ፎቶግራፉ.... በዘውድአለም ታደሰ

ግጥሞች፣ታሪኮች፣ፎቶዎች፣ሙዚቃዎች
Poems,Short stories, graphics,pictures,musics,Technology
User avatar
zeru
Leader
Leader
Posts: 952
Joined: 19 Aug 2009 17:01
Contact:

ፎቶግራፉ.... በዘውድአለም ታደሰ

Unread post by zeru » 26 Aug 2014 22:30

ፎቶግራፉ.. (ዘውድአለም ታደሰ)


ቤታችን ግድግዳ ላይ ከመላኩ ሚካኤል ምስል ቀጥሎ የአባባ ጃንሆይና የእማማ ዘውዲቱ ፎቶግራፍ ተሰቅሏል::ፎቶግራፉን የሰቀለው አባቴ ነው::እናቴ ለምን እንደሆነ በማይገባኝ ሁኔታ ይህን ምስል አትወደውም ነበር.. እንደውም ሁሌም ከቤተስኪያን ስትመጣ ቅዳጅ ጨርቅ ውሀ ውስጥ ነክራ ከሚካኤል ምስል ላይ አዋራ ስታጸዳ የጃንሆይና የእቴጌዋን ፎቶ ንክችም አድርጋው አታውቅም!...
አባቴ ግን ሁሌም ማለዳ ተነስቶ ዳዊቱን ከደገመ በኋላ እንደጾሎቱ ማሳረጊያ የጃንሆይን ፎቶ ትክ ብሎ እየተመለከተ በለሆሳስ ያጉረመርማል...የዘጠኝ አመት ልጅ ሳለሁ ታዲያ አባቴ ይህን ፎቶ እንዲህ አጥብቆ የሚያይበትንና እናቴ ይህን ፎቶ እንዲህ አጥብቃ የምትጠላበትን ምስጢር ለማወቅ ብፈልግም አልተሳካልኝም ነበር...
አንዳንዴ አባቴ እንደሚያደርገው ከተሰቀለው ፎቶግራፍ ፊት ለፊት ባለሶስት እግሯን ዱካ አስቀምጬ እሷ ላይ እቆምና ከፎቶዋ ትክክል ሆኜ ለረጅም ሰአት ፎቶውን አያለሁ...ሁሌም ምስሉ ተመሳሳይ ነው...ንጉሱ ፈገግ እያሉ ይሁን ወይም ተኮሳትረው አይገቡኝም ....እቴጌዋ ደግሞ እማዬን <<ጀላቲ መግዣ ስጪኝ>> ስላት <<ሂድ ወዲያ ያንጀልጅልህ>> ስትለኝ እንደማኮርፈው ያኮረፈች ይመስለኛል( በልቤ ታዲያ ሀለስላሴ እንደኔናት ቋጣሪ ናቸው ማለት ነው ለእማማ ዘውዲቱ ጀላቲ አይገዙላቸውም ብዬ ንጉሱን እገላምጣቸዋለሁ)...
አንድ ቀን <<እማዬ>> አልኳት ምሳቃዬን እየቋጠረችልኝ እያለ...
<<አቤት ጥፍጥፎ>> አለችኝ ቀና ብላ ሳታየኝ(ጥፍጥፍ ስትለኝ እናደዳለሁ ስናደድላት ደስ ይላታል)....ንዴቴን በሆዴ ውጬ...
<<እኚህ ሰውዬ ምናችን ናቸው??>> አልኳት እጄን ወደፎቶው ቀስሬ....
<<ማ?>> ብላ የእጄን ምልክት ተከትላ አይኗን ወደግድግዳው ወርወረችና <<በስማም አረ ሰውዬ አይደለም መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል እንጂ>> አለቺኝ እንደነገሩ እያማተበች...
<<አረ እሱንማ አውቃለሁ እኔ ያልኩሽ ሀለስላሴን ነው እንጂ>>...
<<እህ... ነው እንዴ ያው ሀይለስላሴ ናቸዋ>> አለች ምሳቃዬ እንጀራ አብዝታበት አልዘጋ ስላላት በእጇ ለመዝጋት እየታገለች(እንዲሁ ነች በልቼ ምጠግብ አይመስላትም)...
<<እኮ ሀይለስላሴ ምናችን ናቸው?>> አልኳት ኮስተር ብዬ...
ቀና ብላ ገልመጥ አደረገቺኝና <<ጥጥፎ ሶስተኛ ክፍል ሆነህ ሀይለስላሴን አታውቅም?ንጉሳችን ነበሩዋ>>...
