Page 1 of 1

ክቡር ሚኒስትር

Posted: 20 Dec 2009 09:41
by girreda
(የዓለማችን የአየር ጠባይ ለውጥ ችግርን ለመፍታት የተባበሩት መንግሥታት በዴንማርክ ኮፐንሀገን ባዘጋጀው ኮንፈረንስ ላይ ለመሳተፍ የኢትዮጵያ ሉዑካን ተገኝተዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትሩም እዚያው ናቸው፡፡ አፍሪካውያን ስብሰባውን ረግጠው ሲወጡ አብረው ወጥተዋል፡፡ አዘጋጆቹ ተደናግጠው እዚህም እዚያም አፍሪካውያንን እያነጋገሩ ናቸው፡፡ ክቡር ሚኒስትሩንም ጭምር)
- ክቡር ሚኒስትር እንዴት ስብሰባ ረግጣችሁ ትወጣላችሁ?
- እንዴት አንወጣም? እኛኮ እዚህ የመጣነው የአፍሪካን ችግር ለማቃለል እንጂ አፍሪካን ለሞት ለመዳረግና ለእርድ ለማቅረብ አይደለም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኛኮ የአፍሪካንና የዓለምን ጥቅም ለማስከበር ነው የምንሯሯጠው፡፡ የዓለም የዓየር ጠባይ እናሻሽል ስንልኮ ዓለም የሁላችንም መሆንዋን ስለምንገነዘብ ነው፡፡
- ሃሳባችሁ እንደዚያ ሊሆን ይችላል፡፡ ተግባራዊ እንቅስቃሴያችሁን ስናይ ግን የበለፀጉት አገሮችን ጥቅም ለማስከበርና የአፍሪካን ጥቅም ለመርገጥ ነው፡፡
- ቀስ በቀስ ሕጋዊ በሆነ መልኩ፣ ሁሉም በሚስማማበትና በሚፈራረምበት መንገድ ለመሄድ ስፈለግን ነውኮ፡፡
- ከአሁን በፊት ስምምነት ላይ ተደርሶበት የተፈረመ ውልና ስምምነት ለምን ትረግጣላችሁ?
- ምኑን?
- የሚረጭ የጋዝ መጠንን የሚወስን ውልና ስምምነት ነበር፡፡ እሱን ረግጣችሁና ወደጎን ትታችሁ ለምን ትሄዳላችሁ? የኪዮቶ ስምምነት መከበር አለበት፡፡
- አሜሪካውያኑ ስላልተስማሙበትና ስላልፈረሙበት ነውኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ ያልፈረመውን እንዲፈርም ይደረጋል እንጂ የፈረመው አይረገጥም፡፡
- ምን መሰለዎት ክቡር ሚኒስትር? የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አፍሪካን ወክለው የሚናገሩና የሚደራደሩ ስለሆነ ኢትዮጵያ ከእኛ ጋር ብትሆን ጥሩ ነው፡፡
- የአፍሪካን ጥቅም ከሚያስከብር ጋር እንሆናለን፡፡ መመዘኛችንና እዚህ የመጣንበት ምክንያትም ይኸው ነው፡፡
- አንዴ ይቅርታ፡፡ ሰዎች ስለሚፈልጉኝ ልሂድ፡፡
(ክቡር ሚኒስትሩን የጠሯቸው የናይጄሪያ ዋና ተደራዳሪና የሱዳኑ ተከራካሪ ነበሩ፡ ከክቡር ሚኒስትሩ ጋር መከሩ፡፡ ስብሰባው የአፍሪካን ድምፅ የሚያዳምጥ ከሆነ እንደገና ወደ ስብሰባው እንደሚመለሱም ተስማሙ፡፡ ጂ 77 የተባለው የታዳጊ አገሮች ስብስብ ከጎናቸው እንደሆነ አረጋገጡ፡፡ ይህን መክረው እንደተለያዩ፣ ከበለፀጉት አገሮች የመጣ አንዱ ልዑክ ክቡር ሚኒስትሩ ጋ መጥቶ ማነጋገረ ጀመረ)
- ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ጤና ይስጥልኝ፡፡
- ከሱዳኑ ሰውዬ ጋር አብራችሁ ሳያችሁ እኮ ገርሞኝ ነው፡፡
- ለምን ይገርምሃል?
- ሱዳኖች በዳርፉር ብዙ ግፍ እየፈፀሙ ስለሆነና መሪያቸው አልበሽርም ስለሆነ ኢትዮጵያ ከእነሱ ጋር እንዴት ታወራለች ብዬ ነዋ፡፡
- ሃ...ሃ...ሃ
- ምነው ሳቁ ክቡር ሚኒስትር?
- የሳቅኩበት ምክንያትማ የሚያስቅ ነገር ስለተናገርክ ነው፡፡ የኢንቫይሮመንቱ እንዳይበቃን በዚህ ንግግርህም አፍሪካ ላይ ንቀት እያሳየህ ነው፡፡
- እንዴት ንቀት ክቡር ሚኒስትር?
- በዚህ ስብሰባ ላይ አፍሪካውያን አብረን ስለቆምን የሱዳን፣ የናይጄሪያ፣ የኢትዮጵያ ወኪሎች አብረው ቆመው ስለተከራከሩ በዳርፉር አጀንዳ ገብተህ ልትለያየን ፈለግክ አይደል?
- ለመለያየት አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ነው እንጂ፡፡ ይህ የሱዳን ሰውዬ ጎበዝና ጥሩ ሰው ነው፡፡ ተሟጋችና ተከራካሪ ነው፡፡ በስብሰባው ጥሩ ሃሳብ አቅርቧል፡፡ ዳርፉርን ምን አመጣው?
- ለሁሉም ነገር ዴሞክራሲ ወሳኝ ነው ብዬ ነው፡፡
- ቻይናን እየተለማመጣችሁ ያላችሁት ዴሞክራሲ ቻይና ውስጥ አለ ብላችሁ ነው?
(ሰውዬው ተናዶም ሄደ፡፡ በሩቅ ሆኖ ሲጠብቅ የነበረው አንድ ከቻይና የመጣ ልዑክ ወደ ክቡር ሚኒስትሩ መጣ)
