እንባ - አጭር ልብ ወለድ

ግጥሞች፣ታሪኮች፣ፎቶዎች፣ሙዚቃዎች
Poems,Short stories, graphics,pictures,musics,Technology
selam sew
Leader
Leader
Posts: 604
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

እንባ - አጭር ልብ ወለድ

Unread post by selam sew » 26 Apr 2015 18:41

/በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የ15ኛ ዓመት የስነ-ፅሁፍ ውድድር 3ኛ የወጣው አጭር ልብ ወለድ/

እንባ
----

ማን እንደነገ ረኝ አላውቅም ወይም የት እንዳነበብኩት ትዝ አይለኝም፡፡ የሴት ልጅ ታላቁ ወዳጇ እና መደበቂያዋ እንባዋ ነው አሉ፡፡ ሁሏም ሴት አልቃሻ ላትሆን ትችላለች፤ እኔ ግን ነኝ፡፡ ለኔ እንባዬ ብዙ ነገሬ ነው፡፡ ጥቃቴን የተወጣሁበት፤ ሀሳቤን የከፈልኩበት፤ ጭንቀቴን ያቃለልኩበት እንባዬ ብቻ ነው፡፡
በህይወቴ የመጀመሪያ ምርር ያለ ለቅሶ ያለቀስኩት የአባቴ ቀብር ላይ ነበር፡፡ ሁለተኛውን መራር ለቅሶ ያለቀስኩት ደግሞ እዚያች ክፍል ውስጥ ነበር፡፡ ያ ክፍል ዛሬም ይታየኛል። ግርግዳው ውሃ ሰማያዊ ቀለም ተቀብቷል፡፡ በሩ ግራጫ ቀለም ያለው የብረት በር ነበር፡፡
ክፍሉ ውስጥ ሰፋ ያለ አልጋ አለ፡፡ አልጋው መሃል ላይ ኩርምት ብዬ ስቀመጥ በቀኜ በኩል አነስ ያለች ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠ ግራጫማ ቴፕ ሪከርደር አለ፡፡ ከጠረጴዛዋ ስር የተለያዩ መፅሄቶችና ጋዜጦች ይታዩኛል፡፡ በግራዬ በኩል ደግሞ ሁለት ተካፋች በር ያለው ቡናማ ቁምሳጥን አለ፡ ፡ ከቁምሳጥኑ ላይ አንድ ከፍ ያለ ሻንጣ አለ፡፡
ክፍሉ ውስጥ የማስታውሳቸው እቃዎች እነዚህ ናቸው፡፡ ተመራማሪዎች ከሰውነታችን ስልሳ ፐርሰንቱ ውሃ ነው ይላሉ፡፡ እርግጠኛ ነኝ ይሄ ነገር እውነት ነው፡፡ እንዲያ ባይሆን ኖሮማ እዚያች ክፍል ውስጥ ሊያውም ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ ያንን ሁሉ እንባ ከየት አምጥቼ አነባው ነበር፡፡
ጥር 10/1994 ዓ.ም ያስተዋወቀኝ ታላቁ ወዳጄ እንባዬ ነው፡፡ እንባዬ ጉንጬን ብቻ ሳይሆን ደሜን አጥቦልኛል፡፡ አቅም አልነበረኝም፡፡ ሲመቱኝ መልሼ የምመታበት፤ ሲያጠቁኝ የምመክትበት አቅም አልነበረኝም። ስለዚህ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ፡፡ ማንንም ሴት ጠይቁ። እንባ ስሜትን ያቃልላል፡፡ እንባ የታመቀ ቁጭትን ያረግባል፡፡
ከዚያች ቀን ጀምሮ እንባዬ አብሮኝ አለ፡፡ አሁንም ትዝ ሲለኝ አለቅሳለሁ፡፡
ዛሬ
-----

