የእምዬ ምኒልክ እትብት እና አንጎለላ

ግጥሞች፣ታሪኮች፣ፎቶዎች፣ሙዚቃዎች
Poems,Short stories, graphics,pictures,musics,Technology
selam sew
Leader
Leader
Posts: 558
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

የእምዬ ምኒልክ እትብት እና አንጎለላ

Unread post by selam sew » 27 Feb 2015 10:38

የምኒልክ እትብትና አንጎለላ

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሔኖክ ስዩም በቅርቡ ካሳተመው “የመንገድ በረከቶች” ከተሰኘው መጽሐፉ ይህን ማራኪ ክፍል እንጋብዛችሁ…)

Image

ከተነሳሁባት ደብረ ብርሐን ከተማ ምዕራባዊ አቅጣጫ 11 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እገኛለሁ፡፡ ስንሄድ በስተግራ አንዲት ሐውልት የቆመባት ጤና ኬላ የምትመስል ውብ ጊቢ ውስጥ፤ ወደ ግቢው ገባሁ፤ አንዲት የቀይ ቆንጆ መጣች፡፡ ዞን ባህል ቱሪዝም ነግረዋት እየጠበቀቺኝ ነው፡፡

“ሰላም”
“እንዴት ነሽ….እዚህ ነው የሚኒሊክ ትውልድ ቦታ?”
“ዞኖች የነገሩኝ ጋዜጠኛ ነህ?”
“አዎ!” አልኳት፤ መልሳ እሷም
“አዎ” አለች፡፡
ግራ ገባኝ፡፡
“አዎ ያልሺኝ ምኑን ነው አልኩ መልሼ”
“የአጼ ሚኒሊክ የትውልድ ስፍራ”

ቆጣ ትላለች፡፡ የሀገሬው ሰው ጠባይ ከሆነ ብዬ ብዙ አላወራሁም፡፡ የለበሰችው ቀሚስ ነው፡፡ የነተበች ሲናርላየን ደብተር ይዛለች፡፡ ክዳን የሌለው ስክሪቢቶዋን ወደ አፏ እያስጠጋች፡፡ የምሰራውን ስትታዘብ ቆየች፡፡

“ና ወደዚህ” ከፊቴ ቀደመች፡፡ ተከተልኳት፡፡

በሳር የተሸፈነ ፍራሽ የድጋይ ካብ አለ፡፡ ይህ ስፍራ እምዬ እየተባሉ የተወደሱት ዳግማዊ ሚኒሊክ ከእናታቸው ማህጸን የወጡበት ነው፡፡ አንድ ንጉስ የተወለዱባት የማትመስለው ባድማ በአፍሪካውያን የዘላለም ታሪክ ህያው ስምን የተጎናጸፍ ጥቁር መሪ እትብት የተቀበረባት ስፍራ ናት፡፡

ከንፈር መምጠጥ ብቻ………

ከሚኒልክ የትውልድ ቤት ወጣን፡፡ ከአንድ ኪሎ ሜትር ያልበለጠ መጓዝ አለብን… ልጅ ሚኒልክ ከአጼ ልብነ ድንግል ልጅ ከአጼ ያዕቆብ ትውልድ 13ኛ የዘር ሀረግ ላይ ከሚቆጠሩት የሸዋው ንጉስ ሣህለ ስላሴ የተገኙ የልጅ ልጅ ናቸው፡፡ አባታቸው ኃይለመለኮት ይባላሉ፡፡

የሚኒሊክ እናት ወ/ሮ እጅጋየሁ የነሐሴ ሚካኤል በፍልሰታው የወለዱት ልጃቸውን በተወለደ በአርባ ቀኑ የባለቤታቸው አባት ንጉስ ሣህለስላሴ ወደ አሰሩት የአንጎለላ ኪዳነ ምህረት በመውሰድ ክርስትና አስነሷቸው፡፡

እየተጓዝን ያለንው ወደ አንጎለላ ኪዳነ ምህረት ነው፡፡ ይህቺ ትንሽዬ ቀበሌ የዛሬን አያድርገውና በ1828 ዓ.ም ስትመሰረት የሸዋ ሁለተኛዋ ከተማ ነበረች፡፡ በትንሷ መንደር የቆመችው የአንጎለላ ኪዳነምህረትም እነ አጼ ሚኒልክ ክርስትና የተነሱባት ደብር ናት፡፡ ደብሯን በሚገባ ጎበኘኋት፡፡
አንጎለላ ኪዳነ ምህረት ከአድዋ ጋር የሆነ ቁርኝት አላት፡፡

እንደ ብዙ ቤተ ክርስቲያኖች የውስጧ ግድግዳ በመላእክትና ሰማዕታት ስዕል ብቻ አላሸበረቀም፡፡ የአድዋ ጦርነትን ምስል የሚያሳዩ አያሌ ስዕሎች ተሰቅለውባታል፡፡ አድዋ ለድፍን ምዕተ ዓመት ሲነሳ አንጎለላ ብሎ ነገር ይህ ትውልድ ሰምቶ አያውቅም፡፡