- ክቡር ሚኒስትር ኢትዮጵያ ጥሩ እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ ከጎናችሁ ነን፡፡
- እናመሰግናለን ግን...
- ግን ምን? ክቡር ሚኒስትር ኢትዮጵያ አፍሪካን ወክላ የበለፀጉት አገሮች ለአፍሪካ ካሳ ይከፍላሉ ብላ ያቀረበችው ሃሳብ ሙሉ በሙሉ እንደግፋለን፡፡
- ጥሩ ነው
- እንዲያውም ከአፍሪካ ጎን ስለቆምን የታወቁት ያደጉት አገሮች ቅር ብሏቸዋል፡፡
- ጥሩ ነው ግን እናንተ ቻይናዎችምኮ "ክላይሜት"ን በሚመለከት ችግር አለባችሁ፡፡
- ምን ችግር አለብን ክቡር ሚኒስትር?
- የዓለም የአየር ጠባይ ለማሻሻል በኪዮቶ የተደረሰውን ስምምነት ኢሚሽን መቀነስ ነው፡፡
- አዎን፡፡
- እናንተኮ እየቀነሳችሁ አይደለም፡፡
- እ...
- እየቀነሳችሁ አይደለም ብቻ ሳይሆን ለመቀነስም አትፈልጉም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ቻይና የአፍሪካ ወዳጅ ናት፡፡
- አፍሪካውያን በዚህ ስብሰባ በቻይና ላይም ቁጣ እያሳዩ ነው፡፡ ይህን ታውቃለህ?
- አይቻለሁ፡፡ ይህን ለማስወገድ እኮ ነው ከእርስዎ ጋር ለመነጋገር የፈለግኩት፡፡ በነገራችን ላይ!
- በነገራችን ላይ ምን?
- በመንገድ ሥራ በግልገል ጊቤ ፕሮጀክት ቻይና ኢትዮጵያን ለመርዳት ከፍተኛ ዝግጅት እንዳደረገች ልነግርዎት እፈልጋለሁ፡፡ እንኳን ደስ አለን፡፡
- አልገባኝም?
- ቻይና ኢትዮጵያን ለመርዳት መዘጋጀቷን አለቆቼ ንገራቸው ስላሉኝ ነው፡፡ አሁን በስልክ ነግረውኛል፡፡
- የምናወራው ስለ "ክላይሜት ቼንጅ" መሰለኝ፡፡
- አዎን፡፡
- ቻይና ልትረዳን ነውና ዝም እንድንል ትፈልጋለህ?
- እኔ የተናገርኩት ወዳጅነታችንን ለመግለፅ ነው፡፡
- ወዳጅነታችንን ለማጠናከር በግልገል ጊቤና በሌላም ስለምታግዙን ዝም እንበል?
- ለአፍሪካ ካሳ ካልተከፈለ ቻይና ውሉን አትፈርምም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ግልፅ አድርጉልን ለማለት ፈልጌ ነው፡፡
- ቻይና ራስዋስ ኢሚሽን ለመቀነስ ተስማምታለች? የግሎባል ዎርሚንግ ችግርን ለመፍታት ቆርጣ ተነስታለች ወይ? ብለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢጠይቁኝስ?
- ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር የቻይና ልዑካን ቡድን መሪ እየጠራኝ ነው፡፡ ይቅርታ እንገናኛለን፡፡
- እሺ ቻው፡፡
(ቻይናዊው መሄዱን አይቶ ከሕንድ ልዑካን አንዱ መጣ)
- ክቡር ሚኒስትር እኛ ራሳችንን ታዳጊ አገር ብለን ነው የምንወስደው፡፡ ችግራችን አንድ ነው፡፡ እኛ እጅ ለእጅ ተያይዘን መንቀሳቀስ አለብን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ጥሩ፡፡
- በነገራችን ላይ ክቡር ሚኒስትር እግረ መንገድህ ኢትዮጵያ ከሕንድ ምን እንደምትፈልግ አጥንተህ ና ተብያለሁ፡፡ ሕንድ ኢትዮጵያን ለመርዳት ተዘጋጅታለች፡፡
- የምትረዱን ስለሆነ ክላይሜትን በሚመለከት በእናንተ ላይ ያለን ወቀሳ እንተወው?
- እኛ ታዳጊ አገር ነን፡፡ ምን የሚያስወቅስ አለን ክቡር ሚኒስትር?
- የእናንተ የኢንዱስትሪ አሚሽን አደገኛ ነው፡፡ እናንተም በኪዮቶ ስምምነት መገዛት አለባችሁ፡፡
- ከሕንድ ጋር ጥንታዊ ግንኙነት የነበራት አፍሪካዊ አገር ኢትዮጵያ ናት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እና ይሄ ኢሚሽኑን ይቀንሰዋል?
(ከስብሰባው አዳራሽ ውጭ ከፍተኛ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አለ፡፡ አንዳንድ የሰልፉ ተሳታፊዎችም እየታሰሩ ነው፡፡ ግቢው ውስጥ ልዩነት የሰፈነበት የየቡድን ወሬ እየተጧጧፈ ነው፡፡ አዘጋጆቹ ስብሰባው ያለስኬት እንዳይበተን እየተሯሯጡ ናቸው፡፡ ምሳ ሰዓት ላይ ክቡር ሚኒስትሩ ባሉበት ጠረጴዛ አሜሪካውያንም አውሮፓውያንም አሉ)
- አሁን ጥሩ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡ ፈረንሳይ የደን እንክብካቤን በሚመለከት አዲስ ሃሳብ ይዛ መጥታለች፡፡ ከእንግሊዝ ጋር ሆናም ለክላይሜት ቼንጅ ባጀት ይመደብ ብላለች፡፡ የዱሮ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት አልጎር በሰሜን ዋልታ በረዶ እየቀለጠ እንደሆነ የሚያሳይ ፊልም ይዘው መጥተዋል፡፡ ብቻ ደስ ይላል፡፡
