”ግዕዝ ብማር ደስ ይለኛል”

ግጥሞች፣ታሪኮች፣ፎቶዎች፣ሙዚቃዎች
Poems,Short stories, graphics,pictures,musics,Technology
User avatar
girreda
Runner
Runner
Posts: 55
Joined: 01 Oct 2009 12:45
Location: Adama University
Contact:

”ግዕዝ ብማር ደስ ይለኛል”

Unread post by girreda » 20 Dec 2009 00:34

Teddy Afro, ቴዲ አፍሮ ”ግዕዝ ብማር ደስ ይለኛል”
ወጣቱ፣ እውቁና ታዋቂው ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ ከእስር ከተለቀቀ ሦስት ወር የሆነው ሲሆን፣ በውጭ ሀገር ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን የመገናኛ ብዙኀን ጋር ሰፋ ያለ ቃለምልልስ ያደረገው ከኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ጋር ሲሆን፤ ቃለምልልሱን ያደረገው ከኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ያሬድ ክንፈ ጋር ነው። በዚህ ቃለምልልስ ላይ ያሬድ በቴዲ አፍሮ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ፣ በቴዲ እስር ቤት ቆይታ ላይ፣ በድምፃዊው የሙዚቃ፣ የግጥምና የመድረክ ሥራ ላይ፣ በአርቲስቱ የግል ሕይወት ጉዳይ ላይ፣ ባለፈው ጥቅምት 1 ቀን 2002 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም ለምን ”ያስተሰርያል” የሚለውን ዘፈን እንዳልዘፈነ፣ በስዊድንና በኖርዌይ ኮንሰርቶቹ እሰጥ አገባና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ጥያቄዎችን ለአርቲስት ቴዲ አፍሮ አቀርቦለታል። አርቲስት ቴዲ አፍሮን ለቃለምልልሱ እያመሰገንን፤ መልካም ንባብ ለአንባቢዎቻችን እንመኛለን!

ያሬድ፦ እንኳን ወደ ስዊድን በሠላም መጣህ! እንዴት ከርመሃል? ምን ይሰማሃል በሚል እንዳላሰለችህ ስለ ጤነትህ ብትገልጽልኝ?

ቴዲ አፍሮ፦ በጣም በጥሩ ጤንነት ላይ እገኛለሁ። ጥሩ የመንፈሥ መነቃቃት አለኝ። እናም በጥሩ ስሜት ከሙዚቃ ጓደኞቼ ጋር ወገኖቻችንን በማስደስት ላይ ነን። በመከራ ጊዜ አብረውን ለቆሙት ሁሉ ምስጋና የምናቀርብበት ጊዜ እያሳለፍን ነው። በሄድንበት ሁሉ ቦታ በነበረው ሁኔታ በጣም ተደስተናል።

ያሬድ፦ በእስር ማንም ሰው ይጠቀማል ወይም ይደሰታል ባያሰኝም፤ በአንጻሩ ግን ብዙዎች ”በእስር ሕይወቴ ይህን ተማርኩ፣ ይህን አገኘሁ ...” የሚሉ አሉ፤ አንተስ ምን አተረፍክ?

ቴዲ አፍሮ፦ እስር በመጀመሪያ ደረጃ በአጭር ቃል ሊገለጽ ከባድ ነው። ከባድ ነገር ደግሞ ሲመጣ ያንን ታግሎ መወጣት ለበለጠ ጥንካሬ ይረዳል። ምንም እንኳን ከባድ፣ አስቻጋሪና ፈታኝ ጊዜ ቢሆንም፤ የበለጠ ጠንካራና በሳል አድርጎ እንደሚያወጣ ነው የተረዳሁት።

ያሬድ፦ ከእስር ቤት ከወጣህ በኋላ እረፍት እንደምታደርግ በአንድ ቃለምልልስ ላይ ገልጸህ ነበር። እረፍቱ በቅቶህ ነው ቶሎ ወደ ዘፈን የተመለስከው?