<<እህህ......እሱንማ አውቃለሁ ምናችን ነበሩ ነው ያልኩሽ አልኳት ንድድ ብሎኝ>>....
<<ሂድልኝ እንግዴህ አትጨቅጭቀኝ ንጉሳችን አልኩህ እንግዴህ መቼም ነብስ አባታችን አልልህም አለቺኝ ቆጣ ብላ....
አንድ ቀን ምሽት እንደለመደው አባዬ የጃንሆይ ምስል ፊት ቆሞ ሲያጉረመርም ቀስስ ብዬ ኮቴዬን ሳላሰማ ሚለውን ለመስማት ከኋላው ቆምኩ....
<<ወይኔ አንተ ብትኖርኮ የማንም መጫወቻ አልሆንም ነበር...ህምምም ወይኔ የኔ ዘንካታ የኔ መለሎ የወንድምህ ልጅ እንደማንም ተራ ሰው ሶስት በሶስት በሆነች ኩርማን ቤት ውስጥ እየኖረ ነው እንግዴህ ጉድህን ስማ.. ህምምምም>>...
እናቴ ወደተኛችበት አልጋ ዞር ብሎ እያየ <<ወይኔ ወንዱ ይሄኔ አንተ ብትኖር እኔ ልጅህ የማንም የአፈር ገፊ ልጅ መጫወቻ አልሆንም ነበር>>...ሲል በመጋረጃ ከተከለለው አልጋ ላይ የናቴ የታፈነ ሳቅ አስተጋባ...እኔም ለምን እንደሆነ በማላውቀው ሁኔታ ሳቄ መጥቶ ለትንሽ በሁለት እጄ አፍኜ ያዝኩት(ለምን እንደሆነ አላውቅም እናቴ ስትስቅ እኔም ሳቄ ይመጣል)...
<<ጥርስሽ ይርገፍ>> አለ አባቴ አሁንም ወደናቴ ዞሮ...ቀስስ ብዬ አባቴ ሳያየኝ አልጋዬ ላይ መልሼ ወጣሁ....
ዛሬ የዚህን ፎቶ ትርጉም ግልጽልጽ አለልኝ...አዎ ሀለስላሴ ያባዬ አጎት ናቸው ለካ....ሂሂሂሂ....ሀለስላሴ ዘመዳችን ናቸው....ሂሂሂሂ....በደስታ ልቤ ልትፈርጥ ደረሰች....ትምህርት ቤት እንዴት አሰማምሬ እንደማወራላቸውና እነዱዱሽ, እነቻርሊንና, እነድምቡሎን, እንዴት እንደማስቀናቸው እያሰብኩ የትምህርት ቤት ሰአት አልደርስልህ ብሎኝ...ለሊቱን ሙሉ እንቅልፍ ባይኔ ሳይዞር አደረ...
ለወትሮው ከእንቅልፌ ትምህርት ቤት እንድሄድ የምትቀሰቅሰኝ እናቴ ብትሆንም ዛሬ ግን ቀድሜአት ተነሳሁና ምሳ ቋጥራልኝ ወደትምህርት ቤቴ በግዜ እንድሄድ ወትውቼ አስነሳኋት...
እናቴ የቋጠረችልኝን ምሳቃ አንጠልጥዬ በሩጫ ትምህርት ቤት ስደርስ ጭር ብሏል ገና ስለሆነ ተማሪዎቹም ሆኑ አስተማሪዎቹ አልመጡም...እውነቱን ለመናገር ከቤቴ ትምህርት ቤቴ ድረስ እስክመጣ በጣም ስለምንቀራፈፍ በትምህርት ቤታችን ደንብ መሰረት ሶስት ግዜ ቂጤን በጎማ ሳልገረፍ የገባሁበት ቀን ትዝ አይለኝም ነበር....
<<ዛሬ ደሞ በተራዬ የቀደምኳቸውን አስተማሪዎች እኔ ብዠልጣቸው ጥሩ ነበር!>> አልኩና በራሴ ሀሳብ ሳቄ መጣ...ቂቂቂ...ቲቸር ላጥ አርጌ ቂጡን በራሱ ጎማ ዦጥ ሳደርገው...ቂጡን እያሸ ሲሮጥ... በአይነ ህሊናዬ ሳልኩትና በራሴ ሀሳብ ፍንክንክ እል ጀመር...