- ለአፍሪካ የሚከፈለው ካሳ በሚመለከትስ ምን አላችሁ?
- ክቡር ሚኒስትር አሁንኮ ችግሩ ማን ያዋጣ? ስንት ይዋጣ? የሚለው ለመወሰን እጅግ አስቸጋሪ ስለሆነ ነው፡፡
- ምነው ባንኮቻችሁን ለመደጎም ይህን ያህል ጊዜ አልወሰደባችሁ? ማን ይደጉም? ስንት ይደጉም የሚለው ለመወሰን አይከብድም? ባንኮቻችሁን ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ በቢልዮኖች ደጉማችኋል?
- መሰጠቱማ አይቀርም፡፡ ሄላሪ ክሊንተን እዚህ አለች፡፡ ለኢንቫይሮመንት ያላት ትኩረት የታወቀ ነው፡፡
- በክሊንተን ጊዜ እኮ ነው አሜሪካ የኪዮቶ ስምምነት አልፈርምም ያለችው፡፡ ያኔኮ ቢል ክሊንተን ነበር ፕሬዚዳንቱ፡፡
- ባል ሌላ ሚስት ሌላ ናቸው?
- ያኔማ ሴናተር ነበረች ብዬ ነው፡፡
- ብቻ የበለፀጉት አገሮች ተሰብስበው ጥሩ ውሳኔ ያሳልፋሉ ብዬ አምናለሁ፡፡
- አንዱ ተቃውሟችንኮ ይህ ነው፡፡
- ምኑ? ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዳጊ አገሮች የሌሉበት ለብቻችሁ የምታደርጉት ስብሰባና መመሳጠር ነው የጠላነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ውጤቱ ግን ያስደስታችኋል፡፡ አሁን ጥሩ ውሳኔ እንዲተላለፍ እያረቀቅን እንገኛለን፡፡ ውሳኔውን ስትሰሙት ትደሰታላችሁ፡፡
- ይህም ነው አንዱ ቅሬታችን፡፡
- ምኑ?
- ከእኛ ተደብቃችሁ አታርቅቁ፡፡ እኛም መሳተፍ አለብን፡፡ በውይይቱም በማርቀቁም አፍሪካን የሚያገል ሥራ አትስሩ?
- ከኢትዮጵያ ጋር ችግር የሚኖረን አይመስለንም፡፡ የአፍሪካ ወኪል ሆና ስለመጣች እንግባባለን፡፡ በነገራችን ላይ በቅርቡ ስለሰብዓዊ መብት እየቀረበ ያለው ሪፖርት ሙሉ በሙሉ አልተቀበልነውም፡፡ እናንተ እዚህ ደግፉን እኛም እዚያ እንደግፋችኋለን፡፡
- አልገባኝም?
- ክቡር ሚኒስትር ኢትዮጵያ እንዳትወገዝ እናደርጋለን ማለቴ ነው፡፡
- እናንተ ትደግፉናላችሁ፣ አታወግዙንም ብለን ኢሚሽን እንደፈለገው ይሁን፣ ካሳም አትክፈሉ እንበል፡፡
- እንዲያውም ከካሳው በላይ ለኢትዮጵያ እርዳታ እንዲሰጥና ተራበ የተባለው ስድስት ሚልዮን ሕዝብ ከሞት እንዲተርፍ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡
- ስለዚህ ኢትዮጵያ ለክላይሜት ቼንጂ መሟገት ታቁም፣ አፍዋን ትዝጋ?
- አፏንማ አትዘጋም ለድጋፉም አፏ ይከፈት ማለታችን ነው፡፡
(ምሣውን መብላት አስጠላቸው፡፡ ትንሽ ቀማመሱና ሰላምታ ሰጥተው ሄዱ፡፡ በአቅራቢያቸው በሚገኘው ካፌ ቡና አዘዙ፡፡ እንደአጋጣሚ ኢትዮጵያዊት ወጣት ካፌ ውስጥ እያስተናገደች ነበር)
- ኢትዮጵያዊት ትመስያለሽ?
- ነኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሚኒስትር መሆኔን እንዴት አወቅሽ?
- የሰላማዊ ሰልፉ አባል ነኝ፡፡ ተረኛ ስለሆንኩ እንዳያባርሩኝ መጣሁ እንጂ ስጨርስ እንደገና ሰልፉን እቀላቀላለሁ፡፡ አንዱ ሚኒስትር ናቸው ብሎ አሳይቶኛል፡፡
- እሺ፡፡
- ያሁኑ ዜና ግን አልገባኝም፡፡
- ምን የሚሉት ዜና?
- መሪዎቹ ከመምጣታቸው በፊት ሁሉም ግልፅ ይሆናል፡፡ ለስምምነት ዝግጁ እንሆናለን የሚል ዜና ነበር፡፡
- አልሰማሁትም፡፡
- ስብሰባው ውስጥ አብራችሁ አይደላችሁም?
- በአንዳንድ ጉዳይ ከእኛ ተደብቀው ተነጋግረው ይስማማሉ፡፡
- አያሳትፏችሁም?
- አንዱ ይህ ነው፡፡
- ምን ክቡር ሚኒስትር?
- "አሳትፉን" የሚል ጥያቄ ነው ያለን፡፡
- እናንተም "አሳትፉን" ትላላችሁ?
- አዎን ትልቁ ጥያቄያችን እሱ ነው፡፡ ምነው ሳቅ አልሽ?
- "አሳትፉን" ስትሉ ነዋ ገርሞኝ፡፡
- ለምን ይገርምሻል?
- ሚኒስትሮች አሳትፉን የምትሉ አይመስለኝም ነበር፡፡
- ይኸው እያልን አይደል?
- የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእናንተ ይህን ጥያቄ ቢያቀርብ ምን ባላችሁት ነበር ክቡር ሚኒስትር?
- ምን የሚል ጥያቄ?
- አሳትፉን!

