ፈረንጅ ሆይ ናና በ ዳንኤል ክብረት

ግጥሞች፣ታሪኮች፣ፎቶዎች፣ሙዚቃዎች
Poems,Short stories, graphics,pictures,musics,Technology
selam sew
Leader
Leader
Posts: 616
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

ፈረንጅ ሆይ ናና በ ዳንኤል ክብረት

Unread post by selam sew » 21 Dec 2015 22:43

ፈረንጅ ሆይ ናና

ፈረንጅ ሆይ ናና ፈረንጅ ሆይ ናና
አንተ ስትናገር ይታመናልና
ፈረንጅ ሆይ ናና ፈረንጅ ሆይ ናና
አንተ ስትናገር ትሰማለህና
ፈረንጅ ሆይ፤
አንተ ገድላቱንና ድርሳናቱን፣ ዜና መዋዕሎችንና ታሪከ ነገሥቱን፣ የፍልስፍናውንና የጥበቡን፣ የመድኃኒቱንና የጠልሰሙን ነገር ከግእዝ ወደ እንግሊዝኛ ስትተረጉመው ሁሉም ያደንቅሃል፣ ያነብሃል፡፡ ይጠቅስሃል፡፡ ‹ከውጭ ድረስ መጥተው የኛን ታሪክ አጥንተው› እየተባለ ይነገርልሃል፡፡ እኛ ያደረግነው ቀን ግን ‹የደብተራ ጽሑፍ፣ የነፍጠኛ ድርሰት፣ ያበሻ ተረት ተረት ይባላል፡፡ እናም ፈረንጅ ሆይ ና፡፡ አባቶቻችን ለሺ ዘመናት ያቆዩትን የጽሑፍ ቅርስ ወሰድ፣ ስረቅ፣ አውጣ፣ ግእዝ ተማርና ተርጉም፤ ተርጉምና በዶላር ሺጥልን፡፡ ያን ጊዜ በእንግሊዝኛ ስታመጣው - ፓ- እያልን እናነብሃለን፡፡
ምን ማንበብ ብቻ ግእዙን ብንጠቅሰው የደብተራ ድርሰት፣ የቄሶች ግሳንግስ፣ የድሮ ናፋቂ፣ ምናምን ስለምንባል ምናለ በእንግሊዝኛ ብታመጣልንና ‹የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዜና መዋዕል› ብለን ጠቅሰን መከራ ከምናይ ‹The chronicle of king zare’a yae’qob> ብንል ማናለበት፡፡ እኛ ስለ ንግሥተ ሳባ ስንናገር ተረት ይሆናል፤ አንተ ሮምን የመሠረቷት ሮሙለስና ሙለስ የተባሉ ተኩላ ያሳደገቻቸው ልጆች ናቸው ስትል ግን ሁሉ ያምንሃል፡፡
ደግሞ ያንተ ጥሩነቱ ምንም ነገር ብትጽፍ፣ ምንም ነገር በትናገር - ኦሮሞ ስለሆንክ ነው፣ ጉራጌ ስለሆን ነው፣ አማራ ስለሆንክ ነው፣ ክርስቲያን ስለሆንክ ነው፣ ሙስሊም ስለሆንክ ነው፣ ደርግ ስለሆንክ ነው፣ ኢሕአዴግ ስለሆንክ ነው፣ ተቃዋሚ ስለሆንክ ነው፣ ካድሬ ስለሆንክ ነው- የሚልህ የለ፡፡ አገርህ አይጠየቅ፣ ወንዝህ አይጠና፣ ዘርህ አይፈለግ፣ ብቻ ፈረንጅ ሁን፡፡