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የትምህርት ቤቱ በር ተከፍቶ እንደገባሁ ትምህርት ቤቷ በተማሪዎች መሞላት ጀመረች...የትምህርት ቤቱ ሚኒሚዲያ ክበብ አባላትም የሰልፍ ፕሮግራሙ እስኪጀመር ተማሪዎቹን ለማዝናናት ደፋ ቀና እያሉ ነው...የጠኋቱን ዜና እናሰማለን አለ የ ስድስተኛA ክፍል ተማሪ የሆነው ቶማስ..(በነገራችን ላይ "ቶማስ" በትምህርት ቤታችን ታዋቂ ዜና አንባቢ ነው:: እውነትና ውሸትን እየቀየጠ የሚያቀርባቸው በቀልድ የታጀቡ ዜናዎቹን አይደለም እኛ ተማሪዎች አስተማሪዎቹ ሳይቀሩ ይወዱለት ነበር)...
ዜና...
የሰባተኛ B ክፍል ተማሪ የሆኑት ብሩክና ብሩክታዊት ባሳዩት ያልተገባ ባህሪ የትምህርት ቤታችን ዲያሊክተር ወላጅ እንዲያመጡ መወሰናቸውን በትናንትናው እለት አውቀናል..ዝርዝሩን ያቀረበለን አጃንስ ፕራንስ ፕሬስ ነው...(ሲሳሳሙ እጅ ከፍንጅ ተይዘው ነው)...
...
የአራተኛ D ክፍል ተማሪ የሆነው ተማሪ አሸናፊ ባጫ <<ዩኒፎርሜ ቂጡ ቀዳዳ በመሆኑ ምክኒያት የተማሪዎች ማሾፊያ በመሆኔ ትምህርቴን በአግባቡ መከታተል አቅቶኛል>> ብሎ ለተማሪዎች ህብረት ባመለከተው መሰረት የተማሪዎቹ ህብረት ሀላፊዎች ጉዳዩን በትኩረት ሲከታተሉት እንደቆዩ ይታወቃል...ስለሆነም የተማሪው ጥያቄ ተገቢና አስቸኳይ መፍትሄ የሚያሻው ጉዳይ እንደሆነ ስለታመነ ከተማሪዎች ወርሀዊ መዋጮ ተቀንሶ አዲስ ዩኒፎርም ቢገዛለት የህብረቱ የገንዘብ አቅም ክፉኛ እንደሚጎዳ ስለታመነበት ቀዳዳውን ማስጣፊያ ሀምሳ ሳንቲም ከህብረቱ ካዝና ወጪ ተደርጎ እንዲሰጠው ጥር ሁለት በተካሄደው የተማሪዎች ህብረት መሪዎች ጉባኤ በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁን... የአምስተኛ ክፍል ተማሪዋና የተማሪዎች ህብረት ሊቀመንበሯ "ኩኩሻ ጀማል" ገልጻልናለች!....
...
የትምህርት ቤታችን መዝናና ክበብ ባለቤት ወይዘሮ "ይመኙሻል ጣሴ" አንዳንድ የጨዋ ተማሪ ለምድ የለበሱ ዱርዬ ተማሪዎች ረፍት ሰአት ላይ በፓስቲ ገባያው አካባቢ የሚኖረውን ወከባና ግርግር ተጠቅመው እየሸወዱ ሳይከፍሉ ፓስቲ ይዘው እንደሚሸበለሉና ድርጅታቸው የብዙ አንዳንድ ብሮች ኪሳራ እንደደረሰበት በብዙ ብሶት ተሞልተው ለአባላቶቻችን ገልጸውላቸዋል!
...
ጠጠር ከረሜላን ሎሚ ውስጥ ጨሞሮ መምጠጥ መቼም እጅግ ደስ የሚል ነገር እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን::ግን አንዳንድ ተማሪዎች ሎሚ ውስጥ ጠጠር ከረሜላውን ከትተው በሚመጡበት ሰአት ስሜት ውስጥ ገብተው ከነሎሚው እየዋጡት በመሆኑ ተማሪዎች ሎሚን ከከረሜላ ጋር አዳብለው ሲመጡ ጠንቀቅ እንዲሉ የባይሎጂ አስተማሪያችን ሙያዊ ምክራቸውን ለግሰውናል!....
.
.
ካነበበ አይቀር ምናል እንዲህ ብሎ ቢያነብ አልኩ በሆዴ...እጅግ የምንወዳቸውና የምናከብራቸው "ሞአ አምበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ፍጹመ እግዚአብሄር" በመባል የሚታወቁት ንጉሳችን ቀዳማይ ሀይለስላሴ የትምህርት ቤታችን ተወዳጅ ልጅ የሆነው የአቡሌ አባት አጎት መሆናቸውን አጃንስ ፕራንስ ፕሬስ ገለጸ!...ቢልና ተማሪዎቹ ሁሉ እየሮጡ ወደኔ መጥተው እሽኮኮ አድርገውኝ ቢሮጡ አሊያም ደግሞ ወደላይ እየወረወሩ ሰማይ እያደረሱ ቢቀልቡኝና በዚያውም ማታ ማታ እንደጤፍ ሰማዩ ላይ ሚዘሩትን የወርቅ ኳሶች ዝግን እያደረግኩ እዚህ ለተማሪው ሁላ ባድል ብዬ ተመኘሁ...