Re: ክቡር ሚኒስትር

Posted: 23 Dec 2009 02:48
by girreda
(ተከዜ ሃይድሮኤሌክትሪክ ለምረቃ እየተዘጋጀ ነው፡፡ ክቡር ሚኒስትር፣ ከምረቃው ጥቂት ቀናት በፊት ግድቡን ማየት ስለነበረባቸው ወደ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እየሄዱ ናቸው፡፡

ቦሌ መንገድ ጫፍ በሚሊንየም አዳራሽ ግቢ የሰዎችና የኮንስትራክሽን መኪኖች ሽር ጉድ ሲሉ ተመለከቱ፡፡ ሾፌሩን አንዴ ለማየት የምፈልገው ነገር አለ ብለው በቦሌ ቀለበት መንገድ ሥር ዞሮ ተመልሶ ወደ አዳራሹ በር እንዲያመራ ነገሩት፡፡ ዞሮ ተመልሶ በሩ ላይ ቆመ፡፡ ከመኪና ወርደው እያዩ በግቢው መኪና ውስጥ ተቀምጠው ሽር ጉዱን እያዩ ይደሰቱ የነበሩ ሁለት ሰዎች ወደሳቸው መጡ)
- ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴ፣ እንዴ እርስዎ ነዎት እንዴ? እዚህ አገር መሆንዎን አላወቅኩም ነበር፡፡ ሽር ጉዱን አይቼ ደስ ብሎኝ ነው እንኳን ደስ አለን፡፡ ቢዘገይም አሁን ማፍረሳችሁ ጥሩ ነው፡፡
- እያፈረስን እኮ አይደለም፡፡ እየገነባን ነው፡፡
- የቆርቆሮ መጋዘኑን አፍርሳችሁ በእቅዱ መሠረት ኮንቬንሽን ሴንተሩን ለመገንባት ነው አይደል?
- ክቡር ሚኒስትር በጣም ይሞቃል፡፡ ወበቅም ስላለ ውሃ ልስጥዎት፡፡
- አንተም ከውስኪ ውጭ ውሃ ትጋብዛለህ እንዴ? ይኸውልህ እኔ ደስ ያለኝኮ በአንድ ነጥብ ሶስት ቢልዮን ኮንቬንሽን ሴንተር እሰራለሁ ብለህ ቦታውን ፈርመህ ስለወሰድክ ግንባታ የጀመርክ መስሎኝ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በችኮላ ነው መሰለኝ ኮትዎ ተጨማዷል፡፡
- እና ግንባታ አይደለማ፡፡
- ግንባታማ ግንባታ ነው፡፡
- መጋዘኑ ሳይፈርስ?
- ግቢውን አስፋልት እያደረግን ነን፡፡
- ከሚሊንየም በኋላ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ መጋዘኑ ፈርሶ ግንባታ ይጀመራል ብለህም እንደገና ፈርመህ ነበር፡፡ አንደኛውም ሁለተኛውም ፊርማ ሳይከበር ቀረ፡፡ አይደል?
- ልዩ አስፋልት ነው ክቡር ሚኒስትር ምነው ምነው የተሻለ መኪና የለም እንዴ ይህችን መኪና የሚይዙት?
- አስፋልት ብቻ ነው ግንባታው?
- አዳራሹ ውስጥም አበባና ሌላ ሌላ አርማ እየተከልን ነው፡፡ ሰሞኑን ግቢው በሙሉ በማስታወቂያ ሰሌዳዎች ፏ ይላል፡፡ በከተማውም እንደዚሁ እያንዳንዱ ድርጅት የራሱን አርማ ይሰቅላል፡፡
- ልማት ፏ ሲል እንጂ ጌጣ ጌጥ ፏ ቢያደርገው በማግስቱ ይከስማል፡፡
- እውነት አሁን ይህ ቦታ ወይ መጀመሪያ ለጠየቁት ተሰጥቶ አልለማ ወይ አንተ አላለማኸው እንዲያው... አሁን ጋዜጣው ይህን አይቶ ቢፅፍ ይፈረድበታል?
- ሁለተኛ እንዳይጽፍ መንግሥት አስጠንቅቆታል ሲባል ሰምተን ደስ ብሎናል፡፡
- ምን ብሎ ነው ደግሞ ጋዜጣውን የሚያስጠነቅቀው?
- ሁለተኛ በእሳቸው ላይ እንዳትፅፍ ብሎ አንዱ ሚኒስትር ተናግሯል አሉ፡፡
- ያንተ ሚኒስትር እንደሆነ እንጂ የመንግሥት ሚኒስትር እንደዚያ አይልም፡፡
- እና አሁንም ሊቀልድብን ነው ማለት ነው?
- ብታለማኮ ቀልዱን ባቆመ ነበር፡፡
- የማለማ ስለሆነ ነው ብዙ እኮ የሳውዲ ባለሃብቶችን የማስመጣው፡፡
- መምጣታቸው ጥሩ ነው፡፡ ያንተን አካሄድ ከተከተሉ ግን ችግር ነው፡፡
- በል በል ልሂድ፡፡
- ምሣ ለምን አብረን አንበላም ክቡር ሚኒስትር?
- እኔ ወደ ልማት እየሄድኩ ነው፡፡
- የቱ ልማት?
- ተከዜ ግድብ ሊመረቅ ነው፡፡ የተቋቋመ ኮሚቴ ስላለ ወደዚያ እየሄድኩ ነው፡፡ በእቅዱ መሠረት ግንባታ የተጀመረ መስሎኝ ደስ ብሎኝ ለማየት ነበር የመጣሁት፡፡ ሳየው ግን ጌጣ ጌጥ ነው፡፡
- ምነው አስፋልቱን ናቁት ክቡር ሚኒስትር?
- ከልማት ጋር ቢመጣ በወደድኩት፡፡ ግንጥል ጌጥ ምን ያደርጋል ብለህ ነው?
- ሳውዲዎቹ እዚህ ስብሰባ የሚያደርጉ ከሆነ ደስ ይላቸዋል፡፡
- ስብሰባውን ለመንግሥት ተወው፡፡ አደራ ደግሞ ሲርየስሊ ወስደው፡፡ ሠርግ አታስመስለው፡፡ እኔ ልሂድ ነገር ግን አደራ፡፡ የሳውዲዎቹ መምጣት ለልማት እንጂ ሰውየው እንዲህ አደረገ የምትባልበት መሸፋፈኛ መድረክ አታድርገው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እርስዎም ጋዜጣው ያሉኝን እየደገሙት ነው እኮ፡፡
- ጋዜጣው ምን አለህ?
- ነገሮችን ለማድበስበስ "ነጠላ ዜማ" ይለቃል፡፡
- በል፣ በል ልሂድ ቻው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር የሳውዲዎቹ ኢንቨስትመንት ይሳካል አይጠራጠሩ፡፡ በተለይ በእርሻ ጉድ ነው የሚሉት፡፡
- እነሱንኮ አልተጠራጠርኩም፡፡
- እኔን ግን ይጠራጠሩኛል?