ፈረንጅ ሆይ ና፤
ስለ ዳጉሳ፣ ስለ ቆጮ፣ ስለ ክትፎ፣ ስለ ቡላ፣ ስለ ገንፎ፣ ስለ ቃተኛ፣ ስለ ጨጨብሳ፣ ስለ ቆሎ፣ ስለ ንፍሮ፣ ስለ በቆሎ ጥብስ፣ ስለ ጠላና ጠጅ፣ ስለ አረቂና ቦርዴ፣ ስለ ቅቅልና ጥብስ በእንግሊዝኛ ተናገር፡፡ ይኼው ስንት ዓመት ስንመገበው ‹ከወኔ በቀር ሌላ የለውም› ሲባል የነበረው ጤፍ አንተ በእንግሊዝኛ ስትናገርለት አበሻ ሆዬ በኩራት ‹‹የጤፋችን ፓተንት ይመለስ›› ማለት ጀመረ አይደል? ትናንት እንኳን ስለ ፓተንቱ ስለመኖሩስ ማን ያስብ ነበር፡፡
አይ ፈረንጅ ቀን ይውጣልህ፤ ይኼው ለጥቁር ጤፍ እንኳን ቀን አወጣህለት፡፡ ማን ነበር ትናንት ቸግሮት ካልሆነ በቀር ጥቁር ጤፍ የሚሸምተው፡፡ ‹‹የሚበላው ነጭ፣ የሚጠጣው ጠጅ‹‹ አልነበር ፉከራው፡፡
ቢቸግረኝ እንጂ ጥቁር የምበላ
ያደግኩ ነበረ በማር በወለላ - ይባል ነበርኮ፡፡
ማን ነበር ትናንት ድግስ ላይ ጥቁር እንጀራ የሚያቀርበው? ሰፈር እንዲረግመው ካልፈለገ በቀር፡፡ ማን ነበረ ትናንት ጥቁር እንጀራ ምግብ ቤት ውስጥ የሚያቀርበው፤ የሚያስቀርበውስ፡፡ አእምሮው ተነክቶ ካልሆነ በቀር፡፡
ይኼው አንተ ‹‹ጥቁር ጤፍ ምናምን አለው፤ ከምናምን ነጻ ነው፤ ለምናምን መድኃኒት ነው›› ብለህ ተናግረህ አበሻ በኩራት ‹ነጭ ጤፍኮ ጥሩ አይደለም፤ ጥቁር ጤፍ ነው መብላት፤ እንትን እንዳለው ታውቃለህ አይደል›› እያለ የዕውቀት መለኪያ አደረገው፡፡ መቼም የወደቀን እንዳነሣህ የወደቁትን የሚያነሣ አምላክ ያንሣህ፡፡ አንተ አይደለህ እንዴ የገብስ ዳቦ፣ ጥቁር ዳቦ፣ የጥቁር ጤፍ ዳቦ፣ የሚባል ነገር ያመጣህብን፡፡ ደኅና ነጩን እንዳንበላበት፡፡ ድሮ እናቶቻችን ‹የጥቁር ገብስ ጠላ፣ የጥቁር ጤፍ እንጀራ፣ የጥቁር ስንዴ ዳቦ ጎን ይደግፋል› ሲሉ ማን ሰምቷቸው፡፡ እንኳን ለምግብነት ለኩስነት እንኳን ነጭ ነበርኮ የሚመረጠው፡፡
የፈሩ አህዮች ለጅብ በቀቁት ነጠላ ዜማ ላይ፡-
ምን ጥቁር ቢበሉ ነጭ ነው ኩስዎ
ምን ከሩቅ ቢጮኹ ይሰማል ድምጥዎ
አሁን የርስዎን ልጅ ምን አገኘብዎ፤
አይደል እንዴ ያሉት፡፡ ምናለ ጥቁሩን ጤፍ ከነጭ እንዳስተካከልከው እዚያው በነካ እጅህ፣ በሀገርህ ጥቁሩን ሰው ከነጭ ምናለ ብታስተካክለው፡፡
