉ አሉ" ይላል ወጣት ያሬድ ከስራው ተሞክሮና ከአካባቢው ያስተዋለውን በመጥቀስ፡፡

"የወደፊት ሕይወት የተቃናም የተጣመመም የሚሆነው በወጣትነት በሚሰራ ተግባር ነው" የሚለው ያሬድ የ23 ዓመት ወጣት ነው፡፡ ቀኑን ሙሉ በበጎ ፈቃደኝነት ስራ ላይ ተጠምዶ እንደሚውል ይናገራል፡፡ እሱ እንደሚለው ትርፍ የሚባል ጊዜ የለውም፡፡ በአዲስ አበባ ለሚገኙ አምስት የወጣት ማዕከላት ተጠሪ እንደመሆኑ መጠን ወጣቶችን ለመምራትና ለማስተማር የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመስራት ጊዜውን ያሳልፋል፡፡ ጎን ለጎንም በሕግ ትምህርት ዲፕሎማውን ይዟል፡፡ በሙያውም በኮንትራት የተለያዩ ስራዎችን ይሰራል፡፡ አሁንም በማታው ክፍለ ጊዜ በሌላ ሙያ እየተማረ እንደሆነ ይናገራል፡፡ በስራ በመጠመዱም ለተለያዩ ሱሶች እንዳይጋለጥና አልባሌ ቦታ እንዳይውል አድርጎታል፡፡ "ለመሄድ እንኳን አላስበውም፡፡ ሌሎች ወጣቶችን ጥሩ ስነ ምግባር ይኑራችሁ እያልኩ ስመክር ብውል የኔ ስነ ምግባር የተበላሸ ከሆነ ውጤት አይኖረውም፡፡ ምሳሌ መሆን እንዳለብኝ አምናለሁ፡፡ በወጣትነታችን ብንማርና ብንሰራ ጥሩ ራዕይ ይኖረናል፡፡ ወጣቱ ስሜቱ እንደመራው ከመጓዝ ይልቅ ቆም ብሎ ማሰብና ማስተዋል፣ ለመማርና ለማወቅ መጣር አለበት፡፡ ያወቀና መረጃው ያለው ሰው ይጠነቀቃል፡፡ መማርም የወደፊቱን ሕይወት የተቃና ያደርጋል" ሲል ይመክራል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ ወጣቶች ዘንድ እየተስተዋለ ያለው ያለ እድሜ ወሲብ መጀመርና ልቅ ወሲብ መፈፀም እንደሚያሳስበው ይናገራል፡፡ የበኩሉን ለማበርከት በበጎ ፈቃደኝነት ሲንቀሳቀስ ቢቆይም ለወደፊቱ ግን በተማራቸው ሙያዎች በመስራት የራሱን ሕይወት ለመኖር እየተዘጋጀ እንደሆነ ገል"ል፡፡

ወጣት እፀገነት አሰፋም በሸገር የወጣቶች ማዕከል በበጎ ፈቃደኝነት በማገልገል አራት ዓመቷን ይዛለች፡፡ አሁን በ25 ዓመቷ ከበጎ ፈቃደኝነት ስራዋ ጎን ለጎንም ነርሲንግ በማጥናት ዲፕሎማዋን ይዛለች፡፡ በበጎ ፈቃደኝነት በመስራቷ ለራሷ ስለ ስነተዋልዶ ጤና የተሻለ ለማወቅ መቻሏን በመጥቀስ በምትሰጠው አገልግሎትም የብዙ ወጣቶችን ሕይወት ለመቀየር እንደቻለች ትገምታለች፡፡

ይሁንና እንቅፋቶች እንደነበሩባት ታስታውሳለች "ቤተሰቦቼ 24 ሰዓት ስትዞሪ እየዋልሽ ያንቺ ጥቅም ምንድነው ይሉኝ ነበር፡፡ ስለ በጎ ፈቃደኝነት ካላቸው ዝቅተኛግንዛቤ የተነሳ ነው፡፡ ለኅብረተሰቡ የማሰራጫቸውን የወሊድ መከላከያ ኪኒንና ኮንዶሞች ወደ ቤት ስወስድ እናቴ ትቆጣ ነበር፡፡ ከብዙ ትግል በኋላ ነው የተቀበለችኝ"

እፀገነት እንደምትለው የስነ ተዋልዶ ጤናን በተመለከተ ለወጣቱ በተለያየ መልኩ ትምህርት ቢቀርብለትም ከሚሰማው የማይሰማውና የሚያላግጠው ይበዛል፡፡ ጫት ቤት ውስጥ ገብተው በሚያስተምሩበት ወቅት ወጣቶች ይደሰታሉ፡፡ የሚያስደስታቸው ግን የሚያገኙት ትምህርት ሳይሆን በነፃ የሚታደላቸውን ኮካኮላ ለጫት መቃሚያ ስለሚጠቀሙበት መሆኑን ከአንደበታቸው እንደሚሰሙ ትናገራለች፡፡