- እውነቱን ልንገርህ?
- ይንገሩኝ፡፡
- ማን የማይጠረጥርህ አለ?
- ወደ እርሻ እንድንገባ ብዙ ኢንቨስተር እያስመጣሁ ነው፡፡ የምጠረጠረው ለምንድነው?
- በፕራይቬታይዜሽንና በሌላ ስም ሰላሳ ሁለት የእርሻ ቦታዎች ወስደህ አላለማህም፡፡ ሰላሳ ሁለት ካላለማህ ሰላሳ ሶስተኛው ላይ እንዴት ልመንህ?
- የሰው ወሬ እየሰሙ እንዳይታለሉ፡፡
- ይልቁንስ አንተ የምስለኔህን ወሬ እየሰማህ ገደል እንዳትገባ፡፡ ለመግባት እንኳ ገብተሃል ግን በአስቸኳይ ውጣ፡፡ ቃል የገባኸውን ፈፅም፡፡
- በየቦታው ጀምሬ የለም?
- በጀመርከውም ሰው እየሳቀብህ ነው፡፡
- ምን ብሎ ክቡር ሚኒስትር?
- አንተ ራንዴቩ ካፌ ትለዋለህ፡፡ ሰዉ ደግሞ "እንደ ሰው ካፌ" ብሎታል፡፡
- ምን ማለት ነው?
- ካፌው ለሕብረተሰቡ ሁሉ ክፍት አይደለም፡፡ ሰው እየተለየ ለአንዳንዱ ይከፈታል፡፡ አገልግሎት የሚሰጠው እንደየ ሰዉ ዓይነት ነው ይባላል፡፡ ተፈላጊ ሰው ሲገኝ እኩለ ሌሊትም ቢሆን ይከፈታል፡፡ እንደ ሰው ነው ይሉሃል፡፡
- እህም""
- "ሜድ ኢን ቻይና" አጥር እየፈረሰ "በሜድኢን ኢታሊ" አጥር ይተካዋል እንጂ አይገነባም ይሉሃል፡፡
(ክቡር ሚኒስትር ወደ ኤርፖርት ገብተው ተሳፈሩ፡፡ ከኮሚቴያቸው ጋር ተከዜ ሀይድሮኤሌክትሪክ ግድብ ደረሱ፡፡ እየተዘዋወሩ ጎበኙ)
- እንዴት አያችሁት?
- ኮራን ክቡር ሚኒስትር፣ ተበረታታን፡፡ የዓለም ባንክ፣ የዓለም ገንዘብ ድርጅት፣ ሳንል በራሳችን አቅም ገንብተን ልናስመርቅ ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነት ችግር እያቃለልን ልንሄድ ነው፡፡
- ደስ ይላል፡፡ ይህን ይህን ሳይ ነው ልማት የሚገባኝ፡፡
- እውነትዎን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡ ሌላ ሌላ ከምናወራ ስለ ልማት ብናወራ፡፡ መንገድ፣ ግድብ፣ ወዘተ. እናሳይ፡፡
- ገባኝ፡፡
- ይህን ለሕዝብ እያሳየን ልማታዊ መንግሥት ነን ከማለት ይልቅ እየዛትን እንውላለን፡፡ መናገር ተስኖናል፡፡ ስለመንግሥት ይናገራሉ ያልናቸውም ስለሌላ ነው የሚናገሩት፡፡
- ክቡር ሚኒስትር አንዱ በቀደም ይህ መሥሪያ ቤት "ፕራይቬታይዝድ" ሆነ ወይ? ብሎ ቀለደ፡፡ ይህን ምን አሰኘህ ስለው "አቶ እንትናን አትንኩ" ማለት ብቻ ሆነ አለኝ፡፡
- እስቲ ሌሎች ግድቦችም እንደዚሁ ይጠናቀቃሉ ብለን ተስፋ እናድርግ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ፖሊሲያችንን አሠራራችን ብናጠናክርኮ ብዙ መሥራት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ጧት የሰማነው የሳውዲ ኢንቬስተሮች መምጣት መንግሥት ብዙ ሊሰራበት ይችላል፡፡ ግን"" እ
- ምነው ግን ብለህ ቆምክ?
- መንግሥት ሊመራውና ሊከተታለው ይገባል፡፡ ስብሰባውንም ሂደቱንም ውይይቱንም ሊከታተለው ይገባል፡፡
- በተቻለ መጠን ማበረታታት ነው፡፡ ገና ለገና አይሆንም፣ አይሳካም ከማለት ይልቅ እንዲሳካ መሥራት፡፡
- አንዳንድ ሰዎች የኢንቨስተሮች አያያዙ ትክክል አይደለም ይላሉ፡፡ ይመለሳሉ፣ ይሠራሉ ይባላል፡፡ ነገር ግን አያደርጉም፡፡ መንግሥት ለምን ተግባር ላይ አልዋለም ብሎ ቢገመግም ጥሩ ይመስለኛል፡፡ አለበለዚያ ብዙ ያመልጠናል፡፡ በዱከም ኢንቨስተሮች በቻይና ይገነባል የተባለው የኢንዱስትሪ መንደር እንዴት እየሄደ ነው? በለገጣፎ በቱርኮች ይመሠረታል የተባለው የኢንዱስትሪ ሰፈርስ? በዱባይ ባለሃብቶች ይገነባል የተባለው የባቡር መስመርና የነዳጅ ቱቦስ?
- ስታስበው ያስጎመጃል፡፡
- ሲያመልጥ ግን ያናድዳል፡፡
(ሁሉም ነገር ተጠናቅቆ ለምረቃው ቀን ዝግጁ መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ኮሚቴአቸውን ይዘው ክቡር ሚኒትሩ ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡ ስለጉዟቸው እያወሩ ነው)
- ጉዟችንን እንዴት አያችሁት?
- ከእርሶ በላይ ብዙ ተምረን ተደስተን መጥተናል፡፡
- እንዴት ከእኔ በላይ?
- ኤርፖርት የተቀበለን ሾፌር በጣም በጣም ኮሚክ ነበር፡፡ እርስዎ እንዳይሰሙት እየተጠነቀቀ ስለ ትግራይ ብዙ አጫውቶናል፡፡
- አመናችሁት?
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር፡፡ ስለ ትግራይ ብዙ ሲወራ እውነት ይመስለኝ ነበር፡፡ ትግራይ ወርቅ በወርቅ ሆናለች ሲባል አምን ነበር፡፡ በመኪና ብዙዎቹ የትግራይ አካባቢዎች ስናቋርጥ ግን ኋላ ቀር አካባቢ ሆና ነው ያገኘኋት፡፡
- ሐዋሣን በደንብ ታውቀዋለህ? ከመቀሌ ጋር ስታወዳድረው እንዴት አገኘኸው?
