ስኮትላንድ ከታላቋ ብሪታኒያ ጋር የመሠረተችውን ትዳር ማደሷን አወጀች – ከበእውቀቱ ስዩም

ግጥሞች፣ታሪኮች፣ፎቶዎች፣ሙዚቃዎች
Poems,Short stories, graphics,pictures,musics,Technology
selam sew
Leader
Leader
Posts: 558
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

ስኮትላንድ ከታላቋ ብሪታኒያ ጋር የመሠረተችውን ትዳር ማደሷን አወጀች – ከበእውቀቱ ስዩም

Unread post by selam sew » 22 Sep 2014 01:13

ጀርመን ገብተን፣በራሂን ወንዝ ዋኝተን፣ ኔዘርላንድ ገብተን፣ በአምስተል ወንዝ ግብርውሀ ወጥተን፣ ኦስሎ ገብተን፣ በኖቬል ሽልማት-ቤት ፊትለፊት ፎቶ ተነሥተን፣የሁለት ሰንበት ዙረታችንን አጠናቅቀን ለሚወደንና ለምንወደው ህዝባችን ጥቅም ስንል ወደ ሸገር ተመልሰናል፡፡ በተመልስንበትም ቀን ስኮትላንድ ከታላቋ ብሪታኒያ ጋር የመሠረተችውን ትዳር ማደሷን አወጀች፡፡


ፍቅር ያሸንፋል ይሉሀል ይህ ነው፡፡
እስቲ በስማም ብየ፣ ዝናሽን ልናገር
የቀሚስ ለባሾች፣ የነዋላስ አገር

አንዳንዴ ሳስበው፣እናንተ የዓለም ጨው ናችሁ የሚለው የመሲሕ ቃል የተፈጸመው በስኮቶች ይመስለኛል፡፡አሁን የምንኖርበትን ዘበናይ ዓለም በራሳቸው አምሳል ጠፍጥፈው የፈጠሩት… ስኮቶች ናቸው፡፡ምነው ወዳጄ ለሙገሳም ለከት አለው፣ ትንሽ አላጋነንከውም የሚለኝ ሰው ካለ
የሰው ልጅን ህይወት ታምራዊ በሆነ መንገድ የቀየሩ ብዙ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግኝቶች የስኮት አእምሮ ውጤት ናቸው፡፡

አንች ወዲህ ማዶ፣
እኔ ወዲህ ማዶ
አንገናኝም ወይ ተራራው ተንዶ

የሚል የጨነቀው የድሮ አፍቃሪ የዘፈነው ዘፈን ትዝ ይላችኋል?፡፡ተራራው ሳይናድ ፣ወድያ ማዶ የምትኖር ቆንጆ ወዲህ ማዶ ካለው ወዳጅዋ ጋር እንድትገናኝ ያደረገው የስልክ ፈጣሪ እስክንድር ቤል ስኮቴ ነው፡፡እነ ቲቪ፣እነ የእንፋሎት መርከብ እነ ብስክሌት፣እነ መኪና ጎማ-ከብዙ በጥቂቱ የስኮት አእምሮ ውጤቶች ናቸው፡፡

የዘመናዊ ፍልስፍና ፈጣሪ ዳዊት ሂውም፣የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ሊቅ አዳም ስሚዝም እዚያው ናቸው፡፡

ስኮቶች በኢትዮጵያ ላይም አሻራቸውን ትተዋል፡፡

የአባይን መፍለቂያ ለመጀመርያ ጊዜ ያገኘው አንድ ስሙ ያልታወቀ፣የወይጦ አሣ አጥማጅ መሆን አለበት፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ያሠሠው ግን የስኮትላንዱ ተወላጅ ያቆብ (James)ብሩስ ነው፡፡በዘመነ መሳፍነት ዋዜማ ላይ ኢትዮጵያ ይልቁንም ጎንደር ምን እንደምትመስል የምናውቀው፣ጀምስ ብሩስ በጻፈልን፣ባለ አምስት ጥራዝ ማስታወሻ ነው፡፡

ባገራችን ባህላዊ ፍልስፍና ሱሪ የጀግንነት መለኪያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡‹‹እገሌን ብፈራው ሱሪ አልታጠቅሁማ›› ይላሉ አባቶቻችን ሲፎክሩ፡፡እድሜ ለስኮቶች፣ቀሚስ የጀግነነት ምልክት ሆነ፡፡
ስኮቶች፣የበደልና የጭቆና ታሪክ ማሳለፋቸውን ይናገራሉ፡፡ተነጥለው ጎጆ የመቀለስ አቅሙም ነበራቸው፡፡ግን በመከባበር ላይ የተመሰረት አንድነት መምረጣቸው ጀግንነት ነው እላለሁ፡፡ አርአያቸውን በልቦናችን ያሳድረው ከማለት በቀር ምን ይባላል?


Image
Scotland and United Kingdom

Post Reply

Return to “Ethio Art and Culture..ኢትዮ ጥበብ ፤ስነ ጽሁፍ ፤”