ሚስቴን አከሸፏት (እየተራበች ነው ) ከአሌክስ አብርሃም

ግጥሞች፣ታሪኮች፣ፎቶዎች፣ሙዚቃዎች
Poems,Short stories, graphics,pictures,musics,Technology
Post Reply
User avatar
zeru
Leader
Leader
Posts: 952
Joined: 19 Aug 2009 17:01
Contact:

ሚስቴን አከሸፏት (እየተራበች ነው ) ከአሌክስ አብርሃም

Unread post by zeru » 19 Sep 2014 16:58

ሚስቴን አከሸፏት (እየተራበች ነው )

ከአሌክስ አብርሃም


‹‹አብርሃም ››
‹‹አቤት ››
.‹‹እ…..ና ለዚች ተልካሻ ምክንያት ብለህ ሚስትህን ልትፈታት ነው ? ›› ስትል ዳኛዋ ጠየችኝ ! እዩዋቸው እንግዲህ ክብርት ዳኛ ቋጥኝ ሴትነታቸው ተንዶ ዳኝነታቸውን ሲጫንባቸው ! እስኪ አሁን ችሎት ላይ የቀረበን የአመልካችን ብሶት ‹‹ ተልካሻ›› ብሎ ማጣጣል ተገቢ ነው ? አይ መብቴማ ሊከበር ይገባል ! እንዴ አንዱ ልማደኛ ሌባ ባለፈው ለሰባተኛ ጊዜ ስልክ ነጥቆ ሊያመልጥ ስል ተይዞ ፍርድ ቤት ቀረበ … ታዲያ ዳኛው በብስጭት
‹‹ አንተ ልክስክስ ዛሬም እንደገና ሰርቀህ መጣህ ?›› ቢሉት ሌባው ኮስተር ብሎ
‹‹ ክቡር ዳኛ …. እንዲህማ አይዘልፉኝ ..ደንበኛ ክቡር ነው ›› አለ አሉ ! እውነቱን ነው ‹‹ደንበኛ ›› መከበር አለበት …የግድ ጉዳየ እንዲካበድ ሚስቴን ከሌላ ወንድ ጋር ማግኘት አልያም በገጀራ ጨፍጭፊያት ፍርድ ቤት መቆም ነበረብኝ እንዴ ….ለምን ምክንያታችንን ያናንቃሉ … የማንን ምክንያት ማን በትከሻው ተሸክሞ መዝኖታል ….
ደግሞ ስንት ጊዜ ነው ለዚች ዳኛ ስለጉዳዩ የምነግራት ? ከዚህ በፊትም ደጋግማ ጠይቃኝ ደጋግሜ መልሻለሁ !
‹‹ አይ ምክንያቱ ለእኔ ከበቂ በላይ ነው ክብርት ዳኛ ›› ስል በትህትና ‹‹ተልካሻ›› ብላ ያናናቀችውን ምክንያት ሚስቴን ለመፍታት በቂ መሆኑን አረጋገጥኩላት ! (ክብርት የሚለው ቃል ከብረት የተሰራ ይመስል አፌ ላይ ከበደኝ )
‹‹ እኮ ሚስቴ ካለፍቃዴ ፀጉሯን ተቆረጠች ብለህ የፍች ጥያቄ ይዘህ ፍርድ ቤት መጣህ ? ›› አለች ዳኛዋ አሁንም ተገርማ ….
‹‹ አዎ ›› ስል ኮስተር ብየ መለስኩ ! ዳኛዋም ዝም ችሎቱም ዝም ! ሁሉም ሰው እንደእብድ እየተመለከተኝ ነበረ ! ዳኛዋ እንደዳኛ ሳይሆን እንደሴት መናገር ጀመረች …ስልችት ያለኝን ዝባዝንኬ የሞራል ወግ ….
‹‹ ስማ አብርሃም ! ባለቤትህ እኮ ህፃን ልጅ አይደለችም… የሚጠቅምና የሚጎዳትን ነገር በሚገባ ራሷ ታውቃለች… ስትቆም ስትቀመጥ አንተን ማስፈቀድ የለባትም … ምንም እንኳን ባሏ ብትሆንም ያገባሃት በባርነት ልትገዛት እና የአንተን ብቻ ፍላጎት ልትጭንባት አይደለም ….ይህ ዘመናዊ አስተሳሰብም አይደለም ….አንተ ወጣት ነህ የተማርክ የከተማ ልጅ ነህ …. በመቻቻልና በመተሳሰብ እንዲሁም አንድኛችሁ የአንድኛችሁን ፍላጎት በመረዳት ትዳራችሁን አክብራችሁ ….›› በ ለ ው …..አንተረተረችው !