- ክቡር ሚኒስትር ሐዋሳ ይበልጣል፡፡ ጥሩ አስፋልት፣ የእግረኛ መንገድ፣ ጥሩ ጥሩ ሆቴሎች አሉ፡፡ ዘመናዊ ከተማ ነው፡፡ መቀሌ ግን ያሳዝናል፡፡ ዓድዋ ከተማ ለማየት ጓጉቼ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመልሰው ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ሄደው አያውቁም ወይ ነው ያልኩት፡፡ ኋላ ቀር ከተማ እንደ ዓድዋ አላየሁም፡፡
- (ሌላ ተናጋሪ) በፖለቲካ ይሻል እንደሆነ እንጃ እንጂ በልማቱስ መንገድ እንኳ የለውም፡፡
- (ሌላኛው) ክቡር ሚኒስትር በፖለቲካውም ችግር ያለ ለመሆኑ ሾፌሩ ተከዜ እስክንደረስ ስንት ቀልድ ነው የነገረን?
- እስኪ የነገራችሁን ንገረኝ፡፡
- በባለሥልጣናት ላይ ስለሆነ ላይወዱት ይችላሉ፡፡
- ግዴለም ንገረኝ፡፡
- አንዳንዶቹ የክልሉ የአመራር አባላት በዱሮው በታጋይነት ደረጃ እንጂ ከዚያ በኋላ ተገቢ ትምህርት ያልተማሩ ናቸው በማለት የነገረን ቀልድ ያስቃል፡፡
- እስኪ እኛም እንሳቅ፡፡
- አንዱ ሹመኛ ለጉብኝት እንግሊዝ አገር ተልኮ ሲመለስ በክልሉ ባለው ሬዲዮ ጣቢያ ስለጉብኝቱ ቃለ መጠየቅ ይደረግለታል፡፡
- እሺ፡፡
- "በእንግሊዝ አገር በጣም ያስደነቀህ ምንድነው ነው?" ተብሎ ተጠይቆ ሲመልስ "ኢትዮጵያ ውስጥ ትልልቆች እንኳ እንግሊዝኛ መናገር እያቃተን እንግሊዝ አገር ግን ትንንሽ ልጆች ሲያቀላጥፉት እጅግ በጣም በጣም አስገርሞኛል" ብሎ መለሰ (ሁሉም ሳቁ)
- (ሌላኛው ተናጋሪ) ስለ ቋንቋ ከተነሳማ የተነገረን ቀልድ እሱ ብቻ አይደለም፡፡
- እስቲ አንተ ደግሞ ሌላ ቀልድ ንገረን፡፡
- ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በህወሓት ሊቀመንበርነታቸው በመቀሌ ስብሰባ እየመሩ ነው አሉ፡፡
- እሺ፡፡
- አንዳንዶቹ የክልሉ አመራሮች የህወሓት አባላት የስብሰባ ሥነ ሥርዓት ሳያከብሩ በስሜት ይናገሩ ጀመር፡፡
- እሺ፡፡
- አቶ መለስ ሥነ ሥርዓት እንዲያከብሩ አሳስበው አንዳንዶቹ አልሰማ ቢሏቸው እንዲህ አሉ፡፡
- ምን?
- "ከአሁን በኋላ ሥነ ሥርዓት ካላከበራችሁ ስብሰባውን በእንግሊዝኛ እመራዋለሁ" (ሁሉም ሳቁ)
- ዋናው ቁም ነገር ብዙ የታገለ ሕዝብ ያለበት አካባቢ ስለሆነ ፍትሕ ማግኘቱ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በፍትሕና በሌላ ሌላም ዙሪያ ሾፌሩ አሪፍ ቀልድ ነግሮናል፡፡
- አሪፍ አሪፍ እያልክ ልባችንን ሰቀልከው እኮ አሪፍ ከሆነ ነገረን፡፡
- እሺ ልንገራችሁ፡፡ ቀልዱ እንዲህ ነው፡፡ የኤርፖርት አንዳንድ ድርጅቶችን ማኔጅ ለማድረግ የውጭ ሰዎች ይቀጠራሉ፡ በዚህ ሕዝቡ ቅር ይሰኛል፡፡ ልጆቻችን ተሰውተው የተገኘ ንብረት ለፈረንጆች ተሰጠ እያለ ቅር አለው፡፡
- እሺ
- ከዚያ ድርጅቱ ለማስተዳደር እንጂ ንብረቱ ተሸጦላቸው እንዳልሆነ ሕዝቡ እንዲያውቅ ይደረግ የሚል ውሳኔ ተላልፎ በየቦታው ስብሰባ ይካሄዳል፡፡
- እሺ፡፡
- በአንድ ስብሰባ የሚያስረዳው ሰው እንዲህ ይላል፡፡ "ንብረታችን ተሸጠ እያላችሁ ቅሬታ እንዳደረባችሁ ሰምተናል፡፡ የሰማችሁት ውሸት ነው፡፡ ንብረት አልተሸጠም፡፡ አሁንም የእናንተው ነው፡፡ ለማኔጅመንት ብቻ ነው የመጡት፡፡ ሃቁ ይህ ነው፡፡ አስተያየትና ጥያቄ ካላችሁ ግለፁ ብሎ መድረክ ላይ ለተሰበሰበው ሰው ክፍት ያደርጋል፡፡
- እሺ፡፡
- ተሰብሳቢው "ለማኔጅመንት ብቻ ቢሆንስ ለምን ለፈረንጆቹ ይሰጣል? ማኔጅ የሚያደርግ ሰው እዚህ የለም?" ብሎ ይጠይቃል፡፡
- እሺ፡፡
- ሰብሳቢው "እነሱ የተሻለ ማኔጅ ማድረግ ይችላሉ፡፡ እነሱ ማኔጅ ካደረጉ ንብረት አይባክንም፣ ሰራተኛ አይበደልም፣ ድርጅቱ አትራፊ ይሆናል፣ በትርፉም ሌላ ብዙ የልማት ሥራ ይሰራል፡፡ ድህነት የሚቀነሰውም እንደዚህ ነው" ብሎ ይመልሳል፡፡
- እሺ፡፡
- አሁንስ ቅሬታችሁ መልስ አገኘ? ቅሬታ አለን የምትሉ ካላችሁ እጃችሁን አውጡ አለ፡፡
- እሺ፡፡
- በዚህ ጊዜ አዳራሹ ውስጥ የነበረው ሰው ሁሉ እጁን አወጣ፡፡
- እሺ፡፡
- ሰብሳቢው ግራ ገብቶት መልስ ከሰጠኋችሁ በኋላ እንዴት ቅሬታው ይጨምራል? እንዴት ሁላችሁም እጃችሁን ታወጣላች? ብሎ ለአንድ አዛውንት ዕድል ይሰጣል፡፡ አዛውንቱም ቀጠሉ፡፡
- እሺ፡፡
- እነሱ ማኔጅ ካደረጉ ሠራተኛ አይበደልም፣ ንብረት አይባክንም፣ አትራፊ ይኮናል፣ ልማት ይቀላጠፋል፣ ድህነት ይወገዳል ብለሃል? አይደል ይሉታል፡፡ ሰብሳቢውም አዎን አላቸው፡፡
- እሺ፡፡
- አዛውንቱ ቀጠሉና እንግዲያውስ እነሱ ሲያስተዳድሩ ውጤቱ ይህ ከሆነ ቅሬታዬ እጥፍ ድርብ ሆኗል አሉት፡፡
- ለምን ቢላቸው ምን ብለው መለሱ መሰላችሁ? ለምን ፋብሪካ ብቻ ሆነ መላው ትግራይን ለምን አትሰጧቸውም!

