ሞዴሏ ሊያ ከበደ የምትተውንበት ፊልም...

ግጥሞች፣ታሪኮች፣ፎቶዎች፣ሙዚቃዎች
Poems,Short stories, graphics,pictures,musics,Technology
User avatar
morefun
Leader
Leader
Posts: 152
Joined: 06 Sep 2009 01:52
Contact:

ሞዴሏ ሊያ ከበደ የምትተውንበት ፊልም...

Unread post by morefun » 25 Oct 2009 09:58

Image
ሞዴሏ ሊያ ከበደ የምትተውንበት ፊልም በአውሮፓ ለእይታ ይበቃል

ኢትዮጵያዊቷ ሞዴል ሊያ ከበደ የምትተውንበትና "ዘ ደዘርት ፍላወር" (የበረሃዋ አበባ) የተሰኘ ፊልም ለእይታ እንደሚቀርብ ዶቸ ቬሌ በድረ ገጹ ዘገበ፡፡

ሰሞኑን በጀርመን የሚቀርበው ፊልም፣ በዋሪስ ዳሪ ሲዘጋጅ በአፍሪካ ሴቶች ላይ የሚፈጸመው ግርዛት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት መሆኑ የሚያሳይ መሆኑ ታውቋል፡፡ የጀርመንና የአሜሪካ ዜግነት ባላት የፊልም ዳይሬክተር በተቀናበረው ፊልም ኢትዮጵያዊቷ ሞዴል ሊያ ከበደ ተዋናይ ሆናበታለች፡፡

የፊልሙ መነሻ ድርሰት፣ ሶማልያዊቷ ዋሪስ ዳሪ ከጻፈችው ግለታሪኳ የተወሰደ ሲሆን፣ መጽሐፉ በተለያዩ አገሮች ውስጥ በከፍተኛ ቁጥር የተሸጠ እንደሆነም ይነገርለታል፡፡ በ1957 ዓ.ም. ግድም የተወለደችው ደራሲዋ ዋሪስ ዳሪ፣ 13 ዓመት ሲሞላት ቤተሰቦችዋ ሊድሯት ማሰባቸውን በማወቋ ከገጠር ወደ ሞቃዲሾ ከተማ በመሸሽ፣ በተፈጠረላት አጋጣሚም እንግሊዝ በመግባት ለፎቶ ሞዴልነት ለመብቃትና ዝናን ለማትረፍ ችላለች፡፡

Image

ዝናዋ በመናኘቱ ምክንያት ላነጋገራት ቢቢሲ ጋዜጠኛ በሰጠችው ምላሽ፣ የሶማሊያን በረሃ በባዶ እግሯ አቋርጣ፣ ሞቃዲሾ መድረሷ ከዚያም ወደ ለንደን በቤት ሠራተኛነት መምጣቷን በተለይ ደግሞ ለማታውቀው ወንድ፣ ቤተሰቦቿ ሊድሯት በዝግጅት ላይ እንደነበሩና ለዝግጅቱም መገረዝዋን በመግለጽዋ የምዕራቡን ዓለም ትኩረት እንደሳበች ዶቸ ቬሌ ዘግቧል፡፡

አጋጣሚውም ለዋሪስ ዳሪ ከሞዴልነት ተግባርዋ ጎን ለጎን የሴት ልጅ ግርዛትን በመቃወምና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት መሆኑ በመግለጽ የተባበሩት መንግሥታት ልዩ አምባሳደር ለመሆን አስችሏታል፡፡

ውጣ ውረዷ "ዘ ደዘርት ፍላወር" (የበረሃዋ አበባ) የተሰኘውን ግለታሪክ መጻፍ እንዳስቻላትና ለፊልም እንደበቃም ዜናው አመልክቷል፡፡ የደራሲትና የውቢት ሶማሊያዊት ታዋቂ ሞዴል ታሪክን የያዘውና ሰሞኑን በጀርመንና በሌሎች የአውሮፓ አገሮች ለመጀመሪያ ጊዜ የሚታየው ፊልም፣ መሪ ተዋናይዋ ኢትዮጵያዊቷ ታዋቂ ሞዴል ሊያ ከበደ ነች፡፡ በጀርመናዊት ፊልም ዳይሬክተር የተቀናበረው ፊልም የሁለት ሰዓት ርዝመት ሲኖረው በጅቡቲ፣ በኒውዮርክ፣ በኮለኝና በሙኒክ ከተማዎች ቀረፃው ተካሂዷል፡፡

በዶቸ ቬሌ ድረ ገጽ አዘጋገብ፣ ፊልሙ እንደ ሰንደሪላ ታሪክ እልም ካለ ገጠር ወጥታ፣ በረሃን አቋርጣ ለሕይወት ታግላ በዓለም ታዋቂነትን ስላገኘች ሴት ታሪክ ይተርካል፡፡

ፊልሙ በአዳጊ አገራት በተለይም በአፍሪካ በሚታየው የሴት ልጅ ግርዛት ሰበብ በርካታ ሕፃናት በደም መፍሰስና በንጽህና ጉድለት ሳቢያ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ይተርካል፡፡ በፊልሙ ማብቂያ ጥናታዊ ዘገባዎች እንደሚገልጹት በቀን 6000 ልጃገረዶች እንደሚገረዙ ሲያሳይ፣ ይህም አጉል ልማዳዊ ድርጊት በመሆኑ መቅረት እንዳለበት በግልጽ ያስቀምጠዋል፡፡

ሶማሊያዊቷ ደራሲት ዋሪስ ዳሪ፣ "ከበረሃዋ አበባ" በማስከተልም "የአርብቶ አደሩ ልጅ"፣ "ሕመምተኞቹ ሕፃናት' እና "ለእናቴ ደብዳቤ" የተሰኙ መጻሕፍትን ለአንባብያን ማቅረቧ ታውቋል፡፡ ዋሪስ "የሴት ልጅ እንዳትገረዝ በሚለው መርኋ ጸንታ በዓለም ዙሪያ ቅስቀሳ በማካሄድ ላይ ስትሆን፣ በአውሮፓ ኅብረት ለበርካታ ጊዜ በመጋበዝ ንግግር ማድረጓንና ከፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኒኮላ ሳኮዚ፣ ከቀድሞ የሶቭየት ኅብረት መሪ ሚኻኤል ጎርባቾቭና ከቀድሞዋ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮንዶሊዛ ራይስ ሽልማት መቀበሏ ይታወቃል፡፡

Image


Post Reply

Return to “Ethio Art and Culture..ኢትዮ ጥበብ ፤ስነ ጽሁፍ ፤”