ቴዲ አፍሮ፦ አንድ ሁለት ወር ጊዜ አረፍኩኝ፤ ምክንያቱም ሁለቱም ቦታ የተለያየ ነው። መታሰርና መለቀቅ የተለያየ ስሜት ነው። ከአንድ ነገር ወደ ሌላ ነገር ዝም ብሎ መግባት ራሱ በተረጋጋ መንፈሥ ካልሆነ የተጣደፈ ይሆናል። የሙዚቃ ወይም የኪነጥበብ ሰው ሙያ ደግሞ ሁልጊዜ መንፈሥን አረጋግቶ ነው ማንኛውንም ተግባር ሲጀምር። ስለዚህ በቂ የዕረፍት ጊዜ አድርጌ ነው ሥራዬን የጀመርኩት።


ያሬድ፦ ወጣት ነህ፤ ያለህበት ዕድሜ ለትምህርት የሚያግዝ ነው፤ ልትማር ሃሳብ አለህ ወይ?

ቴዲ አፍሮ፦ መማር ጥሩ ነገር ነው፤ ነገር ግን ብዙ ሰዎች አንዳንዴ ”መማር አለብኝ” ብለው ስለሚያስቡ ብቻ ይማሩና በተማሩበት ነገር ሳይሠሩ ሊቆዩ ይችላሉ። አንድ ሰው መማር ያለበት ከራሱ ከሙያው ጋር የሚሄድ፣ ወይንም ደግሞ ከወደፊት ዕቅዱ ጋር፣ በጣም ከስሜቱ ጋር የሚሄድን የትምህርት ዓይነት መርጦ የመማር መንገድ ነው መከተል ያለበት። እና እኔ አለሙያዬ መማር አልፈልግም። ነገር ግን ከሙያዬ አንፃር ወይንም ደግሞ በተለያዩ ነገሮች ላይ፤ በተለይ በተለይ ግዕዝ ብማር ደስ ይለኛል። ከዚያ በተቀረ ብዙውን መጻሕፍት በማንበብና ራስን በማዳመጥ ሁል ጊዜም ትምህርት ላይ ነኝ ማለት ይቻላል።

ያሬድ፦ ከግዕዝ ሌላ ለሙዚቃህ የሚረዳህ ትምህርት ልትማር ያሰብከው አለህ?

ቴዲ አፍሮ፦ የሙዚቃ መጠነኛ ኮርሶች መውሰድ ጥሩ ነው። በእርግጥ የሙዚቃ አቀነባባሪ ብሆን የበለጠ ብማር ጥሩ ነበር። አሁን ግን የበለጠ ስለሙዚቃ አንዳንድ ነገሮች ባነብ ነው የሚረዳኝ። ከሁሉ በላይ ሙዚቃ የነፍስ ቋንቋ ነው። የመንፈሥ ሥራ ስለሆነ፤ መንፈሥን አረጋግቶ ቀና መሆን በተለይ ከምንም በላይ ፖዘቲቭ የሆነ ቲንኪንግ (ቀና አስተሳሰብ) ካለው አንድ ባለሙያ ለበለጠ የፈጠራ አቅም ይሸጋገራል። ስለዚህ ብዙውን ጊዜ መንፈሤን ቀና በማድረግ ራሴን ለማሠልጠን ሁል ጊዜ ሙከራ ላይ ነኝ።

ያሬድ፦ ከእስር ከወጣህ በኋላ መጀመሪያ ለህዝብ ያቀረብከው ”ሰው - አቤልና ቃዔል” የሚለው ዘፈንህ ስለጎዳና ተዳዳሪዎች ሰቆቃ የሚገልጽ ነው። ይህ የሆነው እንዴት ነው? በፊትም ታስበው ነበር? ወይስ በእስር ቤት በቆየህበት ጊዜ የሚያነሳሳ ሁኔታ ገጥሞህ ነው?