ከማስዋቡ ጎን ለጎን ጥንቃቄ

Posted: 23 Dec 2009 02:52
by girreda
አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማና የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት፣ የአውሮፓ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መቀመጫ ስለሆነች መዋብና ማማር ይኖርባታል፡፡


የአፍሪካ ጎዳናን ለማስዋብ የሚደረገው እንቅስቃሴ ለሰዎች የሥራ ዕድል አስገኝቷል፡፡ በመንገዶቹ መካከል ያሉት ሣርና ሌሎች ተክሎችን ከመረጋገጥ ለመጠበቅ እየታጠረ ነው፡፡

ውበት ለመጨመር ሲባል በብረት ችካሎች ላይ ቅጠላማ ሐረግ መስለው የተጠመጠሙት ጠንካራ ሽቦዎችና ጫፎቻቸው አፈንግጠው ስናያቸው በሰዎችና በእንስሳት ጤና እንዲሁም ንብረት ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉትን አደጋ ይሰቀጥጠናል፡፡

በእግር የሚንቀሳቀሱ ማየት የተሳናቸው ወገኖች፣ ታዳጊዎች፤ በጨለማ መንገድ ለሚያቋርጡ፣ በመጠጥም ሆነ በሌላ አዕምሮ መታወክ ምክንያት ራሳቸውን ለማይቆጣጠሩ ለአደጋ የሚያጋልጥ ይመስለኛል፡፡

አንድ መኪና ከእነዚህ የአጥር ሽቦዎች ጋር ቢጋጭ ሽቦዎቹ ተሳፋሪውን ሊወጉ ይችላሉ፡፡

በአፍሪካ ጎዳና ላይ ሰሞኑን በመሠራት ላይ ያለው የብረት አጥር ለአደጋ ስለሚያጋልጥ ሌላም አማራጭ ይታሰብበት፡፡
(ከአካባቢው ነዋሪ)

ዕድለ ቢሱ - እኔ

የረቡዕ ኅዳር 30/2002 ዓ.ም. ሪፖርተር ጋዜጣ በዕለቱ ለእኔ ይዞልኝ የመጣው ነገር ቢኖር መርዶ ነበር፡፡ "አዲስ ነገር" ከህትመት ውጪ መሆኗ ለእኔ አስደንጋጭ ወሬ ነበር፡፡ የፕሬስ ነፃነት ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ እጅግ በርካታ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን በማንበብ ብዙ ዕውቀት ለማግኘት ችዬ ነበር፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ እነዚያ ጠንካራ የነበሩ የህትመት ውጤቶች (ነፃ ጋዜጦች) ዛሬ የሉም፡፡ ..ነፃው ፕሬስ.. ሲወለድ፣ ሲያድግና በተለያዩ ተጽዕኖዎች ወደ መቃብር ሲወርድ ታዝቤያለሁ፡፡

በኢንፎርሜሽን ዘመን ጋዜጦች ለአንድ ኅብረተሰብ የ..የእህል ውሃ..ን ያህል አስፈላጊ ናቸው የሚል አስተሳሰብ ካላቸው ወገኖች አንዱ ነኝ፡፡

አንድ ጥሩ ጅምር ጎልብቶ፣ ጠንክሮ ከመዝለቅ ይልቅ ድንገት ወድቆ ሲሰበር ማየት "ዕድለ ቢስ" ከመሆን ሌላ ምን ያሰኛል? አገሬ መጀመር እንጂ መዝለቅና መጨረስ አይታይባትም፡፡
(ታዬ ይልማ፣ ከአቧሬ)