እኔ ሰናይት ሀይሉ ዛሬ ሃያ ዘጠኝ ዓመት ሞላኝ። ዛሬ የመጀመሪያ ዲግሪዬን በህንፃ ምህንድስና ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተቀብያለሁ፡፡ የማስተርስ ዲግሪዬን በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ከኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ አግኝቻለሁ፡፡ በግል የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ተቀጥሬ እሰራ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ከሁለት ጓደኞቼ ጋር የራሳችንን የኮንስትራክሽን ድርጅት ለመክፈት እየተሯሯጥን ነው፡፡ ስፖርት እወዳለሁ፡፡
ዛሬ በወርልድ ቴኳንዶ ቀይ ቀበቶ ይዣለሁ፡፡ የማንቼ ቀንደኛ ደጋፊ ነኝ። ደቪድ ቤካምን ከልቤ እወደው ነበር፡፡ እርሱን ለማየት የማንቼ ጨዋታዎችን መከታተል ጀመርኩ እና በዚያው ተለክፌ ቀረሁ፡፡ ዛሬ እናቴን የምጦረው ቤቱን የማስተዳድረው እኔ ነኝ፡፡
ዛሬም ግን ልቤ እዚያው ክፍል ነው፡፡ ትንፋሻቸው ይቀረናኛል፤ የላባቸው ጠረን ይሸተኛል፤ በኔ ስቃይ ያገኙት ወሲባዊ ደስታ ትዝ ይለኛል፡፡ ዛሬም በሶስት ጎረምሶች የተደፈረች የአስራ ስድስት ዓመት ልጅ ነኝ፡፡ አይኔን መጨፈን ብቻ ወደዚያ ክፍል መልሶ ያስገባኛል፡፡ ዛሬም እፈራለሁ፡፡ ዛሬም እበረግጋለሁ፡፡
ወንድ
-----

ለእኔ ወንድ በሁለት ይከፈላል፡፡
ከወገቡ በላይ እና ከወገቡ በታች፡፡ ከወገብ በላይ ማለት ልቡ፤ መንፈሱ እና ነፍሱ ያለበት ቦታ ነው፡፡ ከወገቡ በታች ደግሞ አውሬነቴ ያለበት ቦታ ማለት ነው፡፡ ያን ቀን ሶስቱም ከወገብ በላይ ሙታን ነበሩ፡፡

በህይወት ያለው የሚያስበው እና የሚንቀሳቀሰው ከወገባቸው በታች ያለው ማንነታቸው ነበር፡፡ ነፍሱ ከራሱ ጋር ያለ ሰው እንደዚያ አውሬ አይሆንም፡፡ እናት ያለው፣ እህት ያለው እንደዚያ አይጨክንም፡፡
ከዚያች ቀን በፊት ወንድን የማውቀው ከወገቡ በላይ ነበር፡፡ ለምሳሌ ኤልያስ ሳህሉ፡፡ ኤልያስ የልጅነት ጓደኛዬ ነው፡፡ አንድ ግቢ ነበር የምንኖረው።
እስከ አስራ አራት ዓመቴ ድረስ የማንነጣጠል ጓደኛሞች ነበርን፡ ፡ ያደግነው ጥቁር አንበሳ አካባቢ ወይም ሜትሮሎጂ አጠገብ ካለው የኪራይ ቤቶች አፓርትመንት ነበር፡ ፡ የነሱ ቤት ሁለተኛ ፎቅ ላይ፣ የኛ ቤት ደግ ሶስተኛ ፎቅ ላይ ነበር፡፡
ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት እየሄድኩ አንዳንዴ ከኤልያስ ጋር አብረን እናጠናለን፡፡ ከግቢው ልጆች ጋር ስንጫወት ከመቱኝ ወይም ካናደዱኝ ስለእኔ ይከራከርልኝ ይጣላልኝ ነበር፡፡ በጣም ልጆች ሆነን ደግሞ እቃ እቃ ስንጫወት እርሱ ባል፣ እኔ ደግሞ ሚስት እንሆን ነበር፡፡
የእቃ እቃ ሰርጋችን ላይ እጄን ይይዘኝና እንደሙሽራ ቀስ እያልን ስንራመድ፣ ሌሎቹ ልጆች ሙሽራዬ ይሉልን ነበር፡፡ የእሱ ቤተሰቦች ቤት ሰርተው ንፋስ ስልክ አካባቢ ገቡና ተረሳሳን፡፡ እኔ ወንድን ከዚያች ቀን በፊት ከወገቡ በላይ ነበር የማውቀው፡፡
ያን ቀን ግን የማላውቀውን የወንድ ማንነት እንዳውቅ ተገደድኩ፡፡ ወንድ ከወገቡ በታች አውሬ ነው፡፡ ለቅሶ የማያግደው፤ እንቢታ የማያቆመው፤ ጩኸት ግድ የማይሰጠው፤ ደም የማያራራው አውሬ!!!
አልጋ ልብስ
-----------