ቶማስ ቀጥሏል...<<አሁን ደግሞ አጠር ያለ ግጥም የምንሰማበት ሰአት ነው ግጥሙን የምታቀርብልን የአምስተኛ ክፍል ተማሪ የሆነቺው "እስከዳር ሰለሞን" ነች (በነገራችን ላይ እስከዳር ግጥሙን የጻፈቺው ራሷ መሆኗን ለኮሚቴዎቻችን በመሀላ አረጋግጣላቸዋለች)>> ብሎ ማይኩን አቀበላት....
ትምህርት ቤቴ
እጅግ የምወድሽና የማከብርሽ ትምህርት ቤቴ
ለጤናሽ እንደምን አለሽ አናቴ
ኮትኳቼ አሳዳጊዬ ህይወቴ
አልረሳሽም እስከለተ ሞቴ!
አጼ ዘርአያእቆብ አንደኛና
መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቴ ...
<ልትወርሰው ነው እንዴ ትምህርት ቤቱን?>> ብለው የአማርኛ አስተማሪያችን ቲቸር "ብሩ" አጉተመተሙ....ተንኮለኛው ጓደኛዬ አብዲ <<ደሞዝ እኮ ስለማትከፍል ነው>> አለኝ...ሁለታችንም ተሳሳቅን....
እስከዳር ቀጥላለች...
አንቺ የጠቅላይ ሚኒስትሮች
አንቺ የፕሬዘዳንቶች
መፍለቂያ...ያ...ያ....ካሁን ካሁን ጨረሰች ብለው በጉጉት ሲጠብቋት የነበሩት የሰልፍ ስነስራቱን የሚመሩት የስፖርት አስተማሪያችን ግጥሟን ሳትጨርስ ማይኩን ነጠቋትና <<እስቲ ተማሪዎች አጨብጭቡላት>> ብለው ሁላችንንም ካስጨበጨቡን በኋላ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ወደቀጣዩ ፕሮግራም አሸጋገሩን....
ከንዳ!...አውርድ!...ከንዳ!....አውርድ!....አሳርፍ!...ተጠንቀቅ!....ሁላችንም እኩል የሰልፍ ስነስራቱን አከናውነንና ብሄራዊ መዝሙሩን ዘምረን ወደክፍል ግቡ ስንባል ተንደርድሬ ወደክፍሌ ገባሁ...
እኛ ዴክስ ላይ ድምቡሎ እንደሁልጊዜው ቀድሞን ተቀምጧል..በነገራችን ላይ ድምቡሎ ፈሱ መከራ ስለሆነ የትኛውም ተማሪ አጠገቡ አያስቀምጠውም... እኛም ሁሌ ጠኋት ጠኋት ገና ትምህርት ሀ ብሎ ሲጀመር እንደማይፈሳ አስምለነው ነው አጠገባችን እንዲቀመጥ ምንፈቅድለት....ዛሬ ግን ለመማማሉ ብዙም ግድ አልነበረኝምና ሮጬ ሄጄ ጎኑ ተቀመጥኩና..
<<ድምቡሎዬ ሀለስላሴ እኮ ያባዬ አጎት ናቸው>> አልኩት እየተፍለቀለቅኩ....
ድምቡሎ ምንም ሳያናግረኝ አያቱ ከሰሩለት የዳንቴል ቦርሳ ውስጥ የታሪክ መጽሀፉን መዥረጥ አድርጎ አወጣና ገጹን ገለጥ ገለጥ ካደረገ በኋላ ንጉሱ ከአንበሳቸው ጋር የተነሱትን ፎቶ እየጠቆመኝ
<< እኚህ ሀለስላሴ?>> አለኝ በጣቱ ፊታቸውን ሞልቶ....
<<አዎ>> አልኩት በታላቅ ኩራት....
እናቱንና.....ሰው እንዲያ ስቆብኝ ከዚያም በፊት ከዚያም በኋላ አያውቅም ወንበር ስር ገብቶ እግሮቹን ወደላይ አንስቶ በሳቅ ፈረሰ....ቂቂቂቂቂ....በአንድ እጄ አፍንጫዬን ቆንጥጬ ይዤ <<መሳቁንስ ሳቅ ግን ፈስህን ትፈሳና አልለቅህም>> አልኩት እየተነፋነፍኩ....