ፈረንጅ በሞቴ ና፤ አባቶቻችን፣ አያቶቻችን የቀመሩትን፣ በባሕላችን ውስጥ ያሳደጉትን፤ ሊቆቻችን ያጠኑትን፤ አሳቢዎቻችን የተናገሩትን ማን ከቁም ነገር ይወስደዋል፡፡ ያውምኮ ለራሳችን ወርድና ቁመት እንዲሆን ሆኖ በራሳችን የተሰፋውን፡፡ አንተ ግን ለራስህ አገር ያዘጋጀኸውን፣ የቀመርከውን ነገር፤ ከባህልህና ከልምድህ፣ ከሕዝብህ ፍላጎትና ዕድገት፣ ከሥነ ልቡናህና ጠባይህ ተነሥተህ ለራስህ የቀረጽከውን ሕግ፣ አሠራር፣ መሥሪያ ቤት፣ ዐዋጅና ፖሊሲ - ‹‹የውጭ ሀገር ልምድ ታክሎበት፣ የሌሎችን ሀገሮች ልምድ በመቀመር፣ ያደጉ ሀገሮችን ሕጎች በማገናዘብ›› እየተባለ ሕግና አሠራር ይወጣልናል፡፡ የኛ ሊቃውንት አንተ ሀገር መጥተው፣ ወይ በትምህርት፣ ወይ በዐውደ ጥናት፣ ወይ በሰባቲካል ሊቭ፣ ወይ በፌሎውሺፕ፣ ወይ በአማካሪነት ያጠኑትን ጥናት ትወስድና፣ በእንግሊዝኛ ትቀይርና፣ ‹‹የውጭ ሀገር ተሞክሮ›› የሚባል የክርስትና ስም ትሰጥና መልሰህ ለራሳችን ትሸጥልናለህ፡፡
አየህ - በኦሮምኛ፣ በትግርኛና በአፋርኛ፣ በወላይትኛና በአማርኛ፣ በሲዳምኛና በሶምልኛ ከምንሰማው በእንግሊዝኛ ብንሰማው የኛም ሊቅነታችን ይታመናል፡፡ ሙሽራ እንኳን ሲዳር
የኛ ሙሽራ ኩሪባቸው
በእንግሊዝ አናግሪያቸው
አይደል የሚባለው፡፡ ተወው ሌላውን፤ የኛኑ ተረት፣ የኛኑ ምሳሌ፣ የኛኑ አባባል፣ የኛኑ አፈ ታሪክ - ከሰሜንና ከደቡብ፣ ከምሥራቅና ከምዕራብ ወስደህ፣ ብቻ የሆነ ርእስ ሰጥተህ - ወይ በፈረንሳይኛ፣ ወይ በጀርመንኛ ወይ በእንግሊዝኛ ስታሳትመው አቤት ያለን ደስታ፡፡ ከዚያ የኛ ሥራ ምን እንደሆነ ታውቃለህ? ‹‹የእንትን ብሔረሰብ ቃላዊ ቅርሶች ለዓለም ሥነ ጽሑፍ ያበረከቱት አስተዋጽዖ› የሚል ጥናት እናደርግና በገዛ ተረታችን አንተን እንጠቅስና፣ ተረታችን በሀገርኛ ቋንቋ ከሚጻፍ ይልቅ በውጭ ቋንቋ ቢጻፍ ለገጽታ ግንባታ ያለውን አስተዋጽዖ እንጨምርበትና፤ ቱሪስቶችን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ያለውን አበረታችነት እናክልበትና በየወርክሾፑ በአበል ማቅረብ ነው፡፡
ኧረ ፈረንጅ እባክህ ና፡፡