አሁን ክብርት ዳኛ የተናገሩት ነገር እንዲሁ ከላይ ሲታይ ትክክል ይመስላል ……ግን ይሄ ሁሉ ዝባዝንኬ በፍታብሔርም በወንጀለኛም በቤተሰብ ህግም ላይ ያለ አይመስለኝም ….ችሎት ውስጥ ሳይሆን የእኛ ሰፈር የሴቶች እድር ውስጥ የቆምኩ መሰለኝ ! ለነገሩ ዳኛዋ ሴት በመሆኗ ሲጀመርም ፈርቸ ነበር ….በኋላ ሳስበው ሙያ መቸስ ፆታ የለውም ….ሴት ዳኛ እንጅ ሴት ዳኝነት የለም …ሴት ሃኪም እንጅ ሴት ህክምና የለም …ቢሆንም ፆታው ሙያው ላይ የሚያሳርፈው ያራሱ ተፅእኖ ይኖራል ልክ እንደዚች ዳኛ ! ደግሞ ‹‹ሚስትህ ህፃን አይደለችም ትላለች እንዴ ›› ምነው ችሎቱን የህፃን ችሎት አደረገችው ! ‹‹ ሴት በዛ ጎመን ጠነዛ ›› ብየ ተረትኩ ! እንኳንም ተረትኩ …ችሎቱን የሞሉት ሴቶች ናቸው …..ሚስቴን ጨምሮ (ሚስቴ ስል እንዴት እንደሚቀፈኝ )
እስቲ አሁን ‹‹ ባለቤትህ እኮ ህፃን ልጅ አይደለችም የሚጠቅምና የሚጎዳትን ነገር በሚገባ ራሷ ታውቃለች…›› ማለት ይሄ ምን የሚሉት ከንቱ ንግግር ነው …አንዲት ሴት ለራሷ ይጠቅመኛል ያለችውን ማወቅ በቃ ሙሉነት ይመስላቸዋል … ትዳር ውስጥ ‹‹ለራሴ ›› የሚጠቅመኝን እኔ አውቃለሁ ማለት የትዳር አጋርን ፍላጎት ካላገናዘበ ምኑን ትዳር ሆነው ?! ‹‹ህፃን ልጅ አይደለሁም የሚጠቅመኝን እኔ አውቃለሁ›› ብየ የፈለኩበት ባድር ሚስቴ ደስ ይላታል ? ‹‹…የሚጠቅመኝን እኔ አውቃለሁ ›› ብየ ፀጉሬን ሳላበጥር ጥርሴን ሳልቦርሽ ብወጣ ሚስቴ ዝም ትላለች ? …… የሚጠቅመኝን እኔ አውቃለሁ ብየ የጨርቅ ሱሪየን እንደጌሾ ካልሲየ ውስጥ ጠቅጥቄው ብወጣ ሚስቴ ዝም ትላለች …. በተራና እሽኮለሌ የሞራል ጩኸት …. ፍቅር ፀንቶ የሚቆም ሊያስመስሉ ሲቀባጥሩ ይገርሙኛል …. ይሄ እኮ ሁሉም ሴቶች ከሰውነት መንበር የተገፈተሩ ሲመስላቸው ጨምድደው እንዳይወድቁ የሚንጠለጠሉበት የተረት ገመድ ነው !
‹‹ ክብርት ዳኛ ያሉት ነገር ከእኔ ጉዳይ ጋር አይገናኝም …. እኔ ሚስቴ ፀጉሯን በአጭር ስለተቆረጠች ህፃን ናት አልወጣኝም ! እኔ ፀጉሯን በመቆረጧ መፋታት እፈልጋለሁ እርሷ ጋር መኖር አልፈልግም ነው እያልኩ ያለሁት…. ደግሞ ቀድሜ ፀጉሯን እንዳትቆረጥ ነግሪያት ነበር የራሷን ምርጫ ተከትላለች እኔም የራሴን ምርጫ እከተላለሁ … ስለዚህ ክቡር ፍርድ ቤቱ ጥያቄን በመቀበል ፍችውን እንዲያፀድቅልኝ በማክበር እጠይቃለሁ ! ›› አልኩ …
‹‹ለመሆኑ ስትፋቱ ያላችሁን ንብረት እኩል እንደምትካፈሉ ገብቶሃል ? ››
‹‹ኧረ በሙሉ ትውሰድ ….ብቻ እንፋታ ›› አልኩ በምሬት እየተንገሸገሽኩ …ሚስቴ ፌቨን ከኋላ ስታለቅስ (ስትነፋረቅ ነው እንጅ ) ይሰማኛል ! ‹‹ጩኸቴን ቀማችኝ ›› ማልቀስስ የሚያምርብኝስ እኔ ! ነጋቸውን የፍቅር እና መከባበር ባህር ከፊታቸው ተዘርግቶ መለቃለቅን ይንቁና እንዲህ ነገር ከእጃቸው ሲያፈተልክ በራሳቸው እንባ የጨው ባህር ሰርተው ነፍሳቸውን ይዘፈዝፋሉ ! እንባቸውን ገድበው ቁጭት ያመንጩበት እዛው ….እንዴት እንደጠላኋት !