አልጋ ልብሱ ደማቅ አረንጓዴ ነበር፡፡ እዚያች ክፍል ውስጥ የደረሰብኝን ስቃይ የምናውቀው እኔ፤ ሶስት ወንዶች እና ያ አረንጓዴ አልጋ ልብስ ነን፡፡ ያ አረንጓዴ አልጋ ልብስ በደሜ ተጨማልቋል፡፡
ያ አረንጓዴ አልጋ ልብስ በሶስት ወንዶች የዘር ፍሬ ላብ ረጥቧል፡ ፡ ያ አረንጓዴ አልጋ ልብስ በእንባዬ ርሷል። እነዚያን አውሬዎች ብከሳቸው ኖሮ አንደኛ ምስክር አድርጌ የምጠራው ያንን ባለውለታዬን አረንጓዴ አልጋ ልብስ ነበር፡፡ በመደፈሩ መካከል ወይም አንዱ ደፋሪዬ ወጥቶ ሌላው እስኪተካ ድረስ ሰውነቴን እሸፍንበት ነበር፡፡ አለም በጨከነብኝ ጊዜ እርቃኔን ሸፍኜበታለሁ፡፡ መደፈሬን ለማንም አልተናገርኩም፡፡
እንዲህ አይነት ነገር ለማን ይወራል? ያን ቀን ተደብቄ ነበር እዚያ ፓርቲ ላይ የተገኘሁት፡፡ አድሬና አምሽቼ ስመጣ እናቴ በጣም ተቆጣችኝ፡፡ እያነከስኩ መምጣቴ እንዳይታወቅብኝ ተጠንቅቄ ወደ መኝታ ቤቴ ገብቼ ተኛሁ፡፡
ለሳምንት ያህል ሽንት ቤትመጠቀምና ሽንቴን መሽናት ለኔ ስቃይ ነበር፡፡ ለእናቴ አልነገርኳትም፡፡ የቤቱ ብቸኛ ልጅ ስለሆንኩ ሌላ የምነግረው ሰው አልነበረም፡፡ ለትምህርት ቤት ሴት ጓደኞቼ እንዲህ ሆንኩ ብዬ መናገሩ ደግሞ የድንጋይ ያህል ከበደኝ፡፡
ለመደፈሬ እራሴንም ጥፋተኛ አደርጋለሁ፡፡ እዚያ ፓርቲ መሄድ አልነበረብኝም፡፡ የሰጡኝንም መጠጥ መጠጣት አልነበረብኝም፡፡
ሙሽራ ቀሚስ
------------