ቴዲ አፍሮ፦ በነገራችን ላይ እኔ እስር ቤት በነበርኩበት ወቅት፤ ስወጣ ምን ምን መሥራት እንዳለብኝ አቅድ ነበር። ስቴጅ ላይ ሁሉ የማቀርብበትን መንገድ ነው የማስበው - መፈታቴንም ሳላረጋግጥ። ምክንያቱም በእግዚአብሔር ላይ በጣም እምነት ስላለኝ፤ ተስፋ ስለማልቆርጥ፤ በእግዚአብሔር ስለምመካ። ቀደም ብዬ ከመታሰሬም በፊት ያሰብኩት የእርዳታ ሥራ ነበር፤ እሱ ሳይሟላልኝ ነው እስር ቤት የገባሁት። ከመታሰሬ በፊትና ከወጣሁም በኋላ ልረዳ ያሰብኩት የአበበች ጎበናን ፕሮጀክት ነበር። ነገር ግን የአበበች ጎበና ፕሮጀክት ራሱን ችሎ ጠንክሮ የቆመ ሠፊ የተደራጀ አቅም ስላለው ከዚህ ሌላስ የሚረዳ ምን ነገር አለ ብለን አየንና የኤልሻዳይን ፕሮጀክት አገኘን። ሁለት ዓላማ ያለው ዝግጅት ነበር። አንደኛ እነዚህን ሰዎች መርዳት፤ ሁለተኛ ደግሞ ሀገሬ ውስጥ ያለውን ህዝብ ሳላስደስት ውጭ ሀገር መውጣት አልፈለግሁም። ሁለት ዓላማ ይዤ ነው የተንቀሳቀስኩት። ሁለቱንም ሃምሳ ሃምሳ ሰጥቼ ማለት ነው። አንዱ ህዝቡን የምስጋና መድረክ ይሆንልኛል ያ ቦታ፤ ሰዉን ሳላገኝ በዚህ አጋጣሚ ሳላስደስት መውጣት አልፈለግሁም። ሁለተኛ ደግሞ ያንን አጋጣሚ ዕርዳታ ሆኖ፤ በራሱ ቀደም ሲል የነበረኝን ሃሳብ የማስፈጽምበት ሌላ አጋጣሚ ሆኖ። በዚህ መንገድ ነው ይሄንን ነገር ያደረግሁት።

ያሬድ፦ ይሄ ያደረግኸው የዕርዳታ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በልመና ላይ ለተሰማሩና ለጎዳና ተዳዳሪዎች ችግር መቅረፊያ ዘላቂ መፍትሔ ሊገኝ ይችላል የሚል ሃሳብ አለህ? ወይስ ይህ እንደመነሻ ሆኖ ተከታታይ ገቢ ማስገኛ ሥራዎች ለመሥራት፣ ለመደገፍና ዕርዳታ ለማሰባሰብ ሃሳብ አለህ?

ቴዲ አፍሮ፦ ይሄ ዝግጅትና ፕሮጀክት አሳማኝ ሆኖ ያገኘሁት፤ ሰዎችን የተቸገሩበት እንጀራ ከሆነ እንጀራ ገዝቶ የዛሬን ቀን ማዋል ሳይሆን፤ እንጀራ የሚገዙበትን የሥራ መስክ የሚያቋቁም መንገድ ሆኖ ስላየሁት ነው ይሄ ፕሮጀክት። ከተማ ያሉት ሰዎች ገጠር እያሉ የእርሻ በሬያቸው ሲሞት ሊሆን ይችላል ወደ ከተማ የወጡት። እነሱን የእርሻ በሬ እየገዙ ማቋቋም ዓይነት ፕሮጀክት ነው። እና እሱ ጥሩ ሆኖ ስላገኘሁት ነው ወደዛ ያደረግሁት።

ያሬድ፦ ትቀጥላለህ በዚህ ዕርዳታህ?

