Page 1 of 1

መልክ የሌላት ህይወት! አጭር ልብወለድ

Posted: 04 Apr 2016 13:36
by zeru
መልክ የሌላት ህይወት! አጭር ልብወለድ ደረጀ በላይነህ

የመኪናውን መሪ የጨበጠበት ጠይም ፈርጣማ
ጡንቻ አንዴ ወደ ግራ፣ ሌላ ጊዜ ወደ ቀኝ እያለ ወደ
ሰሜን ማዘጋጃ ሽቅብ ጋለብን፡፡ የኤክስኪዩቲቭዋ
ሳሎን በሽቶ መዓዛ ታውዷል፡፡
አሽከርካሪው ስልክክ ፊቱን ፊት ለፊት ተክሎ፣
አንዴ ማርሽ ከቀየረ በኋላ መሪውን በሁለት
እጁ እየያዘ በጥሩ ፍጥነት ይጓዛል፡፡ ፊቱ ሲታይ
ጨካኝ ይሁን መራራ፣ ደግ ይሁን ርኅሩህ መለየት
ያዳግታል

ስሜቱን ከፊቱ ላይ ፈልጌ አጣሁት፡፡
ሆኖም “... ወንዶችማ አውሬዎች ናቸው!” ... ብዬ
ጥላቻዬን ከልቤ ፈለፈልኩ፡፡
በዚያ ላይ አንድ ጊዜ እንኳ ጥሩ ፈገግታ ስላላሳየኝ
ከፋኝ፡፡ ለነገሩ እኔ መች ክብር አግኝቼ አውቃለሁ?
... ምናልባት እንደ ሰው የሚቆጥሩኝ ያቺ የሰፈሬ
ሽሮ ቤት ባለቤትና ባለሱቁ ነሥሩ ናቸው፡፡ ነሥሩም
ቢሆን ያው እንስሳነቱ ሲባርቅበት መቀመጫዬን
ተከትሎ ዓይኑን ከማቃዠት ሌላ ውስጤን መች
አሥቦት ያውቃል?
ሌላኛዋ ቤት አከራዬ ናቸው፡፡ እሳቸውም ቢሆኑ
የቤት ኪራይ ሳልከፍል አንድ ቀን ከዘገየሁ በአሽሙር
ይዘለዝሉኛል፡፡ በቃ ባለ ሽሮ ቤትዋ አረጋሽ ናት
ከልብ የምትቀርበኝ፡፡ እንደ ሰው ባትቆጥረኝ መች
የልቧን ታወራኝ ነበር! ... በተለይ ገበያ እምቢ ያላት
ሰሞን የትንሽ ልጅዋን ፀጉር በጣቷ እየቆፈረች ስንት
ወሬ አውርታኛለች? .. ከልጅዋ አባት ጋር እንዴት
እንደተጋቡ፣ ... በኋላ እንዴት መጠጥ እንደለመደ
... ሱሰኛ ሆኖ እንዴት መደባደብ እንደጀመረ ሁሉ
እያለቀሰች ነግራኛለች፡፡ ... ከኖረችበት የገጠር ከተማ
ወደ አዲስ አበባ መጥታ ሰው ቤት መቀጠርዋ
ያመጣባትን ጣጣ ... በቤቱ ባለቤት መደፈርዋን
... ብዙ አሳዛኝ ታሪክዋን ዘክዝካልኛለች፡፡ ከልቧ
የምታመሰግናቸው ግን የቀበሌያቸውን አነስተኛና
ጥቃቅን ኃላፊን ነው፡፡ እርሳቸው ጉስቁልናዋን
አይተው ይህቺን የቀበሌ ቤት ባይሰጧትና ሥራ
ባትጀምር ኖሮ የትም ወድቃ ትቀር ነበር፡፡ ስንቱ
ወድቆ ቀርቶ የለ! ... ትንሽ ጉቦ ነገር ግን ሳይቀበሏት
አልቀሩም! .. መልኳም እኮ ያሳስታል፡፡
ልጃቸውን ይዘው መጥተው አንድ እንጀራ
ለሁለት የሚበሉት መምህርም ሰላምተኛዋ ናቸው