ዳኛዋ በትኩረት ተመለከተችኝ እኔም በትኩረት ተመለከትኳት …. ፀጉሯ ባጭሩ ተቆርጦ ደማቅ ወርቃማ ቀለም ተቀብቷል …..ወርቃማ ቀለም ውስጥ ነክረው ያወጡት ቡርሽ ነው የሚመስለው ችፍርግ ! ፊቷ ላይ ልክ የሌለው ጥላቻ ይንቀለቀላል(ጠላች አልጠላች በህግ እንጅ በፍቅር አትፈርድ ድሮስ ህግ አይጥላኝ) …ጠረንጴዛው ላይ በተቀመጠው መዶሻ አናቴን ብትፈጠርቀው ደስታዋ ….. ኧረ ጎበዝ እኔ ስለሚስቴ ፀጉር ማጠር ሳወራ ዳኛዋ ለራሷም ፀጉር ነው የምትሟገተኝ ….. ግን ህግ ነውና እንደምንም ብስጭቷን ዋጥ አድርጋ ጉዳዩን በሌላ ጊዜ ለማየት ቀጠሮ ሰጠችን ! ሶስተኛ ቀጠሮ መሆኑ ነው ….ቆይ ይች ሴትዮ በቀጠሮ ብዛት የሚስቴ ፀጉር የሚያድግና ሃሳቤን የምቀይር መስሏት ይሆን እንዴ ? መክሸፍ አይገባትም ….በቃ ሚስቴ ለእኔ ከሽፋለች !!
ከችሎት ስንወጣ ሚስቴ ከእናቷ (እኔም ማሚ ነበር የምላቸው ) እና ታናሽ ወንድሟ ጋር በር ላይ ቁመው ነበር …እናቷን ሂጀ ሰላም አልኳቸው (ለእኔ እናት ማለት ናቸው ) ወንድሟ በጉርምስና ደም ፍላት ፊጥ ፊጥ ይላል (ከጥንቱም ነገረ ስራው አያምረኝም ዘመናዊ ወልጋዳ ) …እኔን ሰላም ላለማለት ሸፈፍ ሸፈፍ እያለ ራቅ ብሎ ሄደ !(ለምን እህቱን አስከትሎ ሩቅ ምስራቅ አይገባም መንደር ለመንደር ከመዋል ይሻለዋል ) ሚስቴ ፌቨን አይኗ እንባ ተሞልቶ ፍዝዝ ብላ ታየኛለች …እኔ ደግሞ በተቻለኝ አቅም ሁሉ እርሷን ላለማየት እሞክራለሁ …..ፀጉሯን ከተቆረጠች ጀምሮ ሚስቴ ሳትሆን የሆነ የተወለድኩበት ያደኩበት ብዙ ጣፋጭ ትዝታ ያሳለፍኩበትን ሰፈሬን በግሬደር ካፈራረሱት በኋላ የማየው የፍርስራሽ ቁልል መስላ ነው የምትሰማኝ !
ፌቨን በስልጣኔ ግሬደር በፋሽን ትራክተር ዳግም ላትሰራ ፈራርሳለች !! መፍረስ ቃሉ ያማል ! ‹‹ እቃቃው ፈረሰ ዳቦው ተቆረሰ ›› ሲባል የልጅ ነገር አይደለም ለካ …ድፍን ዳቦ ላይ ያለው ግርማ ሞገስ ምራቅ የሚያስውጥ ጉምዠቱ …ሲቆረስ ከሚኖው ጋር እኩል አይደለም …‹‹ያም ዳቦ ይሄም ዳቦ›› ማለት የዋህነት ነው ….ያ ዳቦ ይሄንኛው ሙሉነቱን የሚሸነሽን ስለት ያለፈበት የዳቦ ቁራሽ የዳቦ ፍርፋሪ ! ፌቨን የፈራረሰ ሰፈር የተቆራረሰ ዳቦ ሆናለች ለእኔ ! የጎኔ ሽራፊ ሳትሆን ከሙሉነት ጎን የተሸረፈች የዳቦ ሽራፊ ….እጠላታለሁ ? አዎ ! ቆንጆና በአበባ የተዋበ ግቢውን በግዴለሽነት ያፈራረሰበትን ሰው ማን ይወዳል ! ፌቨንን በማፈቅራት ልክ ጠላኋት ! በቃ !
‹‹ማናባቱ ያዘኛል ምን የጎበረበት
በገዛ ትዳሬ ውሃ ብደፋበት ›› ብላለች ያች ዘፋኝ... እንዲህ እንደኔ አንጀቷ አሮ እኮ ነው ! እሷስ ክራር አላት እኔ በምን አባቴ ልተንፍስ ?!
*** **** ****
አራት አመት በፍቅር ቆይተናል ፌቨን ጋር ! እድለኞች ነበርን ….ለድፍን አራት አመት ያልቀዘቀዘ ፍቅር ነበረን ! አስር ደይቃ አብረን ለመቆየት የአንድ ሰአት መንገድ አቆራርጠን እንገናኛለን ‹‹ልይህ ብየ ነው የመጣሁት በጣም እቸኩላለሁ ›› ብላኝ ላባችን ሳይደርቅ ወደየመጣንበት ! ላገባት እፈልግ ነበር እርሷ ደግሞ አገባኋት አላገበኋት አያሳስባትም ቀልቧ የትም እንደማልሄድ ነግሯታል ! ቀልቧ ታዲያ ልክ ነበር …