ቴዲ አፍሮ፦ ወደፊት ብዙ ሃሳብ አለኝ፤ ከሙዚቃ ሙያዬ ባሻገር የዕርዳታና የተለያዩ ማኅበራዊ ሥራዎችን የመሥራት ዕቅድ አለኝ - እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ። ይህ ሁሉ እግዚአብሔር ሲፈቅድ ይሆናል።

ያሬድ፦ ”ያስተሰርያል” የሚለውን ዘፈን ጥቅምት 1 ቀን 2002 ዓ.ም. ስታዲየም ባዘጋጀኸው ኮንሰርት ላይ ለምንድን ነው ያልዘፈንከው? እንዳትዘፍን የከለከለህ አካል ነበር ወይ?

ቴዲ አፍሮ፦ በጊዜው ያንን ፈቃድ ለማግኘት ከሚመለከታቸው አካሎች ጋር ስንነጋገር፤ ይህን ዘፈን ብንጫወተው፤ ይሄ ነገር ሌላ መልዕክት አለው ብለው የሚያስቡ ወደ ግጭት ሊያመራብን ይችላልና፤ ይሄን ዘፈን ባትጫወተው ጥሩ ነው የሚል ነገር ሲኖር፤ ይሄንን ዘፈን ባለመጫወት በመጫወት ምክንያት ያንን ዝግጅት ሳላደርግ፣ ህዝቡንም ሳላገኝ፣ ይሄንንም የተቀደሰ ዓላማ ሳላከናውን ከማልፍ ለዚያ ቦታ ብቻ ልለፈው ብዬ ነው ያለፍኩት።

ያሬድ፦ የዘፈኖችህ ዜማና ግጥም ብዙ ጊዜ የራስህ ናቸው፤ ለምንድነው ከሌሎች የማትወስደው?

ቴዲ አፍሮ፦ ከሌሎች የተሻለ ነገር ሳገኝ በማንኛውም ጊዜ ዝግጁ ነኝ። ከሌሎችም እስከዛሬ አልወሰድኩም ብሎ ለማለት አስቸጋሪ ነው፤ አንድም ቢሆን። ቀደም ሲል የነጥላሁንን ዘፈን ተጫውቻለሁ። ከዚያ በስተቀር ሁሉም የራሴ ናቸው። ምናልባት የተሻለ ነገር ካገኘሁ ሁልጊዜም እሞክራለሁ። የተሻለ ሆኖ ስላላገኘሁት ነው። አንተም ካለህ ብትሰጠኝ ዝግጁ ነኝ።

ያሬድ፦ ”ቴዲ መድረክ ላይ የዳንስ እንቅስቃሴ ያንሰዋል” የሚሉ ወገኖች አሉ። አንተስ ራስህ መድረክ ላይ ለሙዚቃዬ የሚመጥን እንቅስቃሴ አደርጋለሁ ብለህ ታምናለህ ወይ?

ቴዲ አፍሮ፦ እኔ የሙዚቃ ሰዉን ለመሳብ የምደንሰው ዳንስ ሳይሆን፤ መጀመሪያ ስሜት ውስጥ ለመግባት የሚሰጠኝን እንቅስቃሴ ራሱ ይመራኛል እንጂ፤ እራሴ እየመራሁት በዕቅድ የመደነስን አልከተልም። የዚህ ዓይነት ስሜት ያላቸው ሰዎችን ደግሞ ስሜታቸው ስለሆነ አደንቅላቸዋለሁ። በጣም ነው የማከብራቸው። የማደንቃቸው። ነገር ግን እኔ የዚህ ዓይነት ፍላጎት አይደለም ያለኝ። በተለይ፣ በራሴ መንገድ ነው የምንቀሳቀሰው። የምንቀሳቀሰውም ሰው ለመማረክ ብዬ ሳይሆን፤ ወደውስጥ ወደሙዚቃው በመግባት፤ ራሴ ውስጥ በምገባ ጊዜ ነው ሰዉም ሊደሰት የሚችለው። በዚህ ስሜት ነው የምሄደው።

ያሬድ፦ በቅርቡ ከሀገር ውጭ የጀመርከው የኮንሰርት ጉዞህ እንዴት ነው? ከሀገር ቤት ከወጣህ ስንት ሀገሮች ተጫወትክ? የህዝቡስ አቀባበልና ስሜትስ እንዴት ነበር?