መረጃ ፍለጋ በየገዳማቱ ብትዞር፣ በየመስጊዱ ብትኳትን፣ በየመሥሪያ ቤቱ ብትሄድ፣ መዛግብት ብታገላብጥ አንተን የሚጠረጥርህ የለ፡፡ የሚከለክልህም የለ፡፡ ፈረንጅ ነሃ፡፡ ፈረንጅኮ አይሰርቅም፡፡ የተዘጋ የገዳማት ዕቃ ቤት ላንተ ይከፈታል፤ ስብሰባ ላይ የሚውል ባለ ሥልጣን ላንተ ሲል ቢሮ ይገባል፤ የተከለከለ መረጃ ላንተ ይሰጣል፡፡ ባለ ሥልጣናቱ እንኳን ለሀገር ውስጥ ጋዜጠኛ ከሚናገሩ በፈረንጅ አፍ ለፈረንጅ ቢያወሩ ይመቻቸው የለ፡፡ የዕውቀት መለኪያ እኮ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊ ለሺ ዓመታት ሲወጣው የኖረውን ደብረ ዳሞ አንተ ስተወጣው በቴሌቭዥን ትቀርባለህ፡፡ በየንግሡ ስንሄድበት የኖርነውን ገርዓልታ አንተ ስትሆን ትደነቃለህ፡፡ ተወው ይኼማ ወግ ነው፡፡ ያልኖርክበትን፣ ያላደግክበትን መስቀልና ጥምቀት፣ አረፋና መውሊድ ጋዜጠኞቹ አንተን አይደል እንዴ የሚጠይቁት፡፡ ዜናውምኮ አንተ ነህ፡፡ ‹‹የመስቀልን በዓል ቱሪስቶች አደነቁ›› ነው ርእሰ ዜናው፡፡ እኛ ብናደንቅ ባናደንቅ ማን ከቁብ ይጥፈናል፡፡ በዓሉ የኛ - የምታብራራው አንተ፡፡
መስቀል አደባባይና ጃንሜዳ ውስጥ ገብቶ ፎቶ ለማንሣት እንኳን ፈረንጅ አንተ ትችላለህ፡፡ ፈረንጅ መሆንህ ከታየ ወይ የመግቢያ ካርድ ይሰጥሃል፤ ደግሞስ ማን ይከለክልሃል፡፡ ቱሪስት ነህና ፎቶ ታነሣለህ፡፡ አበሻን ማን ቱሪስት ያደርገዋል፡፡ ለመሆኑ አኩስምና ላሊበላ፣ ጎንደርና ጣና፣ አርባ ምንጭና ጀጎል የጎብኝ ቱሪስቶች ቁጥር በየዓመቱ ሲነገር ፈረንጅ ፈረንጁ ተመርጦ ነው ወይስ እኛንም ይጨምራል? እኛን ከጨመረ እንዴት ነው ቁጥሩ የሚያንሰው? ነው እኛ ከቁጥር የማንገባ ‹‹አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች›. ነን?
ካሜራው እንኳን ነፍስ ዐውቆ የመስቀሉን ደመራ፣ የጥምቀቱን ባሕር ትቶ አንተን አንተን ነው የሚያሳየን፡፡ እንኳን መስቀልና ጥምቀት ዘፈን ሲዘፈን እንኳን፣ ወይ የሚያጨበጭብ፣ ከተቻለም የሚወዛወዝ፣ ከተገኘም እስክስታ የሚመታ ፈረንጅ ከተገኘ ማን ይምረዋል፡፡ ስለ ሀገራችን ዘፈን ለማሳየት ፈረንጅ ሲዘፍን፣ ስለ ሀገራችን ምግብ ለማሳየት ፈረንጅ ሲበላ፤ ስለ ሀገራችን ሆቴሎች ለማስተዋወቅ ፈረንጅ ሲዝናና ማሳየት ሥልጣኔ ነው፡፡
እንኳንና አንተ ላንተ ቤት ያከራየው ሰውዬ እንኳን ኩራቱ፡፡ ‹‹እርሳቸውኮ ቤታቸውን ለፈረንጆች ነው ያከራዩት›› ይባልላቸዋል ዕድርና ልቅሶ ላይ፡፡ እርሳቸውም ሰው ሰላም ሲሉ በፈረንጅኛ ነው፡፡ ቤታቸውን ለፈረንጅ አከራይተዋላ፡፡ ድንኳን ውስጥም ቤትን ለፈረንጅ ማከራየት ያለውን ጥቅም በመዘርዘር ይታወቃሉ፡፡ ቤታቸውን ለፈረንጅ ስላከራዩም አንዳንድ እንግሊዝኛ ይሞክራሉ፡፡ ታዲያ ቤቱን ለአበሻ ካከራየው ሰው በምን ይለያሉ፡፡