ከዘር ፖለቲካ እንጠበቅ

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለፈው ረቡዕ ኅዳር ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ ገና አዲስ ጀማሪ ስትሆን በአንድ ወቅት በዓለም ላይ ገናና ከነበሩት ስልጣኔዎች ውስጥ አንዷ እንደነበረችና ነገር ግን ለረጅም ዓመታት አንቀላፍታ የቆየች መሆኗን፤ አሁን ግን ከ"እንቅልፏ" እየነቃች መሆንዋን አስገንዝበዋል፡፡ አገሪቷ ያንቀላፋችው ዛፍ ላይ ነው፣ መደብ ላይ ነው፣ አልጋ ላይ ነው፣ መሬት ላይ ነው፣ እርቧት ነው፣ ጠግባ ነው፣ ሲቀሰቅሷት ምን አገኘች? ዴሞክራሲ፣ ዳቦ፣ ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነት፣ መለያየት፣ የብሔር ሽኩቻ፣ ምንድን ነው ያገኘችው? ሲቀሰቅሷት ያጣችው አካሏን ኤርትራን ነው፣ አሰብን ነው?

በአገሪቱ ከበፊቱ የተሻለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መኖሩና በከተማዎች ውስጥ ያለው የፈጣን ግንባታ በአሁኑ ዘመን የተመዘገቡ ስኬቶች ናቸው፡፡

ኢሕአዴግ መንበረ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ ጀምሮ ኢትዮጵያዊነትና የሀገር ፍቅር ስሜት እንደ በረዶ መቀዝቀዙ ሃቅ ነው፡፡ የጎሣ ፖለቲካ የበዛበት መደማመጥ የጠፋበት፣ መጯጯህ የበረከተበት፣ ማስተዋል የጎደለበት ነው፡፡ የዘር ፖለቲካ እንቁላል ቅርፊት ተሰብሮ አንድነቷን የጠበቀች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ እናስረክብ፡፡

(ዜና ማርቆስ፣ ከደብረ ዘይት)


ትንሣኤውን ያብስሩን

ሰሚ ያጣውን የመሥሪያ ቤታችንን ችግር (የኢትዮጵያ ጤናና ሥነ ምግብ ምርምር ኢንስቲትዩት) ለሕዝብና ለመንግሥት ጆሮ በተከታታይ በማድረስ፣ በመጨረሻም የሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች፣ ሰፋ ያለ ውይይት ከመሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ጋር አካሂደው፣ አንዳንድ ችግሮችን ከሞላ ጎደል መረዳት ችለዋል፡፡

ይሁንና የግምገማው ውጤት ለሠራተኛው ሲገለጽ፣ ክቡር ሚኒስትሩ ወይም ሌላ የመንግሥት አካል ይገኛል ብለን ችግሮቻችንን አጉልተን ለመወያየት ብንጠብቅም፣ በአጥፊዎቹ በራሳቸው ሒሳቸውን እንዲቀርብ መደረጉ ለለውጥ የተነሳሳውን ብዙሃን ሠራተኛ እጅጉን ቅር አሰኝቷል፡፡

ስለሆነም መሥሪያ ቤቱ ለአገር ያለውን ጠቀሜታና የተጋረጠበትን አደጋ በመረዳት ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ታች ወረድ ብለው መፍትሄ በማፈላለግ የመሥሪያ ቤታችንን ትንሣኤ ያበስሩን ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

(ከኢንስቲትዩቱ ሠራተኞች)

የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ በግል የተሰጠ አስተያየት

በኢንዱስትሪ የበለፀጉ አገሮች የአየር ንብረትን ለመበከል በዋናነት ተጠያቂ ሲሆኑ፣ የጥቃቱ ሰለባ የሆነው ደግሞ እኛ በመልማት ላይ ያለን አገሮች ነን፡፡

ኢትዮጵያ አገራችን በሚሻሻለው በኪዩቶ ፕሮቶኮል ላይ አፍሪካን ወክላ ለችግሩ መፍትሄ ለማስገኘት በአጠቃላይ የምታቀርበው ሀሳብ እንዳለ ሆኖ በእኔ አስተያየት ኢትዮጵያ እንደበለፀጉት አገሮች እርዳታ ሰጭም ተቀባይም ሆኖ መቅረብ ትችላለች፡፡

ይኸውም የአየር ንብረት ለውጥን ለማምጣት በዋናነት ተፈላጊው ደኖች የሚለሙበትን ቦታ ማግኘት ሲሆን ቀጥሎም ቦታውን በደን ለማልማት የሚጠይቀውን ገንዘብ ወይም በጀት ፈልጎ መመደብ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የሚሻሻለው የኪዩቶ ፕሮቶኮል ውጤታማ እንዲሆን በዋናነት ተፈላጊ የሆነውን ከበለፀጉ ሀገሮች ተርታ በመሰለፍ አንዱ በመሆን ለደን ልማት የሚውሉ ቦታዎችን በፕላን ነድፎ በሚልዮን ሄክታር የሚቆጠር ለደን አገልግሎት ብቻ የሚውልቱን ጋራና ሸንተረሮችን እንዲሁም የችግኝ ማፍላት ሥራውን የመትከያ ጉድጓዶችን በሚያዘጋጁና የሚተክሉ ሰዎችን፣ ከተተከሉም በኋላ የሚጠብቁና የሚንከባከቡ የደን ባለሞያዎችንና የበታች ሰራተኞችን መርጣ ማቅረብ የምትችል ሀገር ስትሆን የበለፀጉ ሀገሮች ደግሞ በጥናቱ መሠረት ድርሻቸውን በገንዘብና በማቴሪያል ወጪውን ከሸፈኑ የአየር ለውጡን ፕሮግራም ውጤታማ ማድረግ ይቻላል የሚል ሙሉ እምነት አለኝ፡፡

(ጌታቸው ማኅተመ ሥላሴ፣ የግብርናና የላንድስኬፕ አርኪቴክቸር ባለሙያ)