<<ፈሳሁ እኮ>> አለኝ ድምቡሎ ድምጹ ቁርጥ ቁርጥ እያለ....
ተዉኝ እስቲ ተማሪው ሁሉ የድምቡሎ ሳቅ ተጋብቶበት ከሀይለስላሴ ጋር የቅርብ ዘመድ እንደሆንኩ ስነግረው ልቡ እስኪወልቅ ሲስቅብኝ ዋለ....
9:30 ሲሆን አንደኛ ወደትምህርት ቤቱ እንዳልገባሁ አንደኛ ከትምህርት ቤቱ በሩጫ ወጣሁ....<<ቆይ ሁሏንም ነገ አባዬን ይዤ መጥቼ እውነቴን እንደሆነ ባላሳያት እኔ አቡሌ አይደለሁም!...ቆይ>>...እያልኩ ከራሴ ጋር ሳወራ ሳላስበው ቤቴ ደረስኩ::.. ወደቤት ተንደርድሬ እንደገባሁ አባዬ ፒሊፕስ ሬዲዮኑን ትከሻው ላይ አስቀምጦ ዶቼቬሌን በተመስጦ ያዳምጣል....
<<አባዬ>> አልኩት ጮክ ብዬ <<ሽሽሽ>> አለኝ በእጁ ምልክት እየሰጠኝ...ለነገሩ ዝም ብዬ ነው እንጂ አባዬ ዶቼቬሌ እየሰማ ከሆነ አይደለም እኔን ነብስ አባቱንኳ ቢመጡ <<ሽሽሽ>> ብሎ ነው ሚያስቀምጣቸው.... ሳልፈልግ ካባዬ አጠገብ ተቀምጬ ዶቼቬሌ እስኪያልቅ ሳዳምጥ ከቆየሁ በኋላ አልቆ አባዬ ቴፑ ውስጥ ያለውን ባትሪ አውጥቶ ራዲዮኗንም ዳንቴል አልብሶ መልሶ ቦታዋ ላይ ሲያስቀምጣት ጠብቄ...
<<አባዬ>> አልኩት
<<አቤት ልጄ>>
<<እኚህ ፎቶው ላይ ያሉት ሰውዬ አጎትህ አይደሉ?>>
<<እንዴታ ልጄ እንዴታ ያባቴ ወንድም አጎቴ ናቸው:: እንዲህ ነው ያባቱን ታሪክ አብጠርጥሮ የሚያውቅ ልጅ ...ለመሆኑ ማን ነገረህ? መቼም እናትህ አትነግርህም!>> አለ እናቴ እንድትሰማ ድምጹን ከፍ አድርጎ...
ደስ ይበለው ብዬ <<ጎረቤት ሲያወሩ ሰምቼ ነው>>...አልኩት...
<<ሀገር ምድሩ እኚህ ኩሩ ሰው አጎቴ መሆናቸውን አውቋል በለኛ>> ብሎ ጀንተል አለ(ሀይለስላሴም እንደሱ አልተጀናተሉ)...
ቀስ ብሎ ከመቀመጫው ተነሳና ወደፎቶግራፉ ሄዶ በጥንቃቄ አወረደው...ከዛ <<አቡሌ ና ልጄ>> አለኝ ፎቶ ግራፉ ላይ እንዳፈጠጠ....ተንደርድሬ ሄጄ እኔም እንዳባቴ ፎቶግራፉ ላይ አፈጠጥኩ...
<<እይ አቡሌ እኚህ ሰው ያባትህ አጎት ናቸው...እያቸው ቁመናቸውን አያምርም??>>
<<ያምራል!>>...
<<እያቸው ጥቁረታቸውን አያምርም??>>
<<ያምራል!>>...
<<እያቸው ቆፍጣናነታቸውን አያምርም??>>
(ቆፍጣና ምንድነው ግን?) <<ያምራል!>>..
<<እይልኝ ዣንጥላ አያያዛቸውን አያምርም??>>...
<<እ>>
<<ዣንጥላ አያያዛቸው አያምርም ወይይ ነው ያልኩህ አቡሌ>>,,,,
<<አባዬ>>
<<አቤት ልጄ>>
<<ዣንጥላ የያዙት ናቸው እንዴ አጎትህ??>>...
<<እንዴታ ልጄ እንዴታ>>...

ምንጭ: ፌስቡክ https://www.facebook.com/zewdalem.tades ... 5165952278

Post Reply

Return to “Ethio Art and Culture..ኢትዮ ጥበብ ፤ስነ ጽሁፍ ፤”