አንተ ቁምጣ ብትለብስ፣ መሬት ብትቀመጥ፣ በነጠላ ጫማ ብትሄድ፣ መንገድ ላይ በቆሎ ገዝተህ ብትበላ፣ በአውቶቡስ ተሳፍረህ ብትሄድ፣ ልጆችህን ሽኮኮ አድርገህ ብትጓዝ፣ ተራ ሻሂ ቤት ገብትህ ዳቦ በሻሂ ብትገምጥ፣ አንተን ማን ገብጋባ ይልሃል፣ ማን ቋጣሪ ይልሃል፤ ማን ‹ምን ነካው› ይልሃል፡፡ ዕድር የለህ፣ ዕቁብ የለህ፣ ሰንበቴ የለህ፣ ማንንስ ትፈራለህ፡፡ እኛ የሆን እንደሁ ስንት ይጠብቀናል፡፡ አንተ ከሆንክ ግን ‹ፈረንጆችኮ ግድ የላቸውም፣ ቀለል ያለ ነገር ይወዳሉ፣ እነርሱ አይኮሩም፣ ጣጣም የላቸው፣ ይሉኝታ የላቸውም፣›› ይባልልሃል፤ ትደነቃለህ፡፡ ሀገርክን ያላየ ያመሰግንሃል፡፡
በምኒልክ አደባባይ አንጂ በፑሽኪን አደባባይ ማን ይከራከራል፡፡ በበላይ ዘለቀ መንገድ እንጂ በቼርችል ጎዳና ማን ይከራከራል፡፡
ፈረንጅ ሆይ ናና
ይኼው ቻይና እንኳን ፈረንጅ ሆና በየፊልሙ፣ በየክሊፑ እያየናት አይደል፡፡ ይኼው በመሬት ላይ መንገድ ልሥራ ብላ የመጣች ቻይና በሰማያችን ላይ ‹ሆስተስ› ሆነች አይደል፡፡ አይ ፈረንጅ መሆን ደጉ፡፡ እንኳን ‹ሆስተስነት› ‹ማናጅመንቱን ለውጭ ድርጅት መስጠት› በሚል ባለቤት አልባ ፍልስፍና በፈረንጅ መመራት የታላቅነት መለኪያ እየሆነ አይደል፡፡ ቀደምቶቻችን የኢትዮጵያ አየር መንገድን፣ ሲቪል አቪየሽንን፣ ፋብሪካና ኩባንያዎችን፣ ዩኒቨርሲቲና ኮሌጆችን፣ መከላከያና ሆቴሎችን ከፈረንጅ አመራር አውጥተው በሀገር ሊቆች እንዲመሩ ለማድረግ ስንት ነበር መከራ የተቀበሉት?
ሀገሪቱ ከልጅነት እስከ ዕውቀት፣ ከሽበት እስከ ኩተት ያሳደገቻቸው፤ ‹ይማርልኝ ብዬ በጌምድር ሰድጄ› እንደተባለው ውጭ ልካ ያስተማረቻቸው፣ በሥራ ልምድ ያበሰለቻቸው ልጆቿን፤ አስሳ፣ የማርያም መንገድ ሰጥታ፣ የጎደላቸውን ሞልታ ‹ያገሩን በሬ ባገሩ ሰርዶ‹ ማድረግ ትታ፣ በአድዋ በኩል ያሸነፍነው ፈረንጅ በአስተሳሰብ በኩል ገብቶ፣ ይኼው በዕውቀት አንሰው በንጣት ለሚበልጡ ሰዎች ‹‹ማናጅመንቱ ይሸጣል››፡፡
ፈረንጅ ሆይ ናና
ባንተ ያምራልና
ትሰማለህና
ትከብራለህና

ተዛማጅ ጽሁፎች


Image

Post Reply

Return to “Ethio Art and Culture..ኢትዮ ጥበብ ፤ስነ ጽሁፍ ፤”