ደግሞ ሌላው የእድለኝነታችን ገፅ ሁለታችንም የሚታይ ለውጥ በሂወታችን እየተከሰተ በሁሉም ነገር ስናድግ ነበር…ፌቨን አካውንቲንግ ተምራ ስራ በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ ስራ አገኘች ….እኔም ልክ ተመርቄ እንደወጣሁ ስራ ያዝኩ..ትዳር ሲታሰብ ... አንዳች ሃይል ነገሮችን ያገጣጥማቸዋል …. (እግዜር እንዳልል ፈርቸ ነው ) እናም እንዲህ አልኳት …..
‹‹ፌቪ››
‹‹ወይየ ›› ሁልጊዜ ስጠራት ከአይኗ ብርሃን ይረጫል …ስሟ ላይ የጨመርኩበት አንዳች ነገር ያለ ይመስል !
‹‹ላገባሽ ነው ››
‹‹እኔ…………. አ ላ ም ን ም … አብረን ልናድር ነው ?›› ብላ ተጠመጠመችብኝ !አቤት ደስታዋ !
በእርግጥ ለሌላ ሰው ይህ አባባሏ ሳያስቀው አይቀርም …ለእኔ ግን የሆነ አስደሳች እና በስሜት የሚንጥ ነገር ነበረው … አብረን ውለን ‹‹በቃ ልሂድ›› ስትል እንዴት ይቀፈኝ እንደነበረ የማውቀው እኔ ነኛ ! አብሮ ማደር የቀለለባቸው ይሄ ተራ ነገር ይመስላቸዋ …. ፌቨን ከእቅፌ ውስጥ ድብርር እያላት ስትወጣ የአለም ቅዝቃዜ ሁሉ ወደኔ ይጋልብና ይወረኛል …. ሸኝቻት .ለአራት አመት በፍቅር ስንቆይ እንኳን ማደር ምሽቱ ምን እንደሚመስል አብረን አይተነው አናውቅም ! የፌቨን እናት ናቸው ምክንያታችን የሚገርሙ ሴትዮ ….ልጆቻቸውን አታምሹ ምናምን አይሉም…ግን የእናትነት የፍቅር መብታቸውን በትክክል ተጠቅመውበታል ….
ልክ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ፌቨን ቡና ታፈላላቸዋለች (የቤቱ ደንብ ነው ) ሁለት ሰአት ራት ይበላሉ …ልጆቹ ካልተሟሉ ራት አይበሉም! እንደውም ሰአቱ ካለፈ ልጆቻቸው ቢሟሉም ራት ሳይበሉ ነው የሚያድሩት ! ፌቨን ታዲያ ይሄው ነገር ተከትሏት መጥቶ እኔ እቤት ካልገባሁ እህል በአፏ አይዞርም …. እንግዲህ ፌቨን ርሃብ እንደማትችል አውቃለሁ ከራባት እንስፍስፍ ነው የምትለው አይኗን እንኳን መግለጥ ያቅታታል ! (አቤት ስታሳዝነኝ እንደነበር ) ታዲያ እንዴት አባቴ ብየ ለእራት እዘገያለሁ …በጊዜ እቤቴ ! የፌቨን እናት በእነዚህ የማይዛነፉ ህጎች ልጆቹን የማይዛነፍ የቤት መግቢያ ሰዓት ድንበር አስምረውላቸዋል ! ካለአባት ስላሳደጓቸው እናታቸውን እንደአባትም እንደእናትም ነው የሚያይዋቸው !
ተጋባን !! ትዳራችን በሚያሰክር ፍቅር የተሞላ ነበር ! እድለኛ ነኝ ያልኩት ለዚህ ነው …ልክ እንደፍቅረኛ ነበር የምንኖረው ከቤታችን መውጣት አንፈልግም ! ሰውም ወደቤታችን ባይመጣ ደስታችን …እውነቴን እኮ ነው ! ክፉ ሁነን ሳይሆን ፍቅር የሚባለው ስካር አልሰከነልንም ነበር … ሰዓት አይበቃንም ….ቅድም ነግቶ ቁርስ በልተን …ምን እንዳወራን ምን እንደሰራን እንኳን ሳናውቀው አንዳንዴ እንዲያውም ምሳ ሰዓት ሁሉ በየት እንዳለፈ ሳይገባን ብቅ ስንል ማታ ሁኗል ! በቃ!! እንዲህ ነበርን እኔና ቬቨን !
‹‹ ሁሉም ሲጀምረው እንዲሁ ነው ›› ይባል ይሆናል ግን ለድፍን አራት አመት ስንኖር ደስታችን ሳይሸረፍ ሳቃችን ሳይከስም ፍፁም ደስተኞች ሁነን ነበር ! ደግሞ አማረብን እንጅ ! ፌቨን ድሮም ቆንጆ ናት ጭራሽ አበባ መስላ አረፈች …እኔ እንኳን አንድ ሁለት ተብሎ አጥንቴ የሚቆጠር ፍጥረት ትንሽ የተገለበጠች ጎድጓዳ ሰሃን የምታህል ቦርጭ ሁሉ ተከሰተችብኝ !