ሽቁጥቁ! ... የልጃቸው እናት ስለሞተችባቸው
የሰራተኛ ደሞዝ መክፈል አቅቷቸው ብዙ ጊዜ ምግብ
የሚያሰናዱት ራሳቸው ናቸው፡፡ ሲደክማቸው ደግሞ
አረጋሽ ሽሮ ቤት ጎራ ይላሉ፡፡ በርግጥ አቀራረባቸው
ትንሽ ያጠራጥራል፡፡ የኔም ቅላት እንደ ፀሐይ ብዙ
ወንዶችን ይጠቅሳል፡፡ መምህሩ የሚያሥቁኝ ግን
“ለምን የማታ አትማሪም?” ሲሉኝ ነው፡፡ እሳቸው
የቀን ተምረው አንድ ሽሮ ላይ ሲራኮቱ እያየሁ፣
እንዴት ነው የማታ ልማር ብዬ የምጓጓው? ... ያቺን
አንድ ሽሮማ መች አጣሁ!
መኪናዋ ሽቅብ ብላ ስትተነፍስ ጀንበርዋ
ከተራራው ሥር ተሰወረች፡፡ ይሄኔ ደስ አለኝ፡፡ “በቃ
ይሄ ሰውዬ ቤቱ ይዞኝ ይገባል፡፡” አልኩ በሀሳቤ፡፡
የከፈተው ሙዚቃ ደስ አይልም፡፡ “...ፍቅሬ...አበባዬ...
ውዴ” የሚል ነገር የለውም፡፡ አብዮታዊ ነው፡፡ ...
ለእናት አገሩ ደንታ የሌለው
ለወገኖቹ ደንታ የሌለው
ከሆዱ ሌላ የማይታየው
... እያለ ይቀጥላል፡፡ ወይ ጉድ! አልኩ፡፡
ጥሩ ቤት ለመተኛት፤ ጥሩ ገንዘብ ለማግኘት
ተመኘሁ፡፡ ግን ስንቴ ተመኝቼ አጥቻለሁ! ... ስንቴ
እሳማለሁ ብዬ ተተፍቶብኛል! ... ወንዶች እኮ
አውሬዎች ናቸው፡፡ ስሜታቸው ሽቅብ በወጣ
ጊዜ ብቻ ነው የሴት ገላ ሲያዩ የሚነድዱት! ...
እንደራበው አውሬ ሴት ላይ የሚከመሩት፡፡ እንደዚያ
ተንገብግበው የልባቸውን ካደረሱ በኋላ እንደ
ቆሻሻ ይፀየፋሉ፡፡ በጥፊ ለማጮል ይቸኩላሉ፡፡
ባለትዳሮቹ ደግሞ ይብሳሉ፡፡ “...ሚስቴ ኋላ ቀር ናት!
... አታረካኝም ... አታስደስተኝም፡፡” እያሉ ይናዘዛሉ

ከዚያ በኋላ ደግሞ ሴተኛ አዳሪን መልሰው “ሲዖል-
-- ሰይጣን --- አሳሳች!” ... ሲሉ የእርግማን መዓት
ያወርዳሉ፡፡ ለዚህች ሸክላ ህይወት ስንት ሰው
ለተንኮል ያጠምዳል?

ሊፍት የሰጠኝ ሰውዬ የጠረጠረኝ ይመስላል፡፡
ቀስ እያለ በቆረጣ ያየኛል፡፡ ግን ፈገግ አይልም፡፡ ፊቱ
ጭልም፣ ውስጡ ስብር ያለ ነው፡፡ ሌሎቹ እኮ የእኔን
ዓይነት ፍም የመሰለ ጭን ሲያዩ እንደ ቀይ ቀበሮ
ብርቅ ይሆንባቸዋል፡፡ ትንፋሻቸው ይቋረጣል፡፡
በተለይ ደግሞ ባለትዳር ከመሰልኳቸው ጉጉታቸው
ያይላል፡፡ ሳንቲም ፈላጊ መሆኔን ሲያውቁ ነው እንደ
ዕቃ የሚያራክሱኝ፡፡
የዛሬ መጨረሻዬ ግን ምን ይሆን? .. ሰውየው
ትዳሩን አክባሪ ይመስላል፤ ጨዋ ቢጤ ነው

