የኛ ሰፈር መንገድ በትሁት ጌታቸው

ግጥሞች፣ታሪኮች፣ፎቶዎች፣ሙዚቃዎች
Poems,Short stories, graphics,pictures,musics,Technology
User avatar
zeru
Leader
Leader
Posts: 952
Joined: 19 Aug 2009 17:01
Contact:

የኛ ሰፈር መንገድ በትሁት ጌታቸው

Unread post by zeru » 29 Aug 2014 11:56


የኛ ሰፈር መንገድ
……………………………………………………………………

እኔ የምላችሁ ………… ሰፈሬን ታውቁታላችሁ እንዴ?

ሰፈሬ ማለት ከ አንድ በመዲናችን አለ ከተባለ አደባባይ ዙሪያ ካሉ ቅያሶች በአንዱ ይኖራል ብላችሁ የማትገምቱት አይነት ሰፈር ነው።

አስፋልት አይደለም ። ኮብል እስቶንም የለውም። ድንጋይ ንጣፍም አይቶ አያውቅ። ኮሮኮንች?............ኧረ አይደለም !

ግን እውነት የሰፈሬ መሬት ከምንድነው የተሰራው?


ከቤታችን ደጃፍ (ግቢ የለንም……..ኧረ እኛ ሰፈር ግቢ አይታወቅም) ደረጃው ላይ ቁጭ ብዬ መሬቱ ላይ ትክ አልኩ……..ከምን እንደተሰራ ለማወቅ

ከአፈር …….ከድንጋይ……እ?......ሌላስ?

ከዋናው መንገድ ጥግ አንዳንድ ድንጋዮች አያለሁ……ከየት እንደመጡ የማላውቃቸው…..ማን እንዳመጣቸው የማላውቃቸው ደግሞም ስማቸውን የማላውቃቸው……..ብቻ በጅምላ ‘ድንጋዮች’ በቃ!

መሃል ላይ ሰፊው መንገድ አለ……ማንም የማያዝንለት ምስኪን መንገድ….ታክሲዎች ፧ የቤት መኪናዎች ፧ ጭነት የጫኑ ፧ ሞተር ሳይክሎች ፧ ሰፈረተኞች ፧ መጤዎች፧ ውሪዎች ፧ባልቴቶች፧ ሴቶች፧ ጎረምሶች………..ነጋ ጠባ የሚረግጡት እና አንድ ቀን ብሶት ሲፈነቅለው ተገለባብጦ አዳሜን የሚያፈርጣት የሚመስል መንገድ………ዝም ብሎ የሚረገጥ……የሚረግጥበትን ቀን የናፈቀ ሆደ ባሻ መንገድ……አዎ መሃል ላይ እሱ አለ።
መንገዱን ሳየው እግዜር በትርፍ ጊዜው (ድንገት ካለው) ገበጣ ምናምን ለመጫወት አስቦ የቦረቦረው ነው የሚመስለኝ……..

አለ አይደል…….በላዩ ውር ውር የምንለው እኛን ጠጠር አድርጎ

እያፈሰ……እየበተነ….ምናምን………

ከአንዱ ጉድጓድ ወደ አንዱ እያዞረ ምናምን…….ምናምን ……..ብዙ ምናምኖች

ባለፈው ነው። አቶ ወንድይፍራው ማታ አንድ ሁለት ‘የአንበሳ ወተት’ (መቼም ‘የአንበሳ ወተት’ አናውቅም እንዳትሉኝ? የቦሌ ልጆች ነን ምናምን ብላችሁ ካካበዳችሁ ግን እነግራችኋለሁ ……..አረቄ!!!! ) ተጎንጭተው ሰፈር ለሰፈር እየዞሩ የቤታቸውን መግቢያ በር ሲፈልጉ ወድቀው በወጌሻ ነው አጉል ከመሆን የተረፉት። ምናልባት የግዜር ተረኛ ጠጠር እሳቸው ይሆኑ ይሆናል በዚያ ቀን………ማን ያውቃል ከሱ በቀር!

ምን አላችሁኝ?

“የቤታቸውን በር ለምን ይፈልጋሉ?”

ይቺ ጥሩ ጥያቄ ነች!

ምን ነካችሁ?

እኛ ሰፈር እኮ የግል በር ያለው ሰው በቁጥር ነው። እንኳን የግል በር የግል አልጋ፧ የግል ድስት ፧ የግል ልብስም ቢሆን ያለው ሰው በመብራት ነው ፈልጋችሁ የምታገኙት (መብራት ካልጠፋ ማለቴ ነው)::

ምሳሌ ልስጣችሁ

አንድ አራት ክፍል ያለው ቤት ውስጥ አራት ቤተሰብ ሊኖር ይችላል። ለዚያውም በአንደኛው ክፍል አምስት ልጆች ያሉት አባውራ ከባለቤቱ ጋር ፧ በሁለተኛው ክፍል ማታ ማታ ራሷን ‘ለጥብስ’ አዘጋጅታ ያችው አንድያ በር ላይ ለራቁት አምስት ጉዳይ የሆነ ገላዋን ይዛ የምትቆም ሴት በሶስተኛው ክፍል እርጅናና ህመም በመሀላ አንድ ሆነው አልጋ ላይ ያዋሏቸው ባልቴት እና በአራተኛው ደግሞ በጉልበቱ አዳሪ ጎልማሳ!