ከልጅነቴ ጀምሮ ሙሽራ ቀሚስ በጣም ደስ ይለኛል፡ ፡ ስድስት አመቴ እያለ አክስቴ ለምለም ስታገባ ሻማ ያዥ ነበርኩ፡፡
ያኔ ታዲያ እሷ የለበሰችውን የሙሽራ ቀሚስ ውድድ አድርጌው ነበር፡፡ ንጣቱ፤ መንዠርገጉ፤ ሙሽሪትን ንግስት ማስመሰሉ ደስስስ ይላል፡፡
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስከ አስራ ስድስት አመቴ ድረስ የሰርግ ዘፈን ስሰማ ወይም ሙሽሮችን ሳይ እራሴን በሙሽሪት ቦታ አድርጌ በሰርጌ ቀን ስለማደርገው የሙሽራ ቀሚስ አልም ነበር፡፡ “ሽነት ነይ ነይ” የሚለውን የሰርግ ዘፈን በጣም እወደው ነበር፡፡ የሰርጌ ቀን በዚህ ዘፈን ከእናትና አባቴ ጋር እስክስ እንደምንል አስብ ነበር፡፡ ግን ምን ያደርጋል? በልጅነቴ አውሬ ሴትነቴን ቀማኝ፡፡
አባቴም በመኪና አደጋ ከመደፈሬ ሰባት ወር በፊት ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ የዛሬ ዓመት የቅርብ ጓደኛዬ ስታገባ አንደኛ ሚዜ ነበርኩ፡፡ ለሷ የኪራይ የሙሽራ ቀሚስ እየዞርን ስንፈልግ የሙሽራ ቀሚስ ፍቅሬ ተቀሰቀሰብኝ። አንዱ ቤት በጣም የምወደው አይነት የሙሽራ ቀሚስ አየሁ፡፡
ጓደኞቼን ካለካሁት ብዬ አስቸገርኩ። ከዚያን ቀን በፊት ወንድን በፍቅር እንደማላስጠጋ፤ የመውለድ እና የማግባት ምኞት እንደሌለኝ ስለሚያውቁ ሙሽራ ቀሚስ ልልበስ ማለቴ ተአምር ነው የሆነባቸው፡፡ ልብሱ ደግሞ የክፋቱ ክፋት ልክክ አለብኝ፡፡ ያንን ቀሚስ ለብሼ መስታወት ፊት ስቆም እንባዬን መቆጣጠር አቃተኝ፡፡
እዚያች ክፍል ውስጥ ወድቆ ለቀረው ሴትነቴ አለቀስኩ፡፡ እኛ ቤት “ሽነት ነይ ነይ… ሽነት ነይ ነይ …የሰንዬ እናት እልል በይ” እንደማይባል ሳስብ አለቀስኩ፡፡ ስም ሀበሻ ግን ምን ነክቶት ነው ስምን መላዕክ ያወጣዋል ብሎ የሚያስወራው? ሃሰት ነው!!! እዚያች ክፍል ውስጥ ነፍሴን ማወቅ ስጀምር ሄኖክ እላዬ ላይ ወጥቶ እራሱን እያመቻቸ ነበር።
መድኀኒት ቢጤ ሰጥተውኝ ስለነበር መጀመሪያ ምን እያደረገ እንደሆነ በደንብ አልገባኝም ነበር። ባለ በሌለ ሀይሉ ክብረ ንፅህናዬን ሲገስ ግን ያኔ በደንብ ነቃሁ፡፡ ሄኖክ የመፅሐፍ ቅዱስ ስም ነው፡ ፡
ሄኖክ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላሳመረ ወደ ሰማይ የተነጠቀ ፃድቅ ነው፡፡ ይሄኛው መላጣው ሄኖክ ደግሞ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ አራት ጊዜ በሃይል ደፍሮኝ በቁሜ ገሃነም አስገብቶኛል፡፡
ደግሞ እንዴት እንደሚስገበገብ? የተደፈርኩት የቤተሰቦቹ ቤት ውስጥ በተሰጠው ሰርቪስ ክፍል ውስጥ ነው። በእናት አባቴ ሱቅ ውስጥ አብሯቸው የሚሰራ የሃያ ሰባት አመት ጎረምሳ ነበር፡፡ ፓርቲውን ያዘጋጀው የሱ ታናሽ ወንድም ነበር፡፡
ሁለተኛ ደፋሪዬ ደግሞ ዳግምይባላል፡፡ የሰፈራችን ልጅ ነው፡፡ በደንብ አንግባባም ነበር፡፡ እርሱ ነው “ቆይና እኔ እሸኝሻለሁ” ብሎ ከጓደኞቼ ነጥሎ አስቀርቶ ለዚህ ስቃይ የዳረገኝ፡፡ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ሶስት ጊዜ ደፍሮኛል፡፡ ሙሉ ስሙ መሆን የነበረበት ዳግማዊ ሳጥናኤል ነበር፡፡ እሱ ግን ዳግም ፍሰሃ ይባላል፡፡ ድንቄም!!!
ሶስተኛው ደፋሪዬ የፓርቲው አዘጋጅ የሄኖክ ታናሽ ወንድም አድነው ነው፡፡ እዚያች ክፍል ውስጥ ከአርብ ከምሽቱ አራት ሰዓት ገብቼ ቅዳሜ ከምሽቱ አራት ሰዓት ስወጣ አንዴ ብቻ ነው የደፈረኝ፡፡ ሳይፀፅተው አይቀርም፡፡ ወደ ቤቴ ልሄድ ስል መፀዳጃ ቤት የወሰደኝ፤ ሰፈሬ ድረስ የሸኘኝ እርሱ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ደፍሮኛል፤ ከመደፈርም አላዳነኝም፡፡
ከዚህ ነገር የምትረዱት… ስምን ፈፅሞ መላክ አያወጣውም!!!