ይሄኔ ሚስቱ ርግብ ትሆናለች! ... እርሱም ክፉ
አይመልስም፤ ደግ መሆኑን ማወቅ ግን ይከብዳል፡፡
ሊፍት የሰጠኝ አዝኖልኝ ከሆነ ደግ ነው ማለት ነው፡፡
ግን አይታወቅም፡፡ አንዳንዱ መጨረሻ ላይ ነው ዛሩ
የሚነሳው፡፡ ወርውሮ አልጋ ላይ ሊጥለኝ ይችላል፡፡
ስንት ጉድ አይቻለሁ እኮ!
ፅዮን ሆቴልን አልፈን ወደ ሸገር ራዲዮ ጣቢያ ጉዞ
ጀመርን፡፡ በስተቀኝ በኩል ካለው ጎዳና ባለ ላዳውን
ተክሉን አየሁት፡፡ ገረመኝ፡፡ እዚህ ድረስ ይመጣል
ማለት ነው? ... ቢያየኝ አንድ አፍታ ይወርድብኝ
ነበር፡፡ እሱ ደሞ ቀልዱና ምሩ አይታወቅም፤ ምላሱ
መቼም አያርፍም፡፡ ሚስቱ ግን ደግ ናት፡፡ አንድ ሰሞን
አሞኝ ብተኛ በየዕለቱ ተመላልሳ ጠይቃኛለች

አንዴ
ሙቅ፣ ሌላ ጊዜ እንጀራ ፍትፍት ይዛ እግዜር ይማርሽ
ብላኛለች፡፡ እርሱ ግን ሲሰማ፤ “ሸርሙጣ ቤት ለምን
ሄድሽ” ብሏታል፡፡
ብዙ ሰው ዛሬ ያለሁበትን ሁኔታ ሲያይ እንዲህ
ሆኜ የተፈጠርኩ ይመስለዋል፤ የህይወት አጋጣሚ
በአንዳች ቀውስ እንደሚታጠፍ አያውቅም

ቤተሰቦቼ እኔን ሲወልዱ ሀብታም ነበሩ፡፡ ጥሩ
ትምህርት ቤትም አስገብተውኝ ነበር፡፡ ግን ሁሉም
ነገር እንደ ጅምሩ አልዘለቀም፡፡ ሁለቱም ወላጆቼ
ታመሙና ሆስፒታል ገቡ፡፡ ስራ ቆመ፡፡ የነበረው
ሀብት በሀኪም ቤት ወጪ ተሟጠጠ፡፡ የቀረችውን
አንዲት ሱቅና መኖሪያ ቤት ለአክስቴ አወረሷት

እኔም ለእርሷ አደራ ተሰጠሁ፡፡ ብዙም ሳይቆይ
በቤተሰቦቼ ቀሪ ሀብት አክስቴና ባለቤቷ ነገሱበት

እኔን ጭራሽ ለአይናቸው ጠሉኝ፡፡ የምበላውን
ምግብ እንኳ ከልክለውኝ፣ ወላጆቼን የሚያውቁ
ጎረቤቶቼ እየደበቁ ያጎርሱኝ ጀመር፡፡ ህይወቴ
ዝብርቅርቁ ወጣ፡፡ ትምህርት አፈር በላ፡፡ አክስቴ
በኔ የከፋችውን ያህል ባለቤቷ ከፋባት፣ እርሷን
አስቀምጦ ሌላ ሚስት አገባ፡፡ እርሷን አውጥቶ
ወረወራት፡፡ እኔም አይኔን ይዤ ወደዚህ መጣሁ፡፡
ሻሸመኔ መወለዴ የጠቀመኝ ቀልጣፋ ለመሆን ብቻ
ነው፡፡ ፈጣን ከተማ ነበረች ሻሸመኔ፡፡ የእኔን ህይወት
ሳስብ ስለ ቀጣይ ህይወቱ እርግጠኛ የሚሆን ማነው?
እላለሁ፡፡ በክብር ጀምሮ በውርደት የሚጨርስ ሁሉ
መች ወድዶ ሆነና?
ጎረቤታችን የነበሩት ወይዘሮ ሸዋነሽን ያህል
ልጆቹ ያቀማጠለ አለ? ማንም አይደርሳቸው! .. ግን
ምን ዋጋ አለው ... አንደኛው ልጃቸው ትምህርቱን
አልማር ብሎ ሀሺሹን ሲጀነጀን ውሎ እያደረ
ጨርቁን ጣለ፡፡ ሦስቴ አራቴ አማኑኤል ሆስፒታል
ገባ፤ ግን አልተመለሰም፡፡ አሁን ብሄራዊ ቴአትር
አጥር ጥግ ቁጭ ብሎ ጫቱን ይቅማል፤ ሀሺሽና
ሲጋራውን ያንበለብላል፡፡ ... ዕድል ነው!
እኒያ አረጋሽ ሽሮ ቤት የሚመጡ መምህር
እንደ ወፍ የአፋቸውን እያጎረሱ ያሳደጉት ልጅ
የት እንደሚደርስ ማን ያውቃል?... ስንት የምሽት
ደንበኞቼ ናቸው ሲሰክሩ እያለቀሱ ...ፀፀታቸውን
የሚያወሩት? ... ደሀዋ እናቴ ጎመን ሸጣ አስተምራኝ
.. እያሉ የሚናዘዙት፡፡ የሰው ኑሮ መልክ የለውም፡፡
“እመቤት እዚህ ነበር ያልሺኝ!” አለኝ ሊፍት
የሰጠኝ ሰውዬ፡፡ ፍጥጥ ብዬ አየሁት፡፡ እውነትም
ያልኩት ቦታ ደርሻለሁ፡፡ ትንሽ እንዲገፋኝ ነገርኩት