ቴዲ አፍሮ፦ ከሀገር ከወጣን ከስድስት ከሰባት ያላነሱ ዝግጅቶችን አቅርበናል። የተለያዩ ሀገሮች ናቸው። ጣሊያን፣ ጀርመን ሁለት ቦታ (ፍራንክፈርትና ሙንሺን)፣ ሆላንድ፣ ኖርዌይ ተጫውተናል። አሁን ስዊድን መጥተናል። እንዲህ እንዲህ እያልን እንቀጥላለን። በሄድንበት ሁሉ በጣም የተለየና ከእስከዛሬው ሁሉ የተሻለ አቀባበል ሆኖ ነው ያገኘነው። እኛም በሠራነው ነገር ሁሉ ተደስተናል።

ያሬድ፦ አንዳንድ ወገኖች የኖርዌዩን የሙዚቃ ድግስህን ቦይኮት ለማስደረግ ጥረት ሲያደርጉ ነበር። በኖርዌይ ነዋሪ የሆኑ አፍቃሪዎችህ ቦይኮት አደረጉህ ወይ? በአጠቃላይ ባለፈው ቅዳሜ ኖቨምበር 28 የተካሄደው የኖርዌዩ ኮንሰርትህ ከዚህ ቀደም በኖርዌይ ካደረግኸው ጋር ሲወዳደር ምን ይመስል ነበር?

ቴዲ አፍሮ፦ እንዴት አገኘኸው አንተ ካለህ መረጃ?

ያሬድ፦ በእርግጥ መረጃ አለኝ፤ ነገር ግን እኔ ያለኝን መረጃ ከምነግርህ አንተው ራስህ ብትነግረኝ ይሻላል። (ከሳቅ ጋር)

ቴዲ አፍሮ፦ ጠያቂ ለመሆን ብቻ ነው የመጣኸው ማለት ነው። ምንም ችግር የለም (ከሳቅ ጋር) ... ከአንድ ሺህ በላይ ሰው ነው የገባው። ከሰዉ ቁጥር በላይ የነበረው ፍቅር ለመግለጽ የሚከብድና ልዩ የሆነ ስሜት የፈጠረ ዝግጅት ነበር። በጣም ደስ ብሎኛል። ይሄ የተባለውም ነገር መሠረት የሌለውና ፍፁም መስመር የሳተ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች እንቅስቃሴ ነው።

ያሬድ፦ በዚህ በስዊድንና በኖርዌይ አካባቢ የነበረውን አንዳንድ የተዛቡ መረጃዎች በምን ምክንያት ሊፈጠሩ እንደቻሉና፤ ምናልባትም ከአቶ ሐብታሙ አለነ ጋር የተገናኘውን ልታስረዳኝ ትችላለህ?

ቴዲ አፍሮ፦ በጣም ባጭሩ ልነግርህ እችላለሁ። የዚህ ሁሉ ውዥንብሩ ምክንያቱ ይሄና ይሄ ብቻ ነው። ምክንያቱም ይሄ ልጅ ከእኔ ጋር መሥራት ይፈልግ ነበር፤ እኔ ደግሞ ጠቅላላውን የአውሮፓ ኮንሰርት ለአዲካ፣ ለአዲስ ቪው ካምፓኒ እና ለኤም.ጂ. ፕሮሞሽን ነው የሸጥኩት። እነዚያ ሰዎች ደግሞ ለፈለጉት ሰው ዝግጅታቸውን የመሸጥ መብታ አላቸው። ላስገድዳቸው አልችልም። ነገር ግን ከእሱ ጋር እንዲሠሩ ቅድሚያ ነግሬአቸው ነበር። ዘግይቶም ቢመጣ ፈቀዱለትና የሚያስፈልገውን ቅድሚያ ክፍያ እንዲፈጽም በጊዜው እንዲልክ ሰጡት ማስጠንቀቂያ። በተባለው ቀን ያንን ቅድሚያ ክፍያ ስላላመጣ እነሱ ያንን ዝግጅት ለሌላ ሰው ፈርመው ሰጡ። በሚቀጥለው ቀን ሌት ሆኖ (ጊዜው ካለፈው በኋላ) መጥቶ ”መሥራት መቀጠሌ ነውና፤ ይሄንን ነገር እንዴት እናድርገው?” ሲል፤ እነሱ ኦሬዲ (አስቀድመው) ተፈራርመው ነበርና፤ ዘገየህ አሉት። የአንድ ቀን የሁለት ቀን ልዩነት ፈጥሮ ነው የመጣው።