እንደ አዳምና ሂዋን የቀደመ ሂወትም ትዝታም ሳይኖረን እዚሁ ቤት በዚሁ እድሜ የተወለድን ይመስል ያለፈውን አለም ቤተሰብ ጓደኛ ምናምን ሁሉ ሁለታችንም እረሳነው … የፌቨን እናት ይደውሉና ‹‹ኧረ እናተ ልጆች ድምጣችሁ ጠፋ …በደህናችሁ ነው ?›› ይሉናል …እኔና ፌቪ ታዲያ ልክ ስልኩ ሲዘጋ ‹‹በደህናችን ነው ግን ?›› ተባብለን እንሳሳቃለን …ከዛ ፕሮግራም እናወጣለን …በቀጣዩ ቅዳሜ የፌቪ እናት ጋር …በዛንኛው ደግሞ እኔ ቤተሰቦች ጋር ‹‹እንዴ ከሰው ተለየንኮ ›› እንባባልና በቀጣዩ ቅዳሜና እሁድ ወፍ የለም !! እንደውም ቅዳሜና እሁድ ማለፉን የምናስታውሰው ሰኞ ነው ! እኛ ሌላ አለም ውስጥ ነን !

ቢጨንቃቸው የቬቨን እናት ራሳቸው መጥተው አዩን ! እና መከሩን ‹‹ ታፍናችሁ አትዋሉ ወጣ እያላችሁ ይንፈስባችሁ ›› ሃሃሃሃሃሃሃሃ ! ምን ያደርጋል ምክራቸው ራሱ ነፈሰበት ! ምናባቴ ላደርግ እኔ ራሱ ከቤት ስወጣ ገና ትላንት ከገጠር እንደመጣ ሰው እደናበራለሁ ! ቤቴ ይናፍቀኛል ! ፌቪ ትናፍቀኛለች ሩቅቅቅቅ አገር የሄድኩ የማልመለስ ይመስለኛል ! ት ና ፍ ቀ ኛ ለ ች …..እንዲህ አይነት ትዳር ከመቶው አንድ ነው አሉ ….ለምን ግባሽ አይሆንም የበረከቱ ተካፋዮች እኔና ፌቨን ነበርን !
ሳወራው ያመኛል …. በተፋቀራችሁ ቁጥር እንደስስ መስተዋት ራሳችሁን ከትንሽም ከትልቅም ግጭት ጠብቁ አንዱ ቸልተኛ ሁኖ ሳት ካለ ፍቅር ሲንኮታኮት ያሰቅቃል ….ደግሞ ብቻውን አይንኮታኮትም ጣፋጭ ትዝታችሁንም ይዞ ነው አፈር ድቤ የሚበላው …..ፌቨንን እወዳት ነበር አከብራት ነበር አፈቅራት ነበር …… ትንሽ ነገር ይሄ ነው የማይባል ምክንያት በውስጤ እሳተ ገሞራ የሚያህል ቅያሜ አፈነዳ … አሁን ይሄ ምኑ ይካበዳል እንኳን ለፍች ለተራ ኩርፊያም አያበቃም ….ይባል ይሆናል .... ግን ፌቨንን አይኗን ማየት ድምፅዋን መስማት ጠላሁ ….ፍች ፈለኩ …..ምክንያቱም ፌቨን ፀጉሯን በአጭሩ በመቆረጧ ነበር …..!! በቃ ይሄው ብቻ ነው ምክንያቴ …..
የፌቨን ፀጉር ምን ቢሆን ነው እንዲህ ጉድ ያፈላው ጎጇችንን በጭንቅላቱ ያቆመው ?ይቀጥላል ……