ፆታዊ ፍቅር
-----------
በደረሰብኝ ጥቃት ምክንያት ወንድን እንደ ስራ ባልደረባ ወይም እንደ ወንድም ወይም እንደ ንፁህ ጓደኛ ካልሆነ እንደ ፍቅረኛ አላቀርብም፤ አልመኝም።

ሁሉም ወንድ አንድ እንዳልሆነ ባውቅም ወንድን ማቅረብ አቃተኝ፡፡ እህ ብዬ ባላደምጣቸውም “ወደድኩሽ” ያሉኝ ወንዶች ገጥመውኛል፡፡ አላመንኳቸውም!!!
ባለፈው ዓመት ግን የማላልፈው ነገር ገጠመኝ፡ ፡ ኤልያስን ከአስራ ሶስት ዓመት በኋላ ቢሮዬ ለጉዳይ መጥቶ አገኘሁት፡፡ ገና ሳየው ልቤ ድንግጥ አለ፡ ፡ እርሱም ደስ ብሎት ሰላም አለኝ፤ ሳመኝ፡፡ ሻይ፤ ቡና፤ ማኪያቶ፤ ምሳ፤ እራት ተገባበዝን፡፡
አንድ ቀን እንዲህ አለኝ፤
“ሰሞኑን ምን እንደሆነ አላውቅም፤ ወንድ እንደምትፈሪ ገብቶኛል፡፡ የደረሰብሽ ነገር እንዳለ ያስታውቃል፡፡ ግን እኔ ወድጄሻለሁ፡፡ የልጅነቴ ነሽ፤ በፍቅር አብረሽኝ ብትሆኚ ደስ ይለኛል፡፡”
በፍፁም ትህትና እንደማልፈልገው ነገርኩት፡፡ ወንድም እና እህት እንደሆንን አስረዳሁት፡፡ ሰማያዊ ግርግዳ ያለበት ክፍል አብረን ብንገባ እና ግራጫውን በር ብንዘጋ አውሬ እንደሚሆንብኝ አውቃለሁ፡፡ ግን ለምንድን ነው አብሬው ስሆን ደስ የሚለኝ? ምን ልሁን ብሎ ነው የምወዳቸውን ዘፈኖች የሚዘፍነው? ለምንድን ነው እንዲያቅፈኝ የምፈልገው? ላብድ ነው እንዴ? እርሱም እኮ ወንድ ነው!!! ግን እርሱ ለምን አይርቀኝም? ሲደውል ካላነሳሁ ይመጣል፡፡
ፊት ስነሳው ስጦታ ገዝቶ ይመጣል። ደግሞ አንዳንዴ ይጠፋብኛል፡፡ ከዚያ ፈልጌ አገኘዋለሁ፡፡ ያኔ ደግሞ እርሱ ደስ ይለዋል። ምን አደርግለታለሁ ግን? እኔ ሙሉ ሴት አይደለሁም። የሆነ የጎደለኝ ነገር አለ፡፡ እነ ሄኖክ ያበላሹት። አረንጓዴ አልጋ ልብስ ላይ ተቆርጦ የቀረ።
ከዚያ ክፍል ማነው የሚያወጣኝ? ማነው በሩን የሚከፍትልኝ?
ቅዠት
-------
በሳምንት ሁለት ሶስቴ ቅዠት ያስቸግረኛል። የሚቀረና የወንድ ትንፋሽ፤ ግራጫ የብረት በር፤ ስግብግብ የወንድ እጆች፤ የሶስት ወንድ ጠረን፤ ሰማያዊ ግርግዳ፤ ስደፈር እቆጥረው የነበረው ጣራ፤ የማይነጋ ሌሊት፤ ከብልቴ የወጣ ደም፤ አረንጓዴ አልጋ ልብስ፤ እንባ፤ ፍራቻ… በቅዠቴ ውስጥ አሉ።