አስጎብኚዬ በቅጡ ወደ አልተደራጀው ሙዚየም ወሰደቺኝ፡፡

አንዲት ደሳሳ ቤት፡፡ በጣም ያረጁ ሸበቶ ሽማግሌ፡፡ በእርግጥ እዚህች ቤት ውስጥ ያለውን ቅርስ ሀገሬው እንደ ዓይኑ ብሌን ይጠብቀዋል፡፡ የቅርስ ንብረት ክፍሉ ግን በአባ ጴጥሮስ ካሳዬ ስር ነው፡፡ ቆሞስ ናቸው፡፡ ለመጣው እንግዳ ከፍተው በማያሳዩት ክፍል በር ላይ ሆነው የሚፈልጉትን ጠየቁን፡፡ ልጅቷ የባህልና ቱሪዝም ሰው ብትሆንም እኚህ ሰው ግን በቀላሉ ወደ ውስጥ እንድንዘልቅ አላደረጉም፡፡ ከብዙ ውይይት በኋላ ወደ ውስጥ ገቡ፡፡ ተከተልናቸው፡፡

የተወሰነ ነገር ብቻ እንደሚያሳዩን ገለጹልን፡፡ ከመስማማት ውጪ ምርጫ አልነበረንም፡፡ በተለይ እኔ፤ የንጉስ ሚኒልክ ዘውድ ክርስትና ለተነሱባት ደብር ተበርክቶ ተቀምጧል፡፡ አያሌ ጽንሐ፣ ጽናጽል፣ እና ንዋያተ ቅድሳት ከሳህለ ስላሴ እስከ ሚኒልክ ለአንጎለላ ኪዳነ ምህረት የተበረከቱ ስጦታዎች ይገኙበታል፡፡

ወደ አንድ ጥግ የተቀመጠ አስደናቂ ነገር ተመለከትኩ፡፡ ሳልጠይቃቸው ምን መሆኑን ይገልጹልኝ ጀመር፡፡

“ይሄ የፊታውራሪ ገበየሁ አጽም ነው፡፡”
ደነገጥኩ፡፡ አድዋ በጦርነት ስትታመስ እኒያን ሰልጥነናል ያሉትን የጣሊያን ወታደሮች ያርበደበዱ ኢትዮጵያውያን ጄነራሎች ብዙ ነበሩ….
"ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ " የተባለላቸው

ፊታውራሪ ገበየሁ አይረሴ የአድዋ ጌጥና የጥቁር ህዝቦች ሰማዕት ናቸው፡፡ ገና አድዋ ሲዘምቱ ተናዘዙ….ስሸሽ ከተመታሁ አሞራ ይብላኝ እኔ እንደአባቶቼ አይደሉሁምና ወግ አይገባኝም፤ ከፊት ከተመታሁ፤ ስፋለም ከወደቅሁ፤ ሬሣዬን ሀገሬ ውሰዱልኝ አሉ፡፡ እንደተባለውም ሆነ፤ በጽኑ ሲፋለሙ ስለ ሀገራቸው ነጻነት አድዋ ላይ ወደቁ፤ እንደ ቃላቸውም አስክሬናቸው ሀገራቸው ገባ፡፡ አሁን ከፊቱ የቆምከት የአድዋው የጦር ሳይንቲስት አጽም ነው፡፡ ምቹ ባልሆነ ሁኔታ አንጎለላ ኪዳነ ምህረት ተቀምጦ ለጎብኚ ይታያል፡፡

ከዚህ በኋላ መነኩሴው የሚያወሩትን መስማት አልቻልኩም፡፡ ወርቅና ብር ከተባሉ ቅርሶች ይልቅ ገበየሁን የመሰለ ጀግና በስሙ እንኳን ሙዚየም መስራት አቅቶን አጽሙ በሳጥን በአንዲት ደሳሳ ቤት ተጋደመ…..፤ ስለሚወዳት ሀገሩ የተሰዋው ጀግና ወትሮም ይህ አይገደው…..፤ ይብላኝ ለኛ…..፤ ቀጣዩ ጉብኝት አላጓጓኝ አለ፡፡ ውስጤን ከፋው፡፡ እንዲያ መነኩሴው ሲለመኑ የነበረው እንዲህ ቅስም የሚሰብር ነገር ላይ ነበር፡፡ ለነገሩ ይህንንስ ቢሆን ማድረግ የቻለችው አንጎለላ ኪዳነ ምህረት አይደለች፡፡

ከቤተ ክርስቲያኗ ቅጥር ወጣን…


Image

አንጎለላ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን::

Image

Post Reply

Return to “Ethio Art and Culture..ኢትዮ ጥበብ ፤ስነ ጽሁፍ ፤”