Source: https://www.facebook.com/alex.abreham.31

Image

User avatar
zeru
Leader
Leader
Posts: 952
Joined: 19 Aug 2009 17:01
Contact:

Re: ሚስቴን አከሸፏት (እየተራበች ነው ) ከአሌክስ አብርሃም

Unread post by zeru » 19 Sep 2014 17:00

ሚስቴን አከሸፏት (እየተራበች ነው ) ክፍል 2
(አሌክስ አብርሃም)


‹‹ፌቨን ›› አልኳት ሚስቴ ፀጉሯን ተቆርጣ የመጣች ቀን
አቤት አላለችኝም !! …. እንደወትሯ ወይየም አላለችም ….ምክንያቱም ፊቴ ላይ የነበረው ጥላቻ ቅስሟን ሰብሮታል …እንዲህ ሙሉ ስሟን ደግሞ ጠርቻት አላውቅም ! ሙሉ ስሟን ከምጠራት ሙልጭ አድርጌ ብሰድባት ይሻላታል …በምርጥ ፍቅረኞች መሃል እኮ በሙሉ ስም ከመጥራት የበለጠ ስድብ የለም !! በአገራችን አቶ ወይዘሮ ምናምን ከሚባሉት ተቀፅላወች ይልቅ ስማችን ሲቀናጣ እንደምነደሰት ይሰማኛል ! አቶ ጉልማው ከመባል ጉሌ ….ጉልየ አጓጉል ብንባልም ደስ ነው የሚለን መቸስ …ፍቅረ - ቅንጦት !
ፌቨን ነገሮች ወደየት እየሄዱ እንደሆ ገብቷታል …ገና በሰላሙ ጊዜ ‹‹ አብርሽ አንተ ከምትጠላቸው ሰወች አንዷ ከምሆን ሞቴን እመርጣለሁ ›› ትል ነበር… ታውቃለች ስወድም ስጠላም ልክ እንደሌለኝ …. ታውቃለች ሳፈቅር ሁሉንም ነገሬን ሰጥቻት የምትረገጠውን የእግሯነ ጫማ ከአናቷ በላይ የምትዘረጋውን ዣንጥላ እንደምሆንላት …. ስወዳት በምድር ላይ የእይታየ አልፋና ኦሜጋ እሷ ብቻ እንደምትሆን ታውቅ ነበር ….በቃ ፀባየ ነው !
ታውቃለች ላፈቀርኩት የዛሬ ልቤን ብቻ የትላንት ታሪኬን የነገ እኔነቴን ጭምር አስረክቤ ባዶየን እንደምቆም እኔን እራሴን ጥቅልል አድርጌ እንደምሰጥ …. አንዳንዱ ሰው ‹‹በአምላኬማ አትምጡብኝ ›› ይላል እኔ ግን ፌቨንን ሳፈቅራት ከእግዚአብሔርና ከሷ ቢሉኝ እርሷን ነበር የምመርጠው እንደውም እግዜርን ራሱን በፌቪየማ አትምጣብኝ ባልለው ነው ! ….እግዜር በዚህ ተቆጥቶ ቢያሻው ምድሩን በመብረቅ ይረሰው ከፈለገ ዲን እሳት ያውርድ እንጅ ካፈቀርኩ እውነቱ ይሄው ነው ! ቤቴን ከሩቅ ስመለከተው የሚንቀዠቀዥ መንፈሴ ደብር እንዳየ አማኝ ይረጋጋል እዛ ደብር ውስጥ የነፍሴ ፅላት ነበረች ፌቨን !
ፌቨን ስርዓት ያላት ትሁት ልጅ ነበረች… ደግሞ ስርአቷ ሰው አለ የለም ብለው ግራና ቀኝ አይተው በአሻነጉሊት ሞራል በአስመሳይ ጨዋነት እንደሚስለመለሙ ሴቶች አልነበረም (ኤዲያ ነበር ለማለት በቃን ) አንዳንዴ እንዲህ ትለኛለች ‹‹ ታውቃለህ …አንተ ጋር ስሆን ተጨማለቂ ተጨማለቂ ይለኛል ሂሂሂሂ›› እንዲህ ነኝ ሳፈቅር …እራሴን ላፈቀርኩት የደስታ ማቅረቢ ሰሃን አድርጌ የምሰጥ ….እና ሳፈቅር ጆሮየ አለምን አይሰማም ድምፅ ሁሉ እሷን ነበር የሚመስለኝ ….ብቻዋን ያለች ያህል እስኪሰማት ልክ የሌለው ነፃነት ነበራት ፌቨን …
እናም ጓደኛዋ (ያች ናዚላ ጓደኛዋ ) እንዲህ ትላታለች ‹‹እናትየ አንችን ጉዝጓዙ ላይ ጥሎሻል በደስታ ለሽሽ ብለሽ የፍቅር እንቅልፍሽን ለጥጭ ሂሂሂሂሂሂሂሂሂ ›› ስታወራ አይኗ ውስጥ መርዘኛ ቅናት አለ !ሳቋ ቡና ቤት በር ላይ ደንበኛ ለመጥራት እንደሚጮኹ የቡና ቤት ሴቶች አይነት ሳቅ ነው ….
ስለጓደኛዋ …….
የፌቨንን ጓደኛ አልወዳትም …..በቃ ሲታይ የሚኮሰኩስ ሰው የለም ? እንደዛ ናት አባጨጓሬ መንፈስ የከበባት ነገር ! ድምፆ እራሱ ይኮሰኩሳል ንግግሯ ከቃል ሳይሆን ከአባጨጓሬ የተሰራ ነው የሚመስለው ! በተለይ ሳቋ እንደዚች ልጅ ሳቅ የሚቀፍ እንደዚች ልጅ ወሬ የሚያቅለሸልሽ ነገር በምድር ላይ ያለ አይመስለኝም ! የሆነ ከአይኗ የሚወጣው የውድቀት ጨረር ሰላም ይነሳል ….እሷን ለማየት ትልቅ የትእግስት መነፅር ያሻል !