አንዴ ከቃዠሁ ተመልሼ መተኛት አልችልም፡፡ ሲቆይ ሲቆይ ጋብ ብሎልኝ እንጂ መጀመሪያ ሰሞንማ በእንቅልፍ እጦት አስራ አንደኛ ክፍልን ደግሜያለሁ። አሁን አሁን ቅዠቴ መልኩን ቀይሯል፡፡
ኤልያስ መጥቶ ከአልጋው ላይ ሲያነሳኝ፤ ከሶስቱ ጋር ስለእኔ ሲደባደብ፤ ተዋት ብሎ ለእኔ ሲከራከር ወይም ከደፋሪዎቼ ሊያድነኝ ሲሞክር ይታየኛል፡፡ ላብድ ነው እንዴ?
አባ ማርቆሬዎስ
--------------
የኤልያስ ፍቅር እያየለብኝ መጣ፡፡ ግን ደግሞ ፍቅረኛው መሆንም አቃተኝ፡፡

የንስሃ አባቴ ጋ ሄድኩና ለማንም ያልነገርኩትን ታሪኬን ነገርኳቸው። በሩን ከፍተው ከዚያች ክፍል እንዲያወጡኝ ለመንኳቸው፡ ብስራተ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አፀዱ ውስጥ ተቀምጠን ተናዘዝኩላቸው፡፡ እህ ብሎ የሚያደምጥ ከተገኘ መናገር ደስ ይላል ለካ፡፡
“ወለተ ማርያም፤ መፍትሄው እኮ በእጅሽ ነው፡ እርግጥ የደረሰብሽ ነገር አሰቃቂ እንደሆነ ይገባኛል፡
እግዚያብሔር ይመስገን ላልተፈለገ እርግዝና ወይም በሽታ አለመጋለጥሽ ደስ ይላል፡፡ ግን አሁን ጊዜው ነው፡”

“ለምኑ?”
አልኳቸው ግራ እንደተጋባሁ፡፡
“ይቅር ለማለት” አሉኝና እርፍ፡፡
“እኮ ደፋሪዎቼን ይቅር ልበል?”
“አዎ ልጄ፡፡ ይቅር ለእግዚአብሔር በያቸውና በሩን ከፍተሽ ውጪ፡፡ የበሩ እጀታ ከውስጥ ነው፡፡ ይቅር የምትይው ለራስሽ ነው፡፡ ከዚህ በሁዋላ የበደሉሽን በደል ይዘሽ ላለመዞር ይቅር ለእግዚአብሔር በያቸው፡ ፡ ዘመንሽን ሙሉ እዚያች ክፍል ተዘግቶብሽ ላለመኖር ስትይ ይቅር በያቸው፡፡

“እንዴ አባ …” አልኩ ግራ ገብቶኝ፡፡ “ይቅር ማለት ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን እርሱ ይቅር እንዳለን የበደሉንን ይቅር ማለት አለብን፡፡ እስከመቼ የነሱን ሀጥያት ይዘሽ ትዞሪያለሽ? እስከመቼ በነሱ ሀጥያት እራስሽን ትቀጫለሽ?” ወደ መቅደሱ ሮጥኩና ተንበረከኩ፡፡ ስነሳ ኤልያስ ትዝ አለኝ፡፡ ደወልኩለት፡፡ ፊልም አብረን ልንገባ ተስማማን።

© ሐወኒ ደበበ

Image

Post Reply

Return to “Ethio Art and Culture..ኢትዮ ጥበብ ፤ስነ ጽሁፍ ፤”