"ጫት ቤት ስንሄድ ዛሬ ለበርጫ ኮካ አናስብም ይሉሻል፡፡ ትምህርቱን በተመለከተማ አይሰሙም ያላግጡብሻል፡፡ ዛሬ ስለ ወሊድ መከላከያ ጥቅምና እንዴት እንደሚወሰድ ስናስተምር አምሽተን ቁጭ ብለው ሲማሩ ያመሹ የ13 እና የ14 ዓመት ታዳጊ ሕፃናት በማግስቱ የድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ሊጠይቁን ይመጣሉ" ትላለች እፀገነት፡፡

አንዳንድ ወጣቶች ስለ ስነተዋልዶ ጤና በተለያዩ መድረኮች በተለያዩ ዘዴ ቢማሩም ተግባር ላይ እንደማያውሉት ያነጋገርኳቸው ሁለቱም ወጣቶች ይገልፃሉ፡፡ እንዲያውም ጉዳዩ እያሳሰባቸው በተገናኙ ቁጥር እንደሚወያዩበትም ገልፀውልኛል፡፡ የየራሳቸውን ስራ ይዘው ሙሉ ጊዜያቸውን ለራሳቸው ሕይወት እስኪያውሉ ድረስ ግን ሁለቱም ወጣቶች ወጣቱ ላይ የተጋረጠውን እንደ አባላዘር በሽታና ኤች አይቪ ኤድስ የመሳሰሉ የስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች ለመቅረፍ የቻሉትን አስተዋፅኦ ለማድረግ እየሰሩ የሚቀጥሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

User avatar
girreda
Runner
Runner
Posts: 55
Joined: 01 Oct 2009 12:45
Location: Adama University
Contact:

አምስት ሴቶች የኖቤል ሽልማቱን ተቀበሉ

Unread post by girreda » 20 Dec 2009 10:30

በያዝነው የፈረንጆች ዓመት በዓለም ላይ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ከሆኑ 13 ሰዎች መካከል አምስቱ ሴቶች ናቸው፡፡

ያለፈው ሐሙስ ስዊድን ስቶክሆልም ላይ በተደረገ የሽልማት ሥነ ስርዓት አምስቱም አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላር ሽልማታቸውን ከስዊድን ንጉስ ካርል 16ኛ ተቀብለዋል፡፡
ከተሸላሚ ሴቶች መካከል ፀሐፊና ተመራማሪ ይገኙበታል፡፡ አምስቱ ሴቶች፤ በኬሚስትሪ፣ በፊዚክስ፣ በሜዲስን፣ በሥነ ጽሑፍና በኢኮኖሚክስ ዘርፍ ሽልማታቸውን ከመቀበላቸው ከሰዓታት በፊት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ኦስሎ ላይ ሽልማታቸውን እንደተቀበሉ ቺካጎ ትሪቢውን ዘግቧል፡፡

የኖቤል ሽልማት መስጠት ከተጀመረበት እ.ኤ.አ 1901 ጀምሮ እስካሁን ድረስ 40 ሴቶች ለሽልማቱ በቅተዋል፡፡

በሽልማት ሥነ ስርዓቱ ላይ እንደተገለፀው የህንድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ኤሊሃር አስትሮም የተሰኙት የ76 ዓመት ሴት የኢኮኖሚክ ሳይንስ የመጀመሪያዋ የኖቤል ተሸላሚ በመሆን ታሪክ ሰርተዋል፡፡ አሜሪካዊቷ ኤልዛቤት ኤች ብላክበርን የተባሉት የ61 ዓመት ሴት ደግሞ የ48 ዓመት ከሆነው ባልደረባቸው ካሮል ጋር በመሆን ሸልማቱን የተካፈሉት ክሮሞዞም በሴል ክፍፍል ወቅት እንዴት ራሳቸውን ከመሸራረፍ እንደሚጠብቁ ተመራምረው በማግኘታቸው ነው፡፡ ሌሎች ሴቶችም በተለያየ ነገር ላይ ባሳዩት ስኬት እንደተሸለሙ ቺካጎ ትሪቢውን ጠቅሷል፡፡

ከሽልማቱ ተካፋይ ሴቶች መካከል ኸርታ ሙለር በሥነ ፅሑፍ፣ ካሮል ደብሊው ግራንድየር በሳይኮሎጂና ሜዲስን እንዲሁም፣ አዳ ዩናዝ የተባሉት እስራኤላዊት በምርምር ዘርፎች ይገኙበታል፡፡

ሽልማቱ ከገንዘብ በተጨማሪ ዲፕሎማና የወርቅ ሜዳሊያ አለው፡፡

Post Reply

Return to “Ethio Art and Culture..ኢትዮ ጥበብ ፤ስነ ጽሁፍ ፤”