‹‹ማሜ ›› ነው ስሟ … እንደው ሳስበው የሆነ ክብ ስም ይመስለኛል ተመልሶ እዛው አይነት ! ለማያድግና ስንዝር እልፍ ለማይል ስብእና የተሰጠ ሽክርክሪት ….ሽክርክሪት የሚያስደስታቸው ህፃናት ብቻ ናቸው ያደገ ሰው እልፍ ማለት ያስፈልገዋል …. ዙሮ ሲመለከት ከትላንትናው ትንሽ እልፍ ማለት አለበት ትላትም …ትላንት ላይ…. ዛሬም ትላንት ላይ ….ነገም ትላንት ላይ የሚቆም ሰው ሌላው ቢቀር ትንሹ ነገር ትዝታ እንኳን በውስጡ የሻገተበት ይመስለኛል ….
ትላንት የሆነ ወንድ ጋር ሶደሬ ዛሬ የሆነ ወንድ ጋር ላንጋኖ ነገ የሆነ ሰውየ ጋ ምንትስ ሆቴል ራት…. ዛሬ እንትና ሰርግ ላይ ሚዜ …ከነገ ወዲያ እከሊት ቀለበት ላይ አጃቢ …… ጧት ሳውና ስቲም ገለመሌ …..ከሰአት ፀጉር ቤት …. ከውስጥ የቆሸሸ ስጋ እንደዶሮ በሙቅ ውሃ ተዘፍዝፈው ስለዋሉ ይጠራ ይመስል ….. ሂወቷ እንደዛ ነው …..በዛ ሂዳ በዚህ ወጥታ ተመልሳ እዛው ! እንዲሁ እንደዞረባት ሳታስበው የእድሜ ሰአቷ ዙሮ ዙሮ ሰላሳ ስምንት ሆነ ! አድሜ በየትኛውም ደረጃ መጥፎ አይደለም እንደእድሜ ካለመሆን በላይ በሽታ ግን ምን አለ ….ሰው በእድሜው ገንዘብ ፍቅር ዘመድ ጓደኛ በተለያየ ምክንያት ላያፈራ ይችላል …ግን ለእድሜው የሚገባ ጥሩ ባህሪ መኖር ማንን ገደለ ?
አሁንም ቦርሳዋን አንጠልጥላ መንደር ለመንደር ከመዞር ሌላ ስራ የላትም ! አንዳንዴ ሳስባት የሰላሳ አምስት አመት ሰይጣን ትመስለኛለች ….ዝናብ ጠራራ ሳይል ኮሲ ለኮሲ ሲዞር የሚውል ሰይጣን ! በዚህ እድሜም የሚገርም አቋም ነው ያላት … ወንዶቹን እንደለማዳ ውሻ ነው የምታስከትላቸው …. ሂወቷም ይሄው ነው ወንድ ማስከተል ወንድ መከተል ….በቃ ! ሰውነቷ ከብዙ ወንዶች ኪስ በተዋጣ ቁርጥራጭ ስጋ የተገነባ ነው የሚመስለኝ ….የየድርሻቸውን ቢያነሱ ማሜ የምትባል ሴትዮ በምድር የማትኖር ዓይነት !
እንግዲህ የዚች ዋጋ ቢስ ፍጥረት የልብ ጓደኛ ናት ሚስቴ ፌቨን ! እዚች ሴትዮ ጋር ተይ ይቅርብሽ አላልኳትም … ቤታችን ስትመጣ ፊት አልነሳኋትም ….ቤቱ ‹‹ሽቶ›› በምትለው ቅርናታም ነገር ሲታፈን ስማቸው ተጠርቶ በማያልቅ መንጋ ወንዶች ተረት ጆሮየ ሲደነቁር ፊት አልነሳኋትም ….ለምን …የምወዳት ሚስቴ ጓደኛ ስለሆነች ! በዛ ላይ ፌቨንን እንደምትቀናባት አውቃለሁ አስተያየቷ ይነግረኛል ….
የፌቨንን ፀጉር በእጇ እየነካካች ‹‹እኔኮ የሚገርመኝ ከእርዝመቱ ብዛቱ ›› ትላታለች ….የፌቨንን ሰውነት ስትነካ ይቀፈኛል አብራቸው በየስርቻው የወደቀቻቸው ወንዶች መንፈስ ሁሉ ሚስቴ ላይ የሰፈረ ነው የሚመስለኝ ! የሚስቴን ለስላሳና ጠይም ጉንጭ እየነካች ‹‹ እስቲ አንድ ቀን ስቲም እንግባ እኔ እጋብዝሻለሁ ፌቭየ አፈር ስሆን …›› ስትላት ትንፋሽ ያጥረኛል ! ‹‹አፈር መሆን ከፈለገች ለምን ብቻዋን አትሆንም ›› የኔ ሚስት ስቲም ስላልገባች …..
ከዚህ ሁሉ የሚከፋው ግን ወሬዋ….ወይኔ ወሬዋ ! ሰው እንዴት በቅሌቱ ‹አንቱ › ለመባል ይጥራል በእግዚአብሔር እኔ ጥሎብኝ ‹‹ዋው እሷ እኮ ተጫዋች ፍሪክ ምናምን › ለመባል ብሎ የሚቀባጥር ሰው ያስመርረኛል … ‹‹ ዋው እንትናየ እንዴት አባቱ የሚጥም ተጨዋች መሰለሽ ….ሙድያለው ጨዋታው ብትይ የሚወስድብኝ ቦታ ብትይ በዛ ላይ አልጋ ላይ ሂሂሂሂሂሂሂሂሂ ›› አፏን እስከመጨረሻው ከፍታ ታሽካካለች …. ይችን ሴትዮ ሳስባት ከእናትና ከአባት ሳይሆን እንደሙጃ ሂወት ይሉት ዝናብ ዘንቦባት ድንገት ሜዳ ላይ ቱግ ብላ ያበቀለች አረም ነው የምትመስለኝ ! የሰው አራሙቻ !
ፌቨን ጋር የተዋወቁት በአንድ የግል ድርጅት ሲሰሩ ነበር …‹‹ኦ ማሜ ማለትኮ እናት ማለት ነች ›› ትላታለች ሚስቴ ይችን ሴት ስታደንቃት …. ! ይታያችሁ እናት ! ለነገሩ ‹‹እናት›› ናት