በኋላ ”በዚህ ምክንያት እኔ የአዳራሽ ከፍያለሁ፣ ...” ምናምን የሚሉ ነገሮች በሚቀጥሉት ቀናት ይዞ መጣ። በሁለት ቀን ውስጥ አንድ ሰው አዳራሽ ይዞ ያንን ሁሉ ቦታ ይይዛል የሚለውን እንግዲህ ማንም አዕምሮ ያለው ሰው ሊፈርደው የሚችል ነው። አንድ ፕሮሞተር ደግሞ ከባለሙያው ጋር ሕጋዊ ውል ሳይኖረው የባለሙያውን ፎቶግራፍ በፖስተርና በፍላየር አሣትሞ የዝግጅት ቀን ፈጥሮ የባለሙያውን ፕሮግራም በህዝብ ዘንድ አሻሚ ማድረግ በሕግ የሚያስጠይቅ ወንጀል ነው። ነገር ግን እኔ ይህን ሁሉ በትዕግሥት ተቋቁሜ አልፌዋለሁ። ያም ከሆነ እንኳን፤ ይሄ ልጅ እንዳይቀየም፣ ወዳጄ ነው፣ ከዚህ ቀደምም ብዙ ስለሠራን አስተናግዱት ብዬ ባልኳቸው መሠረት፤ ”ኪሳራ ካለህ፣ ኪሳራህን በደረሰኝ አቅርብና እንክፈልህ፤ ከልጁ (ቴዲ) ጋር እንድትቀያየም አንፈልግም” አሉት። ደረሰኝም ሊያቀርብ አልቻለም። ይሄ መንገድ አልሆን ሲለው፤ የሄደው መንገድ እንግዲህ ስም በማጥፋት፣ ይሄን ያህል ዘመቻ ውስጥ መግባት፣ ... ነው። ይሄ ትንሽ መስመር ያለፈና በጣም ሥነሥርዓት የጎደለው መንገድ ነው።

ማንም ሰው ደግሞ የፖለቲካን ጉዳይ የጠላውን ሰው የሚያወግዝበት፤ የወደደውን ሰው የሚያሞካሽበት የግል መሣሪያ አይደለም። ከዚህ አስተሳሰብ ካልወጣን በጣም ትልቅ ሆና፣ ፍትህ የነገሠባትን ታላቂቱን ኢትዮጵያ ለማየት በጣም አስቸጋሪ ይሆናል። ለማንኛውም በየቦታው ለነበረው ሁኔታ ጥሩ መስተንግዶ አድርገው ለተቀበሉን ኢትዮጵያውያን ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። በተለይ በተለይ ደግሞ እስር ቤት ሆኜ ብዙ በመጨነቅ፣ በመፀለይ፣ ከዚያም አልፎ ሰልፍ በመውጣት ብዙ ስለእኔ ለከፈሉት ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ከፍተኛ ምስጋናዬን እያቀረብሁ፤ የፍቅር ሠራዊት የሆነውን ባንዳችንን (የሙዚቃ ጓዳችንን) ይዘን ገና ብዙ ለመሄድ እንበረታለን ከእግዚአብሔር ጋር።

ያሬድ፦ ከእስር ከተፈታህ በኋላ በእስር ቤት እያለህ ለመጽሐፍ የሚሆኑ ግጥሞችን መፃፍህን ገልጸህ ነበር። ግጥሞቹን እምን አደረስካቸው?