ፊቱ ድብልቅልቅ ያለ፣ ስሜቱ የተረበሸ መሰለ

ግን “ሽቶሽ ደስ ይላል!” አለኝ፡፡ የበዓሉ ግርማን
መጽሐፍት በማነብበት ደጉ ዘመን መጽሐፉ ውስጥ
የነበሩት ሽቶ ወዳዶች ትዝ አሉኝ፡፡ ሆዴ ሊባባ ከጀለ

ሰውየው ስለ ሽቶ ያወራው ዝም ብሎ አልነበረም፡፡
አልጋ ላይ የሚወረውሩት ዓይነት አድፋጭ መሆኑን
ጠርጥሬአለሁ፡፡
“አብረን ብናድር ስንት ትጠይቂኛለሽ?” አለኝ
ድንገት፡፡
ፈገግ ብዬ ከንፈሬን ላጥኩት፣ ጥርሶቼን ወደ
ውጭ ሸኘኋቸው፡፡ ... አሰብ አደረኩና ሂሳቤን
ነገርኩት፡፡ ወዲያው ቆጥሮ ሰጠኝ፡፡ የጠየኩትን
እጥፍ ነው፡፡ እንዴት አይነት ደግ ነው? እኔም
አንጀቱን አርሰዋለሁ፤ እንደ ቆንቋኖቹ አልሆንበትም

ብዬ በልቤ ደግ ተመኘሁለት፤ ... እንዳሻው
ብሆንለትስ? ... ምስኪን ነው፡፡ እያልኩ ሳስብ፣ “በቃ
ዛሬ ቤትሽ ገብተሽ በሰላም ተኚ! ... እኔም ከሚስቴ
ጋር እተኛለሁ፡፡” አለኝና ፊቱን መሪው ላይ ደፍቶ
ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ፡፡ ግራ ገባኝ፡፡ ላደረገልኝ ደግነት
እጆቹን ጎትቼ ሳምኳቸው፡፡
መኪናዋን ከመንገድ ጠርዝ አውጥቶ ስለነበር
ስጋት አልያዘኝም፡፡
“ምነው ምን ሆንክ?” ጠየኩት በሃዘኔታ፡፡
“እህቴ ዩኒቨርሲቲ ያስተማረችኝ እንዳንቺ የሰው
ፊት እየገረፋት ራስዋን ሸጣ ነበር፤ አይዞሽ!”
“እህትህ አሁን አለች?” አልኩት ከአፉ ነጥቄ፡፡
ልቅሶው ባሰበት፡፡ ወንድ ልጅ እንዲህ ሲያለቅስ
አይቼ አላውቅም፡፡ እናቱ በልምጭ የለበለበችው
ልጅ ይመሥል ሳግ ነቀነቀው፡፡
“አስመርቃኝ በሳምንቱ በአደጋ ሞተች! ... የርሷ
ውለታ ህሊናዬ ውስጥ ይጮሃል! .. ያቃጥለኛል!”
አሳዘነኝ፡፡ ወንድ ሁሉ አውሬ አይደለም ለካ! ...
“አይዞህ የኔ ጌታ! ለኔ ይለቀስ!”
መኪናውን ወደ መጣንበት አዞረው፡፡
“ም - ነ - ው?”
“እሸኝሻለሁ!”
ስንት ዓይነት ሰው አለ? ... ነገሩ ወንድ መሆን
አሊያም ሴት መሆን አይደለም፡፡ .... ነገሩ የፆታ
ሳይሆን የልብ ጉዳይ ነው፡፡ የመልአክ ልብ የተቸረው
ሰውዬ!!

Source: addisadmassnews.com