‹‹ፌቪየ የኔ ማር … ይሄን ሽንኩርት የሚባል ነገር እየከተፍሽ ቆንጅየ እጅሽን ልታበላሽው ነው …. ›› ትላታለች ፌቨን ልታስተናግዳት ጉድ ጉድ ስትል እኮ ነው … ምክሯ ሁሉ ግራ ነው የሚያጋባው …አንዳንዴ ደግሞ እኔና ፌቨንን እየተመለከተች
‹‹እንዴ እናተ ሁለታችሁ ብቻ ናችሁ.... የምን እንጀራ መጠፍጠፍ ነው … የቀን ሰራተኛ ቅጠሪና ወጥ ምናምን ሰርታ ፍሪጅ ውስጥ ማስቀመጥ እንጀራ ከሱቅ ገዛ አድርገሽ ‹መጠቀም › .... ቡናም ቢሆን የምን ጓዝ ማነኳተት ነው … የተፈጨ ቡና አንድ ኪሎ ብትገዥ ለብዙ ጊዜ ይሆንሻል እንደው አበሻ ጓዳ ገብቶ ፍዳውን ካልበላ ካላቦካ ካልተጨማለቀ እሳት ላይ ካልተጠበሰ የበላ የጠጣ ...አይመስለውም … አይደል እንዴ አብርሽ ? ሂሂሂሂሂሂ ይችን የመሰለች ማር የሆነች ልጅማ ሽንኩርት አታስከትፋት … >>
ፌቨን ምሳ ሰርታ ይች ‹መካሪ › በደንብ እያጣጣመች ከበላች በኋላ መልሳ እንዲህ ትላለች
‹‹ላለለት ሰውማ ማን እንደቤት ምግብ እናቴ ትሙት (እናቴ ትሙት ብሎ መሃላ አይቀፍም ?) ….ውይ እንዴት እርቦኝ ነበር ጥሞኝ በላሁ …ፌቪየ ከአልጫዋ ትንሽ ጨምሪልኝ ›› ትላለች ! እውነቱን ለመናገር እንደዚህ ስትል ታሳዝነኛለች…ሴት ራበኝ ስትል አልወድም በዛ ላይ አንዲት ሴት ያውም ኢትዮጲያዊት ሴት የፈለገ የሞራል ውድቀት ውስጥ ብትገባ የዚህ አይነት አኗኗር የምትመርጥ አይመስለኝም ! አንድ ከሂወቷ መፅሃፍ የተገነጠለ የኑሮ ገፅ ይኖራል ….. ወይም አንዱ ደደብ የህያውነት አንቀፀዋን በክፋት ሰርዞታል ! ወዶ አይደለም ወሬዋ የሚምታታው …..
በጣም ቆንጆ ናት (ያውም ውብ የሚባል አይነት) ላግባ ብትል እግሯ ላይ ወድቆ የሚያገባት ሽ ከሚሊየን ነው (በዚህ እድሜዋ እንኳን ላግባ ብትል የሚሻማባት ጎረምሳ ብዙ ይመስለኛል ) ግን ከርታታ ናት በቃ እዛ ስታድር እዚህ ስትውል ሽሽቷን ልታዘምነው አንዴ ትልልቅ ሆቴሎች ሌላ ጊዜ ሌላ የመዝናኛ ቦታወች ብትንከራተትም … አይኗ ላይ እንደሩቅ አቀር እሳት ቢል ቢል ሲል የሚታየው አምሮት ….. እፎይ ማለቻ ጎጆ መናፈቋ ነው !
እናም ፌቨንን እፊቴ ንዲህ አለቻት …..‹‹ፌቪ ማር …ይሄ እንቁላል ቅርፅ ያለው ፊትሽ በዚህ ፀጉርሽ ባይሸፈን ኑሮ መልክሽ የሚያሳብድ ይሆን ነበር ..ብዙ ሳይሆን ትንሽ አጠር ….ምን አሁን እኮ ፀጉር ጀርባላይ ጎዝጉዞ አንበሳ መምሰል ትንሽ ጊዜው አልፎበታል ….ዳሩ አንች ወጣ ብለሽ አታይ …እዚህ ባልሽ ጋር ታፍነሽ እየዋልሽ ሂሂሂሂሂሂ ››
ማታ እንደተኛን ፌቨን ድንገት ከጎኔ ቀጥ ብላ ደረቴ ላይ አገጯን አስደገፈች ጥቁር ፀጉሯ ፊቴ ላይ ተነሰነሰ ….አይኖቸን ጨፍኘ የፀጉሯን ዝናብ ተጠመኩት በደስታ ….እንደሩፋኤል ፀበል …….የፀጉር ዘለላወቿ ፊቴ ላይ እየተንሻለሉ አንገቴ ስር እየተጥመሰመሱ እንደህፃን ልጅ የሚያጫዉቱኝ ይመስሉኛል ጥቁር የተቀደሰ መንፈስ …..
‹‹ አብርሽየ ….››
‹‹እ ››
‹‹አይንህን ግለጣ ›› አለች... ገለጥኩ በጥቁር ደመና መሃል ብቅ ያለች ጠይም ፀሃይ ከበላየ ….
‹‹ ማሜ ያለችው ነገር ግን አልገረመህም ? እንዴት እስከዛሬ አላሰብኩትም ……?››
‹‹ ምኑን? ›› አሁን እኔም ነቃ አልኩ
‹‹ ፀጉሬን ባሳጥረው እንደሚያምርብኝ ፀጉር የምትሰራኝ ልጅም ደጋግማ ነግራኛለች ››
ፊቷ ላይ ያለው ስሜት የማማከር ሳይሆን ፀጉሯን የምትቆርጥበት መቀስ እንዳቀብላት የመጠየቅ አይነት ነበር ....ያበቃለት መርዶ !
((( …….ሁሉም ነገር ቅድሚያ የሚቆረጠውም የሚቀጠለውም …..ልብ ላይ ነው !! )))


ይቀጥላል !

ምንጭ:https://www.facebook.com/alex.abreham.31

Post Reply

Return to “Ethio Art and Culture..ኢትዮ ጥበብ ፤ስነ ጽሁፍ ፤”