ላ’ንዲት የገጠር ሴት (በውቀቱ ሥዩም)

ግጥሞች፣ታሪኮች፣ፎቶዎች፣ሙዚቃዎች
Poems,Short stories, graphics,pictures,musics,Technology
selam sew
Leader
Leader
Posts: 558
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

ላ’ንዲት የገጠር ሴት (በውቀቱ ሥዩም)

Unread post by selam sew » 26 Feb 2015 14:13

ላ’ንዲት የገጠር ሴት (በውቀቱ ሥዩም)

[left]ስትፈጭ የኖረች ሴት፣
መጁ በመጠኗ፣ ወፍጮውም በልኳ ፣
ጓያ ትፈጫለች
ጓያ ሽሮ ሲሆን ያበቃል ታሪኳ።
አስባው አታውቅም..
ወደ ኦናው ምድር ለምን እንደመጣች፣
ከ’ለታት አንድ ቀን፣ከና’ቷ ሆድ ወጣች፣
ከ’ለታት አንድ ቀን፣ ጡት አጎጠጎጠች፣
ከ’ለታት አንድ ቀን፣ ለባሏ ተሰጠች።
ተዚያን ቀን ጀምራ፣
ተዚያን ቀን ጀምሮ፣
ድንግል ድንጋይ ወቅራ፣
ትፈጫለች ሽሮ።

አታውቅም፣
ማን እንደሚባሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣
አታውቅም፣
ሹማምንት በ’ሷ ስም፣ ምን እንደሚሠሩ፣
አነሳኹት ‘ንጂ፣ እኔም ለነገሩ፣
በፖለቲካ ጥበብ ራስን ማራቀቅ፣
ምን ይጠቅማትና ጓያዋን ለማድቀቅ።
ከቶ ማንም የለ, አበባ ‘ሚሰጣት፣
ከቶ ማንም የለ፣ ከተማ ‘ሚያወጣት፣
ከቶ ማንም የለ ፣ በዳንኪራ መላ፣ ወገቧን የሚያቅፋት፣
ልፋቷም፣ዕረፍቷም፣
ወደዚህ መጅ መሳብ
ወደዚያ መጅ መግፋት።
እንደ ዓባይ ፏፏቴ ፣ ሽሕ ዓመት ቢንጣለል፣
ቢጎርፍም ዱቄቱ፣
እንደ ሲኦል ወለል፣ ጫፍ የለውም ቋቱ።
ከዘመናት ባንዱ
መስተዋት ፊት ቆማ፣በተወለወለው፣
ፊቷን ለማዬት፣
ከጸጉራ ላይ ያለው
ዱቄት ይኹን ሽበት. ሲያቅታት መለዬት፣
ያኔ ይገባታል የተሰጣት ዕጣ፣
ከማድቀቅ ቀጥሎ፣መድቀቅ እንዲመጣ።
የመጅ አጋፋፏ-አምሳለ ሲሲፈስ፣
ከቋት ሥስት እንጅ፣ ሢሳይ አይታፈስ፣
ትቢያ ‘ሚተነብይ ዱቄት በዙሪያዋ፣
ከባርኔጣ አይሰፋም፣ የኑሮ ጣሪያዋ፣
‹‹ስትፈጭ የኖረች ሴት ›› ይህ ነው መጠሪያዋ።

Image
[/left]

Post Reply

Return to “Ethio Art and Culture..ኢትዮ ጥበብ ፤ስነ ጽሁፍ ፤”