ለዚህ ነው…. አቶ ወንድይፍራው የቤታቸውን መግቢያ በር ለመፈለግ የተገደዱት።
እና ልጠይቃቸው ሄድኩ። ቤታቸው።

ባለቤታቸው ወይዘሮ አረገድ በር ላይ ሆነው ማሰሻ እየወቀጡ ከነበሩበት ብድግ እያሉ

“አቡሹ” አሉ

“አቤት” አልኩ መሬት መሬት እያየሁ።አንዳንዴ የሌለብኝ ትህትና እላዬ ላይ ይከመርብኝና ሌላ ሰው ያረገኛል……ልክ እንደአሁኑ!

“ምን አደከመህ ልጄ……አንተ ለራስህ ስራውም ፋታ አይሰጥህ…..ምን እሱ እንደው ተው ቢሉት አይሰማ እድሜው የገፋ ሰው ከቤቱ ከወጣ ስንት ጉድ አለበት…..አሄሄሄሄ……ፍርጃ ነው………………” እና የመሳሰሉ እያነበነቡ ወደ ቤት ሲገቡ ተከተልኳቸው።

አቶ ወንድይፍራው አልጋ ላይ ቁጭ ብለዋል።የ ግራ እግራቸው በሆነ ነጠላ ቅዳጅ (ጥቁር እና ነጭ ጥለት ያለው ነበር ነጠላው ነፍሱን ይማረውና!) ተጠቅልሎ መሬት ላይ አርፏል።አጠገባቸው ባለች ትንሽዬ የእንጨት ጠረጴዛ ላይ ‘እናትና ልጅ’ !

“እንዴት ኖት ጋሽ ወንድይፍራው?” አልኩኝ ሲያዩኝ

“ደ……ህ….ና”

“እየተሻሎት ነው?”

“አ….ዎ” አጭር መልስ። እንዲሁ ናቸው። ካልጠጡ መልሳቸው እንደቁመታቸው አጭር ነው የሚሆነው::

“አይዞት ምን የኛ ሰፈር ከዘነበ እኮ ጭቃው ያድጣል” አልኩኝ።

አምልጦኝ ነው ለነገሩ……. አዎ….አመለጠኝ ብል ይሻላል። እንዲያውም ከዚያ ቀን አንድ ቀን በፊት እናቴ ከቤተክርስቲያን አስቀድሳ ስትመለስ የሳሳች ነጠላዋን እያወለቀች
“ኦሆሆሆይይይይ….ሃሩር ኧረ አምላኬ እግዚኦታችንን ስማንና ትንሽ ማቀዝቀዣውን አውርድልን” ስትል አልሰማኋትም? ታዲያ ምን አስቀባጠረኝ??????

“አሄሄሄ…….”. ብለው ዝም አሉኝ እሳቸው።

ለካንስ ቆይቼ ስሰማ እግራቸው ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ነበር የተሰበረው።

“እግዚአብሄር ይማሮት” ብያቸው ስወጣ ከ “አሜን” በቀር ትንፋሽም አልወጣቸውም።

ዛሬ ደግሞ…..ደረጃው ላይ ሆኜ……ወደ መንገዱ ትክ እንዳልኩ ለሰፈራችን መንገድ የይዘት ቀመር ላወጣለት ወሰንኩ…….ወስኜም አልቀረሁ ቆረጥኩ።

ትዝታዎቼን ሰብስቤ …..ትውስታዎቼን አጠራቅሜ ይህንን አልኩ

ሰፈራችን……

የኛ ሰፈር…….
.
.
.
ምናምን ፐርሰንት ሜዳማ ይዘት አለው

ምናምን ፐርሰንት ወንዝማ (ይባላል ግን?) ይዘት አለው (ከቦይ ውጪ አፈንግጦ የሚፈሰውን አፍንጫ የሚወጋውን ፈሳሽ ነው)

ምናምን ፐሰርንት ገደልማ ይዘት አለው (የአስፋልቱን ቦረቦሮች የሚወክል)

ምናምን ፐሰርንት ተራራማ ይዘት አለው (በደጃችን (በረንዳ ልበለው ይሆን?) የምንቆልለውና ከየቤታችን ጣሪያ በላይ ሆኖ የሚታይ ኮተታችንን የሚገልጽ)

በቃ! ……መቶ ፐርሰንት ሞላ!

መደምደሚያ…….

የኛ ሰፈር ማለት …….በቃ……ኢትዮጲያ ማለት ናት…………… ሁሉም ነገር ያላት ……ግን ደግሞ ሁሉም ነገር የሌላት::
.
.
.
እንደዛ መሰለኝ::

(ትሁት ጌታቸው ) ምንጭ: ፌስቡክPost Reply

Return to “Ethio Art and Culture..ኢትዮ ጥበብ ፤ስነ ጽሁፍ ፤”