ቴዲ አፍሮ፦ ግጥሞቹ አሉ። በቂ ዝግጅት አድርጌ በጊዜአቸው ነው የማወጣቸው። ምክንያቱም በተጣደፈ ሁኔታ መውጣት የለባቸውም። ምክንያቱም ብዙ መለቀም ያለበት ነገር አለ። መጽሐፍ በቀላሉ የሚሠራ አይደለም።

ያሬድ፦ ትዳር እንደሌለህ ይታወቃል። እጮኛ ወይንም ፍቅረኛ አለችህ ወይ?

ቴዲ አፍሮ፦ አለችኝ አዎ!
ያሬድ፦ ስሟ ማን ይባላል?
ቴዲ አፍሮ፦ ስሟ ያስፈልጋል?
ያሬድ፦ ብዙ ሰዎች ይወዱሃልና፤ የአንተን ፍቅረኛ ስም ቢያውቁ ደስ ይላቸዋል።
ቴዲ አፍሮ፦ ብሩክታይት ትባላለች፤ አሜሪካን ሀገር ነው የምትኖረው። እስር ቤት ያለሁም ጊዜ ጠይቃኝ ነበር።
ያሬድ፦ ህዝብ የሰጠህን ፍቅር፣ አድናቆትና ክብር ይዘህ ለመቆየት የምታደርገው ጥረት ምን ይመስላል?
ቴዲ አፍሮ፦ እንግዲህ በተቻለኝ መጠን ባለኝ ዕድሜ - በቀረኝ ዕድሜ ለሚወደኝ የሀገሬ ህዝብ፣ ብዙ ለሆነልኝ የሀገሬ ህዝብ ብዙ ልሆንለት ዝግጁ ነኝ። አንድ ነፍስ ነው ያለኝ፤ ሁለት ሦስት ነፍስ ቢኖረኝ፤ ሁለቱንም ሦስቱንም ለመስጠት ዝግጁ እስከምሆን በማይሻር ቃል ነው እየተናገርኩት ያለሁት። ይሄን ያህል ድረስ ነው።
ያሬድ፦ በዚህ በየሀገሩ እየተዘዋወርክ በምታሳየው ኮንሰርትህ እና በስዊድን የፊታችን ቅዳሜ ዲሴምበር 5 በምታደርገው የሙዚቃ ድግስ ላይ የሚያጅብህ የአቡጊዳ ባንድ መሆኑን ሰምቻለሁ። ይሄ እውነት ከሆነ ባንዱ የማን እንደሆነና የአባላቱን ማንነት ብትገልጽልኝ። ቋሚ መቀመጫቸውስ የት ሀገር ወይም ስቴት ነው?
ቴዲ አፍሮ፦ አቡጊዳ ባንድን እኔ ነኝ ያቋቋምኩት። የባንዱ አባላት አብዛኞቹ የሚኖሩት ቺካጎ ነው። ከኪቦርዲስቱ ያሬድ አብርሃም ይባላል፣ ሲያትል ነው የሚኖረው። ቤዝ ጊታር የሚጫወተው ደግሞ ኤርሚያስ ከበደ ይባላል፤ ቺካጎ ነው የሚኖረው። ሊድ ጊታር አበራ ዓለሙ - ቺካጎ። ድራመር ሩፋዔል - ቺካጎ። ሩፋዔል ቀደም ሲል የዚጊ ማርሊ ድራመር ነበር። ከአዲስ አበባ ደግሞ ከጨመርናቸው ኪቦርዲስት አማኑዔል ይልማ፣ ”አበባየሆሽ”ን ያቀናበረው እሱ ነው።
ያሬድ፦ ስለሰጠኸኝ ቃለምልልስ በኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ፣ በአንባቢዎች እና በራሴ ስም አመሰግናለሁ!

ቴዲ አፍሮ፦ ... እግዜር ይስጥልኝ! ስለጠየቅኸኝም አመሰግናለሁ። ጤና ይስጥልኝ!

Post Reply

Return to “Ethio Art and Culture..ኢትዮ ጥበብ ፤ስነ ጽሁፍ ፤”